የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽንን ለዲያስፖራው ለመሸጥ ስለወጣው ማስታወቂያ አንዳንድ አመላካች ሀሳቦች

ከፕ/ር ሰይድ ሀሳን (March 25, 2009)  በቅርቡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ከኢትዮጵያ መንግሥትና የንግድ ባንኩ ጋር በመተባበር የዲያስፖራውን የሕብረተሰብ በቻ የሚያሳትፍ የቦንድ ሽያጭ አቅርቧል። የዚች አጭር ጽሁፍ አላማ ለሽያጭ በቀረበው ማስታወቂያ አንዳንድ አመልካች ሀሳቦች ለማቅረብና የኢትዮጵያ መንግሥትና የኤለክትሪኩ ኮርፖሬሽን በሙስና የተዘፈቁባቸውን አንዳንድ ሁኒታዎችን ለማሳየት ነው።

የቦንድን ጥቅም ባጭሩ ለማለት ያህል፤ “ቦንድ” ማለት ባጭሩ አንድ ሰው ለኩባንያም ሆነ ለመንግሥት ገንዘብ አበደሮ አስቀድሞ በተወሰነ ወለድ የወደፊት ገቢን ማግኘት ማለት ነው። የቦንድ አይነቶች ሊለያዩ ቢችሉም፤ አሁን የኤትዮጵያ ኤለክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ውጭ አገር ለሚኖርት ኢትዮጵያዊን ለመሼጥ ያቀረበው የሚለነም ቦንድ በጣም ቀለል ያለው (simple bond) ነው፡፡ ኩባንያው ለገባያ ያቀረባቸው በ 5፣ 7 እና 10 እመታት የመክፈያ እድሜ ገድብ የሚለዩ ሲሆን፤ እነዚህም ቦንዶች እያንዳንዳቸው 4%፣ 4.5% እና 5% ወለድ በያመቱ ይከፍላሉ ተብሏል።

የቦንድ መግዛት ጥቅሙ በምን ይመዘናል? የሚለነም ቦንዱ ጥቅምስ እንዴት ይመስላል?

ቦንድን በመግዛት የሚገኙት ጥቅሞችና ጉዳቶች የተለያዩ ቢሆንም ቢያንስ የሚከተሉትን ጉዳዮች መጥቀስ ይቻላል። አንዱ የቦንድ መመዘኛ፤ ቦንዱ የሚከፍለው ወለድ ከሌሎቹ አማራጭ የገንዝብ ማግኛ መንገዶች ጋር ሲወዳደር ነው። በዚህ ረገድ የኢትይጵያ መንግሥት ለዲያስፖራው ሕብረተሰብ ለመሸጥ ያወጣው የሚለነም ቦንድ የሚከፍለው ወለድ በጣም ትንሽ ነው። ለምሳሌ የዚች አጭር ጽሁፍ አዘጋጅ ድሕረ-ገጾችን ዞር-ዞር ብሎ ሲቃኝ የሚከተሉትን ማስረጃዎች አግኝቷል። ከነዚህም ምሳሌዎች መካከል ለመጥቀስ ያህል፤ ባለፈው ወር የኢንዶኔዥያ (Indonesia) መንግሥት ለ10 አመቱ ቦንድ በዓመት 11.75% ሲከፍል፤ የቬትናምና የፊሊፒንስ መግንሥታት ደግሞ የ10 ዓመቱ ቦንዳቸው አሥር በሞቶ (10.5%) ይከፍላሉ። በአሜሪካም አንዳንድ ኩባንያዎች ለምሳሌ እንደ ቨራይዘን የተባለው የሞባይል ተሌፎን ኩባንያ እስከ 8.4% ወለድ በየአመቱ እንደሚከፍል በድሕረ-ገጾች ላይ ማየት ችያለሁ። TIAA-CREF ተብሎ የሚጠራውና በትምህርትና በሆስፒታል ተቋማት በሥራ ላይ ለተሰማሩ የአሜሪክ ሕብረተሰብ የመጦሪያ ገንዘብ ማስቀመጫ ኩባንያ እንድሚያመልክተው ደግሞ ለአለፉት 10 አመታት ገንዘባቸውን በቦንድ መልክ ያስቀመጡ ሰዎች እስከ 6.25% በመቶ ያህል ወለድ ተክፍሏቸዋል። ይህ ወለድ ደግሞ ከገንዘብ ግሽበት ነጻ የሆነ ነው! ከዋጋ ግሽበት ነጻ ያልሆነው- እንደ ሚለነሙ ቦንድ ያለው ደግሞ እስከ 9% ያህል ወለድ ከፍሏል ይላል።

በሌላ በኩል ደግሞ እኔ በምኖርበት አካባቢ አንዳንድ ባንኮች ከ4.25% እስከ 5.75% ወለድ ድረስ የሚከፍሉ አሉ። ይህንን የሲ.ዲ. ገባያ ለመጠቀም የሚፈልግ ግለሰብ 20 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ የሲዲውን ኮንትራት መግዛት ይችላል። ሙኒሲፓል ቦንድስ የሚባሉት አንዳንዶቹ እስከ 6% ሲከፍሉ ቦንዱን የሚገዛው ባለሃብት ታክስ ከመክፈል ነጻ ነው። እንደነዚህ ያሉትንና የአሜሪካ መንግሥት የሚሸጣቸውን ቦንዶች ለመግዛት የሚያስብ ግለሰብ ከኮምፒተሩ ፊት-ለፊት ሆኖ ማድረግ ይችላል። በአኳያው ግን የሚለነም ቦንዱ ብዙ ጣጣ ይኖርበታል። ልምሳሌም በማስታወቂያው ላይ ግልጽ እንደሆነው 1ኛ) ቦንዱን የሚገዛው ሰው፤ ገንዘቡን ለመላክ የመላኪያ ገንዘብ ይከፈላል። 2ኛ) ወደተፈለገው ቦታ ለመድረሰ ብዙ መጓዝን የሚጠይቅ ይሆናል። ምናልባት ተሳስተው የሚለነው ቦንዱን የሚገዙ አንዳንድ የዲያስፖራ አባላትም ይህንን “ገባያ” ምክንያት አድርገው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚንሴራሸሩም አንድ ሰው ሊግምት ይችላል። ምናልባት ይህንን የቦንድ ሽያጭ ዘዴ የጠነሰሱት ግለሰቦች ይህንን ለኢትዮጵያ የውጭ አገር ምንዛሬ ማመንጫ እንድሆን አስበው ይሆን?

በሁለተኛ ደረጃ የማስቀምጠው የቦንድ መመዘኛ የቦንድ ሻጩ ኩባንያ እዳውን ለመክፈል የሚኖረው ችሎታ ነው። ተበዳሪው ኩባንያ ውይም መንግሥት ከስሮ ድምጥማጡ ይጠፋል ተብሎ የተገመተ ከሆነ ተበዳሬው የሚከፍለው ወለድ ከፍ ማለት አለበት። የኢትዮጵያ ኤለክትሪክ ኩባንያ እና የመለስ ዘንዊ መንግሥት በሙስና የተጠመዱ ስለሆነ እዳውን መከፈላቸው ቀርቶ እንዳዉም የአቶ መለስ መንግሥት በሥልጣን ላይ የመቆየቱ ሁኔታ አጠራጣሪ ስለሆነ ቦንዱን የሚገዙ ሰዎች ገንዘባቸውን እንደ መጣል ያህል ሊቆጠር ይችላል።

በሌላ በኩል ደግሞ፤ ለሽያጭ የቀረበው የሚለነም ቦንድ በገለተኛ ድርጅቶች አልተመረመረም/አልተመዘነም። ለምሳሌ እዚህ እኔ እምኖርበት አገር አሜሪካ እና እንደ አውሮፓ ባሉት አህጉራት ቦንድ የሚሼጡትን ኩባንያዎችና መንግሥታት ቦንዳቸውን የሚመጥን ሁኔታም ይደረጋል። ለምሳሌ Standard and Poors እና Moody የሚባሉት የቦንድ ጥንካሬን መጣኞች ቦንዶችን በብዙ መልክ ያስቀምጣሉ (ለምሳሌ ይህን ድሕረ-ገጽ ይመልከቱ፡ http://en.wikipedia.org/wiki/Bond_credit_rating)። ከላይ እንዳልኩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን ያዘጋጀው ቦንድ 1ኛ) ያልተመረመረና ያልተመጠነ ስለሆነ፤ 2ኛ) ኩባንያውና የኢትዮጵያ መንግሥት በሙስና ላይ የተዘፈቁ ስለሆኑ፤ ይህ የሚለነም ቦንድ ምንነቱ የማይታወቅ ከመሆኑም ሌላ ኪሳራንም ያስከትላል ብሎ መገመት ይቻላል። ስለዚህም የሚለነም ቦንዱ “ጃንክ ቦንድስ” ተብለው ከሚሰየሙት ጋር ይዛመዳል።

ስለሆነም የሚከፍለው ወለድ በጣም፤በጣም፤ ከፍ ማለት አለበት! በሦስተኛ ደረጃ የማስቀምጠው የቦንድ መመዘኛ አሁን እና ወደፊት የሚኖረው/የሚከሰተው የዋጋ ግሽበት ነው። በቅርቡ የወጡት መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ በዚህ ዓመት (በፈረንጅ አቆጣጠር) በኢትዮጵያ የሚገኘው አጠቃላይ ግሽበት ወደ 45.6% ደርሷል። የእህል እና የጥራጥሬ ዋጋዎች ደግሞ በሚያሰጋ መልክ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በ104.1% ያህል ጨምረዋል። ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን እያሽመደመደ ያለውን አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት (45.6%) ተገድፈን ስንመለከተው፤ አበዳሬዎች ገንዘባቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠቀሙበት ከሆነ የገንዘባቸው ወለድ ወደ እነሱ ኪስ ሲገባ እቃወች የመግዛት አቅሙ በ45.6% ይቀንሳል ማለት ነው። ግሽበቱን ስንቀንስበት (- 42% = 4%- 46%) እውነተኛው ወለድ የአሉታ/ሴቴ (በእንግሊዝኛው negative 42%) ይሆናል ማለት ነው:: ይህንን በቀላሉ ለማስቀመጥ ያህል እኔ የ4 ዓመቱን ቦንድ የገዛሁ ከሆነ እኔ ቦንዱን ለምግዛት የኢትዮጵያ መንግሥት እድሉን ስለሰጠኝ ለኤሌክትሪክ ኩባንያው (ለመለስ ዘናዊ መንግሥት) 42% ያህሉን ገንዘቤን መክፈል አለብኝ ማለት ነው! ይህ የሚያሳየው የነአቶ መለስ ቡድን ለዲያስፖራው ያላቸውን ንቀት ነው። እኔ ግን አበዳሪዎች ተላላ እና ሞኝ ናቸው ብየ ስለማላስብ ይህ የማታለል ተግባር አይሳካም ብየ እገምታለሁ። ከላይ እንደጠቀስኩትም የኢትዮጵያ መንግሥትና የኤሌክትሪክ ኩባንያው በሙስና የተዘፈቁ ስለሆነ እንዳውም ይህንን ያወቁ የዲያስፖራ ሕብረተሰብ አባላት ዋናውን ገንዘባቸውን የሚያጡ መሆናቸውን አውቀው እነ አቶ መለስን “እምቢየው፤ አልሰጥም፤ አላበድርም” ይላሉ ብየ እገምታለሁ። የአለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ወርቁን ሼጦ ካላበደረን “የተጨናገፉ መንግሥቶች” እንሆናለን! የአቶ መለስ ዘናዊ መንግሥት የውጭ ምንዛሬው እጥረት ወጥሮ ስለያዘው፤ ይህንኑ እጥረት ገሸሽ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ ያለም አይመስልም። የቦንድ ሽያጩም አንዱ የዚሁ መፍትሄ መሆኑ ነው። በዚህም የውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ አቶ መለስ የአለም የገንዘብ ድርጅትን ለምነው አንድ አምሳ ሚሊዮ ዶላር ብድር በቅርቡ ወስደዋል።

ይህም አልበቃ ብሏቸው አቶ መለስ ዘናዊ እየተመላለሱ የሚነግሩን ነገር አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ከአለም እርዳታ ካላገኙ “የተጨናገፉ መንግሥቶች” (failed states) እንደሚሆኑ ነው። ይህንን ጉዳይ አቶ መለሰ የአፍሪካ መሪዎች በቅርቡ በአዲስ አበባ በተሰበሰቡበት ጊዜም አሁን ስሞኑን ድግሞ በሎንዶን ከተማ ተገኝተው ህብታም አገሮች ለአፍሪካ አገሮች እርዳታ ካላደረጉ በርከት ያሉ የአፍሪካ አገሮች “የተጨናገፉ መንግሥታት” ይሆናሉ ይሉናል። “የተጨናገፉ መንግሥቶች” (failed states) የሚለውን በሚመለከት በረንጅ ከሁለት አመታት በፊት “ፎረኝ ፖሊሲ” የሚባለው ታዋቂ መጽሄት ኢትዮጵያን አንዷ “የተጨናገፈች አገር” – መንግሥቱም “የተጨናገፈ መንግሥት” ነው ብሎ ሰይሟቸው ነበር። አሁን አቶ መለስ ዘናዊ ይህ ጉዳይ ለምን እንደታያቸው አልገባኝም። በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ገበሬ ሀብታም ሆኗል ብለው ይነግሩናል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በሳራጩት ቪዲዮ፤ በግብርናው መስክ የተገኘው የኤኮኖሚ ድል ከፍተኛ ስለሆነ ከአዎሮፓው “ትንሳኤ” ወይም በእንግሊዝኛው “Renaissance” ተብሎ ይሚጠራ ከነበረው ጥሩ ታሪክ ጋር የሚወዳደር ስለሆነ ኢትዮጵያን በቅርቡ “መለስተኛ ሀብታም” ተብለው ከሚጠሩት አገሮች ጋር ልትመደብ ትችላለች ብለው ነግረውን ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱ በውጭ ምንዛሬ ማነስና ችግር ላይ ስለሆነች አቶ መለስ ከአለም የገንዘብ ድርጅት ለመግሥታቸው ጊዜአዊ ድጎማ አድርጎላቸዋል። ይህ አልባቃ ብሎ አሁን ደግሞ ሀብታም አገሮች ብድሩን መለግስ ካልቻሉ “የተጨናገፍን መንግሥታት እንሆናለን” ፤ በችግሩ የተነሳም “ሕዝባዊ ብጥብጥ ሊነሳ ይችላል” ይሉናል። ይህ የተጨናገፉ መንግሥታት/አገሮች የሚባለው አስተሳሰብ ለአቶ መለስ አሁን ለምን ትዝ አላቸው? አለም ያወቀውን ኢትዮጵያ የተጨናገፈች አገር መሆኗን ሊያበስሩን ነው? ወይስ አሁን ይህ ለሳቸው ታይቷቸው ስለሆነ መግሥታቸው ተጨናግፎ ከወደቀ የራሳቸውን የመሪነት ጉድለት/ውድቀት ለሀብታም አገሮች ለማሟከክ ነው? ለመሆኑሟ እንደዚህ ያለው የማሟከክ ተግባር ለአቶ መለስ ዘንዊ አዲስ ነገር አይደለም።

ካሁን በፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ በርሀብ ላይ ሲወድቅ የአለም ሕብረተሰብ እርዳታውን በቶሎ ወደ ኢትዮጵያ መላክ ካልቻለ ሀላፊነቱ የሳቸው መንግሥት ሳይሆን የአለም ሕበረተሰብ ነው ብለውን የለ? አቶ መለስ የአለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) ለአፍሪካ አገሮች ገንዘብ ለማበደር በካዝናው ያለው ሀብት በቂ ካልሆነ “ወርቁን” ይሽጥ ብለው ደጋግመው ተናግረዋል። ትእዛዝም አስተላልፈዋል። ነገር ግን ማንም የነዚህን ሁለት ድርጅቶችን – ተበዳሪ አገሮችን በማንገላታት የታወቁ ድርጅቶችን- ጠባይ የሚያውቅ ግለሰብ እንደሚረዳው፤ ይህ ለነዚህ ድርጅቶች ከአቶ መለስ ዘንዊ የተላለፈ ትእዛዝ ዋጋ-ቢስ ከመሆኑም በላይ ለፖለቲካ ጥቅም እንዲያገለግል ተብሎ የተደረገ መሆኑን ይገነዘባል። አቶ መለስ ዘናዊ የአለም የገንዘብ ድርጅትንና የአለም ባንክን ለብደር ልመና በሮቻቸውን በየእለቱ የሚያንኳኩ ስለሆነም አቶ መለስ ይህ ጠፍቷቸው አይደለም።

አለም እንደሚያውቀው ደግሞ የተበዳሪ አገሮች ኤኮኖሚዎች ችግር ሲያጋጥማቸው፤ የእነዚህ አበዳሪ ድርጅቶች ላማቸው ወልዳ ብዙ ወተትን ታፈራለች። ይህ ወተት የሚተመነውም በአራጣ መልክ በሚገኘው የወለድ ገንዘብና፤ አራጣውን በመግፋት በሚፈጠረው ሥራ፤ እንድሁም በተበዳሪ አገሮች ላይ ጫና በማድረግ መልክ የሚከሰተው የሀይል ሚዛን ነው። የእነዚህ ድርጅቶች ካዝና የሚቀንሰው የድሃ አገሮች ኤኮኖሚዎች በጥሩ ሁኔታ ሲገኙ መሆኑንና ተበዳሪነት ሲቀንስ መሆኑም ብዙ ታዛቢዎች በተለያዩ ጊዚያት አቅረበውታል። ለምሳሌ በፈርንጅ አቆጣተር በኤፕሪል 21 ቀን 2006 ዓ.ም. በ“ወል ስትሪት ጆርናል” የዘገበውን መጥቀስ ይቻላል።

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽንና የግልገል ግቢው ቅሌት

የኢትዮጵያን የኤለክትሪክ ኩባንያን እና መንግሥቱ የሚያድርጉትን ውንጀሎች “የግልገል ግቢ ቅሌት” ወይም በእንግሊዝኛው “THE GILGEL GIBE AFFAIR” በሚል እርዕስ በድሕረ-ገጽ የወጣውን በሚመለከት ለአንባቢያን ባጭሩ ለማቅረብ ያህል፤

1. በተከዜ ወንዝ ላይ የተተከለው የኤለክትሪክ ሀይል ማመንጫ ወደ $450.00 ሚሊዮን ዶላር ከባከነበት በኋላ ዋጋ-ቢስ መሆኑን አሁን አቶ መለስ ዘናዊ እራሳቸው በቅርቡ በሰጡት ጋዜታው መግለጫ አምነዋል። ይህ የሚያሳየው፤ የተከዜው የመበራት ሀይል ማመንጫ የተሰራው ለኤኮኖሚያዊ ጥቅም ሳይሆን፤ የትግራይ ሕዝብን ቀልብ ለመሳብ ተብሎ ለፖለቲካ ጥቅም የተሠራ መሆኑን ነው። እንድግዲህ የአቶ መለስ ዘናዊ መንግሥት በአንድ በኩል የደሃ አገራችንን ገንዘብ እያባከነ ሲገኝ፤ በሌላ በኩል ድግሞ ተጠቃሚ ያልሆነውን የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ እንደሚንሆን ሲያታልለ እስከ መቸ ድረስ እንደሚኖር አይገባኝም!

2) በግልገል ግቢ 1፣ 2 አና 3 የተሰሩትን የመብራት ኃይል ማመንጫዎች ስንመለከት ሁልቆ መሳፍርት የሆኑ ወንጀሎችና የሀብት ክስረቶች ደርሰዋል/እየደረሱ ይገኛሉ። ይኸው በቅርቡ “የግልገል ጊቢ ቅሌት” በሚል እረዕስ የወጣው ጥናት እንዳመለከትው (ባጭሩ)፤

ሀ) እነዚህ የሀይል ማመንጫወች እንደነ የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ኮንትራቱ ሲስጣቸው፤ ሕገ-ወጥ በሆነና በተጣደፈ መልክ ስለነበር፤ ብዙ የመካሰስ ተግብሮች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በርከት ያሉ ታዛቢዎች እንደጠቆሙት ከሆነ፤ ኮንትራቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ባለሥልጣኖች ሕገ-ወጥ በሆነ መልክ እንዲደረግ ያደረጉበት ምክንያት የግል ጥቅምን ለማድረግ እንዲመቻቸው ይሆናል። እነዚህም የሃይል ማመንጫዎች (በተለይ 3ኛው ግልገል ግቢ) ሕገ-ወጥ በሆነ መልክ ስለተሠሩ/እየተሰሩ ስለሆነ የአለም ባንክና የአውሮፓ የመዋዕለ-ነዋይ ባንክ እነዚህን ተቋሞች ለመገንባት ገንዘብ አናበደርም እስከማለት ደርሰዋል።

ለ) እንደ ተከዜው የሀይል ማመንጫ ሁሉ እነዚህ የኃይል ማመንጫዎች ከሠሯቸው ወንጀሎች መካከልም፤ 1) በቂ ጥናት ሳይደረግ – በለይ የገቢና ወጭ አንዲሁም የወደፊት ጥቅማቸው ሳይሰላ፤ በአካባቢ መበከል የሚደረሰ ጉዳት ሳይመዘን፤ወ.ዘ. ተ.- ግንባታው እንዲደረግ ማድረጋቸው፤ 2) በጉዳዩ ሕዝቡ እንዳያውቅና እንዳይሳተፍ ማድረጋቸው፤ የሚሰሩት ወንጀሎች ሲታወቁና በጋዜጣዎች ሲወጡ በሕገ-ወጥ መልክ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳያውቅ አፈና መደረጉ፤ 3) በወንዞቹ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ሲፈናቀሉ አስፈላጊው የሰፈራ ቦታ ስላልተደረገላቸው፤ በቂ ከፍያም ስላልተደረገላቸው፤ በዚህ የተነሳ የመጣው/እየመጣ ያለው ብጥብጥ፤ 4) እንደ ኬንያ ካሉት ከጎረቤት አገሮች ጋር የመጣው ጭቅጭቅና አለመስማማት፤ 5) የመገንቢያው/የመሥሪያው ብድር መገኘቱ ሳይረጋገጥና ማን አበዳሪ እንደሚሆን ሳይታወቅ ግንባታወቹ መጀመራቸውና በዚህም የተነሳ የገንዘብ እርዳታው ካቆመ ግንባታው ብዙ ገንዘብ ከፈሰሰበት በኋላ ቆሞ ሊቀር እንደሚችልና የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ከሁሉም የበለጠ በጣም ከሚያናድደው አንዱ “3ኛው ግልገል ግቢ” የሚባለው በባሮ ወንዝ አካባቢ አንድ ሽህ አራት መቶ ሚሊዮን ዩሮ (ማለት ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ) ፈጅቶ በመሠራት ላይ ያለው የኃይል ማመንጫ፤ በአንድ በኩል፤ አንዲም ለኢትዮጵያ መንደርተኛ/የከተማ ኗሪ የመብራት ሀይሉ ተጠቃሚ እንደማይሆን እየታወቀ ግንባታው መቀጠሉ ነው። ግልገል ግቢ 3 የተሠራው መብራቱን ለኬንያ ለመሸጥ ስለሆነ፤ ኬንያዊያን በመብራቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድሀ አገራችን ኢትዮጵያ ከውጭ አገር ተበድራ ለኬንያዊያን መዋዕለ-ነዋይ አደረገች ማለት ነው። በእውነቱ፤ በትክክል ለማስቀመጥ ያህል፤ 3ኛው ግልገል ግቢ የተሠራው ለኬንያዊያን ስለሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪዎችን የእኛን ገንዘብ እንዲታባክኑ በኬንያዊያን ተቀጥራችኋልን? ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ እነ አቶ መለስን መጠየቅ ይኖርበታል ባይ ነኝ።

በሁለተኛና አሳዛኝ በሆነው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፤ ኬንያዊያን የግልገል ግቢ 3ትን የውሀ ገድብና የተሠራውን የኀይል ማመኝጫ አሁን እየተቃውሙትና ብጥብጥ እየጫሩ መሆናቸው ነው። እንዲ ከሆነም፤ ኬንያዊያን እንደተጠበቀው መብራቱን “አንገዛም” ሊሉ ይችላሉ ማለት ነው። እንምቢ ካሉም፤ ገንዘቡ (ከ20 ቢሊዮን ብር የማያንሰው ገንዘብ) ባክኖ ቀረ ማለት ነው! 3ኛ) አሁን የተደረሰባቸው ጥናቶች እንዳመለከቱት፤ የ3ኛው ግልገል ግቢ ፕሮጀክት በርካታ የሆኑ የዱር አራዊቶችን የሚጨርስ፤ ይህ ነው የማይባል የአካባቢ ብክለትንም የሚያስከትል መሆኑ ነው። ይህ ከሆነም የአለም ሕዝብ የሚደርሰውን ጉዳት ስለሚቃወመው በዚህ ጉዳይ ላይ የፈሰሰው ገንዝብ ባክኖ ሊቀር ይችላል ማለት ነው።

እንግዲህ፤ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ እንደዚህ ያሉትን ሥህተቶች የሚሠሩ ከሆነ፤ ግንባታውንም ሕገ-ወጥ በሆነና ያለ ጨረታ ለፈለጉት – እንደነ ሳሊኒ ያሉት ኩባንያ በችኮላ የሚሰጡ ከሆነ፤ ብዙ ጥርጣሬዎች ላይ እንድንወድቅ ያስገደደናል። እንደዚህ ባሉት ሙስናዎች የተዘፈቀውን የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽን የሚለነም ቦንድ የሚገዙ ሰዎችም ለሙስናው በተዘዋዋሪ ተባባሪ ይሆናሉ ማለት ነው።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 29, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.