የቡድን መሪው አቶ ብርሃኑ ከበደ መልቀቂያ አስገቡ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን መሰለፍ የማይገባውን ተጫዋች በማስገባቱ፤ ከቦትስዋና ጋር ያደረገው ጨዋታ ተሰርዞ ውጤቱ ለተቃራኒው ወገን እንዲሰጥ መደረጉ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ጥፋቱን በቡድን መሪው እና በጽህፈት ቤቱ ላይ በማድረግ የጽህፈት ቤቱን ሃላፊ ሲያባርር፤ የቡድን መሪው አቶ ብርሃኑ ከበደ ያደረጉትን የመልቀቂያ ደብዳቤ ደግሞ ተቀብሎታል። የስፖርት ፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ አባላቱን ባነጋገረበት ወቅትም፤ አቶ ብርሃኑ ከበደ ልብ የሚነካ ንግግር አድርገው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቀዋል። በወቅቱ ንግግራቸው፤ “የኔ ክብር ከኢትዮጵያ ክብር ስለማይበልጥ፤ ከቡድን መሪ ሃላፊነቴ ለቅቄያለሁ” ብለዋል።

ሆኖም ግን ሌሎች የጠቅላላ ጉባዔ አባላት፤ በተደጋጋሚ “ችግሩ የነዚህ ሰዎች ብቻ አይደለም። የስፖርት ፌዴሬሽኑም ቢሆን ራሱን ማጥራት አለበት” ብለዋል። ብዙዎቹም የቡድን መሪው የአቶ ብርሃኑ ከበደን መልካም ስራ እና ቀደም ሲል ያደረጉትን አስተዋጽኦ በመግለጽ መልቀቂያን ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸውን ተናግረዋል። “ችግሩ እናንተንም ይመለከታል። እናንተ አሁን ችግሩን ለመፍታት የምትሞክሩት፤ የጽህፈት ቤት ሰራተኛ እና መልቀቂያ ያስገባ ሰው በማባረር ነው። እራሳችሁንስ ገምግማችኋል ወይ?” በማለት የፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ አባላትን ጠይቀዋል።

የስፖርት ፌዴሬሽኑ “አጥፍተናል” ቢልም፤ ጥፋቱን ግን በራሱ ሰራተኞች ላይ በማላከክ፤ ስራ አስፈጻሚው እራሱን ንጹህ ለማድረግ  ያደረገው ጥረት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም። ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ቡድን አዲስ የቡድን መሪ ይኖረዋል ማለት ነው።

በመጪው ሴፕቴምበር 7፣ 2013ም ኢትዮጵያ እና ሴንትራል አፍሪካ ይጫወታሉ። ሴንትራል አፍሪካ ብታሸንፍም ሆነ ብትሸነፍ የማለፍ ምንም እድል የላትም። በሌላ በኩል ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ወይም ቦትስዋና አሸንፈው፤ ኢትዮጵያ ከተሸነፈች ከውድድሩ ውጪ ትሆናለች ማለት ነው። ፊፋ በሰጠው ውሳኔ መሰረት ቀደም ሲል ከሰበሰበው 13 ነጥብ 3 ነጥብ ባይቀነስ ኖሮ፤ ቀጣዩን ጨዋታ ሳይጫወት ጭምር የማለፍ እድል ነበረው። አሁንም ቢሆን ከምድቡ በአንደኝነት ደረጃ እየመራ ነው። በምድቡ ካሉት ሌሎች ቡድኖች የተሻለ እድል ያለው የኢትዮጵያ ቡድን ሲሆን፤ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፤ እኩል ለእኩል ቢወጣም ከአስሩ ውስጥ ይገባል።

ለማንኛውም ከሁለት ወር በኋላ ለሚደረገው ወሳኝ ጨዋታ ለቡድኑ መልካም እድል በመመኘት በዚሁ እንለያለን።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on June 24, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.