የተከበሩ አፍሪካዊ ኔልሰን ማንዴላ ስንብት!

ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም ከነጻነት ለሀገሬ

ኔልሰን ሮሺስላሽላ ማንዴላ ለነጻነት የሚያደርጉትን ረዥሙን ጉዞ እ.ኤ.አ በ2013 መገባደጃ ወር ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ደመደሙ፡፡

ፀሐይ የደቡብ አፍሪካን ሕዝብ ከአፓርታይድ የጭቆና አገዛዝ ነጻ ባወጡት ኔልሰን ማንዴላ ላይ የመጨረሻ ማህለቋን ጣለች፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ፈለግ አቸዉን ትተውልን አልፈዋል፡፡ በጥላቻ በተዘፈቀው ዓለም፣ በማያቋርጥ ሁኔታ በፍርሃት ተሸብቦ በሚገኘው ህዝብ፣ በአምባገነኖች በሃይል ተይዞ በሚሰቃየው ብዙሀን ህዝብ እና ስሜት አልባ ተደርጎ በተያዘው ህዘብ ላይ የፀሐይን ማህለቅ ለመጣል የኔልሰን ማንዴላን ፈለግ መከተል አለብን፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ አንፈራም፣ የኔልሰን ማንዴላ መንፈስ ከአጠገባችን ናትና!

ኔልሰን ማንዴላን በፍጹም አግኝቻቸው አላውቅም፣ ባገኛቸው እንዴት ደስ ባለኝ! ለማግኘት የምፈልገው ደግሞ በዓለም ላይ እጅግ ከተከበሩት ሰው ጋር ተገናኝቸ ነበር በማለት ለስሜቴ ክብር ለመስጠት አይደለም፣ ነገር ግን ለአፍሪካውያን ክብርን፣ ኩራትን እና ሞገስን ላጎናጸፉት እኒያን ጀግና ኔልሰን ማንዴላን በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ የምትለዋን ቃል በትሕትና  ለማቅረብ እንጅ፡፡

ኔልሰን ማንዴላ ድልድይ ቀያሽ ነበሩ፡፡ ዘርን፣ ጎሳን እና የህብረተሰብ መደብን የሚያገናኙ ድልድዮችን ገንብተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ እሳት አጥፊ ነበሩ፡፡ በዘር እና በጎሳ ጥላቻ ተቀጣጥሎ የነበረውን ቤት እሳት በማጥፋት በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ እውነት እና ዕርቅ እንዲሰፍን አድርገዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ መንገድ ቀያሽ ነበሩ፡፡ በረዥሙ ጉዞ ወደ ነጻነት የሚያደርሱ በስም “ደግነት“ እና  “ዕርቅ“ የሚባሉ ሁለት መንገዶችን በመገንባት የተናገሩትን በተግባር አሳይተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የህንጻ ንድፍ ነዳፊ/architect ነበሩ፡፡ በአፓርታይድ አመድ ላይ በብዙሃን ዘር ዴሞክራሲ የተዋበውን ማማ ገንብተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ነበሩ፡፡ ጥቁር እና ነጭ እርግቦችን በአንድ ጊዜ በመልቀቅ በነጻነታቸው ተንፈላስሰው እንዲበሩ አድርገዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ለዘላለም የሚኖር የለውጥ ሐዋርያ ነበሩ፡፡ ጥላቻን በፍቅር፣ ፍርሃትን በወኔ፣ ጥርጣሬን በእምነት፣ ታጋሽየለሽነትን በሩህሩህነት፣ ቁጣን በመግባባት፣ ጥላቻን በስምምነት፣ እና ቅሌትን በክብር የሚለውጡ ነበሩ፡፡

ኔልሰን ማንዴላ በዘመናዊው የህብረተሰብ ታሪክ ሂደት ውስጥ እንከን ባለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እንከንየለሽ በመሆን እንከን ያላቸው ሰው ነበሩ፡፡ ሙሉ በሙሉ በዘር፣ በጎሳ እና በመደብ በተከፋፈሉ ወገኖቻቸው ላይ አንከንየለሽ ማህበርን ለማምጣት ጥረት አድርገዋል፡፡ ነጭ ደቡብ አፍሪካውያንን በልቦቻቸው ውስጥ ዘልቀው ከገቡት ከአፓርታይድ መጥፎ ገጽታ እና ከአስቀያሚ ዘረኝነት አድነዋቸዋል፡፡ በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ልቦች እና ነፍሶች ውስጥ ይንከባለሉ የነበሩትን የበቀል ጥላቻዎች  ወደ ፍቅር እና ወንድማዊነት ስሜት ቀይረዋቸዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በእራሳቸው ልብ ውስጥ የፍቅር፣ የስምምነት እና የዕርቅ ጓሮን አልምተዋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ እጅግ በጣም እንከን ለበዛባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ምክራዊ መልዕክት እንዲህ በማለት አስተላልፈዋል፣ “ሰው ከጠላቱ ጋር ሰላም ለማውረድ ከጠላቱ ጋር አብሮ መስራት አለበት፣ እና ያ ጠላት የነበረው ወዳጅ ይሆናል“፡፡ ሌሎቻችን ግን ጠላትን በመግደል ሰላም እናመጣለን ብለን እናምናለን!

ማንዴላ መጥፎ ነገር ለማድረግ ጥሩ ጊዜ የለም በማለት ዓለምን አስተምረዋል፣ ሆኖም ግን “የሚመጣው ጊዜ ሁሉ ጥሩ ነገር ለማድረግ መሆኑን ማመን አለብን“፡፡  ለደቡብ አፍሪካውያን እና ለመላው አፍሪካውያን እንዲህ በማለት አስተምረዋል፣ “ለቆንጆዋ ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ለመላዋ አፍሪካ ህልሞች ካሉ እነዚህ ህልሞች ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ የሚያስችሉ መንገዶችም አሉ“፡፡ ከእነዚህ መንገዶች ሁለቱ “ደግነት” እና “ይቅርታ አድራጊነት” በመባል ሊሰየሙ ችለዋል፡፡ እነዚህን የማንዴላን ቃላት ለዘላለም ስናስታውሳቸው እንኖራለን፡፡ የሮበርት ፍሮስትን አባባል በመዋስ፣

እኛ …ይህንን በጥልቅ ተንፍሰን እንናገራለን፣
የትም በጊዜዎች እና በጊዜዎች ቢሆንም፣
ሁለት መንገዶች ሁለት መንታ መንገዶች በደን ጫካ ዉስጥ ነበሩ
ማንዴላ ጥቂትሰዎች የተጉአዙበትን መንገድ ወሰዱ፣
እና ሁሉንም ልዩነት ያመጣው ይኸ ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ ሁሉንም የመልካም ስራ ልዩነት ያመጡት ደግነት እና ይቅርታ አድራጊነት ናቸው፡፡

ሃያ ሰባት እና ከዚያም በላይ በትንሽ እስር ቤት አድሚያቸውን ያሳለፉ ሰው ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ትክክለኛ ትርጉም እንዲህ በማለት አስተምረውናል፣ “ነጻ መሆን እግረሙቅን ከእጅ ወይም ከእግር ማስወገድ አይደለም፣ ነገር ግን ሌሎችን በማክበር እና ነጻነታቸውን በማራመድ የመኖር መንገድ ነው“ ፕሬዚዳንት ክሊንተን “በተሻለው ቀን ሁሉ ሁላችንም ኔልሰን ማንዴላን መሆን አለብን“ ሲሉ እውነትም ልክ ናቸው፡፡ ነገር ግን ዛሬ መጥፎው ቀናችን ነው፣ ምክንያቱም ኔልሰን ሮሺስላሽላ ማንዴላ አብረውን የሉምና! ዛሬ ማንዴላን ለዘላለም ተነጥቀናል!

ኔልሰን ማንዴላን በፍጹም አላገኘኋቸውም፣ ነገር ግን ብዙ ንግግሮችን ከእርሳቸው ጋ አግኝቻለሁ፡፡ በእርግጥ ሁሉም ምዕናባዊ ነበሩ፡፡ ማንዴላ ግድየላቸውም፣ እንዲህ ብለዋል፣ “በእውኑ ዓለም በእርግጠኝነት ከማየው ይልቅ ራዕይዬ የበለጠ በመጓዝ ምዕናባዊ ኃይሌ ስሜትን/አዕምሮን የሚፈታተን ሀሳብን ይፈጥራል“፡፡ ነገር ግን የኔልሰን ማንዴላን ራዕይ በአዕምሯችን ዓይን ከተመለከትነው የሀሰት ምዕናባዊ ሀሳብ አይደለም፡፡ ከኮሎኒያሊዝም፣ ከኢምፔሪያሊዝም እና ከአፓራታይድ አመድ ነጻ የወጣችውን ጀግና፣ በእራስ የምትተማመን አዲሲቷን የፍቅር አፍሪካ ራዕያቸውን እናያለን፡፡ በኔልሰን ማንዴላ ራዕይ የምትመራዋን አዲሲቷን አፍሪካ ለመገንባት ምዕናባዊ ሀሳባችንን አሁኑኑ መጠቀም አለብን፡፡

አንዳንድ ሰዎች ትልቅ ሆነው ይወለዳሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ የትልቅነት እምነትን ይላበሳሉ እየተባለ ይነገራል፡፡ ምንልባትም አንዳንዶቹ ታላቅነትን በአጋጣሚ ይጎናጸፋሉ፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ታላቅ ነበሩ ምክንያቱም ይሞክሩ ነበር፣ ይሞክሩ ነበር እና ይሞክሩ ነበር፡፡ ማንዴላ እንዲህ በማለት አስተባብለዋል፣ “እኔ ነብይ አይደለሁም፣ ነብይን ሁልጊዜ እንደሚሞክር ሃጢያተኛ ካልቆጠራችሁት በስተቀር“፡፡ ሁላችንም ሃጢያተኞች ሁልጊዜ እስከሞከርን እና እጃችንን እስካልሰጠን ድረስ የሚሞክር ሃጢያተኛ ነብዮች ብንባል ኔልሰን ማንዴላ ሞተውም ቢሆን ህያው ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡

ለኔልሰን ማንዴላ ከፍተኛ የሆነ ሃዘን እና አድናቆት የሚደረግላቸው ናቸው፡፡ በከፍተኛ የስልጣን እርካብ ላይ ያሉ በዓለም ታላላቅ ከተሞች የሚገኙ መሪዎች ስለ ኔልሰን ማንዴላ የነጻነት ታጋይነት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት ያወሳሉ፡፡ የደቡብ አፍሪካ መሪዎች ስለኔልሰን ማንዴላ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ አመራር ሰጭነት እና የማያቋርጠውን እና ኢሰባዊ የነበረውን የአፓርታይድ ገዥ አካል በሰላማዊ እና በትጥቅ ትግል ለመጣል የተጫወቱትን ሚና በማድነቅ ይናገሩላቸዋል፡፡ ተራው የደቡብ አፍሪካ ህዝብ ኔልሰን ማንዴላን በኩራት የሀገራቸው አባት እንደሆኑ አድርገው ይናገራሉ፡፡ ስለኔልሰን ማንዴላ የኖቤል ተሸላሚነት፣ ስለዓለማቀፋዊ የሰብአዊ መብት እና ስልሰው ልጅ ሰብዕና ተከራካሪነት፣ ስለማህበራዊ ፍትህ እና ሰላም ለማስፈን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስላደረጉት ያልተቋረጠ ትግል የዓለም ህዝብ አድናቆቱን ይገልጻል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የማንዴላ ተችዎች ጭቃ ጅራፍ ይዘው ይላሉ፡፡ ለዕርቅና ለሰላም ያላቸው የማይታጠፍ አቋም ለደቡብ አፍሪካ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሃይል ሚዛን የሚያስፈልገውን አብዮት እንዳይመጣ ይከላከላሉ በማለት ይተቿቸዋል፡፡ ማንዴላ ለአፓርታይድ ጨቋኖች ብዙ ትኩረት በመስጠት ከእነርሱ ግን በመልሱ የወሰዱት ነገር አናሳ ነው በማለት ይታቻሉ፡፡ ከአፓርታይድ አለቆች ጋር በእርቀሰላሙ ጉዳይ ላይ ጥረት በማድረግ የመለሳለስ እና ሃይለኛ ሆነው ያለመውጣት ሁኔታ እንዳለባቸው ይተቻሉ፡፡ ተቺዎቻቸው በመቀጠልም አፓርታይድ አሁንም ቢሆን በኢኮኖሚው በኩል ሃያልነቱን እንደያዘ እና ሙስና በአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ የፖለቲካ ህይወት ውሰጥ እየተስፋፋ የመጣ ነቀርሳ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የማንዴላን ውድቀት በተጨባጭ ሁኔታ ለመተቸት አልቻሉም፣ ነገር ግን እነርሱ በምዕናባቸው ሆኖ የሚታያቸውን በማቅረብ ይተቻሉ፡፡ እንዲህም ይላሉ፣ አፓርታይድ ከሞተ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በደቡብ አፍሪካ በከተሞች እና በገጠሮች የሚኖረው ህብረተሰብ ኑሮ ልዩነቱ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ማንዴላ ስለዕርቅ ጉዳይ በትጋት የሰሩት ብዙም ለውጥ አላምጣም ይላሉ፣ እንዲያውም ደቡብ አፍሪካ ቀደም ሲል እንደነበረው በዘር ተከፋፍላ ትገኛለች ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ተቺዎች ደግሞ ማንዴላ ስህተት ሰርተዋል፣ የገቧቸውን ቃልኪዳኖች አላከበሩም ይሏቸዋል፡፡ በከተሞች የሚገኙት ያጡት እና የነጡት በዕየለቱ የዕለት ዳቦ እየለመኑ የሚተዳደሩት ስለማንዴላ መልካም ነገር አይናገሩም፣ ምክንያቱም ማንዴላ አዲስ በፈጠሯት ደቡብ አፍሪካ እራሳቸውን እንደተቆለፈባቸው አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ በገጠሩ የሚኖሩት እና በመገለል ብዛት እየተሰቃዩ ያሉት ህዝቦች ህይወታቸው ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ለውጥ ያላመጣ መሆኑን ይከስሳሉ፡፡

የማንዴላን “የሃጢያት ነብይነት” የተጋነነ ትችት አንድ ነገር ልነግራቸው እፈልጋሉ፣ “እራሳችሁን እረገብ አድርጉ! በማንዴላ ላይ ከባድ ትችት ከመሰንዘራችሁ በፊት 27 ዓመታት ሙሉ በእግር ብረት ታስረው የቆዩትበን የጫማ ጉዞ በመከተል እስቲ አንድ ማይል እንኳ ለመጓዝ ሞክሩ፡፡ በከተማ እና በገጠር ለነጻነታችሁ ስትታገሉ ለቆያችሁት ልጠይቃችሁ የምፈልገው ነገር ማንዴላን ልዩ ኃይል እንዳለው መልዓክ አድርጋችሁ አትቁጠሩ ነገር ግን ማንዴላ እንደማኝኛችሁም ሁሉ ሰው ናቸው፡፡ ማንዴላ ነጻነትን ማጣት ምን ማለት እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ክብርን እና ማንኛውንም ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በሚገባ የሚያውቁ ሰው ናቸው፡፡ ለማናቸውም ባዶ ተስፋዎች እና ተስፋቢስነቶች እንዲሁም ተፈጻሚነትን ላላገኙ ቃልኪዳኖች ኔልሰን ማንዴላን ይቅርታ እንዲያደርጉላቸው እጠይቃለሁ፡፡ ሰዎች ማንዴላን እንደ መላዕክ መቁጥር የለባቸውም፣ ነገር ግን ለሰው ልጅ ጥሩ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለማድረግ የሚሞክሩ ሆኖም ግን ከፍተኛ ጥረትን ቢያደርጉም ሁሉም ነገር ያልተሳካላቸው ሃጢያተኛ ነብይ ነበሩ፡፡

ማንዴላ ተራ ሰው የነበሩ መሆናቸውን እናገራለሁ፣ ተራ ሰው አስገራሚ ከፍታ ላይ የወጡ፡፡ ማንዴላ የህግ ሰው የነበሩ መሆናቸውን እናገራለሁ፣ የሰብአዊ መብት የህግ ሊቅ፡፡ ማንዴላ ያልተከለሱ እና እውነተኛ አብዮታዊ የነበሩ መሆናቸውን እናገራለሁ፣ ደቡብ አፍሪካውያንን እና አፍሪካውያንን በሙሉ ነጻ ማውጣታቸው ብቻ ሳይሆን በጭቆና ቀንበር ስር ወድቆ የሚማቅቀውን የሰው ልጅ ዘር ሁሉ ነጻነት በማውጣታቸው ጭምር እንጅ፡፡ ማንዴላ ታላቁ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የነበሩ ለመሆናቸው እናገራለሁ፣ ለኤች አይቪ በሽታ ሰለባ ለሀኑት፣ ለህጻናት ሰብአዊ መብት ጥበቃ፣ ጥራት ላለው ትምህርት መስፋፋት እና ለገጠር ልማት ስኬታማነት ግንባራቸውን ሳያጥፉ ይታገሉ ነበርና፡፡

የህግ ባለሙያ ለመሆን መረጥኩ ምክንያቱም ማንዴላ ለእኔ ተምሳሌት/ሞዴል አንዱ ነበሩና፡፡ እ.ኤ.አ በኤፕሪል 1964 የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንዴላ በሪቮኒያ የህግ ሂደት ያሰሙትን ንግግር ከሰማሁ ጀምሬ ንግግራቸው አእ ምሮዬ ዉስጥ ተቀርፅዋል፡፡ እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ “ደብዳቤ ከቢርሚንግሀም እስር ቤት“ ሁሉ የማንዴላ ንግግር በአዕምሮየ ተሰንቅሮ እያቃጨለ እንዲህ በማለት ያሳስበኝ ነበር፣ “በህይወት ዘመኔ ሁሉ ለዚህ ለአፍሪካ ህዝብ ትግል ነጻነት እራሴን መስዕዋት አደርጋለሁ፡፡ የነጮችን የበላይነት ለማስወገድ እታገላለሁ፣ እንዲሁም የጥቁሮችን የበላይነት ለማስወገድ እታገላለሁ፣ ሁሉም ህዝቦች በፍቅር እና በእኩልነት፣ ዴሞክሪያሴያዊ እና ነጻ ህዝቦች ሆነው በጋራ የሚኖሩባትን ዓለም እመኛለሁ፣ ለመኖር ቃልኪዳኔ እና እውን ሆኖ ማየት የምፈልገው ፍልስፍና ይኸ ነው፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ይህ ፍልስፍና እውን እንዲሆን ህይወቴን ለመስጠት ያለማመንታት የተዘጋጀሁበት ጉዳይ ትልቅ ጉዳይ ነው“፡፡ ኔልሰን ማንዴላ ይህንን ሲሉ በትክክል ምን ማለታቸው እንደሆነ ለመረዳት አስርት ዓመታትን ወስዶብኛል፡፡

ማንዴላ በሪቭኦኒያ የሕግ ሂደት ጥፋተኛ ተብለው የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸዋል፡፡ ማንዴላ በቁጥር 46664 የአፓርታይድ እስረኛ ተደርገዋል፡፡ የ27 ዓመታት ቁጥር 46664 እስረኛው ማንዴላ የዕለት ከዕለት ውርደት፣ ኢሰብአዊነት፣ ከባድ እና ጭካኔ የተሞላበት የጉልበት ስራ እንዲሰሩ በማስገደድ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከጓደኞቻቸው እንዲለያዩ ተደርጓል፡፡ የልጃቸውን የቀብር ስነስርዓት እንኳ ለመገኘት  አልተፈቀደላቸውም፣ የባለ 46664 ቁጥሩ እስረኛ በአፓርታይድ ጌቶች በሁሉም እይታ እና ተግባር እንዲሞቱ የተወሰነ ነበር፡፡ እስረኛ ቁጥር 46664 ግን አልሞቱም፣ በዚያች እግዚአብሄር በረገማት ደሴት እንዳይታዩ ሆነው ተወረወሩ፡፡ የኔልሰን ማንዴላ የ27 ዓመታት የግዞት እስራት ማንዴላን የሮብን ደሴት ተመላኪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ በጊዜ ሂደት በግለሰብ ደረጃ የማይታወቁት ቁጥር 46664 እስረኛ ተስፋ ለሌላቸው ህዝቦች የተስፋ፣ መጠጊያ እና ኃይል ለሌላቸው ለደቡብ አፍሪካ እና ለሌሎች ዓለም ህዝቦች ደግሞ የነጻነት ቀንዲል ለመሆን በቅተዋል፡፡

ቁጥር 46664 እስረኛ በአብዛኛው የ27 ዓመታት የእስር ሂደት በሚያቃጥለው ፀሐያማ ሀሩር የኖራ ድንጋይ ቁፋሮ እንዲቆፍሩ ይገደዱ ነበር፣ ማታ በእስር ቤታቸው ተቀምጠው ሰለወደፊቱ ዕቅዳቸው እና የአሰራር ስልታቸው ንድፍ ያወጡ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በእራሳቸው፣ በቤተሰቦቻቸው እና በሌሎች ወገኖቻቸው ዘንድ ለመግለጽ በሚዘገንን መልኩ ስቃይ እና መከራ ሲያደርሱባቸው በነበሩት ጠላቶቻቸው ላይ በቀል እና ቅጣት ለመውሰድ አያስቡም ነበር፡፡ ቁጥር 46664 እስረኛ የአፓርታይድ ጨቋኞቻቸው መጥፎ አካሄዳቸውን እና ሰይጣናዊ ድርጊታቸውን እንዲተው ስትራቴጂ ይነድፉ ነበር፡፡ ቁጥር 46664 ህዝቦቻቸውን ከባስቱንታንስ የአፓርታይድ ደሴት ነጻ ለማውጣት ሌሊት ተጋድመው የወረቀት ላይ ንድፋቸውን በመስራት አርቺቴክት መሆን ጀመሩ፡፡ በደቡብ አፍሪካውያን የፖለቲካ ሰውነት ላይ ተንሰራፍቶ የቆየውን የዘረኝነት ቁስል ለማዳን እና ለመጠገን እዕምሯቸውን ክፍት በማድረግ ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ ቁጥር 46664 እስረኛ ከህዝቦች ነቢያትን እና ሃጢያተኞችን ለማውጣት ሌሊቱን በብቸኝነት በያዟት በጠባቧ እስር ቤታቸው ማስፈጸሚያ ዘዴዎችን ማውጠንጠን ጀመሩ፡፡

እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 1 1990 እስረኛ ቁጥር 46664 ከሮበን ደሴት እስር ቤት ኔልሰን ማንዴላ ሲወጡ አየን፡፡ በክብር እና ተስፋን በሰነቀ አቀራረብ በጣም ፈገግ የሚሉ ሰው ተመለከትን፡፡ ለሶስት አስርት ተከታታይ ዓመታት ያህል በእስር ቤት ውስጥ የቆየ ሰው ከእራሱ ጋር በሰላም ለመኖር እና እንዲህ በክብር ለመቆየት እንዴት ይችላል? ወዲያውኑም ግልጽ ሆነ፣ የእስረኛ ቁጥር 46664ን እዚያው እስር ቤቱ ውስጥ በመራራው እና በተሰባበረው የእስር ቤት ጓደኝነት የሲኦል በር በሮበን ደሴት ላይ ተውት፡፡ እንዲህም ብለዋል፣ “የእስር ቤቷን በር አልፌ ወደ እስር ቤቱ አጥር ግቢ በር ስራመድ ወደ ነጻነት እየሄድኩ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ጥላቻየን እና ሰቆቃውን እዚያው እስር ቤት ትቸው ካልወጣሁ አሁንም እዚያው እስር ቤት እንዳለሁ አውቃለሁ“፡፡ ማንዴላ እስረኛ አልነበሩም!  እስር ቤቱ አፓርታይድ እራሱ ብቻ ነበር፣ እስረኞቹም የእስር ቤቱ ኃላፊዎች እና የአፓርታይድ ጌቶች ነበሩ፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይድ የግንብ አጥር ተከልለው በእውን የሚገኙትን ጥላቻ፣ ፍርሀት እና በቀል በማስወገድ ነጻነትን ለማምጣት ሮቤን ደሴትን ለቀው ወጡ፡፡ ማንዴላ ዊኒ ማንዴላን ከጎናቸው በማድረግ በፊታቸው ታላቅ ፈገግታ እና ፍቅርን እንዲሁም ዕርቅ እና ልባዊ እውነትን  በማሳየት ከሮቤን ደሴት እስር ቤት ወጡ፡፡ “ኃጢያተኛውን ነብይን ተመለከትን! ሲራመዱ ሲናገሩ!  በዚያን ዕለት በአይኖቸ አልቅሻለሁ፡፡ ሌላ ያላለቀሰ ማን ነው?

ማንዴላ ሀሳባዊ አልነበሩም፣ ነገሮችን ሁሉ በአንክሮ የሚመለከቱ ጭምር እንጅ፡፡ የዕርቅን እና የዕውነትን መንገድ መረጡ፣ ምክንያቱም እነዚህ ወደ ፍትህ እና ሰላም ይመራሉና፡፡ ጥላቻ እና በቀል ወደ ሲኦል እንደሚወስዱ ማንዴላ ያውቃሉና፡፡ “ሰው የመሆናችን ተፈጥሯዊ ባህሪ አንዳችን ካአንዳችን እንድንተሳሰር ያደርገናል፣ በማዘን እና በጓደኝነት አይደለም፣ ነገር ግን ሰው እንደመሆናችን መጠን አሁን የሚያሰቃዩንን ነገሮች ለወደፊት ተስፋ ባለው ነገር መለወጥ የሚያስችል ችሎታም ስላለን ነው“፡፡ ማርቲን ሉተር ኪንግ ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ ኔልሰን ማንዴላም በተመሳሳይ መልኩ ስልፍቅር… በተለይም ስለሰው ልጅ ያልተገደበ ፍቅር “አፋቸውን ከፈት” አድርገው በማስተማር ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ከአፓርታይድ ጨቋኞች ጋር ዕርቅ ማድረግ የማይቻል ነው ሚሉትን ወገኖች ማንዴላ እንዲህ በማለት አስተምረዋል፣ “ተፈጽሞ አስከሚታይ ድረስ አንድ ነገር የሚሆን አይመስለንም“፣ እንዲህ ሲሉም መክረዋቸዋል፣ “በዚህች ዓለም ላይ ቅጣትን ከመፈጸም ይልቅ ምህረትን በማድረግ ብዙ ነገሮችን ማሳካት ትችላለህ“፡፡ ማንዴላ ትክክል ናቸው፡፡

ማንዴላ “በጎነት እና ይቅርታ አድራጊነት” በሚባሉ ሁለት አውራ ጎዳናዎች ረዥሙን የነጻነት ጉዞ ተጉዘዋል፡፡ ረዥም ጉዞ ነበር ምክንያቱም፣ ብዙ ተለዋጭ መንገዶችን መጓዝ ስለነበረባቸው፡፡ ሰፊውን የጓደኝነት ጎዳና እና ትልቁን የመቻቻል መንገድ መጓዝ ነበረባቸው፡፡ ትንሿን የፍርሀት እና ያለመግባባት መንገድ መጓዝ ነበረባቸው፡፡ በረዥሙ የጉዞ መንገድ ድፍረት፣ ታጋሽነት፣ ፍቅር፣ ጽናት እና ሩህሩህነት በማሳየት ብዙ ቆይታ ማድረግ ነበረባቸው፡፡

ማንዴላ በእስር ቤታቸው ክልል ተወስነው በጊዜ ብዛት ለመለካት በማይቻል መልኩ ታማኝነትን አዳብረዋል፡፡ “ሰዎች በውጭ በሚያከናውኑት መጠን እራሳቸውን ይለካሉ፣ ነገር ግን እስር ቤት ሰውን በውስጥ ጉዳዩች ማለትም ታማኝነት፣ ቅንነት፣ ግልጽነት፣ ሰብአዊነት፣ ለጋሽነት እና የማይለዋወጥ ባህሪ ላይ እንዲያተኩር ያደርገዋል“፡፡ ማንዴላ ወደ እስር ቤት ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ቋሚ ጓደኞች ነበሯቸው፡፡ ሮናልድ ሬጋን እና ማጂ ታቸር የአፓርታይድን መንግስት መርዳት ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማዕቀብም እንዲጣልበት አድርገዋል፡፡ በማንዴላ እና በኤኤንሲ ላይ “የአክራሪነት ባህሪ ዝርዝር ውስጥ“ በማስገባት እ.ኤ.አ እስከ 2008 ድረስ በዘለቀው ሁኔታ ማዕቀብ መጣል አልቸገራቸውም ነበር፡፡ እነዚህ የጊዜው ጥሩ ጓደኞች እና ተመሳሳዮቻቸው ማንዴላ ከፊደል ካስትሮ እና ከሙአማር ጋዳፊ ጋር ጓደኝነት መመስረታቸውን ለመተቸት ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ ማንዴላ በፍጹም መንገዳቸውን የማይቀያይሩ እና ከአመኑበት ነገር ላይ በቀላሉ የሚያፈገፍጉ አልነበሩም፡፡ ማንዴላ እንዲህም ይሉ ነበር፣ “ጓደኛ ማለት የደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በጭንቅ ጊዜም የሚገኝ ነው“፡፡ ወዲያው እንዳዩ ይጣሩ ነበር፡፡ በጊዜ ሂደት አሜሪካ “በዓለም ላይ በቃላት ሊገለጽ በማይችል መልኩ ትፈጽም በነበረው የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ“ ላይ ጠንከር ያለ ትችት ያቀርቡ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ወደ ኢራቅ ጦር ባዘመቱ ጊዜ ማንዴላ በዝምታ አልተመለከቱም ነበር፣ እንዲህ አሉ እንጅ፣”ኢራቅን ለነዳጅ ዘይቷ ሲል“ የወረረ እንዲሁም “በትክክል ማሰብ የተሳነው እና አርቆ ማየት የማይችል ፕሬዚዳንት“ በማለት በትችት ወርፈዋቸዋል፡፡

ማንዴላ የአስታራቂነት ጌታ እና የሰይጣን ነብይነት ከመሆናቸው በፊት አማጺ ነበሩ፣ ነገር ግን አማጺነታቸው በጸረ ዘር መድልኦነት ላይ ነበር፡፡ “አሸባሪ“ ነበሩ ነገር ግን የአፓርታይድን ስርዓት በመቃወም ላይ ብቻ፡፡ ለደቡብ አፍሪካውያን በሙሉ የነጻነት ታጋይ ነበሩ፡፡ ለህግ የበላይነት መከበር ቀናኢ ነበሩ፡፡ አሜሪካ ከህግ አግባብ ውጭ በኦሳማ ቢን ላደን ላይ የፈጸመችውን ግድያ ተችተዋል፡፡ ማንዴላ “የኮሙኒስት” ሽምቅ ተዋጊ እና የቀዝቃዛው ጦርነት አብዮታዊ ስለነበሩ አገራቸው የልዕለ ኃያላኑ የጦርነት መፎካከሪያ ሆና ነበር፡፡ ማንዴላ ለሰራተኛው መደብ መብት ተከራካሪ እና በዓላማቸው የጸኑ ታጋይ ነበሩ፡፡ ለዚህም እ.ኤ.አ በ1990 በዴትሮይት የሚገኙትን የአውቶ ሰራተኞች እንዲህ በማለት ነግረዋቸዋል፣ “እህቶች እና ወንድሞች፣ ጓደኞች እና የትግል አጋሮች፣ አሁን ከእናንተ ጋር ንግግር የሚያደርገው ሰው እንግዳ አይደለም፡፡ አሁን ነግግር እያደረገ ያለው ሰው የዩኤደብልዩ/UAW አባል ነው፡፡ እኔ ስጋችሁ እና ደማችሁ ነኝ፡፡“ በሮቤን ደሴት የኖራ ድንጋይ ቁፋሮ ተገደው ሲሰሩባቸው የነበሩትን ዓመታትን  አልረሱም፡፡ ማንዴላ ቡጢያቸውን የሚጠቀሙ ቦክሰኛ ብቻ አልነበሩም፣ ግን በብሩህ አዕምሯቸው በመመራት ጥብብ በተመላበት ዘዴ በመዋጋት ትጥቅ የሚያስፈቱ ጀግና ነበሩ፡፡  ማንዴላ በጣም ተጫዋች ሰው ነበሩ: በራሳቸዉም ላይ ይሰቁ ነበር፡፡ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸውን በቢሯቸው ካጠናቀቁ በኋላ የነጮች የንግድ ማህበረሰብ ስብሰባ ላይ በመገኘት እንዲህ ሲሉ ነግረዋቸዋል፣ “እኔ በአሁኑ ጊዜ ደኃ ጡረተኛ ነኝ፡፡ ስራ አጥ ነኝ፡፡ ልትቀጥሩኝ ትችላላችሁን?“

ማንዴላ እስከፈለጉበት ጊዜ በስልጣን መንበራቸው ላይ መቆየት ይችሉ ነበር፡፡ እንደሌላው የአፍሪካ አምባገነን ገዥ ሁሉ በስልጣን ላይ ተጣብቀው መቆየት ይችሉ ነበር፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ ስልጣናቸውን ማስረከብ ነው የመረጡት፡፡ በፍላጎታቸው ስልጣን በሚለቁበት ጊዜ ለደቡብ አፍሪካውያን እና ለአፍሪካውያን በሙሉ ሊተመን የማይችል ቅርስ ነው የሰጡት፣ የፖለቲካ ስልጣን የውልደት መብት እርስት አለመሆኑን ነገር ግን በህዝቦች ፍላጎት የሚሰጥ እና ሲያስፈልግም የሚቀማ ኃላፊነት መሆኑን በተግባር አሳይተዋል፡፡ በዚያ ድርጊት መሰረት ማንዴላ የህግ የበላይነትን በህገመንግስቱ እንዲካተት እና የደቡብ አፍሪካ ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ በማድረግ ለሁሉም አፍሪካውያን አርአያ ለመሆን በቅተዋል፡፡

ማንዴላ ስልጣንን የህዝቦች ፈቃደኝነት፣ ፍላጎት ማስፈጸሚያ፣ የዓላማዎች ማሳኪያ ስልት እንጅ በእራሱ የመጨረሻ ግብ እንዳልሆነ አድርገው ነበር የሚመለከቱት፡፡ ጥሩ ነገር ለመስራት ስልጣንን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ፣ ኃይል የሌላቸውን ኃይል ካላቸው ለመጠበቅ፣ ስልጣንን አላግባብ መጠቀምን ለመከላከል፣ ስልጣንን በመጠቀም ኃይል የሌላቸውን ኃይለኞች ለማድረግ፣ ኃይልን በመጠቀም ወጣቶችን ኃይል እንዲኖራቸው ለማድረግ የኃይል መጠቀምን አስፈላጊነት ይናገሩ ነበር፡፡ ህዝብ ተስፋ እንዲኖረው የኃይል መጠቀምን አስፈላጊነት ያምኑ ነበር፡፡ ኃይልን መጠቀም ለመግደል ወይም ለመስረቅ ሳይሆን ህዘቦችን ለማዳን መሆን እንዳለበት ያምኑ ነበር፡፡ በሰላም ኃያልነት ያምኑ ነበር፡፡ ከባንቱስታንስ የዘረኝነት ደሴት በማላቀቅ ብሩህ የህዝቦችን ህይወት መመስረት እንዲቻል በደግ ስራ እና በዕርቅ ኃያልነት ያምኑ ነበር፡፡

ማንዴላ የዕርቅ ዋጋው እውነት ነው፡ ብለዋል፡፡  አንድ ሰው ለሰራው ስራ ወይም ላጠፋው ጥፋት በህዘብ ፊት ኃላፊነትን መውሰድ ዕርቅ የሚፈልገው ጉዳይ ነው፡፡ የአፓርታይድ ሰብአዊ መብት ደፍጣጮች አስከ አሁን ድረስ ለፈጸሙት ወንጀል ኃላፊነት በመውስድ ለፈጸሙት ለጥፋታቸው በህዝብ ፊት አምነው ይቅርታ መጠየቅ ይኖረባቸዋል፡፡ የጥፋት ሰለባዎቻቸው እና ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች የእነዚህን እኩይ ተግባር ፈጻሚዎች እውነተኛ ባህሪ ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እውነት እና እውነት ብቻ እርምጃ ከመውሰድ እና የጥላቻ በቀል ከመውሰድ ያድናል፡፡ ማንዴላ አገራቸውን ከአፓርታይድ የሞራል ዝቅጠት ለማጽዳት እና ህዝቡን ከአፓርታይድ የጨለማ መንገድ ለማውጣት እንዲሁም የብዙሀን ፓርቲ ስርዓት እንዲጎለብት በማሰብ የእውነት እና የዕርቅ ኮሚሽን አቋቁመዋል፡፡

ለሶስት አስርት ሩብ ዓመታት ለነጻነት ረዥሙን ጉዞ የተጓዙት ሰው አሁን ማረፍ አለባቸው፡፡ ረዥሙን ጉዞ ተጉዘዋል፣ ምክንያቱም ነጻነትን የመጠበቅ ቃልኪዳን ነበራቸውና፡፡ አሁን አሸልበዋል፡፡ ለዘላለም በሰላም ይረፉ፡፡

ሆኖም ግን ወደ ነጻነት የሚደረገውን ረዥሙን ጉዞ ለማጠናቀቅ ገና ብዙ ማይሎች እና ብዙ ያልተሳኩ ቃልኪዳኖች ይቀራሉ፡፡ የማንዴላን ረዥሙን ጉዞ አሁን የሚጓዘው ማን ነው? የማንዴላን ቃልኪዳኖች የሚፈጽማቸው ማን ነው? ማንዴላ የአፍሪካ ወጣቶች ቀንዲል…

የማንዴላ ስንብት ለአፍሪካ ወጣቶች፡ “ትግላችሁን ቀጥሉ፣ በፍጹም እጅ እንዳትሰጡ…!”

ለአፍሪካ ወጣቶች ባስተላለፉት የስንብት መልዕክት ላይ እንድደነቅ እና በጉዳዩም ላይ የበለጠ እንዳስብ ያደርገኛል፡፡ ብልሁ የአፍሪካ አንበሳ እረፍት ስለሌላቸው ወጣት የአቦሸማኔ የአፍሪካ ነብሮች ምን ይላሉ?

ትልቅ ለመሆን ድፍረት ይኑራችሁ ፣ ማንዴላ የፍሪካን ወጣቶች ታሪካዊ መጻኢ ዕድል ያስታውሳሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ታላቅ እንዲሆኑ መክረዋል፡፡ “አንዳንድ ጊዜ ታላቅነት በትውልድ ላይ ይወድቃል፡፡ ያንን ታላቅ ትውልድ ልትሆን ትችላላቸሁ፡፡ ታላቅነትህ ያብብ፡፡“

ማህበረሰቡን ከመለወጥህ በፊት መጀመሪያ እራሳችሁን ለዉጡ፣ አሮጌው የጥላቻ እና የፍርሃት መንገድ ለአዲሱ የመግባባት እና የዕርቅ መንገድ ቦታ መስጠት እንዳለበት ማንዴላ ለወጣቶቹ መክረዋል፡፡ መዘጋጀት አለባቸው፡፡ “ድርድር ሳደርግ ከተማርኳቸው ነገሮች አንዱ እራሴን እስክለውጥ ድረስ ሌሎችን መለወጥ አልችልም“፡፡ በፍጹም መጥላት የለባቸውም ምክንያቱም “ጥላቻ መርዝን እንደመጠጣት ያህል ነው፣ ጠላቴን ይገድልልኛል በሚል ተስፋ“፡፡ ጥላቻ ከውልደት በኋላ የሚመጣ ባህሪ ነው፡፡ “ባለው የቆዳ ቀለም ልዩነት፣ ባለው የአስተዳደግ ሁኔታ፣ ወይም ደግሞ በሚከተለው እምነት ምክንያት ማንም ማንንም ሊጠላ አልተወለደም፡፡ ሰዎች ጥላቻን መማር አለባቸው፣ እና ጥላቻን መማር ከቻሉ ፍቅር እንዲኖራቸው ሊማሩ ይገባል፣ ፍቅር በተፈጥሮ ወደ ሰው ልጅ ልብ ውስጥ ከተቃራኒው የበለጠ ለመግባት ስለሚችል::“

ሙከራቹህን ቀጥሉበት፣ ማንዴላ የአፍሪካ ወጣቶች ምንጊዜም እንዲሞክሩ እና በፍጹም በፍጹም እጅ እንዳይሰጡ በመምከር አዲሲቷን ጀግና አፍሪካ የመመስረት ቃልኪዳን ለመጠበቅ አንድ ሰው በቆዳው፣ በጎሳው እና በእምነቱ ጠቃሚነት ከጸጉሩ/ሯ ቀለም ልዩነት በስተቀር ጠቃሚነቱ  እርባና እንደሌለው አጽንኦ ሰጥተው አስተምረዋል፡፡ በአፍሪካ “ፍትህ እንደ ውኃ እንዲንቆረቆር እና እውነት እንደማያቋርጥ የጅረት ምንጭ እንዲፈስ” ወጣቱ መቀጠል እና ሙከራውን ማቆም እንደሌለበት ማንዴላ ምክር ለግሰዋል፡፡  በውድቀት ላይ ተመስርቶ የስኬት አዝመራ እንደሚታጨድ በመገንዘብ ወጣቶች ውድቀትን ሳይፈሩ ትግላቸውን መቀጠል እንዳለባቸው ማንዴላ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ “እኔን በማስገኘው ስኬት አትገምግሙኝ፣ ይልቅስ ምን ያህል ጊዜ እንደወደቅሁ እና ለስኬት ምን ያህል ጥረት በማድረግ እንደተነሳሁ እንጅ“ ውድቀት ኃጢአት አይደለም፡፡ ለመሞከር አለመቻል ነው ውድቀት ማለት፡፡ በህይወት ስንክሳር “ታላቁ ዝና ፍጹም አለመውደቅ አይደለም፣ ነገር ግን ትልቁ ነገር በወደቅን ቁጥር ለመነሳት የምናደርገው ጥረት ነው፡፡” ማንዴላ ለወጣቶቹ ሲመክሩ ወጣቶች በስኬት ማማ ላይ ፊጥ ለማለት ጥረት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ትከሻቸውን በማጠንከር ሊመጡ የሚችሉትን ችግሮቸ ሁሉ በመጋፈጥ በድል አድራጊነት ለመውጣት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ምክንያቱም “ትላቁን ተራራ ከወጣህ በኋላ ሌሎች ብዙ ሊወጡ የሚችሉ ተራሮች እንዳሉ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡“ በማለት አስተምረዋል፡፡

በአንድነት ሁኑ፣ የአፍሪካ ወጣቶች እንደወጣት ኃይል በአንድነት መምጣት እንዳለባቸው ማንዴላ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ እንዲህ ሲሉም መክረዋል፣ “አንድ ነጠላ ሰው ሀገሩን ነጻ ሊያወጣ አይችልም፡፡ አገራችሁን ነጻ ልታደርጉ የምትችሉት በአጠቃላይ በጋራ ስትንቀሳቀሱ ነው፡፡“

ጥሩ ሞራል ያለው/ላት ሰው ሁኑ፣ ደግነት የሞራል ቆንጆነት ነው፡፡ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ጥረት የማድረግ ጉዳይ ነው እና ማንም አዬ አላዬ ጥሩውን ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አለማለት ነው፡፡ “ከዚህ ቀደም እንደተናገርኩት ሁሉ ለእራስ ታማኝ መሆን ነው፡፡ በቅድሚያ እራስህን ካልለወጥክ በህዝብ ላይ ውጤት ሊያመጣ የሚያስችል ተጽእኖ ልታመጣ አትችልም…ታላላቅ የሰላም መሪዎች በሙሉ ሀቀኞች ናቸው፣ ታማኞች ናቸው፣ ነገር ግን ከብር ፈላጊ አይደሉም::“

አገር ወዳድ አርበኛ ሁኑ፣ ማንዴላ በአገር ወዳድ አርበኝነት ላይ እምነት ነበራቸው፣ እናም የአፍሪካ ወጣቶች ለህዝቦቻቸው እና ለአህጉራቸው አርበኛ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል፡፡ ማንዴላ እንዲህ አሉ፣ “በመጀመሪያ ደረጃ እኔ እራሴን ሁሌም የአፍሪካ አህጉር ወዳድ አርበኛ አድርጌ እቆጥራሉ፡፡“ የአፍሪካ አርበኞች የቅኝ ገዥ ጌቶቻቸውን ከአሁጉሩ አባረዋል፡፡ የአፍሪካ አርበኞች አፓርታይድን ያለደም መፋሰስ አስወግደዋል፡፡ የአፍሪካ ወጣቶች በአሁኑ ጊዜ በጋራ በመሆን ድህነትን፣ ድንቁርናን እና አምባገነንነትን ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡

ደፋር ሁኑ፣ ወጣቶቹ ደፋር እንዲሆኑ ማንዴላ መክረዋል፡፡ “ድፍረት የፍርሃት አለመኖር ብቻ አለመሆኑን ተረድቻለሁ፣ ነገር ግን በፍርሃት ላይ ድል መቀዳጀት ማለት ነው፡፡ ጀግና ሰው ማለት ፍርሃት የማይሰማው ማለት አይደለም፣ ነግረ ግን ፍርሃትን የሚያሸንፍ እንጅ::“

ትልቅ ነገር አልሙ፣ ማንዴላ የአፍሪካ ወጣቶች ትልቅ ነገር እንዲያልሙ መክረዋል፡፡ ትልቅ እንዳይሆኑ እና ሀብታም ወንድ እና ሴት እንዳይሆኑ፣ ነገር ግን ሰላሟ የተጠበቀ እና የበለጸገች አፍሪካ እንድትሆን ማለም፡፡ “በእራሷ ሰላሟ የተረጋገጠ አፍሪካን አልማለሁ፡፡ ለቆንጆዋ ደቡብ አፍሪካ ህልሞች ካሉ ወደ ግቧ የሚያደርሱ መንገዶችም አሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱ መንገዶች ደግነት እና ይቅርታ አድራጊነት በመባል ተሰይመዋል፡፡“

ከኋላ ሆናችሁ ምሩ፣ ማንዴላ በጅግናዋ አዲሲቱ አፍሪካ በአሮጌው የአስተዳደር ስልት አንዴ ስልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ እስከሞት ድረስ ስልጣን አልለቅም ማለት ቦታ እንደሌለው ለአፍሪካ ወጣቶች ምክር ለግሰዋል፡፡ ማንዴላ ወጣቶቹን እንዲህ በማለት ተማጽነዋል፣ “ከመንጋዎቹ በኋላ እንደሚሆን እረኛ በጣም ፈጣኑን ከፊት እንዲሆን መፍቀድ፣ሌሎቹ ግን እንዲከተሉ ማድረግ፣ ሁሉም ከኋላ ባለ እንደሚታዘዙ እና እንደሚመሩ እንዲያውቁት ሳይደረግ ጉዞውን ማስኬድ“፡፡ ማንዴላ እንዲህ ይላሉ፣ “ከኋላ ምራ እና ሌሎችን ከፊት አድርግ፣ በተለይም ጥሩ ነገር በሚኖርበት ጊዜ እና ድልን በምታከብሩበት ጊዜ“፡፡ አደጋ በሚኖርበት ጊዜ የፊተኛውን ረድፍ ትይዛላቸሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ህዝብ የናንተን አመራር ሰጭነት ያደንቃል… ከኋላ ሆነህ ምራ ሌሎቹ ከፊት ነኝ የሚል እምነት እንዲኖራቸው አድርጉ፡፡ “መሪነትን ማቆምም መምራት ነው“ በማለት ማንዴላ ወጣቶቹ በአንክሮ አንዲመለከቱት መክረዋል፡፡

ችግርና መከራ በትግል ላይ አንዳለ እወቁ ፣ ለነጻነት በሚደረገው ረዥሙ ጉዞ  ብዙ የህግ ሂደቶች እና ቅጣቶች እንደሚገጥሟቸው ማንዴላ ለአፍሪካ ወጣቶች ምክር ለግሰዋል፡፡ እንደሚሰቃዩ እንደ እንደሚፈረድባቸው፣ እንደሚዋረዱ፣ ኢሰብአዊነት ድርጊት እንደሚፈጸምባቸው ለአፍሪካውያን ወጣቶች ግልጽ አድርገውላቸዋል፡፡ በመጨረሻም ነጻነት እንደሚመጣ እርግጠኞች ሆነዋል፡፡ “ትናንት አክራሪ ተብየ ነበር፣ ከእስር ቤት ስወጣ ግን ብዙ ህዝቦች ጠላቶቸ ሳይቀሩ በእቅፋቸው አስገቡኝ፣ እናም ይኸንን ነው እንግዲህ  ለሌሎች ሰዎች መናገር ያለብኝ በሀገራቸው ለነጻነት የሚታገሉ ሰዎች አሸባሪዎች ናቸው“ የሚለውም መታወቅ አለበት፡፡

ከጠላቶቻችሁ ጋር ሰላም ሁኑ፣ ለሰላም ሲባል ከእነርሱ ጋር መገናኘት፣ እጅ መጨባበጥ እና ጠላቶቻቸውን እቅፍ አድርገው መሳም አንዳለባቸው ማንዴላ መክረዋል፡፡ “ከጠላትህ ጋር ሰላም እንዲመጣ ከፈለግህ ከእርሱ ጋር አብረህ መስራት አለብህ፣ ከዚያም ጓደኛ ታደርገዋለህ፡፡“

ድህነትን ተዋጉ፣ ማንዴላ የአፍሪካ ወጣቶች በአፍሪካ ቀንድ በጣም አንገብጋቢ የሆነ ችግር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ከመጨረሻው የድህነት ቋት ውስጥ ተዘፍቃ የምትገኘውን አፍሪካን የአፍሪካ ታላቁ ትውልድ እና የወደፊቱ ብሩህ ተስፋ መንጥቆ እንደሚያወጣት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ድህነትን ማስወገድ የልገሳ ስራ አይደለም፣ የፍትህ ጉዳይ እንጅ፡፡ እንደ ባርነት እና አፓርታይድ ድህነት ተፈጥሯዊ አይደለም፡፡ ሰው ሰራሽ ነው፣ እናም በሰዎች ጥረት ሊጠፋ እና ድል ሊደረግ ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ትልቅ በሚሆነው ትውልድ ላይ ይወድቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የማንዴላ ታላቅነት በአፍሪካ ወጣቶች ላይ ወድቋል፡፡

በመርሆዎች ላይ በፍጹም አትደራደሩ፣ የአፍሪካ ወጣቶች በመርሆዎች መደራደር እንደሌለባቸው ማንዴላ አጽንኦ በመስጠት ለአፍሪካ ወጣቶች ምክር ለግሰዋል፡፡ ማንዴላ ለወጣቶቹ ሲያስተምሩ እድሜልካቸውን ከአፓርታይድ እና ከዘረኝነት ጋር ስዋጋ ስታግል ኖሪያለሁ ምክንያቱም እነዚህ ጭራቆች ለሰው ልጅ ሟች ጠላቶች ናቸው፡፡ “የዘር መድልዎን እና መገለጫዎቹን ሁሉ በጣም እጠላለሁ “ በህይወት ዘመኔ ሁሉ ስታገል ቆይቻለሁ፣ አሁንም እየታገልኩ ነው እና ቀኖቸ እስኪያልቁ ድረስ መታገሉን እቀጥላለሁ…፡፡”  ይህንን በሚገባ አድረገውታል፣ ፈጽመውታልም፡፡ የአፍሪካ ወጣቶች በጥላቻ እና በሁሉም መገለጫዎቹ ላይ ማለትም በጎሰኝነት፣ በፖለቲካ ማንነት፣ በማህበረሰባዊነት፣ በጎሳ ክፍፍል፣ በጾታ ጭቆና፣ በኢኮኖሚ ብዝበዛ እና በህብረተሰብ አድልኦ ላይ በመርህ ላይ የተመሰረተ እና ድርድር የማያስገባ አቋም መያዝ እንዳለባቸው ማንዴላ በአጽንኦ ጠይቀዋል፡፡

ብሩህ አላሚ እና ጽናት ይኑራችሁ፣ የአፍሪካ ወጣቶች ብሩህ አላሚዎች መሆን እንዳለባቸው ማንዴላ መክረዋል፣ ምክንያቱም የአፍሪካውያን ምርጥ ቀኖች ገና እየመጡ ነውና፡፡ “እኔ በመሰረቱ ብሩህ አላሚ ነኝ፡፡ ከተፈጥሮም መጣ ከእራስ ጥንካሬ የምለው ነገር የለም፡፡ በከፊል ብሩህ አላሚ መሆን ማለት የአንድን ሰው እራስ ወደ ጸሐይ ቀጥ ብሎ እንዲያመለክት እንዲሁም የአንድ ሰው እግሮች ወደፊት እንዲራመዱ የማድረግ ያህል ነው፡፡ በሰው ላይ ያለኝ እምነት በሚገባ በሚፈተሽበት ጊዜ ብዙ የጨለማ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ ነግር ግን ተስፋ ቢስ ለመሆን አጅ አልሰጥም፣ አላደርገውምም አልሞክረውምም፡፡ ያ መንገድ የሽንፈት እና የሞት ነው፡፡“ የአፍሪካ ወጣቶች ያን ረዥሙን ጉዞ መጓዙን መቀጠል አለባቸው፡፡ የማንዴላ ጠንካሮች መሆን አለባቸው፡፡ “ጥንካሬው እና አስፈላጊው ጥበብ ቢኖርህም በዓለም ላይ ወደ ግለሰባዊ ድልነት ልትቀይራቸው የማትችላቸው ጥቂት መጥፎ አጋጣሚዎች አሉ፡፡“   

ተማሩ፣ ህዝብንም አስተምሩ፣ ማንዴላ ትምህርት ለአፍሪካ ወጣቶች ለእራሳቸው ስኬታማነት እና ለወደፊቷ አፍሪካ ቁልፍ ነገር እንደሆነ አስተምረዋል፡፡ “ዓለምን ለመለወጥ ትምህርት ትልቁ መሳሪያ ነው፡፡ ዜጎቹ ካልተማሩ በስተቀር ማንም ሀገር ቢሆን እድገት ሊያስመዘግብ አይችልም፡፡“

ዝምተኛ አትሁኑ፣ በጭራቅነት እና በፍትህ እጦት ጊዜ የምን አገባኝነት ባህሪ መኖር እንደሌለበት ማንዴላ ለአፍሪካ ወጣቶች አስተምረዋል፡፡ ጭራቃዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እየተመለከቱ ዝም ከማለት የበለጠ ጭራቅነት የለም፡፡ ጭራቃዊ ድርጊት በየትኛውም መልኩ ሲፈጸም ስናይ ልንዋጋው ይገባል፣ ወጣቶች ጭንቅላታቸውን ክፍት ካደረጉ እውነት በእራሱ ይገለጽላቸዋል፡፡ “ምንም ዓይነት ድንገት ያገኘሁት ግንዛቤ የለኝም፣ ምንም ዓይነት መረጃም የለኝም፣ እውነት የተገለጸበት አጋጣሚም የለም፣ ነገር ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ጨዋነት የጎደላቸው ድርጊቶች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ውርደቶች፣ እና እንድናደድ፣ እንዳምጽ እና ህዝቤን አፍኖ የያዘውን ስርዓት እንድዋጋ በሺዎች የሚቀጠሩ ላስታውሳቸው የማልችላቸው አጋጣሚዎች ያሉ መሆኑን“ በማለት ማንዴላ ለአፍሪካ ወጣቶች አስተምረዋል፡፡ በተነገርኩት ላይ የተወሰነ ቀን የለም፣ ስለሆነም እራሴን ለህዝቤ ነጻነት መስዋዕት አደርጋለሁ፣ ይልቁንም በተግባር እያዋልኩት መሆኑን እራሴን አዚያው ውስጥ አገኘሁት፣ እንደዚያ ካልሆነ ወደ ተግባር መተርጎም የሚቻል አይሆንም፡፡”

ወደ ነጻነት፣ ዴሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት ጥበቃ የሚደረገው ረዥሙ ጉዞ ቀላል አይደለም…፣ ማንዴላ ለነጻነት፣ ለክብር፣ ለዴሞክራሲ እና ለሰብአዊ መብት ጥበቃ የሚደረገው ትግል ረዥም፣ አስቸጋሪ እና አደገኛ መሆኑን ለአፍሪካ ወጣቶች መክረዋል፡፡ እንዲህም ብለዋል፣ “ወደ ነጻነት የሚያስኬድ ቀላል ጎዞ የትም ቦታ አይገኝም፣ እናም አብዛኞቻችን ከምንመኘው የተራራ ጫፍ ላይ ከመድረሳችን በፊት ደግመን እና ደጋግመን በሸለቆው የሞት ጥላ ስር ማለፍ አለብን፡፡“

ገና ብዙ የሚወጡ ተራሮች ይቀሩኛል፣ ወደ ነጻነት የሚደረገው ታላቁ ጉዞ በኮረብታዎች እና በተራሮች የሚያቋርጥ እና በሸለቆዎች የሚዘረጋ ነው፡፡ በጉዞው ላይ ያልተጠበቁ አደጋዎች ያጋጥማሉ፡፡ ለማረፍ ትንሽ ጊዜ ነው ያለው፡፡ ማንዴላ እንዲህ ብለዋል፣ “ለነጻነት የሚያስኬደውን ያንን እረዥሙን ጉዞ ተጉዠዋለሁ፡፡ በእራስ መተማመንን እንዳላጣ ጥረት አድርጊያለሁ፡፡ በጉዞው መንገድ ላይ የተሳሳቱ ቅደምተከተሎችን ፈጽሚያለሁ፡፡ ነገር ግን ከትልቁ ተራራ ጭፍ ላይ ለመውጣት ገና ብዙ ኮረብታዎችን መውጣት አንደሚኖርብኝ አረጋግጫለሁ፡፡ ለማረፍ ትንሽ ጊዜ ወስጃለሁ፣ ሰረቅ አድርጌም የከበበኝን አስደናቂውን አካባቢያዊ ሁኔታ ተመልክቻለሁ፣ የተጓዝኩትን ርቀት መለስ ብዬ ተመልክቻለሁ፣ ግን ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው ለማረፍ የቻልኩት፣ ነጻነትን ለማግኘት ኃላፊነት መምጣት አለበት፣ እና በምንም ዓይነት መልኩ ከወዲያ ወዲህ እያልኩ አልንገዋለልም፣ ረዥሙ ጉዞዬ አልተጠናቀቀምና፡፡“

ሁልጊዜ ደግ ለመስራት ሞክሩ ፣ ይቅርታ ለማድረግ፣ ዕርቅ ለማውረድ…. ጥሩ ነገር ለማድረግ፣ ይቅርታ ለማድረግ እና ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ጥረት አድርጉ፡፡ የስኬት ቃልኪዳን ባይኖርም ሞክሩ፣ ውድቀት እንዳለ ብታውቁም ሞክር፣ ጥርጣሬ ያለ እና እርግጠኝነት የጎደለ መሆኑን ብታውቅም ሞክር፡፡ ደክመህ እና መቀጠል የማትችል መሆኑን ባታውቁም እንኳ ሞክሩ፡፡ ተስፋ በማይኖርበት ጊዜም ሞክሩ፡፡ ዓላማህን ካሳካህ በኋላም ቢሆን ሞክሩ፡፡ ለመሞከር አስቸጋሪ እና ትርጉምየለሽ በሆነበት ጊዜ እንኳ ቢሆን ሞክሩ፡፡ ምርጫ በሌለበት ግን ሙከራ ብቻ ባለበት ሁኔታም ቢሆን ሞክሩ፡፡ ጭራቅነት በመልካም ተግባር ላይ ድልን እንዳይቀዳጅ ሞክሩ፣ ማንዴላ እንደሞከሩት ሁሉ ሞክሩ፡፡

ስንብት፣ ለእኔ አፍሪካዊ ክቡር! ለእኛ አፍሪካዊ ክቡር!

ብዙ ምናባዊ ንግግሮችን ላደረግሁላቸው ለኔልሰን ሮሊህላህላ ማንዴላ የሚወዱትን እና የሚደሰቱበትን “የሸክስፒርን” ቃላትን በመዋስ የመጨረሻ ስንብቴን ላቅርብ፡፡ ማንዴላ በእስር ቤት ውሰጥ ሳሉ የሸክስፒር ጁሊየስ ቄሳር የቄሳር ቃላት ይስሟሟቸው ነበር፡፡

እስከአሁን ከሰማኋቸው አስደናቂ ነገሮች መካከል ለእኔ እንግዳ የሚሆነው ወንዶች ሞት የሚመጣ የመጨረሻ መሆኑን አይተው መፍራት አለባቸው የሚለው ነው፡፡ አለመፍራት አስደናቂ አይሆንምና፡፡ ለኔልሰን ሮሺስላሽላ ማንዴላ የሆራሽዎ የሀዘን ቃላትን በመጠቀም የመጨረሻ ስንበት አደርጋለሁ፡፡

አሁን የተከበረ ሰው ልብ ተሰብሯል፡፡
የተከበሩ ደህና ይደሩ፣
ነብስዎ በሰላም እንድታርፍ መላዕክት ይዘምራሉ፣

እና በዚህ አሳዛኝ ህልፈት የጆህን ዶኔን ቃላት በመጠቀም እጮሃለሁ፡፡

ሞት ኩራት አይደርብህ፣ አንዳንዶች ኃይለኛ እና አስፈሪ ብለው ቢጠሩህም፣ አትፈራም
ሞት ማዲባን አትገድልም አትችልም!

ዘላለማዊ ክብር ለማንዴላ፣ ዘላለማዊ ክብር ለኔልሰን ሮሊህላህላ ማንዴላ!   

ታህሳስ 2 ቀን 2006 ዓ.ም

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 11, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.