የአፓርታይድ መንደር – በመቀሌ፣ ትግራይ!

በዮናስ በላይ (ከመቀሌ)

ሽፍታ በህዝብ መካከል እንደሚገኝ ሁሉ በተወሰኑ ወያኔዎችም መካከል ሊገኝ እንደሚችል ነው፡፡ እነሱ ግን በደፈናው ..በሽፍታ.. ስም ሊጠሩ አይገባም፡፡
…በትግራይ ህዝብ ላይ የሚዘንበውን የጭቆና ዝናብ ለማስቆም በእውቀትም ሆነ በስሜት ወደ በርሃ የወጡት ..የቁርጥ ቀን.. ወገኖች፣ ..ወንበዴ.. እየተባሉ፣ በተቆጣጠሩት መሬት (ሓራ መሬት) ዋርካ እግር ስር ሆነው ይሰጡት የነበረ ፍትህ ግን የሽፍታ ሳይሆን የራስ ሚካኤልን ፈለግ የተከተለ እንደ ነበር ዛሬም የአይን ምስክሮች አሉ፡፡

እናም እነዚህ ታማኝ ወያኔዎች በሚሰሩት ስራ የትግራይ ህዝብ አመናቸው፤ ይሄ ሁኔታም ራሳቸው እና ህዝቡ መሰላል ሆኖ ከመካከላቸው ጥቂቶቹን ካሰቡት በላይ በሆነ ወንበር ላይ ሰቀላቸው፡፡ የተቀሩት ..ሻማዎቹ..ም ተስፋ ያልቆረጡ ይመስል፤ አሁንም ድረስ እየነደዱ ያበራሉ፡፡ የሆነ ሆኖ ከደርግ ቢኤም. እና የጦር ጀቶች ጋር ፊት ለፊት ገጥመው ያሸነፉትና ከድል በኋላ ..የታገሉለት አላማ.. የተቀለበሰባቸው እነዚህ እልፍ አላፋት ታጋይ አንድ ቀን ግን፤ ባላሰቡትና ባልጠበቁት ጊዜ ለማመን ቀርቶ ለመስማት የሚከብድ ወሬ ከጆራቸው ደረሰ፡፡ የ..አፓርታይድ መንደር በመሀል መቀሌ እየተመሰረተ ነው፡፡..
…መቼም ስለ ..አፓርታይድ ስርዓት.. ያልሰማ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው የአፓርታይድ ስርዓትን የአየነውና የሰማነው በአልማዝ መአድን ክምችት በበለፀገችው ደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ የታላቋ ብሪቲንያ ቅኝ ገዥዎች ባልታሰበ ቀን ተከሰቱ፡፡ መላው ደቡብ አፍሪካንም በመዳፋቸው ስር አስገቡ፡፡ ከዚህ በኋላም ..ነጭ ከጥቁር ይበልጣል.. (White superiority) በሚል ፍልስፍና የተገመደው የአፓርታይድ ስርዓትን በስራ ላይ አውለው፤ ነጭ ባለበት ጥቁር ቢገኝ እስከ ሞት በሚያደርስ ቅጣት ይቀጡ ጀመር፡፡ ይሄ የሆነው በደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ ታዲያ ..በትግራይ አፓርታይድ.. ከየት መጣ? የሚል ጥያቄ ካለ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

…ከመሀል መቀሌ በ2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ..ገረብ ቡቡ.. የሚባል ኮረብታማ ቦታ አለ፡፡ ማንም ሰው ገረብ ቡቡ ኮረብታ ላይ ሆኖ ሙሉ መቀሌን ጥርት አድርጎ ማየት ይችላል፡፡ ይሄ ኮረብታ ከመቀሌ ከተማ የአየር ፀባይ ጋር በተገናኘ፤ ማስተር ፕላን ወጥቶላት በደን እንዲሸፈን በባለሙያ ተጠንቶ የተወሰነ ሲሆን፤ ይህ ካልሆነ ግን መቀሌ በጎርፍና በንፋስ እየታመሰች ዘመኗን ሙሉ ፍዳዋን እያየች እንደምትኖር ተደጋግሞ የተነገረላት ነው፡፡ ይሄ ትንግርት አይደለም፤ በባለሞያ ጥናት የተረጋገጠ እንጂ፡፡ የሆነ ሆኖ ግን በ1997ዓ.ም ገረብ ቡቡ ድንገት በህወሓት ማዕከላዊ ኮሜቴ አባላት ቁጥጥር ስር ዋለች፡፡

በአመቱም (በ1998) ኮረብታው ላይ የዘመናዊ ቪላ መሰረቶች ተጥለው ታዩ፡፡ ጉዳዩንም ነዋሪው ሲያጣራ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ጥቂት ኢንቨስተሮች (በድምሩ 40 ሰዎች ናቸው) ከመቀሌ ከተማ ነዋሪ የተለየ መንደር ራሱን የቻለ የገበያ ማዕከል፣ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ የመዝናኛ ማዕከል እና የመሳሰሉትን ተቋማት ያቀፈ፤ በግልባጩ ሌሎች የመቀሌ ሰዎች ድርሻ እንዲሉ የማይፈቀድበት መንደር እየተመሰረተ እንደሆነ ታወቀ፡፡ በዛን ወቅት ማንም ሰው እነዛ ታጋዮች ከ60ሺ በላይ የትግራይ ሰዎች በሞቱለት ድል ተጠቅመው.. በአፓርታይድ ስርዓት የሚተዳደር መንደር ይመስረታሉ ብሎ አልጠረጠረም፡፡ የሆነው ግን ያልጠረጠረ…
በዚህ ጊዜ እነዛ ታጋዮች፤ እነዛ ሻማዎች ሃይል ያነሰው መብራት መሰሉ፤ ጭለማ ለብሰው ጭለማ ውጠው ሆ ብለው ገነፈለ፡፡ ..ትግራይ የህልውና መሰረቴ.. የሚለውን ህወሓትን አንቀጠቀጡት፡፡

ይህንን ጊዜም ጉዳዩ ከአቅም በላይ መሆኑ በመታወቁ ጠ/ሚኒትሩ ውለው ሳያድሩ መቀሌ ገቡ፡፡ እንደደረሱም በሰማእታት ሀውልት ስር ባለው አዳራሽ ስብሰባ ይሁን አውጫጭኝ ያለየለት ነገር ከሹማምነቶቻቸው ጋር ተቀመጡ፡፡ በሁኔታው የተበሳጩ በሚመስል ድምፅ ..ህዝብን ማገልገል፣ አሊያም ከድርጅቱ ወጥቶ ነጋዴ መሆን…. እንጂ እንዲህ አይነት ነገር በጠራራ ፀሐይ አይሰራም ሲሉ በቁጣ ገለፁ፡፡ ካድሬውም ..አይ.. ፍትህ.. በማለት የጠ/ሚኒስትሩን ንግግር ሲያወድስ፤ ሻማዎቹ ግን ..ፍትህማ በዛ በዋርካ ስር ቀረ…. ሲሉ ተቆጩ፡፡ እንደተባለውም አልሆነም ይህ ሃገር ያስቆጣ ነገር፤ በአስተሳሰብ ደረጃ እንጂ በህግ ..ሙስና የሚባል አይደለም.. ብለው ውስጥ ውስጡን ሻማዎችን መሸርሸርም እለቱን ተጀመረ፡፡ በካድሬው፡፡

በመሆኑም ..ጉድ አንድ ሰሞን ነው…. እንደተባለው ሁሉ ይህ ጉድም ተረሳ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ከአንገት በላይ የሆነ ቁጣቸውን አሰምተው ከሄዱ ከወራት በኋላ የአፓርታይድ መንደር ምስረታ በህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቀጠለ፡፡

Gereb bubu, tigray

Gereb bubu, apartheid's village in Tigray.

…ትግራይ በወያኔ ጊዜ ሶስት ንጉሶች አይታለች፡፡ ..አዲስ ንጉስ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ?.. ያለው ማን ነበር?… ገብሩ አስራት ሄዱ፤ ሃለቃ ፀጋዬ በርሄ መጡ..ሃለቃ ፀጋዬ ሄዱ ሳልሳዊ ንጉሱም ወንበር ያዙ፡፡የመዝገብ ስማቸውም አባይ ወልዱ ይሰኛል፡፡እኚህ ንጉስ ሙስና አይወዱምና ልክ ወንበራቸውን በተረከቡ ማግስት መቀሌ ተተራመሰች፡፡ የሙስና ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆነ፡፡ በተለይ የመሬት ሙስና፡፡ በሃለቃ ፀጋዬ ጊዜ ሙስና ሰሩ የተባሉ ካድሬዎች ከያሉበት ታድነው እስር ቤት ገቡ፡፡ ህገ ወጥ የተባሉ ቤቶችም በገፍ ፈረሱ፤ አላግባብ የተወሰደ መሬትም ተወረሰ፡፡ ከነዚህ ከፈረሱ ህገ ወጥ ቤቶች የአንዱ መንደር አስገራሚ ነበር፡፡ ይህ ሰፈር ገፊሕ ገረብ በመባል ይታወቃል፡፡
እዚህች ጋር ለአፓርታይድ መንደር ጋር ንፅፅር አድርገን መራራውን እውነት እንጨልጣት ዘንድ ስለገፊሕ ገረብ መንደር ጨርፌ ላስተዋውቃችሁ፡፡ …ገፊሀ ገረብ በመቀሌ በስተምዕራብ (የአፓርታይድ መንደር የሚገኘው በስተምስራቅ ነው) የሚገኝ ሲሆን፤ ከመሐል መቀሌም ወደ 6 ኪሎ ሜትር ገደማ ይርቃል፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች በሙሉ ተፈናቃዮች እና ድሆች ናቸው፡፡ በግምት እስከ 10ሺ የሚደርሱ ቤቶች በገፊህ ገረብ መንደር የመስቀል ደመራን ይመስል ተጨናንቀው ይታያሉ፡፡ ሁሉም ቤቶች የተገነቡት እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በጭቃ ሲሆን፤ አልፎ አልፎም የብሎኬት ቤቶች አሉ፡፡ በዚህች መንደር አንድ ቤተክርስቲያንም ታንፆበታል፡፡

በወቅቱ ቤቶቹ ሲሰሩ የቀበሌ ውል አፈራራሚ ሰራተኞችም በህጋዊ ሰነድ ላይ በመመዝገቡ ተሳትፈዋል፡፡ ይሄ ሲሆን ግን የክልሉ አስተዳዳሪ ሃለቃ ፀጋዬ እያንቀላፉ እንደነበረ እንዳይመስላችሁ፡፡ ሰውዬው በጭራሽ አላነቀላፉም፡፡ አረ እንዲያውም እንደዚያን ጊዜ ይበልጥ ንቁ የሚሆንበት ወቅት ያለ አይመስለኝም፡፡ ወቅቱ ምን ስለሆነ ነው ብትሉ? መልሴ የ2002 ምርጫ ዋዜማ የሚል ነው የሚሆነው፡፡
እናም በምርጫ ቅስቀሳው አንዱ ቀን ሃለቃ የገፈ ገረብ ነዋሪን ሰብስበው እንዲህ ሲሉ ሸነገሏቸው፡ ..አይዟችሁ፣ ለመሬት ነው እንዴ? እንኳን ለእናንተ ለቅንጅት እስረኞችም ምህረት አድርገንላቸዋል…. በዚህም ድለላ ዳጎስ ያለ የምርጫ ካርድ ሸምተውበታል፡፡ የትኛው ፀሀፊ ነበር ..እንደ ኮንደም ነው የሚጠቀሙብህ…. ያለው?… ከዛማ ምርጫም አለፈ፤ የሃለቃ ፀጋይ ቃልም ታጠፈና፣ እነዚህ ነዋሪዎች፤ ከሌላ አገር የመጣ በሚመስል መንግስት እንደ ሰው ሳይታዩ ቤታቸው በገፍ ፈረሰ፡፡ …የመፍረሱ ጉዳይ አይደለም፡፡ የመናገር፣ የመሰብሰብ መብት ከልክለው በህዝቡ ላይ ያወረዱት የዱላ መአት፣ የአስለቃሽ ጋዝ ጢስ፣ የእስር ቤቱ ሰቆቃ… ይህንን ሁሉ በአርምሞ የተመለከተ ..እውነት እነዚህ ሰዎች የመስከረም 2/1967ን አዋጅ በመቃወም ነበር ወደ በርሃ የወጡት?.. ሲል መጠየቁ አይቀርም፡፡ በይበልጥ ደግሞ ያውም ከተማውን ከጎርፍ እና ከንፋስ እንዲከላከል በታቀደው ቦታ ላይ (ገረብ ቡቡ) የአፓርታይድ ግልባጭ የሆነው መንደር ተመስርቶ አይቶ እንዳላየ ባለፈ መንግስት፤ የድሆች ሰፈር ሲፈራርስ፡፡ ምሬቱ አይጣል ነው፡፡
…ማንም ሰው ይህንን ግፍ ሲያይ ትዝ የሚለው የእንግሊዛዊው የጆርጅ ኦርዌል ድርሰት የሆነው ..አኒማል ፋርም.. ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በተለይ ለህወሓት ሰዎች ቅርብ ነው፡፡ በ1993 ህወሓት ለሁለት ሲከፈል የጠ/ሚኒስትሩ ቡድን ከህወሓት የወጡትን ሰዎች በ..ቦናፓርቲዝም.. ሲከስ እንደ ማብራሪያ የተጠቀመው ይህንን መጽሐፍ ነውና ነው፡፡ እንዳልኳችሁ በአኒማል ፋርም ውስጥ ጉልበተኛ እንስሳቶች በግድግዳው ላይ የፃፉት ማስታወቂያ እንዲህ ይነበባል፡፡

..እንስሳት ሁሉ እኩል ናቸው፤ ግን አንዳንድ እንሰሳት ከሌሎች ይበልጥ እኩል ናቸው፡፡ ..
በመቀሌ ደግሞ
..ሁሉም ሰዎች እኩል ናቸው፤ ግን የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከሌሎቹ ይበልጥ እኩል ናቸው…..
እነሆ ሄዶ ሄዶ የትግሉ ውጤት እዚህ ደርሶላቸዋል፡፡…የ..ሙስና ጠላት.. ተብለው የሚወደሱት አባይ ወልዱ፣ ጦራቸው አንድ ቦታ ላይ ሲደርስ እንደተብረከረከም የመቀሌ ህዝብ በትዝብት ተመልክቶአል፡፡ ያ የአባይን ጦር ያንበረከከው ቦታ ገረብ ቡቡ ይባላል፡፡ ስለቦታው ሲጠይቁ፣ ..ቦታው የመሬት ገነት የመሰለ፣ ከዛ ቁልቁል መቀሌን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ኮረብታማ፣ ለከተማው የአየር ፀባይ ተብሎ በማስተር ፕላን በደን እንዲሸፈን የተወሰነ፤ ይህ ካልሆነ ግን መቀሌ በጎርፍና በንፋስ አየታመሰች እንደምትኖር….. የተነገረለት መሆኑን ደግሞ ሲሰሙ ነገሩ ገባቸው እና ካቢኔያቸውን ስብሰባ ጠሩ፡፡

“..እናፍርሰው?..”፣ ሲሉ ጠየቁ፡፡

የአፓርታይድ መስራቾችም “..አናፈርስም..”፣ ሲሉ በእብሪት መለሱ፡፡

“ ..ተው ይህ ህዝብ ከሆዱ ካወጣን እንጠፋለን? ብናፈርሰው ይሻላል…” ሲሉም ተለማመጡ፡፡

በዚህ መሃል አንድ የአፓርታይድ መስራች ተነስቶ፣ “..እምቢ.. አላፈርስም ታግዬ ያመጣሁት ነው፤ አላፈርስም….”  ሲል ቡራ-ከረዩ አለ፡፡ ቡራ-ከረዩ ብሎም አልቀረ፣ ቤቱን አጠናቆ ገባበት፤ እኔም ይህን ዜና ስሰማ ማየት ማመን ነውና ወደ ገረብ ቡቡ አቀናሁ፡፡ ወደ አፓርታይድ መንደር፡፡ ..ማንም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው…. የሚለውን የወረቀት ህግ ያነበብኩት ቦታ አሁን ትዝ አልልህ አለኝ፡፡ ሁለት ያለቁ ቪላ ቤቶች አየሁኝ፡፡ እየገረመኝ ወደ ማህደረ ካሜራዬ ላኳቸው፡፡ ከአስር የማያንሱ ቪላ ቤቶች ደግሞ እየተፋጠኑ ነው፡፡ በዚህ ሰዓት ነበር የአንድ ወዳጄ ፕ/ር አባባል ትዝ ያለኝ፡፡ ..ትግል ማለት እኮ ቢዝነስ ነው፡፡ አስራ ሰባት አመት ታግለህ እንዲህ የናጠጥክ ሚሊየነር የምትሆን ከሆነ ቢዝነስ ነው.. ያውም ጥሩ ቢዝነስ.. ቢዝነስ.. .. ተብከነከንኩ፡፡ እነዚያን ሰማእታቶች በአየነ ህሊናዬ አሰብኳቸው፡፡ ይህን ቢያዩ ምን ሊሉ ይችሉ ይሆን? በአፅማቸው እና በትግራይ ህዝብ እየተደነገደ መሆኑን ሲሰሙስ ምን ይሉ ይሆን? ….መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች፡፡
እንዴት ለህዝብ ነው የታገልኩት የሚል ሰው ከህዝብ ተነጥሎ መኖር ይመኛል? ለዛውም ላይና ታች፡፡ እንዴትስ ህዝብ የሚጎዳ ነገር ይሰራል? ለዛውም የህልውና ጉዳይ፡፡ ከህዝብ አፍ የሚነጥቁ ፊውዳሎች ይውደሙ ብሎ የተነሳ ሰው እንዴት ራሱ ፊውዳል ሆኖ ቁጭ ይላል? እነዚህ ሁሉ ዛሬም በትግራይ መልስ ያላገኙ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በቃ.. ማንም ወደ ስልጣን መውጫ መንገድ ሲጨልምበት ነው ይህን ሻማ የሚጠቀምበት? እስከ መቼ ነው ግን ይህ ህዝብ ..መሳሪያ.. ሆኖ የሚያገለግለው? መልሼ ደግሞ ታድያ እንዴት ይኑሩ እያልኩኝ ነው? እነሱስ የሚጠማ ጉሮሮ የሚራብ ሆድ አልያዙምን? እነሱስ መጠልያ አያስፈልጋቸውምን? ብዬ ሳስብ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ገብረመስቀልና ገብሩ፡፡
ገብረ መስቀል በክፍፍሉ ጊዜ የእነተወልደ ቡድን ተብሎ ከሚጠራው ጎራ የነበረ ነባር የህወሓት የአመራር አባል ነው፡፡ ይህ ሰው ተማሪ እያለ የሼክ መሀመድ ሁሴን አላሙዲን ጓደኛ የነበረ በመሆኑ ትግሉ በድል ተጠናቆ ከበረሃ እንደገባ ሼኩ ደጋግመው “..ምን ላድርግልህ?”.. ሲሉ ይወተውቱታል፡፡ ገብረመስቀልም ምንም እንደማይፈልግ ደጋግሞ ይመልስላቸዋል፡፡ አንድ ቀን ግን ሙሉ ሳምሶናይት ገንዘብ (የዶላር፣ እና የፓውንድ ቅልቅል) ይመጣለታል፡፡ ሚስኪኑ ገብረ መስቀል ይህን ብዙ ገንዘብ ተቀብሎ ቤት አልሰራበትም፣ መኪናም አልገዛበትም፡፡ እናስ የት አደረገው? ቀጥ ብሎ ወደ ድርጅቱ (በሱ አነጋገር ..ንውድበይ..)  በመሄድ ያስረክባል፡፡

…ህወሓት ለሁለት ተከፍሎ የነመለስ ቡድን የእነ ተወልደ ቡድንን እንዳገደ፤ ይህ ይሆናል ብሎ ያላሰበው ምስኪኑ ገብረ መስቀል የአእምሮ መታወክ ገጠመው፡፡ እናም የሚያሳክመው አጣ፡፡ ያ..ተራራን ያንቀጠቀጠው.. ታጋይ አእምሮውን ስቶ ሙሉ በሙሉ እንደተቃወሰ ተሰቃይቶ ህይወቱ አለፈ፡፡
በዚህን ወቅት ከእነ ተወልደ ቡድን ነጥሎ አቶ መለስ ያነጋገሩት ሌላው ሰው ደግሞ፤ ገብሩ አስራት ይባላል፡፡ መለስ ገብሩን ወደ እራሳቸው ቡድን ለመመለስ አበክረው ስለፈለጉ ..ገብሩ ተው.. እነሱ የያዙትን ይዘዋል አንተ ግን ትጎዳለህ፡፡ ማሃረምህን አንጥፈህ ነው ወደ መለመን የምትገባው..? አሉና በነባሩ ማስፈራሪያቸው የገብሩን አቋም ተፈታተኑት፤መለስ ዜናዊ፡፡

“..ታጋይ እኮ ነኝ”…. ሲልም ገብሩ መለሰ፡፡ ይህ ብዙ ትርጉም አለው፡፡ ለህዝብ የታገለ፣ በህዝብ ድጋፍ እዚህ የደረሰ ህዝብ ያኖረዋል፡፡ እኔ ወያኔ እንጂ ሽፍታ አይደለሁም ማለቱ ነበር፡፡ አቶ ገብሩ፡፡

እንደነዚህ አይነት ወያኔዎቸም አሉ፡፡ እነዚህ ከወጡ በኋላ ነገረ ስራቸውን አወቅን እንጂ ስንት ምርጥ የህዝብ ልጆች በድርጅቱ ውስጥ እንዳሉ አምናለሁና፤ እንክርዳዱን ከስንዴው መለየት ተገቢ ይመስልኛል፡፡ ወያኔውን ከሽፍታው ወይም ከአፓርታይዱ፡፡

ለነዚህ ፍትህ ላጓደሉ የትግራይ ሰዎች ማስተማሪያ ይሆን ዘንድ በታሪክ ጎማ ወደ ኃላ ተጉዘን የወላጆቻቸውን ተሞክሮ እናካፍላቸው፡፡ …ራስ ስብሓት እየተባሉ የሚታወቁት መሳፍንት ግዛታቸውን በሚያስተዳድሩበት ወቅት አንድ እህታቸው፤ ዝም ብለው ዓይናቸው ያረፈበትን መሬት ሁሉ ከድሃው ህዝብ መንጠቅ ሆነ ስራቸው፡፡ ድርጊቱም እየተደጋገመ ሲሄድ የተማረረው ህዝብ ..ፍትህ ይስጡን..?.. ብሎ ወደ ራስ ይቀርባሉ፡፡ ቀርበው ሲያበቁም ክሳቸውን ያሰማሉ፤ ስለክሱ የተጠየቁ እህታቸውም ድርጊቱን እንደፈፀሙ ያምናሉ፡፡

በዚህን ጊዜ ራስ ተጨንቀው እህታቸውን ሲመለከቱ፤ እንዲህ የሚል ድምፅ ወደ ጆራቸው ደረሰ “..አልጋው ላይ የለህም እንዴ? ወንድሜ በል እንጂ ፍርድህን አሰማኝ?..” አሉ፡፡

ራስም ወሰኑ፡፡ ” ..ለእህቴ ያልሆነ አልጋ ድፍት ይበል.. ሁሉም የራስዋ እንዲሆን ፈርጃለሁ..” ብለው ውሳኔያቸውን ተናግረው ፋይሉን ይዘጉታል፡፡ …ይህ ከሆነ ከአመታት በኋላም አንድ ቀን የአድዋው ገዢ ጦራቸውን አሰልፈው፤ ራስን ሊወጉዋቸው እየመጡ እንደሆነ የሰሙት ራስ ስብሓት ህዝቡን “..ክተት”…. ብለው ሲያውጁ፤ በፍርደ ገምድልነታቸው አዝኖ ለአመታት ለውጥን በመጠባበቅ የነበረው ህዝባቸውም “..እህትዎን ይዘው ይዋጉ….” ብሎ አንድም ሳይወጣ ቀርቶ፤ ለውድቀት ተዳረጉ፡፡

እናም ልብ ያለው ልብ ይበል…መማር የሚችልም፤ይማር፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 2, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.