የስኳርና ዘይት ዋጋዎች ቀነሱ ወይስ ጨመሩ?

ታደሰ ብሩ —

ወያኔ የኢትዮጵያን ህዝብ “ከስግብግብ” ነጋዴዎች ለመታደግ ሲል “መሠረታዊ” ባላቸው ጥቂት የሸቀጥ ዓይነቶች ላይ የዋጋ ተመን ጣለ። ለውይይታችን እንዲመቸን ስኳርና ዘይት ላይ ብቻ እናትኩር።

የሸቀጦች ዋጋ እያሻቀበ፤ ሸማችም እተማረረ መጣ። ኑሮ ከዳገት መውጣት የከበደ ፈተና ሆነ። “ሳይቲስቶቹ” የወያኔ መኳንንት ተሰበሰቡና የስኳርና የዘይትን የዋጋ ጣርያ ወስነው ከዚህ በላይ በሆነ ዋጋ ሲሸጥ የተገኘን “እጅ እንቆርጣለን” አሉ።

ነጋዴው ራሱ በጅምላ ከሚገዛበት ባነሰ ዋጋ እንዲሸጥ ተገደደ። “ተዘረፈ” እንጂ “ሸጠ” መባል አይገባውም ነበር። ጉልበት ገበያ ውስጥ ከገባ፤ ዘረፋ እንጂ “ገበያ” አይባልም። ለጊዜው በዚህ አንከራከርም። ወደ ስኳርና ዘይታችን እንመለስ።

ለጥቂት ሳምንታት በጉልበት በወረደ ዋጋ በነጋዴው እጅ ውስጥ የነበረው ስኳርና ዘይት ተሸጦ አለቀ። በነጋዴው መጋዘን ውስጥ የነበረው ሲያልቅ ሌላ የሚያመጣ ጠፋ። የዋጋ ተመን ጣሪያዎች እንደገና ተከለሱ። ለውጥ የለም። ዘይትና ስኳር ከገበያ ጠፉ።

ህፃናት ሻይ፤ አዛውንት በዘይት የተከሸነች ሽሮ አማራቸው። ስኳርና ዘይት ዋጋቸው ቢቀንስም ክብራቸው ግን እጅግ ከፍ አለ። “ሳይንቲስቶቹ” አውጥተው፣ አውርደው፣ ተመራምረው ሌላ ዘዴ አመጡ። ዘይትና ስኳርን በመንግሥት ማከፋፈያ ማደል።

አሁን አንድ ኪሎ ስኳርና አንድ ኪሎ ዘይት በተተመኑበት ዋጋ መግዛት ይችላሉ – ከመርህ አኳያ።

በተግባር አንድ ኪሎ ስኳርና አንድ ኪሎ ዘይት መግዛት ከፈለጉ በጠዋት ተነስተው በማከፋፈያ በራፍ መሰለፍ፤ ወረፋዎ እስኪደርስ ለሰዓታት በፀሃይ መንቃቃት እና በነፋስ መወልወል ይኖርብዎታል። ከዚህም በተጨማሪ:-

• የሰልፍ ወረፋ አስተባባሪ ሊሰድብዎ፤ ሊገፈትርዎ፤ ከከፋም ፓሊስ ጠርቶ ሊያስጠፍርዎ እንደሚችል ይወቁ፣
• ወረፋ የሚሸጡ ደላላች ስላሉ ሰርገው ሊገቡ፤ አንዳዶቹም በአይን ዓውጣነት እርስዎን በሰርጎ ገብነት ሊወነጅሉዎ ስለሚችሉ ይጠንቀቁ፣
• ሰልፉ ውስጥ ጆሮ ጠቢዎች እንዳሉ አይርሱ፣

ይብቃኝ፤ በዘረርኩት መጠን ሆዴን ያመኝ ጀምሮዓል።

ጥያቄዎች አሉኝ።
• ለመሆኑ በዚህ ሁኔታ የተሸመተ ስኳርና ዘይት በርካሽ ተገኘ ይባላል?
• እኛ አገር ውስጥ የድሃ ጉልበት አንዳችም ዋጋ የለውም ማለት ነው?
• ጉልበቱስ ቢቀር የድሃ ክብር አንድ ሳንቲምም አያወጣም ማለት ነው?

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 15, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.