የኢትዮጵያ እና ሴንትራል አፍሪካ ጨዋታ ቀጥታ ስርጭት ( ኢትዮጵያ 2 – ሴንትራል አፍሪካ 1) ኢትዮጵያ አሸነፈች!!

ኢ.ኤም.ኤፍ – በዛሬው እለት ለአለም ዋንጫ  የማጣሪያ  ጨዋታ እያደረገ ይገኛል። ጥቁር አንበሶቹ  የኢትዮጵያ ቡድን ተጫዋቾች የተለመደውን አረንጓዴ እና ቢጫ መስመር ያለውን ማልያ አድርጎ ነው የገባው። አራቱም ዳኞች ከአልጄርያ የመጡ ናቸው። ጨዋታው ሲጀመር የድምጽ ማጫወቻው ባለመስራቱ የሁለቱም አገር የህዝብ መዝሙር አልተዘመረም። በስቴዲየሙ የሚገኙት ጥቂት የሴንትራል አፍሪካ ቲፎዞዎች ያለሙዚቃ መዝሙራቸውን ጀምረዋል። የኛ በዝምታ ታልፏል። ጨዋታው በገለልተኛ አገር – በኮንጎ ብራዛቪል እየተካሄደ ነው። የኢትዮጵያ ቡድን ይህንን ጨዋታ ካሸነፈ ወይም እኩል ከወጣ ከአስሩ አሸናፊዎች አንዱ በመሆን፤ በሚደረገው እጣ መሰረት ከደረሳቸው አገር ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ያደርጋሉ። በደርሶ መልሶ ጨዋታ ካሸነፉ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ለአለም ዋንጫ ታልፋለች ማለት ነው። ይህንን ጨዋታ በቀጥታ እየተከታተልን እናስተላልፍላችኋለን። አሁን ጨዋታው ከተጀመረ 15 ደቂቃ ተቆጥሯል። ኳስ በብዛት በመሃል አካባቢ ናት። ታዋቂዎቹ አስራት፣  አዳነ፣ ሳላዲን፣ ኡመድ እና  ሽመልስ ወደፊት እያጠቁ በመጫወት ላይ ናቸው።

በረኛው ጀማል ጣሰው ባለፈው ሁለት ቢጫ ካርድ በማየቱ  እዚህ ጨዋታ ላይ መሳተፍ አልቻለም። በመሆኑም ሲሳይ ባንጫ በረኛ ሆኖ ጨዋታው ቀጥሏል። የሴንትራል አፍሪካ አሰልጣኝ ከጨዋታው በፊት እንደተናገሩት፤ “እኛ የኢትዮጵያን ቡድን እናከብራለን። ሆኖም እኛ ያጣነው እድል ነው እንጂ፤ በጨዋታ እንበልጣለን” ብለው ነበር። በርግጥም አሁን እንደምናየው ከሆነ፤ አልፎ አልፎ ሲያጠቁ ይታያል። 25ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ ያለቀላት ኳስ ስቷል። ከሶስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሴንትራል አፍሪካ  ያለቀለት ኳስ ስቷል። ከአምስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሴንትራል አፍሪካ ሌላ እድል አግኝቶ፤ በኬታ አማካኝነት የመጀመሪያ ግብ ኢትዮጵያ ላይ ተቆጥሯል። ጥሩ ዜና አይደለም። ጨዋታው ከተጀመረ 30 ደቂቃ ተቆጥሯል።

32ኛው ደቂቃ ላይ ሴንትራል አፍሪካ እንደገና አጥቅቶ የሚገርም ሙከራ አድርጎ አዳናት። ልትገባ ያለቀላትን ኳስ ነው በእግሩ ጨርፎ አድኗታል። የኢትዮጵያ ቡድን ጨዋታ ብዙም የሚያመረቃ ሙከራ እያደረገ አይደለም። አጭር ቅብብል እያደረጉ ለማለፍ እየሞከሩ ነው ሆኖም  ቶሎ ቶሎ እየከሸፈባቸው ነው። በሌላ በኩል ደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና በሚያደርጉት ጨዋታ 0 -0 ናቸው።

አሁን36ኛው ደቂቃ ላይ… ደቡብ አፍሪካ 1 ጎል አግብታለች። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ… ደቡብ አፍሪካ አሸንፋ፤ ኢትዮጵያ ከተሸነፈች፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጉዳይ ኮንጎ ላይ ያበቃለታል ማለት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ በጨዋታም ቢሆን በልጠውናል። ቢሆንም ተስፋ ሳንቆርጥ እስከመጨረሻው እንቀጥላለን። የመጀመሪያው 45 ደቂቃ አብቅቶ እረፍት ወጥተዋል። ሴንትራል አፍሪካ 1- ኢትዮጵያ ዜሮ። በሌላ በኩል የደቡብ አፍሪካ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። ይህ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለናንተ መናገር አያስፈልግም።

ከእረፍት በኋላ እንደገና ማስተላለፋችንን እንቀጥላለን። ከ እረፍት በኋላ ተጠናክረው ካልገቡ በዚህ አይነት ሁኔታ የማሸነፍ እድላችን የመነመነ ነው።

አሁን እረፍት ወጥተው እያለ፤ አንዳንድ ነገሮች ለማለት አሰብን። ግን ምን ሊባል ይቻላል? ብዙም ጥሩ ጨዋታ አላየንም። አጭር ቅብብል ነው የሚያደርጉት፤ እሱንም ወዲያው እየተነጠቁ እድላቸውን ሲያጡ አይተናል። ቢያንስ ረዥም ኳስ በመጫወት የሚታወቀው ዳዊት እስጢፋኖስ አልገባም። ሌላኛው አጥቂ ጌታነህ ከበደም አልገባም። እንግዲህ ይሄ ሁሉ የአሰልጣኙ ውሳኔው ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም። ያለውን ነገር እንዳለ ተቀብለን፤ ጸሎት ጨምረንበት የሚቀጥለውን ጨዋታ እንከታተላለን።

ለማንኛውም አብራችሁን ቆዩ።

ከእረፍት  ተመልሰዋል። ኡመድ በበሃይሉ አሰፋ (ቱሳ) ተቀይሯል። ከ እረፍት በኋላ 2ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰይድ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። ቢያንስ በዚህ ሁኔታ ከቀጠልን እናልፍ ይሆናል። የኢትዮጵያ ተስፋ እንደገና ጨምሯል።

ከእረፍት በኋላ አሁንም ሴንትራል አፍሪካ  አልፎ አልፎ  ሲያጠቁ እያየን ነው።

ዘጠነኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሌላ ሙከራ አድርጎ ነበር። አሁን ከመጀመሪያው ይልቅ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረዋል። ሆኖም የሚያደርጉት አጭር ቅብብል ስለሆነ ኳስ እንደገና ስለሚነጠቁ፤ ደረጃውን ያልጠበቀ ጨዋታ እየተጫወቱ ናቸው። ጨዋታው ከተጀመረ 15 ደቂቃ ተቆጥሯል። ልክ አስራምስተኛው ደቂቃ ላይ ምንያህል ተሾመ ወሳኝ የሆነች በጣም አሪፍ ጎል አግብቷል። አሁን ኢትዮጵያ 2 – ሴንትራል አፍሪካ 1 ሆነዋል። የሚገርም ነው – ምንያህል ተሾመ የኢትዮጵያን ቡድን እንደገና ክሶታል። ባለፈው ሁለት ቢጫ በማየቱ እና ተመልሶ በመግባቱ ምክንያት ኢትዮጵያ አንድ ጨዋታ ሶስት ነጥብ የተቀሰ ባት መሆኑ ይታወሳል። እናም አሁን ሁለተኛ እና ወሳኟን ጎል በማስቆጠር የኢትዮጵያን ቡድን ክሷል።

አሁን ጨዋታው ሞቅ ማለት ጀምሯል። 2-1 ጨዋታው ከተጠናቀቀ ከምድቡ በ13 ነጥብ አንደኛ ሆነን በማለፍ፤ ከአስሩ የምድብ አሸናፊዎች አንዱ እንሆናለን። ከዚያም በእጣ ከሚደርሳቸው ቡድን ጋር በደርሶ መልስ የሚያደርጉት ጨዋታ ወሳኝ ይሆናል ማለት ነው።

ጨዋታው ከተጀመረ 23ኛ ደቂቃ ሆኗል። ሴንትራል አፍሪካ መልሰው ማጥቃት ስለጀመሩ ሁኔታው የሚያሰጋ እና የሚያጓጓ ሆኗል። የኢትዮጵያ ቡድን ቢያንስ ይሄንን ውጤት ይዞ ቢጨርስ፤ የማለፍ እድሉ የተረጋገጠ ይሆናል።

አሁን ጥሩ ጨዋታ እየተጫወቱ ናቸው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተረጋግቶ በቄንጥ እየተጫወተ ነው። ቄንጡ ቀርቶ ግን ጠንክረው ማጥቃቱን ቢቀጥሉ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል። ስቴዲየሙባዶ ነው ለማለት ይቻላል። ሆኖም ጥቂት ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ማልያ አድርገው ሲጨፍሩ ይታያሉ።

አሁን የኢትዮጵያ ቡድን ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወት ጀምረዋል። አሁን ገና መጫወት ጀመሩ። ባለፈው 15 ደቂቃ ውስጥ ያለቀላቸው ሁለት ግቦች ‘ኦፍ ሳይት’ ሆነውባቸዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 15 ደቂቃዎች ቀርተዋል። እነሱ በጨዋታ፤ እኛ በጸሎት ጭምር ጨዋታውን እየተከታተልን እንገኛለን።

ሴንትራል አፍሪካዎች ሲያጠቁ፤ ሲሳይ ባንጫ ላይ ጉዳት ስላደረሱበት በመውደቁ፤ ጨዋታው ለአንድ ደቂቃ ያህል ተቋርጦ ነበር።  አሁን ጨዋታው ከተጀመረ በኋላ ደግሞ ሽመልስ ተጎድቶ ወጥቷል። ብርሃኑ ቦጋለ (ፋቲጋ) ሊገባ እያሟሟቀ ነው። ብርሃኑ ፋቲጋ በፈጣን ሩጫ እና አክርሮ በመምታት የሚታወቅ ተጫዋች ነው።

ሲሳይ ባንጫ ለኢትዮጵያ ቡድን ባለውለታ እየሆነ ነው። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የሚገርሙ ኳሶችን አድኗል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂቅ ደቂቃዎች ቀርተው፤ የማዕዘን ምት ባገኘንበት ሁኔታ ላይ እያለን… ረብሻ ቢጤ ተነስቶ ነበር። ኢትዮጵያውያኑ የማዕዘን ቅጣት ምቱን እየተቀባበሉ ጊዜ ለማባከን እየሞከሩ ናቸው። ሴንትራል አፍሪካዎች ተናደው የኢትዮጵያ ቡድን ተጫዋቾችን ሲጎነትሏውቸው ይታያል። ሴንትራል የሴንትራል አፍሪካው 15 ቁጥር ቢጫይቷል።

በመጨረሻም ጨዋታው ተጠናቀቀ። የኢትዮጵያ ቡድን ከአስሩ ቡድኖች አንዱ መሆኑ ተረጋገጠ። ኢትዮጵያ 2-1 አሸነፈች። በ13 ነጥብ ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ተሸጋግረናል። ደስ ብሎናል ደስ ይበላቹህ!!

በየቦታው ጨዋታው ካለቀ በኋላ ጭፈራው እና ሆታው ቀጥሏል። እናመሰግናለን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን።

Ethiopian-National-Team

 

 

 

 

 

 

 

 

 

እኛ በጋዜጠኛነታችን ጨዋታውን ዘገብን። ህዝቡ  በጭፈራ ደስታውን ገለጸ፤ ድምጻውያን በድምጻቸው፣ ገጣምያን በግጥም ችሎታቸው ስሜታቸውን አስተጋቡ። እነሆ በዘገባችን መጨረሻ ላይ የገጣሚ መንግስቱ ዘገየን ግጥም ልናካፍላቹህ ወደድን።

እግር ታሪክ ሰራ
ይህ ዋልያ ማለት
መለዮ ቀለሙ ቀንዱ የገነነ
በሰሜን ተራራ ባገሬ ኮረብታ እንደተጀነነ
ዛሬ ታሪክ ሰራ ትልቅ ታሪክ ሆነ፡፡
ተምሮ ነበረ
ተነግሮት ነበረ
አያት ቅድመ አያቱ ታምር እንደሰሩ
ዋሻዉን በእጃቸዉ እየቦረቦሩ
ጭንጫ መረሬዉን እየመነሸሩ
በምትሀት ጣታቸዉ
በጠቢብ እጃቸዉ ህያዉ ስም ተከሉ፡፡
ይህን ያየዉ ጎበዝ
ባዲስ ታሪክ መጣ ተአምሩን ገለጠ
በእጅ የሰሩት ቀርቶ የእግራችን በለጠ፡፡
በዚች ቅድስት ሀገር በዚች ያምላክ ስፍራ
በጳጉሚት ጉባኤ በአዲስ ዘመን ጮራ
በአበሻ እንቁጣጣሽ ባሲሞይ ጭፈራ
እግር ተሞሸረ እግር ታሪክ ሰራ፡፡
(ከመንግስቱ ዘገየ ጳጉሜ 2 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰአት ዉዳሴሃ ለፋኖ ዋሊያ)
Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 7, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.

One Response to የኢትዮጵያ እና ሴንትራል አፍሪካ ጨዋታ ቀጥታ ስርጭት ( ኢትዮጵያ 2 – ሴንትራል አፍሪካ 1) ኢትዮጵያ አሸነፈች!!

  1. AleQa Biru

    September 7, 2013 at 11:15 AM

    “መካከለኛው አፍሪካ” ማለት አይቻልም እንዴ?