የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ ቃለ ምልልስ ሲዳሰስ

በእስክንድር ነጋ (አዲስ አበባ)

«ገራገር ይመስላል» አለኝ አንድ ወዳጄ ትክ ብሎ ምስላቸውን በመመልከት። «ውዥምዥም ሳይሆን አይቀርም» ብሎ ምስሉ ያረፈበትን የአውራአምባ ጋዜጣ ሲያቀብለኝ ከት ብዬ ሳቅኹኝ። የአማርኛ ችሎታው ላቅ ያለ ነው። የእኔ አላዋቂነት መቀለጃው ነው።

«ደግሞ ዛሬ ምን የሚሉትን አማርኛ ይዘህብኝ መጣህ?»

«ውዥምዥም 3 እና 4 ድርብርብ ፍቺዎች ሊሰጡት ይችላሉ» አለኝ ቀብረር ብሎ፤ እንደልማዱ ብዙ ቀልዶብኝ ትርጉሙን ሊነግረኝ ዳር ዳር እያለ።

«ንፉግ ለግሶ ቢሰጥ፣ እጁ ይንቀጥቀጥ፤ ሲባል አልሰማህም እንዴ?…» ብዬ ጎንተል አደረግኹት፤ በአበው ተረት። ኮርኩሮ አሳቀው።

«በል እሺ…» አለኝ እጁን እያወዛወዘ። «ለዛሬ ተምረሃል። ውዥምዥም፣ ረጅም ማለት ነው።»

ቃሏን መዘገብዃት። ገበያ ላይ ያሉት የአማርኛ መዝገበ ቃላት ውስጥ አላየዃትም። ወዳጄ ግዕዝ ይችላል። በዚያ ላይ የከሳቴ ብርሃን መዝገበ ቃላት እንዳለው አውቃለኹ። ሁለቱን እየገጣጠመ አንድ የእውቀት ባህር ሆኗል።

«ገራገር ሁሉ ውዥምዥም ነው እንዴ?» አልኹት። ጋዜጣው ላይ ያለው ምስል የተቀመጠ ሰው ነው።

«በዓይነ ህሊናዬ ስዬው ነው።»

ጨዋታችን ስለዶናልድ ቡዝ ነው፤ ገራገር ስለሚመስሉት የኃያሏ አሜሪካ አምባሳደር።

ቡዝ፣ አዲስ አበባ የገቡት የ2ዐዐ2 ምርጫ ሰሞን እንደነበር አስታውሳለሁ። የዛሬ 12 ወራት ገደማ መሆኑ ነው። አይገርምም? ግዜው ይሮጣል። ያኔ አዲስ አበባ በምርጫ ሽርጉድ ደማምቃ ነበር። «መቼ መጣሽ ሙሽራ፣ መቼ ቆረጠምሽ ሽምብራ?» እንዳይባሉ በመስጋት፣ ያን ሰሞን ከጋዜጠኞች ተደብቀው መሰነባበታቸውን ሰምቻለኹ። መንግሥታቸው ጠጠር ባሉ ቃላት ምርጫውን ያብጠለጠለበት መግለጫ በቀጥታ ከዋሽንግተን ነበር የወጣው፤ ባልተለመደ አሰራር።

አምባሳደር ቡዝ፣ ይኸው መጋቢት 21 ቀን 2ዐዐ3 ዓ.ም ለዓመት የዘለቀውን ታላቁን ፀጥታቸውን ሰብረዋል። ጥሩ ነው ብዬ አምናለኹ። «ብዙ ዝምታ፣ ይሆናል በሽታ» ሲሉ እሰማለኹና አበው።

እንኳን ደህና መጡ፣ አምባሳደር ቡዝ!! ድምፅዎን በመስማቴ ከልብ ተደስቻለሁ፤ በተናገሩት ሁሉ ባልስማማም።

ኢትዮጵያና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከመሰረቱ ከ1ዐዐ ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ላይቤሪያ ብቻ ነች የምትቀድመን፤ በአፍሪቃ። የማንዴላ ደቡብ አፍሪቃ ሂሳብ ውስጥ ሳትገባ፣ ሌሎቹን ቢያንስ በግማሽ ምዕተ ዓመት እንቀድማቸዋለን።

የመጀመሪያዋን አምባሳደር የላከችው ግን፣ ከ5ዐ ዓመታት በኋላ ነበር፤ በ1946 (በእኛ አቆጣጠር፤ በእነሱ በ1953።) እስከዚያ፣ ኤምባሲዎቿ በቆንስላ ደረጃ ነበር የተመሩት። በዘመኑ ለጥቁር ሕዝቦች ከነበረው ኋላ ቀር አስተሳሰብ አኳያ፣ የሚያስወቅሳት አይደለም። እንዲያውም፣ ከአውሮፓ ሀገራት ጋር ስትነፃፀር፣ የኢትዮጵያ አጋር ነበረች፤ ወዳጅነቱ በቁሳዊ ድጋፍ ለመገለፅ ባይበቃም።

በ1946 ዓ.ም ሁሉ ነገር ተለዋወጠ። ከአንድ ዓመት በፊት ከኤርትራ ጋር የተዋሀደችው ኢትዮጵያ፣ የአሜሪካ ጦር አስመራ ላይ ዘመናዊ የስለላ መሣሪያዎች እንዲተክል ፈቀደች። በሺህ የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮችም ለጥበቃ ወደሀገር ውስጥ ገብተው የቃኘው ጦር ሰፈርን አቋቋሙ። እንደድንገት፣ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ እጅግ ተፈላጊ ሀገር ሆነች። የመጀመሪያው አምባሳደር ሹመትም የለውጡ ማብሰሪያ ሆነ።

ለሚቀጥሉት 15 ዓመታት፣ አሜሪካ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት አንደበተ ርቱዕ ጠበቃና ብርቱ ጠባቂ ሆነች። እነመንግሥቱ ንዋይ በ1953 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሲቃጡ፣ አምባሳደሯ ሙከራውን ለማክሸፍ እንደ አንድ የንጉሡ ታማኝ ወታደር ተግተው ላይ ታች ብለዋል። ውጥናቸው በመሳካቱም፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአሜሪካ ላይ ቂም ቋጠሩ። አምባሳደሩ ፈፅመው ባላሰቡት መንገድ ለ«ያ ትውልድ» ግራ አክራሪነት ምንጭና ምክንያት ሆኑ።

በ195ዐዎቹ መጨረሻ፣ የቴክኖሎጂ ምጥቀት የኢትዮጵያን ተፈላጊነት አመከነው። የአሜሪካ ብቃት፣ ከኢትዮጵያ ተራሮች ላይ ከተቃኘ የአየር ሞገድ ጠለፋ ወደ ሳተላይት ስለላ አደገ። ያለምንም ማስጠንቀቂያ፣ በኢትዮጵያ ላይ እንደበረዶ መቀዝቀዝ ጀመረች። የኢትዮጵያ ጉዳይ ሲነሳ፣ የአሜሪካ ባለሥልጣናት በተቀመጡበት እንቅልፍ ይዟቸው ይሄዳል ተብሎ እስከመቀለድ ደረሰ። ኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት የምታቀርባቸው የወታደራዊ ዕርዳታ ጥያቄዎችን ምላሽ ተነፈጋቸው። ቢቸግረው፣ በጎረቤት ሀገር ሱማሊያ የወታደራዊ ኃይል እመርታ ስጋት ያደረበት የአፄ ኃይለሥላፄሴ መንግሥት፣ የቻይናን በር እስከማንኳኳት ደረሰ። በግዜው ስልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዚዳንት ኒክሰን ግን፣ ጨርሰውም ወሬውን ስለመስማታቸው ምልክት ሳይሰጡ ቀሩ።

የቃኘው ጦር ሰፈር መቋቋም ግን፣ በኢትዮጵያ ላይ ከባድ መዘዝ አስከተለ።

የአሜሪካ ጦር በኢትዮጵያ የጦር ሰፈር ማቋቋሙ ያስቆጣት ሶቭየትሕብረት፣ 15 ዓመታታ ባልሞላ ግዜ ውስጥ ሱማሊያን እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወታደራዊ ዕርዳታ አጎረፈችላት።

በአንፃሩ ቃኘው ከተቋቋመ ከ1946 እስከ 197ዐ ዓ.ም በነበሩት 24 ዓመታት፣ የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የ648 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ሰጠ። ከዚህ ውስጥ 366 ሚሊዮን ዶላሩ የኢኮኖሚና የምግብ ዕርዳታ ሲሆን፣ ቀሪው 282 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ዕርዳታ ነበር። ጠቅላላው ዕርዳታ በ24 ዓመቱ ውስጥ ሲበተን፣ በዓመት ከ3ዐ ሚሊዮን ዶላር አልሆነም። ወታደራዊ ዕርዳታው በየዓመቱ በአማካኝ 1ዐ ሚሊዮን ዶላር እንኳን አልደረሰም።

በ196ዐዎቹ መጨረሻ፣ ሱማሊያ የጦር ዝግጅቷን አጠናቀቀች። በጥንቃቄ የገነባችውን የበላይነትም በጦር ሜዳ ላይ በቀላሉ አስመሰከረች፡፡ ለ1 አስርተ ዓመታት ያለጠንካራ አጋር ያዘገመችው ኢትዮጵያ፣ የግዛቷን 1/3ኛ መሬት ለሱማሊያ ጦር በጥቂት ወራት አስረከበች፤ በ1969። ወዳጆቿም፣ ጠላቶቿም ፍፃሜዋን ተነበዩ፤ ከልብም፣ ከአንገትም በላይ የኃዘን እንጉርጉሮ አወረዱላት።

ሟርቱ ግን ሳይሰምር ቀረ። ኢትዮጵያ በተዓምር ከሞት አፋፍ ተመለሰች፤ በሶቭየት ሕብረት የ2 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ዕርዳታ ታግዛ።

የኢትዮጵያ ሕልውና ከባድ ፈተና ላይ በወደቀበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ታሪካዊዋ የኢትዮጵያ አጋር ሆና የኖረችው አሜሪካ የውሃ ሽታ ሆና ቀረች። ይባሱንም፣ ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል የሚያስፈልጓትን የጦር አውሮፕላኖችና የጦር መሣሪያዎች እንዳይሸጡላት በማገድ ታላቅ የታሪክ ሕፀፅ ፈፀመች።

ለዚህ ልብ ሰባሪ ውሳኔ ያቀረበችው ምክንያት፣ ደርግ የፈፀማቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነበር፤ ያውም ከቀይ ሽብር በፊት የነበሩትን (አሰቃቂው ቀይ ሽብር ከወረራው በኋላ ነበር የተከሰተው።)

የዚህ ታሪክ ሸክምና ዕዳ ያለባቸው አምባሳደር ቡዝ፣ ባፈለው ሳምንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰብዓዊ መብት ጥያቄን አቃለው ማለፋቸው ፈፅሞ አላስደሰተኝም። የዛሬ 35 ዓመታት ከኢትዮጵያ ሕልውና በላይ ገዝፎ የታየን ነገር፤ ዛሬ ላይ «ተጨማሪ ውይይት የሚጠይቅ ጉዳይ» ብቻ ለመሆን እንዴት እንደበቃ ቢያስረዱን ከልብ እደሰታለኹ።

ለነገሩ፣ ከእሳቸው በፊት የነበሩት አምባሳደር ያማማቶም ይሄንኑ ሲሉ አስታውሳለሁ። ከያማማቶ በፊት የነበሩት ቪኪ ሀድልስቶንማ ጭራሽ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመኖሩም ይጠራጠራሉ ተብለው እስከመታማት ደርሰዋል። በጥቅሉ፣ በኢሕአዴግ ዘመን ያየናቸው 7 የአሜሪካ አምባሳደሮች —– ማርክ ባስ፣ አይርቪን ሂክስ፣ ዴቪድ ሺን፣ ኦሪያላ ብራዚል፣ ቪኪ ሃድልስቶን፣ ዶናልድ ያማማቶና ዶናልድ ቡዝ—- በሙሉ «የሰብዓዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል እየተወያየን ነው» ሲሉን ኖረዋል። በትዕግስት እንድንጠብቅም ተማፅነውናል፤ ጠብቀናልም።

ችግሩ፣ ከማርክ ባስ እስከ ዶናልድ ቡዝ ይኸው 2ዐ ዓመታት ማለፋቸው ነው። የተሻሻለ ነገር ግን የለም። እንዲያውም፣ በተቃራኒው በእጅጉ መበላሸታቸውን ነው በመስኩ የተደረጉ ጥናቶች ሁሉ የሚያመለክቱት። ፍሪደም ሀውስን (Freedom House) ብቻ እንኳን እንደምሳሌ ብጠቅስ፣ ኢትዮጵያ «በከፊል ነፃነት ካለባት ሃገር» ወደ «ነፃነት የሌለበት ሃገር» ዝቅ ብላለች፡፡ ወደ ደርግ ዘመን ለመመለስ መንገድ ላይ ነን ማለት ነው።

ታዲያ፣ ከ2ዐ ዐመት በኋላ፣ የአሜሪካ አምባሳደሮችን ተደጋጋሚ ቃላትና ባዶ ተስፋ ማድመጥ ሰለቸን ብንል ይበዛብናል? ሚዛናዊነታችንንስ ያስተናል?

ቅንነቱንና ቁርጠኝነቱ ካለ፣ ለሰብዓዊ መብትም ሆነ በአጠቃላይ ለዴሞክራታይዜሽን ሂደቱ አሜሪካ ልታበረክት የምትችለውን አስተዋፅኦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ «ዲፕሎማቲክ ስትራቴጂ (Diplomatic Strategy)$ በሚል ባወጣው መጣጥፉ ላይ ቁልጭ ብሎ ተቀምጦ ይገኛል።

እንዲህ ይላል፡- The interaction of strength and diplomacy can be illustrated by a comparison to labor negotiations. If a labor union is not willing to strike, then the union is not going anywhere because management has absolutely no incentive to agree to union demands. On the other hand, if management is not wiling to take a strike, then the company will be walked all over by the labor union, and management will be forced to agree to any demand the union makes. The same concept applies to diplomatic negotiations.

ኢሕአዴግ ዲሞክራሲ እውን እንዳይሆን ግትር ካደረገው ምክንያቶች መካከል የዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ እርምጃ እንደማይወስድበት ያለው እምነት በዋናነት የሚጠቀስ ነው።

ይሄን ደንቃራ ለማስወገድ ደግሞ፣ አሜሪካ ልትጫወት የምትችለው የመሪነት ሚና ግልፅ ነው። የጎደለው ፍላጎት ብቻ ነው። አባምሳደር ቡዝም ሆኑ በዋሽንግተን ያሉ አለቆቻቸው፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ይሄን ሐቅ እንደሚረዱት ጠንቅቀው ሊረዱት ይገባል።

… ይቀጥላል

ፀሐፊውን serk27@gmail.com ማግኘት ይቻላል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 6, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.