የ’ቢግ ብራዘር’ ትርኢት ትክክለኛ ቀለም

ግደይ ገብረኪዳን 

betty ethiopian sex big brother africa show 2መነሻ

ይህ የፉክክር ትርኢት በአለም ከተስፋፉት ሰብአዊ ክብርን ለመቀነስ ከተፈጠሩ እውነተኛ ክስተት (ወይም ሪያሊቲ) ቲቪ ፕሮግራሞች አንዱ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ተፎካካሪዎቹ እንዲሰብኩለት የሚፈልገው እራስ ወዳድነትን፣ በማንኛውም መንገድ የፈለከውን ማግኘትና ሌሎችን መብለጥ የመሳሰሉ ስሜቶችን በአረመኔያዊ ድርጊቶች አሳቅፎ ማቅረብ ነው፡፡
በቴሌቪዥን መታየት ብርቅ እንደሆነ እንዲህ አይነት የተንኮል ፕሮግራሞች አገር ውስጥ መጥተው ሰው ሲወስዱ ሚድያዎች ከኢቲቪ እስከ ኤፍኤም ሬድዮዎች፣ መጽሄቶችና ጋዜጦች ድረስ በደስታ ተወራጭተው ጉዳዩን ልክ ለክፉኛ ችግር መድሃኒት እንደተገኘ አድርገው ይዘግቡታል፡፡
ቢግ ብራዘር ማለት ወንድም ጋሼ እንደማለት ሲሆን ቃሉን የተዋሱት ጆርጅ ኦርዌል እንደመጥፎ ካቀረበው 1984 ከተሰኘው መጽሐፉ ላይ ነው፡፡ ኦርዌል ወንድም ጋሼን ያሳየን እንድናውቀው እና በዓይነ ቁራኛ እንድንጠብቀው ነው እንጂ በስሙ ትርኢት ፈጥረን እንድንፈዝ አልነበረም፡፡ በኦርዌል አለም ሕዝቡ ወንድም ጋሼ (የወንድም ጋሼ ምስልን የፈጠሩት ገዢ ቡድኖች) የሚያደርጉትን ሁሉ በቴክኖሎጂ ተጠቅሞ እንደሚከታተልና እስከ ሐሳብ ልዩነት የሚያሳየውን ሰው በሐሳብ ፖሊሶች በመያዝ እና ቋንቋን ሁሉ በመቀየር ሰዎች መሰረተ-እውነት (ሎጂክ) የተከተለ ሐሳብ ማራመድ እንዲሳናቸው የሚደረግበት ስርዓት ነው፡፡ ይህን ስም ለትርኢታቸው መምረጣቸውና የትርኢታቸውን ዓርማ በሚስጥር ማህበራት እንደምናውቀው አንድ ዓይና ማድረጋቸው ስለትርኢቱ ብዙ ይነግረናል፡፡
የትርኢቱ መርትኦ ከሌላው ዓለም የተነጣጠሉ ሰዎች ስብስብ አንድ ቤት ውስጥ በደባልነት አብረው እየኖሩ የሚያደርጉት ሁሉ በካሜራ መከታተል ነው፡፡ ፉክክሩን በአንድ ዘመኑ ለ3 ወር ያክል ግዜ ይቆያል፡፡ በፉክክሩ ለማሸነፍ ተሳታፊዎቹ በመሃል ሳይባረሩ መጨረሻ ላይ አንድ ሁኖ መቅረት ይኖርባቸዋል፡፡ ሲያሸንፉ ዳጎስ ያለ ጥቅም በሽልማቱ ያገኛሉ፡፡

ወንድም ጋሼ በአፍሪካ

ይህ ትርኢት የአፍሪካ ግልባጩ አስራ አራት አገሮችን ያሳትፋል በመጀመርያው ዘመኑ አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ማላዊ፣ ናሚብያ፣ ናይጀርያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛንያ፣ ዩጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ይዞ የነበር ሲሆን ከአራተኛው ዘመኑ ጀምሮ ደግሞ ኢትዮጵያ እና ሞዛቢክን ጨምሯል፣ ቀጥሎም በሰባተኛው ዘመኑ ላይቤርያ እና ሴራልዮንን ጨምሯል፡፡ ከእያንዳንድ ሃገር የሚመረጠው ሰው በተነጠለው ቤት ውስጥ ከሌሎቹ ጋር ከዓለም ተገልለው ቤቱ ብቻ ዓለማቸው ሁኖ ዓለምን ረስተው፣ የተመልካች ድምጽ አግኝቶ ሳይባረሩ እስከመጨረሻ ለመቆየት ይታገላል፡፡
የዚህ ዓለም አቀፋዊ ትርኢት የአፍሪካ ስሪቱ የተለያዩ ሃገራትን አጣምሮ ሲያወዳድር የመጀመርያው ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2003 በመጀመርያው ዘመኑ ከ 12 ሃገራት በሰበሰባቸው ሰዎች ነበር የጀመረው፡፡ ሁለተኛ ዘመኑን ዳግም ለማካሄድ የ 4 ዓመት እረፍት አድርገዋል፡፡ አሸናፊዎች እስከ 300,000 ዶላር ማለትም 5,400,000 ብር ድረስ ያገኛሉ፡፡

ወንድም ጋሼ እና ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ የዚህ ትርኢት አካል ለመጀመርያ ግዜ ተደረገችው በአራተኛ ዘመኑ በያእቆብ አቤሴሎም የተባለ ወጣት እንዲሳተፍ ሲደረግ ነበር፣ ይህም እ.ኤ.አ. በ2009 መሆኑ ነው፡፡ አቤሴሎም ማለት የቀስተደመና ስፖንጅ ፋብሪካ ባለቤት ናቸው፡፡ በቀጣዩ ዓመት የትርኢቱ አምስተኛ ዘመን ከዚህ በፊት በትርኢቱ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች መልሰው መጥተው የተወዳደሩበት ሲሆን ያእቆብ ዳግም ከኢትዮጵያ ተሳትፏል፡፡ ያእቆብ እና አጋሩ በአራተኛው የውድድር ዘመን ለሳምንት ያህል ጊዜ እንደበግ እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ፈተና ወድቀው ነበር ከውድድሩ ለመጣል የበቁት፡፡ በአምስተኛው ዘመን ያእቆብ በራሱ ጥያቄ ከፉክክሩ እራሱን አግልሏል፡፡ በውድድሩ 35ኛ ቀን ጎተራና በረት ቤት ውስጥ እንዲኖር ከተወሰነበት በኋላ በ50ኛው ቀን በራሱ ጥያቄ በትርኢቱ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ እራሱን አግሏል፡፡
በቀጣዩ ዘመን ኢትዮጵያ በሁለት ዳኒ እና ሃኒ የተባሉ ወጣቶች ተወክላ ተሳትፋ የነበረ ሲሆን፣ ቀጥሎ በነበረው በሰባተኛው ዘመን ኢትዮጵያ ተሳትፎ አልነበራትም፡፡ አሁን በስምንተኛው ዘመን ደግሞ ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ያስገደደኝ ቤቲ የተባለች የትእይንቱ ድረ-ገጽ መረጃ መሰረት ከአዲስ አበባ የሆነችና 26 ዓመቷ የሆናት በሙያዋ መምህር የሆነች ወጣት ተወክላለች፡፡ ምስሏን ላየ እድሜዋ ትክክለኛ ግምት ቢያንስ አንድ ቢበዛ አንድ ከግማሽ አስር ዓመት እንዳልተመዘገበ ልብ ይሏል፡፡
ይህን ጽሑፍ በቤቲ ምክንያት ስጽፍ ቤቲ ላይ በማነጣጠር ነጠላ ክስተትና በቀርቡ የምትረሳ ሰውን ለመውቀስ አይደለም፡፡ እርሷ በስልት ከዚህ አፀያፊ ተግባር አካል እንድትሆን ተደርጓል፣ ዋናው ግባችን በዘላቂው ስለ ትርኢቱ ሰፊ መረዳት እንዲኖረንና ለወደፊቱ ከዚህ ሞኝነት እራሳችንንና ሃገራችንን የምንጠብቅበት ጥንቃቄና አስተዋይነት እንዲኖረን ማድረግ ነው፡፡ በቀጥተኛ አማርኛ በሚቀጥለው ዓመት ትርኢቱ በሃገራችን ለምልመላ ሲመጣ ፍቃድ ነስቶ ማባረርና ከአሁኑ ሰዓት ጀምሮ ደግሞ ትርኢቱ በሐገራችን ማሰራጨትን መከልከል ለማለት ነው፡፡
መታወቅ ያለበት ይህ የቤቲ ብቻ ጥፋት ሳይሆን ክብር እንዳለው መስሎ በከፍተኛ ወጪ አሸብርቆ የሚመጣው ክብረ ቢስ ትርኢት ውጤት ነው፡፡ ለቤቲም ቢሆን መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማት ከመመኘት ውጪ ምንም በክፋት እንድትታይ አልመክርም፣ ሰለባ ነች እንጂ አጥቂ አይደለችም፣ ሴትየዋ ብትገነዘበውም ባትገነዘበውም፡፡

የወንድም ጋሼ መጥፎ ገጽታ

አሁን ታሪኩን ለማስተዋወቅ ከ560 ቃላት በላይ ከተጠቀምን በኋላ ወደ ዋናው ጉዳያችን እንገባለን፡፡ በግሉ የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ ስራዬ ብሎ ወንድም ጋሼ ትርኢትን ተከታትሎ ስለማያውቅ ማንኛውም ተራ ታዛቢ ሊያስቀምጥ የሚችለውን ወጣ ያለ የትርኢቱን ልማዶች መጥቀስ አይችልም፣ መጥቀስም አያስፈልግም፡፡ እንደ በግ ለአንድ ሳምንት ሁኑ የሚሉት ትእዛዝ ምን ይሉታል? ምን ለማስተላለፍ ተፈልጎ ነው? መጥፎ ገጽታውን ለማሳየት በቅድሚያ የፖሮፖጋንዳ ስልትንና ዓላማን በመዳሰስ የወንድም ጋሼ ትርኢት ፕሮፖጋንዳንና አወዛጋቢ ገጠመኞችን እናያለን፡፡

                1.  ፕሮፖጋንዳ እና ማሕበረሰብ ቀረጻ

ሚድያ በሕዝብ ግንኙነት፣ ፕሮፖጋንዳ እና የአእምሮ ውጊያ ወይም የስነልቦና ውጊያ ላይ ጥናት ያደረጉ የደህንነት ሰዎች በአንድ ህዝብ ላይ ያለውን ተጽእኖ አሳምረው ያውቁታል፡፡ በህዝብ ገዢዎች ደረጃ ይቅርና በማስታወቅያ እንኳን እንዴት ተመልካቹን መስለብ እንደሚቻል በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፣ ለማወቅ ከፈለጉ የሚተዋወቁትን ሸቀጦች መሸመት የሕይወት ግባቸው ያደረጉትን ማየት ያስረዳዎታል፡፡ ይህ የሆነው ተመልካቹ ሞኝ ስለሆነ ሳይሆን ማስታወቅያው በስነ ልቦና ሳይንስ መርሆ ተሞርክዞ ልቦና እንዲሰርቅ ተደርጎ ስለሚሰራ ነው፡፡ እኚህ ዘዴዎችን አሁን መመልከት አንችልም፣ አያስፈልገንምም፡፡
የፕሮፖጋንዳ አስፈላጊነት እየጨመረ የመጣውና ሕብረተሰብን በሚፈለገው አቅጣጫ መቀየስ ከጉልበት ይልቅ በማሳመን መተግበሩ ከስነ ልቦና እድገት ጋር በሃያኛው ክ/ዘመን መባቻ ነበር፡፡ የህዝብ ግኝኙነት አባት የሚባለውና የታዋቂው ስነ ልቡና ሙያተኛ ሲግመንድ ፍሮይድ እህት የሆነችው አና ልጅ የሆነው ኤድዋርድ በርኔይስ መሰረታዊ መርሆቹ የሕብረተሰብን ያህል እድሜ ያስቆጠሩ እንደሆኑ ይነግረንና ዋና ነጥቦቹም፡
ህዝብ ማሳወቅ፣ ህዝብ ማሳመን፣ ወይም ህዝቦችን ከህዝቦች ጋር ማዋሃድ ናቸው፡፡ እናም ይህን ማድረጊያው መሳርያዎችና ዘዴዎች ህብረተሰብ በተቀየረ ቁጥር እንደሚቀየሩ ልብ ይሏል ይላል፡፡ (Crystallizing Public Opinion, 1923)
ከዚህ ጋር በተያያዘ በሌላ መጽሐፉ ስለ አንድ ሐሳብን ወይም ምልከታን ማስፋፋት የሚከተለውን ይላል፡
“ይህ በግዙፉ የሚመረትበት ዘመን ነው፡፡ ቁሶች ደግሞ በግዙፉ ሲመረቱ ከእዚህ ጋር አብሮ የሚሄድ የማሰራጨት ሰፊ ዘዴ ተፈጥሮ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዚህ ዘመንም ሐሳቦችን በሰፊው የሚሰራጩበት ዘዴ ሊኖር ይገባዋል፡፡”(Manipulating Public Opinion, American Journal of Sociology 33 (May, 1928), p. 958–971.)
በ1920ዎቹ ሐሳብ በሰፊው የሚሰራጭበት ዘዴ ፍለጋ ሲጽፍ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ እጅግ ተቀይሯል፡፡ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ከለር ቴሌቪዥን፣ ሸክላ፣ ዲቪዲ፣ 3ዲ፣ ሳተላይት ቲቪ ተገኝተው ሐሳቦች በስፋትና አማላይ መንገድ የሚሰራጩበት ቴክኖሎጂ አግኝተዋል፣ ሆሊዉድ እና የሙዚቃ ኢንዱስትሪው በነዚህ ግኝቶች እጅግ ትርፋማ ሁነው ቁንጮ ተቆጣጣሪዎቻቸው መልእክት በማሰራጨት ተሰማርተዋል፡፡ የነዚህ የዜና ማሰራጫ ተብዬዎቹ እና የደህንነት ኤጀንሲዎች ትስስር ወይም የጥምረት ታሪክ ለመዳሰስ ሌላ ጽሁፍ ያስፈልጋል፣ የሚድያ ሰዎች ግን በደህንነቶች እንደሚሰለጥኑና ሚድያዎች የቁንጮዎች ወንጌል መስበክያ እንደሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡
የነዚህ መድረኮች ስኬት የሚለካው ከግለሰብ ድካም ሳይሆን ከመንጋ ስነ ልቡና አንጻር ነው፡፡ የህዝብ ግንኙነት አባቱ እንደሚከተለው ይላል፡
“አንዳንዴ የሚሊዮኖችን አመለካከት መቀየር ይቻላል፣ የአንድ ሰው አመለካከትን መቀየር ግን አይቻልም፡፡” (Quoted in L. Tye The Father of Spin (1998) p. 102)
ይህን ዘዴ “የዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ” ድብቅ ገዢዎች በጥንቃቄ ሲተገብሩት ኑረዋል፡፡ የህዝብ ግንኙነት አባት እንደሚከተለው ይላል፡
“በዲሞክራሲያዊ ሕብረተሰብ የብዙሃኑን ልማዶችና አመለካከቶች በታሰበበት እና ብልሃት በታከለበት መንገድ መጠምዘዝ  (ማኒፑሌሽን) ዋና አካሉ ነው፡፡ ይህ የማይታየውን የህብረተሰብ መዘውርን የሚቆጣጠሩ አካሎች የአገራችን [ዩ.ኤስ.ኤ.] ትክክለኛ ገዢ ኃይሎች የሆኑት የማይታየው መንግስት አካሎች ናቸው፡፡ የምንገዛው፣ አእምሯችን የሚቀረጸው፣ ምርጫችን የሚፈጠረው፣ የሐሳቦቻችን ፍንጭ የሚሰጠን፣ በአብዩ ሰምተናቸው በማናውቅ ሰዎች ነው፡፡ ይህ ዲሞክራሲያዊ ህብረተሰባችን የተደራጀበት መሰረተ-እውነታዊ (ሎጂካል) ፍጻሜው ነው፡፡ በአግባቡ የሚሰራ ማህበረሰብ ውስጥ አብረው መኖር ካለባቸው ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በዚህ መንገድ መተባበር (መከተል) ይኖርባቸዋል፡፡” (Propaganda (1928) Ig Publishing edition, 2004, p. 37.)
የሰጠውን የማይታዩት ገዢዎች ተግባር ምስክርነቱን ብንቀበልም ይህ የአደረጃጀቱ መሰተረተ-እውነታዊ መቋጫ ነው ብለን ግን አንቀበልም፣ ይህን ውጤት የፈጠረው ስርዓቱ ሳይሆን ተደብቀው ስርአቱ ላይ በሚያሴሩ ሰይጣናዊ ቁንጮ ቤተሰቦች መሆኑን እንረዳለንና፡፡ በማከልም ስለፕሮፖጋንዳ እንደሚከተው ይለናል፡
“ፕሮፖጋንዳ የማይታየው መንግስት ስራ አስፈጻሚ ክንዱ ነው፡፡” (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 48፡፡)
እናም በዚህ መሰረት እንደሚከተለው ይደመድማል፡
“የመንጋው ጭንቅላት አሰራርና መነቃቅያን መረዳት ከቻልን፣ አሁን ብዙሃኑን እነርሱ ሳያውቁት በእኛ ፈቃድ መሰረት መቆጣጠርና ማደራጀት እንችላለን ማለት ነው፡፡” (ዝኒ ከማሁ፣ 1928 እትም፣ ገጽ 71፡፡)

                2.   ጋጠወጥነት ከወንድም ጋሼ

እናም አሁን ወደ ወንድም ጋሼ ትርኢት ጉዳያችን ስንመለስ ደግሞ ከዚህ በፊት የኤም ቲቪ ምርኮዎች በሚለው ስለ ጣብያው ተጽእኖ በቃልኪዳን ይበልጣል ጸሐፊነት ከታዛቢ እይታ አንጻር እንደተዳሰሰው፣ በታዳጊ ተማሪዎቹ ሰፊ የባህል ወረራ እያደረሰ እንዳለ አይተን ነበር፡፡ ይህም ወንድም ጋሼ ትርኢት የየሀገራቱ ስም በማስጠራት ሽፋን የሕዝቡን ቀልብ በመያዝ ዓለሙን እንዲረሱ ተደርገው በሚቀመጡበት ስፍራ 24 ሰዓት በካሜራ ቁጥጥር ስር የሆኑ ተፎካካሪዎች የሚሰሩት ወጣ ያለ ስራ፣ ከሚታዘዙት ወጣ ያለ ትእዛዝ ጋር እና ይበልጥ ወጣ ያለ ከፍ ያለ የማለፍ እድል እያገኘ፣ አፉን ከፍቶ እንግዳ ትርኢቱን የሚቀለበው ተመልካች ላይ ያለውን ተጽእኖ ያዩት ይፈርዱታል፡፡
ትርኢቱ እጅግ ጋጠወጥ ሲሆን በተለያየ ዘመን ባቀረባቸው ትርኢቶች የተለያዩ ለፕሮግራሙ በከፍተኛ ወጪ ማስተዋወቅያ እንደሚነገርለት ሳይሆን ክብረ ነክ የሆኑ ድርጊቶች፣ እራቁት መታየት፣ ስካር፣ ወንዶችና ሴቶች እራቁታቸውን ፍል ውሃ ውስጥ ተዘፍዝፎ መታየትና አብሮ መታጠብ ወዘተ. የተለመዱት ናቸው፡፡ ይህ እንዲሁ ሁኖ የአገራችን ኤፍ ኤም ሬድዮ ፕሮግራሞች በሚከፈላቸው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ስለ ፕሮግራሙ ጥሩ ማውራት እንጀራቸው ነው፡፡ አክብረን አንብበን ወዳጆቻችንም እንዲያነቡ የምንመክራቸው የህትመት ውጤቶችም ስለዚህ ክብረ ቢስ ፕሮግራም በተከበረው ወረቀቶቻቸው ላይ ውደሳ ያጎርፉለታል፡፡ ከዚህ በፊት ባለማወቅ ከሆነ እንዲህ የተደረገው ለቀጣይ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ደረጃ እንዲታገድ አበርትተው እንዲታገሉ እንጠይቃለን፣ እንዲህ ካልሆነ ግን በአንባቢው ዘንድ ክብርን እንዳይጠብቁ እንንገራቸው፡፡ ክብረ ቢስ ድርጊቶች በሚከበሩ ሚድያዎች መገኘት የለባቸውምና፡፡ ሁሉም የየራሱ ቦታ አለው፡፡ የዚህ ትርኢት አደጋም አለክብሩና አለቦታው መቀመጥ መቻሉ ነው፡፡
እንዲህ የመሰሉ የእውነተኛ ክስተቶች ትርኢት ወይም ሪያሊቲ ሾው ግማሽ  ክ/ዘመን በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ሲሆን ከሁሉ አነጋጋሪው ይህ ዓለም አቀፋዊው ወንድም ጋሼ  የተሰኘው ሪያሊቲ ሾው ነው፡፡ ሪያሊቲ ሾው ለፕሮፖጋንዳ የተመቸ ነው፣ ማሸነፍ ከፈለጉ የትርኢቱ መሪ ፍልስፍናዎችን ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋልና ተወዳዳሪዎቹ ለዚህ ሲሉ የማይሆኑት ነገር የለም፡፡ ከዝር ባጭሩ የፕሮግራሙ ቅሌቶችን እንፈትሻለን፡-
አፍሪካ፣ 2003
ወንድም ጋሼ በአፍሪካ በመጀመርያ ዘመኑ ነበር ውዝግብ ያስነሳው የዩጋንዳው ካግዋ እና የደቡብ አፍሪካዋ ፕሌትጀት በቀጥታ ስርጭቱ ወሲብ እያደረጉ ያለ የሚመስል ነገር ታይቶ ነበር፣ በወቅቱ ፕሮግራሙ ይህን ሲያሳይ በማላዊ እንዲቋረጥ ተደርጎ ነበር፡፡ (So, Why watch Big Brother? The East African)
ብራዚል [2012?]
ሞኒክ የተባለች ተፎካካሪ ሰክራ እራሷን ስታ አልጋዋ ውስጥ ተኝታ እያለ ያለ ፈቃዷ ሌላው ዳኒኤል የተባለ ተፎካካሪ አልጋው ውስጥ ገብቶ ወሲብ ፈጽሟል ያለ ፈቃዴ ነው በማለቷ፣ ክብረ ንጽህናዋን (ፉክክሩ ውስጥ ሲገቡ ክብር የሚባል ነገር የለምና ሌላ ቃል ከመጠቀም ተብሎ ነው) ተዳፍሯል ተብሎ ወድያው ከውድድሩ ተባሯል፡፡  Big Brother in Brazil rocked by allegation of drunken rape
ዩ.ኤስ. አሜሪካ፣ 2001
ጀስቲን ሴቢክ የተባለው ተወዳዳሪ ሌላ ተወዳዳሪን ጩቤ በመያዝ የግድያ ዛቻ አድርሶባታል፡፡ ክሪሳት ስቴጋል የተሰኘችውን ተወዳዳሪ ቢላ አንገቷ ስር ይዞ ሲያስፈራራት እየሳመ ነበር፡፡ ይህም ከትርኢቱ እንዲባረር ተደርጓል፡፡
አፍሪካ፣ 2008
ታዋና ሌባኒ የተባለች ተፎካካሪ ተገቢ ያልሆነ ወሲባዊ ድርጊት በቲቪ እየታየች ፈጽማለች፡፡ ታኮንዳዋ ንኮንጄራ የተባለ ተፎካካሪን ብልት በአፏ ስትነካካ ነበር፡፡ ይህቹ ሴት ሌላ ተፎካካሪ ሴት ከሁለት ወንዶች ጋር በውድድሩ ወቅት በመተኛቷ “ሰይጣን” ብላ ያወገዘቻት ስትሆን ተመልሳ እራሷ ሙንያራድዚ ቺድዞንጋ እና ሪካርዶ ቬናንቾ ከተባሉ ወንዶች ጋር በአንድ ግዜወሲብ ፈጽማለች፡፡ ቀጥላም ከውድድሩ ተሸንፋ ስትወጣ በትርኢቱ ለመጨረሻ ግዜ ያደረገችው የሃገሯን ቦትስዋና ባንዲራ ለብሳ “ብልት እወዳለው፡፡” “I love dick” ብላ ማወጇ ነበር፡፡ Big Brother, bad behaviour: reality show’s darkest days
አውስትራሊያ፣ 2005
ማይክል ብሪክ እና ማይክል ኮክስ የተባሉ ተወዳዳሪዎች በፈጸሙት ወሲባዊ ጥቃት ከትርኢቱ እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡ ብሪክ የተባለው ካሚላ ስቭሪ የተባለች ተወዳዳሪን በጉልበት ከያዛት በኋላ ኮክስ የተባለው ተወዳዳሪ ብልቱን ፊቷ ላይ አድርጓል፡፡ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆን ሃዋርድ የትርኢቱ አስተላላፊ የነበረው ቻነል 10 ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ይህ ጅላንፎ ትርኢትን ከአየር ላይ እንዲያግድ ጥሪ አቅርቦላት ነበር፣ ትርኢቱ እስከዛሬ ቀጥሏል፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
ብሪታንያ፣ 2005
ኪንጋ ካሮልክዛክ ወጣ ባለ ጋጠወጥ ባህሪዋ (በዋሾነት፣ ሰከራምነትና እራቁት በመሆን) በትርኢቱ ስም ካኖረች በኋላ በፉክክሩ ግማሽ አከባቢ እጅግ ወጣ ያለ ድርጊት ፈጸመች፡፡ እንደልማዷ ሰክራ በቤቱ አጸድ እግሯን በልቅጣ ተንጋላ ከተኛች በኋላ ባዶ የወይን ጠርሙዝ ተጠቅማ እራሷን ለማስደሰት ወሰነች፡፡ ኮሮልክዛክ በኋላ ላይ ለደይሊ ሚረር እንዲህ ያደረገችው የትርኢቱ ባለቤቶች መደለያና ከትርኢቱ ትባረርያለሽ በሚል ዛቻ ተጠቅመው አስገድደዋት ያደረገችው እንደሆነ ተናግራለች፡፡ (ዝኒ ከማሁ)
አፍሪካ፣ 2007
ቅጥ ያጣ አልኮሆል ከወሰዱ በኋላ ሪቻርድ ቤዙዴንሃውት እራሷን ስታ የተኛች ከምትመስለው ኦፉኔካ ሞሎክዉ አጠገብ በመተኛት በእጆቹ ብልቷን ነካክቷል፡፡ ሌላ ሴት የሚሰራውን እንዲያቆም እየጮኸች ከተናገረች በኋላ ነበር ያቆመው፣ ይህ አሰቃቂ ድርጊት በቲቪ በቀጥታ እየተሰራጨ የነበር ሲሆን እዚህ ነጥብ ላይ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ወድያው የህክምና እርዳታ አድራጊዎች የደረሱላት ሲሆን እንዲህም ሁኖ አስገድዶ መድፈር መሆኑ ተረጋግጦ እያለ ትርኢቱ ኤምኔት በተባለው የዲኤስቲቪ ጣብያ አማካኝነት በፈቃድ የተደረገ ነው በሚል እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ መጨረሻ ላይ ደፋሪው አንደኛ ተደፋሪዋ ሁለተኛ ወጥተው ፉክክሩ አልቋል፡፡ (ዝኒ ከማሁ፣ Big Brother’s South African rape horror show)
አሁን ደግሞ በ2013 ከኢትዮጵያ የወሰዷት ቤቲ የተባለች ተፎካካሪ ወሲብ ስትፈጽም ታይቷል፡፡ በአፍሪካ ጋጠወጥ ተግባራት በዲኤስቲቪው ኤምኔት ሲፈጸም ሃይ ባይ ያጣ ይመስላል የተወሰኑ ሃገሮች እንደ ማላዊ ያሉና በናይጄርያ ኤንቢሲ ቴሌቪዥን ጣብያ እንዳይተላለፍ እገዳ ጥለውበት ነበር፡፡ የቤቲ ጉዳይም ጊዜ የሚፈታው ይሆናል፡፡ ተታላ ነው ተገድዳ ወይስ በምርጫዋ?
መጥፎ ተግባር የሚፈጽሙት ማሸነፋቸው ለአፍሪካ ወጣቶች ምን ዓይነት ትምህርት ነው የሚሰጠው፡፡ የ2007ቱ ደፋሪ ባለትዳር ሲሆን ይህን ያደረገው ሚስቱ በቲቪ መስኮት እያየች ነበር፡፡ የሴቶች መብት ተከራካሪዎች እና እንስታውያንስ ስለዚህ የሴቶችን ክብር የሚነካ ጉዳይ ምን ይላሉ? ይደግፉት ይሆን?
ይህ ሁሉ የሚደረገው እንደብሪታንያዋ ኪንጋ ካሮልክዛክ የደይሊ ሚረር ኑዛዜዋ በስልታዊ መንገድ እንዲፈጽሙት ተገደው የሚደረጉበት እውነታ ነው ያለው፡፡ ይህ የሚደረገው የዋሁ ለመዝናናት የሚያፈጠውን ማህበረሰብ ሳይታወቀው አመለካከቱን ለመቀየር ነው፡፡ የሚገርመው በአፍሪካ በትርኢቱ ጋጠ ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ እርምጃ የማይወሰድባቸው መሆኑ ነው፡፡ ማህበራዊ ምህድስናው፣ ህብረተሰቡ ምን እንዲቀበል ነው ይህ ፕሮግራም በአህጉር ደረጃ የሚሰራቸው?

                3.   የወንድም ጋሼ ፕሮፖጋንዳ ፋይዳ

የሚገርመው ፕሮግራሙን የሚያሞካሹ ፓን-አፍሪካውያን መገኘታቸው፡፡ So, Why watch Big Brother? The East African የተሰኘው ጽሑፍ የሚከተለውን ይላል፡
“የሆነ ሁኖ መልካም የሚባል ነጻነት ነው፡፡ አፍሪካን ስታዲስ ሪቪው የተሰኘው ጆርናል ዝነኛ ባሕል እና ሕዝባዊ መድረክ በአፍሪካ፡ የባሕል ወለድ ዜግነት እድል (Popular Culture and Public Space in Africa: The Possibilities of Cultural Citizenship) በተሰኘ ርእስ ስር እንደጻፈው ቢቢኤን (ወንድም ጋሼ አፍሪካን) እንደ አብዮት ነበር የቆጠረው፣ እንደሚከተለው በማለት “ከዚህ በፊት የአፍሪካ ቁንጮዎች ስለ ፓን-አፍሪካዊነት የሚያወሩበት ብዙ አጋጣሚዎች ተፈጥረውላቸው ነበር፡ በተባበሩት መንግስታትና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ እና ሃገር የማይገድባቸው ድርጅቶች አማካኝነት፣ በከባቢያዊ የአፍሪካ ድርጅቶች እንደ ኔፓድ እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ በቀድሞ ቀኝ ገዢዎች መዲና ለንደንና ፓሪስ፣ እና በብሪታንያ፣ አሜሪካና ካናዳ ዩኒቨርስቲዎች፡፡”
“… አሁን ሁላችንም ማህበራዊ ሳይንቲስቶች ሁነናል፡፡ የብሪታንያው ከጎልድስሚዝ ዩኒቨርሲቲ፣ ለንደን የስነ ማህበረሰብ (ሶሽዮሎጂ) ፕሮፌሰሩ ቤቨርሊ ስኬግስ [የትርኢቱን] ቅርጽ የማህበረሰቡ የኃይል አወቃቀር ከማህበራዊ ለውጥ ጋር እንዲለወጥ የሚያደርግ፣ የሰዎች፣ ስብእናቸው እና ተግባሮቻቸው በጥሩ እና መጥፎ ምድቦች የሚከፋፈሉበት የግምገማ መንገድ ነው ይሉታል፡፡
“ይህ የተሰነጣጠቀ እውነታ ክስተት (ሪያሊቲ) ነው፣ አማራጭ እውነታ ነው፣ የታነጸ /የተቀረጸ እውነታ ነው፡፡ በእውነትም የባህል ዳግም ግንባታ የሚከናወንበት ስፍራ ነው፣ ይህም ሰፊ የስነ ምግባር ክርክሮች ያስነሳ ሲሆን … ተፎካካሪዎች ህግ ተሰቷቸው ህገፎቹን በማውጣት ምንም ተሳትፎ የሌላቸው ተፎካካሪዎች በህጎቹ መሰረት ይቀጣሉ አልያም ይሸለማሉ፡፡”
አንድ አፍሪካዊ ባህል መፍጠርያ መድረግ አድርገውላችኋል እንግዲህ፡፡ ምን ዓይነት ባህል ነው? ነጮቹ ዛሬ ቤተ ክርስትያኖቻቸውን ጭፈራ ቤትና ሰይጣን ማምለክያ አድርገዋቸዋል፡፡ እንዲህ የሆኑት የዘመናት የስነ ምግባር ውጊያ ከተደረገባቸው በኋላ ነው፡፡ አሁን ደግሞ አፍሪካውያን በተራቸው እንዲጣፋባቸው እየሰሩ ነው፡፡

መደምደምያ

ተወዳዳሪዎቹ መቼም ገና ሲገቡ ህጎቹ እንደሚነገራቸው እና ከዚህ ቀደም የተደረጉት ፕሮግራሞችንም ስለሚያውቁ የሚጠበቅባቸውን ያውቃሉ የሚል ግምት ይወሰዳል፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ቤቲ ወሲብ ስትፈጽም እንደምትተላለፍ አሳምራ እንደምታውቅ ጥያቄ የለውም፡፡ ነብይ ሆንክ አትበሉኝና እሷና ያስተናገደችው ሴራሊዮናዊ ተወዳዳሪ ደግሞ ከነሱ የባሰ ጋጠ ወጥ ነገር አድረገው የሚበልጧቸው ካልመጡ የማሸነፍ እድላቸው ሰፊ ነው፡፡
አሁንም በድጋሚ ይህ ጋጠ ወጥ የቲቪ ፕሮግራም በሃገራችን እንዳይገባ ያገባናል የሚሉ ሰዎች እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እንማጸናለን፡፡
በተረፈ ይህ ጽሑፍ የተጻፈው በወግ አጥባቂ ነው፣ እውነታውን አያሳይም የሚል ካለ እጅጉኑ ተሳስቷል፡፡ ከቀረበው መረጃ አንጻር የትኛውም ሰው ቢሆን ሰብአዊ ክብሩን መንፈሳዊ ሰላሙንና ነጻነቱን የሚወድ ከሆነ ከዚህ ስልታዊ ማህበራዊ ምህንድስና እራሱንና የሚቆረቆርለትን ሊጠብቅ ይገባል፡፡
ስለዚህም መፍትሄው ምንድን ነው? ከማሳገድ ውጪ መረጃን በመረጃ መታገል ነው፣ የሕዝብ ግንኙነት አባት የተባለው ኤድዋርድ በርኔይስ የሚከተለውን ይላል፡
የፕሮፖጋንዳ ምርጡ መመከቻው፣ ተጨማሪ ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ (Quoted in L. Tye The Father of Spin(1998) p. 102)
ስለዚህም ይህን ጽሑፍ ከማሰራጨት ጀምሮ ወንድም ጋሼ በኢትዮጵያ ምድር ድርሽ እንዳይል በየመጽሄቱና ጋዜጣው በመወትወትና ሕዝቡን በማንቃት የብእር ትግል ሊደረግ ይገባል፡፡

የምስል ማስረጃ

ትርኢቱ ተፎካካሪዎቹ ያልተቆራረጠ በሚል በድረ ገጽ እርቃናቸውን ሁነው የሚያደርጉትን ሁሉ ይለቃል፡፡ እነዚህን ምስሎች ማሳየት አያስፈልግም ሆኖም ግን ተጠራጣሪ ይኖር እንደሆን ፕሮግራሙ እንደሚታሰበው ሳይሆን ጋጠ ወጥ መሆኑን እንዲመለከት የሚከተሉት ስእሎች ተጨምረዋል፡፡
Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 11, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.