የኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ሰልፍ በጃፓን በተሳካ ሁኔታ ተጠናቀቀ

 አንተነህ ዘውዴ ( ከቶኪዮ)

በሩቅ ምስራቋ ጃፓን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው መንግስት በዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ኢሰብአዊ ድርጊት በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል።

   ኢትዮጵያውያኑ በተለይ በቅርቡ ራሱን በእሳት አቃጥሎ የተሰዋውን መምህር የኔሰው ገብሬን ስም ከፍ አድርገው በማንሳት እና በሃገሪቱ የተንሰራፋውን ግፍ እና በዜጎች ላይ የሚደርሱ በደሎችን በመፈክሮቻቸው እና ባነገቧቸው መልእቶች  ለጃፓን ህዝብ እና መንግስት ለማሳየት ሞክረዋል።

   የመምህር የኔሰው ገብሬ ያልተመለሱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች መሆናቸውን የተቃውሞ ሰልፈኞቹ አመልክተዋል። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት በጸረ ሽብርተኝነት ስም በተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች፣ በጋዜጠኞች፣እንዲሁም በሰብአዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች እና ነዋሪዎች ላይ እያደረሰ ያለውን በደል እና ግፍ እንዲያቆም ጠይቀዋል።

    ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፣ እስክንድር ነጋ ይፈታ ፡ ርእዮት አለሙ ትፈታ፣ መንግስት ህገ መንግስቱን ያክብር፣ አፈና ይቁም፣ የጃፓናውያን የታክስ ገንዘብ ለአንባገነን አገዛዝ ድጋፍ ሊውል አይገባውም እና ሌሎች በርካታ መልእቶችን በአማርኛ እና ጃፓንኛ ቋንቋዎች ሲያስተጋቡ  ቆይተዋል።

    በቶኪዮ በሚገኙ ሁለት ክፍላተ ከተሞች ውስጥ በመዘዋወር የተቃውሞ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙት ኢትዮጵያውያኑ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ካለበት ድረስ በመሄድ ግልጽ ደብዳቤያቸውን እማኝ የጸጥታ ሰዎች ባሉበት በፖስታ ሳጥኑ ውስጥ አኑረዋል። በተቃውሞ ሰልፉ ላይ  የእስያ ህዝብ ወዳጅነት ማህበር እና የጃፓን የጸረ ዘረኝነት  ማህበር  ከተሰኙ ሁለት አንጋፋ እና ታዋቂ ማህበራት አመራሮች እና ደጋፊዎቻቸው  የኢትዮጵያውያኑን ተቃውሞ በመደገፍ አደባባይ ወጥተዋል።

    የኢህአዴግ መንግስት የእርዳታ ገንዘብን ለፖለቲካዊ ጥቅም ከማዋልም ባሻገር የህዝብ ማፈኛ መሳሪያ በመሆኑ የጃፓን መንግስት እና ህዝብ ጉዳዩን እንዲያጤኑት  ኢትዮጵያውያኑ አሳስበዋል። በጃፓን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም በስደት በዚሁ ሃገር በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ሊያሳርፍ የሚሞክረውን ጫና እንዲያቆምም ጠይቀዋል። ለዚህም ከስደተኛው ወደ ኤምባሲው ወሬ በማመላለስ ለደህንነታቸው ስጋት የሆኑ ሰዎችም እጃቸውን እንዲሰበስቡ አሳበዋል።

   ይህንኑ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ የቶኪዮ ከተማ የደህንነት ሰዎች እና ፖሊሶች አስፈላጊውን ጥበቃ እና እገዛ በማድረግ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስችለዋል። ከተለያዩ  መገናኛ ብዙሃን የመጡ ጋዜጠኞችም ኢትዮጵያውያኑን ሲያነጋግሩ እና  ሽፋን ሲሰጡ ለማየት ተችሏል። 

    በስተመጨረሻም ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ወደየመጡበት  በተለያዩ አቅጣጫዎች የተመለሱ ሲሆን በአንድ ቡድን በመሆን ተሰብስበው ሲሰነባበቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ግን አስገራሚም አሳዛኝም ነገር አስተናግደዋል። የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዋና ጸሃፊ እና በዚሁ ሃገር ለስደተኝነት አመልክቶ የሚኖር  ሌላ ኢትዮጵያዊ  በስተመጨረሻ  ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡትን በመከታተል ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ማስተዋል ተችሏል።

    የዛሬውን የተቃውሞ ሰልፍ በተሳካ ሁኔታ ያጠናቀቁት ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው የሰፈነው አስከፊ ስርዓት እና ሁኔታ እስካልተስተካከለ ድረስ እንዲሁም ዜጎች በእኩልነት እና በነጻነት የሚኖሩበት ሁኔታ እስካሌለ ድረስ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እንደሚያሰሙ  አስታውቀዋል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 9, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.