የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪቃ (ዝርዝር ዘገባ)

(ኢ.ኤም.ኤፍ) በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 አመታት በኋላ የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያን በማለፍ፤ ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ደቡብ አፍሪቃ ገብቷል። በርካታ ተጫዋቾች ከደቡብ አፍሪቃ ሆነው ከሸገር ሬዲዮ ጋር በቀጥታ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ለማሸነፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን… ነገር ግን ያረፉበት ሆቴል ወይም በአካባቢው የሚፈልጉት አይነት ምግብ ቀርቶ መደበኛውን ምግብ ያለማግኘታቸውን ሲገልጹ ነበር። የፊት አጥቂ የሆነው አዳነ ግርማም በአድማስ ሬዲዮ ላይ ቀርቦ፤ ከምድቡ በተሻለ ውጤት እንደሚያልፉ ተናግሯል።
South-Africa-2013-Ethiopia

(Picture: Excitement and jubilation as Ethiopian in South Africa received delivery of the original national flag.)

ከአገራችን ሚዲያዎች በተጨማሪ ካሁኑ እንደ ቢቢሲ እና ሲ.ኤን.ኤን. ያሉ ትላልቅ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ ቡድን አንዳንድ ነገር ማለታቸው አልቀረም። የስፖርት ዜና ሽፋን የማግኘታቸው አንዱ ምክንያት ደግሞ፤ በኢትዮጵያ ቡድን ውስጥ አለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ተጫዋቾች መኖራቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። በርግጥም 23 ተጫዋቾችን ያካተተው የኢትዮጵያ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚጫወቱ ኢትዮጵያዊያንን ይዟል።

እነዚህ ሶስት አይን የተጣለባቸው ወጣቶች፣ ሳላዲን፣ ዩሱፍ እና ፉአድ ናቸው። ሳላዲን ሰኢድ ከቤንሻንጉል የተገኘ ወጣት አጥቂ ነው። ለግብፅ ቡድን እየተከፈለው የሚጫወት ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ የተገዛ ተጫዋች ነው። ሳላዲን በርካታዎቹን ግቦች ለኢትዮጵያ በማስቆጠር ብሄራዊ ቡድኑ አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ያደረገ ባለውለታ ነው።

ሌላኛው ዩሱፍ ሳላህ ይባላል። ዩሱፍ ሳላህ ደግሞ ለስዊድኑ ሲሪያንስካ በግራ ክንፍ በኩል የሚጫወት፤ አንዳንዴ ኳስ እግሩ ከገባ ወደ አስደናቂ ግቦች የሚቀይር የ29 አመት ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው። ሌላኛው በመሃል አከፋፋይ ሆኖ በመጫወት የሚታወቀው፤ አሁን ደግሞ በአጥቂ መስመር የተመደበው ፉአድ ኢብራሂም ነው። ፉአድ የተወለደው ድሬዳዋ ከተማ ሲሆን፤ የስምንት አመት ወጣት ሳለ ነው ወደ አሜሪካ የመጣው። ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ኦሮምኛ እና ሱማልኛ ቋንቋ በትንሹ ያውቃል። ለአሜሪካ ወጣት ቡድን ተመርጦ ሲጫወት በእድሜ ትንሹ ልጅ ነበር። የ16 አመት ወጣት ነበር በወቅቱ። ከዚያ በኋላ ለቶሮንቶ ከዚያም ለሜንሶታ ስታርስ ቡድን ይጫወታል። የመጨረሻ ስሙን ኢብራሂም በማሳጠር ብዙዎች “ኢቢ” ብለው ይጠሩታል። ዛሬ የአየር ሽፋን አግኝቶ በሲ.ኤን.ኤን ቴሌቪዥን ላይ ሲቀርብም፤ “ኢቢ” እያሉ ነበር የጠሩት። ፉአድ ኢብራሂም በዛሬው የሲ.ኤን.ኤን ቃለ መጠይቅ፤ “አሁን ጊዜው ለአገሬ የምጫወትበት ነው። ለተወለድኩባት አገሬ!” ብሏል።

Go_Ethiopia2

እንግዲህ ሶስቱን ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ጨምሮ የኢትዮጵያ ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ አምርቷል። ከመሄዳቸው በፊት ተደርጎ በነበረው የ እራት ግብዣም ላይ ሼኽ መሃመድ አላሙዲን ተገኝተው ለቡድኑ የአስር ሚሊዮን ብር ሽልማት ሰጥዋል። በደቡብ አፍሪቃ የሚደረገው ጨዋታ የመክፈቻ ዝግጅት ቅዳሜ፣ ጃኑዋሪ 19 ቀን ተጀሯል።። አሰላለፋቸውን ገና አላወቅንም። ሆኖም የኢትዮጵያን ቡድን ወክለው የሚጫወቱት ተጫዋቾች ስም ዝርዝር እና የሚሰለፉበት ቦታ ከዚህ የሚከተለው ነው።

የተመረጡት በረኞች… ጀማል ጣሰው (ከቡና)፣ ሲሳይ ባንቻ (ደደቢት)፣ ዘሪሁን ታደለ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ናቸው።
ተከላካዮች ስዩም ተስፋዬ፣ አሉላ ግርማ፣ አይናለም ሃይሉ፣ ደጉ ደበበ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ አበባው ቡጣቆ እና ብርሃኑ ቦጋለ ሆነው ተመርጠዋል።
መሃል አከፋፋዮች በሃይሉ አሰፋ፣ አዲስ ህንጻ፣ አስራት መገርሳ፣ ያሬድ ዝናቡ፣ ዳዊት እስጢፋኖስ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ምንያህል ተሾመ እና ከስዊድን አገር የመጣው ዩሱፍ ሳላህ ይገኙበታል።
በአጥቂ መስመር ላይ… ኡመድ ኡክሪ፣ አዳነ ግርማ፣ ጌታነህ ከበደ፣ ለግብፅ ቡድን የሚጫወተው ሳላዲን ሰይድ እና በአሜሪካ ለሜኒሶታ ስታርስ የሚጫወተው ፉአድ ኢብራሂም ይገኛሉ።

በዘንድሮው 29ኛ የአፍሪካ ዋንጫ፤ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ጨዋታ በቦምቤላ ስቴዲየም ጃኑዋሪ 21 በአሜሪካ ኢስተርን ታይም በ10:00 AM ET ከዛምቢያ ጋር ታደርጋለች።
ሁለተኛው ጨዋታ የሚሆነው ከቡርኪና ፋሶ ጋር ነው። ጃኑዋሪ 25 ቀን በአሜሪካ ኢስተርን ሰአት 1:00 PM ከሰአት በኋላ ይከናወናል። የምድቡ የመጨረሻው ጨዋታ ጃኑዋሪ 29 ከናይጄሪያ ጋር በ12:00 PM ይሆናል። እንዲህ እንዲህ እያልን መጨረሻ ከደረስን፤ ፌብሩዋሪ 10 ቀን የዋንጫ ጨዋታ ይሆናል።

በነገርዎ ላይ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ከዛምቢያ እና ከናይጄሪያ ጋር ስትመደብ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። ከ31 አመት በፊት…” እየተባለ ብዙ በሚነገርለት የ1982ቱ ጨዋታ ላይ ከነዚህ ቡድኖች ጋር ነበር የተመደበችው። 31 አመት ወደኋላ እንመልሳችሁ።

ከ31 አመታት በፊት ቤንጋዚ፣ ሊቢያ ላይ በተደረገው ምድብ ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ናይጄርያ፣ ዛምቢያ እና አልጄርያ አንድ ምድብ ውስጥ ነበሩ። ይህም ማለት ከቡኪና ፋሶ በቀር ሁሉም ቡድኖች ከ31 አመት በኋላ እንደገና ተገናኝተዋል ማለት ነው። ወደኋላ ተመልሰን በወቅቱ የነበረውን ጨዋታ ስንመለከት፤ በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ በናይጄርያ እና በዛምቢያ ስትሸነፍ ከአልጄርያ ጋር ዜሮ ለዜሮ ወጥታለች። በወቅቱ ዛምቢያ ኢትዮጵያን 1-0፤ ናይጄሪያ ደግሞ 3-0 ነበር ያሸነፈችው። በሌላ ግጥሚያ ዛምቢያ ናይጄሪያን 3-0 በማሸነፏ… ናይጄርያ እና ኢትዮጵያ 3ኛ እና 4ኛ ወጥተው ከምድብ B ሳያልፉ መቅረታቸው ይታወሳል። በኋላ ላይ ከዚህ ምድብ ያለፉት አልጄርያ እና ዛምቢያ ለደረጃ ተጫውተው ዛምቢያ 3ኛ ወጥታ ነበር። ሊቢያ እና ጋና ለዋንጫ ከደረሱ በኋላ 1-1 በመውጣታቸው በፍጹም ቅጣት ምት ተለያይተዋል በውጤቱም ጋና 7-6 አሽንፋ ዋንጫውን አንስታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አዲሱን ባለንቅሳት ባንዲራ በመቃወም፤ መሃሉ ላይ የአንበሳ ስዕል ያለበትን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በማውለብለብ ላይ ናቸው። በነገርዎ ላይ እንደአዲሱ የሰንደቅ አላማ ህግ ከሆነ፤ መሃሉ ላይ ንቅሳት የሌለበትን፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ማውለለብ ያስቀጣል። በደቡብ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ይህንን ለመቃወም ጭምር ይመስላል፤ የቀድሞውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርገው በማውለብለብ ላይ ናቸው። የኳስ ቡድኑንም ዋልያዎቹ ሳይሆን “ጥቁር አንበሶች” በሚል ስያሜ ነው የሚጠሯቸው።

ኢ.ኤም.ኤፍ ሁሉንም ጨዋታዎች በቀጥታ እየተከታተለ፤ እንደከዚህ በፊቱ በጽሁፍ በድረ ገጻችን እና በፌስ ቡክ የሚገልጽ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል።

 

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 20, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.