የሾላ ፍሬ ሲናድ…ሲናድ…

Muluneh Eyoelሙሉነህ ኢዮኤል – ከዋሽንግተን ዲሲ

የታሪኩ ዳራ
አባቴ የሚያህሉና እንደሱም የማከብራቸው ሰው የአቶ አንዳርጋቸውን አባት የአቶ ጽጌ ሀብተ ማርያምን መታሰር ሰምተው ስልክ ደውለውልኝ ነበር። እኝህ ሰው የአንድ ወቅት የአቶ ጽጌ ተማሪ ነበሩ። አቶ ጽጌ የደብረብርሃን አጼ ዘርአ ያዕቆብ ት/ቤት ዳይሬክተርም መምህርም በነበሩበት ወቀት እሳቸው ተማሪ ነበሩ። ጊዜዉ ከሃምሳ ዓመታት ይበልጣል፡፡

ዛሬ አቶ ጽጌ በሰማንያ አመታቸው ‹‹የግንቦት ሰባት አባል በመሆን መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሲያቅዱ ከፍተኛ ክትትል ሳደርግ ቆይቼ በቁጥጥር ስር አውያቸዋለሁ›› በማለት መለስ ካሰራቸዉ ሰላሳ አምስት ሰዎች አንዱ መሆናቸው ከንክኗቸው ነበር እኔ ዘንድ ስልክ የደወሉልኝ።

አቶ ጽጌ ሀብተ ማርያም ከዛሬ ሰላሳ አመት በፊት አረመኔው ደርግ በጭካኔ ልጃቸውን አምሃን ገድሎባቸው አስክሬኑን ከብዙ የሬሳ ክምር መሃል እንዲፈልጉ አድርገዋቸው፣ እጆቹ ከትከሻው ተሰባብረው፣ ሮጦ ያልጠገበውን የልጅ ልቡን ያፈነዳውን የጥይት ወጭ 100 ብር አስከፍለው ሬሳውን እንዲወስዱ ፈቅደውላቸው፣ ተመልሰው ደግሞ ከመንግስት እሬሳው እንዳይለቀቅ መመሪያ ደርሶናል ብለው፣ ሳጥን ውስጥ ከገባ በኋላ አስከሬኑን ቀምተው የወሰዱባቸው፣ የልጃቸውን አስክሬን በአግባቡ ለመቅበር እንኳ ያልታደሉ፣ የልጃቸው ሬሳ የወደቀበትን ማወቅ አለመቻላቸው ልባቸውን እንዳስመረረ የኖሩ ልባቸው በሀዘን የተሰበረ የሰማንያ አመት አዛውንት ናቸው፡፡ እኝህ ሰው ብዙ መከራ በህይወታቸው የተፈራረቀባቸው አንዲት ባንዳ ካገባች ልጃቸው በቀር ከሞት የተረፉ ልጆቻቸው በሞላ በስደት በመበታናቸው ወልዶ በልጅ መጦርና መጠየቅ እንዳማራቸው ያን እድል ሳያገኙት የኖሩ፣ ዘመናቸው ሁሉ የሰቆቃ የሆነባቸው፣ በህይወታቸው ከተፈራረቀው መከራ ብዛት ልባቸውን የታመሙ፣ የልብ ህመምተኛ ናቸው።

ብካይ የባንዳ ልጆች ዛሬ አቶ ጽጌን የመንግስት ግልበጣ ተሳታፊ ብለዋቸው ማዕከላዊ ናቸው። አኚህን የቀድሞ ዳይሬክተራቸውና የዛሬዉ የሰማንያ አመት አዛውንት የመንግስት ግልበጣ ዜና ሰምተው ነው እንግዲህ አንድ የማከብራቸው ሰው ስልክ ደውለው ነካክተውኝ ይህን ጽሁፍ እንድጽፍ ምክንያት የሆኑት።

እንዲህ አይነት ጉድ አዲስ አይደለም ታዲያ ምን ይደንቃል?

ጀርባቸውን ሰርጀሪ ያደረጉ ከሳሎን ወደ መኝታ ቤታቸው ከቤታቸው ወደ መኪናቸው በከዘራ ተደግፈው የሚሄዱ ከእርጅና የተነሳ የአይናቸው ብርሃን እየቀነሰባቸው የመጡ አቶ ነጋ ቦንገርም በስልክ ግንኙነት ሳያደርጉ አይቀሩም በሚል የቁም እስረኛ ሆነዋል። ወ/ሮ አበበች ወልደጊዮርጊስም ለወንድማቸውን አርባ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ጸሎተ ፍትሃት ለማድረግ አልታደሉም። ከልጃቸው ጋር ስለ መፈንቅለ መንግስቱ የተነጋገሩት ነገር ቀፎው ውስጥ ይገኝ ይሆናል ተብሎ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው ተወስዶባቸዋል። በተለይ የአቶ ነጋም የወ/ሮ አበበችም ስልክ የተቀማው ከልጃቸው ጋር የሶሶስትዮሽ (three way) ስለ መፈንቅለ መንግስቱ ውይይት አድርገው ሊሆን ይችላል ተብሎ ይሆናል። በተለይ አሁን ይህን ሁሉ ሰቆቃ የሚፈጽምባቸው የደርግን ጭቆና ስትቃወም ያ አረመኔው ስርአት ከበላት ከውድ ልጃቸው ከአስካለ ነጋ ጋር በአንድ ክፍል ተማሪ የነበረው መለሰ ዜናዊ መሆኑ እጅግ ሳይቆጫቸው የሚቀር አይመስለኝም። ያች ውድ ልጃቸው የተቃወመችው ስርአት ከደርግ በከፋ ሌላ አፋኝና ዘረኛ አምባገነን መተካቱ፣ የልጃቸው ህይወት ጠፍቶ እርሱን የተካው ከፊተኛው የባሰ አምባገነን ከዚያኛው በተለየ ሁኔታ ደግሞ ዘረኛ መሆኑ እንዴት አያስቆጭ?

ሌላም አለ፦ ሃጂ መሃመድ ሙሳ፣

ታህሳስ አስር ቀን 1999 ዓ.ም ከአለም በቃኝ ተቀይሬ ወደ ቃሊቲ ዞን ሶስት ከመጣሁ በኋላ የሰማሁት ታሪክ ነው። አቶ መሃመድ ሙሳ ይባላሉ። እድሜያቸው ከሰባ አመት በላይ የሆኑ አዛውንት። ከሀረርጌ ከጭሮ አካባቢ የመጡ አርሶ አደር ናቸው። እኝህ ሰው እዚያው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ህክምና ተከልክለው ከሞቱ ገብዙ እስረኞች አንዱ ናቸው። ሌላ ድርጊት መፈጸም ሳያስፈልጋቸው አሮሞነታቸው ብቻ በቂ ወንጀል ሆኖባቸው በመለስና በበረከት ምክንያት ተፈልጎላቸው ከታሰሩ በሺዎች ከሚቆጠሩ እስረኞች መካከል አንዱ ነበሩ። እኔ እኝህን ሰው ለማየት አልታደልኩም። እኔ እሳቸው ወደነበሩበት ዞን ተቀይሬ ስመጣ ሞተው ነበርና። “ፌዴሬሽንን ለመገንጠል” መሞከር በመባል በሚታወቀው የኦሮሞዎች ክስ የታሰሩ ድንቅ አባት ነበሩ። ከእርሳቸው ጋር በተመሳሳይ ክስ ታስረው የነበሩ ሰዎች ስለ እሳቸው አውርተው አይጠግቡም። ከሜጫና ቱለማ ጋር በተያያዘ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከታሰሩ ተማሪዎች አንዱ ስለ እሳቸውና ስለ ክሳቸው ብዙ አጫውቶኛል። ከነገረኝ ታሪክ በአጭሩ እዚህ ላይ ላንሳ። ስለሃጂ ማሃመድ የነገረኝ ሰው እሳቸውን እዚያው ቃሊቲ ነው የተዋወቀው። ሃጂ መሃመድ ህክምና ተከልክለው በክብር የሚገንዝ ወገን በሌለበት እዚያው ቃሊቲ ህየወታቸው እስካለፈበት እለት ድረስ አንገታቸውን እንዳቀኑ፣ ሞራላቸው ሳይሰበር፣ ስለፍትህ ስለእኩልነት፣ ስለሰው ልጅ ክቡርነት እና አብሮ ስለመኖር አስፈላጊነት የሰሟቸውን ሁለ ታከተኝ ሳይሉ አስተምረዋል። ባይሰማቸውም ለዳኛውም ሳይቀር ነግረውታል። ወንጀላቸው አሮሞነታቸው እንደሆነ ሳይፈሩ ተናግረዋል። ኦሮሞ የሆኑት ደግሞ ፈልገው ሳይሆን ልክ ዳኛውም ሆነ ሌላው ሰው ማንነቱን ሆኖ እንዳገኘው በሚገርም ብስለት አስረድተዋል። በተለይ እኔና በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሰነበትን ስለእሳቸውና እሳቸውን ስለሚመስሉት ሌሎች ብዙ ሺዎች የመዘከር እዳ አለብን።

ስለ ክሳቸው ጥቂት ልበል። ሃጂ መሃመድ ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በመሄድ ላይ በነበረ ባቡር ላይ ፈንጂ አፈንድታችኋል ተብለው ከታሰሩ 48 ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው። አንድ ቦምብ ፈነዳ አሉ። ያፈነዱት ደግሞ አርባ ስምንት ሰዎች ናቸው አሉ። አስቡት አንድ ቦምብ ለአርባ ስምንት ሆነው ሲያፈነዱ። በእድሜ በአስራዎቹ የሚገኙ ልጆችና የሰባ አመት ሃጂ መሃመድ ሙሳ አንድ ላይ ሆነው አንድ ቦንብ አፈነዱ። በተለይ ”ፌዴሬሽንን መገንጠል” በሚባል ክስ የሚወነጀሉ ሰዎች ጨርሶ የማይተዋወቁ፣ አንዱ ከአምቦ ሌው ከሆሮ ሌላው ደግሞ ከሀረርጌ ሌሎቹ ደግሞ ከባሌ ሆነው ነው። ሃጂ መሃመድ በእስር ቤት ውስጥ ታመው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ህክምና እንዳያገኙ ስለከለከላቸው ፍርድ ቤት ውስጥ ለዳኛው እባካችሁ መሞቴ ነው ድረሱልኝ እያሉ ሲለምኑ ልዑል ገ/ማርያም ጥያቄያቸውን ሳይቀበልላቸው ለፍርድ ቤቱ ባመለከቱ በጥቂት ቀናት ህይወታቸው እዚያው ነበር ያለፈው። እኔ እስከነበርኩበት ቀን ድረስ በእነ ሃጂ መሃመድ ሙሳ መዝገብ ተከሰው ፍርድ ቤት ከሚመላለሱ ሰዎች ውስጥ ሶስቱ እዚያው ቃሊቲ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ ሰላሳ ስምንቱ ሰዎች ደግሞ ስምንት አመት ሙሉ በእስር ከማቀቁ በኋላ በነጻ ተሰናብተዋል። የቀሩት ሰባቱ ተከላከሉ ተብለው አንዱ ብቻ እከላከላለሁ ስላለ ፍርድ ቤት ይመላለሳል። ስድስቱ ግን ምን እንከላከላለን የፈለከውን ፍረድብን ስላሉ አንደኛው አስራ ስምንት አመት ሌሎቹ አስራ አምስት አመት ተፈርዶባቸዋል። ዛሬ ቃሊቲ ወይም ዝዋይ ይሆናሉ። አንዳንዶቹ ሞተውም ሊሆኑ ይችላሉ።

ሌላም አለ እንጂ፡ ጎንደሬው ልጅ ምትኩ

በተለይ ህገ መንግስቱን በሃይል ስለመናድ ሲነሳ አንድ ከግንቦት ምርጫ በኋላ ከጎንደር ተነስቶ አዲስ አበባ ቄራ ካለች እህቱ ዘንድ ሲመጣ ቄራ እንደደረሰ መንገድ ላይ ድንገት አጋዚዎች አግኝተውት የታሰረውን የአስራ አምስት አመት ልጅ የምትኩን ታሪክ ያስታውሰኛል። ምትኩ በዚያች ቀን እርሱ ከመጣበት ጉዳይ ጋር በምንም በማያገናኘው ሁኔታ በማያውቀው ጉዳይ “ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ ሞክረሃል” ተብሎ ልክ እንደ እርሱ ለምን እንደታሰሩ ከማያውቃቸው በእድሜ እርሱን የሚያካክሉ የልጅ ልጆች ካደረሱ ሰዎች ጋር የታሰረ የአስራ አምስት አመት ልጅ ነው።

ምትኩ አመጣጡ ከጎንደር ይሁን እንጂ የገጠር ልጅ ነው። ምትኩ ፊደልም የቆጠረ አልነበረም። ከጎንደር እህቱን ፍለጋ አዲስ አበባ ቢመጣም መድረሻው የእህቱ ቤት አልነበረም። መጀመሪያ አለም በቃኝ፣ በነጋታው ዴዴሳ፣ ከዚያ ዝዋይ፣ ከስምንት ወራት በሗላ ደግሞ ተመልሶ አለም በቃኝ ከዚያም አለም በቃኝ ሲፈርስ ቃሊቲ ቤቱ ሆነ። ምትኩ ከአለም በቃኝ እስር ቤት ወደ ፍርድ ቤት ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ ሞክረሃል ተብሎ ይመላለሳል። ወንጀሉ ሲዘረዘር ደግሞ ድንጋይ በመወርወር፣ አውቶብስ በማቃጠል…ወዘተ ይላል። ከየትኛውም ስለሌለበት የሚሉት ገብቶት አያውቅም። ሁል ጊዜ እስረኞች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ችሎቱ ከተሰየመ በኋላ ክሳቸው ተነቦ ተከሳሾች የእያንዳንዳቸው ስም እየተጠራ በእለቱ መገኘታቸው ስለሚጣራ ፍርድ ቤት በቀረበ ቁጥር ህገ መንግስቱን ለመናድ፣ ድንጋይ በመወርወር አውቶብስ በማቃጠል…ወዘተ መባሉ ይከነክነዋል።

አንድ ቀን አላስችል ብሎት ተከሳሾች መልስ እንዲሰጡ ሲጠየቁ እሱም እጅ አወጣ። እጅ ያወጣው የቀረበበትን ክስ ለመከላከል ሳይሆን በውስጡ የሚከነክነውን ጥያቄ ለመጠየቅ ነው። ክሳቸውን የሚያየው ችሎት መሃል ዳኛ አሰፋ አብርሃ ይባላል። እንዲናገር እድል ሲሰጠው ቆመ። ሰው ሁሉ ከመናገሩ በፊት ክቡር ፍርድ ቤት እያለ እንደሚጀምር በእነዚህ ፍርድ ቤት በተመላለሰባቸው ጊዜያት ተምሯል። እርሱም እድሉ ሲሰጠው እንደሌሎቹ ክቡር ፍርድ ቤት ለማለት ፈልጎ ክቡር ፍርድ ቤት የምትለዋ ሀረግ ጠፋችበት። ፍርድ ቤቱን ለማክበር አንድ ነገር እንደሚባል ስለገባው ብቻ “ጋሼ ፍርድ” ቤት ብሎ ጀመረ። “ጋሼ ፍርድ ቤት ህገ መንግስቱ የሾላ ፍሬ ነው እንዴ በድንጋይ የሚናደው ሲል” ይጠይቃል። የልጁን ጥያቄ የሰማ ሁሉ በሳቅ ነበር የፈነዳው – ከመሃል ዳኛው አሰፋ አብረሃ በቀር። ‹‹ህገ መንግሰት›› የሚባል መንግስት ከሚህል አስፈሪ ነገር ጋር የተቆራኘ ነገር የሾላ ፍሬ ይመስል በድንጋይ (ያውም እንኳን እርሱ ሊወረውር ቀርቶ ሲወረወር ያላየው ድንጋይ) ናድከዉ ተብሎ ሲከሰስ ታድያ ምን ይበል? ያ ልጅ ዛሬ ይፈታ እዚያው ቃሊቲ ይሁን አላውቅም።

ምን ይደንቃል? ምንስ ቢሉ ምን ይገርማል?

ታዲያ ዛሬ አቶ ጽጌ በመንግስት ግልበጣ ተጠርጥረው ታሰሩ ቢባል ምን ይደንቃል? አቶ ነጋም ሆኑ ወ/ሮ አበበች የቁም እስረኛ ቢሆኑ ማን ነው የሚገርመው? ጀኔራል ተፈራ ማሞ፣ አቶ መላኩ ተፈራ፣ ሃጂ መሃመድ ሙሳም፣ ጎንደሬው ልጅ ምትኩ፣ በቃሊቲ ሲኦል በዴዴሳ ጫካዎች፣ በደንቆሮ ዋሻ፣ በብር ሸለቆ ሀሩር የሚነዱ ሌሎች ለአገርና ለወገን የሚፈይድ አንዳች ነገር ለመፍጠር የሚሆን አእምሮ በሌላቸው መለስና በረከት በሚባሉ ብካዮች ወንጀል እየተፈረከባቸው ዘብ ጥያ የወረዱ ሺዎች ጥፋታቸው ምንድነው? ከተባለ የሚከተሉት ነገሮች ብቻ ናቸው ሊሆኑ የሚችሉት።

ጄኔራል ተፈራ፣ ሃጂ መሃመድ፣አቶ ጽጌ፣ አቶ ነጋ፣ አቶ መላኩ እና ሌሎችም አማራ፣ኦሮሞ፣ጉራጌ ወይም ሌላ መሆናቸው፣
ባርነትን በጸጋ ተቀብሎ ለመኖር የማይፈቅዱ፣ አልያም
ባርነትን ተቀብሎ ለመኖር ፈጽሞ አይቻለንም የሚሉ ልጆች የወለዱ መሆናቸው ነው።

እርግጥ አቶ ጽጌ ደግሞ ሌላም ጥፋት አለባቸው። ፋሽስት ጣልያንን ሲዋጉ የተሰው የአርበኛው ሀብተ ማርያም ተሰማ ልጅ ማን ሁኑ አላቸዉ? እነ መለሰ ደግሞ ለፋሽስት ጣልያን ወዶ ገብ፣ የባንዳ ልጆች ናቸው። የባንዳ ልጆች ደግሞ የበታችነት መንፈስ ሁል ጊዜም ይከሳቸዋል። የአርበኛ ልጅ ምንም ባያደርጋቸው እንኳ በህይወት መኖሩ ብቻ ህሊናቸውን ሲጠቀጥቃቸው፣ የባንዳ ልጆች መሆናቸውን ሲያስታውሳቸው ይኖራል። እነርሱ ደግሞ ከህሊናቸው ጦርነት “ናጽነት” የሚወጡ የሚመስላቸው አርበኛን ከነልጆቹና ከነሀገሩ ሲያጠፉት እንደሆነ ይሰማቸዋል። ታማኝነት በዘር ነው ብለው ስለሚያምኑ ደግሞ ከእነርሱ ውጭ ያለውን ሰው ሁሉ ይጠረጥሩታል። ባለፈ ባገደመ ቁጥር መንግስታቸውን የገለበጠ ይመስላቸዋል። ህገ መንግስታቸው ደግሞ በዘር ታማኝነት ላይ የተገነባ ስለሆነ ሁል ጊዜም እንዳይናድባቸው ይፈራሉ። አብረው በጋራ ያልሰሩት ቤት ሁሌም እንደሚፈራርሰው እንዲሁ ዘረኞች እንገነባለን የሚሉት ህገ መንግስትና ህገ መንግስታዊ ስርአት እረኞቹ እነ ልጅ ምትኩ እህታቸውን ለመጎብኘት ከጎንደር አዲሳባ በመጡ ቁጥር፣ የአማራ አልያም የኦሮሞ ጄኔራሎች መንገድ ላይ ሲሄዱ የሚያሰሙት ኮሽታ፣ ባርነትን አንቀበልም የሚሉት የአርበኛ የልጅ ልጆች ካሉበት ሆነው ከሚያሰሙት ጩሀት ጋር ተዳምሮ መንግስታቸው የተገለበጠባቸው እየመሰላቸው በድንጋጤ ሚይዙትን ሚጨብጡትን አሳጥቷቸዋል። ትናንት በሁለት ሺ ብር አብዮት ሊያካሄድ ነው ብለው ያላጋጡበትን ድርጅት “መንግስት ሊገለብጥ ሲል ደርሼ አከሸፍኩበት” ሲሉ አለም በአግራሞት ሰምቷቸዋል። አሁን አሁንማ መለስ አይደለም ሌላን ሰው የገዛ ራሱን ጥላ ማመን እየከበደው መጥቷል። በጋምቤላ ከአኙዋክ መወለድ ወንጀል ሆኖባቸው በደማቸው በጸሃይ ሀሩር የነደዱ የጋንቤላን በረሃዎች ያረጠቡት የአኙዋክ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለአምላካቸው የሚያሰሙት የተበቀልልን ጩሀት ከጋምቤላ እስከ ዲሲ ዘልቆ እነ ጄኖሳይድ ዎችን የተኛ ፋይል ቀስቅሰው የእስር ማዘዣ በመለስ ላይ ይውጣበት የሚል ተማጽኖ እንዲያሰሙ አድርጓቸዋል። እነ መለስ በዚህ ሁሉ ጩሀት እየባነኑ እንቅልፍ እያጡ ማደር ጀምረዋል። ለዚህም ይመስላል ከመለስ ቢሮ አከባቢ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ ከቆሻሻ መጣያዎች ውስጥ የሚገኙት “ወይኔ ጉዴ” የሚሉ በመለስ የእጅ ጽሁፍ የተጻፉ መሆናቸው በደህንነት ሰዎቻችን የተረጋገጡ ብጫቂ ወረቀቶች እየተገኙ ያሉት። በተለይ “ማን ተይዞ ማን ሊቀር” በሚል ከትናንት ጀምሮ ማንም የወያኔ ባለስልጣን ወደ ውጭ ሀገሮች ለመሄድ ሲዘጋጅ ከመውጣቱ በፊት አስቀድሞ እንዲያሳውቀው የደህንነት ሹሙ ጌታቸው አስፋው በመለስ እንደተነገረው እየሰማን ነው። እነ መለስ የቱንም ያህል ስሙን አንቆለጳጵሰው ቢጠሩት፣ “ህገ መንግሥታዊ ሥርዓታቸው” እንደ ጎንደር እረኞች የሾላ ፍሬ ክምር ከመናድ በቀር ሌላ ምን ምርጫ አለው? የመለስ እጣው በደንብ ወለል ብሎ እየታየ ነው። ቀኑን በውል ባያውቁትም የጄኖሳይድ ዎቹ ግሬጎሪ ስለነ መለስ መጨረሻ እንዲህ ሲሉ ተንብየዋል፦

መለስን አየሁት፣ በዴንሃግ ጎዳና፣
ቀኙ ከበረከት፣ ግራው ከስብሃት፣ ታስሮ በካቴና፣

ያሰንብተን!

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 29, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.