የኢሳትን ህልውና የተፈታተነ አደጋ፣

 የካቲት 13 ቀን 2004 ዓ/ም |

 ኢሳት አሁን በደረሰበት ደረጃ ብሄራዊ ተስፋ ሆኗል ማለት ማጋነን አይሆንም። ለዚህም ምክንያቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ ለሚያደርገው ትግል እንደ አንድ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ በመሆን ትግሉን ከውጤት ለማድረስ የራሱን አስተዋጸዖ ለማድረግ የገባውን ቃል፣ በተግባር ያስመሰከረ የመገናኛ ብዙሀን በመሆኑ ነው።

ኢሳት የነገዋ የእኩልነት ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል ፍንጭ የሰጠ የብሩህ ተሰፋ ምልክት ነው። ለዚህም ነው በሚያስገርም ደረጃ ባለፈው የፈረንጆች ጀንዋሪ ወር 96,305 (ዘጠና ስድስት ሺ ሶስት መቶ አምስት) ጎብኚ፣ 429,477 (አራት መቶ ሃያ ዘጠኝ ሺ አራት መቶ ሰባ ሰባት) ጊዜ፣ የኢሳት ደህረ ገጽን የጎበኙት። በሀገር ውስጥም በቴሌቪዥን ለመድረስ ያለው ጥረት እንደቀጠለ ሆኖ፣ በቀን አንድ ሰዓት በሰባት የተለያዩ አጭር ሞገዶችና በሳተላይት የ24 ሰአት የኢሳት ራድዮ በሚያስተላልፈው ዝግጅቱ የከፍተኛ መረጃ ምንጭ ሆኖ ወደ በርካታ ዜጎች በመድረስ እያገለገለ ያለው።

ኢሳት በዚሁ ከቀጠለና በተጨማሪም የሀገር ውስጥ የቴሌቪዥን እቅዱን ካሟላ፣ በቅርብ ግዜ ውስጥ ብሄራዊ ቅርስ እንደሚሆን ምንም አያጠራጥርም። ዛሬ ስለኢሳት ሲነሳ የጋራ መልካም ስሜት ተቋዳሽነት የሚሰማው ሰው በሀገርም ውስጥም ሆነ በውጭ ቁጥሩ እጅግ ብዙ እንደሆነ በርግጠኝነት መናገር ይቻላል። እዚህ ላይ የሚገርመው ጉዳይ ግን ከረጅም ግዜ በኋላ ኢሳት በመሀከላችን የጫረው የጋራ መልካም ስሜትን እንዲያድግና ጠንክሮ ለቁም ነገር እንዲበቃ ሌት ተቀን ደፋ ቀና የሚሉት እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ወገኖች መሆናቸው ናቸው።

በብሄራዊ የጋራ ስሜት መቀስቀስ የቻለን ኢሳት፣ ጥቂት ሰዎች የፈለጋቸውን ያህል እራሳቸውን መስእዋት ለማድረግ ፍቃደኛ ቢሆኑም፣ ለረጅም ግዜ ይዘውት ሊዘልቁ አይችሉም። ኢሳት በአሁኑ ግዜ በርካታ አገር ወዳድ ዜጎች በነጻ ወይም እዚህ ይግቡ በማይባል ክፍያ ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ፣ በየወሩ በሶስት ማእከል ለሚገኙት ስትዲዮችና ሌሎች ፕሮግራም አስተላላፊ ድርጅቶች የሚያወጣው ገንዘብ በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

ከዚህ በፊት ኢሳት በተለያዩ ዘመቻዎች በተሰበሰበ ገንዘብና ከበጎ አድራጊዎች በተደረገለት እርዳታ እስከዛሬ ደርሷል። ከዚህ በኋላ ግን ወደፊት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቀጠል አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ያስፈልገዋል።

እስካሁን ያለው ልምድም እንደሚያሳየው በየወሩ ከግለሰቦች በቋሚነት የሚያደርጉለት ድጋፍ ከሁሉም በላይ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። ኢሳት ወርሃዊ ወጭውን ሸፍኖ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመቀጠል እንዲችል በትንሹ በወር $20 የአሜሪካ ዶላር በቋሚነት የሚከፍሉ 3750 (ሶስት ሽ ሰባት መቶ ሃምሳ) ወገኖች ያስፈልጉታል። በአሁኑ ግዜ ይህን የወር ቋሚ ክፍያ እየፈጸሙ ያሉት ወገኖች ቁጥር ግን በጣም ዝቅተኛ ነው። 

ኢሳት በማንነታችን ላይ የፈጠረውን የጋራ ብሩህ የተሰፋ ስሜት፣ $20 ዶላር በወር በቋሚነት ከራሳችን፣ ከቤተሰቦቻችን፣ ከጓደኞቻችን፣ ከዘመዶቻችን በማሰባሰብ ከዚህም በላይ እንዲጎለብትና እንዲያድግ ማድረግ መቻል ይኖርብናል። ይህንን ማድረግ ሳንችል ብንቀር እና የኢሳት ህልውና አደጋ ውስጥ ቢወድቅ እስካሁን ያቆጠቆጠው ብሩህ የጋራ የተስፋ ስሜት ወደ ጋራ ተሰፋ ቢስ ጨለማ እንደሚቀየር ማንኛችንም ለአንድ አፍታም ቢሆን ልንጠራጠር አይገባም። ስለዚህ ኢሳት የገጠመውን የገንዘብ ፈተና በጋራ ለመወጣት ሳንውል ሳናድር፣ ዛሬውኑ ጥረታችንን እንጀምር።

የኢሳትን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ድርሻዎን ይወጡ፣ ዛሬውኑ ቋሚ ድጋፎትን  www.ethsat.com በመጎብኘት ያስጀምሩ!

ኢሳት የኢትዮጵያ ህዝብ ዓይንና ጆሮ ነው!!!

የኢሳት – ማኔጅመንት

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 21, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.