የአቶ አሳምነው ጽጌ ባለቤት ለመለስ የተማፅኖ ደብዳቤ ጸፉ

Sunday, 05 December 2010 (በታምሩ ጽጌ)

በግንቦት ወር 2000 ዓ.ም. በህቡዕ በመሰባሰብ መንግሥትን በኃይል ለመጣል በመስማማትና ግንቦት 7 ከሚባለው አሸባሪ ቡድን ጋር በመቀላቀል ተሳትፈዋል በሚል አምስት ክስ ተመስርቶባቸው በሁሉም ጥፋተኛ ተብለው በእድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ከተወሰነባቸው መካከል፣ የአቶ አሳምነው ጽጌ ባለቤት ቤታቸው እንዳይወረስባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተማፅኖ ደብዳቤ ጻፉ፡፡

የአቶ አሳምነው ጽጌ ባለቤት ወይዘሮ አልማዝ አስፋው ሕዳር 9 ቀን 2003 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ፤ ‹‹ባለቤቴ አሳምነው ጽጌ በተከሰሰበት የወንጀል ድርጊት በፍርድ ቤት ተወስኖበት እየተቀጣ ይገኛል፡፡ ጥፋቱም ይቅርታ እንዲደረግለት እኔና ልጆቼ እየጠየቅን ባለንበት ሁኔታ ምንም ያላጠፉ ሕፃናት ልጆቼ የሚኖሩበት ሰርቪስ ቤት በሰበታ ከተማ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ እንዲወረስ ስለተወሰነ፣ ከምንኖርበት ቤት በስተቀር ሌላ ትርፍ ቤት የሌለንና ይኼ ቤት ቢወረስ እነኚህ ሕፃናትን ይዤ የምገባበት ምንም አማራጭ ስለሌለኝ፤ መንግሥት መቀጣት ያለበትን ቀጥቶ ምንም የማያውቁ ሕፃናት ልጆች አብረው እንዳይቀጡ እንዲያደርግልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ልጆቼ ከዚህ ቤት ቢወጡና በጎዳና ላይ ቢያድጉ ለአገርም ሆነ ለወገን የሚጠቅሙ ስለማይሆኑ መንግሥት የጠየቅነውን ይቅርታ ከግንዛቤ አስገብቶልን ለእነዚህ ሕፃናት ሲል ቤቱን ከመወረስ እንዲያተርፍልን ስል በድጋሚ በእኔና በሕፃናት ልጆቼ ስም እማፀናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ወይዘሮ አልማዝ እንደገለጹት፤ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት ምንም ዓይነት ገቢ የላቸውም፡፡ በመሆኑም መንግሥት ችግራቸውን ተመልክቶ ይቅርታ እንዲያደርግላቸው በመተማመን ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ደብዳቤ ለመጻፍ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ አሳምነው ጽጌ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው የከፍተኛው ፍርድ ቤት በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ሲወስን፣ ዓቃቤ ሕግ እንዲወረስ የጠየቀውን የጥፋተኛውን ድርሻ (በ200 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሰርቪስ ቤት) ውርስ ውድቅ አድርጎት ነበር፡፡ ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርፍ ቤት ይግባኝ በማለቱ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአቶ አሳምነው ጽጌ ንብረት እንዲወረስ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 9, 2010. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.