የኢትዮጵያ እና የዛምቢያ ጨዋታ ቀጥታ ስርጭት (1 – 1)

ቀጥታስርጭት-  ኢትዮጵያ 1 – ዛምቢያ 1 ። (EMF) የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ቢጫ ማሊያቸውን ነው የለበሱት። ስቴዲየሙን የሞሉት የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ነው የሚመስለው። የህዝቡ ብዛት… “በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ከአርባ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ጨዋታውን ለማየት ቲኬት ቆርጠዋል።” የሚለውን ዜና የሚያረጋግጥ ይመስላል። በኢትዮጵያ ቡድን በኩል የተሰለፉት የሚከተሉት ናቸው። በረኛ ጀማል፣ ተከላካዮች ስዩም ተስፋዬ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣አበባው ቡጣቆ እና ብርሃኑ ቦጋለ ሲሆኑ፤ መሃል አከፋፋዮች በሃይሉ አሰፋ፣ አስራት መገርሳ፣ አዳነ ግርማ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ጌታነህ ከበደ እና ሳላዲን ሰይድ በአጥቂ መስመር ተሰልፈዋል። የቡድኑ ካፒቴን አዳነ ግርማ ነው።
ጨዋታው ከተጀመረ 7 ደቂቃሆኗል። ኢትዮጵያዊያን በማጥቃት ላይ ናቸው። ስቴዲየሙ በኢትዮጵያዊያን የተሞላ ይመስላል።የኢትዮጵያ ቡድን ያደረገውን አይነት ቢጫ ማሊያ ያደረጉ ተመልካቾች፤ አንደኛውን የስቴዲየም ስፍራ አደይ አበባ አስመስለውታል።10 ኛው ደቂቃ ላይ የዛምቢያው 13 ቁጥር ሱዙኑ በሳላዲን ላይ ጥፋት በመፈጸሙ የመጀመሪያውን ቢጫ አግኝቷል። ጨዋታው ከፍተኛ ፉክክር የሚታይበት ነው። (ዘገባችን ይቀጥላል። አብራችሁን ቆዩ።)

ለጥቁር አንበሶቹ መልካም እድል እንመኛለን።

ለጥቁር አንበሶቹ መልካም እድል እንመኛለን።

16ኛው ደቂቃ ላይ… በጣም አስደናቂ ጎል… የዛምቢያው በረኛ ወጥቶ ሳላ፤ በአናቱ ላይ አሳልፎ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጣች። የሚገርም ሙከራ ነው። በዚህ አይነት አጨዋወት ከቀጠሉ የኢትዮጵያ ጥቁር አንበሶች ተስፋ አላቸው። ሆኖም ዛምቢያዎቹ በድንገት ጥቃት እየሰነዘሩ ናቸው። ምናልባት በኢትዮጵያ ላይ ድንገተኛ ግብ እንዳያስቆጥሩ ያሰጋል። ጨዋታው ቀጥሏል። ውጤት 0 – 0።

 

Ethiopia 1 – 1 Zambia – highlights

የኢትዮጵያ ቡድን ወደጎል ሊመታ ሲል ተጠለፈ። ኢትዮጵያ ፍጹም ቅጣት ምት አገኘች። 23ኛው ደቂቃ። ሳላዲን ፍጹም ቅጣት ምቱን መታ። ሆኖም የዛምቢያው በረኛ ተወርውሮ መለሰው።

አሁን ጨዋታው የሚደምቀው፤ ስቴዲየሙ የሚነቃቃው ኢትዮጵያውያኑ ኳስ ሲይዙ ሆኗል። ቀደም ሲል እንዳልነው አልፎ አልፎ ዛምቢያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሜዳ ሲገቡ ግን… አስገራሚ ሙከራ እያደረጉ ነው። የሚያስፈራ ጨዋታ ነው። አሁን ጨዋታው ከተጀመረ 30 ደቂቃ ሆኗል። ሳላዲን ወደፊት እየገፋ ሁለት ጊዜ የግብ ሙከራ አድርጓል። አሁንየኢትዮጵያ ጥቁር አንበሶች ወደፊት እያጠቁ ናቸው። ሆኖም 30ኛው ደቂቃ አካባቢ የዛምቢያው አጥቂ ብቻውን ኳስ ይዞ ሲመጣ በረኛው ጀማል እግሩን ሰንዝሮ ስለመታው፣ በራሱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ይመስላል። (አሁን በተጎዱት ተጫዋቾች ምክንያት ጨዋታው ተቋርጧል።)

ጀማል በቃሬዛ እየወጣ ሳለ ዳኛው ቀይ ሰጡት። የኢትዮጵያ ቡድን በአስር ተጫዋቾች ሊቀጥል ነው ማለት ነው። ጥሩ ያልሆነ ነገር ነው። ተጫዋቹና ተመልካቹ ተቃውሟቸውን እየገለጹ ናቸው። በረኛው ቀይ ስላየ አንድ ተጫዋች ተቀንሶ፤ በረኛ ተቀይሯል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ ዘሪሁን ታደለ ተቀይሮ ገብቷል። ዛምቢያ የተሰጠውን የቅጣት ምት ስቶታል።

በጣም ያሳዝናል። ክዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ቡድን የማጥቃት ስራ ሰርቶ ቢያንስ አንድ ጎል ካላገኘ ሁኔታው በጣም ያሰጋል። አሁን ኳሱን ዛምቢያዎች በተራቸው የተቆጣጠሩት ይመስላል። ምናልባት በዛምቢያ የግብ ክልል ውስጥ እነሳላዲን ጥሩ ኳስ ካገኙ ጎል ያስቆጥራሉ የሚል እምነት አለ። ተመልካቹ ለጥቁር አንበሶቹ የሚሰጠውን ሞራል አላቋረጠም። 45ኛው ደቂቃ ላይ የዛምቢያው 4 ቁጥር ጥፋት በመፈጸሙ ቢጫ ካርድ አይቷል። የመጀመሪያው ግማሽ ጨዋታ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ቀርተዋል።

ባለቀ ሰአት ዛምቢያ አንድ አገቡ። 9 ቁጥሩ አስገራሚ ጎል ነው ያገባው። ወደኢትዮጵያዊያኑ ሄደው ሊደንሱ ሲሉ በጠርሙስ መቷቸው። ጨዋታው ከመሃል ሜዳ እንደጀመረ… ፊሽካ ተነፋ እረፍት ወጡ። ከ እረፍት በኋላ ኢትዮጵያዊያኑ በአስር ተጫዋች ብቻ ስለሚጫወቱ፤ ውጤት የማግኘቱ ነገር ያስፈራል። ቢሆንም ከሚቀጥሉት 15 ደቂቃዎች በኋላ እንደገና ተስፋ ሰንቀን እንጠብቃለን።

ዛምቢያ 1 – ኢትዮጵያ ዜሮ

ከ እረፍት በኋላ – በ እረፍት ወቅት ያነጋገርናቸው አንዳንድ ሰዎች፤ ሳላዲን ከሳተው ፍጹም ቅጣት ምት ይልቅ ጀማል ጣሰው የፈጸመው ፋወል የተቆጩ ይመስላል። ጨዋታው ተጀመሯል። ኢትዮጵያዊያኑ ጥቁር አንበሶች በማጥቃት ላይ ናቸው። በጨዋታ ኢትዮጵያውያን ቢበልጡም፤ታንዛንያዎቹ ድንገት የሚያገኙትን ኳስ ወደፊት በመግፋት የሚያስደነግጥ ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ናቸው። ሰውነት ቢሻው የመሀል ተጫዋቾች እየተመላለሱ እንዲጫወቱ ምልክት በመስጠት ላይ ናቸው። በርግጥም መሀሉ ወደፊት እና ወደኋላ በመመላለስ የጎደለውን የአንድ ሰው ቦታ መሙላት ይኖርባቸዋል። አጨዋወታቸው ብዙም ተስፋ አያስቆርጥም። ከ እረፍት በኋላ ጨዋታው ከተጀመረ 5 ደቂቃ አልፏል።

ከ እረፍት በኋላ ጨዋታው ከተጀመረ 15 ደቂቃ አልፎታል።  ይህ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እየተላለፈ አልነበረም። ሆኖም አንድ ማስታወቂያ ተላለፈ፤ እንዲህ ይላል። “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይህንን ፕሮግራም ለዋናው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሳያሳውቅ እያስተላለፈ ነው። ይህም ህገ ወጥ ተግባር ነው የሚል ማስታወቂያ ታየ። በዚህ መሃል ጌትነት ከበደ በአዲስ ህንጻ ተቀየረ:፡ ወዲያው አዲስ ህንጻ ለሳላዲን፣ ሳላዲን ለአዳነ ግርማ ሰጠውና አንግሉን ገጭቶ የሚገርም የሚደንቅ የመጀመሪያውን ጎል ለጥቁር አንበሶች አስቆጠሩ። አሁን ስቴዲየሙ አበደ። ህዝቡ ጮኸ…. ሰውነት ቢሻው እየጨፈረ ነው… እየዘለለ ነው። ዋው የሚገርም ጎል… 19 ቁጥሩ አዳነ ግርማ አዳነን! ጨዋታው አንድ እኩል ሆኗል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ ብቻ ነው የቀረው። በአስር ሰው ተጫውተው በዚህ ውጤት ቢለያዩም የሚያስቆጭ አይነት አይደለም። ያለፈውን አመት የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ዛምቢያን ማሸነፍ ቀላል ነገር አይደለም።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ላይ አይናለም ተሾመ በፉአድ ኢብራሂም ተቀይሮ ነበር። ሆኖም ምንም ሳይጫወት ጨዋታው ተፈጸመ። ዘጠና ደቂቃው አበቃ። የኢትዮጵያ ጥቁር አንበሶች፤ ፍጹም ቅጣት ምት ስተው፤ በጎዶሎ (10) ተጫዋቾች ያለፈውን የአፍሪካ ሻምፒዮን ጋር እኩል ለእኩል ወጡ። ጨዋታው ካበቃ በኋላ ተጫዋቾቹ ደስታቸውን ገልጸዋል። ህዝቡም የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ እያውለበለበ ያሸነፉ ያህል… ደስታቸውን እየገለጹ ነበር። ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጨዋታ የሚሆነው ከቡርኪና ፋሶ እና ከናይጄርያ ጋር ይሆናል።

በዛሬው የዚሁ ምድብ ጨዋታ ቡርኪና ፋሶ እና ናይጄርያም 1 -1 ሆነው ጨዋታውን ጨርሰዋል። ይህ ደግሞ የዚህ ምድብ ቡድኖች ሁሉም እኩል ነጥብ እንዲኖራቸው ያደርጋል። በተለይም ጨዋታው ሊጠናቀቅ የመጨረሻ ሴኮንድ ላይ ቡርኪና ፋሶ ያስቆጠረቻት ግብ ናይጄሪያዎቹን ያስደነገጠ ነበር። በርግጥም የናይጄሪያ መሸነፍ ለኢትዮጵያ ጥሩ አጋጣሚ ነው የሚሆነው። ቀጣዮቹን ጨዋታዎች በቀጥታ የጽሁፍ ስርጭት በማድረግ ውጤቱን እናሳውቃችኋለን። እስከዚያው ለጥቁር አንበሶቹ መልካም እድል እንመኛለን።

ከመሰናበታችን በፊት አንድ ነገር እንበል። ጨዋታው እየታየ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በህገ ወጥ መንገድ ጨዋታውን የሚያስተላልፍ መሆኑ በሁሉም ቴሌቪዥኖች በጽሁፍ ታይቷል። ድርጊቱ ህገ ወጥ እና የአፍሪካ እግር ኳስ ደንብን የጣሰ መሆኑም በዚያው ማስታወቂያ ላይ ተገልጿል። ነገሩ ያሳፍራል። ኢትዮጵያ የተጠየቀችው 18 ሚሊዮን ብር ወይም አንድ ሚሊዮን ዶላር ነው። “እንደ ኢሳት ያሉ እና ሌሎች ጣቢያዎች በኢትዮጵያ እንዳይተላለፉ የአየር ሞገዱን ለማበላሸት በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ይባክናል። ምናለበት ሚዲያን ለማፈን ከሚጠቀሙበት በጀት ቀንሰው፤ ሳይሰርቁ እና ሳይሳቀቁ ጨዋታውን ቢያስተላልፉ?” እንላለን።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 21, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.

One Response to የኢትዮጵያ እና የዛምቢያ ጨዋታ ቀጥታ ስርጭት (1 – 1)

  1. Maza Girma

    January 23, 2013 at 11:21 AM

    After all the circumstances they made it even. I am happy with the outcome. Our players were determined and diligent. They have shown confidence even when they were down zero to one with one less player. Since they overcome today’s game obstacles, I believe they have the potential to go all the way to the top. I am sending all my prayers and positive spirits to South Africa to energize our team (Tikur Anbesewooch).
    If anyone missed the game on TV, I recommend you to read the article written by EMF on thewww.Ethiopiaforum.com. It is as if you were inside the stadium in South Africa. Dawit Kebed puts it explicitly to cover the entire game (90+minuts) well descriptive and written. It forces you to feel the moment. Dawit, you are one amazing and very talented writer that I have ever known. I have always admired and enjoyed your scripts and articles. Thank you for sharing your phenomenal talents. I will stay tune for the next game on Friday, Ethiopia vs. Burkina Faso. I am sure you will definite the game to us with your writing once again.
    Oh, and I love the team picture that you created and the name you gave them, “Tikur Anbesewooch”.