የኢትዮጵያ ወጣት፡ ፈተናና ተስፋ፤ የኔ የርቀት እይታ

Teklemichael Abebe…ይህ ወጣት፡ ችግርን ወይም የሀሳብ አለመመሳሰልን አድበስብሶ ከማለፍ ይልቅ መጋፈጥ መልመድ አለበት። ሀሳቡን በመጋፈጥ ከሚመጣው ችግርና ስቃይ ይልቅ ሀሳቡን ባለመጋፈጥ የሚመጣው ችግር የከፋ ነው። ለምሳሌ የትግራይ ህዝብ ሚናና የኢህአዴግ አገዛዝን እንውሰድ። ትግሬነትና ወያኔነት ወይንም አሁን ያለውን አገዛዝ ብንሸሸውም፡ እነዚህ ርእሶች በህልማችንም ጭምር የሚያውኩን ሰዎች አለን።…  ተክለሚካኤል አበበ …..

ክፍል አንድ

ተክለሚካኤል አበበ፡ እሁድ፡ 29 March 2009 ዓ.ም. ዋሽንግተን ዲሲ፡

“ውይይት ለሰላምና ለጋራ ዓላማ በኢትዮጵያ” ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የቀረበ ጽሁፍ

እንደመግቢያ፡ እንደ ዳራ

ስለኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር መናገር እያዳገተኝ መጥቷል። መሰረታዊ ችግራችንን የሚያገዝፉት የጥቃቅን ችግሮች ስብስብ ከጠበቅነው በባሰ ፍጥነት ስለሚለዋወጡ፡ ዋናው ችግር እንዲህ ነው፡ መፍትሄውም እንዲህ ይሁን ብሎ መናገር ቸግሯል። የዛሬ ስምንት አመት አገር ስለቅ፡ ሶስት መቶ ብር ትቼው የወጣሁት ጤፍ፡ ዛሬ አንድ ሺህ ገብቷል። ሰው ኑሮውን ይመስላልና፡ እንደ እህል ዋጋ፡ እንደ ኑሮ ውድነት፡ የችግራችን መፍትሄስ አልተለዋወጠ እንደሁ በምን አውቃለሁ፤ የሚል ጥያቄ ይመጣብኛል። ባለፈው ሳምንት በቅርቡ ከኢትዮጵያ ከመጣ ወዳጄ ጋር ስንጫወት፡ አልፎ አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ብር ስልክ፡ የምልክላቸውን ሰዎች፡ ለእከሌ ሀምሳ ብር ለእከሌ ደግሞ መቶ ብር ስጡልኘ ስል እንደከረምኩ ስነግረው ነው፡ የኢትዮጵያ ብር ወደኬንያ ሽልንግ እንደተጠጋ ያረዳኝ።1 የሆነ ሆኖ፡ ስለኢትዮጵያ መናገር አየከበደኝ የመምጣቱ ዋና ምክንያት፡ የሁኔታዎች በፍጥነት መለዋወጥ ነው። ድሮ ድሮ ለውጥ ቀስ እያለ ነበር የሚመጣው። መሰለኝ። አጼ ሀይለስላሴ ከስልጣን እስኪወርዱ ከሀምሳ ዓመት በላይ ቆይተዋል።ያሁኑ መንግስት 18 ዓመታት በስልጣን ቢዘልቅም፡ አሁን አሁን ግን ነገሮች በኛ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ በከፍተኛ ፍጥነት እየተለዋወጡ ነው። ትናንት ወዳጅ የነበረው ባላወቅነው ፍጥነት ጠላት ሆኖ ይገኛል። የዛሬ አስራ ስምንት ዓመት፡ ጥቂት ቢሊዮን ብር ይዞ ኢትዮጵያ የገባው ሼክ፡ ይኸው አሁን 9 ቢሊዮን ገባ፡ 43ኛ ወጣ።2 እየገሰገሰ ነው። ጥቂት ቀጥሎ ኢትዮጵያ የሕወሀት/ኢህአዴግ መሆኗ ቀርቶ የመለስ/አላሙዲ/ስብሀትና ቤተሰቦቹ ልትሆን ነው። ነው ሆናለች መሰል?

በርግጥ እነሱም/ኢህአዴግ በዚህ አያያዘቸው፡ በተለይ ደግሞ እኛ ተቃዋሚዎች በዚህ አያያዛችን ከተጓዝን፡ የምንመኘው ዴሞክራሲ ለመወለዱ፡ ሰዎቹ ያስራ ስምንቱን እጥፍ ላለመቆየታቸው ምንም ዋስትና የለም። የማንም፡ ሙሉ ክፍለዘመንም ስልጣን ላይ መቆየት ላያስጨንቅ ይችላል። የሚያስጨንቀው ግን፡ በስልጣን ላይ ያሉ መንግስታት አትመው የሚያልፉት የጥፋት ማህተም እንጂ። በቅርብ ከሰባት አመት መለያየት በኋላ ያገኘሁት አንድ ወዳጄ፡ “አባቴ፡ አንድ መንግስት ስልጣን ላይ፡ አስር፡ አስራ አምስት አመት ከቆየ፡ እሱን ብቻ የሚያውቀው ትውልድ ፈጠረ ማለት ነው ይለኝ ነበር” ብሎኛል። በተከታታይነት እጦት በታጠነ ፖለቲካዊ ባህልና ታሪክ፡ አዲስ መንግስት ያለፈውን መንግስት ስራ ምንም ሳያስቀር ድምጥማጡን በሚያጠፋበት አገር3 ደግሞ፡ አንድ መንግስት እሱን ብቻ የሚያውቀው ትውልድ ፈጠረ ማለት፡ በኛና በዚያ ከኛ በኋላ በመጣው ትውልድ መካከል የአመለካከት ግጭት ሊፈጠር መግባባት ሊጠፋ ነው ማለት ነው።4 ስለኢህአዴግ ብሄር ብሄረሰቦች ፖለቲካና ስለትውልድ፡ እነሆ አንድ ነጥብ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄሮች ተበድለዋል አልተበደሉም ወደሚል ጥልቅ ክርክር መግባት የዚህ ጽሁፍ ዓላማ አይደለም። ብቻ ይሄ በዚህ አስራ አምስት አስራ ስድስት ዓመታት ውስጥ የተፈጠረው ትውልድ፡ ኢህአዴግ ያስተማረውንና ኢህአዴግ የቀረጸውን ታሪክ ብቻ ከሆነ የሚያውቀውና፡ ይሄ የኢህአዴግ ትምህርት ደግሞ ባብላጫው ወይም በከፊል ከፋፋይ ከሆነ፡ ይሄንን ትውልድ ለማዳን ይሄንን ትውልድ የሚመስል የዚህን ትውልድ ችግር ከግምት ያስገባ የዚህን ትውልድ ጭንቅላት የሚመጥን ዘመኑን የዋጀ መፍትሄ ያሻል ማለት ነው። በዚህ ሰዓት፡ የኢትዮጵያ፡ በተለይም የወጣቱ ዋና ችግር ምንድነው የሚለውን ብዙዎቻችሁ እንደ ወጣት፡ መልስ ስትፈልጉለት የኖራችሁትን ጥያቄ ለመመለስ ባልሞክርም፡ በዚህ መልስና መፍትሄ አሰሳ፤ የምሁራን ድርሻ ምን ሊሆን ይገባል የሚለውን እንደወጣት ለመመለስ እጥራለሁ። አንዳንድ መጻህፍትን ለማገላበጥ ብሞክርም፤ ይሄ ወረቀት ባብዛኛው መሰረት የሚያደርገው፡ ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስት ዓመት ተኩል ቆይታዬ ተነስቶ፡ በኬንያ የአራት ዓመት ቆይታ ከዚያም በዚህ በካናዳ ባለኝ የአራት ዓመት ህይወት፡ በራሴ በተሳተፍኩበትና ባለፍኩበት እንዲሁም ባስተዋልኩት ካንዳንደቻችሁ ጋርም ባደረግኩት ውይይት ላይ የተመሰረቱ አመለካከቶችን። ለዚህ ውይይት ስዘጋጅ በተቻለ መጠን ጽሁፌ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲሄድና፡ ሚዛናዊ እንዲሆን ጥረት አድርጌያለሁ። ግን ይሄንን ጽሁፍ የጻፍኩት በጸረ-ኢህአዴግ መንፈስ መሆኑን ልደብቅ አይቻለኝም። እነሆ ሀሳቤ።

የዚህ ትውልድ ችግር፡ በዚህና በዚያ ትውልድ አይን

መቼም የዚህን ትውልድ ችግር መዘርዘር ለቀባሪ ማርዳት ቢሆንም ቅሉ፡ አንዳንድ ግዜ ግን፡ የዚህን ትውልድ ችግር ትንሽ ትንሽ ለቀባሪውም ቢሆን ማስታወስ በጎ ነገርነው። በመሰረቱ፡ የዚህ ትውልድ ችግር ከተቀረው ህብረተሰብ ችግር የተለየ አይደለም። ከስራ አጥነት እስከ ስደት፡ ከጭቆና እስከ እስራት፡ ከተስፋ ማጣት እስከ ተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ፤ ችግራችን ስፍር ቁጥር የለውም። ችግራችን በጋም የለውም። ለዘመናት የማያባራ የችግር ክረምት እንጂ። ሴተኛ አዳሪነት፡ መሀይምነት፡ በሽታ፡ ረሀብ፡ ሙስና፡ የማያስፈልግ ጦርነት፡ የደን መመንጠርና የአካባቢ መበከል ድርቅ፡ ጥቂቶቹ ናቸው።5 አገር በቀል ያልሆኑ የዴሞክራሲና የህግ የበላይነት መርሆች ባፍንጫችን ይውጡ ብንል እንኩዋን፤ የለም ይሄ መንግስት ህገ መንግስት ሰጠን፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም እንደልባቸው እንዲንቀሳቀሱ ይፈቅዳል ብንል እንኩዋን፡ በርግጥም ይሄ መንግስት ካለፉት መንግስታት ይሻላል፡ ስልጣን ከያዘ ጀምሮም የአገሪቱ አመታዊ ምርት በተከታታይ አድጓል የሚለውን ፉከራ ብንቀበል እንኩዋን፡ በማናቸውም መለኪያ የማናስተባብላቸውና የማያከራክሩ ችግሮቻችን ዝርዝር የትየለሌ ነው። አንዱ ችግራችን ሌላኛውን ችግራችንን አያቆመውም። ረሀብ ገባ ብለን መውለድ አናቆም ነገር የህዝባችን ቁጥር እያሻቀበ ነው። ምጣኔ ሀብታችን በድርብ ቁጥር አደገ ቢባልም፡ የምግብ እርዳታ ፈላጊ ቁጥር በያመቱ እያሻቀበ ነው። እንግዲህ በዚህ ሁሉ መካከል ነው ወዳጄ ተክሌ የሻውና ዶ/ር አክሎግ እስኪ ስለኢትዮጵያ ወጣት ተስፋ ምኞትና አመለካከት፡ በተለይም ከኦባማ መመረጥ ጋር ተያይዞ የተስፋችንን ቅኝት የሚለውጥ ነገር ተከስቶ ይሆንን? ይሄ ትውልድስ፡ ወጣቱ ማለት ነው፡ ከምሁራን ምን ይማራል? ብለህ ብትጽፍ ብትናገርም ብለው የጠየቁኝ።6 ስለኢትዮጵያ ወጣት አስተያየትና አለመካከት እንዲሁም ምኞት መጻፍ ብዙ ላያስቸግር ይችላል። ግን የምር እንጻፍ ከተባለ፡ ተስፋው ምሬት ብቻ ይሆናል። ስለዚህም ስለኢትዮጵያ ወጣት የምር ተስፋ የምር መጻፍ አቀበት ሆነብኝ።

አንድ ኢትዮጵያ በሶሻል ወርክ ትምህርት ሁለተኛ ድግሪውን እየሰራ ያለ ወዳጄ የላከልኝ የጥናት ወረቀት እንደሚያመለክተው፡ ብዙዎቻችሁም እንደምታውቁት፡ የኢትዮጵያ ወጣት ገበሬውም ይሁን ተማሪው፡ ከተሜውም ይሁን ገጠሬው ኑሮው እየተበለሻሸና ቁልቁል እያደገ ነው የሄደው። ምናልባት ይላል ይሄ ጸሀፊ፡ በየከተማው ውስጥ ታላላቅ ሆቴሎች ተገንብተው፡ ታላላቅ ህንጻዎች ታንጸው ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ ህንጻዎች የተያዙት በጥቂት ግለሰቦች ነው።7 እኔ ከዚህ ጸሀፊ በተሻለ ነጻነት ውስጥ ስለምኖር፡ በዚህ ጸሀፊ ላይ የምጨምረው ነገር ቢኖረ እየፈጠርን ያለነው ጥቂት ሀብታሞችን ብቻ ሳይሆን ጥቂት ያንድ ብሄር ሀብታሞችን ነው እላለሁ።8 በሀብታምና ደሀ መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ከመምጣቱ የተነሳ፡ የብዙ ወጣቶች ሞራል ወድቋል። ተስፋም መቁረጥ ተንሰራፍቷል። የትምህርት ፖሊሲው ፈጠራንና ምርምርን ከማበረታታት ይልቅ ሽምደዳንና ለፈተና ብቻ ማጥናትን የሚያበረታታ በመሆኑ ችግር ፈቺ ትውልድ ማፍራት ያስቸግራል። እንደ አሜሪካና አውሮፓ ያሉ ታላላቅ ኢኮኖሚዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ስራ አጥነት ካስገቡ፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለች አገር ደግሞ በዚህ ሰዓት ምን ያህል ልትጠቃ እንደምትችል መገመት አዳጋች አይደለም። ዛሬ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በገዢው ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ካልተሳተፉ ስራ ትምህርትና ሌላም ብዙ እድል ማግኘት የጠበበ ነው።9 የስራ ዋስትናም የለም።10

ካንደኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ፡ ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት ፡ ቁጥሩ የማይቀንስ ነገር፡ የኢትዮጵያ ገበሬና በደን የተሸፈነው መሬታችን ናቸው። ኢህአዴግ የገበሬው ቁጥር እንዳይቀንስ፡ የደናችንም ፕርሰንት እንዳይንቀሳቀስ የገዘተው ይመስላል።ኢህአዴግ ከደርግ አገሪቱን ከነጠቀ በኋላ ለብዙ አመታት 85 እና ሶስት ፐርሰንት፡ ሆኖ ቆይቶ፡ አሁን ገና ትንሽ ፈቀቅ አለ መሰል ?! ኢትዮጵያ ውስጥ አሁንም 80 ከመቶው ህዝብ የሚተዳደረው በግብርና ሲሆን የአገሪቱ 50 ከመቶ የሚሆነው ምርት የሚገኘውም ከግብርና ነው። በ2005 የወጣ ሰነድ እንደሚያመለክተው ከኢትዮጵያ ውስጥ እድሜያቸው ከ15-29 አመት የሆነ፡ ወደ ሰላሳ ከመቶ የሚጠጉ ወይንም ከ20 ሚሊዮን ወጣቶች ይገኛሉ።11 የሆነ ሆኖ፡ ይሄ ገበሬ የሚወልዳቸው፡ አንድ የጋሞ ገበሬ በምሬት እንደተናገሩትም እድሜያቸውን ሁሉ ገበሬ ሆነው እንዲኖሩ የተፈረደባቸው ሌሎች ገበሬ ልጆቹ፡12 መሬት በመንግስት በተያዘበት አገር በዚያችው አምናም ካቻምናም በያዟት መሬት ላይ ነው በድህነት የሚርመሰመሱት። ስለዚህ የዚህ ወጣት አንዱና ዋንኛው ችግር ድህነት ነው። ድህነቱን ማን ፈጠረው፤ ድህነቱን ለማጥፋት ተስፋ አለን፡ ምሁራንስ ለዚህ ምን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ? የሚሉት ጥያቄዎች ለክፍለዘመን ያልተመለሱ፡ አብረን የምንመልሳቸው ጥያቄዎች ናቸው። አንድ ነገር ግን ርግጥ ነው፡ በቡሀ ላይ ቆረቆር እንዲሉ፡ እነሆ ዘመነ አመጣሽ ችግር በመጣ ቁጥር፡ ለምሳሌም የዓለም ኢኮኖሚ ሲናጋ፡ ምርጫን ተከትሎ ህዝብ በብዛት ቢታሰር፡ ቢገደል፡ ጦርነት ቢመጣ፡ የመጀመሪያ ተጠቂው፡ ገንዘብ የሌለው፡ መሬት የሌለው፡ ሀብት አማራጭም የሌለው ወጣት ነው።

ተስፋ ፍለጋ፡ የአማራ ተስፋ፡ የክርስቲያን ተስፋ ?

በዚህ የችግር ክምረት ውስጥ ነው፡ ተስፋን ፍለጋ፡ በተለይም ከምሁራን ሊፈልቅ ስለሚችል ነገር እንድመረምር የተላኩት። በቅድሚያ፡ ወደ መጽሀፍ ቅዱስ ገባሁ። ይሄንን ሰውየ ይዘኸዋል እንዳትሉኝ እንጂ ከመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ድንገት ለዚያ ለታምራት ላይኔ የዘነበለት ተስፋና ፍቅር፡ ለኔም ለኢትዮጵያም ያካፋ እንደሁ ብዬ ነው፡ ወደ መጽሀፍ ቅዱስ የዘለቅኩት። በጥንት ዘመን ለእስራኤሎች በግብጽ፡ በምድረ ፈርኦን ቀንበር ስር ይታያቸው የነበረ ተስፋ፡ ለኛም በዚህ ዘመን ፈርኦናት አገዛዝ ስር ላለነው ወጣቶች ይገለጥ እንደሁ፡ ከዘፍጥረት አስከ ራእየ ድረስ ወረድኩት ብዬ ባልዋሻችሁም፡ የተጓዝኩትን ያህል ተጉዤም፡ ያንን ተስፋን የበላው ጅብ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ሊጮህልኝ አልቻለም። ተስፋን ባላገኘውም ግን፡ የተስፋችን ባህርይ ምን መሆን እንዳለበት ከመጽሀፍ ቅዱስ ተስፋ አግኝቻለሁ። የኢትዮጵያዊያን ተስፋ የክርስቲያኖች ብቻ ተስፋ አይደለም። የኢትዮጵያ ተስፋም የአማሮች ብቻ ተስፋ መሆን የለበትም። መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ተስፋን ባገኘውም እንኩዋን፡ ያ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ተስፋ ተስፋነቱ፡ ለዚያ በመጽሀፉ ለሚያምኑ ብቻ ነውና የመጽሀፍ ቅዱስ ተስፋ ለትዮጵያዊያን ሁሉ ተስፋ ሊሆን አይችልም አልኩ። በሌላ አነጋገር፡ ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ተስፋ ከዚያ ከሀይማኖቱ ተከታዮች ስለማይዘል፡ በሀይማኖት መጻህፍት ውስጥ የማደርገውን አሰሳ ለጊዜው ገታሁት።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ መጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ያጣነውን ተስፋችንን በስህተትም ቢሆን አሁን ያለው መንግስት ላይ መጣል የማይታሰብ ነው። ከህግ ትምህርት አንዱና የትም ቦታ ለማሸነፍ የሚያስፈልገን መርህ፡ የተቃራኒን ክርክር በገለልተኝነት ለማየት ሞክር የሚለው ነው። የተቃራኒውን ክርክር በቅጡ ሳይመለከት የራሱን ምክንያት የቆለለ ተሟጋች አያሸንፍም። በንግድ ሂዱ፡ በጦርነት በሉ፡ በትምህርት፡ በዲፕሎማሲ በሉ፡ ሁልግዜም የሌላኛው በኩል፡ ምን ይላል ብሎ መመርመር የግድ ነው። እና ወደ ኢህአዴግ ሄድኩኝ። እንዳታማትቡብኝ እንጂ አንዳንድ ግዜ እንደው ምናልባት፡ ኢህአዴግ፡ ደርግ ወይንም የቀደሙ የኢትዮጵያ መንግስታት መጥፎ በሆኑበት መልኩ ነው መጥፎ የሆነው ይሆን? ስለዚህስ ምናልባት ብናግዘው፡ እንደውም አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት፡ አሁን ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተደረገ ነውና፡ እነዚህ ሰዎችኮ ምናልባት እየተከተሉ ያሉት አካሄድ መልካም ይሆናልና እንደው እናግዛቸው ይሁን? የሚሉ የሀሳብ ሐጢያቶች ሽው ይሉብኛል። ግን ያ የራበኝን ተስፋ ከኢህአዴግ ማየት አልቻልኩም። ኢኮኖሚያችን በድርብ ዲጂት አድጎ ሊሆን ይችላል። ብዙ ዩኒቨርስቲዎች ተከፍተው፤ መንገዶችና ቤቶች ተገንብተው ይሆናል። ሰው ግን መንገድ አይበላም። ኢህአዴግ ሲመጣ የገባልን በቀን ሶስት ግዜ የመብላት ተስፋ እንደውም ወደታች ወርዶ፡ ዘመኑ ለብዙዎች የግዴታ ጾም መሰለ። በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ሳይራብ ያሰለፍንበት ዓመት ትዝ አይለኝም። ምግብ ያልበላ ህዝብ፡ ምግብ ያልበላ ትውልድ ደግሞ ጤናማ አይሆንም። ተስፋ እንኩዋን እንዳንበላ ነጻ መገናኛ ብዙሀን፡ ነጻ መተንፈሻ፡ ነጻ መደራጃ፡ ነጻ የፖለቲካ መንቀሳቀሻ የለንም።

ምእራቡን ዓለም፡ በተለይም አሜሪካንንና ካፒታሊዝምን ተስፋ ማድረግን መረመርኩት። ያ ታሪክ አበቃ፤ ከዚህ በኋላ ታሪክም አልፋም ኦሜጋም ሊበራሊዝምና ነጻ ገበያ ነው ተብሎ የተዘመረለት ስልተ ምርት ራሱን እየበላ ባለበት ሁኔታ፡ የጠራ ካፒታሊዝምንና አሜሪካንን ተስፋ ማድረግ የማይታሰብ ነው። አሜሪካ የራሷ የቤት ስራ የራሷ ጣጣ ያላት አገር ነች። ምናልባት በጉልበታችን በተናጠል ለቤተሰቦቻችን የምንገነባው ተስፋ እንዳለ እንጂ፡ ከአሜሪካና ከምትከተለው ስልተ ምርት የምናገኘው አስተማማኝ ተስፋ የለም። ማርክሲዝም። እኔ እንጃ፡ ምርክሲዝምን ብዙ አላውቀውም። ባውቀውም ሞቷል መሰለኝ። ስለዚህ እንደወጣት ተስፋችን ሁሉ ከአሳ ነባሪና ከማእበል ጋር እየተጋፉ፡ ከኬንያ ፖሊሶችና ከደቡብ አፍሪካ ወሮበሎች ጋር እየተፋለሙ፡ ባህር መሻገርና በስደት መንከራተት ሆነ።13 እውነቱን ለመናገር ተስፋ የሆነ ተስፋ የለንም። ተስፋ ልናገኝ የምንችልበት አንድ ተስፋ ግን አለን። እሱን በኋላ እጠቅሰዋላሁ። ከምንም በላይ ግን ተስፋ የሚያስቆርጠው፡ ከምንም በላይ ግን መጪውን ዘመን ጨለማ የሚያለብሰው የኢህአዴግ አገዛዝ አይደለም። ኢህአዴግ ክፉ ነው። አከተመ። የራሳችንን ጓዳ ገንቢና ተስፋ ሰጪ ነገር መራቆት መመልከት ግን ተስፋ ይነሳል። ከምንም በላይ ተስፋ የሚያስቆርጠው በኛ ጓዳ ያለው ሽኩቻ ነው። ብዙ ተብሎለታል። ብዙም ይባልለታል። ስለዚህ ብዙ አልልበትም። ትንሽ ግን ጣል ላድርግበት።

የበለጠ የሚያበሽቀው ይሄ ስርአት ተስፋችንን ማብነኑ አይደለም። ችግሩ ከመንግስት ወይም ከስርአቱ በኩል ብቻም አይደለም፤ በተወሰነ መልኩ ከኛም ነው የሚመነጭ። ከዚህም ከዚያም ትውልድ። ለምሳሌ ከዚህ ትውልድ። ዶ/ር ዮናስ አድማሱ፡ በ1992 ዓ/ም በአዲስ አበባ በተዘጋጀ የስነ ጽሁፍ ምሽት ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋብዘናቸው ስለዚህ ትውልድ ምን ይላሉ አልናቸው። ከዚህ ትውልድ ጋር ያላቸውን ችግር ባንድ አረፍተ ነገር አስቀመጡት። “ይህ ትውልድ አያነብም” አሉ። ያ ችግር ይስተዋላል በትክክል። ለዚያ እኔ ራሴ ምስክር ነኝ። በ2001 ዓ.ም. ወደኬንያ ስሰደድ ስለዓለም የነበረኝ እውቀት በትምህርት ክፍለግዜ የምማረውና ከጋዜጦች የምቃርመው እንዲሁም በስማ በለው የምለቃቅመው ብቻ ነበር። ያም ሆኖ ምን ያህሉ ወጣትስ ያ ይደርሰዋል? ቤቱ ይቁጠረው። ብዙዎቻችን፡ በተለይ በየእለቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የምንሳተፍ ወጣቶች ለእለት ፍጆታ በሚሆኑ፡ በየእለቱ በሚከሰቱ ጉዳዮች ላይ ብቻ ነው የምናተኩረው። መሬት ለሱዳን ተሰጠ፡ ብርቱካን ታሰረች፡ የቅንጅት መሪዎች ታሰሩ፡ ኦባማ ተመረጠ፡ ልደቱ ባንዳ ሆነ። እነዚህ ሁሉ መልካም ናቸው። እነዚህ ሁሉ ግን ዜና ናቸው። ዜና ደግሞ ብቻውን እውቀት አይሆንም። የሀገራችንን ችግር በደንብ በሚያሳይ፡ ከዚያ ባሻገር ጥልቅ በሆነ ምርምርና ችግሮቻችንን በሚገልጥልን ዘላቂ የታሪክና የፍልስፍና ንባብ ላይ አናተኩርም። ይሄ አንዱ የኔ ትውልድ ችግር ነው፤ በኔ አይን። የምሁራን ችግር ግን ይበዛል።

የምሁራን ነገር፡ እንደ ችግርም እንደመፍትሄም

ሀ- ጠላትን/ኢህአዴግን ስለመብለጥ፡ ስለእልህ ስለብልጠት

አንድ የአምቦ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ ወዳጅ አለኝ። በብሄሩ ኦሮሞ ነው። እንከራከራለን። “አንዳንድ ግዜ እኮ ተክሌ፡ ለኛ ከአንድነት ሀይሎች ይልቅ፡ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ቢቆይ ይሻለናል፡ ምክንያቱም የአንድነት ሀይሎች በኢህአዴግ ያገኘነውን መብቶች ሊያሳጡንም ይችላሉና።”14 ይሄንን ስጋት መጋራት አለብን። ለዚህ መድሀኒቱ፡ ኢህአዴግ ለአንዳንድ ብሄሮች ለሽንገላም ይሁን የምሩን የሰጣቸው መብቶች ወይም ጥቅማ ጥቅሞች ካሉ፡ ያንን የምናጠፋና የምንቀማ መስለን መታየት የለብንም። እንዲያውም የምናጎለብት እንጂ። ይሄንን በቅርቡ ከብርቱካን ጋር በተያያዘ በጻፍኩት ጽሁፍ ላይ አስፍሬያለሁ። እንደ ምርጫ ብናየው፡ ከኢህአዴግ የተሻለ ግብዣና ስጦታ ማድረግ አለብን። ለምሳሌ የእኔ እምነት፡ ኢህአዴግ ለኢትዮጵያ ኦሮሞ ህዝብ ጠቀማቸው አልጠቀማቸው፡ በራሳቸው ቋንቋ የመማር፡ በራሳቸው ቋንቋ የመገልገል፡ በራሳቸው ተወላጆች የመዳኘት፡ በራሳቸው ቋንቋ ባህላቸውን የማዳበር መብት ሰጥቷቸዋል የሚል ነው። እንደኔ እንደኔ እምነት በምንም መልኩ በራሳቸው በኦሮሞዎች ጥያቄ ካልሆነ በስተቀር ይሄንን መብት የሚጋፋና የሚያሰጋ አጀንዳ ይዘን መንቀሳቀስ የለብንም። እንዲያውም ልናቀርብላቸው የሚገባው ምርጫ፡ ከዚያ የተሻለና ምናልባትም የኦሮሞን ህዝብ ከተቀረው ህዝብ ጋር የበለጠ የሚያዋድድ፡ ኢህአዴግ ያሰበው አይነት የተከፋፈለና ምንግዜም ሊፈርስ የተዘጋጀ ኢትዮጵያዊነትን ሳይሆን እንዲያውም የተሻለ የተዋሀደ ኢትዮጵያዊነትን የሚፈጥር ምርጫ ነው። ባፍ ቋንቋ መማር ብቻ አይደለም፤ የኦሮምኛ ቋንቋን ከአማርኛ ተጨማሪ አገር አቀፍ የስራ ቋንቋ እናደርጋለን አይነት አጀንዳ በሰፊው ማራመድ።

በዚህ መስመር ልግፋበት። ለምሳሌ ብዙ የኢትዮጵያን ክፉ ማየት የማይሹ ሰዎች፡ ኦነግን አጥብቀው ይጠላሉ። ለኔ፡ ኦነግን መጥላትና መዋጋት መፍትሄ አይሆንም። ምክንያቱም አላማውን መሰረት አድርገን ከምናራምደው ኦነግን የማግለል ቅስቀሳ፡ ይልቅስ በተቃራኒው ያንን ቅስቀሳ አይተው በወገናዊነታቸው ተሸንፈው ኦነግን የሚደግፉ ሰዎችን ልናፈራና ልናበዛ እንችላለን። ብዙ እኔ የማውቃቸው የኦነግ ደጋፊዎች ኦነግን አፍቅረው ወይም ወደው የገቡ ሳይሆኑ፡ በሀሳባቸውና በእምነታቸው ብቻ ኦነግ ተደርጎ ከመፈረጅና፤ ቢሆንም ባይሆንም ያው ወገኔ ይሻለኛል ከሚል ስሜት በመነጨ የመጡ ናቸው። ኦነግ ተቀባይነት ከሌለው በራሱ ሰአት ተኖ ይጠፋል። ማተኮር ያለብን ኦነግን ማውገዝ ላይ ሳይሆን፡ ኦ.ህ.ኮ.ን ማቅረብ ላይ ነው። “ቆንጆ፡ ኢህአዴግ በቋንቋችሁ እንድትዳኙ አደረገ። መልካም። እኛ ደግሞ ጎንደርም ገብታችሁ በኦሮምኛ እንድትዳኙ እናደርጋለን” ማለት አለብን። መቼም ጎንደሬው ወዳጄ፡ ተክሌ የሻው15 የሚከፋው አይመስለኝም። ለነገሩ የታሪክ አጋጣሚ እንጂ ኦሮምኛ የኢትዮጵያ ቋንቋ የማይሆንበት ምን ምክንያት አለ?

ሌላ ምሳሌ፤ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ አሁን ያለውን የኢህአዴግ ሕገ መንግስት ይቀበሉታል። የሚጠሉት አፈጻጸሙን እንጂ። ይሄንን ሕገ መንግስት የተቀበሉት በርግጥም ይሄ ህገ መንግስት እኛ እንደምናስበው፡ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ ሆኖ ላይሆን ይችላል። ይልቅስ ከኛ በኩል ይሄንን ህገ መንግስት ሊቀይር የተሰናዳው ሀይል፡ ያገኘናትን ትንሽም ጥቅም ያሳጣናል ከሚል መነሻ ይመስለኛል።16 ይሄንን፡ ያ ከላይ የነገርኳችሁ ወዳጄ ኦሮሞው ገረሱ በግልጥ አስቀምጦታል። በቅርቡ የዶ/ር ነጋሶን ቃለ ምልልስ ስመለከት፡ በስልጣን ላይ በነበሩበት ግዜ ከሰሯቸው ስራዎች ውስጥ የሚኮሩበትና ለኦሮሞ ያበረከቱት ስራ የትኛውን ነው ሲባሉ “ህገ-መንግስቱ ትልቁ ለኦሮሞ ህዝብ ያበረከትኩት ገጸ-በረከት ነው ብለው እንደሚያኑ ተናግረዋል።17 ዶ/ር ነጋሶ ይሄንን ያሉት፡ ዛሬ ከኢህአዴግ ተለያይተው በነጻነት በሚኖሩበት ወቅት ነው። ቢከፋም ቢለማም ዶ/ር ነጋሶን የመረጣቸው ህዝብ አለ። ያ ህዝብ ሲመርጣቸው እምነታቸውን ተጋርቶ ነው። ይሄ ስጋት፡ ይሄ የሚኮሩበት፡ የኦሮሞ ልጆች በቋንቓቸው እንዲዳኙ እንዲገለገሉ፡ የኦሮሞ ባህል ተመልሶ እንዲያንሰራራ ያደረገው ህገ መንግስት የሳቸው ብቻ አይደለም። ስለዚህ ዶ/ር ነጋሶና ተከታየቻቸውን ኢህአዴግ በዚህ ባስራ ስምንት ዓመታት የሰራውን ሁሉ እንደከዚህ ቀደሙ መንግስታት እናፈርሳለን ብንላቸው፡ አብረውን አይሰለፉም።

ለ- ነገሮችን ስለማድበስበስ፡

ይህ ወጣት፡ ችግርን ወይም የሀሳብ አለመመሳሰልን አድበስብሶ ከማለፍ ይልቅ መጋፈጥ መልመድ አለበት። ሀሳቡን በመጋፈጥ ከሚመጣው ችግርና ስቃይ ይልቅ ሀሳቡን ባለመጋፈጥ የሚመጣው ችግር የከፋ ነው። ለምሳሌ የትግራይ ህዝብ ሚናና የኢህአዴግ አገዛዝን እንውሰድ። ትግሬነትና ወያኔነት ወይንም አሁን ያለውን አገዛዝ ብንሸሸውም፡ እነዚህ ርእሶች በህልማችንም ጭምር የሚያውኩን ሰዎች አለን። ይሄ ችግር ያለው በሁለቱም በኩል ነውና፡ ማለትም በውይይቱ ወይንም ከታች በምሳሌዎች እንደማብራራው፡ ብዙ የትግራይ ተወላጆች ወደ ተቀረው ኢትዮጵያዊ ከተቀረውም ኢትዮጵያዊም ብዙዎቻችን፡ ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በመካከላችን አለመተማመንና ጥርጣሬ ስለሰፈነብን ችግሩን አንስተን መወያየት አለብን። የትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሁሉ ወያኔ ነው? ይሄንን ጥያቄ ማንሳትና መነጋገር እንጂ መድበስበስ የለበትም። መነጋገሩ ከሚያመጣው ችግር ይልቅ፡ መድበስበሱ የሚያመጣው ችግር ይበልጣል። ለምሳሌ አቶ ገብሩ አስራት ባለፈው መቀሌ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ሲናገሩ፡ አንዱ ተሰብሳቢ ለምን የትግራይን ህዝብ ከሚጠሉት ሰዎች ጋር ተሰለፍክ ብሎ ጠየቃቸው። አቶ ስዬ አብርሀም እንደዚሁ የቅንጅት አባል ስለመሆናቸው የሚወራው ወሬ እሳቸውን ከትግራይ ህዝብ ጋራ ለማጣላት ሆን ብሎ የሚደረግ ዘመቻ እንደሆነ ተናግረዋል። ስለዚህ ይሄ ጥያቄ ያስነሳል። የሳቸው የቅንጅት አባል መሆናቸው የትግራይን ህዝብ ያስቀይማል? እሳቸውንም ከትግራይ ህዝብ ያጣላል ማለት ነው? የትግራይ ህዝብ ለምን ያንን ይጠላል? የአቶ ገብሩ በሌሎች ተቃዋሚዎች ሰፈር ሲያልፉ መገኘት ለምን ሌሎች ትግሬዎችን አስቀየመ? በነዚህ ሁሉ ላይ መወያየት ችግሩን እንዲጠራ ያደርገዋል። ምሁራን ይሄንን ያለማድበስበስ ዘመቻ በምሁራዊ ትንታኔና ምርምር መቃኘትና መንደፍ አለባቸው።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 20, 2009. Filed under NEWS. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.