የቴዲ አፍሮ ጉዳይ አልበዛም?

(በግርማ ደገፋ ገዳ)

ዘላለም ገብሬ፤ በአዲስ አድማስ ላይ ለወጣው ጽሁፍ ምላሽ ይሆናል ብለህ ስለቴዲ አፍሮ የጻፍከውን አስተያየት አነበብኩት። ጊዜ ኖሮህ ያንን ሁሉ በመጻፍህ ያስመሰግነሃል። ግን ቴዲ አፍሮን አጋኖ ለማድነቅ ተብሎ ቤትና ጨርቅ አስጥል የሆኑ ዘፈንና ዘፋኞች በሙሉ በአንድ ሙቀጫ ታጉረው ባንተ ብእር መወቀጣቸው በጣም አስገርሞኛል። እነዚያን የመሰሉ ባህላዊም ይሁኑ ዘመናዊ ዘፋኞች “ከቴዲ አፍሮ የሚወዳደሩ አይደሉም” ልትለን ከዳዳህ፤ የላንቻና ኩባንያውን ፍሬን ሸራ ግዛና እዚያ’ጋ ፍሬን ያዝ አልልህም።

Teddy Afro

Teddy Afro


አስቴር አወቀ በያመቱ የምታወጣው ሲዲ ወይም ካሴት የላትም። በሰባትና ስድስት ዓመትም አይሞክራትም። ዘፈንና ዘፋኝ የሚለካው በሚሸጠው ገንዘብ ቁልል ብዛት ከሆነ፤ ብዙ ጣፋጭ ሙዚቃዎችና አቀንቃኞቻቸው አፈር በሉ ማለት ነው። አስቴርን በሌላ አቅጣጫ ለማጥቃት ካስፈለገ እሱ አንድ ነገር ነው፤ በሙዚቃ ሥራዎችዋ በኩል ግን የሚሳካ አይደለም። በዚያ በኩል ደካማ ጎን አላት ለማለት ወደ ውስጥ ጠልቆ ሙያዊ ግምገማ ማድረግ ይጠይቃል። ያንተም ሆነ የኔ አስተያየት ግን በአድናቂነት ከምናስተውለውና ከሚሰማን ስሜት የመነጨ ስለሆነ የስሜታችንንና የትዝብታችንን ለአንባቢያን መጠቃቀሱ ክፋት የለውም።

የአስቴር አወቀ ዘፈኖች ለገበያ ሽሚያ ተብለው “እንደ ጨረቃ ቤት” በጥድፊያ ይወጡ እንደነበር የሚያሳይ አስረጅ ያለ አይመስለኝም። ዛሬ እንዲህ ዘፋኝ በየመንደሩ በተኮለኮለበትና ወደ ውጭ ሃገር ለመክነፍ ቪዛ በቀላሉ በማይገኝበት ወቅት፤ አስቴር በሙዚቃ ሥራዎቿ ሰበብ ውጭ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ ደረጃው ሰማይ የነካ ሙዚቃ ነው የሰራችው። አንዴ ስደት የገባ የሙዚቃ ባለሙያ ከውኃ የወጣ ዓሳ የሚሆንበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። ወደ ውኃው ተመልሶ የመግባት እድል ቢኖረው እንኳ የበፊቱ ዓይነት ደረጃ ያለው ሙዚቃ ለመሥራትም ይቸግረዋል። “የሃገር ጉዳይ መስመር ሳይዝ ስለሴት ልጅ ባትና ዳሌ ንክችም አላደርም” ያለው ዘፋኝ፤ የሃገር ጉዳይ መስመር ሳይዝ ስለወንድ ልጅ ቅንድብ መዝፈኑ አንድ ምሳሌ ነው። አስቴር ግን ከውኃውም ወጥታ በዓለም አቀፍ የሙዚቃ ገበያ ውስጥ በመግባት አንድ እርምጃ ወደ ፊት መራመዷን አሳይታለች። በቂ ገንዘብም አግኝታለች። የገዛቻቸውን ጫማዎቿን ከመርሳት እስከ መምረጥ መቸገር ድረስ የሄደች ናት። ጫማ ከቢኤምደብሊው አይበልጥም ከተባለ እንግዲህ እሷስ ማክ ይኑራት ታንክ፣ ጂፕ ይኑራት ጅብ በበኩሌ የማውቀው ነገር የለኝም።

ከአስቴር ጉዳይ ጎን ለጎን አብሮ ሊነሳ የሚችለው ደግሞ የማህሙድ ጉዳይ ነው። ማህሙድን፤ አንድ ጥቁር ወይም ሲልቨር ኪቦርድ እንደ አኮርዲዮን ወይም ሃርሞኒካ አንጠጥሎ በየመድረኩ መታየት በጣም የሚያስደስተው አይመስለኝም። እየዘፈነ ወደ ኋላ ዞር ባለ ቁጥር አንጀቱ ምን ያህል እንድሚቃጠል ይታየኛል። በተሟላ ባንድ ይዘፍን በነበረበት ወቅት፣ የባንዱ አባላት ማህሙድ የሚሰጣቸውን የዓይን ምልክት እየተከተሉ ሙዚቃውን ሞቅና በረድ ያደርጉ ነበር።

ዛሬ አንድ ጊዜ አይደለም አስር ጊዜ ወደ ኋላው ቢዞር እነዚያ የሙዚቃ መሳሪያ ጋጋታዎች ሕልም ሆነው የቀሩ መስለዋል። የባንድ አባላት አጥር መስለው አድምቀውት ባለመታያቸው፤ ባኞ እየታጠበ ለራሱ የሚዘፍን ሰው ያህል ቢሰማው ምንም አያስደንቅም። ግን፣ በብዙ መሳሪያዎች አጃቢነት ጣፋጭ ዘፈኖቹን ለአድማጮቹ እያሰማ፣ የወጣትነቱን ዘመን ጨርሾ፣ የጉልምናውን ድልድይ ተሻግሮ በሕይወት የመጨረሻዎች አጥሮች አጠገብ ለደረሰ አንድ በጣም ታዋቂ የዘፈን ባለሙያ፤ “የአንድ ኪቦርድ” ጉዳይ በሕይወቱ ላይ ያለውን መሰናክል ብዛት የሚያሳይ እንጂ የሙዚቃ ሕይወቱ ማሽቆልቆሉን የሚያመላክት ነው ለማለት ድፍረት የለኝም። ቴዲ አፍሮ ወደ ፊት እንደ ማህሙድ አንድ ኪቦርድ ሳይሆን አይፎንን በምታክል ትንሽዬ የሙዚቃ መሳሪያ ላለመታጀቡ ማረጋገጫ ሊሆን የሚችል ምንም ነገር የለም።

በመጀመሪያ ደረጃ እኔ የቴዲ አፍሮ ሙዚቃ አድናቂ ነኝ። የሚዘፍናቸው ቁም ነገሮች ልብ የሚነኩ ናቸው። “ያስተሰርያል” የተባለውን ሲዲ ጨምሮ አብዛኛው ዘፈኖቹ ነበሩኝ። በተለይ ያስተሰርያል በ2005(እኤአ) ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ተካሂደው የነበሩትን ትላልቅ የተቃውሞ ሰልፎችን ያስታውሰኛል። በየሰልፎቹ ላይ ለመሳተፍ ስወጣ የመኪናዬን አራቱን መስኮቶችና የሲዲውን ድምጽ እስከ መጨረሻው ከፍቼ ያስተሰርያልን እየሸከሸኩ ነበር ዲሲን የማቆራርጠው። ሙዚቃ እንደዚያ አድርጌ ከፍቼ አላውቅም።

ይሁንና ዘላለም ገብሬ እንደጻፈው ቴዲ አፍሮ ያንን ሁሉ የሚያሟላ ዘፋኝ አይደለም። በጣም ነው የተጋነነው። አንድ በገጣሚነቱና በዜማ ደራሲነቱ የሚታወቅ ብሔራዊ ዘፋኝ፤ አንድ ሲዲ ለማውጣት አምስትና ስድስት ዓመት የማይበቃው ከሆነ ስንት ዓመት ነው የሚበቃው? ይሄ ሁሉ የተሟላለት ዘፋኝ ያን ያህል ከወሰደ ሌላው ስንት ዓመት ይወስድበታል? ቴዲ አፍሮ “እንደ አስቴር ለገበያ አይጨነቅም” የሚባለውም አባባል የሚያሳምን አይደለም። ምክንያቱም ከሥጋዊ ሞት በኋላ ስላለው አጓጊ ሕይወት ሲሰብክ አልሰማንም። ምናልባት የፕሮቴስታንት መዝሙር ዜማዎች የሚመስሉ ብዙ ቅንብሮቹን ሰምተን የ“ዘፋኝ ዘማሪ” ልናደርገው ካልዳዳን በስተቀር፤ ሙያው ዘፋኝነት ነው። ዘፋኝ ሆኖ ያንን ሁሉ ዓመት ያለአዳዲስ ዘፈን ማሳለፉ ‘በገቢው ላይ የተጋነነ ችግር አያስከትልም’ ተብሎ ጭፍናዊ አስተያየት ቢሰጥ እንኳ፤ በገንዘቡ ቦታ ሥራውን የሚወዱለትን አድናቂዎቹን እያጣ መሄዱ ግን አይቀሬ ነው። እሱም ያ አያስፈነድቀውም።

ሌላው ሊነሳ የሚገባው ደግሞ ዜማና ግጥሞችን ከድሮ ታዋቂ ዘፋኞች እየቀነጨበ ከራሱ ፈጠራዎች ጋር ማጣበቁ ነው። ኤርትራዊ ዘፋኞችም ከዚህ ዒላማ አልተረፉም። በርግጥ የ“እንደ ቢራቢሮ” እና “ፊዮሪና” ዘፋኞች፣ ኤርትራ ራሷን የቻለች አንድ ሃገር ከመሆኗ በፊት የተዘፈኑ በመሆናቸው “የተወሰዱት ከኢትዮጵያውያን ዘፋኞች ነው” ተብሎ ሌላ የሕግ ክርክር እስካልተከፈተ ድረስ የሚወስደውን ወስዷል። “…..የኢትዮጵያንና የኤርትራን አንድነት ከልቡ መመኘቱ…..” ‘ሁለቱን ሃገራት በድሮ ዘፈን ለማገናኘት ነው’ …. ያንን ማድረጉ እንዲያውም የተረሱትንና “…የዘፈነው ዘፋኝ ማንነት በማይታወቅበት ሁኔታ…..” እና “…..በኤርትራውያን ዘንድ እስከነፈጠሩ የተረሳ…..” እየተባሉ ቴዲ አፍሮን የበለጠ በመሞጭለፍ ሥራ ላይ ተጠምዶ
እንዲከርም የሚያበረታቱ የሚመስሉ ሁኔታዎችም አሉ። “ስድስት ዓመት ሙሉ መከራውን የሚያየው የተዋጣለት ሥራን ለሸማቾቹ ለማቅረብ ነው” የሚባለው ታዋቂ ዘፋኝ፤ በስድስት ዓመቱ፣ “ማንነታቸው ከማይታወቀው” ዘፋኞች የተወሰኑ ግጥሞችና ዜማዎችን ቀነጫጭቦ ለገበያ ወጣ ሲል፤ አድናቂዎቹ እያጨበጨቡ ሳይሆን አንጀታቸው ተቃጥሎ ከንፈራቸውን በምሬት እየመጠጡ እንደሚቀበሉት የተረዳው አይመስለኝም።

እኔ የቴዲን አዳዲስ ዘፈኖች የያዙ ሲዲዎችን ቢያንስ በየሁለት ዓመቱ ባገኝ በጣም ደስ ይለኛል። በየስድስት ዓመቱ ግን አይሆንም። በጣም የምንወደው የዓለም ዋንጫ እንኳ በጣም እየቆየ በየአራት ዓመት ነው የሚመጣው። አንድ አዲስ የዘፈን ሲዲ ለማዳመጥ ስድስት ዓመት ሙሉ ወረፋ መጠበቅ የት ነው ያለው? ለዚያውም የሚሰጠው ምክንያት ደግሞ ጭራሽ የሚያናድ እየሆነ። “የቴዲ ዘፈኖች ተሰረቁ!” እየተባለ ስድስት ዓመት ከምንቆይ፣ ያለምክንያት ስድስት ዓመት ወረፋ መጠበቁ ይሻላል። እኔ የማይገባኝ ነገር፣ ቴዲ አዳዲስ ሙዚቃዎችን የሚለማመደው ከሌቦች ጋር ነው? “ሌቦች ሆይ! ኑ! …..አዳዲስ ዘፈኖች እያወጣሁ ነው። ስለማመድ እዩኝ። አይታችሁም ዝም አትበሉ፣ ስረቁኝ!” እያለ ነው የጥሪ ወረቀት የሚሰጣቸው? ዘፈኑን ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም ምክንያቱን መቀያየር ያስፈልጋል። የምክንያት ዜማና ግጥም ከጨረሰም እንደፈረደበት “ማንነታቸው ከማይታወቅ” የምክንያት ደራሲ ኤርትራውያን ላይ ለመውሰድ ይሞክር።

የቴዲ አፍሮ የሕይወት መስመር ሲጠቀስ በሕይወት በነበሩበት ዘመን ብቻ ሳይሆን ከሕይወታቸው ሕልፈት በኋላም የዓለምን ሚዲያ ሲያንጫጩ የነበሩና ነበሩ የሚባሉ ሟቾችም ተጠቅሰዋል። ኤልቪስ ፕሪስሊ፣ ማርሊን ሞንሮ እና ዳያና (የዌልሷ ልእልት) ናቸው። ይህን ሳነብ ቴዲ አፍሮ ከሞቱት ሰዎችና ሥራዎቻቸው ተርታ መሰለፉ ግራ ነው የገባኝ። እሱን ለማጋነን የተዘጋጀው ትችት፣ የሆነ ሰው መቃብር ላይ ቆሞ የሚያነበው ነው የመሰለኝ። ዘላለም ገብሬ ባይጠቅሰውም ብዙ የቴዲ አድናቂዎች ቴዲን ከቦብ ማርሌይ ጋር ያወዳድሩታል። ለመሆኑ ቦብ ማርሌይ እና ቴዲ አፍሮ ምናቸው ይመሳሰላል?

ቦብ ማርሌይ በሰላሳ ስድስት ዓመቱ ድፍት እስካለበት ጊዜ ድረስ፣ “የፍትህ ያለህ?” ይል ለነበረው የጀማይካ ሕዝብ ልሳን ከሆኑት አንዱ ነበር። በማህበራዊና ፖለቲካ ውጥንቅጥ ትርምስምሷ ለወጣው ትንሿ ጀማይካ፣ በሙዚቃው ማድረግ የሚገባውን ያደረገ ስመ-ገናና ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ሰው ነበር። የጀማይካ አምባገንን ገዥዎች ሲያዋክቡት እየፈራ ወይም እያፈረ የጀማይካ ሕዝብ የወደዱለትን ዘፈኖች አልተዋቸውም። ከጀማይካ አልፎ ለጥቁር ሕዝቦች አሌኝታ ከሆኑ የድሮ ዘፈኖቹ መሃል የዘፈኖቹ አንኳር፣ አንኳር የሆኑ ግጥሞቹን እየነቃቃለ የትም አልጣላቸውም። ያመነበትን ጽፎ፣ ዜማ አውጥቶና ደጋግሞ ዘፍኖ ይቺን ዓለም ተሰናብቷል። ቴዲ አፍሮስ?
ቴዲ አፍሮ ይሄንን ምሳሌ፣ በጣም ከሚወደው የሬጌ አቀንቃኝ ሲወስድ አላየንም። ይልቅ በሰላሳ ቤት እድሜው ከሕዝብ ልብ ውስጥ የጨመሩትን ቃላቶች ላይሞቱ እያደነ ሲገድላቸው ነው የተስተዋለው። የራሱን ግጥምና ዜማዎች

ተጸይፎ “ማንነታቸው ካልታወቀ” ከሚባሉት፤ ነገር ግን ማንነታቸውን የሙዚቃው ዓለም በምንም ዓይነት ከማይረሳቸው ዘፋኞች ዜማና ግጥም መቀነጫጨብ ሆኗል ምርጫው። እነዚያም ቅንጭብጫቢዎች የሚሰሙት ከስድስት ዓመት “ተሰረቅኹኝ” ዜናና የሞት ሽረት ወረፋ በኋላ ነው። ኧረ ለመሆኑ ተክሌ ተስፋዝጊ ማንነታቸው ከማይታወቅ ዘፋኞች ሰልፍ መሃል እንዴት ገባ? በስህተት መሆን አለበት! …..የተክሌ ተስፋዝጊን ህልፈተ ሕይወት ሰምተው የነበሩ የዛን ጊዜ የአሥመራ ኮረዶች’ኮ ጥቁር ልብስ ለብሰውለታል። የዛሬ ዘመን የአሥመራ ውቦችም ያንን ታሪክ ሳይሰሙ ቀርተው በቴዲ አፍሮ አዲሱ “ፍየሪና” ያብዳሉ ብለህ ነው? አይመስለኝም። ጭራሽ ከዚህ ቀደም ሰጥተውት የነበረውን ልባቸውን መልሰው እንዳይወስዱበት እሰጋለሁ። “ፍየሪናን ሳይሆን ፍርዬን ከፈለግህ እሷን እንደፈለግህ አድርግ፣ ወዲ ተስፋዝጊን ግን ለቀቅ አድርግልን” ካላሉት ይገርመኛል።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ዋና ከተማዋን ጥለው ወደ ሌላ ዋና ከተማ ሳይሆን፤ ጦር ሜዳ ሄደው በዘፈናቸው የተዋጉ አሉ። ስንቱን አንጋግተው ጦር ሜዳ የጨመሩ ሞልተዋል። አንዲት ቀስቃሽ ዘፈን ሲሰሙ ሞፈራቸውን ሰቅለው፣ ቡሃቃቸውን አሽንቀንጥረው ወደ ቀለጠው ፍልሚያ ያቀኑ መዓት ናቸው። ከዚያ ሃገራዊ እይታ አንጻር ሲታይ መስመራቸው ይለያይ እንጂ የቴዲ አፍሮ ሥራዎች ያደረጉት ሃገራዊ አስተዋጽኦች አሉ። ግን ዘላለም እንደጻፈው አይደለም። ያንን በማመን ይህንን ጽሁፍ እቋጫለሁ፤ ቴዲ አፍሮ አሜሪካ ሲመጣም እንደፈረደብኝ ቲኬቱን ለመግዛት እሻማለሁ።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 10, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.