የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጥታ ዘገባ (ኢትዮጵያ 2 – ደቡብ አፍሪካ 1)

የኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጥታ ዘገባ (ኢትዮጵያ 2 – ደቡብ አፍሪካ 1)

(Watch video)
የዛሬው የኢትዮጵያ እና የደቡብ አፍሪካ ወሳኝ ጨዋታ ሊጀመር፤ አስር ደቂቃ ቀርቶታል። ተጫዋቾች ወደሜዳው እየገቡ ነው። የኢትዮጵያ ቡድን ባለ አረንጓዴ እና ቀይ ባለመስመር ማልያ አድርገው ገብተዋል። ደቡብ አፍሪካዎች ቢጫ ማልያ አድርገዋል። ስቴድየሙ ጢም ብሎ ሞልቷል። የሁለቱም አገሮች ብሄራዊ ህዝብ መዝሙር እየተዘመረ ነው። ኢ.ኤም.ኤፍ. ሙሉ ዘገባውን በቀጥታ ማቅረቡን ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ቡድንን በመወከል የሚጫወቱት በረኛው ጀማል ጣሰው፣ ተከላካዮች ስዩም፣ ቢያድግልኝ፣ አይናለም እና አበባው ናቸው። መሃል ላይ ምንያህል፣ አዲስ ህንጻ፣ አስራት መገርሳ ሲሆኑ አጥቂዎች ደግሞ ሽመልስ፣ ኤርሚያስ እና ሳላዲን ናቸው። በትላንት ዘገባችን እንደገለጽነው ደጉ ደበበ በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም። አዳነ ግርማም ከእረፍት በኋላ ይገባል።
የህዝቡ ሞራል በጣም የሚገርም ነው። ገና ጨዋታው ሳይጀመር ስቴዲየሙ በጭፈራ ደምቋል። አራቱም ዳኞች ከግብጽ ናቸው። ግብጻዊው ፋሩቅ አህመድ ጨዋታውን አስጀምረዋል።
3፡00 AM በኢትዮጵያ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ጨዋታው ተጀመረ። ጨዋታው ከተጀመረ አምስት ደቂቃ ሆኗል። ሁለቱም ቡድኖች ጫና ፈጥረው ለመጫወት እየሞከሩ ናቸው። የኢትዮጵያ ቡድን የደቡብ አፍሪካ ክልል ውስጥ ቅጣት አግኝቷል። ቅጣት ምቱ ተመታ። የተመታችውን ኳስ ሳላዲን ሰኢድ ጥሩ የግብ ሙከራ አደረገ። በረኛው መለሰበት እንጂ ጥሩ ሙከራ ነበር። ከክቡር እንግዶቹ በስተቀር የተቀመጠ አንድም ተመልካች ያለ አይመስልም። ህዝቡ ቆሞ እየጨፈረ ሞራል በመስጠት ላይ ነው። በክቡር ትሪቡን አካባቢ መቶ የሚሆኑ የደቡብ አፍሪካ ደጋፊዎች ይታያሉ። ጨዋታው ቀጥሏል።
8ኛው ደቂቃ ላይ… የኢትዮጵያ ተከላካዮች ተዘናግተው ሳለ፤ ደቡብ አፍሪካ ግሩም የሆነ ሙከራ አድርጓል። ሁለቱም ቡድኖች ለማጥቃት እየሞከሩ ነው። 10ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ እና ጌታነህ በግሩም ሁኔታ ተቀባብለው አልፈው ነበር። ሆኖም ተከላካዩ አክሽፎበታል። 12ኛው ደቂቃ ላይ አሁንም የኢትዮጵያ ቡድን ተቸማሪ ሙከራ አድርጎ ነበር። የደቡብ አፍሪካ ተከላካዮች ለሳላዲን የሚሰጡ ኳሶችን በቀላሉ እያከሸፉበት ናቸው። 13ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ሙከራ በጌታነህ ከበደ… እንደገና ከሽፎበታል። የሚገርም ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጥሩ እየተጫወቱ ናቸው። 15ኛው ደቂቃ ላይም ሌላ ሙከራ በኢትዮጵያ ቡድን ተደረገ። የኢትዮጵያ ቡድን ኳሱን ተቆጣጥሮ እየተጫወተ ይገኛል። 17ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሌላ ሙከራ ከርቀት አድርጓል – በረኛው መለሰበት እንጂ ግሩም ሙከራ ነበር።
ጨዋታው ከተጀመረ 19 ደቂቃ ሆኖታል። ደቡብ አፍሪካዎች ድንገት ከሚያደርጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ በስተቀር፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያለማጋነን፤ ጥሩ ጨዋታ በማድረግ ላይ ይገኛል።
20ኛው ደቂቃ ላይ የደቡብ አፍሪካ ቡድን ተቀባብሎ በማለፍ፤ ፓርከር ግሩም ሙከራ አድርጎ ነበር። በረኛው ጀማል ጣሰው አክሽፎበታል። ኳስ በፈጣን ሁኔታ ከአንደኛው ሜዳ ወደሌላው እየሄደች ነው። ጨዋታው ተሟሙቋል።
ጨዋታው ከተጀመረ 30 ደቂቃ ሆኖታል። አሁን ኳሷ በደቡብ አፍሪካዎች ቁጥጥር ስር የሆነች ይመስላል። ባፋና ባፋናዎች ተረጋግተው ማጥቃት ጀምረዋል። የደቡብ አፍሪካው ተጫዋች በግብ ክልል ውስጥ የመታውን ኳስ፤ ጀማል ጣሰው ቤጁ በትቶ አወጣት። ሆኖም የደቡብ አፍሪካው ተጫዋች እንደገና በቴስታ የመታትን ኳስ፤ ጀማል ጣሰው በተመሳሳይ መልኩ በቴስታ መትቶ መልሷታል። የሚገርም ግሩም ሙከራ ነበር።
የመጀመሪያው ግማሽ ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ናቸው የቀሩት። ሆኖም 17 ቁጥሩ ፓርከር በኢትዮጵያ ቡድን መረብ ላይ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። ደቡብ አፍሪካውያን እያጠቁ ናቸው።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ 8 ደቂቃ ቀርቶታል። ህዝቡ በዝምታ ተውጧል። 40ኛው ደቂቃ ላይ ደቡብ አፍሪካዎች ተቀባብለው አልፈው ሌላ የግብ ሙከራ አድርገው ነበር። ጀማል ጣሰው አከሸፈበት።
42ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ የመጀመሪያውን ጎል ለኢትዮጵያ አስቆጥሯል። ግሩም ጨዋታ ነው። ስቴዲየሙ እንደገና በጩኸት እና በጭፈራ ተደበላልቋል።
እረፍት ለመውጣት ሁለት ደቂቃ ቀርቷቸዋል።

ጎል!

ጎል!

ግብጻውያኑ ዳኞች እንደተፈራው ሳይሆን፤ በጥሩ ሁኔታ ዳኝተዋል።
አሁን ሁለቱም ቡድኖች እረፍት ወጥተዋል።
==============

ከእረፍት በኋላ ጨዋታው ቀጥሏል። ጨዋታው ከተጀመረ 8 ደቂቃ ሆኗል። ደቡብ አፍሪካዎች አዲስ በተቀየሩት ተጫዋቾቹ እያጠቁ ናቸው። አዳነ ግርማ እያሟሟቀ ነው። አዳነ ግርማ ተቀይሮ ገብቶ ለሚቀጥለው 30 ደቂቃ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል።
19 ቁጥሩ አዳነ ግርማ፤ በሽመልስ በቀለ ተቀይሮ ገባ። የአዳነ ግርማ መግባት ጨዋታውን ሊቀይረው ይችላል። በተለይም ከሰላዲን ሰ ኢድ ጋር የሚያደርጉት ቅብብል ግሩም በመሆኑ፤ ተጨማሪ ግብ ሊያገቡ ይችላሉ። ጨዋታው እንደመጀመሪያ ሳይሆን ቀዝቀዝ ብሎ ቀጥሏል። አዳነ ግርማ ከገባ በኋላ ከመሃል ሜዳ ኳስ እያደራጁ በመሄድ ለማጥቃት እየሞከሩ ነው።
ምንያህል ተሾመ በበሃይሉ አሰፋ ቱሳ ተቀይሮ ገብቷል። ጨዋታው ከተጀመረ 20 ደቂቃ ሆኗል። በሁለቱም ቡድኖች መካከል ጨዋታው ቀዝቀዝ ያለ ይመስላል። ደጋፊዎችም አልፎ አልፎ እንጂ፤ በተቀናጀ መልኩ ሳያቋርጡ ድጋፍ ሲሰጡ አይሰማም። ይህ ማለት ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ እኩል ከወጡ፤ ኢትዮጵያ ከሴንትራል አፍሪካ ጋር በምታደርገው ጨዋታ ማሸነፍ አለባት።
24ኛው ደቂቃ ላይ ባልታሰበ ሁኔታ፤ በርናርድ ፓርከር በቴስታ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል። ኢትዮጵያ 2 – ደቡብ አፍሪካ 1። ፓርከር አንድ ለራሱ፤ አንድ ለኢትዮጵያ ቡድን በማስቆጠር እስካሁን፤ ብዙ ግብ በማግባት እየመራ ነው (ፈገግታ)
አልፎ አልፎ የርስ በርስ ሽኩቻ ታይቷል። ረብሻ ሊነሳ ሲል፤ ዳኛው ሁለቱም ቡድኖች ወደየሜዳቸው እንዲመሱ አድርገው ቸዋታውን አረጋግተው ቀጥለዋል። ህዝቡ “ዋ! ዋ! ዋ!” በማለት እየጮኸ ነው። አሁን ጨዋታው ሊጠናቀቅ 13 ደቂቃ ቀርቷል። አበባው ቡጣቆ ተጎድቶ በመውጣቱ የኢትዮጵያ ቡድን በአስር ተጫዋች እየተጫወተ ይገኛል። የተጫዋች ቅያሪ ሊደረግ ነው። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃ ቀርቷል። ብርሃኑ ቦጋለ በአበባው ቡጣቆ ምትክ ገብቶ እየተጫወተ ይገኛል።
ጀማል ጣሰው ደቂቃ በማባከኑ… ሁለተኛውን ቢጫ አግኝቷል። ይህ ማለት በፊፋ ህግ መሰረት ለሚቀጥለው ኢንተርናሽናል ጨዋታ አይሰለፍም።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ብቻ ቀርቷል።
መደበኛው ጨዋታ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ቀርቷል። ኢትዮጵያከምድቧ በአንደኝነት ቀጥላ ከአስሩ ውስጥ ለመቀላቀል ጥቂት ደቂቃዎች ቀርተዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ሳላዲን ሰኢድ ብቻውን አልፎ ሊያስቆጥር የሚችለው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቷል። አስር ሴኮንድ ቀርቷል። አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ተለበለበ።
ፊሽካ ተነፋ! ጨዋታው ተጠናቀቀ! ኢትዮጵያ 2 – ደቡብ አፍሪካ 1።
ኢትዮጵያ ለሚቀጥለው የአለም ዋንጫ ለማለፍ በመጨረሻው ምእራፍ ላይ ይገኛል። እንኳን ደስ ያላቹህ! መልካም የአባቶች ቀን!! Happy Father’s day!

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 16, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.