የኢትዮጵያ እና አይቮሪኮስት ጨዋታ ቀጥታ ስርጭት (አይቮሪኮስት 5 – ኢትዮጵያ ዜሮ)

(EMF) ጨዋታው ተጀምሯል። የአይቮሪኮስት ተጫዋች ወደ ኢትዮጵያ ግብ ክልል ውስጥ ኳስ እየገፋች ስትመጣ፤ የኢትዮጵያ በረኛ በፔናልቲ ክልል ውጪ ወጥታ ኳሷን ለመምታት ሞከረች። ሆኖም ኳሷን ስለጨረፈቻት፤ የአይቮሪኮስቷ አጥቂ ያቺኑ ኳስ አክርራ በመምታት ጎል አግብታለች። ሜዳው ውሃ አለው፤ ለጨዋታ አመቺ ባይሆንም የኢትዮጵያ ቡድን በአጭር እየተቀባበሉ ስለሚጫወቱ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም የይቮሪኮስት ቡድን ሌላ ሙከራ  አክርሮ አደረገ። በረኛዋን አልፎ ኳሷ የኢትዮጵያ ተከላካይ እግር ውስጥ ናት። በሚገርም ሁኔታ እዚያው ጎል ስር ኳሷ ከ እግሯ ሾልኮ ሁለተኛው ግብ ተቆጠረ።

በኢትዮጵያ እና በአይይቬሪኮስት የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮና እንደቀጠለ ነው። አይቮሪኮስት ጨዋታውን እየመራ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ሉሲዎች ቆንጆ ጨዋታ እያሳዩ ነው ግን 2-0 እየተመሩ ናቸው። አሁን አርባኛው ደቂቃ ላይ ቤዛ ራሂማ ቢጫ ካርድ ተሰጣት። ዳኛዋ ለምን ቢጫ እንደሰጠቻት ግልጽ አይደለም። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃ ቀርቷል – ኢትዮጵያ 2-0 እየተመራች ነው።

በዚሁ ውጤት ላይ እንዳሉ እረፍት ወጥተዋል።

ይህ ሉሲዎች ያሉበት ቡድን ታላላቆቹ የአፍሪቃ እግር ኳስ ቡድኖች ያሉበት ሲሆን፤ የሞት ቡድን ተብሎ የሚጠራ ነው። በዚህ የሞት ምድብ ቢ ውስጥ ናይጄሪያ፣ ካሜሩን፣ አይቮሪኮስት እና ኢትዮጵያ ይገኙበታል።

ዛሬ የካሜሩን እና የናይጄሪያ ቡድኖች ተጫውተው ናይጄሪያ ካሜሩንን 2- 1 አሸንፏል። ከዚህ ጨዋታ ቀጥሎ የኢትዮጵያ ሴቶች ከካሜሩን እና ከናይጄሪያ ጋር መጫወት ይጠበቅበታል። ከ እረፍት በኋላ የኢትዮጵያ ቡድን ቢያንስ አንድ ጎል፤ ከቻለ ሁለት ቢያገባ ከምድቡ ላለመውጣት ያለውን እድል ያሰፋለታል። ከእረፍት በኋላ እንደገና እንገናኛለን።

ሁለቱም ቡድኖች እንደገና ወደ ሜዳ ተመልሰዋል። አይቮሪኮስት የፍጹም ቅጣት ምት አገኘ። 3ኛ ጎል አስቆጠሩ። አይቮሪኮስት 3 – ኢትዮጵያ 0።

 የግቡን አናት ሜቶ አራተኛ ጎል ገባ። አይቮሪኮስት 4 – ኢትዮጵያ 0። ብዙም የተሳካልን አይመስልም። ጨዋታው ቀጥሏል። 54ኛው ደቂቃ ላይ እንገኛለን። ከ እረፍት በኋላ በ8 ደቂቃ ውስጥ 2 ጎል ኢትዮጵያ ላይ ገባ። ይህ ጥሩ እድል አይደለም። ቢሆንም ጨዋታው እንደቀጠለ ነው። እስከመጨረሻው 90 ደቂቃ ድረስ ተሸንፈናል ማለት አይቻልም። ሜዳው በውሃ በመጨቅየቱ ለጨዋታ አስቸጋሪ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያውያን በአጭር ቅብብል ለማለፍ የሚያደርጉት ጥረት በኮትዲቩዋር (አይቮሪኮስት) ተጨዋቾች እየከሸፈባቸው ይገኛል። አሁን አይቮሪኮስቶች ጨዋታውን የተቆጣጠሩት ይመስላል… ጨዋታው እንደቀጠለ ነው።

60ኛው ደቂቃ ላይ እንገኛለን።

 77ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ቲያ ለራሷ 3ኛውን… ለአይቮሪኮስት ደግሞ 5ኛውን ግብ አስቆጠረች። አይቮሪኮስት 5 – ኢትዮጵያ ዜሮ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ቀርተዋል።
ለአሁኑ ዘጠናው ደቂቃ አልቆ ፊሽካ ተነፍቶ ጨዋታው ተጠናቋል።

ጨዋታው በአይቮሪኮስት 5 – ለዜሮ አሸናፊነት ተጠናቋል። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ሴቶች ቡድን ከናይጄሪያ እና ከካሜሩን ጋር ሌላ ፍልሚያ ይጠብቀዋል። ከምድቡ ለማለፍ ብዙ ጎሎችን ማግባት ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሴቶች ቡድን ለስምንተኛው የአፍሪካ ሴቶች የዋንጫ ውድድር የመድረስ እድሉ ከወዲሁ የተጨናገፈ ይመስላል።

ማጠቃለያ፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የመጀመሪያው ግብ ከኢትዮጵያ በረኛ የተሰጠ ስጦታ ነው ለማለት ይቻላል። ሁለተኛው ግብ የተከላካያችን ሌላ ስጦታ ነበር። 3ኛዋ ግብ በፍጹም ቅጣት ምት የተገኘ በመሆኑ ወቀሳ አያስፈልገውም። 4ኛ እና አምስተኛው የአይቮሪኮስት ግብ በንጹህ ጨዋታ የተገኙ በመሆናቸው፤ ምንም ማለት አይቻልም። በሜዳው ላይ የነበረውን ውሃና ጭቃ እንደምክንያት ማቅረብ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ውሃውም ጭቃውም ለሁለቱም ቡድኖች አስቸጋሪ ፈተና ነበርና። ይልቁንም የመጀመሪያዋን ኳስ በረኛችን ጨርፋ የወጣችባት አንድም ከልምድ ማነስ ወይም ኳሷ በውሃ በመራሷ ሊሆን ይችላል። 2ኛዋም ግብ በዚሁ አይነት የገባች ሳትሆን አትቀርም። ምክንያቱም ኳሷ ከኢትዮጵያ ተከላካይ እግር ስር ሾልካ ነው ያመለጠቻት። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ፍጻሜው ለማለፍ ካሜሩን እና ናይጄሪያን በጥሩ ነጥብ ማሸነፍ ያስፈጋል። ላይሆን ይችላል፤ ሊሆን የሚችልበትም አጋጣሚ ኖሮ ሉሲዎች ያስደንቁን ይሆናል። ማን ያውቃል? በዚያም ተባለ በዚህ ግን በዛሬው ጨዋታ አይቮሪኮስት ከምድቡ በብዙ ነጥብ እንዲመራ አድርጎታል። ናይጄሪያ 2ኛ፤ ካሜሩን 3ኛ፤ ሉሲዎች ደግሞ በአራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ከኢትዮጵያ ከመውጣታቸው በፊት ሼክ አላሙዲን የ5ሚሊዮን ብር ሽልማት ሰጥተዋቸው ነበር። ይህንን ጨዋታ አሸንፈው ለዋንጫ ቢያልፉ ኖሮ ደግሞ፤ ለያንዳንዳቸው ባለሁለት ክፍል ኮንዶሚኒየም ቤት ቃል ተገብቶላቸዋል። ግን የተሳካላቸው አይመስልም። ቀጥሎ የሚጫወቱት ካሜሩንም ሆነ ናይጄሪያ ከአይቮሪኮስት የማይተናነሱ ቡድኖች ናቸው። ለማንኛውም ቀጣዩ ጨዋታ ኖቬምበር 4 ቀን ይካሄዳል። በቀጥታ ለማስተላለፍ እንሞክራለን።

 

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 29, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.