የታሪክ፡ ተጠያቂወች፡ ሁነናል። – አክሎግ ፡ ቢራራ (ዶር)

(ክፍል፡ አንድ)

የህወሃትን ፡ አስከፊ ፡ አገዛዝ፡ ስናማርር፡ ሃያ፡ አንድ፡ አመታት፡ ቆይተናል። ይህ፡ የጠባብ፡ ዘረኛ፡ቡድን፡ ክተጠነሰሰበት፡ ወቅት፡ ጀምሮ፡ ሆነ፡ ብሎ፡ የሚያደርገውን፣ ሰላማዊ፡ ሕዝብ፡ ማሰቃየት፤ ሰብነት፡መግፈፍ፤ ማሳደድ፤ መግደል፤ከአገር፡ ማስወጣት፤ ማን፡ ገዥ፤ ማን፡ ተገዥ፡ እንደሆነ፡ ማሳመን፡ ሞክሩል። ማንን፡ ማጥቃት እንዳለበትም፡ ደንግጓል። ብዙ፡ በማስረጃ፡ የተደግፉ፡ ጽሁፎች፡ እንዳሳዩት፤ በተለይ፡ ኢላማ፡ አድርጎ፡ የተነሳው፡ የአማራው፡ ህብረተሰብ፡ ሰብነትና፡ ክብር፡ እንዲገፈፍ፤ በራሱ፡ ባህልና፡ ታሪከ፡ እንዲያፍር፡ ማድረግ፤ ራሱን፡ እንዲጠላና፡ አግብዳጅ፡ እንዲሆን፡ ማስገደድ፤ አስተዋጾው፡ ቀፎ፡ ነው፡ ብሎ፡ እንዲቀበልና፡ ራሱን፡ እንዲጠራጠር፡ ማሳመን፤ “የሕዝቦች፡ እስር፡ ቢት፡” ተብላ፡ በህወሃትና፡ በተመሳሳይ፡ ጠባብ፡ ዘረኛ፡ ክፍሎች፡ የምትጠራውን፡ ኢትዮጵያን፡ የአማራ፡ ህብረተሰብ፡ ለጭቆናና፡ ለዘረፋ፡ እንደዳረጋት፡ በማሳመን፡ የሞራል፡ ክስ፡ በአማራ፡ ህብረተስብ፡ ላይ፡ ለማቅረብ፡ መሞከር፤ ለዚህም፡ይህ፡ ህብረተሰብ፡ ሃላፊነትና፡ ተጠያቂነት፡ እንዳለበት፡ ለማሳመን፡ መጣር፤ ቀስ፡ በቀስ፡ ከሃብቱ፤ ከማሳውና፡ ከንብረቱ፤ ከሃገሩና፡ ከወገኖቹ፡ እየወጣ፡ ቁጥሩ፡ እንዲቀንስና፡ ለስደት፡ እንዲዳረግ፡ ለማድረግ፡ መጣር፡ ወዘተ፡ ናቸው። አሁን፡ በጉራ፡ ፈርዳ፤ የደቡብ፡ ክልል፡ ወስጥ፡ በሰላማዊ፡ ህጻናት፤ እናቶች፤ አባቶችና፡ በማሳቸው፡ የግብርና፡ ምዋያ፡ የሚተዳደሩ፡ የአማርኛ፡ ተናጋሪ፡ ኢትዮጵያዊያን፡ ላይ የሚያካሂደው፡ ኢስባዊ፡ መፈንቀልና፡ ለዘር፡ ጽዳት፡ ዳራጊ፡ ተግባር፡ ታሪክ፡ እየመዘገበው፡ ያለው፤ የህወሃት፡ ዋና፡ ዋና፡ መሪዮች፡ በህግ፡ የሚያስጠይቅ፡ ወንጀል፡ ነው።

ይህ፡ የኢትዮጵያ፡ ህብረተሰብ፡ አካል፡ ለዚህ፡ አሰቃቂ፡ የመፈንቀልና፡ የዘር፡ ማጽዳት፡ ድርጊት፡ ኢላማ፡ የሆነበት፡ ዋና፡ ምክንያት፡ ወንጀል፡ ስለሰራ፡ ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያ፡ የተሰበጣጠረ፤ ጎን፡ ለጎን፡ አብሮ፡ በሰላምና፡ በመከባበር፡ ለሚኖር፡ ህብረተሰብ፡ ድልድይ፡ ስለሆነ፤ ለኢትዮጵያ፡ አንድነትና፡ ሏአላዊነት፡ ምሰሶ፡ ሆኖ፡ ስላገለገል፡ ነው። ከጅምሩ፤ የህወሃት፡ የዘር፡ ፖለቲካ፡ ፈጣሪወች፡ በኢትዮጵያ፡ “የማይታረቁ፡ ልዩነቶች” አሉ፡ በሚለው፡ “የከፋፍለህ፡ ግዛው፤” የፖለቲካ፡ አደረጃጀት፡ ስልት፡ የተጠቀሙትና፡ በዚህ፡ ላይ፡ የተመሰረተ፡ የክልል፡ ስራትን፡ ከስራ፡ ላይ ያዋሉት፡ ሕዝብ፡ ከሕዝብ፡ ጋር፡ ለማጋጨት፡ እንጂ፡ ለተጎዱ፡ የኢትዮጵያ፡ ህብረተስብ፡ ክፍሎች፡ በማሰብ፡ አይደለም። ለኢትዮጵያ፡ ሏላዊነትና፡ ለመላው፡ ሕዝቧ፡ ፍትሃዊ፤ ዲሞክራሳዊና፡ በእኩልነት፡ ላይ፡ የቆመ፡ አማራጭ፡ እውን፡ መሆን፤ የአማራው፡ ህብረተሰብ፡ ተመሳሳይ፡ ፍላጎት፡ ካላቸው፡ አጋሮቹ፡ ጋር፡ ሆኖ፡ አስተዋጾውን፡ እንደሚያደርግ፡ ስለሚታወቅ፡ ጭምር፡ ነው። በህወሃት፡ አለቆች፡ ግምት፡ ይህን፡ አብሮ፡ ተቻችሎ፡ የመኖር፡ እስየት፡ ለመከላከል፡ የአማራ፡ ሕዝብ፡ በተክታታይ፡ ያስመሰከረውን፡ ድልድይነት፡ መስበር፡ ይገባል፡ የሚል፡ ነው። ስለሆነም፡ የአማራ፡ ህብረተሰብን፡ አሰቃቂ፡ በሆነ፡ መንገድ፡ ከኑሮው፤ ከማሳው፤ ከሃብቱ፤ ከስራውና፡ ካለበት፡ ቦታ፡ ሁሉ፤ በሰላም፤ በክብርና፡ በርጋታ፡ እንዳይኖር፡ ማድረግ፡ የአማራ፡ ህብረተሰብ፡ ብቸኛ፡ ችግር፡ ነው፡ ማለቱ፡ አያዋጣም። የኢትዮጵያና፡ የኢትዮጵያዊያን፡ ፈታኝና፡ ወሳኝ፡ ችግር፡ ነው።
ስለ፡ ሆነም፤ እስክ፡ አሁን፡ በሚገባ፡ ያልመረመርነው፡ አበይት፡ ነገር ቢኖር፡ የዘረኝነት፡ አደጋውን፡ የምንቀበል፤ስራቱን፡ የምንቃወም፤ የሕዝባችን፡ ስቃይና፡ መከራ፡ በየቀኑ፡ የምናይ፤ ይሀ፡ ስብነትን፡ የተፈታተነ፡ ሰቆቃ፡ ከራሳችን፡ ድክመት፡ ጋር፡ የተያያዘ፡ መሆኑን፡ ጭምር፡ ነው። የኢትዮጵያ፡ ታሪክ፡ ተከልሶ፡ በውሸት፡ ሲጻፍ፡ ዝም፡ አልን። ህብረ-ብሂራዊ፡ ስራት፡ ቀስ፡ በቀስ፡ ሲናድ፡ ዝም፡ አልን። የሃገር፡ ሏላውይነት፡ እየተቦረቦረ፡ ሲናይ፡ ችላ፡ አልን። ምትክ፡ የማይገኝላቸው፡ አገራዊ፡ ተቋሞች፡ እየተናዱ፡ ስናይ፡ ድምጻቺን፡ ጠፋ። ለም፡ ማሳወች፡ ለውጭ፡ መንግስታትና፡ ድርጂቶች፤ ለምርጥ፡ ግለሰቦች፤ በጂምላ፡ ሲስጡ፡ ድምጽ፡ ሳነሰማ፡ ቆየን። መንፈሳዊ፡ አባቶቻችን፡ የሚጠቀሙበት፤ መተኪያ፡ የማይገኝለት፡ ምድርና፡ ደን፤ ተከታታይ፡ መንግስታት፡ ያከበሩት፡ የዋልድባ፡ ገዳም፡ ለህወሃት፡ ደጋፊ፡ ድርጂቶችና፡ ታማኞች፡ ለስኳር፡ ማምረቻና፡ ፋብሪካ፡ ሲቆፈር፡ እያየን፡ አንዳንዶቻችን፡ ድምጽ፡ ስናሰማ፡ ብዙወቻችን፡ የቁም፡ ተመልካች፡ሆነን፡ ቆይተናል። የአማራ፡ ሕዝብ፡ ልክ፡ ለእርሱ፡ ብቻ፡ በመጣ፡ የወረርሽኝ፡ በሽታ፡ እዳለቀ፡ ሁሉ፡ ቁጥሩ፡ እንደቀነሰ፡ ወይንም፡ በፈቃዱ፡ ማንነቱን፡ እንደለወጠ፡ ተደርጎ፡ በሚያስደነግጥና፡ በሚያናድድ፡ ደረጃ፡ ቁጥሩ፡ ከ፫፬፡ ሚሊዮን፡ ወደ፡ ፩፯ ሚልዮን፡ እየቀነሰ፡ እያየን፡ ዝም፡ ብለናል። ይህ፡ ህዝብ፡ ቁጥሩ፡ የቀነሰው፡ ወደ፡ ጨረቃ፡ ስለተጓዘ፡ እንዳልሆነ፡ እውቅ፡ ነው። ታድያ፡ የት፡ ደረሰ፡ ለማለት፡ ይቻላል። ከአማራ፡ ክልል፡ ውጭ፡ ይኖር፡ የነበረው፡ የአማርኛ፡ ተናጋሪ፡ ወይንም፡ ህወሃት፡ “አማራ፡ እንጂ፡ ኢትዮጵያዊ፡” አይደለህም፡ ብሎ፡ የደነገገበት፡ ሕዝብ፡ ሆነ፡ ተብሎ፡ ማንነቱን፡ እንዲለውጥ፤ ቀስ፡ በቀስ፡ የመጥፋት፡ እድሉ፡ ጠለቅ፡ እንዲል፡ ለማስገደደ፡ መሆን፡ አለበት። አለበለዚያ፡ በ፪፩ኛው፡ መቶ፡ ክፍለ፡ ዘመን፡ የዚህ፡ አይነት፡ የሰብነት፡ ገፈፋ፡ ባልተካሃደ፡ ነበር።

የህወሃት፡ መሪ፡ አላማ፡ የአማራ፡ ቁጥር፡ ሲቀንስ፡ የሚያስከትለው፡ የኣማራው፡ አቅምና፡ ጉልበት፤ ያለው፡ አገር፡ አቀፍ፡ ሚና፡ ይለወጣል፡ የሚል፡ ነው። ቀስ፡ በቀስ፡ የአማራው፡ ሕዝብ፡ ቁጥር፡ ወደ፡ ነኡሰነት፡ ይቀየራል፡ የሚል፡ ዘገባ፡ ስላለም፡ ነው። የሚያሰጋው፡ ቢቻል፡

ህልውናው፡ ጭራሽ፡ እንዲጠፋ፡ መሆኑ፡ ነው። ሆኖም፤ ህወሃት፡ ቢወድም፡ ባይወድም፡ አመራሩ፡ ሊለውጠው፡ የማይችለው፡ ሃቅ፡ ግን፡ ይህን፡ ይመስላል። አማርኛ፡ ተናጋሪወች፡ የአማራ፡ ህብረተሰብ፡ አባላት፡ ብቻ፡ አይደሉም። በአሁኑ፡ ወቅት፤ ቢያንስ፡ ከ፱፻ ሚሊዮን፡ ሕዝብ፡ ፸ ሚሊዮን፡ የሚሆነው፡ አማርኛ፡ ተናጋሪ፡ ነው። ቢያንስ፡ ፶ በመቶ፡ የኢትዮጵያ፡ ህዝብ፡ ድብልቅ፡ ነው። አንደ፡ አማራ፡ ህብረተሰብ፡ ክሁሉ፡ ህብረተስብ፡ ጋር፡ አብሮ፡ የሚኖር፤ የሚጋባ፤ የተደበላለቀ፡ አለ፡ ለማለት፡ አስቸጋሪ፡ ነው። የህወሃት፡ ጠባብ፡ ዘረኛ፡ ቡድን፡ ይህን፡ ሃቅ፡ በምንም፡ ሊቀይረው፡ አይችልም። ሆኖም፡ አማርኛ፡ ተናጋሪው፡ በያለበት፡ የራሱን፡ ህልውና፡ የመጠበቅ፡ ስልት፡ መሻት፡ አለበት፡ የሚለው፡ አስተሳሰብ፡ የወቅቱ፡ አንገብጋቢ፡ ጉዳይ፡ መሆኑ፡ አያጠራጥርም፤ አያከራክርም።

ይህ፡ መረጃ፡ እንዳለ፡ ሆኖ፡ አሁንም፡ የምናየው፡ ተከታታይ፡ ድክመት፡ የእኛው፡ ነው። የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ብዙ፡ የወል፡ እሲየቶች፡ እንዳሉት፡ ከተቀበልን፡ ከሚያራርቁን፡ ንኡስ፡ ነገሮች፡ ላይ፡ ማተኮራችን፡ ለዚህ፡ በዳይ፡ ስራት፡ ምርኮኛ፡ መሆናችን፡ ያሳያል። ተስማምተን፡ ለመስራት፡ ካልቻልን፤ ይህ፡ አሰቃቂ፡ ስራት፡ ይቀጥላል። ጥሩው፡ ነገር፤ በአሁኑ፡ ወቅት፡ የራሳችን፡ ድክመት፡ ለወገኖቻችን፡ ሆነ ለአገራችን፡ አስከፊ ጉዳት፡ ማምጣቱን፡ ከልባችን፡ ለማመን፡ ሙከራ፡ የምናደርግ፡ እየበዛን፡ ሂደናል። ይህ፡ ጥሩ፡ ጅመራ፡ ነው። ግን፡ በቂ፡ አይደለም። ብዙ፡ ስራወች፡ ከፊታችን፡ ይጠብቁናል። አሁንም፡ ካሉ፡ ችግሮቻችን፡ መካከል፡ የለውጥን፡ ጠቃሚነት፡ በሚገባ፡ አለማስቀመጥ፤ አለመተማመን፤ ለጥቅም፡ መገዛት፤ እውነትን፡ በድፍረትና፡ በጨዋነት፡ አለማሳየት፤ ራስ፡ወዳድነት፤ፍርሃትና፡ መከፋፈል፡ ይገኙበታል።
የህወሃት፡ መንግስት፡ ዞሮ፡ዞሮ፡ የአንድ፡ ክልል፤ እንዲያውም፡ የአንድ፡ መንደር፡ የበላይነት፡ መንግስት፡ መሆኑን፡ አሁን፡ ሳይሆን ስልጣን ከያዘበት፡ ጀምሮ፡ እንዳሰመረበት፡ ብናውቅም፤ ለዚህ፡ ችግር፡ መፍቻ፡ ተባብረን፡ ለመስራት፡ የተነሳን፡ ጥቂቶች፡ ነን። ይህን፡ ድክመት፡ አለመገንዘብ፡ ቂልነት፡ ወይንም፡ አውቆ፡ የስራቱ፡ ተባባሪ፡ መሆን፡ ነው። የችግሩን፡ ክብደት፡ በሚገባ፡ የማመዛዘኑን፡ ጥበብ፡ ካላወቅን፡ መፍትህየ፡ ለመጠቆም፡ አንችልም፤ የኢትዮጵያን፡ ሕዝብ፡ ለመርዳት፤ ታሪክ፡ ያላትን፤ ለጥቁር፡ ህዝቦች፡ ሁሉ፡ አራያ፡ የነበርችውን፡ ኢትዮጵያን፡ ካለችበት፡ ፈተና፡ ለማዳን፡ አንችልም። ልዩነቶችን፡ ወደ፡ ጎን፡ አድርገን፡ በመተባበር፡ ከሰራን፡ ግን፡ ምንም፡ ሃይል፡ አያግደንም። የአረብ፡ አገሮች፡ በሕዝብ፡ የተመሩ፡ ለውጦች፡ የሚያሳዩን፡ አቅጣጫ፡ ይህን፡ ነው። እኛም፡ የራሳችን፡ ልምድ፡ አለን። ምርጫው፡ የእኛው፡ ነው።
አንዱ፡ መረዳት፡ ያለብን፤ ይህ፡ ነው። ገንቢ፡ ለውጥ፡ ለማምጣት፡ የሚቻለው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ለመነሳት፡ ሲወስንና፡ ተባብሮ፡ ለፍትህ፤ ለርትእ፤ ለእኩልነት፤ ለሰላም፤ ለዲሞክራሲ፤ ለህግ፡ የበላይነት፡ ወዘተ፡ ሲነሳ፡ ብቻ፡ ነው። የመነሳት፡ ልምድ፡ አለው። ለመነሳት፡ እንደሚፈልግ፡ ብዙ፡ ምልክቶች፡ አሉ። ውጭ፤ ያለን፡ ለአገርና፡ ለሕዝብ፡ ሰብአዊ፡ መብት፡ የቆምን፡ ተረዳድተን፡ ለአገርና፡ ለሕዝብ፡ በማንኛውም፡ መንገድ፡ የማያቋርጥ፡ ድጋፍ፡ መስጠት፡ ግዲታችን፡ የሚሆነው፡ ለዚህ፡ ነው። ይህን፡ ለማድረግ፡ የሚጎድለን፡ ገንዘብና፡ እውቀት፡ ሳይሆን፡ ፈቃደኛነትና፡ ቁርጠኝነት፡ ነው።
ህወሃት፡ ያጠመደልንን፡ ወጥመድ፤ የብዙ፡ ማህበረ፡ ሰብን፡ አገር፡ በዘር፡ መከፋፈል፡ ችላ ብለን፤ ካለንበት፡ ደረጃ፡ ደርስናል። ይህ በራሳችን፡ ድክመት፤ በራሳችን፡ መበታተን፤ በራሳችን፡ እርስ፡በእርስ መኮራረፍ፤ በራሳችን አገር ሳይኖረን፡ ከፖለቲካ ዉድድር፡ ላይ፡ ማተኮር፤ በራሳችን ራስ ወዳድነት፤ በራሳችን፡ ትእቢት/ጉራ፤ በራሳችን ፍርሃት እና በራሳችን፡ ስንፍና፤ ህወሃት፡ ባጠመደልን፡ ወጥመድ፡ ገብተን፡ እርስ፡ በእርስ ሰንጣላ፡ ወገኖቻቺን፡ የመሪ ያለህ፤ የድርጅት ያለህ፤ እያሉ ነው። ህወሃት፡ እየነጣጠለ፡ ሲመታን፡ አደጋው፡ እኛጋ፡ እስከሚደርስ፡ የምንጠብቅ፡ ብዙ፡ ነን። ምንም፡ እንኳን፡ ኢትዮጵያ፡ በምንም፡ ትጠፋለች፡ ብየ፡ ባላምንም፤ አሁን፡ ከዱሮው፡ በመረረ፡ አገር፡ የማጣት፡ እድላችን ያመዝናል፡ የሚለው፡ ትንተና፡ ቁም፡ነገር፡ እንዳለው፡ እጋራለሁ። ኢትዮጵያ፡ የሱማልያ፤ የርዋንዳ፤ የላበሪያ፤ የኮንጎ፡ ኪንሻሳ፡ አይነት፡ እድል፡ ሊገጥማት፡ ይችላል፡ ብሎ፡ ለአላማ፡ አንድነት፡ መሰብሰብ፡ ከማንኛውም፡ ወቅት፡ የበለጠ፡ አስፈላጊ፡ ነው። የመጀመሪያው፡ መሰረተ፡ እምነት፡ የኢትዮጵያ፡ መንፈስ፡ በምንም፡ አይናጋም፤ ኢትዮጵያ፡ የምትባል፡ አገር፡ አገራችን፡ ናት፤ ታሪካችን፡ የአንድ፡ ነገድ፤ ወይንም፡ የአንድ፡ ዘር፤ ወይንም፡ የአንድ፡ ሃይማኖት፡ ብቻ፡ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ፡ የጋራችን፡ ናት፤ተባብረን፡ መድረስ፡ የሁላችን፡ ሃላፊነት፡ ነው፡ ማለት፡ ስንችል፡ ብዙ፡ ነገሮች፡ መልክ፡ እንደሚይዙ፡ ማመንታት፡ የለብንም። ይህ፡ ሊሆን፡ የሚችለው፡ እኛ፤ በተለይ፤ ተማርን፡ የምንለው፡ የድሃ፡ ህዝብ፡ በረከት፡ ውጥየቶች፡ እንደገና፡ ለመማር፡ ፈቃደኛ፡ ሆነን፡ በዘር፡ የተቀባና፡ የተመረዘ፡ የፖለቲካና፡ የስነልቦና፡ ፍልስፍና፡ ስናስወግድ፡ ነው።

ራሳችን፡ ሳንለውጥ፡ ለማንም፡ የለውጥ፡ ሃዋርያ፡ ለመሆን፡ አንችልም። ስራቱ፡ ባስቀመጠልን፡ መርዝ፡ አዙሪት፡ ታውከን፡ ለውጥ፡ አናመጣም። እንዲያውም፡ ራሳችን፡ ካልለወጥን፡ የችግሩ፡ አካል፡ እንሆናለን። በቋንቋ፡ ብቻ፡ ተለያይተን፡ መላው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ የደማላትን፤ የሰው፡ ፍጥረት፡ መነሻ፡ የሆነችውን፡ አኩሪ፡ አገር፡ ብናጣ፡ ውርደቱ፡ የሁላችን፡ ነው። ህወሃት፡ ቋንቋን፡ እንደ፡ ማነቆና መለያያ፡ አድርጎ፡ ለመሳርያ፡ የሚጠቀምበት፡ የተቆላለፈውን፡ ህብረተስብ፡ ለመበታተን፡ ነው። ተቆላላፊነት፤ አብሮ፡ በሰላም፡ መኖር፤በጋራ፡ አገርን፡ መጠበቅ፤ ዘላቂነትና፡ ፍትህ፡ ያለበት፡ ስራት. መሻት፡ ከጥሩ፡ እስየቶቻቺን፡ መካከል፡ ተቀዳሚነት፡ አላቸው። ህወሃት፡ ይህን፡ ህብረ፡ ብሂየራዊ፡ የተስፋ፡ ቅርስ፡ እየናደው፡ ነው።

ለዚህ፡ አስተሳሰብ፡ ዋና፡ የመደምደሚያ ምክንያት፡ ፈላጭ፡ ቆራጭ፡ የሆነው፡ የመለስ፡ መንግስት የራሱን ህገ መንግስት ፣ አንቀጽ፡ ፫፪ን፡ ሙሉ በሙሉ ጥሶ፡ የዘር ማጥፋት ፡ ኢላማውን፡በተባባሰ፡ ሁንየታ፡ በአማራ ሕዝብ፡ ላይ መዘርጋቱ ፡ አዲስ፡ መለኪያ፡ ስለሆነ፡ ነው። ህግ፡ በማይከበርበት፡ አገር፡ በሰላም፡ ለመኖር፤ ኑሮን፡ ለማሻሻል፤ለማደግ፤ ንብረት፡ ለማፍራት፡ አይቻልም። አሁን፡ የምናየው፡ ኢትዮጵያዊነት፤ የማንኛውም፡ ኢትዮጵያ፡ ተወላጅ፡ መብት፡ ሳይሆን፡ ህወሃት፡ እንደፈለገ፡ የሚሰጠው፤ አንደፈለገ፡ የሚነጥቀው፡ ሁኗል። ማንም፡ በኑሮው፤ በማሳው፤ በሃብቱ፤ በሰብነቱ፡ ሊመካ፡ ከማይችልበት፡ ደረጃ፡ ላይ፡ ደርሰናል። ማንም፡ በአገሩ፡ ሊኖር፡ አይችልም። ማንኛውም፡ መብት፡ ከመቅጽበት፡ ሊወሰድ፡ እንደሚችል፡ ደጋግመን፡ አይተናል። የመናገር፤ የመሰብሰብ፤ የመንቀሳቀስ፡ ወዘተ፡ መብቶች፡ ሁሉ፡ እንደ፡ ችሮታ፡ በህወሃት፡ የሚሰጡ፤ እንደቅጣት፡ የሚነሱ፡ ሆነዋል። የሕዝብን፡ ሰቆቃ፡ ከህገ፡ መንግስቱ፡ አንጻር፡ ብናየው፡ ይህኑ፡ ጸረ፡ ፍትህ፤ ጸረ፡ እርትእ፤ ጸረ፡ ርጋታ፤ ጸረ፡ ኢትዮጵያዊነት፤ ጸረ፡ዘላቂነትና፡ ጸረ፡ተሳትፊያዊነት፡ እድገት፡ ነው። ሰው፡ በሃገሩ፤ ሃብት፡ ለመያዝ፤ ለመኖር፤ ለመንቀሳቀስ፤ ማሳ፡ ኑሮት፡ ለማረስ፤ ራሱን፡ ለማሻሻል፡ ካልቻለ፡ ዚየግነቱ፡ የት፡ ላይ፡ ሊሆን፡ እንደሚችል፡ ለማወቅ፡ አይቻልም። የበላይ፡ አዛዦችን፡ ባህርይና፡ ተግባር፡ የሚያሳይ፡ ሰእል፡ ከፊታችን፡ ተደቅኖ፡ የሚታይ፡ ለዚህ፡ ነው። የህግ፡ መከበር፡ ለሰላምና፡ ርጋት፤ ለእኩልነትና፡ እድገት፤ ለዚግነት፤ ለአገራችን፡ ተክታታይነት፡ ቁልፍ፡ነው። ይህ፡ ርጋታና፡ ዘላቂነት፡ የአማራ፡ ሆነ፡ ልዩ፡ ልዩ፡ የህብረተሰብ፡ ክፍሎች፡ በተለያየ፡ ወቅት፡ በህይወታቸው፡ ዋጋ፡ እየከፈሉበት፡ ነው። በታሪካችንም፡ በህይወታቸው፡ ዋጋ፡ ከፍለውበታል።
ህጉ፡ ምን ፡ ይላል?

ህጉ፡ የሚለውን፡ አይቶ ማነው፡ ወንጀለኛ፡ ብሎ፡ ማመዛዝን የሁላቺንም፡ አጣዳፊ፡ ተግባርና፡ ሃላፊነት ነው። “ማንም ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ወይንም ፡ በህግ፡ በኢትዮጵያ፡ የሚኖር፡ ሁሉ በአገሩ፡ ለመንቀሳቀስና፡ ለመኖር መብቱ ነው፡” የሚለው ህግ ማን በዚህ፡ ህግ፡ ለመጠቀም፤ ማን፡ ለመኖር፤ ማን ላለመኖር እንደሚችል በተግባር፡ እየመሰከረ ነው። የአማራ፡ ሕዝብ፡ የዚህ፡ መብት፡ ተሳታፊ፡ አይደለህም እየተባለ፡ ነው። የዚህ፡ ህብረተስብ፡ አገዳ፤ በሃይል፡ መሰደድ፤ መፈንቀል፤ ከማሳው፡ መወገድ፡ ወዘተ፡ ከፖለቲካ፡ የበላይነትና፡ ከተፈጥሮ፡ ሃብት፡ ቁጥጥር፡ ጋር፡ የተያያዘ፡ መሆኑ፡ ብዙ፡ ማስረጃ፡ አለ። አይጋ ፡የተባለው፡ የህወሃት (ድረ፡ ገጽ)፡ እና፡ በአዲስ፡ አበባ፡ ነዋሪ፡ የሆነች፡ የፓርቲው፡ ደጋፊ፡ ወይዘሪት፡ ሚሚ ሰብሃቱ፡ ያሉትን፡ ስናይ፡ ነገሩ፡ አስክፊ፡ ደረጃ ፡ ላይ መድረሱንና፡ ፕሮፓጋንዳ፡ እንደ፡ እውነት፡ የሚነገር፡ መሆኑን፡ ያሰምርልናል። ሁለቱም፡ የፖለቲካ፡ እንጅ፡ የህግ ምንነትን፡ ለማሳየት፡ አልሞከሩም፤ አልፈለጉም። አብዛኛው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ የሚለው፤ በአሁኑ፡ ወቅት፤ ያለምንም፡ ገደብ፤ የትም፡ ቦታ፡ ለመኖር፤ ለመስራት፤ ለመግዛት፤ ቦታና፡ ማሳ፡ ለመመራት፤ ስራ፡ ለማግኘት፡ የከፍተኛ፡ ትምህርት፡ እድል፡ ለማግኘትና፡ ሃብት ለመያዝ የሚችሉ፡ የፓርቲው፡ ባለስልጣኖችና፡ ከፍተኛ፡ አባላት፤ ሁነኛ፡ ደጋፊወች፤ ምርጥ፡ የትግራይ፡ ተወላጆች፤ የውጭ፡ ባለሃብቶች፡ ብቻ፡ ናችው።ሁላችንም፡ እዚህ፡ ግንዛቢየ፡ ላይ፡ብንደርስ፡ አያስደንቅም። ለዚህ፡ የህዝብ፡ አስተሳሰብ፡ ዋና፡ ምክንያት፡ የሆነው፡ ስራቱ፡ በይፋ፡ የሚያደርገው፡ አይን፡ ያወጣ፡ በበላይ፡ ባለስልታኖች፡ ብልግና፤ በህወሃት፡ ወገናዊ፡ አድሎና፡ ዘረፋ፡ ነዉ፡፡ ሑለቱም፡ ከላይ፡ የተጠቀሱት፡ ደጋፊወች፡ ያሉት እንዲህ ነው።

ካሉበት፡ ተገደው፡ የወጡት፤ ሰብነታቸውን፡ ህወሃት፡ የገፈፈው፡ አማራዎች “ከህግ ዉጭ፡ ባልተፈቀደላቸው፡ ቦታ፡ ሰለሚኖሩ” ነው፤ ይላል። እነሱ፡ በሃገራቸው፡ “ህገ፡ወጥ፡” ናቸው፡ ማለት፡ ነው።እዚህ፡ ላይ፡ ብቻ፡ የሚያጠያይቀው፡ የአማራ፡ ህብረተሰብ፤ ህገ-ወጥ፡ ከሆነ፡ የትግራይ፡ተወላጆችን፡ ከትግራይ፡ ውጭ፡ ለመኖር፤ ለመስራት፤ የከተማ፡ ቦታና፡ ማሳ፡ የትም፡ ክልል፡ ውስጥ፡ ለመያዝ፤ ሃብት፡ለማከማቸት፤ የትም፡ ቦታ፡ ለመነገድ፡ ወዘተ፡ ማን፡ ህጋዊ፡ አደረጋቸው፡ ብሎ፡ አንድ፡ ሰው፡ ቢጠይቅ፡ መልሱ፡ እንቆቅልሽ፡ ነው። አጋላጭ፡ ነው። ከዚህ፡ ላይ፡ ታሪክ፡ የሚመዘግበው፡ የኢትዮጵያዊነት፡ መለኪያ፡ ጋዚየጣዊ፡ መግጫ፡ ከሰጡት፡ የፖለቲካ፡ ድርጅቶች፡ መካከል፡ አንዱ፡ የኢትዮጵያን፡ በእኩልነት፡ የተመሰረተ፡ አንድነት፡ የሚደግፍ፡ የኦነግ፡ ከፍል፡ በዚህ፡ ወር፡ አጋማሽ፡ ላይ፡ “ህወሃት፡ በሰላማዊ፡ የአማራ፡ ህብረተሰብ፡ ላይ፡ የሚያደርገው፡ ኢሰባዊ፡ መፈንቀል፤ ያለ፡ አግባብ፡ በሃይል፡ ከማሳና፡ ኑሮ፡ አስገድዶ፡ ማስወጣት፡ ወንጀል፡ ነው” ያለው፡ እንከን፡ የለውም። በተለይ፡ ይህ፡ ድርጊት፡ በህጻናት፤ በአናቶች፤ በአባቶች፤ በማሳ፡ የግብርና፡ ስራ፡ የተሰማሩ፡ ኢትዮጵያዊያን፡ ላይ፡ የሚደረገው፡ ዘመቻ፡ ህዝብን፡ ከህዝብ፡ ጋር፡ ለማጋጨት፤ እርስ፡ በእርስ፡ ለማጣላት፤ ብሎም፡ የህወሃትን፡ የፖለቲካና፡ የተፈጥሮ፡ ሃብት፡ የበላይነት፡ ለቡድኑ፡ ለማስተላለፍ፡ ስለፈለገ፡ ነው፡ የሚለው፡ አግባብ፡ አለው። የሰውን፡ ስሚት፡ በመቀስቀስ፤ የኢትዮጵያን፡ ህዝብ፡ እርስ፡ በእርስ፡ ከማጣላት፡ ባሻገር፡ ለማንኛውም፡ ህብረተሰብ፡ ክፍል፡ አይበጅም። የኦነግ፡ መግለጫ፡ የህወሃት፡ ደጋፊዎወችን፡ ሁሉ፡ ያጋልጣል። ሆኖም፡ የኢትዮጵያን፡ ሕዝብ፡ ያቀራርባል። ተቻችሎ፡ ሰላምን፤ የሕዝብ፡ መብትን፤ በእኩልነት፡ አዲስ፡ የትግል፡ምራፍ፡ ለመክፈት፡ ያመቻቻል፤ በር፡ ይከፍታል።

አይጋ፡ በተለይ ያለው፡ የሚዘገንን፡ አባባል፡ “የአማራው ሕዝብ የአካባቢውን፡ ነዋሪወች፡ አንጡራ፡ የተፈጥሮ፡ ሃብት ወስደ። ይህ፡ ማራቆትና፡ እና፡ ማደህየትን ያመጣል።” የትም፡ ሃገር፤ ማንኛውም፡ የሃገር፡ ተወላጅ፡ በዚግነቱ፡ አገሩ፡ ውስጥ፡ ሰርቶ፡ መኖር፡ የአካባቢ፡ ህዝብ፡ ይጎዳል፡ ሲባል፡ የመጀመሪያ፡ መሆኑ፡ ነው። በአሁኑ፡ ወቅት፡ ለሙሉ፡ ዘረፋ፤ ሙስና፤ ያለ፡ አግባብ፡ በአመት፡ ከ፫፡ ቢሊዮን፡ ዶላር፡ በላይ፡ ወይንም፡ ከአምሳ፡ አምስት፡ ቢሊዮን፡ የኢትዮጵያ፡ ብር፡ በላይ፡ ከአገር፡ ህገ-ወጥ፡ በሆነ፡ መልክ፡ የሚያሸሽ፡ ማን፡ እንደሆነ፡ የውጭ፡ አገር፡ ዘገባወች፡ ያሳያሉ። እነዚህ፡ የስራቱ፡ አዲስ፡ ተጠቃሚወች፡ በአንድ፡ በኩል፡ የትም፡ ለመኖር፤ የትም፡ ሃብት፡ ለማካበት፤

የትም፡ ለመንቀሳቀስ፤ የትም፡ የተፈጥሮ፡ ሃበት፡ ለመያዝ፤ የትም፡ ለመዝረፍና፡ እቃና፡ ገንዘብ፡ እንደልብ፡ ለማሸሽ፡ ወዘተ፡ ይችላሉ። የፖለቲካ፡ የበላይነት፡ ለስርቆት፤ ለአድሎ፤ገንዘብ፡ ለማሸሽ፤ ወዘተ፡ እየረዳ፡ እናየዋለን።
በአሁኑ፡ ወቅት፡ አዲስ፡ አበባ፡ ቦልየ፡ ሰፈር፡ የምርጥ፡ ትግራይ፡ መኮንኖች፡ በርካታ፡ ሰማይ፡ ጠቀስ፡ ፎቆች፤ ግምታቸው፡ እያንዳንዳቸው፡ ክ45 እስክ 90 ሚሊዮን፡ ብር፡ (ክባንክ፡ የመጣ)፡ የሚሆን፡ ስለተደረደሩበት፡ ይህን፡ አካባቢው፡ ሕዝቡ፡ “ክልል፡ አንድ” ብሎታል። ይህ፡ ስም፡ የትግራይ፡ ክልል፡ መሆኑን፡ አንባቢው፡ ይረዳዋል፡፡ የህወሃት፡ ደጋፊወች፡ የማይቀበሉት፡ የስልጣንና፡ የሃብት፡ ክምችት፡ መብት፡ ለትግራይ፡ ገዢ፡ ቡድንና፡ ታማኝ፡ ደጋፊወች፡ ብቻ፡ ነው፡ የሚለውን፡ የህወሃትን፡ የግል፡ ፍልስፍናና አመራር፡ ነው። በዚህ፡ ፍልስፍና፡ መሰረት፡ ይህ፡ ቡድን፡ ስልጣን፡ ላይ፡ ለመቆየት፤ ሃብት፤ ለማካበት፡ የግድ፡ ተወዳዳሪ፡ የሆኑ፡ ወይንም፡ ሊቀናቀኑ፡ ይችላሉ፡ የሚላቸውን፡ ሁሉ፡ ማቀበ፡ ወይንም፡ ማስወገድ፡ አለበት። ቁልፍ፡ የሆኑ፡ የተቋም፡ መሪወችን፡ ከደሞዛቸው፡ በላይ፤ ግልጽና፡ አሳፋሪ፡ በሆነ፡ መልክ፡ የፍጆት፤ የቅንጦት፡ አኗኗር፡ እንዲኖሩ፡ ያደርጋል። የህወሃት፡ ጀነራሎች፡ ታላላቅ፡ ፎቆች፡ ለመግዛትና፡ ወይንም፡ ለመገንባት፡ የቻሉት፡ በዚህ፡ “ደግፈኝ፡ እደግፍሃለሁ” በሚል፡ የስልጣን፡ ማቆያ፡ ስልት፡ ነው። ደጋፊወች፡ ለመቀበል፡ የማይፈቅዱት፡ ግን፡ አማራ፡ ሆነ፤ ኦሮሞ፤ አፋር፡ ሆነ፤ ሶማሊ፡ወዘተ፡ በሃገሩ፡ ያለ፡ ገደብ፡ ሊወዳደር፤ የግል፡ ሃብት፡ ለማቋቋም፡ አይችልም። የህወሃት፡ አመራር፡ ፈቃድና፡ ታማኝነት፡ ያስፈልገዋል። ጥቅሙ፡ መታየትና፡ መገምገም፡ አለበት። ማንኛውም፡ ማስረጃ፡ የሚያሳየው፡ የተዘረጋው፡ የኢኮኖሚ፡ የበላይነት፡ ፍጹም፡ የትግራይ፡ ምርጥ፡ ቡድንና፡ ታማኝ፡ ደጋፊወቹ፡ መሆኑን፡ ነው። ይህ፡ ሊሆን፡ የቻለው፡ የፖለቲካውና፡ የኢኮኖሚው፡ ዘርፎች፡ የተቆላለፉ፡ በመሆናቸው፤ ተወዳዳሪነት፡ ባለመኖሩ፤ ባለመፈቀዱ፤ ክልክል፡ በመሆኑ፡ ነው። በብዙ፡ የአፍሪካ፡ አገሮች፡ በታሪክ፡ እንደታየው፡ ሁሉ፤ የፖለቲካ፡ ስልጣን፡ መያዝ፡ ለሃብት፡ ክምችት፡ ቁልፍ፡ ነው። ለሙስና፡ አስፈላጊ፡ ነው። የኢትዮጵያን፡ ለየት፡ የሚያደርጉት፡ ብዙ፡ ምክንያቶች፡ አሉ። ጥቂቶቹ።
የህወሃት፡ ምርጥ፡ ቡድን፡ የሃብት፡ ክምችት፡ በቃኝን፡ አያውቅም። ይሉኝታን፡ አያውቅም። ይቅር፡ ባይነትን፡ አያውቅም። የሰው፡ ልጅ/የግለሰብ፡ መብትን፡ አያውቅም። በህግ፡ የመዳኘትን፡ ምንነት፡ አያውቅም፤ አይቀበልም። በህግ፡ የበላይነት፡ አያምንም። አብሮ፡ መኖርን፡ ይፈራል። የሚያውቀው፡ ዋና፡ እምነት፡ ፍጹም፡ የጠባብ፡ በዘርና፡ በጠባብ፡ ቡድን፡ የተደራጀ፡ የበላይነትን፡ ብቻ፡ ነው። የተፈጥሮ፡ ሃብትን፡ ሙሉ፡ ቁጥጥር፡ ማየት፡ ለዚህ፡ ይጠቅማል፡
የኦክላንድ ተቋም (ኦክላንድ፡ ኢንስቲቱት) ያለውን፡ ማየት፡ በቂ ነው። በጋምቢየላ ብቻ 75 በመቶ የሚሆነው፡ ለውስጥ፡ ባለሃብቶች፡ የተስጠው፡ ማሳ (ለም፡ የእርሻ፡ ቦታ) ለትግራይ ተወላጆች፡ መሆኑን፡ መዝግቧል። በኢኮኖሚው፡ ዘርፍ፡ የሚታየው፤ ይህንን፡ የሚመስል፡ ፍጹም፡ የበላይ፡ ቁጥጥር፡ የውጭ፡ ታዛቢወችን፡ ለብዙ፤ አመታት፡ ሲያነጋግር፡ ቆይቷል። “ትግራይ የግላችን፡ ኢትዮጵያ የጋራቺን” የሚለው፡ የኢትዮጵያዊያን፡ ከዚህ፡ የበላይነት፡ የመነጨ፡ ነው። ለምርጥ፡ የትግራይ አዲስ ሃብታሞች፡ አገልጋይ፡ እስከሆነ፡ ድረስ፡ ማንኛውም፡ የስራ፡ ዘርፍ፡ ህጋዊነት አለው። ቡድኑ፡ እንደፈለገ፡ አገር፡ ሊቸረችር፤ ይችላል። ግድያም፡ ሊያደረግ፡ ይችላል። የራሱ፡ ታማኝ፡ ደጋፊ፡ ካልሆነ፡አንድ፡ ሰው፡ ህገወጥ፡ ነህ፡ ለማለት፡ ይችላል። ህጉን፡ ጠምዝዞ፡ ለማሰር፡ ይችላል። አዙሮ፡ ሰው፡ ባልፈጸመው፡ ወንጀል፡ “ይቅርታ፡ ጠይቅ/ጠይቂ” ለማለት፡ ይችላል። ባጭሩ፤ በኢትዮጵያ፡ መኖር/አለመኖር፡ በዚህ፡ መነጽር፡ የሚታይ፡ እየሆነ፡ ሂዷል። እዚህ፡ ላይ፡ ማስተዋል፡ ያለብን፡ እበይት፡ ነገር፡ አለ።

የመለስ፡ መንግስት፡ ሕጉን፡ ሲጠመዝዝ፡ ድርጊቱ፡ አብዛኞቹ፡ የአለም፡ መንግስታት፡ ከተቀበሏቸው፡ የህግ፤ የሚዛናዊ፡ እድገት፡ መስፈርቶችና፡ የሰባዊ፡ መብት፡ መለኪያወች፡ እጅግ፡ የተራራቀ፡ ነው። ለምን፡ እንደተራራቀ፡ እናውቃለን። የብድር፡ ለጋሾች፡ ህገ፡ መንግስቱ፡ ሲጣስ፡ ለምን፡ ዝም፡ እንዳሉ፡ እናውቃለን። በውድድር፡ እናምናለን፡ የሚሉ፡ ለጋስ፡ መንግስታትና፡ አበዳሪ፡ ድርጅቶች፤ በተለይ፡ አለም፡ ባንክ፡ ለምን፡ በድፍረት፡ ውድድር፡ አልባ፡ ስለሆነ፡የኢኮኖሚ፡ አመራር፡ እንድማይናገሩ፡ እናያለን። ምክንያቱ፡ ይህ፡ ነው። የራሳቸው፡ ጥቅም፡ እስካልተነካ፡ ድረስ፤ አንድን፡ አገር፡ “ስይጣን” ወይንም፡ “ዝንጀሮ” ቢገዛ፡ ግድ፡ የላቸውም። የአፍሪካ፡ አንድነት፡ ድርጅት፡ ሆነ፡ የተባበሩ፡ መንግስታት፡ የሰባዊ፡ መብት፡ ድርጅት፡ የህወሃትን፡ ኢሰባዊ፡ ድርጊቶች፡ ተጠያቂ፡ መሆን፤ የሚመለከታቸው፡ ባለስልጣኖች፡ እነማን፡ እንደሆኑ፡ ያውቃሉ። ዝም፡ ብለው፡ የሚመለከቱበት፡ ዋና፡ ምክንያት፡ እኛ፡ በመካከላችን፡ያለው፡ በአንድ፡ ድምጽ፡ ለመናገር፡ አለመቻል፤ ለኢትዮጵያና፡ ለመላው፡ ሕብረተሰብ፡ መብቶችና፡ ጥቅም፡ አብረን፡ ለመቆም፡ አለመደራጀት፡ ናቸው። ይህ፤ ባስቸኳይ፡ መፈታት፡ አለበት። የጎሳና፡ የቋንቋ፡ ስራትና፡ አስተዳደር፡ በምንም፡ ሰላምና፡ ፍትሃዊ፡ እድገት፡ አያመጣም። እንደ፡ አለም፡ ባንክ፡ የውስጥ፡ ዘገባ፤ “የህዝብ፡ ተሳትፎ፡ የሊለበት፡ የልማት፡ አመራር፡ ድህነትን፡ አያጠፋም፤ የአብዛኛውን፡ ኑሮ፡ አያሻሽልም።” እንኳን፡ ለቀረው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ኑሮ፡ መሻሻል፡ ቀርቶ፡ ለኢሃደግ፡ ሰፊ፡ አባላትም፡ አያዋጣም፡ ማለት፡ ነው።
በአልጭሩ፤ ከላይ፡ የቀረበው፡ እንደሚያሳየው፡ ለጥቅምና፡ ለፖለቲካ፡ ፍጹማዊ፡ የበላይነት፡ የቆመው፡ የኢሃደግ፡ ስራት፤ በተለይም፡ ህወሃት፡ በበላይነት፡ የሚመራው፡ መንግስት፤ ለሃገር፡ ዘላቂ፡ ጥቅም፤ ለሏአላዊነትና፡ ለነጻነት፤ ለመላው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ሰላም፤ ለሰው፡ ክብር፤ ለሰብነት፤ ለአብሮ፡ መኖር፤ ለሰባዊ፡ መብት፡ ለሁሉም፡ እድገት፤ ለጋራ፡ ብልጽግና፤ ለፍትህ፡ ወዘተ፡ ደንታ፡ የለውም።

በተግባር፡ የሚያሳየው፡ ሊኖረው፡ እነደማይችል፡ ነው። ለዚህ፡ ጨለማ፡ ለሚመስል፡ የህወሃት፡ አገዛዝ፡ በደል፡ ጥልቀት፡ ያላቸውን፤ በማስረጃ፡ የተደገፉ፡ ሃሳቦችና፡ አማራጮች፡ በተከታታይ፡ አቀርባለሁ።

ክፍል፡ ሁለት፡ ይቀጥላል
ሚያዝያ፡ ፲/፪ዖ፬

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 23, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.