የባንክ ዕዳ ሲፈለግ የሸፈተው “ታጋይ”

ሲሳይ አጌና  — [ Picture in PDF]

አባባ ታምራት፣አርቲስቶቻችን እና የህዳሴው ግድብ” በሚል ርዕስ  ባለፈው ባቀርብኩት ጽሁፍ  ላይ ያልተቋጨ እና  በይደር የተውነው ነገር መኖሩ ዕውነት ነው፤በዚያ ጽሁፍ ላይ የሰዎቹ ስም ባለመጠቀሱ ቅር ያላቸው፣ልብ ወለድም የመሰላቸው አጋጥመውኛል፤በኤሌክትሮኒክስ የመልዕክት ሳጥኔ ውስጥ::እንከሳለን ያሉም ጽፈውልኛል ፤ክሱ ሄግ ይሁን ልደታ ባይታወቅም።እርቃን ዳንስ ቤት የተገኘው ሚንስትር ማነው?ኮተቤው ጠንቋይ ቤት የተገኘውስ ? የአባባ ታምራት ደንበኛ የነበሩትስ እነማን ናቸው.? ….ከባንክ ብድር ወስዶ በዕዳ ሲፈለግ ጫካ የገባውስ ማነው ?ዛሬስ የየትኛው ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር  ነው የሆነው ?ኢህአዴግን ስትከዳ በኢሕአዴግ ማጋጣነቷ የተጋለጠባት ማነች?  የሚሉት  ጥያቄዎች  በርክተው  ቢመጡም  ለሁሉም ምላሽ መስጠት ባለመቻሌ አዝናለሁ፤የቢዮንሴን ጫማ  ያደረገላት ሰው ማንነት የብዙዎቹን ትኩረት መሳቡ ግን ያልጠበኩት ነበር።

     ..እነዚህን  በነውር  የተሞሉ፣በሃጢያት የተበከሉ ሰዎችን በስም ያልጠቀስኩዋቸው  በዋናነት  ይታረማሉ በሚል  ሳይሆን፣በነርሱ ነውር  የእነሱ ብቻ ያልሆኑት ፣ የኢትዮጵያ ጭምር የሆኑት ልጆቻቸው እንዳይሰበሩ ለመጠበቅ ነው።

           “የአባባ ታምራት” ደንበኛ ስለመሆኗ ፍርድ ቤት በምስክሮች ስሟ የተጠቀሰ እና ይኸው  በጋዜጣ ላይ የወጣባት  አርቲስት በልጆቿ ላይ በትምህርት ቤታቸው የደረሰባቸውን በወቅቱ ሰምተን ብዙዎች አዝነናል፤ሌሎች ሕጻናት እንዲሰበሩ አልፈልግም፤… ይሁን እና  በዘመነ ኢህአዴግ ሌብነት ነውርነቱ እየቀረ፣በአዋቂነት እየተመነዘረ  ነውና  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ገንዘብ  ይዘው  ከነዕዳቸው ጫካ የገቡትን፣ይህንን ታማኝነታቸውን እና ልምዳቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የአንድ ኢሕዴግ ሰራሽ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር የሆኑትን  ገድል መተረኩ  ግን የሚታለፍ አይደለም፤በሀገር ሀብት ላይ  የተፈጸመ ዘረፋም ነውና።

         እኚህ ሰው  “አማራው ወያኔ” በሚለው መጠሪያ ይበልጥ  ይታወቃሉ፤በብሄረሰብ  አማራ ሆነው ሕወሃትን ስለተቀላቀሉ የወጣላቸው ስም ነው፤ሕወሐትን የተቀላቀሉት ደግሞ በዓላማ ሳይሆን ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደሩትን ገንዘብ  መመለስ አቅቷቸው ሲሸሹ ነበር፣ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቴዎድሮስ ቅርንጫፍ 45 ሺህ ብር ተበድረው እስከ ሐምሌ 24/1976 ከነወለዱ 101 ሺህ ብር ደረሰ ፣በጋዜጣም  ተጠርተው ሊገኙ ስላልቻሉ በፍትሃብሄር መዝገብ ቁጥር 1000/77  መስከረም 22 ቀን 1978  ውሳኔ ሲተላለፍባቸው ርሳቸው ትግራይ በረሃ ውስጥ ከሕወሐት ጋር ነበሩ።አዎን እኚህ ሰው ከድል በዃላ  ለብአዴን ተሰጥተው  ከብአዴን አመራሮች አንዱ ሆነው ቆይተዋል፤ዛሬ ደግሞ በዋናነት ብአዴን  ያቋቛመው  ዓባይ ባንክ የቦርድ አመራር ናቸው፤ወንድወሰን ከበደ ይባላሉ፤ “ሞኝ እና ወረቀት” ሆነ እና  አቶ ወንድወሰን ከኢሕአዴግ ጋር አዲስ አበባ ሲገቡ  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነገረ ፈጆች ደረሱባቸው፤እዳቸውን  እንዲከፍሉም፡ጠየቁዋቸው።

      በኢትዮጵያ ሕግ ከመደርደሪያ ጌጥነት ባሻገር የሚጨበጥ አይደለም እና  አቶ ወንድወሰን አሻፈረኝ አሉ፤ሕወሐትም የገንዘብ ጉዳይ ሲነሳባቸው የገንዘብ ሚኒስትር አድርጎ ሾማቸው።ከርሳቸውም ልምድ በመውሰድ 1.7 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኤፈርት ስም  ተበደረ፤አቶ ወንድወሰን ከበደ ጠመንጃ ስሌላቸው ጠመንጃ ወደ ነበራቸው አማጺያን ከነእዳቸው ሲሸሹ፣ጠመንጃው በእጁ የሆነው ሕወሀት   በኤፈርት ስም የተበደረውን የተበላሸ ብድር በሚል  ወደ ልማት ባንክ እንዲዞር አደረገ፤ፋይሉም ድራሹ ጠፋ።አሁንም ይህ አልበቃ ብሎ  የመሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካን ለማስፋፋት  ከኢትዮጵያ  ልማት  ባንክ በብድር መልክ ዘረፋውን ለመቀጠል አቶ መለስ ዜናዊ መመሪያ ሰጥተዋል፤ “አንበሳ ምን ይበላል ተበድሮ፣ ምን ይከፍላል  ማን  ተናግሮ ?” ነው ሚባለው?(በቀድሞው የሕወሐት ታጋይ በአቶ አማረ አረጋዊ በሚዘጋጀው ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የወጣውን  ምስክርነት ይመልከቱ.. የኤፈርት የብድር ፋይል ከብድር ክፍል መሰወሩን ነው የሚነግረን)..የሀገሪቱ የሕዝብ ሃብት  የሆኑት  ባንኮች የሕወሀት የግል ካዝና ሆነዋል ::          በግለሰብ ስም ከሀገሪቱ ባንኮች  በብድር መልክ  እየተዘረፈ ከሚገነባው የሕወሃት ገዢዎች ሕንጻ በተጨማሪ በኤፈርት ኩባንያዎች ስም  ቦሌ መንገድ ከአስር ዓመት በፊት ከቆመው  ሜጋ  ሕንጻ በተጨማሪ፣በጎኑ ሌላ ግዙፍ  ሕንጻ በመገንባት ላይ ይገኛል።

      የሕወሃት ንብረት የሆኑት ሬዲዮ ፋና እና ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል  በአዲስ አበባ ግዙፍ ሕንጻ ሰርተዋል፤በጦርነቱ ወቅት ከተሞችን ሲቆጣጠሩ ከመንግስት ባንኮች  እየዘረፉ የመጡትን የሕዝብ ሐብት  እንደምርኮ ንብረት የግላቸው እንዳደረጉት ሁሉ፣መንግስታዊ ስልጣን ከያዙ ከ20 ዓመታት በዃላም   የዘረፋ ሱሳቸው ሊረካ አልቻለም፤ነባሮቹ  እና  በላባቸው ጥረው ግረው ያደጉት ነጋዴዎች  በሰበብ አስባቡ ወደ ወህኒቤት እየተነዱ ሀብት ንብረታቸውን እየተዘረፉ ይገኛሉ። ግፉ፣ጉድፉ ብዙ ነውና የኤፈርትን ጉዳይ  ለዝርዝር ዕይታ  ለሌላ ግዜ  መርተነው ወደ “አማራው ወያኔ ” እንመለስ።

             አቶ ወንደሰን  ከሕወሃት  ወደ ብአዴን በዝውውር መሄዳቸውን ሳወሳ ከብአዴን  ወደ ጉሕአዴን ዝውውር ያደረጉት የቁጨው ዶክተር ትዝ አሉኝ፤የኢህአዴግ ነውረኛነትም ጭምር። እንዲህም ሆነ -ኢሕአዴግ ግንቦት 20/1983 ሀገሪቱን ተቆጣጠረ፤ለአንድ ወር ከአራት ቀናት በግዚያዊ መንግስትነት  ሀገሪቱን ከገዛ በዃላ ሰኔ 24 የሽግግር መንግስት መስራች ጉባዔ ተካሄደ፤በዚህም መሰረት ኢሕአዴግ 38 ፣ኦነግ 12፣ ሌሎችም  በየደረጃው ወንበር ተሰጣቸው፤በዚህ ድልድል መሰረት የጉራጌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የተባለ ድርጅት 3 ወንበር  አገኘ፤የዚህ ግንባር መሪዎች ዶ/ር ፈቃደ ገዳሙ እና ዶ/ር ሃይሌ ወልደ ሚካኤል ነበሩ፤እነዚህ ሰዎች  የታጠቀ ስራዊት ባያደራጁም የዕውቀት  ማዕረጋቸው በማህበረሰቡ ውስጥ ባለከባድ ሚዛን እንደሚያደርጋቸው የታወቀ ነው፤የጉራጌ ብሄረሰብ ደግሞ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ሚናው የሚታይ ነበር፤ዛሬ ከጨዋታው  ሜዳ እየተገፋ  ቢሆንም።

         እናም ሕወሃቶች ለከባድ ሚዛኖቹ ከባድ ሚዛን  ተፎካካሪ ከብአዴን አዲስ ወደ ተመሰረተው ጉሕአዴን ዝውውር አካሄዱ፤ጉሕአዴን-የጉራጌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ነው።ወደ ጉህአዴን የመጡት እና የፓርቲው መሪ ሆነው የተሰየሙት  “ዶክተር” አህመድ. ሀሰን. ነበሩ፤እኚህ ሰው አስከ 1988 እና ከዚያም በዃላ  ኢህአዴግን ወክለው በፓርላማ አባልነታቸው ቀጥለዋል፤በ1988 ዓ.ም “ትኩረት” ይባል የነበረው ጋዜጣ  በእኚህ ሰው ላይ አንድ ጉድ ይዞ ወጣ፤”ዶክተር ነኝ ባዩ  የሁለተኛ  ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አለመውሰዳቸው ተረጋገጠ” በሚል ዘገበ፤በርግጥም ጉድ ተባለ፤ሰውየው የዶ/ር ገጸ ባህርይ እንዲላበሱ የተፈለገው  እነዚያን ዶክተሮች ለመፎካከር  ነበር ፤ከተነቃ ምን ይደረጋል? ለአራት ዓመታት ያህል ከተጠሩበት በዃላ በፓርላማው ውስጥም ከፓርላማ ውጭም አቶ መባል ጀመሩ፤….ሕወሀት/ ኢህአዴግ ማለት እንዲህም ይዘቅጣል።

            የሽግግሩ ዘመን ሲነሳ የሽግግር መንግስቱን ጸሃፊ አቶ ተስፋዬ ሃቢሶን ማስታወስ ግድ ይላል፤…እኚህ ሰው በቅርቡ በአንድ ወንጀል እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ይታወቃል።እኚህ ሰው ከሩብ ምዕተ ዓመት በፊት ዶ/ር  ኮሊን ዳርሽ  በተባሉ ደቡብ አፍሪካዊ   ምሁር ከ35 ዓመት በፊት  የተጻፈን  ጽሁፍ ሰርቀው ተያዙ፤ ርዕሱን ጭምር ሳይለውጡ የራሳቸው አድርገው በስማቸው በኢንተርኔት ላይ የበተኑትን የአዲስ ቮይሱ አበበ ገላው አጋለጠ፤በትውልድ እንግሊዛዊ በዜግነት ደቡብ አፍሪካዊው ምሁር  በኢትዮጵያ ተማሪዎች ትግል ላይ የጻፉትን ይህን ጽሁፍ  አቶ ተስፋዬ  በራሳቸው ስም ለማውጣት በጽሁፉ ላይ ያደረጉት አስተዋጽኦ  የጸሃፊውን ስም በማንሳት  ራሳቸውን ስም መተካታቸው ብቻ ነበር።

         በርግጥ  የፊደላቱን  መጠን ከፍ በማድረግ  ገጹ እንዲበዛ አደርገዋል፤በጊነስ  ዎርልድ ሪከርድስ ላይ ሊመዘገብ የሚገባው የተባለው ይህ ፕላጀሪዝም (የአዕምሮ ስራ ስርቆሽ?)  ስርዓተ ነጥቦች ጭምር ሳይዛቡ  የተፈጸመ ነው። ስርቆሹ የተፈጸመው ከተጻፈ ከ33 ዓመታት በዃላ  ነበር። “የእጅ አመል” ነው  የሚባለው? የኢትዮ-ሚዲያው  አብርሃ በላይ በሌላ ስርቆሽ እጅ ከፍንጅ ያዛቸው፤ጽሁፉ የተሰረቀወ  ከጋናዊ  የድረ ገጽ ጸሃፊ  ያው ሶፊዝም ሲሆን፣የተጻፈው የዛሬ 8 ዓመት በኦክቶበር 2003 ነበር።

            ጽሁፉ በጋና ህዝባዊ ውይይቶች ላይ በማቆጠቆጥ ስለሚገኙ ጉድለቶች ይተቻል፤በርግጥ እዚህኛው ላይ አቶ ተስፋዬ የርሳቸው አስተዋጽኦ ተመዝግቧል፤ በጋናዊ  ስለጋና  የተጻፈ በመሆኑ አቶ ተስፋዬ ጋና የሚለውን ኢትዮጵያ እያሉ በመተካት  ብዙ ተጨንቀዋል፤በተረፈ ያደረጉት አስተዋጽኦ የጸሃፊውን ስም በመሰረዝ የራሳቸውን ስም ተክተዋል፤ሌሎች ስርቆቶችም እንዲሁ ለአደባባይ በቅተዋል።ኢትዮጵያ  ጨለማ ውስጥ ሆና አቶ ተስፋዬ ብርሃን የሚታያቸው፣ዴሞክራሲው ያወዳቸው ርሱንም ከጋና ኮርጀው ስለሚነግሩን ሊሆን ይችላል፤…እንዲህ እጅ ከፍንጅ  ከተያዙ በዃላ መቼም  እንደበፊቱ  ቦሌ “ኤሌፋንት ዎክ” በረንዳ ላይ ለማኪያቶ ማልደው እንደማይሰየሙ ይታመናል፤ባይሆን ወጪ ወራጁ እንዳያያቸው ወደ ፒኮክ  ዞር ቢሉ ቢያንስ ዛፉ ከመጠቋቋም ያድናል፤በደቡብ አፍሪካ እና በኡጋንዳ የኢህአዴግ አምባሰደር፣ የሽግግር መንግስቱም ጸሃፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ሃቢሶ እንዲህ ያለ ገድል እያላቸው የኢሠፓ አባልነት  ጠይቀው መከልከላቸው ግን  የሚገርም ነው።።

        አቶ ተስፋዬ ሃቢሶ በደርግ ዘመን የኢሰፓ አባል ለመሆን ጠይቀወ የተከለከሉ መሆናቸውን ሙዳይ መጽሄት  በ1985 ከነ እጅ ጽሁፋቸው አጋልጣ ነበር ፤….ለማንም የሚታደለውን ኢሰፓነት ተማጽነው ሲከለከሉ ምን ምክንያት እንደተሰጣቸወ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣መጠየቃቸውን  የእጅ ጽሁፋቸው ሲያጋልጥ፤መከልከላቸውን   የሚያረጋግጠው ደግሞ የሽግግር መንግስቱ ሲመሰረት የኢሰፓ  አባላት  እንዳይደራጁ በሕግ መከልከላቸው ነው፤አቶ ተስፋዬ ግን የኢሰፓ አባል ስላልነበሩ፣ማለትም  ጠይቀው ስለተከለከሉ የከምባታ ሕዝብ ኮንግረስ የሚባል ፓርቲ መስርተው የሽግግሩ ምክር ቤት  አባል እና ጸሃፊ ነበሩ።

(አቶ ተስፋዬ የራሳቸውን ማንነት በጥቂቱ ገልጸው ፣ አድሃሪ ያሉትን ሥርዓት አውግዘው ፣ አብዮቱን አወድሰው  ግንቦት 10ቀን 1976 ዓ.ም  ኢሠፓ አባል ለመሆን ጽኑ  ፍላጎት እንዳላቸው  በእጅ ጽሁፋቸው የገለጹበትን  ማመልከቻ ይመልከቱ።)

          እነዚህን መሰል ሁኔታዎችን ስናይ፣በባለፈው ጽሁፌ ያነሱዃቸውና መሰል   ጉዳዮች ሲታከሉ የሕወሃት ሰዎች  አንድም ብቃት የሌለውን ፣ብቃት ካለውም ጉድለት ያለውን በማሰስ እና ለአገልጋይነት በማሰለፍ እንደ ትጥቅ ትግሉ ተሳክቶላቸዋል፤ በቀጥታ በራሳቸው  ላይ የሚታይ ጉድለት ባይኖርባቸው እንኩዋን  በቤተሰባቸው የጎደፈ ታሪክ  ሳቢያ  ሕወሐት በመሳሪያነት የሚጠቀምባቸው አሉ።

          ኢህአዴግን ሕገ መንግስት በማርቀቅ  እና በሌሎች መሰል ጉዳዮች ጉልህ ሚና የነበራቸው ነፍሳቸውን ይማረው እና አቶ ክፍሌ ወዳጆ እንደነበሩ ይታወሳል። አባታቸው አቶ ወዳጆ አሊ ለጣሊያን አድረው  በጣሊያኖች ፍርድ ቤት  በሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ላይ ሞት  የፈረዱ  መሆናቸውን  ስንሰማ  የሕወሐት የ ”አደን” ችሎታ ይከሰትልናል፤ስለ አቶ ክፍሌ ስናነሳ ስለርሳቸው በመጻፉ  የሁለት ዓመት ከ ስድስት ወር እስራት ተፈርዶበት የነበረው እና ራሱን በራሱ የፈታው ጋዜጠኛ ጌታሁን  በቀለ ይታወሳል፤ጌታሁን በቀለ በታህሳስ 1988  የሀገሪቱን ዋና እስር ቤት ከርቸሌን በቀን ብርሃን ሰብሮ ነበር ያመለጠው፤እንዳመለጠም እነሆ 15 ዓመታት ተቆጠሩ።.የኢትዮጵያም  ሕዝብ  በሕወሀት እንደታሰረ 20 ዓመታት አለፉ፤የሚፈታን ማነው?የምንፈታውስ መቼነው? ወደ ነጻነት የሚያደርሰን የቡአዚዝ መንገድ ወይንስ   የካቢላ መስመር? 

እነሆ አድራሻዬ፦ lualawi2000@yahoo.com

ነሀሴ 3/2003

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on August 10, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.