የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ያረጋል አይሸሹም ታሰሩ

(አውራምባ Times) – የቀድሞ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከትናንት በስትያ በፌዴራል የሥነ-ምግቦር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገለፀ።

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባልና የህብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያረጋል አይሸሹም በቁጥጥር ስር የዋሉት የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን የተጠርታሪው ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ለምክር ቤቱ ያቀረበውን ጥያቄ መሠረት በማድረግ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 7 ቀን፣ 2004 ዓ.ም ባካሄደው የሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ መወሰኑ ይታወሳል።

ከተጠርጣሪው የሙስና ወንጀል ምርመራ ጋር በተያያዘ ኮሚሽኑ ከ2003 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ ባደረገው ክትትልና ማጣራት በፌዴራል መንግስት የበጀት ድጎማ እና በክልሉ በጀት በ1998 ዓ.ም የጣና በለስ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤቶች፣ የግልገል በለስ መምህራን ኮሌጅን እና የአሶሳ ሙያና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ተቋምን ለማስገንባት በተደረገው እንቅስቃሴ የጨረታውን ሂደት አዛብተዋል።

በዚህ መሠረት የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ከነበሩት ከአቶ ሀብታሙ ሂካ እና ከጥቂት ኮንትራክተሮች ጋር በመመሳጠር በመንግስት የግዥ መመሪያ መሠረት በግልፅ ጨረታ በማውጣት አቅሙ ያላቸው ተወዳዳሪዎችን በመጋበዝ በጥራት ማሰራት ሲገባቸው፣ በውስን ጨረታ እንዲፈፀም ትዕዛዝ በመስጠት በመንግስት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ ተጠርጥረዋል።

በሌላ በኩል የእነዚህ ፕሮጀክቶች ስራ ውል ከተገባበት ከ1998 ዓ.ም መጨረሻ እና ከ1999 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ በ13 ወራት ውስጥ ተሰርቶ እንዲጠናቀቅ ውል የተገባ ቢሆንም፣ ከተቋራጮቹ ጋር አስቀድሞ በተፈጠረ ሕገ-ወጥ የጥቅም ግንኙነት ምክንያት ፕሮጀክቶቹ እስካሁን ካለመጠናቀቃቸውም በላይ ለተቋራጮቹ ከውሉ ውጭ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፈል ምክንያት መሆናቸው ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ያረጋል የመንግሥት ተቀጣሪ ቢሆኑም በሕጋዊ መንገድ ሲያገኙት ከነበረው ገቢ በላይ ሀብት ያፈሩ ለመሆኑ አመላካች ማስረጃዎች መገኘታቸውንም ኮሚሽኑ ባካሄደው ማጣራት እንደደረሰበትና ቀደም ሲል በቁጥጥር ስር የዋሉት የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ሂካ እና በጉዳዩ በአባሪነት የተጠረጠሩ የሥራ ተቋራጮችም በምርመራ ላይ የሚገኙ መሆኑንም ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።

ምንጭ፡ አውራምባ Times

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 23, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.