የአንዷለም አራጌ “ያልተሔደበትን መንገድ” መጽሃፍን የቃኘ መድረክ

(በዘሪሁን ሙሉጌታ) ባለፈው እሁድ በአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት ውስጥ አንድ የመፅሐፍ ምረቃ ፕሮግራም ተካሂዶ ነበር። መፅሐፉ “ያልተሄደበት መንገድ” በሚል ርዕስ በቅርቡ ለሕትመት የበቃ መፅሐፍ ነው። መፅሐፉን ያሳተመው በአሁኑ ወቅት በሽብርተኝነት ክስ ጥፋተኛ ተብሎ የዕድሜ ልክ ፍርደኛ በሆነው የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር አባል የነበረው አንዱአለም አራጌ ነው።

መፅሐፉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሁሉ አቀፍ ህፀፅ የሚዳስስ ታሪክ-ቀመስ የፖለቲካ መፅሐፍ ነው። ከመድረኩ ሲገለፅ እንደሰማነው 10ሺህ ቅጂ ታትሟል። በዕለቱ መፅሐፉን ቀደም ብለው አንብበው አስተያየት እንዲሰጡ የተፈቀደላቸው ሁለት ሰዎች ነበሩ።
አንደኛው የቀድሞው የአረና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ አስራት አብርሃም ሲሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነበር። ሁለቱም አስተያየት ሰጪዎች የመፅሐፉን አንኳር ጉዳይ ነቅሰው በማውጣት የየራሳቸውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዕለቱ የሁለቱም አስተያየት ሰጪዎችን ትኩረት የሳቡት በዋናነት ሦስት ወይም አራት ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው። የመጀመሪያው ጠቅለል ባለ ዕይታ የሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ሲሆን፤ ይህንኑ ደካማ የፖለቲካ ባህልን ተከትለው የሚታዩ ጎጂ ልማዳዊ የፖለቲካ አስተሳሰቦችን ነው። በተለይም የጉልበት ፖለቲካ ባህል፣ የትግራይ ሕዝብና ህወሓትን አለመለያየት፣ የሰላማዊ ትግል የአተገባበር ችግርና የብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት ዙሪያ ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ። በአቶ አስራት አብርሃም እምነት መፅሐፉ የተፃፈው ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ ህሊና በመሆኑ በሚዛናዊ አስተሳሰቦች የታጀበ መሆኑን አስምረውበታል። በአብዛኛዎቹ የመፅሐፉ ገዢ ሃሳቦች እንደሚስማሙበት ገልፀዋል።

የሀገሪቱ ምስቅልቅል የፖለቲካ ጉዞ መነሻ የሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል አለመዳበር መሆኑን፤ በተለይም ከሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ባህልን ለማስረፅ የኦሮሞ ብሔር ባህላዊ አስተዳደር ዘይቤ የሆነውን የገዳ ስርዓት በሀገሪቱ ውስጥ ቢኖርም እንደ ሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል አለመወሰዱ፤ በአንፃሩ የሰሜኑ የጉልበት ፖለቲካ፣ በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ሚዛን ደፍቶ መታየቱ ለሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል አለመዳበር በማሳያነት ቀርቧል።

የኦሮሞ የገዳ ስርዓት ከስልጣን ሽግግር አንፃር ዴሞክራሲያዊ መልኮች ቢኖሩትም የሴቶችን ተሳትፎ ላይ ካለው ውስንነት አንፃር ጠቃሚ የሥልጣን ሽግግር ባህል ተደርጎ በአንዱአለም መፅሐፍ መገለፁ አግባብ መሆኑን አቶ አስራት አስምረውበታል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች በከፊል

የአንዷለም አራጌ “ያልተሔደበትን መንገድ” መጽሃፍ ግምገማን ለመከታተል ከተገኙት ተሳታፊዎች በከፊል


የሰሜን የጉልበት ፖለቲካ እንደ ሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ተደርጎ የተወሰደበትን አግባብ ሲያሳዩም ከመፅሐፉ አንድ ምሳሌ ጠቅሰዋል። ነገሩ የሆነው በ1983 ኢህአዴግ የደርግን ሥርዓት ጥሎ ስልጣን ከያዘ በኋላ ወሎ ውስጥ የኢህአዴግ ካድሬዎች ሕዝቡን ይሰበስቡና “አሁን ነፃ ወጥታችኋል። ደርግም የለም። እስቲ የመሰላችሁን ተናገሩ። አሁን ዴሞክራሲ አለ” ይላሉ። ይሄንን የሰሙ አያ ሙሄ የሚባሉ ሰው እጅ አውጥተው “ለምሳሌ እናንተ [ካድሬዎቹን] ልክ ልካችሁን ብንነግራችሁ ምንም አትሉኝም?” ይሏቸዋል። “ይናገሩ ችግር የለውም” ተባሉ። በዚህ ወቅት አያ ሙሄ “እናንተ ሀገር አስገንጣይ…. ናችሁ” ብለው ቁጭ አሉ። በአያ ሙሄ ንግግር የተበረታቱት አቶ ይመር የሚባሉ ሌላ ሰው፤ “አያ ሙሄ እንዳለው” ብለው ወደ እሳቸው ዞረው ሲያዩ፤ አያ ሙሄ በቦታቸው አልነበሩም። አቶ ይመርም ለመናገር ከተነሱ አይቀር “ዴሞክራሲ አያ ሙሄ እንዳለው ዴሞክራሲ ነው” ብለው ተቀመጡ። ይህ ምሳሌ የሰሜን የጉልበት ፖለቲካና የኢህአዴግ ዴሞክራሲ የይስሙላ ዴሞክራሲ መሆኑ አመላካች እንደሆነም ገልፀዋል። ኢህአዴግ በንድፈ-ሃሳብ ከደርግ ቢለይም በተግባር ግን ብዙ የሚያመሳስለው መገለጫዎች እንዳሉት ነው የገለፁት።

ለጉልበት ፖለቲካ ባህል መዳበር ሀገሪቱ የክርስትና ሃይማኖትን ተቀብላ ተግባራዊ ያደረገችበት ሁኔታ እንደሆነም በመፅሐፉ ውስጥ ትሁት በሆነ አቀራረብ መጠቀሱን ያደነቁት አቶ አስራት፤ በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውስጥ “ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ” የሚለው ብሂል የገዢዎችን የተጠያቂነት የፖለቲካ ስርዓት ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር እንደሆነም ገልፀዋል።

በገጠሪቱ ኢትዮጵያም፤ “ኢህአዴግን ያመጣው እግዚአብሔር ነው” የሚል ኀሳብ መኖሩን ያስታወሱት አቶ አስራት፤ ይህን አመለካከት ተከትሎም “እግዜር ያመጣውን እግዜር ያውርደው” የሚል አረዳድ መኖሩን አስረድተዋል። እንደዚህ ብሎ በሚያስብ ማህበረሰብ ውስጥ ለዴሞክራሲ የሚደረግ ትግልም በጣም አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል። እግዜር መቼ እንደሚያወርደው አይታወቅም። “ምክንያቱም አንዳንድ የቤተ-ክህነት ሰዎች እንደሚሉት ለእግዜር አንድ ሺህ ዓመትም አንድ ቀን ሊሆን ስለሚችል እግዜር እስኪያወርደው መጠበቅ አይገባም” ብለዋል። ፖለቲካ የምድራዊ ጉዳይ በመሆኑ ሰማያዊ ገፅታን ማላበሱ ተገቢ አለመሆኑንም አስምረውበታል።

የሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል የጉልበት በመሆኑም በመፅሐፉ ውስጥ ሦስት አይነት የፖለቲካ አማራጮች ብቻ መኖራቸውን አቶ አስራት ገልፀዋል። እነሱም አርፎ መቀመጥ፣ መሰደድ ወይም መታሰር መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። በዚህ ወቅት መታሰር ደግሞ ጀግንነት መሆኑን በማውሳት “የጀግና ቤቱ እስር ቤት ነው” የሚለውን የአቶ አንዱአለምን ኀሳብ ይበልጥ አጠናክረውታል።

ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ የተለያዩ መሆናቸው በመፅሐፉም መጠቀሱን እንዲሁም እሳቸውም እንደሚያምኑበት ገልፀዋል። “የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አንድ ቢሆኑ፤ እኔም ዛሬ በዚህ መድረክ ላይ ባልተገኘሁ” ያሉት አቶ አስራት “የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል” እንዲሉ ሕወሓትንና የትግራይን ሕዝብ ደባልቆ መመልከት ተገቢ አይደለም ብለዋል። አንድ ሥርዓትና ሕዝብ አንድ የሚሆኑበት አጋጣሚ እንደሌለ በመግለፅ በዚህ በኩል ያለው መደናገር ሊስተካከል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሌላው በመፅሐፉ የተገለፀው የሀገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባህሪና መገለጫ ነው። በሀገሪቱ ሦስት አይነት አደናጋሪ የፓርቲ አይነቶች መኖራቸውም እነሱም በኢህአዴግ የሚመሰረቱና ለኢህአዴግ ዓላማ የቆሙ፣ በንፁህ ህሊና ተቋቁመው እየበረቱ ሲሄዱ ኢህአዴግ ሰርጎ ገብ አስገብቶ ፓርቲዎቹ እንዲከፋፈሉ የሚደረጉና እንዲሁም ሕዝብን መቀስቀስና ማደራጀት ያልቻሉ የሌሎችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተፅዕኖ መቋቋም ያልቻሉ፣ እንዲሁም ኢህአዴግ ከሚሰነዝርባቸው ዱላ የተነሳ ለኢህአዴግ የሚያገለግሉ ፓርቲዎች መኖራቸውን መጠቀሱ ተገቢነት ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዲያስፖራ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ በመፅሐፉ ላይ በእውቀትና ድፍረት ላይ የተመሠረተ ኀሳብና ትችት መቅረቡን ያወሱት አቶ አስራት በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በገንዘብ የሚረዱ በመሆኑ የእነሱን ደካማ ጎን መግለፅ አስቸጋሪ ነው፤ እነሱም ቶሎ የሚገነፍሉ ናቸው ብለዋል። አንዱአለም ግን በህሊናው በመመራት እነሱን መተቸቱ ተገቢ እንደሆነም ገልፀዋል። በዳያስፖራ ዴሞክራሲ ያለገደብ ቢኖርም አጠቃቀሙን ካላወቅንበት በኋላ ለእኛም አስቸጋሪ እንደሆነም አስገንዝበዋል። በዲያስፖራ በዘር፣ በሃይማኖትና በጎጥ ያለው መከፋፈል አስፈሪ ከመሆን አልፎ ተስፋም የሚጣልበት ከመሆን እየራቀ ነው ብለዋል።

ብሔራዊ መግባባት አስፈላጊነት በተመለከተም በመፅሐፉ መገለፁ ተገቢ እንደሆነ ያስረዱት አቶ አስራት የሀገሪቱ ፖለቲካ የጉልበት ፖለቲካ ባህል መሆኑን ተከትሎ ደም መፋሰስ በመፈፀሙ ብሔራዊ የመግባባት ጥያቄ መነሳቱ ተገቢ መሆኑን አውስተዋል። በዚህ ረገድ አንዱአለም ይሄንን የእርቅ ጥያቄ ማንሳቱ በአዎንታዊ ጎኑ የሚታይ እንደሆነና እንደዚህ አይነቱ አመለካከት በእነማንዴላና በእነ ማሕተመ ጋንዲ ይቀነቀን የነበረ አጀንዳ እንደነበረም አስረድተዋል።

በመቀጠል በመፅሐፉ ላይ አስተያየት የሰጠው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ነው። የተመስገን አስተያየቶች አቶ አስራት ከሰጡት አስተያየት ጋር ተቀራራቢነት ያላቸው ነበሩ። መፅሐፉ የተፃፈበት ሁኔታ አስቸጋሪና ውስብስብ በመሆኑ ደካማ ጎኑን ለማንሳት አስቸጋሪ እንደሆነም አመልክቷል። መፅሐፉ በብርድ ልብስ ተከልሎ የተፃፈ ከመሆኑ አንፃር የመፅሐፉን ደካማ ጎን ከማጉላት ይልቅ መፅሐፉ ተፅፎ ለንባብ መብቃቱን በአዎንታዊ ጎኑ መመልከቱ ተገቢ እንደሆነም አስምሮበታል።

መፅሐፉ ምስጢራዊ በሆነ መልኩ በመፃፉና በማረሚያ ቤቱም “መለስ ከልጅነት እስከ እውቀት” ከሚል መፅሐፍ በተለየ ሌሎች ማጣቀሻ መፅሐፎችን ማግኘት ስለማይቻል በማጣቀሻ መፅሐፎች ባይዳብር ላይገርም እንደሚችል ገልጿል።

በመፅሐፉ የሀገሪቱን የፖለቲካ ውጣ ውረድ የተገለፀ ቢሆንም ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ግን ብዙዎች ተስፋ አድርገው እንደነበር፤ ከእነዚህም መካከል አንዱአለምም አንዱ እንደነበር የጠቀሰው ጋዜጠኛ ተመስገን ኢህአዴግ ጫካ በነበረበት ጊዜ የሚያቀርበው ፕሮፓጋንዳ ደርግን አባሮ አራት ኪሎ ቤተ-መንግስት ለመግባት ሳይሆን፤ እየሱስ ክርስቶስን ማርኮ ገነትን ለመቆጣጠር ይመስል ስለነበር በወቅቱ በኢህአዴግ ላይ ተስፋ ማድረጉ ላይገርም ይችላል ብሏል። ነገር ግን ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ ከገሃነብ ያልተሻለ ሀገር ነው ያለን ሲል ገልጿል።

በመፅሐፉ ከቤተ-እምነቶች ጋር ተያይዞ የተነሳው ኀሳብ ትኩረት የሚስብ መሆኑን የጠቀሰው ተመስገን የቤተ-እምነቶች ልዕልና ማጣትን ተከትሎ የአፋሸ አጎንባሽ ልማድ በመስፋፋቱ ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለቄሳር መገዛት መጠቀሱ ተገቢ መሆኑን አስምሮበታል። ይህ ልማድ አሁን ላለው የሴራ ፖለቲካ መስፋፋት አስተዋፅኦ እንዳለውም አመልክቷል።

ህወሓትና የትግራይ ሕዝብን በአንድ ላይ ጨፍልቆ የመግለፅ አዝማሚያ ተገቢ አለመሆኑን የጠቀሰው ተመስገን፤ ኢህአዴግ አድዋ ላይ ማር አላዘነበም። አድዋ ላይ ህወሓትን የደገፈ ይጠቀማል። ጎንደር ላይ ብአዴንን የደገፈ ይጠቀማል። ወለጋም ላይ አባዱላንና ኦህዴድን የተወዳጀ ይጠቀማል እንጂ የአንድ ብሔር የበላይነት አይደለም ብሏል። ነገር ግን በዚህ አመለካከት “የሚጀነጅኑ” መኖራቸውን የጠቀሰው ተመስገን በተለይ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ህወሓትንና የትግራይን ሕዝብ የመቀላቀል ሁኔታ መኖሩንም አውስቷል።

“ነፍጠኛ አማራን አይወክልም ብለን፤ ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ይወክላል የሚል ፖለቲካ መኖር የለበትም” ሲል የገለፀው ተመስገን፤ ፓርቲዎችም ይህንኑ ግልፅ በማድረግ ጉልበተኛውን ስርዓት ከሕዝቡ መለየት አለባቸው ብሏል። ፓርቲዎቹ በ1967 ዓ.ም ህወሓት እንጂ የትግራይ ሕዝብ አልተመሰረተም ብለው አፅንኦት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብሏል።

በትግራይ ሕዝብ ስም የተቋቋሙ ድርጅቶችም የስርዓቱን ተዋንያኖች ከመጥቀም ባለፈ የትግራይን ሕዝብ ተጠቃሚ አለማድረጋቸውንም ጋዜጠኛ ተመስገን ገልጿል።

የአደናጋሪ ፓርቲዎች ውልደትና ሚና ከእነመኢሶን ጊዜ ጀምሮ ያለ ችግር መሆኑን የጠቀሰው ጋዜጠኛ ተመስገን በታጠረ መንገድ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን በተመለከተም በመፅሐፉ የተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ውህደትን የመፍራትና ተያያዥ ችግሮችን መገለፁን አስረድቷል።

አንዱአለም የራሱን ፓርቲ አንድነት ጭምር መተቸቱ ተገቢ እንደነበረም አመልክቷል። በተቃዋሚ ፓርቲዎች ያደፈጠ ሽኩቻ መኖሩም ለፓርቲዎች መዳከም ጉልህ ሚና መጫወቱንም አስረድቷል።

በውጪ ሀገር ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አንዱአለም በመፅሐፉ በሁለት መክፈሉን ያወሳው ተመስገን፤ የመጀመሪያዎቹ ሞክረው፣ ሞክረው ያልተሳካላቸው ኦነግን ጨምሮ መኢሶን፣ ኢህአፓ ሲሆኑ፤ ሁለተኛዎቹ ስሪታቸው እዛው ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ የሆኑ ግንቦት ሰባትን የመሰሉ ናቸው ብሏል። በተለይ “ግንቦት ሰባትን” በተመለከተ አንዱአለም በመፅሐፉ ውስጥ መረር ያለ ነገር መግለፁ ዋጋ ያስከፈለው ጉዳይ በመሆኑ ነው ያለው ተመስገን፤ አንዱአለም “ኢህአዴግ ግንቦት ሰባት ያልዘራውን እንዲያጭድ አድርጎታል” የማለቱ ውጤት ትክክል መሆኑንና በርካቶችንም ለእስር እንዲዳረጉና ለሰላማዊ ትግሉ መዳከምም አስተዋፅኦ ማድረጉን አስረድቷል።

አንዱአለም የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ መሆኑ የሚደገፍ እንደሆነ የጠቀሰው ጋዜጠኛ ተመስገን የሥርዓት ለውጥ በጠመንጃ አፈሙዝ ከመጣ ለውጥ አይመጣም ብሏል። በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታም በአፈሙዝ የመጣው ለውጥም የሥርዓቱን ቁንጮዎች ቱጃር ከማድረግ ባለፈ አስተማማኝ የዴሞክራሲ ስርዓት አለመገንባቱንም አስረድቷል። ይሁን እንጂ የሰላማዊ ትግሉን በአግባቡ በመጠቀም ላይ ችግር መኖሩንም አስረድቷል።

“ዛሬም አስፈቅደን ነው የተቃውሞ ሰልፍ የምናደርገው። ጋዳፊም ሆኑ ሙባረክ በፍቃድ ሰልፍ አይደለም ከስልጣን የተወገዱት። እኛን የሚያስቆጣ በቂ ምክንያት ስላለን የሥርዓት ለውጥ ለማድረግ በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ሰልፍ መውጣት አለብን” ሲል ተመስገን ተናግሯል።

ጋዜጠኛ ተመስገን በዲያስፖራው በኩልም ኢትዮጵያውያን ከተሰደዱ በኋላ በሃይማኖትና በብሔር የሚከፋፈሉበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን አንዱአለም በመፅሐፉም መገለፁ እሱም የሚጋራው ስጋት እንደሆነ ገልጿል።

ክፍፍሉ “የጎንደሬ ገብሬል፣ የትግራይ ማርያም” እስከመባል መድረሱ ዞሮ ዞሮ እየጠቀመ ያለው 22 ዓመት ስልጣን ላይ ለቆየውና ለሌላ 22 ዓመት እየተዘጋጀ ላለው ሥርዓት ነው ብሏል። ስለሆነም በመፅሐፉ ላይ ለዲያስፖራው የተላለፈው መልዕክት ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብሏል።

በመጨረሻም በመፅሐፉ ውስጥ ያልተሄደበት መንገድ ሲባል ሰላማዊ ትግል መሆኑን ነገር ግን ሰላማዊ ትግሉ በሚገባ ያልተተገበረ መሆኑን ለመግለፅ ነው ያለው ተመስገን፤ ለነገዋ ኢትዮጵያ የተቀመጠው የብሔራዊ መግባባት የመውጫ መንገድ (exit strategy) ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግሯል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 27, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.