የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በከተማዋ ፍርስራሽ ሥር

(From: Mohammed Ali Mohammed)
የአዲስ አበባ ቤቶች ይፈርሳሉ፣ መንገዶች ይቆፈራሉ፣ የውሀ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ይቆረጣሉ፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ፣ የመብራትና የስልክ አገልግሎት ይቋረጣል፣ ችግሩ ተደራራቢ ነው፡፡ ቢሆንም ህዝቡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ለመልሶ ግንባታ ነው በሚል ይፅናናል፡፡ ሆኖም ግን በችኮላ የፈረሰው ሁሉ በፈረሰበት ፍጥነት ሲገነባ አይታይም፡፡ ግንባታዎች ቢጀመሩም ለአመታት ይጓተታሉ፡፡ አንዱ በሌላው ያሳብባል፡፡ መተማመን የለም፡፡

በዚህ መሓል ነዋሪው በትራንስፖርት ችግር ይሰቃያል፣ ማንም ሰው በፈለገበት ሠዓት ተነስቶ የፈለገበት ቦታ መድረስ አይችልም፡፡ የቸኮለ ሰው ገንዘቡን ከፍሎ የፈለገበት ቦታ መድረስ የሚያስችለው የትራንስፖርት አገልግሎት የለም፡፡ ከብዙ መጉላላት በኋላ ትራንስፖርት ቢገኝም እንደልብ የሚያስኬድ መንገድ የለም፡፡ የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ተቆፍረዋል፡፡ በቀሩት መንገዶች ያለው የትራፊክ መጨናነቅ ሌላ ጭንቀት ይፈጥራል፡፡ ከመታገስ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ አለበለዚያ ጨጓራን መላጥ ነው …
በአዲስ አበባ ጧትና ማታ ረጅም ሰልፎችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ ህዝቡ ምሬቱን ዋጥ አድርጎና ፀጥ ብሎ ወረፋ እስከሚደርሰው ይጠብቃል፡፡ እኩሉ ውሀ ፍለጋ ይንከራተታል፣ ውሀ አለ በተባለበት ቦታ ቢጫ ጀሪካኖች ይደረደራሉ፣ እነሱም እንደህዝቡ ረጅም ሰልፍ ይሰራሉ፡፡ ድንገት ውሀ ሄደ ከተባለም የጀሪካኖቹ ሰልፍ ይፈርሳል፡፡ ሰው ግን ጀሪካኑን እያንጠለጠለ ውሀ ያለበት ሌላ ቦታ ፍለጋ ይኳትናል፡፡ ሲንከራተት ውሎ ባዶ ጀሪካን ይዞ መመለስ አዲስ ነገር አይደለም፡፡

የአዲስ አበባ ህዝብ ውሀ ጥሙንም ተቋቁሞ ይኖራል፡፡ ረሀቡ ጋር ተቻችሎ መኖር ከጀመረማ ቆይቷል፡፡ ለካስ ረሀብም ይለመዳል፡፡ ሰው ወዲያም ወዲህም ተሯሩጦ ረሀቡን ማስታገስ ከቻለ ተመስገን ብሎ ያድራል፡፡ ለፍቶ የሚያገኘው ገንዘብ የረባ ነገር መግዛት አያስችለውም፡፡ የመንግሥት ሚዲያዎች የዋጋ ንረቱ መቀነሱን ያበስሩታል፡፡ በተጨባጭ ግን የሁሉም ነገር ዋጋ የማይቀመስ ነው፡፡ ህዝቡ ሚዲያው የሚያወራው ነገር መሬት ላይ ካለው ሀቅ ጋር ምን ያህል የተራራቀ መሆኑን እየታዘበ ይኖራል፡፡ ትዝብቱን በውስጡ ይዞት ይኖራል እንጅ በግልፅ አያወጣውም፡፡ ሚዲያውም ከአፈርኩ አይመልሰኝ በሚል የፕሮፓጋንዳ ዶፉን በማዝነብ ሊያደነዝዘው ይሞክራል፡፡ የሚዲያው ተልዕኮ ረሀቡን ማስረሳት ይመስላል፡፡ ግና ረሀብን እንዴት መርሳት ይቻላል?

የአዲስ አበባ ህዝብ የውሀ ብቻ ሳይሆን የመረጃ ጥማትም አለበት፡፡ እውነቱን ማመዛዘን የሚያስችለው አማራጭ የሚዲያ ተቋም የለም፡፡ ብዙ ወጣቶች አማራጭ የመረጃ ምንጭ ፍለጋ በየኢንተርኔት ካፌው ከኮምፒውተር ጋር ተፋጥጠው ይውላሉ፡፡ ግን ጠብ የሚል ነገር የለም፡፡ ኔትወርክ የለም፡፡ አሁን አሁንማ ሌላ መረጃ ይቅርና ዘመድ ወዳጅ በስልክ ተገናኝቶ የእግዜር ሰላምታ እንኳ መለዋወጥ እያስቸገረ ነው፡፡ ቴሌ ምክንያቱን ሲጠየቅ በኃይል መቆራረጥ ያሳብባል፡፡ እውን ትክክለኛ ምክንያቱ የኃይል መቆራረጥ ነው?

የኃይል መቆራረጥ ነገር ሲነሳ እንደ ኬኒያ ባሉ ሀገር ዜጎች መቅናታችን አልቀረም፡፡ የእነሱ መንግሥታት የኃይል አቅርቦታቸውን ለመጨመር ወደ ውጭ ይማትራሉ፡፡ የኛዎቹ ደግሞ የተገኘችውን ሸጠው ዶላር ለማግኘት ከውጭ ገዥ ያፈላልጋሉ፡፡ ጎረቤቶቻችን የኢትዮጵያ ግድቦችን ትሩፋት ሲቋደሱ እኛ ጨለማ እየዋጠን ነው፡፡ “ከሞኝ ጓሮ ሞፈር ይቆረጣል” ነው የሚባለው? ወይስ “ሳይተርፋት አበደረች፣ ሳትቀበል ሞተች”? ለነገሩ ተረት በሌሎች ሲነገር ያምራል መሰለኝ፡፡ ምናልባትኮ እኔን በአማራነት እንዳያሙኝ ፈርቼ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የኃይል መቆራረጡም ሆነ እሱን ተከትሎ የሚፈጠረው የኔትወርክ ችግር መንስኤና መፍትሄ እንደሰማይ ርቆብናል፡፡

ለእኛ ሁሉም ነገር ሩቅ ነው፡፡ እኛም ሁሉን ነገር በሩቅ በማየት ብልሃት ተክነናል፡፡ እሱ ነው የሚያዋጣው የሚል ገዥ አስተሳሰብ አዳብረናል፡፡ አብዛኞቻችን ለችግራችን መንስኤም ሆነ መፍትሔ ሩቅ ነን፡፡ ችግሩ እስከ አፍ ጢማችን ቢያጠልቀንም ይህ ሁሉ ለዕድገት የሚከፈል መስዋዕትነት እንደሆነ ሲነገረን ባናምንበትም ፀጥ ብለን እንሰማለን፡፡ አለን ሁሉን ችለን፡፡ በአዲስ አበባ ቤቶችና መንገዶች ፍርስራሽ ሥር….

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 19, 2014. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.