የኢትዮጵያ ቡድን በኮንጎ 1-0 ተሸነፈ

(EMF) የአፍሪካ ሻምፒዮን በደቡብ አፍሪቃ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ቡድን ያለበት ምድብ “ሲ” ኢትዮጵያን ጨምሮ፣ ጋና ኮንጎ እና ሊቢያን ያካተተ ነው። ከጥቂት ቀናት በፊት በተደረገው የመክፈቻ ጨዋታ ሊቢያ – ኢትዮጵያን 2-0 ማሸነፏ ይታወሳል። ዛሬ በተደረገው ጨዋታ ደግሞ 0-0 ቆይተው ጨዋታው ሊጠናቀቅ 10 ደቂቃ ሲቀረው፤ በኮንጎ 1-0 ተሸንፈናል።

በሌላ በኩል ደግሞ በዚሁ ምድብ ዛሬ የተጫወቱት ሊቢያ እና ጋና 1-1 ወጥተዋል። የመጨረሻው ጨዋታ የሚሆነው ጃኑዋሪ 21 ቀን ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከጋና ጋር፤ ሊቢያ ከኮንጎ ጋር ይጫወታሉ። ኢትዮጵያ ማጣሪያውን ለማለፍ ያላት እድል እዚህ ላይ ያበቃ ነው የሚመስለው። በቀጣዩ ጨዋታ ኢትዮጵያ ጋናን 3-0 ብታሸንፍ፤ እና ኮንጎ ደግሞ ሊቢያን ብታሸንፍ ወይም አቻ ብትወጣ፤ ጋና ወድቃ ሊቢያ እና ኮንጎ አላፊ ይሆናሉ።

በአጠቃላይ በቀጣዩ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡድን የሚያደርገው ጨዋታ፤ የአንዱን እድል አሳምሮ ሌላውን ለመጣል ካልሆነ በስተቀር፤ ቀጣዩ ጨዋታ ለኢትዮጵያ ቡድን እምብዛም ጥቅም የሚሰጥ አይሆንም። በዛሬውም ጨዋታ ሳላዲን ሰኢድ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ጌታነህ ከበደ እና አዲስ ህንጻ አልተጫወቱም። ይህ የሆነበት ምክንያትም በአፍሪካ ቻን ሻምፒዮና፤ የአገር ውስጥ እንጂ ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች መጫወት ስለማይፈቀድላቸው ነው። ሳላዲን፣ ሽመልስ፣ ጌታነህ እና አዲስ ህንጻ ለውጭ አገር ቡድን ስለሚጫወቱ ቻን ላይ መሳተፍ አልቻሉም።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለደረሰው ተደጋጋሚ የኢትዮጵያ ቡድን ሽንፈት ብዙዎች፤ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ባለፈው ከሊብያ ጋር በተደረገውም ጨዋታ ቢሆን፤ ህዝቡ እና ጋዜጠኞች በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ላይ ሲናደድ ነበር። በተለይም አሰልጣኙ በተደጋጋሚ ለጋዜጠኞች በሚሰጡት መግለጫ ላይ፤ የተጫዋች እና አጨዋወት ለውጥ ማድረግ ማስፈለጉን አስመልክቶ ጥያቄ ሲነሳ ወይም አስተያየት ሲሰጥ ቶሎ የመናደድ እና፤ “የሚሆኑኝን ተጫዋቾች እና አጨዋወት እኔ ነኝ የምመርጠው” ሲሉ ይደመጣል። ይህ አይነቱ አነጋገር በሌላው የሰለጠኑ አገሮችም… አሰልጣኞች ላይ የሚታይ ባህሪ ነው። ይህ አይነቱ ባህሪ ደግሞ በውጤት ካልታገዘ፤ አሰልጣኙ ወቀሳ ውስጥ መግባቱ አይቀርም። የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ፉከራ እና ቁጣ በውጤት ባለመደገፉ፤ እስካሁን ሲናደዱባቸው ለነበሩት ሰዎች፤ አሰልጣኙን ለመተቸት ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል።

በሌላ ወገን የሚገኙት ወገኖች አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ላይ የሚሰነዝሩት ትችት… “አዳዲስ እና ጎበዝ የሆኑ ወጣት ተጫዋቾችን አላሳተፍም” የሚሉ እና “ሁልጊዜ ተጫዋቾቻችን፤ ከኋላ ጀምረው ኳስ አደራጅተው ወደ ተቃራኒ ቡድን ይዘው አይሄዱም” ይገኙበታል። ከዚያ በተጨማሪም በአጭር ቅብብል የሚደረገውን የተካ ተካ አካሄድ የሚተቹ ሰዎች አሉ። በዚያም ተባለ በዚህ… ለቻን የአፍሪካ ሻምፒዮና የተደረገው ጉዞ እዚህ ላይ አብቅቷል። ከላይ እንደገለጽነው፤ ቀጣዩ ጨዋታ በኢትዮጵያ እና በጋና መካከል የሚካሄደው ነው። ብናሸንፍም ብንሸነፍም ወደቀጣዩ ጨዋታ የማለፋችን እድል ተዘግቷል።በመሆኑም…  እንዲያው ለወዳጅነት ወይም ለልምድ ያህል እንደሚደረግ ጨዋታ ይቆጠራል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 17, 2014. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.

One Response to የኢትዮጵያ ቡድን በኮንጎ 1-0 ተሸነፈ

  1. much

    January 19, 2014 at 5:47 AM

    በጣም አስቂኝ እና አስገራሜ አሰልጣኝ ነው። ምንም ብቃት የለለው አሰልጣኝ ነው ባለፈው ባአፍሪካ ዋንጫ እንዳየነው እና ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከናይጀሪያ ጋር በተደረገው ጭዋታ ላይ ጭራሽ ብቃት የለሊው መሆኑን አስመስክሮዋል አሰላለፉን እንደጭዋታው ሁኒታ አይቀይርም የተጫዋቾቹን የግል የአካል ብቃት እና የግል ችሎታ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ አሰላለፍ ነው የሚመርጠው ብቻ በላፈው የተገኘው እድል ባጋጣሚ የመጣ እንጂ ብችሎታ እንዳልመጣ የታየበት ውድድር ነው ያደረጉት ከተሳተፉት ሃገሮች በሙሉ ደካማ ጭዋታ ያሳየው የኢትዮጵያ ቡድን ነው:: ገና ብዙ ይቀረናል