የአቶ በረከት የ40 አመት መርገም.

የኔሰው “አበደ እና ራሱን አቃጠለ::” የሆስፒታሉ ጄነራል ማናጀር አቶ መብራቱ መሰቦም ይሄንኑ አረጋገጡ:: የአካባቢው ነዋሪዎች እና ዘመድ አዝማዶቹ ሳይቀሩ ምስክርነታቸውን ለገዢው ኤሌክትሮኒክ “አፍ” ዋልታ ሰጡ:: ኢትዮጵያ የነጻነት እና ዴሞክራሲ ጥያቄዋ ከተመለሰላት እነሆ ሃያ ዓመታት ሞላት:: ፍትሕ ፍለጋ በሚል ‘እብደት’ ዋጋው የናረን ነዳጅ ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ አባክኖ ነፍሱን የሚያጠፋ መኖር የለበትም፤ በኢሕአዴግኛ እሳቤ::
ትግል እንደ እንደነማርታ፣ ዋለልኝ፣ ለገሰ ዜናዊ … ቼጉቬራ እና ሆቺሚኒ ማርክሲዝምን እና ሌኒንዝምን ቸክለህ አንብበህ ካልሆነ በፌስቡክ እና በትዊተር የማይታሰብ እንደሆነ የኢትዮፒካ ሊንኩ ብርሃኔ ንጉሴ ‘አበሰረን’:: በሆሊዎድ እና በምዕራባዊያን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አዕምሮው የተገዛ ትውልድ አብዮት ሊያስንሳ እና ለውጥ ሊያመጣ አይሞክረውም ነው የብሬኒየም( የብርሃኔ የሚሊኒዬም ስሙ ነበር) መከራከርያ ድምዳሜ::
ብሬ ይኽን አስቦ ይሆን ሆሊዉድ ጋዜጣን እና ኢቴቪ ሚዩዚክን ሲያስኮሞኩመን የነበረው? ምናልባት ከአፄ ቴዎድሮስ እና አብዲሳ አጋ ይልቅ ቱፓክ እና የያንጊዜው ፓፍ ዳዲን ያጠምቀን የነበረው ለዛሬው ትንታኔው ለመብቃት አልሞ ይሆናል:: እነተጋዳላይ ሙሴ እና ኃየሎም ወይም አቦይ ስብኸት ከእርሱ ሕያዋን ጅግኖች ቼ እና ሆቺሚኒ ተስተካክለው የጥንቶቹ ባለታሪኮች፤ የኢትዮጵያ ምልክቶች አንሰው ታይተውት ይሆናል:: ማን ያውቃል? ዛሬ ያልተዋረደ፣ መሬት ያልተነጠፈ፣ በእርሱ አባባል የአማራን ገዥ መደብ ያልሆነ የለም::
ሽመልስ ከማል ጋዜጠኞችን እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን ሽብርተኞች ሲያደርጓቸው በቅርቡ ከኬንያ ጋራ በአልሻባብ ጉዳይ እሰጥ-አገባ ውስጥ የገባቸውን ኤርትራን አያይዘው አንስተዋል:: የአልሻባብ አጋር ተብላ ከምትጠረጠረዋ እና የዩኤን.ኤች.ሲ.አር ማዕቀብ ሰለባ ከሆነችው ኤርትራ ጋራ ጋዜጠኞች እና የፓርቲ አመራሮቹን ግንኙነት አላቸው መባሉ አሸባሪነታቸውን ያጎላዋል:: ምክንያቱም የገዢው መንግስት ወዳጅ ሀገሮች “ሽብርተኛ” የሚለው ቃል ሳይቀር ስለሚያስበረግጋቸው የአቶ ሽመልስ ማብራርያ ዋይት ሐውስ ሰተት ብሎ ለመግባት የረቀቀ የፍተሻ ጊዜ አይወስድበትም:: በብሮድካስቲንግ ፕሮፖጋንዳ ቀመር::
ኢሕአዴግ “የሲኒዋን ማዕበል” ድምር ውጤት የማስላት ስህተት በፈጸመበት የ97 ምርጫ ማግስት ሕገ መንግስት ንደዋል ያላቸውን የቅንጅት አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ የሲቪል ማኅበራት ሠራተኞች እና ከተቃዋሚ ፓርቲ ጎራ ተሰልፈዋል ያላቸውን ግለሰቦች በየእስር ቤቱ በማጎር የቤት ሥራውን ከጀመረ ወዲህ አላንቀላፋም::
የድርጅቱ እና የሀገሪቱ አድራጊ- ፈጣሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ደጋግመው እንደነገሩንም ፓርቲያቸው ያለፈውን “ስህተት” አልደገመም:: ፓርቲ አቋቁሞ በአደባባይ ሊቃወማቸው ከተዘጋጀ አንስቶ በመንደር ሻይ ቤት ተቀምጦ በሹክሹክታ መንግስትን ለሚያማ ቅንጣት ክፍተት የሚታሰብ አይደለም:: ወሬ አቀባዮችን በቅጡ አደራጅተዋል::
ኢሕአዴግ በዋናነት የተሸበረባቸውን የተቃዋሚ ድርጅቶች አባላት አደገኛ ቦዘኔ፣ ስግብግብ ነጋዴ፣ ሕገ መንግስት የሚንድ፣ ነፍጠኛ፣ ጥገኛ፣ … የሚል ተቀጥላ ሰጥቶአቸዋል:: ስለዚህ የእነ በረከት ካርታ ሞልቷል:: ቀሪው የቤት ስራ በተፈለገ ጊዜ፣ ስጋት በመጣ ጊዜ መጫወቻውን እየመዘዙ በተፈለገው ሰዐት መውረድ ብቻ ነው::
“ላሟን” እንዳሻቸው የሚያልቡትም ሼኽ መሐመድ አል አሙዲም “ሥነ ሥርዓትን፣ ታጋሽነትን፣ ለአገር ልማት ማሰብን፣ አገር መውደድንና ለአገር ሕይወት መስጠትን ያስተማሩኝ የኢሕአዴግ አባላት ናቸው፤” በማለት ኢሕአዴግ ነፈስ እና ስጋቸው መሆኑን አወጁልን:: በ97 ምርጫ አንዱ ሰለባ እኔ ነበርኩ፡፡ የኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ያየሁበት ጊዜ ነው፡፡ ሲያቀብጠኝ የዓረብ ሳት በመከራየቴ በየአገሩ በሄድኩ ቁጥር የምሰማው እነሱን (ቅንጅትን) ነው፡፡ በረከትም መስኮቱን ከፍቶ ስለሰጣቸው እንደልባቸው ይሠሩ ጀመረ፡፡ ሰዎች ‘ኢሕአዴግን ትወዳለህ’ ይሉኛል እወዳለሁ፤ አራት ነጥብ::” ሲሉ እንቅጩን ነገሩን፡፡
ሼኹ እውነታቸውን ነው፤ 97 ዓ.ም የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያየንበት ጊዜ ነበር:: የሕዝቡ ጥያቄ ግን ከምርጫው ሳይሆን ከውጤቱ እንደነበር ማወቂያ አጡ ወይም የሚነግራቸው ጠፋ እንጂ::
አርቲስት እመቤት ወልደ ገብርኤል፣ ሐረገወይን አሰፋ፣ ደበሽ ተመስገን እና ፍቃዱ ተክለ ማርያም በበረከት ስምኦን የተጻፈው “የሁለት ምርጫዎች ወግ” የተሰኘው መጽሐፉ መስጧቸዋል:: ከዚያም አልፎ በመጽሐፉ ውስጥ መስጠውናል ያሏቸውን ቅንጫቢ ታሪኮች በምረቃው ላይ ለተገኙ ታዳሚዎች አቅርበዋል፡፡ ምናልባት ከሕትመቱ በፊት አንብበውት የአቶ በረከት ቃላት አደራደር፣ አረፍተ ነገር አስራር፣ ታሪክ አሰናሰል ቅንጅትን አዘላለፍ… መሰጧቸው ይሆናል፣ ሊሆን ይችላል:: በቦታውም መገኘቱ ኃጢያት አይደለምም:: ነገር ግን ተመስጥኦውን ለመግለጽ መድረኩ ላይ ለመውጣት ግዳጅ ነበረው ወይ? ያጠያይቃል:: አርቲስት ሲባል ምን እሴት አለው:- ለሀገር፣ ለሕዝብ፣ ለትውልድ? ባለነዋዩ ሲያጎበድድ “አይ ምን ያድርግ ብለህ ነው ሀብቱን እንዳያጣ ብሎ ነው” ስንል፣ ደኻው ላላመነበት ምንጣፍ ሲሆን “አዬ ‘ባክህን አትፍረድ ድኽነት የማያደረገው የለ” ብለን ስናስተዛዘን፣ አርቲስቱ ሞያዊ ዋጋውን አጥቶ ማፈስ-ማጎንበሱን ስንመለከት ምን ልንል ነው?
የ2002ቱ ምርጫ ያለተቀናቃኝ በድል ችቦ ሲጠናቀቅ፣ ብርቱካን በተሰበረ ቅስም ዳግም ይቅርታ ጠይቃ ስትወጣ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች በሺሆች ኪሎ ሜትር ከሕዝቡ ሲርቁ፣ የሕዝቡ እስትንፋስ የሆኑት ጋዜጠኞች “ጥገኝነት ለማግኘት ሲሉ” እግራቸው ወደመራቸው ሲሰደዱ፣ ደበበ እሸቱ በአኬልዳማ ፊልም “መሪ ተዋናይ” ሆኖ ስናየው ሰውነትን ብርክ ብርክ ይላል:: ጀግናው የኢሕአዴግ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ ሀገሪቷን “መቆጣጠሩን” ያረጋግጣል::
ኢሕአዴግ ቻይንኛ “ጥበብንም” በአግባቡ እየተካነበት ነው:: ፎረም እና ሊግ እያለ እንደያኔው እንደጥንቱ አኢሴማ እና አኢወማ ወጣቶችን ማደራጀቱን ተያይዞታል:: በየመንገዱም ካሜራ ተከልኩ ብሎናል:: በቅርቡ ደግሞ በኢንተርኔት መጠቀሚያ ቤቶች ሰዎች የሚጠቀሙትን ዌብ ሳይቶች ከመከታተል ባለፈ እስከ መያዝ መደረሱንም ሰምተናል::
ወደውጭ ሀገር የሚያስደወሉ ቤቶች በየቦታው ተከፍተዋል:: ሕገ ወጥ ስራ ቢሆንም ጨረቃው መንግስታችንን እድሜ እስካራዘመ ድረስ ማንኛውም ጉዳይ ሕጋዊ ነው:: ሕብረተሰቡ የሚጠቀምበት የግል መገልገያ የስልክ መስመሮች፣ ስልኮች፣ ሲም ካርዶች የራሴ ለማለት እንደማያስደፍሩ ከተነቃም ቆይቷል:: በቻይና እና ሕንድ ሀገር ተልከው ስልክን ከመጥለፍ ቀላል ስራ እስከ መንግስትን ሊሸረሽሩ ወይም ሊንዱ የሚችሉ ቃላቶችን እየለቀሙ ግለሰቦችን የሚያስመነጥሩ የህወሀት ታማኝ ስልጡን ተማሪዎች እንዳሉ ብዙ ምስክር አያስፈልግም::
ይኼ ሁሉ እንግዲህ ሰዎች ስለእኔ ምን ያወራሉ ነው:: ኃጢያት ሲበዛ እኮ የአዕምሮ እረፍት አይሰጥም:: ሁሉም ጠላት ይመስላል:: የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሩም፣ የውጭ ሀገር ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ጋዜጠኛውም፣ ጋዜጣ አዟሪው፣ በጣቶቹ የባላ (ቪ) ምልክት ያሳየ መንገደኛም… ጥላውም ሳይቀር ያስፈራዋል:: ስጋት ይጨምራል:: መበርገግ እና መደንገጥ ደግሞ ወደ ስሜታዊ እና ጭፍን እርምጃ ይወስዳል:: እድሜን ብቻ ማራዘም:: በኩነኔ ለሚኖር “አምላክ የሚሉት”፣ የፍርድ ቀን የሚባል ባይኖር እንዴት ደስ ባለው::
ሁሉም ነገር ታፍኗል፤ መተንፈሻ ቀዳዳ የለም:: የሚፈቀደው መስራት፣ መብላት እና መጠጣት ብቻ ነው፤ ከተገኘ:: ነገር ግን ኢሕአዴግ ያልገባው አንድ ነገር አለ፣ የሕዝብ ልብ! ፎረም፣ ሊግ፣ ወሬ አቀባይ፣ አጎብዳጅ፣ የጥቅም ተገዢ እና አባል ማድረግ፣ ማስገደድ፣ አሸባሪ ብሎ መሰየም፣ ማሰር፣ ይቅርታ ማስባል፣ ፊልም ማሰራት ይቻላል:: ልብን ማግኘት ግን ይከብዳል፤ ፈጽሞ አይቻልም:: ሰው የሚያስብውን ማወቅ ይከብዳል:: የቻይና እና ሕንድ ቴክኖሎጂ እዚያ ደረጃ አልደረሰም፣ አይደርስምም::
እነዚህስ ይሁኑ ግድ የለም ብለን ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን ለመቀጠል ስናወጣ ስናወርድ ‘ተጋዳላዩ’፣ ባለስልጣኑ እና ደራሲው አቶ በረከት ስምዖን ህወሀት እና ኢሕአዴግ ለዐርባ ዓመታት እንደሚገዙን ነግረውን አረፉት:: ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ጋዜጣ እና ጋዜጠኛው፣ አርቲስቱ፣ ባለሀብቱ፣ ፌስቡክ እና ትዊተር… በቃ ሁሉም ነገር ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኗል::
40 ዓመታት!!!??? ስለዚህ ተስፋችን ማን ነው???
በጣሊያን ወረራ ወቅት ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ተሰልፈው ፋሺሽት ኢጣሊያን የተዋጉት ቼኮዝሎቫኪያዊው አዶልፍ ፓርለስካ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ Habesska Odyssea /የሐበሻ ጀብዱ/ የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል:: በዚያ ድርሰት ላይ ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ አወዳደቅ ጽፈው ነበር::

የአርሲዋ ትንቢተኛ አሮጊት
ከድሬዳዋ በአውራሪስ ባቡር ተሳፍረን ለገሀር ስንገባ የሀገሬ ልጅ አቶ ሉድሺክ ካልቮዳ ተቀብሎን ቤት እስክንከራይ ድረስ በእንግድነት እንድናርፍ በዋናው አደባባይ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ወሰደን:: ደከም ያለ ንፋስ በመተኛት ላይ ያሉትን ለምለሞቹን እና ረጃጅሞቹን የአዲስ አበባ ባህር ዛፎች ያወዛውዛቸዋል:: ራቅ ብሎ የተራቡ ጅቦች ጩኸት ይሰማል:: ለጅቦቹ ጩኸት የአዲስ አበባ ውሾች ከየጎጆው ከፍ ባለ ጩኸት ይመልሳሉ:: በዚህ መኻል አንዲት ደረቅ ጥይት ጮኸች:: ወዲያው ጅቦችም ውሾችም ዝም አሉ::
የሀገሬ ልጅ ሉድቪክ ካልቮዳ አንዷን ሲጃራ አጭሶ ይተረኩሳትና አንዲት ቃል ሳይተነፍስ ሁለተኛውን ይለኩሳል፤ ሶስተኛውን፣ አራተኛውን:: በቻ በዝምታ ያስባል፤ ይተክዛል:: እንዲህ መተከዙ አይፈረድበትም:: እነሆ የሰኔ ወር መጨርሻ ዓ.ም ነው:: የወልወል ግጭት ጣጣ በጠቅላላው ነፃዋ የኢትዮጵያ ምድር ላይ የጦርነት ዳመናውን ከጣለ ሰነባብቷል:: ይኼ የጦርነት ዳመና መብረቅ ከወለደ ጦርነት መፈንዳቱ ነው:: ጦርነት ተጀመረ ማለት ደግሞ ሉድቪክ ካልቮዳ ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ጉልበትንና ገንዘቡን አፈስሶ የገነባው ድርጅት ፍሬ ማፍሪያው ሲቃረብ በጦርነት እሳት መንደዱ ነው:: ከዚህ ትካዜው ድንገት ብንን ብሎ “ስለ አርሲዋ ትንቢተኛ ሰምተሃል” ሲል ድንገት ጠየቀኝ:: “አልሰማሁም” አልኩት::
ወዲያው የአርሲዋን ትንቢተኛ አሮጊት አስገራሚ ትንቢት ያወጋኝ ጀመር:: ከንግሥት ዘውዲቱ ሞት በኋላ “ሬገንት ባለ ሙሉ ስልጣን እንደራሴ ራስ ተፈሪ መኮንን” ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ዘውድ ሲጭኑ አዲስ አበባ ከምንጊዜውም በላይ ደምቃና አምራ ነበር:: በንግሥናው ስነ ስርዓትም ላይ በርካታ የባህር ማዶ ነገሥታትና መሳፍንት፣ ፕሬዝዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮችና ሌሎች ታላላቅ ሰዎችም ተገኝተው ነበር::
ከንግሥናው ስነ ስርዐት በኋላ በአዲስ አበባ የተለያዩ ትንቢቶች በሰፊው መወራት ጀመሩ:: የአርሲዋ አሮጊት ትንቢት ግን ከሁሉም ትንቢቶች በልጦ ከአዲሱ ንጉሥ ጆሮ ደረሰ:: ትንቢቱም “ኃይለ ሥላሴ የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሥ ነው:: ለረጅም ጊዜ አይገዛም:: በጠላት እጅም ይሞታል:: ዘውዱም እስከመጨረሻው ይወድቃል::” የሚል ነበር::

ይህንና ሌሎችንም የአርሲዋን አሮጊት ትንቢቶች የሰሙት አዲሱ ንጉሥ ለመንግስታቸው ጥሩ መሠረት እንደማይሆኑ ተረድተው አሮጊቷን የአርሲ ትንቢተኛ እንዲያመጡ ወታደሮቻቸውን ወደ አርሲ ቢልኩም፤ አሮጊቷን ትንቢተኛ እንዲያመጡ የተላኩት ወታደሮች አንዳቸውም ሳይመለሱ ቀሩ::
የአዲስ አበባ ክፉ ወሬኞች እንዳወሩት አሮጊቷ ትንቢተኛ ሰማያዊ ኃይል ያላትና የዱር አራዊትንም የማዘዝ ኃይል ስለነበራት ንጉሠ ነገሥቱ የላኳቸውን መልዕክተኛ ወታደሮች እባቦች እየነደፉ፣ አንበሶች እየበሉ በዚያው አስቀሯቸው እያሉ አወሩ::
ጊዜው ይዘግይ እንጂ የአርሲዋ እመቤት ትንቢት ጠብ አላለም:: ንጉሡ በጠላት እጅ ሞቱ፤ የዘውድ ስርዓትም ፍጻሜ ሆነ::
ለዚህ ትውልድም “ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመጨረሻው አምባገነን መሪ ይመስሉኛል:: ኢሕአዴግ ለረጅም ጊዜ አይገዛም:: ጭቆናውም እስከመጨረሻው ይወድቃል::” የሚል አዋቂ ወይም ነቢይ ቢገኝ?

Source: Fetehe Newspaper

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 1, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.