የታሪክ፡ ተጠያቂወች፡ ሁነናል። ለጎሳዊ፡ ስነ፡ ልቦና፡ አናጎብድድ

ክፍል፡ ሶስት፡

አክሎግ፡ ቢራራ (ዶር)

ይህ፡ በተከታታይ፡ የማቀርበው፡ ሁለ-አቀፍ፡ ትንተና፡ ሶስተኛ፡ ክፍል፤ ካለፉት፡ ሁለት፡ ትንተናወች፡ ለየት፡ ይላል። የሚለይበትም፡ ዋና፡ ምክንያት፤ ባለፉት፡ እንዳስቀመጥኩት፤ የህወሃት፡ ጠባብ፡ ብሄርተኛ፡ ቡድን፡ ፍልስፍና፡ መሰረት፡ መነሻው፡ ባለፉት፡ መቶ፡ አመታት፡ የአማራ፡ ብሄር፡ ህብረተሰብ፡ “ጨቋኝ፤ ነብሰ-ገዳይ፤ ነፍጠኛ፤ የተጠላ፤ ዘራፊ፤ ቅኝ-ገዥ”፤ በሚሉ፡ በመርዝ፡ የተቀባ፡ የዘር፡ መለያ፡የስነ-ልቦና፡ ጦርነት፡ ማካሄዱና፡ በተለይ፡ አብዛኛውን፡ ሃሁ፡ የቆጠረውን፡ ክፍል፤ በዚህ፡ መሰረት፡ በሌለው፡ ክስ፡ተስቦና፡ ተበክሎ፤ እራሱን፡ እንዲጠራጠር፤ በእራሱ፡ እንዳይተማመን፤ ማንነቱን፡ እንዲከዳ፤ በአጎብዳጅነት፡ እንዲኖር፤ ፈሪና፡ አሞት፡ የሌለው፡ እንዲሆን፤ እርስ፡ በእርሱ፡እንዲከፋፈል፡ ማድረጉ፡ ከባድ፡ ሸክም፡ ሆኖ፡ ቆይቷል። ይህን፡ ሸክም፡ ማስወገድ፡ ያለብን፡ እኛ፡ እንጂ፡ህብረተሰባዊ፡ ምሰሷችን፡(the pillars of community and affinity)፤ ታጥቆ፤ እያናጋው፡ ያለ፤ ህወሃትና፡ደጋፊወቹ፡ ሊሆኑ፡ አይችልም።
የህወሃት፡ ፈጣሪወች፤ ህዝብን፡ ከህዝብ፡ ጋር፤ ሃይማኖትን፡ ከሃይማኖት፡ጋር፡ ካላጋጩ፤ ሰውን፡ለጥቅም፡ ፍላጎት፡ ካልሳቩ፤ ተቃዋሚ፡ የሆነውን፡ ካላሳደዱ/ካላሰሩና፡ ሁሉ፡በፍርሃት፡ በእራሱ፡ ላይ፡ ያለውን፡ እምነት፡ ካላስካዱ፤ በስልጣን፡ እንደማይቆዩ፤ ለጠባብ፡ አዲስ፡ “ከኪራይ-የሚገኝ፡ ሃብት፡ ፈላጊወች (new rent-seekers)፤ ጋር፡ በጥቅም፡ ተደጋግፈው፡ ሃብት፡ እነደማያካብቱ፡ያውቁታል። ጽንሰ-ሃሳቡን፡ ከውጭ፡ ቀድተው፡ ስራ፡ላይ፡ ያዋሉት፡ የበላዮች፤ የአማራ፡ ህብረተሰብእ፡ ለትግራይ፡ ብሄረሰብ፡ “አጥፊና፡ አቆርቋዥ” መሆኑን፡ ቀስ፤ በቀስና፡ በዘዴ፤ እኛንና፡ ሌሎችን፡ አሳምነው፡ የፖለቲካ፤ የባህል፤ የኢኮኖሚ፤ ወዘተ፡ ስልጣንና፡ አቅም፡ ከአማራውና፡ ከሌሎች፡ ነጥቀው፡ ወደ፡ ትግራይ፡ ጠባብ፡ ቡድን፡ በዘዴ፡ ማሸጋገሩን፡ በተናጥል፤ ማለትም፤ ከእኛ፡ ባህርይና፡ አሰራር፡ ለይተን፡ መመልከት፡ አንችልም፡ እላለሁ። ምክኒያቱም፤ ውሸት፡ በህወሃት፡ ተደጋግሞ፡ ከተነገረ፡ እውነት፤ እውነት፡ ይሸታል። ይህን፡ ውሸት፡ ህወሃትና፡ ደጋፊወቹ፡ ብቻ፡ ሊያሰራጩት፡ አይችሉም። ለምሳሌ፤ ሌላውን፡ ለማሳመን፡ የተቀነባበረ፡ ፕሮፓጋንዳ፡ ደጋግመው፡ ማስተጋባት፡ አለባቸው። የኢትዮጵያ፡ ምጣኔ፡ ሃብት፤ በድርብ፡ አያደገ፡ ፍትሃዊ፡ ውጤት፡ አሳይቷል፡ የሚለውን፡ እንይ።

በዚህ፡ ሳምንት፡ በአሜሪካ፡ ድምጽ፡ ሬዲዮ፡ ተጋብዠ፡ ከአንድ፡ በ ኢትዮጲያ፡ ከሚኖሩ፡ ባለሙያ፡ ጋር፡ “ፍትሃዊ፡ እድገት፡(equitable growth) አለ፡ ብለው፤ በአንድ፡ የአለም፡ አቀፍ፡ ስብሰባ፡ ላይ፤ ጠቅላይ፡ ሚኒስትር፡ መለስ፡ ስለተናገሩት፡ ያደረግነውን፡ ክርክር፡ ለአንባቢ፡ አቀርባለሁ። እኒህ፡ ባለሙያ፤ ጠቅላይ፡ ሚኒስትሩን፡ ደግፈው፡ የኢትዮጵያ፡ በአመት፤ አስራ፡ አንድ፡ በመቶ፡ እድገት፡ ያሳየው፡ እኮኖሚ፡ (ምጣኔ፡ ሃብት)፤ “ፍትሃዊ” መሆኑ፡ የሚታየው፡ “የገጠሩ፡ሰማንያ፡ አምስት፡ በመቶ፡ የሚሆነው፡ ገበሬ፡ ሕዝብ” በአገራችን፡ “ያልታየ፡ የኑሮ፡ መሻሻልን፡አስመስክሯል፤ ይህን፡ ባይናችን፡ እያየነው፡ ነው፡” ያሉት፡ ነው። ተናጋሪው፡ ይህን፡ ማቅረባቸው፡ አላስገረመኝም፤ ስርአቱን፡ ከደገፉ፡ ተጻራሪ፡ ሃሳብ፡ ለማቅረብ፡ አይችሉም። መብታቸውን፡ አከብራለሁ። እኔ፡ የማየው፤ ከአብዛኛው፡ ድሃ፡ ህዝብ፡ ድህነት፤ በምግብ-የዋጋ፡ ግፍሸት፡ ከሚሰቃየው፡ ኢትዮጵያዊ፤ በ፡ 2012 “የህጻናት፡ መድህን፡ (Save the Children)፤ ባወጣው፡ “ከ20 አገሮች፡ ኢትዮጵያ፡ አስራ-ሰባተኛ፡ በመሆን፡ ለህጻናት፡ ሲኦል፡ ናት፡” ከሚለው፡

አንንጻር፡ ነው። ለተወሰኑማ፡ ዛሬ፡ ኢትዮጵያ፡ ገነት፡ መሆኗ፡ ምንም፡ አያጠያይቅም። ያስደነቀኝ፡ እንደዚህ፡ ያለ፡ተራ፡የፈጠራ፡ ወሬ፡ በኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ላይ፡ ሲካኄድ፡ ሌሎቻችን፡ (አብዛኛወቻችን፡ ማለቴ፡ ነው)፤ በያለንበት፡ አለማስተባበላችን፡ ነው። እንዲያውም፤ ከእውነት፡ የራቀ፡ አነጋገር፡ በተደጋጋሚ፡ እየተነገረ፡ ብዙወቻችን፡ “በሬ፡ ወለደ” የሚሰኘው፡ የእድገት፡ መጠን፡ እውነት፡ ይመስለናል። ማንኛውም፡ በሃቅ፡ የቀረቨ፡ ዘገቫ፡ የሚያሳየው፤ እንኳን፡ ፍትሃዊ፡ እድገት፡ ሊኖር፤ ምስኪንነት፤ ድህነት፤ እርሃብ፤ የሰውና፤ የገንዘቭ”፤ ፍልሰት፤ (destitution, poverty, hunger, human and financial capital flight): በተባባሰ፡ ህኔታ፡ ስፋትና፡ ጥልቀት፡ እያሳዩ፡ ነው። በቅርቡ፤ ቢል፡ ጌተስ፡ እንዳሉት፡ “በድህነትና፡ እርሃብ፡ የተነሳ፤ አብዛኛው፡የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ከአለም፡ አገሮች፡ በበለጠ፡ ደረጃ፤ የምግብ፡ እርዳታ፡ የሚያስፈሊጋት፡ አገር፡ ውስጥ፡ ይኖራል.” እድገት፡ ፍትሃዊ፡ ለመሆን፡ የሚችለው፡ ጥቂት፡ ሃብታሞች፡ ሚሊየነር፤ ቢሊየነር፡ ስለሆኑ፡ ሳይሆን፡ አብዛኛው፡ የኢትዮጵያ፡ ድሃ፡ ሕዝብ፡ የእድገቱ፡ ተካፋይ፡ ሲሆን፡ ነው። የነፍ፡ ወከፍ፡ እያደገ፡ ስሄድ፡ ነው። የዚህም፡ መለኪያ፡ ቢያንስ፤ አንድ፡ ዜጋ፤ በቀን፡ ሶስት፡ ምግብ፡ በልቶ፡ ሲያድር፤ ልጁን፡ ሲያስተምር፤ ጤናው፡ ሲጠበቅ፤ የተሻለ፡ መጠለያ፡ሲኖረው፤ ንጹህ፡ ውሃ፡ ለመጠጣት፡ ሲችል፡ የተማረው፡ ልጁ፡ ያለ፡ አድሎ፡ ስራ፡ ለመያዝ፡ ሲችል/ስትችል፤ ወጣቶች፡ በአገራቸው፡ እድል፡ ሲኖራቸው፡ ወዘተ፡ ነው።

ሰለሆነም፤ ከጠቅላይ፡ ሚንስትሩና፡ ከታዛዦቻቸው፡ ውጭ፡ እድገት፡ “ፍትያዊ፡ ለመሆኑ፡ምንም፡ ማስረጃ፡ የለም። እድገት፡ መኖሩን፡ ግን፡ እኔም፡ አልክድም። ዋናው፡ ጥያቄው፡ እድገቱ፡ ማንን፡ እየጠቀመ፡ ነው፡ የሚለው፡ ነው። በአመት፡ አስራ፡ አነድ፡ በመቶ፡ የሚለው፡ ግን፡ መንግስት፡ የፈጠረው፤ በነጻ፡ ታዛቢወች፡ ያልተመረመረ፡ መሆኑን፡ ለማመልከት፡ እገደዳለሁ። ኢትዮጵያ፡ እንዴት፡ ከቻይና፤ ከህንድ፤ ከቬትናም፡ ከብራዚል፤ ከጋና፤ ወዘት፡ የላቀ፡ አመት፡ በአመት፡ እድገት፡ ልታሳይ፡ እንደቻለች፡ የሚያስረዳኝ፡ አላገኝሁም። የገጠሩ፡ ህዝብ፡ ኑሮ፡ አስደናቂ፡ በሆነ፡ መንገድ፡ መዋቅራዊ፡ ለውጥ፡ የሚያሳይና፡ ህይወት፡ ለዋጭ፡ ኑሮ፡ መኖር፡ ጀምሯል፡ የሚያስብል፡ አለመሆኑን፤ ቢል፡ ጌትስ፡ ባሉት፡ የመለስኩት፡ ይመስለኛል። በርሻ፡ እረድፍ፡ የአለም፡ ባንክ፡ ባለሙያወች፡ ያጠኑት፡ የሚያሳየው፡ “የኢትዮጵያ፡ መንግስት፡ በሚለው፡ መሰረት፡ የእርሻ፡ ውጤቷ፡ አመት፤ ከአመት፡ ካደገ፡ በዚህ፡አለም፡ ያልታየ፡ ማንም፡ ያልደረሰበት፡ የአርንጓዴ፡ ለውጥ፡ ተቀናጂታለች፡ ማለት፡ ነው” ብለው፡ ባለፈፍው፡ አመት፡ የደመደሙት፤ የመንግስትን፡ የፈጠራ፡ ወሬ፡ ያመለክታል። ስለዚህ፤ ፍትሃዊ፡ እድገት፡ አለ፡ የምንል፡ ሁሉ፡ የፈጠራው፡ወሬ፡ ተባባሪ፡ እንዳንሆን፡ እሰጋለሁ። የስነ-ልቦና፡ መለወጫ፡ ዘዴ፡ ስለሆነ። ህወሃት፡ የሚለውን፡ ሁሉ፡ እንደ፡እውነት፡ ከተቀበልን፤ ለአብዛኛውን፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ አሰቃቂ፡ ኑሮ፡ ክብደት፡ አንሰጠውም፡ ማለት፡ ነው።
ቁም፡ ነገሩ፡ ግን፤ በህወሃት፡ ላይ፡ ብቻ፡ የማተኮር፡ ስነ-ልቦና፤ አገራችንና፡ ከዘጠና፡ ሚሊዮን፡ በላይ፡ የሆነውን፡ ሕዝቧን፡ ያደረሰባቸውን፡ ፈተና፡ ሙሉ፤ በሙሉ፡ አያሳይም። በጥቅሉ፡ ብናየው፡ አራት፡ ነጥብ፡ አምስት፡ ሚሊዮን፡ የሚሆን፡ የትግራይ፡ ህብረተሰብ፡ ወካይ፡ ነኝ፡ የሚለው፡ ህወሃት፡ ስልጣኑንና፡ ጥቅሙን፡ ሊያረጋግጥ፡ የቻለው፡ በእራሱ፡ ሃይል፡ ብቻ፡ አይደለም። ዋናው፡ የስልጣኑ፡ ምሰሶ፡ አድርጎ፡ የሚጠቀምበት፡ የሌሎቻችንን፡ ስነ-ልቦና፡ በመቨረዝ፤ በመስለቭ፤ በማዳከም፤ እርስ፡ በእርሳችን፡ እንድንጣላ፡ በማድረግ፤ በመከፋፍል፤ በጥቅም፤ ለጥቅም፤ ለስልጣን፡ እንድንገዛ፡ በመሳብ፤ በፍርሀት፡ ተጠምደን፡ ማንነታችን፡ እንድንክድና፡ ደፍረን፡ ለፍትህ፤ ለእርትህ፡ እንዳንቆም፡ በማድረግ፤ እንዳንደራጂ፡ የመከፋፈያ፡ ዘዴወችን፡ በያለንበት፡ በመዘርጋት፡ ጭምር፡ ነው። የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ የመዘገበው፡ በዘጠና፡ ሰባቱ፡ ምርጫ፡ ላይም፡ ያሳየው፡ በዘር፡ መለያየትን፡ ሳይሆን፡ በኢትዮጵያዊነት፡ ለአግሩና፡ ለመብቱ፡ የሚቆም፡ መሆኑን፡ ነው። ሰላማዊይ፡ ወገኑን፡ መግደል፡ ልምዱ፤ ባህሉ፤ አለመሆኑን፤ ነው።

የህወያትን፡ የተቀነባበረ፡ የስነ-ልቦና፤ ፕሮፓጋንዳና፡ እቅድ፡ መንሰኤና፡ ያስከተለውን፡ አስከፊ፡ ውጤት፡ በሚገባ፡ ለመረዳት፡ የሚቻለው፡ ከኢትዮጵያ፡ ተማሪወች፡ እንቅስቃሴና፡ ከተከተለው፡ ክፍፍል፤ እ.አ.አ. ከ 1960s ወዲህ፡ ስር፡ በመስደድ፡ ላይ፡ ያለውን፤ ጥቂቶቻችን፡ ይህ፡ በዘር፡ ልዩነትና፡ ጥላቻ፡ ላይ፡ የተመሰረተ፡ ጉዞ፡ ለማንም፡ አያዋጣም፤ አገራችን፡ ይጎዳታል፤ ሕዝቧ፡ በድህነት፡ አዙሪኝ (cycle): እንዲጠመድ፡ ያደርገዋል፡ ብለን፡ ስንከራከርበት፡ የቆየነውን፤ መተኪያ፡ የማይገኝላቸውን፡ ብዙ፡ መቶ-ሽህ፡ የሚሆኑ፤ ከሁሉም፡ ብሄር፤ ብሄረሰብና፡ ህዝብ፡ ክፍሎች፡ የተወጣጡ፤አገር፡ ወዳድ፡ ኢትዮጵያዊያን፡ ለሃገር፤ ለወግን፡ ብለው፡ መስዋእት፡ የከፈሉበትን፤ አሁንም፡ የሚከፍሉበትን፤ በጎሳ፡ የማይታረቅ፡ ልዩነቶች፡ ላይ፡ማር፡ ቀብቶ፡ ያዘጋጀልንን፤ የከፋፍለህ፡ ግዛው፡ የፍልስፍና፡ ጉዞ፡ ጠለቅ፡ ብሎ፡ በመመርመርና፡ በመረዳት፡ የሚገኝ፡ ሃቅ፡ ነው። ይህን፡ ለታሪክ፡ እተወዋለሁ። ዙሮ፡ ማንንም፡ ለመኮነን፤ ለመውቀስ፡ ሳይሆን፡ የስነ-ልቦና፡ ጦርነቱ፡ እኛን፡ ያደከመንና፡ ያከፋፈለን፡ መሆኑን፤ አሁን፡ የተጀመረ፡ አለመሆኑን፤ ይህን፡ ጎጅ፡ የፖለቲካ፡ ባህል፡ ማቆም፡ እንዳለብን፡ ለማመልከት፡ ብቻ፡ ነው።

ሀወሃት፡ አሁን፤ ከስራ፡ ላይ፡ አውሎት፡ የምናየው፡ “የብሄሮች፡ የማይታረቅ፡” ፍልስፍና፡ መሰረት፤ የአማራው፡ ህብረተሰብ፡ ሆነ፡ ተብሎ፡ በተለይ፤ በትግራይ፡ ህብረተሰብና፡ በሌሎች፡ እንዲጠላ፤ አማራው፡ እራሱን፡ እንዲጠራጠር፤ እርስ፡ በእርሱ፡ እንዲጣላና፡ እንዳይተባበር፤ በተከሰሰበት፡ አምኖ፤ አጎብዳጅ፡ እንዲሆን፤ ቀስ፡በቀስ፡ በኢትዮጵያ፡ የፖለቲካ፤ የባህል፤ የኢኮኖሚ፡ ዘርፎች፡ ሁሉ፡ አቅም፡ ያለው፡ ተወዳዳሪ፡ ሆኖ፡ እንዳይሳተፍ፤ ታሪክና፡ አስተዋጾውን፡ ሁሉ፡ እንዲያፍርበት፤ አንዳይቀበል፤ ቢቻል፡ የተማረው፡ ክፍል፡ በሙሉ፤ አገር፡ ለቆ፡ በስደት፡ እንዲኖር፡ ለማድረግ፡ ነው። ካልተቻለ፡ ደግሞ፡ ጸጥ፤ ለበጥ፡ ብሎ፤ አንገቱን፡ ሰብሮ፤ ማንነቱን፡ ክዶ፤ ተነስ፤ ውጣ፡ ሲባል፤ መብት፡ እንደሌለው፡ እዲወጣ፤ ህሊናው፡ ተበርዞ፤ እርስ፡ በእርሱ፡ ተናክሶ፤ አዲሱን፡ ስርአት፡ እንዲቀበል፡ ነበር፤ አሁንም፡ ነው። ይህ፡ ስልት፡ በአንጻሩ፡ የጣሊያን፡ ቅኝ፡ ገዦች፡ ያስተናገዱት፡ የከፋፍለህ፡ ግዛው፡ ስልት፤ የደቡብ፡ አፍሪካ፡ አፓርታይድ፡(Apartheid) የመሰለ፡ ስልት፡ መሆኑን፡ ብዙ፡ ማስረጃወች፡ መዝግበውታል።

በቅርቡ፡ አቶ፡ ገብረመድህን፡ አራአያ፡ ጠቅላይ፡ ሚንስትር፡ መለስ፡ “አማራ፡ ዋና፡ ጠላታችን፡ ነው። ይህን፡ ህብረተሰብ፡ ከስሩ፡ ማጥፋት፡ አለብን፡” ያሉት፡ ማስረጃ፡ ነው። ጠቅላይ፡ ሚኒስትሩ፡ ይህን፡ ያሉበትን፡ ዋና፡ ምክንያት፡ ብዙ፡ የውጭ፡ አገር፡ ባለሙያወች (Paul Collier/ethnic civil war; Bill Easterly, Ethiopian poverty; Michela Wrong, ethnic-based corruption and illicit outflow, etc)፤ ልይ፡ ልዩ፡ ተቋሞች (Human Rights Watch, Amnesty International, Oakland Institute, Survival International, ec)፤ የኢትዮጵያ፡ ምሁራን፤ ተመልካቾች፤ የስባዊ፡ መብት፡ ተቛሞች፡ አስረድተዋል። እኔም፡ በተከታታይ፡ ከዘጠና፡ ሰቫት፡ ምርጫ፡ በኋላ፡ ባቀርብኳቸው፡ አራት፡ መጽሃፎች፤ በተለይ፡ በ “Waves: endemic poverty that globalization can’t tackle–በተባለው፡ ላይ፡ ከብዙ፡ ዓቅጣጫ፤ በብዙ፡ ማስረጃ፡ አስቀምጨዋለሁ።

ህዝብ፡ የማይሳተፍበት፡ እድገት፡ ፍትሃዊ፡ ሊሆን፡ አይችልም፡

እነዚህና፡ ሌሎች፡ ጥናቶች፡ የሚያመለክቱት፡ ማንኛውም፡ የክልልና፡ ጠባብ፡ ብሄርተኛ፡ ስርአት፡ፍትህ/እርትህ፡ የሌለበት፤ በህግ-የበላይነት፡ የማይዳኝ፤ የህዝብ፡ ድምጽና፡ተሳትፎ፡ የሌለበት፤ የውስጥ፡ ውድድር፡ የተከለከለበት፡ ወይንም፡ አድሏዊ፡ ሆነበት፤ ግልጽነት፡ የሌለበት፡ ነው። ስለሆነም፤ እድገቱ፤

ዘላቂነትና፡ ፍትሃዊነት፡ ያለው፡ ሊሆን፡ አይችልም። ዘረኛው፡ ቡድን፤ ማን፡ ሃብታም፡ እንደሚሆን፤ ማን፡ የስራና፧ የትምህርት፡ እድል፡ እንድሚኖረው፤ ማን፡ የከተማ/የገጥር፡ መሬት፡ እንደሚያገኝ፤ ማን፡ የስራ፡ ፈቃድ፡ እንደሚሰጠው፤ ማን፡ ከፍተኛ፡ ቀረጥ፡ እንደሚከፍል፤ የማን፡ ገቪ፡ ከፍ፤ የማን፡ ዝቅ፡ እንደሚል፡ ይወስናል። ይህ፡ ስርአት፤ የሚጎዳው፡ አንድ፡ ብሄረሰብ፡ ሳይሆን፡ አብዛኛውን፡ የኢትዮጵያ፡ ድሃ፡ ህዝብ፡ ነው። ስርአቱ፡ ካልተለወጠ፡ ሁሉም፡ ይጎዳል። ጥቂት፡ ሰወች፡ ብቻ፡ ስልጣንና፡ ሃብት፡ ያካብታሉ።

ዋናው፡ ለማመልከት፡ የምፈልገው፤ ሁላችን፤ ልናጤነው፡ የሚገባን፤ ከህወሃት፡ የመነጨውን፡ የስርአት፡ ችግር፡ ከሁሉ፡ አቅጣጫ፡ ስናየው፡ ፍትያዊ፡ አይደለም፤ ሊሆንም፡ አይችልም። ይህን፡ ከተረዳን፤ ችግሩን፡ ደጋግመን፡ ብናኝክ፤ ቀን፡ ቀን፡ ከሌት፡ ብናወጣ፡ ብናወርድ፡ ቀጣይ፡ ሁኖ፡ የሚታየው፡ ክፍተት፡ የእኛው፡ ድርጂታዊ/አመራራዊ (organizational and leadership crisis)፤ መሆኑ፡ አያጠራጥም። ግፉን፡ እናያለን፡ የምንል፡ ሁሉ፡ በሚያስማሙን፡ የአገርና፡ የመላው፡ ህዝብ፡ ጉዳዮች፡ ላይ፡ ተነስተን፡ እቅድን፡ ወደ፡ ተግባር፡ ለመተርጎም፡ እንቅፋት፡ የሆኑትን፤ በተቃዋሚው፡ ዘርፍ፡ ተዘርግተው፡ ያሉትን፡ ማነቆወች፡ በግልጽ፡ ተወያይተን፡ መፍትሄ፡የምንፈልግበት፡ አሁን፡ ነው። እራሳችን፡ የምንፈጥራቸውን፡ ችግሮች፡ እስካላየን፡ ድረስ፡ የትም፡ አንደርስም። ለምሳሌ፤ ብናውቀውም፡ ባናውቀውም፤ ብንቀበለወም፤ ባንቀበለውም፤ አንዳንድ፡ በፖለቲካና፡ ማህረሰብ፡ ስብስቦች፡ ውስጥ፡ የሚገኙ፡ ግለሰቦች፡ ሌላውን፡ ያለ፡ ምንም፡ ማስረጃ፡ ስም፡ ማጥፋት፤ መወንጀል፤ መኮነን፤ ማስጠላት፤ ተግባራቸው፡ ሲሆን፡ የማይረዱት፡ ይህ፡ ባህሪይ፡ ህወሃትን፡ ደጋፊ፡ መሆኑን፡ ነው።

የእነዚህን፡ አይነት፡ ባህሪይ፡ በቀጥታ፡ መከላከል፡ የሁላችንም፡ ተግባር፡ ሲሆን፤ አብዛኛውን፡ ጊዜ፡ ሰው፡ ይቀየማል፡ ብለን፡ እናልፋለን። የፈጠራ፡ ወሬ፡ ሰምተን፡ ሳንናገር፡ ዝም፡ እንላለን። እውነት፡ ስለመናገር፡ አንድ፡ ፈላስፋ፡ ሲናገሩ፡ “ስለ፡ እራስህ/እራሽ፡ እውነት፡ ለመናገር፡ ካልቻልክ/ካልቻልሽ፤ ስለ፡ ሌላ፡ ሰው፡ ለመናገር፡ አትችልም/አትችይም፡” የተባለው፡ ሙሉ፡ በሙሉ፡ እውነትነት፡ አለው። የዘመኑ፡ ምሁር፡ ትውልድ፡ ስለ-እራሱ፡ እውነት፡ ከመናገር፡ ይልቅ፡ ስለ፡ ሌላው፤ ስለሚቃወመው፡ “ሃጢያት/መጥፎነት፡ ፈጥሮ፡ መናገር፡ ይቀለዋል። ይህ፡ልምድ፡ የጥላቻ፡ ምልክት፡ ነው። መቀቨል፡ ያለብን፤ ከየትም፡ አቅጣጫ፡ ቢመጣ፤ የፈጠራ፡ ወሬ፤ የጥላቻ፡ ፖሊቲካ፤ ስም፡ ማጥፋት፤ ለእውነት፡ ቀጥ፡ ብሎ፡ አለመቆም፡ የንጹህን፡ ሰው፡ ክብር፡ የግፋል፤ አመኔታን፡ አያጠናክርም። እንዲይውም፤ ደጋፊ፡ የሆነን፡ ግለሰብ፡ ከተሳታፊነት፡ ያባርራል፤ ተመልካች፡ የሆነን፡ “ፖለቲካ፡ ኮረንቲ፡ነው”፡ ብሎ፡ ወደ-መሃል፡ ሰፋሪነት፡ ይመራል። በተቃዋሚው፡ ክፍል፡ ደጋግግሜ፡ ለብዙ፡ ጊዜ፡ ያየሁት፡ ሌላው፤ ልንፈታው፡ የሚገባን፡ ችግር፡ ውይይት፡ በቁም፡ ነገሩ፤ በሃሳቡ፤ በችግሩ፡ ላይ፡ ትኩረት፡ መስጠት፡ ሳይሆን፡ በግለሰቡ፡ ላይ፤ በአለፈው፡ ታሪኩ፡ ላይ፡ የምናደርገው፡ ትኩረት፡ ጎጂ፡ መሆኑ፡፡ነው። ይህ፡ ባህሪይ፡ አገራችን፡ እየጎዳት፡ ነው። ግለሰብ፡ ከሃሳብ፡ አለመለየት፡ ኋላ፡ ቀር፡ አመለካከት፡ ነው። ለገንቢ፡ ለውጥ፡ ማነቆ፡ ነው። ጥላቻን፡ የሚፈጥር፡ መሆኑን፡ ደጋግመን፡ አይተናል።

ይህ፡የሽሙጥ፡ አይነት፡ ባህሪይ፡ ለገንቢ-ለውጥ፤ አብሮ፡ ለመስራት፡ እንቅፋት፡ ሁኗል። ሁለቱንም፡ ጎጂ፡ ባህሪወች፡ ለመለወጥና፡ ለሃያ፡ አንደኛው፡ መቶ፡ ክፍለ-ዘመን፡ የሃገር፡ እድገት፡ አስተዋጾ፡ ለማድረግ፡ ከፈለግን፤ የእኛን፡ ድፍረት፤ ፈቃደኛነት፡ እንጂ፤ የህወሃት፡ ፈቃድ፡ አይጠይቁም። አነኝህን፡ የመሳሰሉ፡ የባህሪይ፤ የአስተሳሰብና፡ የስነ-ልቦና፡ ሁኔታወች፡ አለመለወጥ፤ ያለውን፡ የተማረ፡ የሰው፡ ሃይል፡ በታትነውታል። ለአገራዊና፤ ለወገናዊ፡ ገንቢ፡አስተዋጾ፡ እውን፡ መሆን፡ ማነቆ፡ ሁነዋል። የባሰውን፤ ስም፡ማጥፋት፤ ያለ-ማስረጃ፡ ሰውን፡ መክሰስ፤ አንድ፡ ግለሰብ፡ አቅዋሙን፡ ሲለውጥ፡ መጠራጠር፤ ወዘተ፡

የአገራችን፡ ተወዳዳሪ፡ የማይኖርለት፡የሰውና፡ የእውቅና፡ሃይል፡ በታትነውታል፤ ለመጠቀም፡ ማንቆ፡ ሆነዋል። ተቃዋሚ፡ ነን፡ እያልን፤ ህወሃትን፡ በመዋሸት፡ እየከሰስን፤ እየኮነን፤ እኛ፡ ከዋሽን፡ ልዩነቱ፡ የት፡ ላይ፡ እንደሆነ፡ መጠየቅ፡ አለብን። ተስማምተን፡ አገርና፡ ህዝብ፡ ለመርዳት፡ ከፈለግን፡ ተባብረን፡መስራት፡ አለብን። አብረን፡ ለመስራት፡ ሃቀኛ፡ መሆን፡ የሞራል፡ ግዴታችን፡ ንው።

ይህን፡ በደንብ፡ የተረዱት፤ የኢትዮጵያን፡ የጥንትና፡ ዘመናዊ፡ ታሪክ/ሂደት፡ የሚያውቁት፡ የኢትዮጵያ፡ ወዳጂ፡ አሜሪካዊ፡ ሊቅ፤ ፕሮፌሰር፡ ዶናልድ፡ ለቪን፡ የተናገሩት፡ በአእምሮየ፡ ውስጥ፡ ጸንቷል። አንድ፡ ኢትዮጵያዊ፡ ተማሪ፡ የጠየቃቸውን፡ በማስታወስና፡ በመጥቀስ፡ እንዲህ፡ ይላሉ፡፡ “ለመሆኑ፤ ኢትዮጵያዊያን፡ በጋራ፡ ሁነው፡ አንድ፡ አገራዊ፡ ችግር፡ የሚፈቱበት፡ ጊዜ፡ መቸ፡ ነው።”

ይህን፡ አባባል፡ በሙሉ፡ እጋራለሁ። እኔ፡ በተወለድኩበትና፡ ባደግኩበት፡ ክፍል፤ ጎንደር፤ የሚነገር፡ ቀልድ፡ መሳይ፡ ቁም፡ ነገር፡ ላስቀምጥ። ጎንደሬወች፡ በያለሉበት፡ ታታሬ፡ መሆናቸውን፡ የተመለከተ፡ አንድ፡ ታዛቢ፤ እንዲህ፡ ይላል። “አንድ፡ ጎንደሬ፡ የአንድ፡ ሽህ፡ ሰው፡ ስራ፡ ለመስራት፡ ይችላል። ሆኖም፤ ሽህ፡ ጎንደሬወች፡ አንድ፡ ቤት፡ አብረው፤ ተባብረው፡ ለመስራት፡ አይችሉም።” ጎንደሬወች፡ ሆኑ፡ ሌሎች፡ ዛሬ፡ የተስማሙበትን፡ ነገ፡ “ያፈርሱታል.” ተባብረው፤ የተቃጠለ፡ ቤት፡ አያጠፉም። ከማዳን፡ ይልቅ፡ ለማጥፋት፡ የሚደረገው፡ባህል፡ያይላል፡ ለማለት፡ የሚያስደፍሩ፡ ብዙ፡ ሁኔታወች፡ ይታያሉ።

የሚያስፈራው፡ ይህ፡ አባባል፡ አገራዊ፡ መሆኑ፡ ነው። ይህ፡ ሁሉ፡ ተደማምሮ፡ የሚረዳው፡ ህወሃትን፡ ነው።
የታሪክ፡ ተጠያቂ፡ ከሚያደርጉን፡ ምክንያቶች፡ መካከል፡ ከተወሰነች፡ ገቢው፤ ቀረጥ፡ ከፍሎ፡ ላስተማረን፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ዛሬ፤ እኛ፡ የህብረተሰብ፡ “ምርጦች፤ (political and social elites)” ፤ በምናሳየው፡ባህሪና፡ ተግባር፡ የተነሳ፤ ተባብረን፡ ለአንድ፡ አላማ፡ ቆመን፡ የህዝብን፡ ውለታ፡ ለመክፈል፡ አልቻልነም። ህወሃት፡ እፎይ፡ ይላል፤ አብዛኛው፡የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ “የድርጂት/የመሪ፡ ያለህ፤ የተማሩት፡ የት፡ አሉ፤ የት፡ ገቡ፡” ብሎ፡ የጠይቃል። ነጥቡ፤ ለአላማ፡ አንድነት፡ ዛሬ፡ ተቻችለን፡ ካልተነሳን፤ መቸ፡ ነው፡ የምንደርስለት፡ የሚለውን፡ በህሊናችን፡ እንድናብላላ፡ ያስገድደናል። ይህን፡ ወሳኝ፡ ጥያቄ፡ ካልመለስን፡ የታሪክ፡ መፋረጃ፡ መሆናችን፡ አይቀርም።

በአጠቃላይ፡ ሲታይ፤ የእርስ-በእርስ፡ ክስ፤ የእርስ-በእርስ፡ መዘላለፍ፤ የእርስ-በእርስ፡ መጠላለፍ፤ ስም፡ማጥፋት፡ ወዘተ፤ ሌላው፡ (ቢያንስ፡ ከህወሃት፡ ችግር፡ ጋር፡ የሚወዳደር)፡ ቅጥ፡ ያጣ፤ በግልጽ፡ የማንነጋገርበት፡ የሰነ-ልቦና፤የባህሪይ፤ የእሴት፤ የአመለካከት፡ ችግር፡ ሁለተኛው፡ ከእራሳችን፡ የመነጨ፡ ማነቆ፡ ሁኗል፡ በማለት፡ ባቀርበው፡ ከሃቁ፡ የወጣሁ፡ አይመስለኝም። ይህ፡ እራሳችን፡ መፍታት፡ ያለብን፡ ችግር፡ ነው።

ስለሆነም፤ ችግሩን፡ በሁለት፡ ዘርፍ፡ ማስቀመጥና፡ መፍትሄ፡ መፈለግ፡ የያንዳዳችን፡ ሃላፊነት፡ ሆኗል። የችግሩ፡ መፍትሄ፡ ፈላጊወች፡ ካልሆን፤ የችግሩ፡ አጋሮች፡ መሆናችን፡ አይቀርም። ሁኔታው፡ ከቀጠለ፡ ተጠቃሚው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ ሳይሆን፡ ህወሃት፡ ነው።

የችግሮች፡ ሁለት፡ መልክ፤

አንድ፡
የጠባብ-ዘረኝነት፡ ስርአት፡ ያመጣውን፡ ጣጣ፡ በሚገባ፡ ለማስቀመጥ፡ ከተፈለገ፡ ቢያንስ፡ ከሁለት፡ አንጻር፡ መመርመር፡ ተገቢ፡ ነው። አብዛኛው፡ የተቃዋሚ፡ ዘርፍ፡ ያደረገውና፡ አሁንም፡ የሚያደርገው፡ ሃይሉን፤

እውቀቱን፤ ስብስቡንና፤ ውይይቱን፡ ከህውሃት፡ ጠባብ፡ ቡድን፡ ችግር፡ ላይ፡ ማፍሰስ፡ ነው፡ ለማለት፡ ይቻላል። ችግሩን፡ ሚዛናዊ፡ በሆነ፡ መንገድ፡ በማስረጃ፡ እየደገፉ፡ ማስቀመጥ፡ ተገቢ፡ መሆኑን፡ ባቀርብኳቸው፡ ትንተናወች፡ ሁሉ፡ አሳይቻለሁ። የእራሳችን፡ ድክመት፡ አያይዘን፡ ሳናጤን፡ በህወሃት፡ በደል፡ ማተኮራችን፡ ለመገንዘብ፤ የሚጻፈውንና፡ የሚነገረውን፡ ብቻ፡ ማየት፡ ይበቃል። ህወሃት፡ ለአሰበው፡ ‘የኢትዮጵያ፡ ተቃዋሚ፡ ሃይሎች፡ በምንም፡ አይስማሙም፤ እርስ፡ በእርስ፡ መጠላለፍ፡ ልምዳቸው፡ ስለሆነ፡ እየገባሁ፡ መከፋፈል፡ እችላለሁ’ ብሎ፡ ከስራ፡ ላይ፡ ላዋለው፡ እቅድ፡ የተጠቀመባቸውን፡ መሰረተ፡ ሃሳቦችና፡ ዘዴወች፡ ስንመለከት፡ ይህ፡ ዘዴ፡ ምን፡ ያህል፡ አገራችንና፡ ህብረተስቡን፡ እንደጎዳው፡ እናያለን። ከዚህ፡ አዙሪኝ፡ ችግር፡ ለመውጣት፡ በመጀመሪያ፡ የአስተሳሰብ፤ የአሰራር፤ የአወቃቅር፤ የአመራር፡ ለውጠች፡ ለማድረግ፡ ፈቃደኛ፡ ብቻ፡ ሳይሆን፡ ዝግጁና፡ ብቁ፡ መሆን፡ ያስፈልጋል።

ህወሃት፡ በኢትዮጵያዊነት፡ ፋንታ፡ የጎሳ፡ ስነ፡ ልቦና፡ (psychological make-up and mindset)፡ በኢትዮጵያዊያን፡ ልብ፡ እንዲቀረጽ፡ ማድረጉ፡ ለክፍፍል፡ ፖለቲካ፤ ዋና፡ መሳሪያ፡ ሆኗል። “ብሄር፤ ብሄረሰብና፡ ህዝቦች፡ በምንም፡ ሊታረቁ፡ አይችልም፤ መገንጠል፡ መብታቸው፡ ነው” የሚለውን፡ የፖለቲካ፡ አመራር፡ በ አንቀጽ፡ 39፤ አስገብቶ፡ ድጋፍ፡ ሰጭ፡ መሪወችን፤ ደጋፊወችን፡ መመልመል፤ ህዝቡና፡ አገሪቱ፡ ገደብ፡ ከሌለው፡ ርጋታ፡ የለሽ፡ ወጥመድ፤ (permanent suspense) ውስጥ፡ እንዲገቡ፡ ማድረጉ፡ ለአንድ፡ አላማ፡ ላለሞቆማችን፡ አስተዋጾ፡ እያደረገ፡ ቆይቷል። የሚያሳየው፡ ተቃዋሚው፡ የሚመራው፡በእራሱ፤ ወይንም፡ በኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ አጀንዳ፡ ሳይሆን፡ በህወሃት፡ አጀንዳ፡ ነው፡ ያሰኛል። ህወሃት፡ ይህን፡ ዘዴ፡ ስራ፡ ላይ፡ ሲያውለው፡ የአብዛኞቻችን፡ ደካማነት፤ መከፋፈል፤ የመጠራጠር፡ ባህል፤ ለስሜት፤ ለጉራ፤ ለግለኝነት፤ ለጥቅም፤ ወዘተ፡ በቀላሉ፡ የመውደቅ፡ ዝንባሌን፡ በደንብ፡ ስላጤነ፡ ነው። በእኛ፡ ላይ፡ የስነልቦና፡ ሰለባ፡ ከተካሄደ፡ የተቃዋሚው፡ ክፍል፡ እየደከመ፡ ይሄዳል፤ በረባ-ባረባው፡ ይከፋፋል።ጉልበቱን፤ እውቀቱን፤ ገንዘቡን፡ የሚያጠፋው፡ በመከላከል፡ ላይ፡ እንጂ፡ በማሸነፍ፡ ላይ፡ ያልሆነው፡ ለዚህ፡ ነው። እስከ፡ አሁን፡ የሚታየው፡ ህወሃት፤ ያለ፡ ብዙ፡ ወጭ፤ የተቃዋሚው፡ ክፍል፡ ተሳስቦ፤ እንደ፡ ሰንሰለት፡ ተያይዞ፡ በአንድ፡ አላማ፡ አይቆምም፡ የሚል፡ ስሌቱ፡ እኛ፡ በምናወራውና፡ በምናደርገው፡ ሲሳካለት፡ ቆይቷል፤ አሁንም፡ ያው፡ ነው። ማሻማት፡ የሌለባቸው፡ ምሳሌወች፡ ልስጥ።

የክርስትና፡ ሃይማኖት፡ አመራርንና፡ ተከታዮችን፡ ብንወስድ፤ ህወሃት፡ መከፋፈልን፡ ለመጠቀም፡ ገደቭ፡ እንደሌለው፡ ያሳየናል። የክርስትና፡ ሃይማኖት፡ ተከታዮች፡ የምናመልከው፡ አንድ፡ “ታቦት፤ አንድ፡ አምላክ” ነው፡ ካልን፤ ቢያንስ፡ የ 1,700 አመታት፡ ታሪክ፡ ያላት፡ የኢትዮጵያ፡ ኦርቶዶክስ፡ ቤተክርስቲያን፡ መሰብሰቢያችን፤ መታወቂያችን፤ የመንፈስ፡ ምሽጋችን፡ እንጂ፡ የጠባብ፡ ብሄርተኞች፡ መከፋፈያ፡ ቤት፡ መሆን፡ የለባትም፡ ነበር። ስለሆነም፡ በዚህ፡ እራሳችን፡ ልንጠብቀውና፡ ልንከባበከው፡ በምንችል፡ ታሪካዊ፡ ተቋም፡ ውስጥ፡ የሚካሄደው፡ ክፍፍል፡ ከየት፡ እንደመጣ፡ አውቀን፡ መፍትሄ፡ መሻት፡ የህወሃትን፡ ፈቃድ፡ አይጠይቅም። ተቋሙን፡ መጠበቅ፡ ለፍትሃዊ፡ ስርአት፡ እውን፡ መሆን፤ ለኢትዮጵያ፡ ዘላቂነት፤ ለኢትዮጵያዊያን፡ ክብር፤ ለማንነታችን፡ አስፈላጊ፡ ስለሆነ። ይህ፡ የህወሃትን፡ ፈቃድ፡ አይጠይቅም።

የተቋማት፡ አድሏዊ ፡ሚና፡

በአንድ፡ የዘረኛ፡ ክልል፡ ቡድን፡ ፍላጎትና፡ ጥቅም፡ የሚመራ፤ በስልጣንና፡ የኢኮኖሚ፡ ጥቅም፡የተሳሰረ፤ የተቆላለፈ፤ እርስ፡ በእርሱ፡ የሚረዳዳ፤ ተቋሞቹን፡ ሁሉ፡ (የአመራር፣ የመከላከያ፤ የስለላ፤ የፌደራል፡

ፖሊስ፤ የውጭ፡ ጉዳይ፤ የባንክ፤ የገንዝ፤ የመሬት፡ ይዞታ፤ ሌሎች፡ የተፈጥሮ፡ ሃብት፡ ዘርፎች፡ አስተዳደርና፡ ስርጭት፤ የውጭ፡ እርዳታ)፡ ሙሉ፡ በሙሉ፡ የበላይነት፡ ወደ፡ እራሱ፡ ደጋፊወቹና፡ ፓርቲው፡ ተቆጣጣሪነት፡ ያዛወረው፡ ሌላው፡ አጎብዳጅና፡ ጥገኛ፡ እንዲሆን፡ በማሰብና፡ በማድረግ፡ ነው። ለዚህ፡ ዘዴ፡ እንዲጠቅ፡ ተብሎ፡ ህወሃት፤ የትግራይን፡ ክልል፡ ከሌላው፡ ለይቶ፤ ከመጠን፡ በላይ፤ ግልጽ፡ አድሏዊነት፡በሚያሳይ፡ መልኩ፡ ፈርጂ፡ የሌለው፡ መዋእለ፡ ንዋይ፡ (financial and material investments): ከማእከላዊ፡ መንግስት፡ እየወሰደ፡ ለመሰረተ፡ ልማት፤ ለፍጆት፡ እቃ፡ ማምረቻ፤ ለስራ፡ እድል፡ ማስፋፊያ፤ ለጥቂቶች፡ መክበሪያ፡ ወዘተ፡ ብዙ፡ ቢሊየን፡ ብር፡ አፍስሷል፤ አሁንም፡ ያፈሳል። ህወሃት፡ ይህን፡ ሲያደርግ፡ ዋጋ፡ የሚከፍሉት፡ ሁለት፡ የህብረተስብ፡ ክፍሎች፡ ናቸው። አንዱ፤ ቀረጥ፡ ከፋይ፡ የሆነው፡ አብዛኛው፡ የኢትዮጵያ፡ ድሃ፡ ሕዝብ፡ ሲሆን፤ ሌላው፡ በአድሎ፡ እድገት፡ አገኘ፡ የሚባለው፡ የትግራይ፡ ህብረተሰብ፡ ነው። ለዚህ፡ ህብረተሰብ፡ ጎጂ፡ የሚሆነው፡ ቀረጥ፡ ከፋዩ፡ አብዛኛው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ አድሎውን፡ ሙሉ፡ በሙሉ፡ ስለሚያውቅ፡ ሊረሳው፡ አይችልም። የትግራይ፡ ወጣቶች፡ የትምህርት፤ የስራ፡ የመሾም፡ እድል፡ ሲያገኙ፡ ሌላው፡ እንዴት፡ ይህ፡ ሊሆን፡ ቻለ፡ ብሎ፡ መጠየቁ፡ የማይቅር፡ ነው። ስርአቱ፡ ፍትሃዊ፡ ስርጭትን፡ ለማምጣት፡ አለመቻሉን፡ ህዝቡ፡ በግልጽ፡ እያየው፡ ነው። ስለሆነም፡ የትግራይ፡ ህብረተሰብ፡ ይህን፡ የአጭር፡ ጊዜ፤ ከፖለቲካና፡ ከጠባብ፡ ዘረኝነት፤ ከዘር፡ ጥላቻ፡ የመጣ፡ ጥቅም፡ መቃወም፡ አለበት። ወደፊት፡ የሚያመጣውን፡ አደጋ፡ ማየት፡ ለዚህ፡ ይጠቅማል።

አድሎ፡ ስላለ፡ በጀምላ፡ መወንጀል፡ ይቁም፡

ይህ፡ የህወሃት፡ ሙሉ፡ የፖለቲካና፡ የኢኮኖሚ፡ የበላይነት፡ ቢያንስ፡ ሁለት፡ ያልተጠበቁ፡ ሁኔታወችን፡ ያሳያል። በአንድ፡ በኩል፡ ሌላ፡ መግቢያ፡ ቀዳዳ፡ስለሌለ፡ ብዙ፡ ኢትዮጵያዊያን፡ ወደዱም፡ ጠሉም፡ መሬት፤ ቤት፤ ፋብሪካ፤ ተቋም፤ ሌላም፡ ሃብት፡ ለመያዝና፡ ለማቋቋም፡ ከህወሃት፡ ባለስልጣኖች፡ ፈቃድ፡ ማግኘት፡ ግዴታ፡ ሁኖባቸዋል። በሃገራቸው፡ ይህን፡ ስላደረጉ፡ መወንጀል፡ አለባቸው፡ የሚል፡ ግምት፡ የለኝም። ኢላማው፡ ስርአቱን፡ ለመለወጥ፡ እንጂ፡ ማንንም፡ ለመኮነን፤ ለማውገዝ፤ ለመወንጀል፡ መሆን፡ የለበትም። ጎሳ፡ መኮነን፤መወንጀል፡ የህወሃት፡ ጠባብ፡ ቡድን፡ እሴት፡ እንጂ፡ የአብዛኛው፡ ኢትዮጵያዊ፡ እሴትና፡ ልምድ፡ አይደለም። የአማራ፤ የትግራይ፤ የኦሮሞ፤ የጉራጌ፤ የአኗክ፤ ወዘተ፡ ባህልና፡ ልምድ፡ አይደለም። ሁለተኛው፡ ነጥብ፤ ህወሃት፡ ሆነ፡ ብሎ፤ ትግራይን፡ እንደምሽግ፡ ለመጠቀም፤ ህብረተሰቡን፡ ከሌሎች፡ ወገኖቹ፡ ጋር፡ እንዲጣላ፡ ለማድረግ፡ ያቀደውን፡ ስልት፡ አይተን፡ መላውን፡ የትግራይ፡ ህብረተሰብ፡ የጠባቡ፡ ቡድን፡ አጋር፡ ነህ፡ ማለቱ፡ ህወሃት፡ ካጠመደው፡ ወጥመድ፡ መግባትና፡ ጠባቡን፡ ቡድን፡ የሌለ፡ ክብር፡ መስጠት፡ ነው። ይህን፡ ስል፡ በሁለቱም፡ ጎራ፡ ያሉ፡ ግለሰቦች፡ ለጥቅም፡ ብቻ፡ ብለው፡ ህሊናቸውን፡ አልሸጡም፡ ማለቴ፡ አይደለም። ባጠቃላይ፡ ሲታይ፡ ግን፡ በጀምላ፡ ማንንም፡ ክፍል፡ መኮነን፤ መዝለፍ፤ ማዋረድ፤ መወንጀል፡ ወደ፡ ተፈለገው፡ ብሩህ፡ አላማ፡ ሊወስደን፡ አይችልም። ይህ፡ የመወነጃጀል፡ ባህል፡ በሙሉ፡ እንዲቆም፡ ሁላችንም፡ ጥረት፡ የምናደርግበት፡ ጊዜ፡ አሁን፡ ነው።

የሰብአዊ፡ መብቶች፡ መገፈፍ፡ በ ጎሳ፡ መለየቱ፡ ያዘገንናል፡

ከላይ፡ የጠቀስኳቸውንና፡ ሌሎች፡ የአስተሳሰብ፡ ለውጦች፡ (redirection) ከስራ፡ ላይ፡ ለማዋል፡ እራሱን፡ መርጦ፡ የስልጣን፡ ቁንጮ፡ የያዘው፡ ብሄርተኛ፡ ቡድን፤ ህወሃት፤ እኛን፡ በግልጽ፡ ሆነ፡ በምስጢር፡ ለመያዝና፡ ለመሳብ፡ አጎልማሽ፡ ሁኔታወችን፡ (enabling conditions) አስቀድሞ፡ መፍጠሩን፡ ማጤን፡ያስፈልጋል። አጎልማሽ፡ ሁኔታወችን፡ ፈጥሮ፡ እኛን፡ የእራሱ፡ አጀንዳ፡ ተከታዮች፡ ማድረጉ፡ ጥንካሬውን፡

ያሳያል። ለምን፡ ብንል፤ እያወቅንም፡ ሆነ፡ ሳናውቅ፡ ብዙወቻችን፡ ባዘጋጀልን፡ የጥላቻ፡ መርዝ፡ ተዘፍቀናል፤ ለመውጣት፡ ሲያዳግተን፡ እንታያለን። ለምሳሌ፤ በቅርቡ፡ የአማራ፡ ህብረተሰብ፡ ክፍል፡ ሆነ፡ ተብሎ፡ (deliberate ethnic cleansing and dispossession) ‘የተፈረደበት፡’ ህብረተሰብ፤ እንደከብት፤ በጀምላ፡ ከጉራ፡ ፈርዳ፤ ደቡብ፡ ክልል፡ ኢሰባዊ፡ በሆነ፡ መንገድ፡ ተገዶ፡ ለስደት፡ ሲዳረግ፡ ስንት፡ የፖሊቲካና፡ የማህበራዊ፡ ድርጂቶች፤ የታወቁ፡ ግለሰቦችና፡ መሪወች፡ የማያሻማ፤ የሚያስተማምን፤ የሚያቀራርብ፤ ህዝብን፡ ከህዝብ፡ ጋር፡ በሰላም፡ እንዲኖር፡ የሚረዳ፡ አቋም፡ እንደወሰዱ፡ አይተናል። የሰባዊ፡ መብቶች፡ መገፈፍ፡ በዘር፤ በጾታ፤ በሃይማኖት፤ በእርዮት፤ በእድሜ፡ አይለዩም። የአማራ፡ ህብረተሰብን፡ የምንለይ፡ መሆናችን፡ መለኪያው፤ ድምጻችን፡ ባለማሰማት፤ ህወሃት፡ ከሚያደርገው፡ የዘር፡ ልዩነት፡ ፍልስፍና፡ ጋር፡ ከመቆም፡ ምንም፡ ለመለየት፡ አለመቻሉ፡ (indistinguishable)፡ መሆኑ፡ ነው። በፍትህ፤ በእርትእ፤ በህግ-የበላይነትና፡ በሰብአዊ፡ መብቶች፡ ማመን፡ ማለት፡ ማንንም፡ ኢትዮጵያዊ፡ ከሌላው፡ ሳይለዩ፡ ድምጽ፡ ማሰማት፤ አቋም፡ መውሰድ፤ መታደግ፡ ማለት፡ ነው።

ሰባ፡ ስምንት፡ ሽህ፡ ህዝብ፡ በአንድ፡ ጊዜ፤ ከአንድ፡ ቦታ፤ ከአንድ፡ ብሄረሰብ፤ በቋንቋው፡ ተለይቶ፡ ከማሳው፡ ተፈነቅሏል። አንዲት፡ እናት፡ ልጂ፡ ወልዳ፡ በወለደችበት፡ ሌሊት፡ ከቤቷ፡ ተገዳ፡ ወጥታለች። እርጉዝ፡ ሴቶች፡ ለጤናቸው፡ በሚያሰጋ፡ ሁኔታ፡ እንደ፡ ተራ፡ ወንጀለኛ፡ ክብራቸው፡ ተገፎ፡ ቤታቸውን፡ ለቀው፡ እስር፡ ቤት፡ ገብተዋል። ህጻናት፤ ወጣቶች፤ እናቶች፤ እሰከ፡ ሰማኒያ፡ ዘጠኝ፡ አመት፡ የሆናቸው፡ አዛውንቶች፡ ለእስር፡ቤት፡ ተዳርገዋል። ሰላማዊ፡ ገበሬወች፡ ከእርሻ፡ መሬታቸው፡ ከሰብላቸው፤ ከአትክልታቸው፤ ከኑሯቸው፡ ተገደው፡ ህየወታቸው፡ ወደ፡ አስጊ፡ ደረጀ፡ ተለውጧል። እነዚህ፡ ኢትዮጵያዊያን፡ ሁሉ፤ ከቤታቸው፤ ከሃብታቸው፤ ከንብረታቸው፡ ተገደው፡ ሲሰደዱ፤ ሲታሰሩ፤ የሚገፈፉት፡ ሃብት፡ ብቻ፡ አይደለም።
ሰው፡ ለምኖም፡ ቢሆን፡ ያድራል። አሰቃቂው፡ ግን፡ ከክብራቸው፤ ከማእረጋቸው፤ ከማንነታቸውን፤ ከሰብእነታቸውን፡ ጭምር፡ መሆኑ፡ ነው። በአማራው፡ ሆነ፤ በአፋር፤ በኦጋዴን፤ በኦሞ፡ ሸለቆ፤ በጋምቤላ፤ በኦሮሚያ፤ ለሚካሔደው፡ ማንኛውም፤ የሰብእነት፤ የክብር፤ የማንነት፡ ገፈፋ፡ (recurring violations of human dignity and human rights)፤ ለገጠማቸውና፡ ለሚገጥማቸው፡ ሁሉ፡ ያለ-አድሎ፤ በግልጽ፡ መቃወም፡ አዲሱ፡ መለኪያችን፡ (criteria) መሆን፡ አለበት። ድምጽ፡ ሳያሰሙ፤ አቋም፡ ሳይወስዱ፡ እንዲሁ፡ ህወሃትን፡ መኮነን፡ በቂ፡ ሊሆን፡ አይችልም። በመኮነን፤ በመወንጀል፤ ስም፡ በማጥፋት፡ ለውጥ፡ ለማምጣት፡ ቢቻል፡ ኖሮ፡ ህወሃት፡ እስካሁን፡ በስልጣን፡ ላይ፡ አይቆይም፡ ነበር። የዘጠና፡ ሰባቱ፡ ምርጫ፡ የሚያሰተምረን፡ በመወነጃጀል፤ ለስልጣን፡ በመወዳደር፤ በመካካድ፡ ባህል፡ የኢትዮጵያን፡ ሕዝብ፡ አመኔታ፡ አጥተናል። ልዩ፡ ልዩ፡ መልኪያወች፡ የሚያሳዩት፤ ከህዝቡ፡ ጋር፡ የሚቆምበት፡ “ስድሳ፡ ስድስት፤ ስድሳ፡ ስድስትን” የሚሸትና፡ የሚመስል፡ ጊዜ፡ እያየን፡ ነው። ይህን፡ እድል፡ በጥበብ፡ ለመጠቀም፡ የህወሃትን፡ ፈቃድ፡ አይጠይቅም።
ይህን፡ ግንዛቤ፡ ለማቅረብ፡ ያስቻሉኝ፡ ምልክቶችና፡ ምክንያቶች፡ እነሆ። በመሬት፡ ነጠቃና፡ በህዝብ፡ መፈናቀል፡ የተነሳ፡ የጋምቤላ፡ ህብረተሰብ፡ እራሱን፤ ክብሩን፤ ጥቅሙን፡ ለማስከበር፤ በህይወቱ፡ መስዋእት፡ እየከፈለ፡ ነው። የኦጋዴን፡ ህብረተሰብ፡ አሁንም፡ ለመብቱ፡ እየሞተ፤ ዋጋ፡ እየከፈለ፡ ለመብቱ፡ ይታገላል። የአፋር፡ ህብረተሰብም፡ እንደዚሁ። የኦሮሞ፡ ህብረተስብ፡ በህይወቱ፡ ዋጋ፡ ሲከፍል፡ ቆይቷል፤ አሁንም፡ እየከፈለ፡ ነው። በስሜን፡ ኢትዮጵያ፡ የጎንደር፡ ክፍለ፡ ሃገር፡ ህዝብ፡ የህዋሃት፡ መንግስት፡ የውስጥና፡

የውጭ፡ የመሬት፡ ነጠቃ–ለሱዳን፡ መንግስት፡ በምስጢር፡ ለም፡ መሬት፤ ደንና፡ ወንዞች፡ ከህግ፡ ውጭ፤ ህዝቡን፡ ሳያማክር፡ የሚያደርገውን፡ አገርና፡ ደንበር፡ ለዋጭ፡ ተግባር፡ ሲቃወም፡ መቆየቱን፡ ታሪክ፡ ይመስክራል። ከጥቅም፡ ላይ፡ ያልዋለ፡ ሰፊ፡ መሬት፡ አለ፡ የሚለው፡ ህወሃት፤ የጥንት፡ ቅርስ፡ የሆነውን፤ ለተከታታይ፡ ትውልድ፡ መታወቂያና፡ መኩሪያ፤ መተኪያ፡ የማይገኝለትን፡ የዋልድባ፡ ገዳም፡ ለም፡ መሬት፡ ለስኳር፡ ፋብሪካ፡ በሚል፡ ሲያርሰው፡ ህብረተሰቡ፡ በህይወቱ፡ ዋጋ፡ ለመክፈል፡ መዘጋጀቱን፡ እያሳየ፡ ይገኛል። ይህ፡ ጥሪት፡ የጎንደሬ፡ አማራ፡ ብቻ፡ አለመሆኑን፡ አውቆ፡ አብሮ፡ መሰለፍ፡ የህወሃትን፡ ፈቃድ፡ አይጠይቅም። ሌላው፤ የኢትዮጵያ፡ ገበሬ፡ መሬት፡ ጠቦት፡ ሊለማ፡ የሚችልውን፡ ለም፡ መሬትና፡ ደጋፊውን፡ ወንዝ፡ በብዛት፡ ሆነ፡ ብሎ፡ 36 አገሮችን፤ 8,000 የውጭ፡ ግለሰብ፡ ሃብታሞችን፡ ለም፡ ጋብዞ፡ ሲያቀራምት፤ ይታያል። ይህ፡ ከእርሻ፡ መሬት፡ ጋር፡ የተያያዘ፡ አዲስ፡ የቅኝ፡ ገዦች፡ ግብዣ (colonization by invitation) መላውን፡ ህዝብ፡ እንዳሳሰበው፡ ምልክቶች፡ አሉ። ይህን፡ እያደረገ፡ ዙሮ፡ ዋልድባን፡ ለስኳር፡ ማምረቻ፡ አርሳለሁ፡ ማለቱ፡ የሚያሳየው፡ የፖለቲካ፡ እቅዱን፡ እንጂ፡ ለጎንደር፤ ወይንም፡ ለመላው፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ እድገትና፡ ደህንነት፡ መቆሙን፡ አይደለም። ጉዳቱ፡ ለጎንደር፡ ህዝብ፡ ብቻ፡ ሳይሆን፡ ለመላውን፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፤ በተለይ፡ የክርስትና፡ ሃይማኖት፡ ተከታይ፡ ለሆነው፡ ነው፡ ለማለት፡ ያስችላል፡፡ ስለሆነም፡ አብዛኛውን፡ የሃይማኖት፡ ተከታይ፡ ሁሉ፡ አስቆጥቶታል፤ አስነስቶታል። እኔ፡ እንደማየው፡ ዋልድባ፡ የሚፈለገው፡ የጎንደርን፡ ህብረተሰብ፡ ኑሮ፡ ለማሻሻል፡ ሳይሆን፡ ይህን፡ የመንፈሳዊ፡ ማማና፡ ለም፡ መሬቱን፡ ወደ፡ ትግራይ፡ ለመጠቅለል፡ ነው። የጎንደር፡ ህዝብ፡ ይህን፡ ሴራ፡ አውቆ፡ ትግሉን፡ ቀጥሏል። ስለሆነም፡ ለማንኛውም፡ የህብረተሰብ፡ ክፍል፡ ትግል፡ ሊሰጠው፡ የሚገባ፡ ድጋፍ፡ ለዚህም፡ ህብረተሰብ፡ ክፍል፡ መሰጠት፡ አለበት።

ሌላው፡ ማንም፡ ሊክደው፡ የማይችል፡ የኑሮ፡ ውድነትና፡ የዋጋ፡ ግፍሸት፡ በየቀኑ፡ ማደግ፤ የነፍስ፡ ወከፍ፡ የገቢ፡ አለማደግ፤ የሃብትና፡ የኑሮ፡ ሁኔታ፡ በሚያሰቅቅ፡ ደረጃ፡ መራራቅ (gross income inequality) የሰብአዊ፡ መብቶች፡ መገፈፍ፤ ሁኔታው፡ ያስመረረው፡ አስተማሪ፡ የሰላም፡ ተቃውሞውን፡ አገር፡ አቀፍ፡ በሆነ፡ ደረጃ፡ ማቅረቡ፡ የአደባባይ፡ ምስጢር፡ ናቸው። በአጼ፡ ሃይለ፡ ስላሴ፡ ዘመነ፡ መንግስት፡ የአብዮት፡ ቀስቃሽ፡ ሆኖ፡ አገራችን፡ ለለውጥ፡ ያሸጋገራት፡ ዋናው፡ የህብረተሰብ፡ ክፍል፡ የአስተማሪወች፡ ተሳትፎ፡ ነው፡ ብል፡ አልሳሳትም። የእስልምና፡ ሃይማኖት፡ ተከታዮች፡ ህወሃት፡ በእምነት፡ ውስጥ፡ ገብቶ፡ የሚያደርገውን፡ ብጥብጥና፡ መከፋፈል፤ ሃይማኖትን፡ ለፖለቲካ፡ ስልጣን፡ መሳሪያ፡ ማድረግ፡ ተቃውመው፡ ከዘጠና፡ ሰባት፡ ወዲህ፡ ታይቶ፡ የማያውቅ፡ ሰላማዊ፡ ሰልፍ፡ አድርገዋል።ብዙ፡ ሰላማዊ፡ ሰወች፡ ሙተዋል። ይህን፡ ሰላማዊ፡ ሰልፍ፡ የክርስትና፡ ሃይማኖት፡ ተከታዮች፡ እንደሚደግፉት፡ ይነገራል። ተስፋ፡ የሚሰጠው፡ እነዚህ፡ አንጋፋ፡ የሃይማኖት፡ ዘርፎች፡ ከጥንት፡ ጀምሮ፡ በሰላም፤ በመከባበር፤ የቆየውን፡ የኢትዮጵያዊነት፡ እሴት፡ ከስራ፡ ላይ፡ እያዋሉ፡ መሆናቸው፡ ነው። ይህ፡ የመተባበር፡ ሰላማዊ፡ ትግል፡ ከቀጠለ፡ ትኩረቱ፡ ከዋናው፡ የህወሃት፡ ከፋፋይ፡ ስርአት፡ ላይ፡ እንጂ፡ ከህዝብ፡ ክፍፍል፡ ላይ፡ አይሆንም፡ የሚል፡ ግምት፡ አለኝ። የታሪክ፡ ሃላፊነት፡ የሚጠይቀው፡ ይህን፡ ተባብሮ፡ አገርን፡ ከአደጋ፡ መከላከል፤ የኢትዮጵያን፡ ሕዝብ፡ በሙሉ፡ በሰላም፤ ከድህነት፤ ከእርሃብ፤ ከስደት፤ ከኋላ፡ ቀርነት፡ ነጻ፡ የሚሆንበት፡ ድልድይ፡ በየፊናችን፡ ማመቻቸትና፡ መገንባት፡ ብቻ፡ ነው።

በሌላ፡ በኩል፡ የምገነዘበው፡ በየቦታው፡ የምናየው፡ ይህ፡ ሁሉ፡ ያልተቀነባበረ፡ የሰላማዊ፡ ህዝብ፡ እንቅስቃሴ፡ አገር-ቤት፡ ሲካሄድ፡ በውጭ፡ ሆነ፡ በውስጥ፡ ያሉ፡ የፖለቲካና፡ የማህበራዊ፡ ስብስብስቦች፡ የማቀነባበር፤ የአቅጣጫ፡ መስጠት፤ የገንዘብ፤ የሃሳብ፤ የዲፕሎማቲክ፤ የሞራል፤ ድጋፍ፡ የመስጠት፡

ሚናቸው፡ አለመታየቱ፡ ለምን፡ ይሆን፡ የሚለውን፡ ነው። ከላይ፡ እንዳሳየሁት፤ ህወሃት፡ የፈጠረልን፡ የስነ-ሊቦና፡ ወጥመድ፡ ማነቆ፡ መሆኑ፡ አያጠራጥርም። መረዳት፡ ያለብን፤ አገር- ቤት፡ ለሚካሄደው፡ ሰላማዊ፡ የፍትህ፤የእርትህ፡ ትግል፡ ድጋፍ፡ የመስጠት፤ ያለመስጠት፡ አዛዡ፡ ህወሃት፡ አይደለም፤ ሊሆንም፡ አይችልም። የፖለቲካ፡ ሆነ፡ የማህበራዊ፡ እንቅስቃሴወች፡ ሁሉ፡ በህወሃት፡ አጀንዳ፡ አንመራም፡ ብለው፡ ካመኑ፡ ልዩ፡ ልዩ፡ እድሎችን፡ የመጠቀም፤ የማያያዝ፤ የመሰብሰብ፤ የማገናኘት፤ የማቀናጀት፤ (connecting the dots) አበይት፡ ተግባራቸው፡ መሆኑን፡ የመረዳት፡ ሃላፊነት፡ አለባቸው። አገር-ቤትም፡ ሆነ፡ ውጭ፡ የሚገኙ፡ የተቃዋሚ፡ ሃይሎች፡ ይህን፡ የተቀደሰ፡ ተግባር፡ ከስራ፡ ላይ፡ ለማዋል፡ በቅተው፡ ካልተነሱ፡ የታሪክ፡ ተጠያቂወች፡ ይሆናሉ፡ ለማለት፡ የምደፍረው፡ ለዚሁ፡ ነው።

በአጠቃላይ፤ ኢትዮጵያና፡ መላው፡ ሕዝቧ፡ የሚስፈልጋቸው፤ ከድህነት፤ ከእርሃብ፤ ከስደት፤ ከጥገኝነት፤ ከሃፍረት፤ ከፍርሃት፤ ከአድሎና፡ ከሙስና፤ ከማንኛውም፡ ዘርኝነት፡ ወዘተ፡ ነጻ፡ የሚያወጣቸው፤ በነጻ፡ ምርጫ፤ በህግ፡ የበላይነት፤ በእኩልነት፤ በመተሳሰብና፡ በመፈላለግ፤ በጋራ፡ ጥቅም፤ በጋራ፡ አገር፤ እሴቶችና፡ መሰረተ-ሃሳቦች፡ ላይ፡ የተመሰረተ፡ የፍትሃዊነትን፡ ምንነት፡ በሁሉ፡ ዘርፍ፡ እውን፡ የሚያደርግ፡ የፖለቲካ፡ አማራጭ፡ ጭብጥ፡ ማድረግ፡ ነው። ይህን፡ ለማመቻቸትና፡ የኢትዮጵያ፡ ሕዝብ፡ የእራሱ፡ እድል፡ ወሳኝ፡ እንዲሆን፡ ያልተቆጠቨ፡ ድጋፍ፡ መስጠት፡ የህወሃት፡ አለቆች፡ ፈቃድ፡ አይጠይቅም።

በዚህ፡አጭር፡ ትንተና፡ እንዳሳየሁት፡ ለዚህ፡ ተስፋ፡ አስተዋጾ፡ ለማድረግ፡ በመጀመሪያ፡ እያንዳንዳችን፡ ካለፈው፡ ከመራራ፡ ፖለቲካ፤ ከቂም፡ በቀልነት፤ ከሃሜት፤ ከአሉባልታ፤ ከፍርሃት፡ ባህል፡ በተቻለ፡ መጠን፡ እራሳችን፡ ነጻ፡ ማውጣት፡ አለብን። ህወሃት፡ በቀባን፡ ወይንም፡ እራሳችን፡ በፈጠርነው፡ የጥላቻ፡ መርዝ፤ የሃሜት፤ የእርስ፡ በእርስ፡ መጠላለፍ፤ የጉራ፡ ወዘተ፡ ባህል፡ ተዘፍቀን፡ ለአሁኑና፡ ለወደፊቱ፡ ትውልድ፡ አርአያ፡ ለመሆን፡ እንችልም። ለዲሞክራሲ፡ ስርአት፡ አስተዋጾ፡ ለማድረግ፡ እራሳችን፡ ዲሞክራሲን፡ ከስራ፡ ላይ፡ ማዋል፡ አለብን። አለበለዚያ፡ ጸረ-ዲሞክራሲ፡ ከምንለው፡ ከህወሃት፡ የምንለይበት፡ መሰረት፡ ሊኖረን፡ አይችልም።

ይቀጥላል
May 7, 2012

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 8, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.