የአብዮትና የረሃብ አዙሪት!

Ethiopian Revolution

The Ethiopia Revolution

አሥራደው (ከፈረንሳይ)

መንደርደሪያ:

I. በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን፤

* « የምትወደንና የምንወድህ ሕዝባችን ሆይ ! » እየተባለ፤

* « አባባ ጃንሆይ የኛ እናት አባት፤

አሳድገውናል በማር በወተት »

* « ኃይለሥላሴ ሃዋርያ፤

የሰላም መሪ ባለሞያ »…..ወዘተ እያለ በችጋር ረገፈ፤

በዚህ የተነሳ፤

* « በደል ጥቃት ለምደህ አልነሳም ካልከኝ፤

ቀሚሴን ልኬያለሁ ሱሪህን ላክልኝ : » የሚለው

የቀድሞ የእተጌ መነን አዳሪ ት/ቤት ሴት ተማሪዎች የትግል ጥሪ :

* በ « አትነሳም ወይ ! አትነሳም ወይ !፤

የግፍ አገዛዝ አይበቃህም ወይ ! »

በቃ፤ ተነስ ! በቃ፤ ተነስ !

በሚለው የተማሪዎች ትግል ተጀምሮ እንዲያ እንዲያ እያለ፤ በወሎ ድርቅና

ረሃብ ታጅቦ፤ አብዮት ፈነዳ፤ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተሰናበቱ፤

II. ወታደር ሥልጣን ያዘ፤

* ያለምንም ደም እንከኗ ይውደም፤

በቀና መንፈስ ኢትዮጵያ ትቅደም፤ ……..ብሎ፤ ወደ

* የፍየል ወጠጤ ልቡ ያበጠበት፤

እንዋጋ ብሎ ለነብር ላከበት፤….. በሚለው ተተካ :

ከፎካሪው ዓላማ በተቃረነ መልኩ በመጠቀም ተዜመ፤ ተደለቀ፤ …. ከዚያም፤

ዲሞን በዲሞትፈር ! አናርኪስቶች አብዮቱን አይቀለብሱም!

አብዮቱ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት ተሸጋግሯል !……..ወዘተ እያለ ቆይቶ ሲጨነግፍ በዚያው በጨንጋፋ ማሕጸን ውስጥ፤ ላላ የአልባኒያ ሶሻልዝም አቀንቃኝ ተረግዞ፤

III. የወያኔ አብዮት ተወለደ፤

* ከአሁን በኋላ ጠመንጃና መድፍ ተቀጥቅጠው ማረሻ ይሆናለ! በተባለ ማግስት ሻዕቢያና ወያኔ ሲሰርቁ ሳይሆን፤ ሲካፈሉ ስለተጣሉ በባድመ የጦርነት እልቂት ሆነ፤ ወገኖቻችን እንደ ቅጠል ረገፉ፤ ሃብት ባከነ:: አሁን ማን ይሙት : ምክንያቱ ለኛ የማይነገር ሆኖባቸው እንጂ የበሬ ግንባር በማታክል መሬት ያ ሁሉ ወገናችን ከሁለቱም በኩል ማለቅ ነበረበት ?

* ከአሁን በኋላ ሕዝቦች በቀን ሦስቴ ይበላሉ! ተባለ፤ ሦስቴ ቀርቶ አንደም ጭንቅ ሆኖ አረፈው::

* ከአሁን በኋላ በቆሎ ከራሳችን ተርፎ ወደ ውጪ እንልካለን! በተባለ ማግስት የልመና አቁማዳ ተይዞ በዓለም ዙሪያ ቀፈፋ ተጀመረ::

* የግልገል ጊቤ ግድብ የሃይል አቅርቦታችንን አሟልቶ ወደ ውጪ እንልካለን! ተብሎ ከበሮ በተደለቀ ማግስት ግድቡ ፍርስርስ ተስፋውም ፍርክስክስ አለና ሕዝቡን ጨለማ ወረሰው::

* ከአሁን በኋላ አገሩን በዘይት እናጥለቀልቀዋለን! በተባለ ማግስት፤ ሕዝቦች የኑሮ ዘይት እያዳለጣቸው እንክትክት፤ የሚላስ የሚቀመስ ጥፍት፤ አለ

(በነገራችን ላይ ሕዝቦች የሚለው የነሱ አጠራር የብዙዎች ብዙ በመሆኑ አጸያፊ ሲሆን በሰዋሰዋዊ ብዜት አሕዛብ ነጠላ ሲሆን ሕዝብ ደግሞ ብዙ በመሆኑ ሌላ ብዜት አያሻውም፤ እየተንኳኩ ለማደንቆር ካልሆነ በቀር)

* ስኳር የጠፋው ገበሬው ስኳር መላስ ስለጀመረ ነው! ባለ ማግስት ስኳር ከከተማ እብስ….ወዘተ እረ ስንቱ !!

እሳቸውን አይቶ መለስ ከማለት ይልቅ፤ አይቶ አያልቅበት ብለን ብንጠራቸው በይበልጥ ምግባራቸውንና ሰብዕናቸውን ቁልጭ አርጎ የሚያሳይ ይመስለኛል ::

* አሁን ደግሞ፤ የአባይ ግድብ ሕዳሴ ይለናል! ጉድ እኮ ነው: ዲሪቶ ተለብሶ

አቁማዳ ተሸክሞ እየቀፈፉ ሕዳሴ! « ቂጥ ገልቦ ክንብንብ! » ይላችኋል ይች ናት:.

እስቲ የዓባይን ግድብ በተመለከተ ጥቂት ጥያቄዎችን እናንሳ፤

1. ለምን የአምስት ዓመት የዕድገትና Transformation እቅድ ውስጥ ሳይገባ ቀረ?

2. ዓባይን የመገደቡ ጉዳይ ለምን አሁን ተነሳ ?

3. ለአቶ መለስ ይችን ሃሳብ ማን ሹክ አላቸው ?

4. በዚህ ጫጫታ የወያኔ ትርፍ ምንድነው ?

5. ለምን ዘርፈ ብዙ የሆነ ግድብ እንዳይሠራ ተፈለገ ?

6. ለምን ሱዳን ጠረፍ ላይ ሄድ መገንባት አስፈለገ ?

7. ለምን እጅግ ትልቅ ግድብ እንዲሆን ተመረጠ ?.…ወዘተ

ቁጥር 3 እና 6 ን ጨረፍ አድርጌ የቀሩትን ለናንተ እተዋለሁ፤ ተወያዩበት !

ቁ.3 የሰሜን አፍሪካና የአረብ አገር አምባ ገነኖችን የመታው ሕዝባዊ አውሎ ንፋስ እንቅልፍ የነሳው እሳቸውንና እሳቸውን መሰል አምባ ገነኖችን ብቻ ሳይሆን በአረብ አገራት ዙሪያዋን የተከበበችው እስራኤልንም ጭምር በይበልጥ አስጨንቋታል፤ በተለይ የግብጽና የእስራኤል የሠላም ስምምነት ይናጋ ይሆናል የሚለው አንደ ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ፤ ግብፆች ከኢራኖች ጋር እያደረጉ ያለት መቀራረብ፤ ሁለቱ የፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅቶች በግብጽ አማካኝነት እርቅ ማድረጋቸው…. ወዘተ የእስራኤልን ስጋት ጨምረዋል::

ታዲያ ይህን ስጋት ለማስተንፈስና ግብጽን ተይ የምትሠሪው ሥራ ለኛ አይበጅም ለማለት አማራጭ ሲፈለግ፤ ግብጽን ከአናት ሆና የምታስፈራራ አገር ኢትዮጵያ ተገኘች፤ ፈጥነው እስራኤሎች ለአቶ መለስ ይችን ሹክ ሲሎቸው፤ ዘወትር ባገኙት አጋጣሚ ላይ ቶሎ ፊጢጥ የሚለት የዘወትር የገጠመኝ ተጠቃሚው አቶ መለስ (opportunist)፤ አንካሳ ድሮ ሳትቀድማቸው 20 ዓመት ሙለ ትዝ ያሌላቸውን ኢትዮጵያዊነትና የዓባይን ግድብ እንገንባ፤ አታሞ መደለቅና ማስደለቅ ጀመሩ::

ይቺ የፖለቲካ ቁማር በመጠኑም ቢሆን ለጊዜው የሠራች ይመስላል፤ ግብጾች ጉዳዩ ስላሳሰባችው መልክተኞች ልከው ከአቶ መለስ ጋር እንዲነጋገሩ በማድረግ፤ የግድቡ ሥራ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ተደርጓል፤ ፤ ይህ ሁለ ውሳኔ የተደረገው በአንድ ፈላጭ ቆራጩ አቶ መለስ ዜናዊ ብቻ ሲሆን፤ በፓርላማ እንደ በግ አጉረው፤ እሳቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲሳደቡና ሲያንጓጥጡ፤ ለመሳቅ፤ ሲደነፉ ለማጨብጨብ፤ ከድሃው ወገናችን በተሰበሰበ ቀረጥ የደለበ ደሞዝ የሚከፈላቸው የፓርላማ አባል ተብዬዎች የሚያውቁት አንድም ነገር የለም ::

ሌላው አስቂኝ ድራማ ግብጾች በግንባታው ሥራ እንዲሳተፉ የተጠየቁት ሲሆን፤ ስንት ዘመን የቅኝ ገዢዎች የዓባይ ውሃ ስምምነት እንዳይለወጥብን እያለ ሲጮሁ የነበሩ፤ ማን ይሙት ዛሬ ለኛ ቅን አሳቢ ሆነው፤ ለግንባታው ወይስ ለጥፋቱ ሊሳተፉ?!

ነገሩ ሁላ የአንባ ገነን የጣር የነብስ አውጪኝ ጩኸት ሲሆን፤ በአንፃሩ አሳዛኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ የኑሮው ውድነት አልበቃ ብሎት፤ አፍንጫውን እየተሰነገ፤ ለዓባይ ግድብ ገንዘብ አዋጣ መባለነው::

ዓባይ እንዳይገደብ የሚፈልግ አንድም ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር እርግርጠኛ ነኝ፤ ግን እንደ ብል ከስር ስር ያገኙትን ጭዳ የሚያደርጉ፤ ነቀዞች (ሙሰኞች) አገሪቷን እያነቀዙ ባለበት፤ አገሪቱ የማፍያዎች መፈልፈያ በሆነችበት ወቅት፤ እንዴት ተደርጎ ይህ ዕቅድ በሥራ ላይ ይውላል?

በተጨማሪ የአቶ መለስን የተለመደ ደባ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው፤ «እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው» እንዲሉ፤

ካልጠፋ ቦታ ሱዳን ጠረፍ ላይ ሄደው፤ የዓባይን ግድብ ካልገነባን ብለው፤ የኑሮ ውድነት የፈነካከተውን ቁስለኛ ሕዝብ ውጥር አርግርው በመያዝ፤ ቁም ስቅለን ማሳየታቸው ነው ::

ዓባይ መገንባቱ ባልከፋ፤ « አክሱም ለመሃል አገር ሰው ምኑ ነው?» እንዳለን ነገ ደግሞ የአባይ ግድብ ለሱዳን እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምኑ ነው ቢለንስ? እሳቸው እንደሆነ በርበሬ ከመቀንጠስ ይልቅ አገር መቀንጠስ ይቀላቸዋል፤ አያስነጥሳቸው ዓይናቸው አይቀላ::

ታዲያ መጠርጠር ይነሰን? « ያልጠረጠረ ተመነጠረ » እንዲለ ሆኖ አይደል: ከወታደር አገዛዝ የከፋ: ምንም ቢሆን አይመጣም በማለት: ሕዝብ እጁን ዘርግቶ ቢቀበላቸው ዛሬ ጀርባው ላይ ፊጢጥ ብለው: ለም መሬቱን ለባዕድ እየቸበቸቡ እሱን በችጋር የሚያስለበልቡት::

ከዓባይ ግድብ ከተል አርገው እስራኤሎች ከፍልስጤማውያን ወንድሞቻቸው ለመለየት የገነቡት የሃፍረት ግንብ (Le mur de la honte) ዓይነት በኛና በትግራይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መሃል ትልቅ የዘር ግንብ እንዲገነባ በዕቅድ ላይ ሳይሆን ይቀራል?! “ጠርጥር እሸቱ ሳይጠጥር!!”

ሰሞኑን ደግሞ ሳር ቅጠለ ሳይቀር ሽብርተኛ ሆነ ብለው፤ ተሸብረው ያሸብራለ::

ጋዜጠኞች ሽብርተኛ፤ እከሌ ሽብርተኛ፤ እነእከሌ ሽብርተኛ፤ ግንቦት7 ሽብርተኛ፤ ብለው ፈራርጀው ሲያበቁ፤ « የዘመድ ጥል የስጋ ትል » ሆነባቸው መሰለኝ እንደ እንቁላል አቅፎ የፈለፈላቸው ሻዕቢያን በሽብርተኝነት አለመፈረጃቸውን ስንመለከት፤ የአቶ መለስ ዜናዊና የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ጥል ለኛ ለማስመሰያ እንጂ ለብቻቸው ቢገናኙ፤ ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው አጁሃ ከሜአለሃ ከተባባለ በኋላ ለመቶ አመት የሰጡንን የቤት ሥራ እምን እንዳደረሱት ቁጭ ብለው እየተሳሳቁ እንደሚያወጉ አንጠራጠርም::

«ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል» ይሎችኋል ይቺ ናት:: ለነገሩ አልኩ እንጂ፤ የኛ ሰው ነቄ ነው እንኳን ይችን የዝንብ ጠንጋራ በጨረቃ ነቅሶ ያወጣል ::

የሚያሳዝነው፤ ከሚወራው ሁለ አንደ እንኳን በተግባር የማይውልባት አገራችን፤ መከረኛው ሕዝብ፤ ኑሮን ለመኖር ሳይሆን፤ ለመከራ የተፈጠረ፤ በስሙ እየማለና እየነገደ በጀርባው ላይ የሚያናጥሩበትን ተሸክሞ ጀርባው እንደጎበጠ ወደ መቃብር የሚያዘግም፤ በምድራዊ ገሃነም ውስጥ የሚኖር፤ ያልታደለ የመከራ አምራቾች አስተናጋጅ መሆኑ ነው::

በየጊዜው ከ5 እስከ7 ሚሉዮን የሚሆን ሕዝብ መራቡ አሳሳቢ እንዳልሆነ በመቁጠር፤ እንደነሱ አባባል የተለመደ «Normal» መሆኑን የወያኔ ባለስልጣናት ባንድ ወቅት ገልጸዋል፤ እንግዲህ እነዚህ ወገኖቻችን የወያኔ የመለመኛ አቁማዳ ለመሙያ እንደ መያዣ እንዲያገለግለ የተፈረደባቸው መሆኑን ኢትዮጵያዊ ሁለ ሊረዳው ይገባል::

ወያኔ ለሕዝባችን መራብ ተጠያቂ ነው ! በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፤ እንደ ወያኔ ዘመን ያህል ዕርዳታ የዘነበበት፤ ብድር የተነከርንበት ጊዜ የለም፤ ታዲያ ይህ ሁለ ሆኖ የረሃብና የአብዮት አዙሪት አላበቃም !

በሰለጠነው ዓለም ውሻና ድመት…..እንኳን ተራቡ ተብሎ ለእንስሳት መብት ሲጮህ: በኛ አገር የሰው ልጅ ሲራብ የተለመደ ነው ይባላል :: …………

(ክፍል ሁለት)

የመጀመሪያዋ ሰንካላ አብዮት: ፊውዳልን ኮንና፤ ከበርቴን አስጨንቃ፤ ምሁራንን ተጠራጥራ፤ ባለሞያዎችን አግልላ፤ በወታደሮች ስትመራ: ገና ከጥዋቱ አንካሳ እንደነበረች የተረዱ ጥቂቶች አልነበሩም ::

የአገርን ድንበር ከውጪ ጠላት የሚከላከለው፤ የውስጥ ጸጥታንና: ሠላምን ያስከብር የነበረው ወታደር: እጁን በየቦታው መክተት ጀመረ፤ ድርሻውን አልፎ: የሰው ድርሻ መንጠቅ አዘወተረ፤ ርሕራሄ ጎደለው፤ እራሱን ወደደ፤ ስልጣንን ሙጥኝ በማለት፤ ከያለ ምንም ደም: ወደ ፍየል ወጠጤ፤ ከዚያም ወደ ቀይ ሽብር በማለፍ፤ እጁን በደም ታጠበ:: ይህ ሁለ ሲሆን በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እየማለ ነበር ::

ታዲያ ሕዝቡ ለሱ ብላ የመጣች አብዮት: መልሳ ለምን እሱኑ እንደምትለበልበው: ሊገባው አልቻለም ነበር ::

ነባራዊ የተፈጥሮ ሕግጋት በቅዠት ይለወጡ ይመስል: ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ዳዳው፤ ሽማግላዎችና አሮጊቶች ተናቁ፤ አባትና እናት ተሰደቡ፤ የማንነታችን ጥንስስ፤ የመወለዳችን ምንጭ፤ እንዳልሆኑ ክብር ተነፈጉ፤ ሃዘናቸው ጸና፤ የወለዱትን ላለመርገም ሲሉ፤ ዕንባ ባቆረዘዙ ዓይኖቻቸው አንጋጠው: ፈጣሪያቸውን ተማጠኑ፤ አይመኙት ምኞት ሞትን ተመኙ::

ገበሬው እንደዘራ: አብዮት ይፈነዳና የዘራው በእርሻ ላይ ይቀራል፤ ቤት ለመሥራት ያቀደ: መገንባት እንደጀመረ አብዮት ይፈነዳና ሳይኖርበት ይፈርሳል፤ ልጁን ለማስተማር ያቀደ: ትምህርት ቤት እንደላከ አብዮት ልጁን በልታበት የወላድ መሃን ይሆናል፤ ትዳር ያማረው: ትዳር ለመመስረት ቀለበት እንዳሰረ: አብዮት ይፈነዳና ወንደ ላጤ: ሴተ ላጤ እንደሆኑ ዘመናት ይቆጠራሉ፤ የፊቱ ቆዳ ይሸበሸባል: ፀጉሩ ይለወጣል፤ የወጣትነት ዘመኑ እየሸሸ: የሽምግልና ወይም የአሮጊትነት ጥላ: ማንዣበብ ይጀምራል::

የተወለደ ሕፃን ቢኖር የአባትና የእናት ፍቅር ሳይቀበል፤ የመወለድ ምሥጢሩን ሳይረዳ፤ አብዮት ፈንድታ እናትና አባቱን ትበላለች ::

የአብዮት ጭራቅነት በዚህ ብቻ አላበቃም፤ ባልን ከሚስት፤ ወንድምን ከእህት፤ ጓደኛን ከጓደኛው፤ ጎረቤትን ከጎረቤት፤ ዘመድን ከዘመድ አናክሳ፤ አከላቷን በደም ታጠበች፤ ባሕር ቀላ፤ ወንዝ ደፈረሰ፤ ሰማይ አጉረመረመ፤ ተፈጥሮ ተቆጣ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ፤ የክት ልብስ ጥበብ ኩታውን አስወልቃ፤ የሃዘን ልብስ ጥቁር ጠል አስለበሰችው:: ታዲያ በዚህ ሁሉ ድርጊቷ ተኩራራች እንጂ አላዘነችም::

ሁለተኛዋ ሰንካላ የወያኔ (ኢህአዳግ) አብዮት ደግሞ፤ የአልባኒያ ሶሻሊዝም ቆቧን ቀዳ፤ የኮምኒዝም ጥብቆዋን አውልቃ፤ አዛዦቿ አሜሪካና እንግሊዞች፤ የመጸወቷትን ዲሪቶ ደርታ፤ ከረባቷን ሸምቅቃ፤ ብቅ ብትልም፤ አመጣጧ ቂም አርግዛ በደል ለመውድ በመሆኑ፤ ጓድችን በታጋዮች፤ ክፍለ ሃገርን በክልል፤ ኢትዮጵያዊነትን በጎሳ፤ ከፋፍላ « የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል » የሚል መፈክሯን እያቅራራች: የኢትዮጵያን ሕዝብ በጎሳ፤ በሃይማኖትና በዘር፤ በመከፋፈል፤ ወገን ከወገን በማናከስ፤ ድንበር በማስገሰስ፤ የበደል ክምር ከማሪ በመሆን 20 ዓመታት ብታስቆጥርም አሁንም ስሟ አብዮት ነው::

ለመሆኑ የሕዝብን ልብና ዕምነት ሳያገኙ አገርን ማስተዳደር ይቻል ይሆን?! እስከመቼ?!

ሲምሉበትና ሲገዘቱበት የነበረው የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ አሁንም ከዳር ሆኖ የሁለተኛዋ ሰንካላ አብዮት ፍርፋሪ ናፋቂ የሚሆነውስ እስከመቼ ነው?!

በአገራችን ፖለቲከኞችና ሕዝቡ ከተለያዩ ሰንበትበት ብሏል፤ ፖለቲከኞች ሕዝቡን ወደ ጎን ትተው በየጎራው በመሆን የየራሳቸውን የግል አጀንዳ እሰጥ አገባ እንጂ፤ የወቅቱ የሕዝብ ስቃይና እለት በእለት በመቦርቦርና በመገዝገዝ ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ሕልውና ጉዳይ ወደ ጎን ትተውታል ::

በወቅቱ ያለትን ማህበራዊ፤ አገራዊው፤ ክፍለ ዓለማዊና ዓለማአቀፋዊ ሁኔታዎችን በማጤን፤ ሕዝቡን አቻችሎ በማሰባሰብ ለድል የሚያበቃ የትግልና የድርጊት ቀመር በመንደፍ ታግሎ በማታገል፤ ለድል እንዲበቃ ከማድረግ ይልቅ፤ ወያኔ በሚሰጣቸው አጀንዳ ላይ በመነታረክ ጊዜያቸውን ማጥፋት መርጠዋል::

ጥቂቶቹም አምስት ዓመት ጭንቅላታቸውን በአሸዋ ውስጥ ቀብረው ከከረሙ በኋላ፤ ከወያኔ ጋር «የዝም በል ስምምነት» በመፈራረም በወያኔ ምክር ቤት ውስጥ ሲጢጥ፤ ሲጢጥ፤ የሚል ወንበር ለማግኘት በሽቅድምድም ላይ እንዳለ የወያኔ የቆሎ ሽርክነት አብቅቶ፤ ወያኔ ኪሱን በቆሎ ሞልቶ ሲያጓምጥ፤ የነሱን ኪስ ምች መቶት እያዛጉ ላላ አምስት ዓመት ያንቀላፋለ::

ሕዝቡም የጠባብ ፖለቲከኞችና፤ የስልጣን ቋማጮች የፖለቲካ ቅርሻት ስለሰለቸው፤ በነሱ የፖለቲካ ቅርጫ ውስጥ ገብቶ የአገሩን አንድነት ላለመቀራመትና በፖለቲካ ድጥ ዳግመኛ ላለመንሸራተት እንቢ ብሎል::

ያም ሆኖ ሁለተኛዋ ሰንካላ የወያኔ (ኢህአዴግ) አብዮት፤ ሕዝብን ሳታቅፍ በጎሰኝነት ከዘራ ማነካከሷን ቀጥላለች::

– ወታደር ተበተነ፤ አብዮት ነው !

– ሕዝብ ተፈናቀለ፤ አብዮት ነው !

– ተማሪ ሞተ፤ አብዮት ነው !

– ምሐር ተባረረ፤ አብዮት ነው !

– ወጣቱ ሥራ አጥ ሆነ፤ አብዮት ነው !

– ሠራተኛ ተበተነ፤ አብዮት ነው !

– ሕዝብ በረሃብ አለቀ፤ አብዮት ነው !

ለሕዝብ ሳይሆን በሕዝብ ላይ የመጣ አብዮት !!

ማለቂያ የላለው የአብዮትና የረሃብ አዙሪት! እንዲያው ብቻ በአብዮትና በረሃብ ቀለበት ዙሪያ መሽከርከር፤ በሄደበት መመለስ መመላለስ፤ በጀመሩበት መጨረስ፤ ድግም ድግግም፤ ማለቂያ የላለው የማነህ ሰሞነኛ አብዮት !!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያና ሕዝቧን ይባርክ !!

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 28, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.