የኛ ችግር፤ በተለይ የግንቦት ሰባት፤ “ከኤርትራ ሽሽት” በየኔታ ተክሌ

ከዚያ ወደዚህ ስመለስ፤

ከአንድ ወር ቆይታ በሁዋላ ወደምኖርበት ከተማ ተመልሼ ከአውሮፕላን ዱብ ከማለቴ ነው ከአውሮፕላን ጣቢያ የተቀበለኝ ሰው “ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ሞቱ እየተባለ ይወራል” ብሎ ያረዳኝ። ይሄ ወዳጄ ዜናውን ሲሰብርልኝ፤ ስሜቴ ሁሉ ተሰባበረ። የኛ አገር ፖለቲካ ሁኔታ የባሰውን ጨለመብኝ። ሰማይ ተደፋብኝ። አዘንኩኝ። ደበረኝ። ለመሆኑ እኚህ 30 አመት ኢትዮጵያን የወጉና ምናልባትም የአገራችንን ያለፉትን 21 አመታት ታሪክ የቀያየረውን ሂደት የመሩ፤ አሁንም በብዙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እንደወዳጅ የማይታዩ ሰው ሞት ለምን አስደነገጠኝ? ብዙ ምስጢር የለውም። ባጭሩ የፕሬዚደንት ኢሳይያስ መሞት፤ የኤርትራን ፖለቲካ ሊለውጠው፤ ያ ደግሞ በተራው የኛን ያማራጭ ድርጅቶች (ተቃዋሚዎች የሚለውን ቃል አልወደውም) ጉዞ የባሰ ሊያዘበራርቀው ወይንም ሊያጨልመው ይችላልና የሚል ስጋት ነው።
ኢሳያስ ቢሞቱ የሚተኩት ሰዎች ፕሬዚዳንት ኢሳያስ እስካሁን ሲከተሉት የነበረውን አካሄድ ይገፉበታል ብዬ አልጠብቅም። ከመለስ ጋር መስማማት ወይንም መግባባት ሊኖርባቸው ይችላል። ምንም ከመለስ ጋር ቢስማሙ፤ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች በሙሉ አሳልፈው ይሰጣሉ የሚል ፍርሀት የለኝም። ቢያደርጉትም ግን አይገርመኝም። ምክንያቱም የምንጠያየቅበት ይሄ ነው የሚባል ይፋዊ ውል የለንምና። ይሁን እንጂ፤ የኢሕአዴግን ተቃዋሚዎች ማስጠለል ይቀጥላሉ ብየም አላስብም። ስለዚህ እኚህ ሰው ድንገት ቢሞቱ ምን ሊውጠን ነው፤? ከኤርትራ/ሻእቢያስ የተሻለ ምን ምርጫ አለን? ለዚህ ነው ባጭሩ የኢሳያስ ሞት ጭምጭምታ ያስደነገጠኝ። በዚህ ላይ ደግሞ፤ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ያለውን የኛን አብይ አማራጭ ፖለቲካ ድርጅቶች ፍራቻ አክሉበት። ስለዚህም …

ኤርትራን እያጣናት ነው፤ በራሳችን ስንፍናና ገብጋባነት

ይሄንን በተለይ ትልቁ ተቃዋሚ ድርጅታችን ግንቦት ሰባት የተረዳው አይመስለኝም። ከተረዳውም ፈርቷል ይሆን? በጸጥታና እጁን አጣጥፎም ባይሆን፤ ባደባባይ ምንም ሳይለንና ሳይጠቀምበት የኤርትራ እድል ሲያመልጠው እየተመለከትን ነው። እንዳቅሙ እየጣረ የሚገኘው ባለ4 አመቱ ግንቦት 7 ደግሞ እንዲሁ እንዳለ ባለ 40 አመቱን ድርጅት ሊሆን ይችላል። አሁን ባለው አካሄድ፤ ኤርትራ እያመለጠችን ነው ብዬ አምናለሁ። ኤርትራን አታንሱብን፤ በኤርትራ በኩል ትግል ከቶም አይታሰብም ብለው የሚያስቡት፤ የዚህ ጽሁፍ ጉዳይ አይደሉም። ይሄ ጽሁፍ የሚሞግተው፤ በኤርትራ በኩል ትንሽ ተስፋ አለ ወይንም ነበር ነገር ግን እነዚህ እነዚህ ችግሮች አሉና መስተካከል አለባቸው ብለው ለሚከራከሩ ወይንም ኤርትራ ውስጥ ሄደን እንዲህ ያለ አፈናና በደል ተፈጸመብን ብለው ምሬታቸውን ለሚዘበዝቡት ነው። ስለዚህ ኤርትራን እንደ እድል ለማትመለከቱ፤ በዚህ ጽሁፍ ላይ ጊዜ አታጥፉ።

አንዳንድ ሰዎች፤ እዚያው ኤርትራ ሄደው የሞከሩትን ጨምሮ፤ በኤርትራ በኩል የሚታገሉ ድርጅቶች ውጤታማ ያለመሆን ችግር የሚመነጨው ከኤርትራ እንደሆነ ይናገራሉ። ከዚህ ቀደም ጥቁር ጫካ እያለ ይጽፍ የነበረ ሰው፤ እንዲሁም አቶ ሙሴ ተገኝ ጥቂቶቹ ናቸው። ይሁን እንጂ በኔና እዚያ ተጉዘው በመጡ ሌሎች ሰዎች አመለካከት ዋናው ችግር ያለው ከኤርትራ ሳይሆን፤ ከኛም ነው። የኤርትራ መንግስት ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም፤ ያለውን ሁሉ ቢያቀርብም፤ ከአውሮፓም ከአሜሪካም ወደኤርትራ የሚሄዱት ሰዎች፤ እንዲሁም ከኢትዮጵያም ወደኤርትራ የሚመጡት ርስ በርሳቸው እየተከፋፈሉ፤ እያሴሩና ለሴራ ተባባሪ እየሆኑ መስራት እያቃታቸው፤ በሁዋላ ላይ ወደውጭ የመውጣት እድል ሲያገኙ፤ ሌላ ሰው እንኳን ተራውን እንዳይሞክር፤ ያስጠጋቸውን የኤርትራ መንግስት ወደማውገዝ ይዘላሉ። የኤርትራን ገንዘብ ቁርጥም አድርገው የበሉ ሁሉ በኤርትራ እርዳታ፤ አውሮፓ ወይንም አሜሪካን ሲገቡ ኤርትራን መሳደብ ይጀምራሉ። ችግሩ ግን በከፊል የራሳቸው የተቃዋሚዎች የግል ችግር፤ ወይንም ስልጣን ወዳድነት፤ ጽኑ የስልጣን ፍትወት እንጂ ሙሉ በሙሉ የኤርትራ አይደለም ብዬ አምናለሁ።

ችግሩ የነሱ ብቻ ነው ወይስ የኛም?

የኛ ተቃዋሚዎች ወይንም ግለሰቦች በዚህ በኤርትራ በኩል ስለሚደረገው ትግል የሚያቀርቡት አንዱ ክስ፤ “ሻእቢያ አያፈናፍነንም፤ እንደፈለግነው እንድንሆን ነጻነት አይሰጠንም፤ እንደውም ሀቀኛ ተቃዋሚዎችን ያስራል፤ ይገርፋል፤ ይገድላል” የሚለው ነው። በመሰረቱ ኤርትራም ይሁን ሌላ ሉአላዊ አገር፤ እንኩዋንስ ለትጥቅ ትግል፤ ለጉብኝትም ስንሄድበት፤ ያገራቸውን ልማድና ህግ ልናከብር ተስማምተን ስለሆነ፤ ኤርትራ ገብተን በነጻነት እንዳንንቀሳቀስ አደረጉን የሚለው ክስ ተቀባይነት የለውም። መጀመሪያውንም ስንሄድ ያንን አውቀን ነውና። ችግሩ ወዲህ ነው። ለምሳሌ፤ ኮሎኔል ታደሰ ይፈታ ብሎ መጠየቅ አንድ ነገር ነው። ያሉ ችግሮችን ማስቀመጥና የመፍትሄ ሀሳቦችን መሰንዘርም በጎ ተግባር ነው። እከሌ የተባለው የናንተ መኮንን ተነስቶ በምትኩ ሌላ ሰው ካልሾማችሁ አብረን አንሰራም ማለት ግን አግባብ አይደለም። ከኛ በኩል የምናቀርባቸው አንዳንድ ጥያቄዎች የኤርትራን ሉአላዊነት የሚጻረሩ ናቸው። ኤርትራን እንደመንግስት ካየን፤ ልክ ካናዳን ወይንም አሜሪካን ወይንም እንግሊዝን በምናይበት አይን ማየት አለብን። የነዚህን አገራት ሉአላዊነት የሚጻረሩ ስራዎች እንደማንሰራው ሁሉ፤ ኢህአዴግን ለመውጋትም ይሁን ለመርሳት ወደኤርትራ ካቀናን፤ የኤርትራን ሉአላዊነት ከሚጻረሩ ድርጊቶች መቆጠብ አለብን። በኔና በኛ አስተያየት፤ ትልቁ ችግር ያለው፤ የኛ ሰዎችና ድርጅቶች ጋር ነው።

ከተለያዩ ኤርትራ ደርሰው ከመጡ ታጋዮች ጠይቄ እንደተረዳሁት፤ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ያለው ዋንኛ ችግር፤ እንደ ግንቦት ሰባት ወይም ጥምረት ያሉ ፕሮፌሽናል አገር ወዳድ ፖለቲከኞች ወይም ድርጅቶች በግልጽ በከፍተኛ ልኡካን ደረጃ ግንኙነት ለመፍጠር ከመሞከርና ከኤርትራ ጋር በይፋ በልብ ሙሉነት ከመዋዋል ፈንታ፤ ከመስራትና ከመተባበር ይልቅ፤ ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት በምስጢርና በጥርጣሬ ወይንም በግማሽ ልብ ወይንም ፈራ ተባ እያሉ መያዛቸው ይመስለኛል። እንደግንቦት ሰባት ያለው ተቃዋሚው ሀይል፤ እንደ ድርጅት፤ እንደ አንድ አገር-ወካይ ድርጅት፤ እንደ አንድ ለስልጣን የሚታገል ድርጅት፤ (ከዚህ ቀደም ከግንቦት ሰባት ውስጥ የማይመቸኝ አባባል የምንታገለው ለስልጣን አይደለም የሚለው ነው ብዬ ጽፌያለሁ። ሳይያዝ የሚተላለፍ ስልጣን የለምና)፤ በልበ ሙሉነት ከኤርትራ ጋር ስለሚኖረን የወደፊት ግንኙነት ለሻእቢያና ለኤርትራ ግልጽ ፖሊሲ አላቀረብንላቸውም። ምናልባት ከዚህ ቀደም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዳመኑት፤ እሳቸው አንድ ሁለት ግዜ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ሊሆን ይችላል። እስከምናውቀው ድረስ ግን ያኔም ቢሆን በምስጢርና መጀመሪያ ላልታወቀ፤ በሁዋላ ግን ለተገለጠ ተልእኮ እንጂ፤ ባደባባይ በተለይ ግንቦት ሰባት ከኤርትራ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት ግልጽ አቋማቸውን አሳውቀው አልሄዱም። ይሄ ምክንያቱ ፍራቻ፤ ጥርጣሬና ስጋት ይመስላል። ግንቦት 7 ወኔው አጠረው እንጂ፤ በብዙ መልኩ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ወክሎ፡ ከኤርትራ ጋራ ወደፊት ሕዝቡ የሚያድሰው ወይም የሚያፈርሰው፤ ውል መዋዋል ይችላል ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም፤ ታጋይ ይመርጣል እንጂ አይመረጥም።

ግንቦት ሰባት፤ ህዝብና ኤርትራ

ከኤርትራ ጋር በተያያዘ አልፍ አልፎ በግንቦት ሰባት አመራር አባላት የተደረጉትን ቃለምልልሶች ተመልክቻለሁ። እነዚያም ድፍን ናቸው። ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ከኤርትራም ይሁን ከማንም ጋር እንሰራለን የሚል ጠቅላላ ፖሊሲ ነው። እንጂ፤ የኤርትራን አገርንት አውቀው፤ ሀሰብና የባህር በር ገለመሌ የሚለውን ጉዳይ ትተው፤ አብሮ እንደጎረቤት አገሮች መኖር እንችላለን በሚል ሀሳብ ላይ ሳይሆን፤ ወደፊት የኢትዮጵያ ህዝብ ይወስናል በሚል ሀሳብ ላይ የተመሰረተ ነው። ይሄ እንዳይሆን አንዱ የግንቦት ስጋት ህዝቡ ይመስለኛል። በፖለቲካ ውስጥ ህዝብ ተከታይ ነው። መሪዎቹ በዚህ ሂድ ካላሉት፤ ህዝብ የሚሄድበት መንገድ ወደገደል ወይንም የራሱን ጥቅም ወደሚጎዳም አቅጣጫ ሊሆን ይችላል። በርግጥ ሕዝብ የመሳሳት መብት አለው። ይሁን እንጂ፤ በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶች የተነሳ ህዝብ ባይቀበለውም እንኩዋን፤ እኛ የኤርትራንም ይሁን ሌላ የሆነን መንገድ ተስፋ ካደረግንበት ወይንም ተስፋ ካየንበት፤ ከመጠቀም ወደሁዋላ ማለት የለብንም። እኛ እርግጠኛ መሆን ወይንም በደንብ ማሰብ ያለብን፤ ያለህዝቡ እሺታም ቢሆን፤ መንገዱ ያስኬዳልን? ለድልስ ያበቃናልን የሚለውን ነው። ህዝብ ቀስ በቀስ እየተቀበለው ሊመጣ ይችላል። አሁን ባይቀበለውም እንኩዋን፤ ካሸነፍን ቀስ እያለ ይቀበለዋል። ከዚህ ቀደም ከሰፊው እውቀቴ ቀድቼ እንደጻፍኩት ደግሞ “ድርጅት ደግሞ ህዝቡን ቀድሞ መምራት አለበት። የኢትዮጵያ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የኤርትራን መንገድ ሊያጸድቅ አይችልም። መንገዱን ቀዶ መሞከርና ሄዶ ማሳየት የድርጅቶች ፈንታ ነው። የሚደግፍ ይደግፋል። የሚቃወምም ይቃወማል። ግንቦት ሰባት ግን የኤርትራን መንገድ ማፈርም መፍራትም የለበትም።” አሁንም ይሄን እደግመዋለሁ።

እስካሁን ምን ሆነ? ወደፊትስ ምን ይዘየድ?

ቀደም ባለው ግዜ ከሞላ ጎደል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኤርትራን እንደደመኛና ጸረ-ኢትዮጵያ አድርገው ቢያዩም፤ በዚህ አስር አመት ውስጥ፤ በህዝብ ዘንድ ኤርትራን እንደወዳጅ ባይሆንም፤ እንደ አማራጭ የማየቱ ሁኔታ እያደገ መጥቷል ማለት ይቻላል። ለዚህም የብዙ ኢትዮጵያዊያን የኤርትራን ቴሌቪዥን መመልከት አንድ ማስረጃ ነው። ለሽሽትም ይሁን ለትግል ብዙ ኢትዮጵያዊያን ወደኤርትራ የሚያደርጉት ጉዞም ሌላ ማስረጃ ነው። ስለዚህም፤ ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት ይፋዊና በመገናኛ ብዙሀን በደንብ የምንለፍፈው መሆን አለበት እንጂ የምናፍርበት፤ የምደብቀው ወይንም የምንሸማቀቅበት መሆን የለበትም ብለን እናምናለን። የኛ ሀሳብ እንዲህ ነው፤ ከበሰለውና ከመደበኛው ተቃዋሚው ሀይል በኩል፤ በግልጽ ወደኤርትራ ተጉዞ ከኤርትራ መንግስት ጋር የሚመክርና ለህዝብ ይፋ የሆነ ፖለቲካዊ ውል የሚዋዋል ልኡክ ያስፈልጋል። ከኤርትራ ጋር፤ ወደፊት ስራችንን የምመዝንበት፤ የምንለካበት፤ ህዝብም ተከብሯል ወይንም አልተከበረም ብሎ የሚታዘብበት፤ ግልጽ ፖለቲካዊ ውል መግባት አለብን ብለን እናምናለን። ያ ውል ወይንም ሰነድ ወይንም ግልጽ ስምምነት ነው ኤርትራ በርግጥም ከተቃዋሚው ጋር ለመስራት ፍላጎት አላት ወይንስ የላትም የሚያሰኘን። በርግጥ ባዶ ውል ብቻውን የሚፈይደው ነገር የለም። ይሁን እንጂ፤ ለመጪው ጉዟችን ይፋ ውል በጣም ወሳኝ ነው። ያለ ይፋ ውል ወደኤርትራ የምናደርገው ጉዞ ያው ያለፉትን አስራ13 አመታት የተጓዝንበትን አይነት ነው የሚሆነው።

“ሻእቢያ አይረዳም፤ እንዲያውም የኢትዮጵያን ታጋዮች እየጠበቀ ሽባ ያደርጋል” የሚሉትን ሀይሎች ክስ ችላ ባንለውም፤ ሻእቢያዎቹ በይፋ ባይሆንም፤ “እኛ ሁሉን አድርገናል ነገር ግን ተቃዋሚዎቹ ናቸው ደካሞች” የሚሉት መልስም ችላ የሚሉት አይደለም። “እኛ ክላሽ፤ ፓስፖርት፤ ስልጠና፤ ስንቅ አቀረብን፤ እነሱ ግን አልሰሩበትም” ነው የሚሉን። ኮሎኔል መንግስቱ እኛ ትጥቅና ስንቅ ሰጠን፤ እንግዲህ ወኔና ልብ አናስታጥቅ እንዳሉት መሆኑ ነው። በነገራችን ላይ የሻእቢያ ተንኮልና አሻጥር ኤርትራ ደርሰው በመጡ (አንዳንዶቹ የበሉበትን የኤርትራ ወጭት ሰባሪዎች ናቸው) ተነግሯል። የኤርትራ ውለታ ግን እስአከአሁን በብዛት አልተነገረም። ምናልባት የሚያበረውን ተዋጊ ጀት ወደኤርትራ ይዞ የገባውና ካናዳ የመጣው የቀድሞ የአይር ሀይል አብራሪ፤ ሻምበል ተሾመ ተንኮሉ ብቻ ነው የኤርትራን ውለታ የመሰከረው። ኤርትራ ለኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሀይሎች ያደረገችው እርዳታ፤ ሻእቢያና ወያኔ ወደጫካ ሲገቡ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ካገኙት እርዳታ የላቀ ነው። ኤርትራ ረዳችም አልረዳችም፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን በተገቢው መንገድ ረድታለች አልረዳችም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል፤ ለዚህም ይሁን ለሌሎች ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች በከፊልም ቢሆን መልስ የሚሆን፤ ነገ ውዝግብ ቢፈጠር የምንከራከርበት፤ ወይንም ከጊዜ በሁዋላ ኤርትራን ራሷን ቃሏን እንዳልጠበቀች የምንከስበት፤ በግልጽ የምንነጋገርበት ይፋ የሆነ ውል ወይንም ሰነድ የት አለንና ነው? የእስካሁኑ ጉዟችን ሰነድ የለሽ ወይንም ውል የለሽ ነው። ይሄ መታረም አለበት።

አሁንም ግልጽና ይፋዊ ውል ያስፈልገናል

በዚህ ከኤርትራ ጋር በሚኖረን ግንኙነት ላይ ከዚህ በፊት ጽፌያለሁ። ይሄ የነዚያ ቅጣይ ተደርጎ ይወሰድልኝ። ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት ይፋና በይፋ ውል መሆን ስለሚገባበት አግባብ ብዙ ምክንያት መደርደር እንችላለን። አንዱ፤ ይፋ የሆነ ውል፤ ከዚህ ከምእራቡ ዓለምም ይሁን ከአፍሪካ ወደኤርትራ ለምንሄደውና የምእራብ አገር ዜግነት ላለንም ይሁን ለሌለን ሰዎች፤ ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ ለሚነሳብን ክስ እንደመከላከያ ያገለግላል። ኤርትራ ከአልሸባብም ይሁን ከሌሎች ሽብርተኞች ጋር በተያያዘ በሚነሳባት ክስ አብረን ተከሳሽ አንሆንም። ብንከሰስም እንኩዋን፤ አስቀድመን አላማችንንና ከኤርትራ ጋር ያለንን ግንኙነት ግልጽ ካደረግነው የከፋ ውንጀላ ሊደርስብን አይችልም። ፖለቲካዊ አካሄዳችን ግን ስውር ከሆነ፤ አንዳንዶቻችንን፤ በተለይ የምእራብ አገር ፓስፖርት ወይንም በቤተሰብ፤ ማለትም በሚስቶቻችን ወይንም በልጆቻችን ከምእራብ አገራት ጋር ትስስር የሌላቸውን ለጥቃት ያጋልጣል)። ይልቅስ ከኤርትራ ጋር የሚኖረን ግልጽ ውል፤ ስራችንን ለሚመለከታቸው አለማቀፍ ተቋማት (የተባበሩት መንግስታት፤ የአፍሪካ ህብረት) አሳውቀን በልበሙሉነት ለመንቀሳቀስ ያግዘናል። በኤርትራ ጉዳይ ላይ፤ ለጠላት ህቡእ ብንሆን ለወገኖቻችንና ለምእራባዊያን ህቡእ መሆን ግን የምንችል አይመስለኝም። መሆንም የለብንም።

ስለህቡእነት ሲነሳ፤ ስለኛ ድርጅቶች የሚያናድዱኝ አንዳንድ ነገሮች አሉ፤ ብዙ ነገሮቻችን ከራሳችን ሰዎች ድብቅ ናቸው፤ ከጠላት ግን ድብቅ አይደሉም። ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት ራሱ አንድ ምሳሌ ነው። ጠላት በሚገባ ያውቀዋል ወይም ባያውቀውም እንደሚያውቀው በግምትና በስማ በለውም ቢሆን ያስወራል። ወዳጆቻችን ግን ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ከጠላት ሰምተው እንደሁ እንጂ ከፖለቲካ ድርጅቶቻች ተነግሯቸው የሚያውቁት ውሱን ነው። ሁለተኛ፤ አንዳንድ ነገሮችን እስመጨረሻው ልንደብቃቸው ካልቻልን፤ ወዳጆቻችን ከኛ ከራሳችን ማወቅ አለባቸው። ለምሳሌ፤ የፖለቲካ መሪዎቻችን በምስጢር ወደኤርትራ ከተጓዙ፤ የፖለቲካ መሪዎቻችን በከፍተኛ ምስጢር የተያዘ የኤርትራ ጉዞ ጉዳይ ይፋ ወጥቶ እኛን መሳቂያ፤ ወዳጆቻችንን ደግሞ ማሸማቀቂያ ከሚሆን፤ መጀመሪያዉኑ ከኤርትራ ጋር የመስራቱን ጉዳይ ምስጢር አለማድረግ ጥሩ መፍትሄ ነው። የተቃዋሚ መሪዎች እንደአመራር ወደኤርትራ ስንገባም ስንወጣም በይፋ ቢሆን መልካም ነው። ሌሎች ሚስጥራዊ ጥብቅ ተልእኮዎች እንደተጠበቁ ሆነው ማለቴ ነው። ለዚህ በይፋ ከሌላ አገር ጋር ስለመስራት ጉዳይ ደግሞ የኤርትራ ተቃዋሚዎች ራሳቸው ጥሩ ምሳሌ ናቸው። ራሳቸው የኤርትራ ተቃዋሚዎች እኮ ከኢህአዴግ ጋር መስራታቸውን ምስጢር አላደረጉትም። ስለዚህ እኛ ለምን እና ከማን ምስጢር እናደርገዋለን??

ለነገሩ፤ ወያኔም ነቅቶብናል

ለነገሩ ወያኔዎቹም ከኤርትራ ጋር መስራት ሐጢያት ነው ብለን እንደምናስብና እንደምናፍርበት ነቅተውብናን መሰል እየደጋገሙ የሚከሱን በሁለት ነገሮች ነው፤ ከሻእቢያ ጋር በመስራትና በሽብርተኝነት። ኢህአዴግ ብቻ አይደለም፤ አልፎ አልፎ ኢህአዴግን የሚተቹ እንደሪፖርተሩ አማረ አረጋዊ አይነት የኢህአዴግ ደጋፊዎችም ያገር ቤቱንም ያገርውጩንም ተቃዋሚ የሚከሱበት አንዱ ነገር፤ ሻእቢያን በግልጽ አለማውገዝ ወይንም ከሻእቢያ ጋር መስራት ነው። እኛም በተደጋጋሚ እንዳይታወቅብን የምንሸሸው ይሄንን ከኤርትራ ጋር የመስራትን ጉዳይ ነው። በመሰረቱ እኛ ለኢትዮጵያ ያለን ፍቅር የኤርትራ ተቃዋሚዎች ለኤርትራ ካላቸው ፍቅር የሚያንስ አይመስለኝም። የኤርትራ ተቃዋሚዎች ደግሞ በግልጽና በአዋጅ ከአዲስ አበባ አዋሳ፡ ከአዲስ አበባ መቀለ እየተመላለሱ ይሰራሉ። ስለዚህ እኛ ከኤርትራ ጋር መስራትን ልናፍርበትም ልንሸሸውም አይገባም። በውልና በሰነድ በይፋ እስከሆነ ድረስ። እንጂ ኤርትራንና ሻእቢያን ስንከስ መኖር የለብንም። አንዳንዶቹ የኛ ተቃዋሚዎችማ በተቃራኒው፤ አሁንም ከ21 አመት በሁዋላ፤ ሻእቢያን ነው እንደጠላት አድርገው ቀን ተሌት የሚያወሩት። እነአረና ትግራይን አልፈርድባቸውም፤ የትግራይን ህዝብ የሚማርኩበት ሌላ አጀንዳም የላቸውምና። የመድረክ ግን ምን ይባላል? ጭራሹኑ ብሶበት፤ ከጉራፈርዳ ወረዳ በሺዎች የሚቆጠሩ አማሮች ተባረሩ፤ የተወሰኑትም በመኢአድ ቢሮ ተጠልለዋል የሚል ዜና እየተሰራጨ፤ “በሁመራ አካባቢ ወርቅ የሚያወጡ 250 ኢትዮጵያውያን በሻእቢያ ተጠለፉ” ብሎ መግለጫ ያወጣል። አሁን በማዬ ሞት ይሄ የራሱ የኢህአዴግ እንጂ የመድረክ ችግር ሊሆን ይገባል? የሆነ ሆኖ …

በዚህ ሁኔታ ውስጥ፤ እንደግንቦት ሰባት ያሉ ጠንካራና ታላላቅ ድርጅቶች፤ ኤርትራን በይፋ እንደአጋር አውቀውና ይዘው፤ በግልጽ ውል ወደኤርትራ ገብተው ግንባር ቢመሰርቱና የትጥቁንም የፕሮፓጋንዳውንም ትግል ከዚያ ቢያደርጉ፤ የወያኔ ጦር እየከዳ ወደግንቦት ሰባት የማይገባበት ምክንያት አይታየኝም። ለምሳሌ የዛሬ አራት አምስት አመት አካባቢ እነከማል ገልቹ ከዱ ሲባል ጦሩ ከየግንባሩ መከተል ጀምሮ ነበር። ከዚያ በሁዋላ ግን እኛም አልገፋንበት፤ ጦሩም ብዙ አልከዳም። ይሄ የጦሩን ማስከዳት ስልት አንዱ የትግል ስልት ሊሆን ቢችልም፤ የራሱም ችግር አለው የሚሉም አልታጡም፤ ኤርትራ ውስጥ የተጠናከረ የተቃዋሚ ጦር ካለ፤ ወያኔ ኤርትራን ወሮ ይይዛል የሚል ስጋት። ይሄ በኛ የጦር አማካሪዎች ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ወያኔ ከኤርትራ ቢገጥም በቀላሉ ያሸንፋል አያሸንፍም የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ወያኔ አለማቀፍ ህግጋትን ጥሶ ኤርትራን ይወራል ወይ የሚለውም አንድ መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው። ስጋቱ ቢያስኬድም እንኩዋን፤ አምነን የምንገባበት ስጋት ነው እንጂ፤ ያንን አስበን ከኤርትራ ጋር ለመስራት ወይንም ካምፓችንን በዚያ ለማድረግ የምንተውበት አጥጋቢ ምክንያት አይደለም።

ባጠቃላይ፤ ከኤርትራ ጋር የኤርትራን ሉአላዊነት ያወቀና የኤርትራንም የኢትዮጵያንም ብሄራዊ ጥቅም ያስቀመጠ ውል መግባት አንዱ የትግል አማራጫችን ነው። በኤርትራ በኩል ያለው ትግል ያልገፋው ከኤርትራ ጋር በግልጻና በይፋ የሚዋዋል ጠንካራና ደፋር ሀገር ወዳድ ድርጅት ስላልተገኝ ነው። ያንን ክፍፈት ሊሞላ የሚችል ደግሞ ከግንቦት ሰባት የተሻለ የለም። ግንቦት ሰባት ግን እስካሁን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ ተሻሸ እንጂ አልቆረጠም። የመቁረጥ ቀን ካለፈ ሰነበተ። ባለአርባ አመቶቹን ድርጅቶች እየተቸን፤ እኛም በነሱ ሰማኒያ ላይ አርባችንን እንዳናከብር አሁን ወደኤርትራ መጓዝ አለብን። ይሄ ለግንቦት ሰባት ብቻ አይደለም። ለሰኔ ሰባቶችም ለሀምሌ ሰባቶች እንጂ። ለዳላሶች። የሽግግር ምክርቤት መቋቋም ያለበትም፤ ኦታዋና ዳለስ ዲሲና ለንድን ሳይሆን፤ አስመራና ምጽዋ ነው። እዚያው አፍንጫቸው ስር። የሕወሀት አፍንጫ ስር። እየተሽለኮለክንና በሽፍንፍን ሳይሆን፤ በግልጽ ካልቀረብናቸው በስተቀር፤ የኤርትራ መንግስትን ሙሉ-እርዳት ልናገኝ አንችልም። በግልጽ አጀንዳ አብረውት የሚሰሩት እነ ኦነግ እያሉም፤ የኤርትራ መንግስት አጀንዳችንን በሆዳችን ደብቀን የምንጠጋውን ሌሎች ኢትዮጵያዊያን የሚረዳበት ምክንያት አይታየኝም። ግልጽና ይፋዊ ፖለቲካዊ ውል ከኤርትራ ጋር አሁኑኑ። ነው ወይስ ግራ ገብቶኛል?
ለማንኛውም ከበረታሁ ይሄንን ርእስ እቀጥልበታለሁ። በተለይም የኤርትራና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞች ሳይጋጩ ጎን ለጎን መሄድ ይችላሉን? ለኤርትራ ሕልውና የኢትዮጵያ መፈራረስ የግድ ነውን? በሚሉት ርእሶች ላይ እቸከችካለሁ።

የኔታ ተክሌ ነኝ፤ አሁን ደግሞ ሕይወት ቶሮንቶ ጥሎኛል። ሰኔ፤ 2004/2012

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 27, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.