የስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ዝርዝር የፍርድ ቤት ውሎ

(ሙሉ ገ./)

ሐሙስ ታህሳስ 12 ቀን 2004 ዓ.ም፡- በፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባትና የጋዜጠኝነት ሙያን እንደ ሽፋን በመጠቀም ለሽብርተኝነት ድጋፍ በመስጠት ወንጀል የተከሰሱት ሁለቱ ሲዊዲናዊያን ጋዜጠኞች ጥፋተኞች ተባሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ- ሕግን ማክበጃ ከተቀበለ እስከ 16 ዓመት ከስድስት ወር የሚደርስ ቅጣት ሊጠብቃቸው ይችላል ተብሏል፡፡ አንድ የሲዊዲናዊያኑ ጋዜጠኞች ጠበቃ በውሳኔው መበሳጨታቸውን ለሪፖርተራችን ተናግረዋል፡፡

በሰኔ 2003 ዓ.ም በኢትዮጵያ የጸጥታ ኀይሎች እና በኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በተደረገ ጦርነት ወቅት በቁጥጥር ሥር ዋሉ የተባሉት ጋዜጠኛ መርቲን ካርል ሽብየ እና ፎቶ ጋዜጠኛ ጁሃን ከርል ፐርሸን ለምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ ያለ ቪዛ በሕገወጥ መንግድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባታቸው ይቅርታ ጠይቀው በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ላይ ጉዳት ለማድረስ እንዳልተንቀሳቀሱ፣ በሽብርተኝነት ተግባርም እንዳልተሰማሩ ለችሎቱ ቀደም ሲል አስረድተዋል፡፡

ፍረድ ቤቱ የግራ ቀኙን ማስረጃ ከመረመረ በኋላ “በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አምነው ለሽብር ድጋፍ መስጠታቸውን ክደው ተከራክረዋል ከተነሳው ጭብጥ ጋር የሚሄድ መከላከያም አቅርበዋል” ያለ ሲሆን “ዐቃቤ ሕግ ‘በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የመጡት ለጋዜጠኝነት ሥራ አይደለም’ ብሎ የተከራከረበትን ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም፡፡

ተከሳሾች ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው የኦብነግ አባላትንና ጉዳት የደረሰበትን የኦጋዴን ሕዝብ ለማናገር ያደረግነው ሙከራ በመያዛችን ተቋረጠ ያሉትን ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም ይሄም በእርግጥ ተከሳሾቹ የመጡበት ዓላማ ለጋዜጠኝነት ሥራ ብቻ ነው ብሎ ለመደምደም ያዳግታል ምክንያቱም መጀመሪያ ለንደን ሄደው የኦብነግ አባላትን አናግረው ነበርና ሲል በፍርድ ሐሳቡ ገልጿል።

ፍርድ ቤቱ “አራተኛ ተከሳሽ ጁሃን ከርል ፐርሰን በምስሉ ላይ ይዤ የታየሁት መሳሪያ የሆቴሉ ጠባቂ ነው ያሉት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነው ምክንያቱም ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት በሕገ ወጥ መንገድ በኦብነግ ሰዎች በመሆኑ ነው” ብሏል። አያይዞም ተከሳሻቹ የሙያ ምስክር አድረገው ያቀረቧቸው 3ተኛ እና 4ተኛ ምስክር “ተከሳሾች የሀገሪቱን ሕግ መጣሳቸውንና በሕገ ወጥ መንገድ መግባታቸውን ሙያው በሕገ ወጥ መንገድ ገብቶ ይሠራል ብለው አላስረዱም” ሲል ፍርድ ቤቱ አብራርቷል።

ተከሳሾቹ 17 ዓመት የተፈረደባቸውን አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች አብዲወሊመሀመድ እስማኤል እና ከሊፍ አሊን አናውቃቸውም ቢሉም ዐቃቢ ሕግ ባቀረበው የድምጽና የምስል ማስረጃ ላይ በማሳየቱ ውድቅ ተደርጓል፡፡

ፍርድ ቤቱ ሁለቱ ሲዊዲናዊያን ጋዜጠኞች የአገሪቱን የግዛት ወይም የፖለቲካ ሉአላዊነት በመተላለፍ ለሽብርተኝነት ድጋፍ በመስጠት ወንጀል በሙሉ ድምጽ ጥፋተኛ ናቸው ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

“2ተኛው ምስክር እነዚህ ተከሳሾች ናይሮቢ ላይና ሲዊዲን ላይ ይሄን መረጃ ቢያገኙ ወደ ኢትዮጵያ አይገቡም ነበር ብለው የመሰከሩት ፍርድ ቤቱ ከክሱ ጭብጥ ጋር ሲያየው እነርሱ እዚህ መጥተው የሰሩት፣ ያናገሩት፣ ሰው ባለመኖሩ ይሄን ለመቀበል ያዳግታል፣ ይሄን የኢትዮጵያን መንግሥት ጠይቀው ማድረግ ይችሉ ነበር፤ እነርሱ ግን ለንደን ሄደው የኦብነግ አመራርን ነው ያገኘት ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል፡፡” ሲሉ ዳኛው አብራርተዋል።

“በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የሄዱበት ሁኔታ መረጃ ለመፈለግ ብቻ ሳይሆን በጋዜጠኝነት ሙያ ሽፋን ከአሸባሪው ኦብነግ ጋር ተሳትፎ እንዳደረጉ የሚያሳይ ነው”  በማለት ፍርድ ቤቱ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ በመግባትና ለሽብር ወንጀል ድጋፍ በመስጠት ጥፋተኞች ናቸው በማለት ውሳኔ አስተላልፎ ከዐቃቤ- ህግ እና ከተከላካይ ጠበቆች የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ አስተያየቶችን አድምጧል፡፡

ዐቃቤ ሕግ “በሁለቱ ሲዊዲናዊያን ጋዜጠኞች ላይ የምናቀርበው የማክበጃ እርከን የለንም፣ ጥፋተኛ የተባሉት በ2ተኛ እና በ4ተኛ ክሶች በመሆኑ እነዚህ ክሶች ደረጃ አልወጣላቸውም፤ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ከፍተኛ ደረጃ ብሎ ይውሰድልን ምክንያቱም ወደ ኢትዮጵያ የመጡት መጀመሪያ ለንደን ላይ ከኦብነግ ጋር በመመካከርና በማቀድ ወደ ሶማሊያ በመምጣት፣ ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሆን ብለው አስበውበት በለሊት በመሆኑ የወንጀል አፈጻጸሙ ከባድ የሚያስብል ነው” ብሏል።

“በሁለተኛ ደረጃ ይህ ፈጸሙ የተባለው ወንጀል ዓለማቀፋዊ በመሆኑ ሕዝቡ ላይ ፍርሃት፣ ጥቃት፣ ሽብር በመፍጠር ሙያዊ የሚዲያ ሽፋን መስጠት ስለሆነ በከባድ ተወስዶ በልዩ ሕጉ ከ10 እስከ 15 ዓመት ነው የሚለው፣ ከባድ የሚለው ከ12 እስከ 13 ዓመት ሆኖ መነሻው 12 ዓመት ከ6 ወር እንዲወሰድልንና በድምሩ 15 ዓመት ከ6 ወር ስለሚሆን ይሄን በእርከን 35 እንዲወሰድ፤ ተከሳሾቹ በወንጀሉን የፈጸሙት በተናጥል ሳይሆን በቡድን በመሆኑ እርከኑ ወደ 36 ከፍ እንዲል ፍርድ ቤቱን እንጠይቃለን” በማለት ዐቃቤ ሕግ ቅጣት ማክበጃውን አቅርቧል፡፡

የተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት ሁኔታ አንድ ክስ ሆኖ የቀረበው እንደገና ደግሞ ማክበጃ ሆኖ ቀርቧል፣ የክሱ አንድ አካል የክሱ ማራመጃ በመሆኑ በዝቅተኛ እንዲወሰድልን ፍርድ ቤቱን እንጠይቃለን፡፡ ከኦብነግ ጋር መገናኘታቸው አልተካደም እንደገና ክሱም ነው ማክበጃ ተደርጎ የቀረበው፡፡ የሚዲያ ሽፋን ማግኘታቸው እንደ ማክበጃ ቀርቧል፣ ይህ እንደ ዓላማ ሲታይ ሽፋን መስጠት ሙያቸው ሲሆን ይሄም ያልተተገበረ በመሆኑ በሙከራ ደረጃ ስለሆነና ይሄን የሚያሳይ ማስረጃ ባልቀረበበት ሁኔታ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ይሄን ውድቅ እንዲያደርገው በፍርድ ቤት የቅጣት ማኑዋል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም አቅልሎ ያየዋል ስለሚል፣ በተጨማሪም እነዚህ ጋዜጠኞች ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የወንጀል ሪከርድ ስለሌለባቸው ይህ ደግሞ መልካም ስነምግባር እንዳላቸው ስለሚያሳይ እነዚህ ሰዎች ከአገራቸው ውጪ ከዘመድ አዝማድ እርቀው መሆኑን ግንዛቤ በመክተት ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን አቅልሎ እንዲወስድልን እንጠይቃለን፡፡” ሲሉ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለታህሳስ 17 ቀን 2004 ዓ.ም ጠዋት ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተበትኗል፡፡ 

 Source: አዲስነገር ኦንላይን)

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 24, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.