የኢትዮጵያ ድንበርና የሉዓላዊነት ጥያቄ

yacob_210708በያዕቆብ ኃይለማርያም (20 July 2008 ) –የሰሜን፣ የምሥራቅ፣ የደቡብና የምዕራብ ድንበሮቻችን በጊዜው የነበሩት የአገራችን መሪዎች ጐረቤት አገሮችን ይገዙ ከነበሩት ቅኝ ገዢዎች ጋር በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው በነፃ ድርድርና ስምምነት የተወሰኑ አልነበሩም፡፡

ወቅቱ አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛትነት የሚቀራመቱበት ስለነበረ ኢትዮጵያ በቅኝ ገዢዎች ክራንቻ ውስጥ እንዳትገባ አጼ ምኒልክ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር፣ ሲሆን በረቀቀ ዲኘሎማሲ አልያም በኃይል ተከላክለዋል፡፡ አጼ ምኒልክን በሰሜንና በምሥራቅ ጣልያኖች፣ በምሥራቅና በደቡብ ምዕራብ እንግሊዞች፣ በምሥራቅ ደግሞ ፈረንሳዮች አስጨንቀው ይዘዋቸው ግንባራቸው ላይ ሽጉጥ ደግነው ያስፈረሙአቸው ያህል የሚቆጠሩ ከአራት የማያንሱ ውሎችን ፈርመዋል፡፡

ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ከጣልያን ጋር ከተፈራረመቻቸው ውሎች በስተቀር ሌሎቹ ሁሉም በሂደት ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ስለሆኑ በተዋዋዮቹ መሃከል ተፈጻሚነት አላቸው፣ ወይንም አሳሪ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ጣልያን ኢትዮጵያን በመውረርዋና ውሎቹን በመጣስ ድንበሮቹን በመቀየርዋ ውሎቹን ስለሰረዘች፣ ኢትዮጵያም በበኩልዋ ከጣልያን ጋር የገባቻቸውን ውሎች ስለሻረች ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል ከቅኝ ገዢዋ ከጣልያን የወረሰችው የድንበር ውል አልነበራትም፡፡ እ.ኤ.አ 2000 ኢትዮጵያና ኤርትራ በአልጄርስ ከተማ የተፈራረሙት ስምምነት ሁለቱም ተዋዋዮች በሻሯቸው ውሎች ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ሕጋዊ ስምምነት ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ያም ሆኖ ግን ስምምነቱ በጊዜው አገሪቱን ተቆጣጥሮ የሚያስተዳድር መንግሥት የተቀበለው ስለሆነ ለኢትዮጵያ በጀም አልበጀም አሳሪነት አለው፡፡

የኢትዮጵያ ድንበሮች በኢትዮጵያውያን ደም የራሱ፣ በኢትዮጵያውያን አጥንት የተገነቡ ሲሆኑ ድንበሮቻችንን ለማስከበር ከሁልቆ መሣፍርት፣ ተራ ዜጐች አንስቶ እስከ አንድ ታላቅ ንጉሠ ነገሥት አጼ ዮሐንስ አንገታቸው ሰጥተዋል፡፡ በዶጋሊ፣ በጉራዓ፣ በጉንዲት፣ በመተማ፣ በአድዋ፣ በወልወል በቅርብ ጊዜያት ደግሞ በሶማሊያና በኤርትራ የፈሰሰው የኢትዮጵያውያን ደም የሌላውን ግዛት በመቋመጥ ሳይሆን ድንበሬን አላስነካም በሚል ነበር፡፡ እንደዛሬው መኪና ወይንም ባቡር ባልኖረበት የቀደምት ኢትዮጵያውያን ከመሃል አገር ተነስተው በእግር ለወራት በረሃውን አቋርጠው፣ ተራራውን ወጥተው፣ ንዳዱን ተቋቁመው፣ ወባውን ደፍረው ከሙስታሂል እስከ ጋምቤላ፣ ከራስ ካሣር እስከ ሞያሌ ዘልቀው ድንበሩን ሰፍረው ኢትዮጵያን ለዚህ ትውልድ አስረክበው ሄዱ፡፡ ይህ ተረካቢ ትውልድ የተረከበውን መሬት ሳይቀነስ ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላልፋል ወይ ለሚለው ጥያቄ መልሱ አሉታዊ መሆኑ ይፋ እየሆነ መጥቶአል፡፡ ኤርትራ ባድመና አካባቢውን ስትረከበብ ሱዳን ደግሞ ከኢትዮጵያ የወሰደችው መሬት ሲቀነስ ኢትዮጵያ እያነሰች መሄድዋ ግልጽ ነው፡፡

የድንበር ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን ቁራሽ መሬት ለሌላ መንግሥት የመስጠት ነገር ብቻም አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ አለመደፈርም ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማንም ባሻው ጊዜ የሚደፍራት ጋለሞታ አይደለችም፤ አልነበረችም አትሆንምም ብሎ ለዓለም ሁሉ በተለይም ለአንዳንድ ጐረቤቶቻችን ማስጠንቀቂያ የመስጠትም ጉዳይ ነው፡፡ የአካባቢአችን አደገኛነት ልንቋቋመው የምንችለው በአትንኩኝ ባይነት እንጂ መሬት ቆርሶ በመስጠትና በልምምጥ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የማንንም አትፈልግም የራስዋን ደግሞ ለሌላ አሳልፋ አትሰጥም የሚለው የቆየ መርህ እስከ ዛሬ አዝልቆን ነበር፡፡ ቀደምት የአገሪቱ መሪዎችም አንዳንዶቹ በጨቋኝነት ሊፈረጁ ቢችሉም አንዲት የኢትዮጵያ መሬት ግን ለሌላ አሳልፈው ሰጡ ብለው ጠላቶቻቸው እንኳን አያሙአቸውም፡፡

የዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች ጊዜ አንስቶ የሕዝብ ጭንቀት እየሆነ የመጣው የአገሪቱ ድንበርና የሉዓላዊነት ጥያቄ ምን እንደሚመስል ለመገምገም ነው፡፡

የሰሜኑ ድንበራችን

የሰሜኑ ድንበራችንን በተመለከተ ኤርትራ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት፣ ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ከመደምደሙ በፊት ይውል ያድር እንደሁ እንጂ እንደማንኛውም ጦርነት ተጠናቅቆ ወደ ስምምነት መሄዱ የማይቀር ነበር፡፡ በስምምነቱም ወቅት የድንበር መካለሉ በኢትዮጵያ ላይ በግድ በተጫኑ ውሎች መሆኑ የአገራችንን ጥቅም እንደሚጐዳ ለኢሕአዴግ ምክር አዘል ሐተታዎችን አቅርበን ኢሕአዴግ የተከተለውን የተሳሳተ አካሄድ ለማስቀየር በብዙ ማሰንን፡፡

በተጨማሪም በኢትዮ ኤርትራ መሃከል የነበረው የማካለል ጥያቄ በተባበሩት መንግሥታት በተቋቋመው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (International court of justice) መታየት ሲገባው ለማንም ተጠያቂ ባልሆኑ ግለሰቦች በተዋቀረ ኮሚሽን እንዲዳኝ ሆነ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ዓይነት፣ ውሳኔው ይግባኝ እንዳይባልበት ኢሕአዴግ ተስማማ፡፡ ይህም የኢሕአዴግ አካሄድ ስህተት መሆኑ በጊዜው ብዙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ጠቁመው ነበር፡፡ ኮሚሽኑም ለጦርነቱ መንስኤ (cosus belli) የሆነው ብዙ ኢትዮጵያውያን ያለቁበት ባድመ፣ ከፊል ኢሮብን፣ የሰሜን ምዕራብ ትግራይ እንዲሁም በምሥራቅ አንዳንድ ቦታዎች ለኤርትራ ሰጠ፡፡ ጣልያኖች ኤርትራን በሚገዙበት ወቅትም ሆነ ኤርትራ ከተገነጠለች በኋላ አንድም ቀን የኢትዮጵያ አካል መሆንዋ ጥያቄ ውስጥ ያልወደቀችው፣ ሕዝቡ ተወካዮቹን መርጦ ለኢትዮጵያ ፓርላማ ሲልክ ለኢትዮጵያ መንግሥት ቀረጥ ሲከፍል የኖረባት ባድመ ለኤርትራ መሰጠቱ ፍፁም ዓይን ያወጣ ፍርደ ገምድል ውሳኔ ነበር፡፡ ሊታለፍ የማይገባውና ሰሚ ሊያምነው የማይችለው የጾረና ጉዳይ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ጾረና የኢትዮጵያ አካል መሆንዋን እያረጋገጠ የኢትዮጵያ ወኪሎች የለም ጾረና የኢትዮጵያ ግዛት አይደለችም የኤርትራ ነች ብለው ስለተከራከሩ ኮሚሽኑ እየተገረመ ጾረናን ለኤርትራ ሰጠ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም እስከ ዛሬም ጾረና የኤርትራ እንጂ የኢትዮጵያ አይደለችም በማለት ለምን እንደተከራከረና ጾረናን ለኤርትራ ለምን እንዳስረከበ ለሕዝብ አልገለፀም፡፡ ሕዝቡም እየጠበቀ ነው፡፡

ባድመና ሌሎችም ለኤርትራ የተፈረዱ አካባቢዎች በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት ለኤርትራ አስረክቦ በድንበሩ ላይ ችካሎች እንዲተከሉ የተላለፈው የኮሚሽኑ ትዕዛዝ ለመፈፀም ኢሕአዴግ አልተባበርም አለ፡፡ ይህም በመሆኑ ኮሚሽኑ ከጥቂት ወራት በፊት በራሱ አስመሳይ ክለላ (virtual demarcation) አድርጌአለሁ ብሎ ጉዳዩን በዚሁ ዘጋው፡፡ አስመሳይ (virtual demarcation) ማለት በወረቀት ላይ ችካል የሚተከልባቸው ቦታዎችን ማመላከት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አከላለል ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅድሚያ ያልተስማሙበት የአከላለል ዘዴ ባለመሆኑ ድርጊቱ ሕገ ወጥ ቢሆንም ይግባኝ ሊባልበት አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር በኤርትራ አትራፊነት በኢትዮጵያ ኪሣራ ለአንዴና ለሁሌም ተካሏል ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው አቶ ኢሣያስ አፈወርቂ በተደጋጋሚ እንደ ኢትዮጵያና እንደ ኤርትራ ድንበር በግልጽና በዝርዝር የተካለለ አፍሪካዊ ወሰን የለም የሚሉት፡፡ ይህንን አከላል ምክንያት በማድረግም አቶ ኢሣያስ ብልጠት በተሞላበት አባባል በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል ምንም ዓይነት የድንበር ጭቅጭቅ ወይንም አለመግባባት የለም ይላሉ፡፡ አቶ ኢሣያስ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚያውቀው ሉዓላዊ የኤርትራን ግዛት በኃይል ይዛለችና በአስቸኳይ ትውጣ እያሉ ለዓለም ሕብረተሰብ ጩኸት እያሰሙ ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ኢሕአዴግ ወደደም ጠላም ኤርትራ በሌላ ሁኔታ እስካልተስማማች ድረስ ለኤርትራ የተፈረዱት አካባቢዎች ከማስረብ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ የኮሚሽኑ ውሳኔ የማስፈፀም ኃላፊነት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ኃላፊነት ስለሆነ ይህንን ውሳኔ ለማስፈፀም የኢኮኖሚ እቀባ ከዚያም ያለፉ የተለያዩ እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል፡፡ ናይጄሪያና ካሜሩን በነበራቸው የወሰን ውዝግብ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለካሜሩን የፈረደውን 33 የድንበር ከተሞችና በቤንዚንና በዓሣ ሃብት የበለፀገችው ባካሲ ፔኒንሱላ ናይጄሪያ የዓለም አቀፉ ግፊት መቋቋም ስላልቻለች ለካሜሩን ማስረከብ ግድ ሆነባት፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ የዓለም አቀፍ ሕግ አካል እንደመሆኑ መጠን በዓለም አቀፍ ሕግ ላይ ሸፍቶ ለዘላለም መኖር አይቻልም፡፡

የምዕራቡ ድንበራችን

የሰሜኑ ድንበራችን በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ በቅርቡ የኢሕአዴግ መንግሥት መጠነ ሰፊ መሬት ለሱዳን መስጠቱንና አያሌ ኢትዮጵያውያን ከመሬታቸው እንደተፈናቀሉ በአገር ውስጥና በውጭ መገናኛ ብዙሃን በሰፊው ተገልፆአል፡፡ የኤርትራው ቁስል ሳይሽር አሁንም ተጨማሪ መሬት ለሱዳን ተሰጠ መባሉ ኢትዮጵያውያንን ያስጨነቀ ጉዳይ መሆኑ አያስገርምም፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ ኤርትራ ከኢትዮጵያ መሬት ከወሰደች፣ ሱዳንም እንደዚሁ ድርሻዋን ከተሰጣት መሬት ከኢትዮጵያ እንደዚህ በቀላሉ የሚገኝ ከሆነ ጅቡቲስ፣ ኬንያስ፣ ወሰኔ አዋሽ ነው የምትለዋ ሱማልያስ ነገ ከኢትዮጵያ መሬት ከመጠየቅ ምን ይከለክላቸዋል፡፡ ለሱዳንም ሆነ ለሌላ መንግሥት መሬት መስጠት ከዚህ ቀደም በነበሩት መንግሥታት ተደርጐ የማይታወቅ አደገኛ ምሳሌ ወይንም precedent ነው፡፡

የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ድንበር በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መሃከል እ.ኤ.አ 1902 እና በ1907 በተፈረሙ ውሎች ተወስኗል፡፡ እንግሊዞች ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሻለቃ ግዌን የተባለ የእንግሊዝ የጦር መኮንን ተመድቦ ሁኔታው በሚፈቅደው መሠረት ማለትም በአንዳንድ ቦታዎች ችካል በመትከል በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ድንጋይ በመቆለል ወሰኑን በሁለት ከፍሎ አካልሏል፡፡ ወሰን ለመካለል የግድ ምሰሶ ወይንም ችካል መተከል አለበት የሚል ሕግ የለም፡፡ ሱዳኖች እንደገና መካለል የሚፈልጉት ከስምምነቶቹ ውጪ መሬት ወደ ኢትዮጵያ ሄደብን በሚል ነው፡፡ አሁን ኢሕአዴግ ለሱዳን ሰጠ የተባለው መሬት በጣም ለምና ለሰሊጥ የሚሆን ነወ፡፡ ሱዳኖች ለዘመናት ሲቋምጡት የነበረ ሲሆን፣ ምንጊዜም ከኢትዮጵያውያን ገበሬዎች እጅ ወጥቶ አያውቅም ነበር፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎችና የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች መፈናቀላቸውን ቢያረጋግጡም መንግሥት በተደጋጋሚ በሱዳንና በኢትዮጵያ የጋራ ድንበር የተፈናቀለ ኢትዮጵያዊ ገበሬ የለም ብሏል፡፡ መንግሥት እንደሚለው ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ባይፈናቀሉ እንኳን ኢሕአዴግ ለሱዳን መሬት አለመስጠቱ አያረጋግጥም፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ከመሬታቸው ሳይፈናቀሉ መሬታቸው ወደ ሱዳን ሊታጠፍ ይችላል፡፡ ሁኔታው ወደፊት የባድመ ነዋሪዎች የሚገጥማቸው ዓይነት ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ ባድመን ለኤርትራ በምታስረክብበት ጊዜ ነዋሪዎቹ መሬታቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ አይገደዱም፡፡ ዓለም አቀፍ ድንጋጌ (universal Declaration of Human Rights) አንድ ሰው ዜግነቱን የመምረጥ መብት ይሰጠዋል፡፡ የመረጠው ዜግነት ያገኝ አያገኝ እንደሆነ ሕጉ እንደየአገሩ ይለያያል፡፡ ስለሆነም የባድመ ነዋሪዎች ዜግነታቸው ወደ ኤርትራዊነት ለውጠው ወይንም ደግሞ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ይዘው እንደውጭ አገር ዜጋ በባድመ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አልተፈናቀሉም የተባሉት ኢትዮጵያውያን ሁኔታም ይህንን ሊመስል ይችላል፡፡ መንግሥት ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች አልተፈናቀሉም ሲል መሬት ለሱዳን አልሰጠሁም አለማለቱ መሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡

ሁኔታው ይኸ ከሆነ ለመሆኑ መንግሥት፣ የሥራ አስፈጻሚው አካል ከኢትዮጵያ መሬት ቆርሶ ለሌላ አገር ወይንም መንግሥት የመስጠት ሥልጣን አለው ወይ? እንዲህ ዓይነት ስጦታስ ሕጋዊ ነው? ለወደፊቱ በኢሕአዴግ እግር የሚተካው የኢትዮጵያ መንግሥት (መቼም ኢሕአዴግ ዘላለማዊ አይደለም) ስጦታውን ሰርዞ መሬቱን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ማስመለስ ይችላል ወይ? የሚሉ በሕዝብ አእምሮ የሚጉላሉ ጥያቄዎችን በአጭር በአጭሩ ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡

ግልጽ እንዲሆንልን ከኤርትራ እንጀምር፡፡ ከኤርትራ ጋር የተደረገው የመካለል ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ በጊዜው በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትን ተከትሎ (ፓርላማ ያፀደቀው ስለሆነ) በኢትዮጵያ ላይ አሳሪነት አለው፡፡ በቀጣዩ መንግሥትም ላይ እንዲሁ፡፡ ሁለት ሉዓላዊ አገራት ስምምነት በሚፈራረሙበት ጊዜ ተፈራራሚ መንግሥታቱ ዴሞክራሰያዊ ይሁኑ አምባገነን ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ አገሩን ተቆጣጥሮ የሚያስተዳድር መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ ይሁን ወይም አምባገነን ከሌላ ሉዓላዊ አገር ጋር የሚያደርገው ስምምነት በአገሩ ላይ አሳሪነት አለው፡፡ ይህም ሲባል ተዋዋዮቹ መንግሥታት የተዋዋሏቸው ስምምነቶች የአገሮቻቸው ሕግ በሚደነግገው መሠረት በፓርላማም ይሁን ወይንም በወታደራዊ ካውንስል መጽደቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ከኤርትራ ጋር የተደረገው ስምምነት በሕጉ መሠረት በፓርላማው የፀደቀ ስለሆነ በኢትዮጵያ ላይ አሳሪነት አለው፡፡

የአሰብ ጉዳይ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ከተወሰነበት ምክንያቶች የኤርትራ ሕዝብ ፍላጐትን ጨምሮ የኢትዮጵያ የባሕር በር መብትንም ለማክበር ሲባል እንደነበረና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ኢትዮጵያ በአሰብ ላይ ያላት መብት ስለተረጋገጠ የኮሚሽኑ ውሳኔ አሰብን መንካት አይገባውም ነበር፡፡ ከመጀመሪያውኑ ኢትዮጵያ የአልጀርስን ስምምነት ስትፈራረም አሰብ ከዚያ ውጭ መሆኑን ማስገንዘብ ሲገባት ባለማድረጓ የአሰብ ጉዳይ ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡

ለሱዳን ተሰጠ የተባለው መሬት ሕዝብ ሳያውቀው ሕጉ በሚደነግገው መሠረትም ፓርላማው ሳያፀድቀው የሆነ ስለሆነ ስጦታው በሕግ ፊት ዋጋ ቢስ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች” መሆናቸው ተደንግጓል፡፡ ይህም ማለት ኢትዮጵያ የምትባል አገር የሉዓላዊነት ሥልጣን በራስዋ የላትም፡፡ የሉዓላዊነት ሥልጣን ሕገ መንግሥቱ በግልጽ እንደሚደነግገው የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የሕዝቦች ነው፡፡ ይህ በዓለም በየትኛውም ሕገ መንግሥት የማይገኝ እጅግ አስገራሚ የሆነ አንቀጽ ትንታኔ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡ ለአሁኑ ግን መሬት ከኢትዮጵያ ቆርሶ ይሰጥ ቢባል እንኳን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትን የያዙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ይሰጡ እንደሆነ እንጂ ኢሕአዴግ አይደለም፡፡

አገራት ወሰን ሲካለሉ አንዱ ከሌላው መሬት ሊረከብ ይችላል፡፡ በዓለም ዙሪያም የተለመደ አሠራር ሲሆን አሰራሩ ግን በምስጢር ሳይሆን የአገሪቱን ሕግ ተከትሎ መሆን አለበት፡፡

በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የሉዓላዊነት ባለቤት የሆኑት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሳያውቁትና ሳያፀድቁት ከኢትዮጵያ አንዱን ክፍል ቆርሶ ለሌላ አገር የመስጠት ድርጊት ወንጀል ውስጥ ሊወድቅ ይችል ይሆናል፡፡ በ1997 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 “ማንም ሰው . . . አገሪቱ እንድትከፈል ወይንም ከአገሪቱ ግዛት ከፊሉ እንዲገነጠል የሚያደርግ ተግባር የፈፀመ ሰው” እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል ቅጣት ሊወሰንበት ይችላል ይላል፡፡ መሬት ከአገር ቆርሶ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ለሌላ መስጠት በዚህ በተጠቀሰው አንቀጽ ውስጥ ይወድቅ አይወድቅ ጉዳዩ ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ ዳኛ የሚወስነው ይሆናል፡፡

ሱዳኖች ከኢትዮጵያ መሬት በሚወስዱበት ጊዜ ሕጋዊነቱን ለማረጋገጥ ምን ኃላፊነት አለባቸው? ሱዳኖች ከኢትዮጵያ መሬት በሚረከቡበት ጊዜ ርክክቡ የኢትዮጵያ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መፈፀሙን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ ቢያንስ መሬት አስረካቢው አካል ይህንን መሬት ቆርሶ ለሱዳን የመስጠት ሕጋዊ ሥልጣን አለው ወይ? ስምምነቱስ የኢትዮጵያ ሕግ በሚደነግገው መሠረት ሥልጣን ባለው አካል ፀድቋል ወይ ብሎ በመጠየቅ የኢትዮጵያን ሕግ መፈተሽ ይኖርባቸዋል፡፡ ሱዳን ከኢትዮጵያ መሬት ቆርሳ ስትወስድ ወይንም በሥራ አስፈፃሚው ሲሰጣት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ባለቤት በሆኑት በብሔር፣ በብሔረሰቦችና በሕዝቦች ተወካዮች እንዳልፀደቀ ታውቃለች፣ ወይም ማወቅ ይገባታል፡፡ ስለሆነም ሱዳን በሕገ ወጥ መንገድ የተረከበችው የኢትዮጵያ መሬት ወቅቱ ሲፈቅድ መመለስ ይኖርባታል፡፡ ለዚህም በቀጣዩ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 105 በሚደነግገው መሠረት ተሻሽሎ ኢትዮጵያ እንደ አገር የሉዓላዊነት ሥልጣን ሲኖራት ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት አቅርባ ፍርድ መጠየቅ ትችላለች፡፡ ለኢትዮጵያ ይፈረድ አይፈረድ፣ ፍርዱ ይፈፀም አይፈፀም በአብዛኛው በሁለቱ አገሮች ያለው የኃይል ሚዛን የሚወስነው ይሆናል፡፡

የደቡብና የምሥራቅ ድንበሮቻችን

በደቡብና በምሥራቅ በኩል የድንበራችን ሁኔታ ከምዕራቡና ከሰሜኑ በጣም በተሻለ መልኩ ተስተናግዷል፡፡ በጅቡቲና በአገራችን መሃከል ያለው ወሰን ያለቀለትና አጨቃጫቂ ነገር የሌለው ነው፡፡ በደቡብ ከኬንያ ጋር ያለን ድንበርም በ1957 ዓ.ም. ተካልሎ እልባት አግኝቷል፡፡ በየጊዜው በሁለቱ አገሮች ድንበር የሚነሱ ግጭቶች ከከብት ዘረፋ ጋር የተያያዙ የጐሣ ግጭቶች እንጂ ከድንበሩ ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡ በምሥራቅ የሱማሌላንድና የኢትዮጵያ ድንበር ተካልሎ ችካልም ተተክሎ ሁለቱን አገሮች የሚለይ ጥርጊያ መንገድ ተሰርቷል፡፡ ከሶማሊያ ጋር ያለው ድንበር ቢያንስ ሁለት ጊዜ ለጦርነቶች መንስኤ ሆኖ የቆየ ሲሆን አሁንም ችግሩ ያልተፈታ በመሆኑ ወደፊት በድርድር መካለል ይኖርበታል፡፡

የድንበር ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን እጅግ ከባድ መሆኑን መገንዘብና በጥንቃቄም መያዝ አለበት፡፡ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት ልትሰጥ ነው ሲባል የሰሙ አንድ አዛውንት “ዳር ዳሩ ሲሄድ በኋላ መሃሉ ዳር ይሆናል” ብለው ያስጠነቀቁት ምን ጊዜም መዘንጋት የለበትም፡፡

ከዚህ በላይ የተጻፈው የድንበሮቻችን ሁኔታ የሚገልጽ ቅንጫቢ እንጂ መላውን ታሪክ የሚዘረዝር አይደለም፡፡ የድንበር ውሎች፣ ስምምነቶችና ሌሎችም ዶኩሜንቶች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አርካይቭ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ ቢሆን የኢትዮጵያ የድንበር ሁኔታ ዘወትር ከሕዝቡ ተደብቆ በምስጢር ሲያዝ ኖሯል፡፡ ስለሆነም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የማስታወቂያ ሚኒስቴር በመተባበር ድንበሮቻችንን አስመልክቶ በየጊዜው ለሕዝብ ማብራሪያ ቢሰጡ ለግንዛቤ በረዳ ነበር፡፡

Former NSU professor and UN prosecutor, Yakob Hailemariam is one of the key figures of the former Coalition for Unity and Democracy Party (CUDP) during the May 2005 elections in Ethiopia.

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 21, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.