የመድረክ ስብሰባ በአትላንታ (ቀጥታ ስርጭት)

እሁድ፣ ሴፕቴምበር 23 ቀን፣ በአትላንታ ከተማ የመድረክ ስብሰባ በ5፡00 ላይ ተጀምሯል። የመድረክ ፓርቲን በመወከል ከኢትዮጵያ የመጡት አቶ ተመስገን ዘውዴ እና አቶ ገብሩ አስራት ወደ ስብሰባ አዳራሽ ሲገቡ የሞቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በቅድሚያ በኢትዮጵያ የተሰዉ እና የታሰሩ ኢትዮጵያዊያንን በማሰብ የህሊና ጸሎት ተደርጓል።

5፡15 PM – አቶ ግርማዬ ግዛው የአትላንታ የመድረክ ድጋፍ ሰጪ አካል ተወካይ፤ ከኢትዮጵያ የመጡትን አቶ ገብሩ እና አቶ ተመስገንን በማስተዋወቅ ላይ ናቸው። የመጀመሪያው ተናጋሪ አቶ ገብሩ አስራት ነበሩ። አቶ ገብሩ አስራት በ2002 ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚነት ከወጡ በኋላ፤ አረና የሚባለውን የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አቋቁመው ከአጋሮቻቸው ጋር በሰላማዊ ትግል በኢትዮጵያ ለማምጣት ከሚሰሩት ኢትዮጵያዊ አንዱ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር እና የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ናቸው።

የአቶ ገብሩ አስራት ንግግር በከፊል፡ ብዙዎቻችሁ መድረክን የምታውቁት ይመስለኛል። እንግዲህ የኛ ፓርቲ የተመሰረተው ከአምስት አመታት በፊት በፊት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ስድስት ፓርቲዎችን አቅፏል። ብዙ ሰዎች “ከኢህአዴግ በምን ትለያላችሁ?” የሚሉ ጥያቄዎች ከደጋፊዎችም ሆነ፤ ከሌሎች ሰዎች ይቀርብልናል። ከኢህአዴግ ከምንለይባቸው ነገሮች አንዱ… ኢህአዴግ የሚከተለው አብዮታዊ ዲሞክራሲን ነው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ደግሞ የአፈና ተቋም ነው። ነጻነትን የሚያሳጣ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ኢህ አዴግ የሰብ አዊ መብቶችን የማያስከብር፣ የነጻ ፕሬስን የሚያጠፋ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አባላትን በሰበብ አስባቡ የሚያስር   በመሆኑ ይህ ትልቁ ልዩነታችን ነው። ሌላው መድረክ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ የጋራ ስምምነት ላይ ደርሷል። የመገንጠል አደጋ እንዲኖር መድረክ አይደግፍም። በመሆኑም በኛ አቋም የመገንጠል ሁኔታን የሚሰብኩ አንቀጾች ከህገ መንግስቱ ላይ እንዲሰረዙ ጭምር እናደርጋለን። ይህም ሌላው ልዩነታችን ነው።

የአልጀርሱ ስምምነት የ ኤርትራን እንጂ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም የማያስጠብቅ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ እንዲሰረዝ ሁሉም የመድረክ ፓርቲዎች ስምምነት ላይ ደርሰዋል። እንዲያውም አልፎ ተርፎ ኢትዮጵያ የባህር ወደብ ያስፈልጋታል የሚል አቋም አለን። ከዚህም በተጨማሪ በልማት አካሄዱ ላይ ልዩነት አለን። በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ እና አባላቱ ትላልቅ የንግድ ኮርፖሬሽኖችን እያቋቋሙ ነው። እነዚህን ኮርፖሬሽኖች የግል የልማት እና የንግድ ተቋማት የሚቋቋሙት አይሆንም። የመሬት ይዞታን በተመለከተ ከኢህ አዴግ ጋር ልዩነት አለን… ነፍሳቸውን ይማረውና የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር እንዳሉት፤ “መሬት የመንግስት ከሆነ፤ የመንግስት ሌቦች ይቸበችቡታል።” ብለው ነበር። በርግጥም ትክክል ነው። አሁን ኢህአዴግ እያካሄደ ያለው  መሬትን የራሱ ይዞታ ማድረጉ ትክክል ነው ብለን አናምንም። ስለዚህ መሬት የህዝብ እንጂ የመንግስት መሆን የለበትም የሚል ልዩነት አለን።

ሌላው በመድረክ ውስጥ ያለነው የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አንድ ውሁድ ፓርቲየሚመጡበትን ነገር እየሰራን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ህዝቡ፤ የትግል ስልታችንን አስመልክቶ የሚያቀርብልን ጥያቄዎች አሉ። በርግጥ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር በጣም ጠባብ ነው። ሆኖም ትግሉ በአዞ አፍ ውስጥ የሚካሄድ ትግል ነው። ፍርሃት የለብንም፤ የማይቻለውን እንዲቻል ለማድረግ አባሎቻችንን እናደራጃለን ግንዛቤ እንፈጥራለን። ይህንን በማድረጋችን ብቻ ከኢህአዴግ ብዙ ብዙ ጫና እየደረሰብን ነው። አቶ አንዷለን፣ አቶ በቀለ፣ አቶ ኦላና፣ አቶ ናትናኤል እና ሌሎችም በአሁኑ ወቅት እስር ቤት ናቸው።

እኛ የምንገልጸው በህዝብ ዘንድ የሚታወቁትን እንጂ፤ በገጠር እና ራቅ ባሉ ቦታዎች በርካታ አባሎቻችን ይታሰራሉ፤ ከስራ ይባረራሉ፤ ይሰደዳሉ፤ ይገደላሉ። በመሆኑም ይህንን ፈርተን ከሰላማዊ ትግሉ አናፈነግጥም። በአሁኑ ወቅት ኢህአዴግ መከላከያውንም ሆነ፣ ፖሊስ እና ደህንነቱን በስሩ አድርጎ እያንቀሳቀሰ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከ2002 ምርጫ በኋላ የተማርነው ቁምነገር ቢኖር፤ ድክመታችንንአርመን ወደፊት መንቀሳቀስ እንዳለብን ሲሆን፤ የገንዘብ አቅማችንን ማደራጀት ይኖርብናል። በአሁኑ ወቅት ኢህ አዴግ የራሱ የሆኑ ትላልቅ የንግድ ተቋማትን በማንቀሳቀስ እራሱን ይረዳል። ኢህአዴግ የመንግስት ገንዘብን እንደድርጅት ገንዘብ ያዝበታል። ሌላው ቀርቶ በህጉ መሰረት መንግስት ለተቃዋሚ ድርጅቶች ገንዘብ እንዲሰጥ ይላል። በዚሁ መሰረት ለራሳቸው ደጋፊ ድርጅቶች፤ እስከ 300 መቶ ሺህ ብር ድረስ ይሰጣሉ። በዚህ መሰረት ለኛ 3ሺህ አምስት መቶ ብር ወይም 195 ዶላርነበር የሰጡን… እኛም ይህንን አንቀበልም ብለን ነው የመለስነው። ኢህአዴግን ለማሸነፍ የግድ የነሱን ያህል ገንዘብ ባናሰባስብም፤ የሃይል ምንጫችን አድርገን የምናየው ህዝቡን ነው። ህዝቡን ይዘን ለመንቀሳቀስ ግን ቢሮ መክፈት አለብን። ለዚያ ደግሞ ገንዘብ ያስፈልገናል።

ስብሰባው ቀጥሏል። አቶ ተመስገን ዘውዴ (የቀድሞ የፓርላማ አባል ንግግራቸውን ቀጠሉ) የድህረ መለስ ዜናዊን ሁኔታ እየተነተኑ ነው። አቶ መለስ ዜናዊ አልፈው፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር ሲያደርጉ… “የመለስ ዜናዊን ሌጋሲ እንዲቀጥል አደርጋለሁ ብለዋል” እድሉን ባገኝ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን የምጠይቃቸው ነገሮች ነበሩኝ።

አቶ መለስ ዜናዊ የጭቆና ስርአት አውራ ናቸው። አቶ መለስ ዜናዊ ጎሰኛ ነበሩ።  በጎሳ ፖለቲካ የሚያምኑ ሰው ነበሩ። ብዙዎች ተገድለዋል። ታስረዋል። አገራችን ብዙ ነገር አሳልፋለች። በተለይ በአሁኑ ወቅት ጋዜጦች እየተዘጉ ናቸው… የአቶ መለስ ዜናዊን ሌጋሲ የሚቀጥሉት ይህንን አፈና ነው? እነ አንዷለም አራጌ፣ እነ እስክንድር፣ እነ ር እዮት አለሙ ሌሎችም በእስር ላይ ይገኛሉ።

ይህ መንግስት እኮ በውጭ አገር ከሚገኙ ሰዎች ጋር ኢሜይል ተለዋውጣችኋል፤ በስልክ አነጋግራችኋል፤ ተብለው 18 እና ሃያ አመታት የተፈረደባቸው ወጣቶች አሉ። እነዚህ ነገሮች እያየን ህሊናችን እንዴት ዝም ይላል? ነጻ ሬዲዮ የለም። ጀርመን እና የአሜሪካ ድምጽ ባስፈለገ ጊዜ ይታፈናል። ይህንን እያየን እንዴት ዝም እንላለን። በአሁኑ ወቅት እኮ መንግስት ማለት የኢህአዴግ ፖለቲካ ድርጅት እየሆነ ነው። ምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያ፣ ፖሊስ እና መከላከያው የህዝብ ቢሆንም፤ አሁን እነዚህ ሁሉ የአንድ ድርጅት እየሆኑ ናቸው። አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ወቅት እንዳሻቸው ይናገሩ እና ያስፈራሩ ነበር እኮ። ለምሳሌ “ተቃዋሚዎች እግር እስከሚያወጡ እንጠብቃለን። እግር ሲያወጡ እንቆርጣለን።” ይኅ እስኪ ምን ማለት ነው? ይህን ሲሉን ነበር እኮ። ይህ እንዴት ሊባል ይችላ? በህይወት ሳሉ ፓርላማ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች እጠይቃቸው ነበር። ሳልጠይቃቸው በማለፌ ከሚቆጩኝ ጥያቄዎች አንዱ… “ተቃዋሚዎች እግር እስከሚያወጡ እንጠብቃለን። እግር ሲያወጡ እንቆርጣለን… ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?” ብዬ ብጠይቃቸው ደስ ይለኝ ነበር።

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ይህንን የአቶ መለስ ዜናዊን ሌጋሲ ነው ለማስቀጠል የሚፈልጉት። በአሸባሪነት ስም እነ  አንዷለም አስረዋል። ይህ ሌልጋሲ ነው ወይ የሚቀጥለው?

አቶ መለስ ዜናዊ ህግ አውጪ ነበሩ፣ ህግ አስፈጻሚ ነበሩ። በአቶ መለስ ዜናዊ በህይወት በነበሩበት ወቅት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ሁሌ የሚሉት ነገር አለ። “ጂ.ዲ.ፒ 11 አመት አድጓል” ይሉን ነበር አሁንም ይህንኑ እየተባልን ነው። ጂ.ዲ.ፒው አሁንም አቶ ኃይለማርያም ከተሾሙ በኋላይህንን ነው የሚቀጥሉት?

እኔ አዚህ አገር እኖር ነበር። ሃምበርገር $ 2.00 ዶላር የምበላበት ወቅት ነበር። አሁን አምስት ዶላር ነው። ኢትዮጵያ የዛሬ 15 አመት ስሄድ ጤፍ 400 ብር ነበር አሁን 2000 ብር ነው። ይሄ የኢኮኖሚ ግሽበት እንጂ፤ የኢኮኖሚ እድገት የሚባለው ምኑ ላይ ነው? ህዝቦች በገቢያቸው መተዳደር ካልቻሉ፤ መዝናናቱን እንተወው ለመኖር ካልቻሉ.. እንዴት ነው የኢኮኖሚ እድገት አለ የሚባለው። የተወሰኑ ሃብታሞች እላይ ተንጠልጥለው ፎቅ ስለሰሩ እንዴት ነው ህዝቡ አድጓል የምንለው። በነጻ ኢኮኖሚ መሬት እና ካፒታል በግል ኢኮኖሚ ነው የሚተዳደሩት። በአገራችን ግን የገዢው ፓርቲ የንግድ ድርጅቶች ናቸው ንግዱን የሚቆጣጠሩት። እነዚህ ድርጅቶች ናቸው ኢኮኖሚውን እየመሩ ያለው። እናም አቶ ኃይለማርያም ደግመው ደጋግመው በፓርላማ – የመለስ ዜናዊን ሌጋሲ ለመቀጠል ቃል እንደገቡ ሁሉ… እኛም የአቶ መለስ ዜናዊ የጭቆና ሌጋሲ እንዳይቀጥል ለህዝቡ ቃል እንገባለን። (ጭብጨባ)

በአገራችን የህግ የበላይነት እና የዳኝነት ነጻነት እውን አልሆነም። የዜጎች መደራጀት፣ የጋዜጠኞች ሃሳብን በነጻነት መናገር አስቸጋሪ እየሆነ ነው። እንኳንስ አገር ቤት ቀርቶ እዚህ ሆኜ ለምናገረውምፍራቻ ሊኖር ነው ማለት ማለት ነው። ስለዚህ ይህንን መናገር ያልቻሉትን ኢትዮጵያውያንን አስቧቸው።

የኢትዮጵያ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የኢትዮጵያን ህዝብ ማገልገል አለባቸው። አሁን ያለው ሁኔታ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥኑ የአንድ ፓርቲ አገልጋይ እየሆነ ነው። ፈቃድ እንዳለው ፓርቲ መድረክ ሆነ ሌላው ፓርቲ ሃሳቡን በሚዲያ ለህዝቡ ማሳወቅ ይኖርበታል። ይህ ግን በኢትዮጵያ የሚታሰብ አይደለም።

ገለልተኛ የሆነ የምርጫ ቦርድ ብቻ ሳይሆን፤ ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢዎች ሊኖሩ ይገባል። ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ2002 ምርጫ የአውሮፓ ህብረት አባላት ምርጫውን ለመታዘብ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከታዘቡ በኋላ፤ ወደ አውሮፓ ተመልሰው የኢትዮጵያ የምርጫ ሂደት አለም አቀፉን ደረጃ የጠበቀ እንዳልሆነ በመናገራቸው፤ ምርጫው ሲጀመር እነዚህ ታዛቢዎች ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ሲሉ ቪዛ ከለከሏቸው። ይህ ነው በአገራችን እየተከናወነ ያለው። ወደፊትም አምባገነኖችን አውርደን ሌላ አምባገነን ለመተካት አይደለም ትግላችን መሆን ያለበት።

የአቶ ተመስገን ዘውዴ ንግግር በከፊል ይህንን ይመስላል። በአሁኑ ወቅት የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት ተጀመሯል። ለጨረታ የቀረበው በአሁኑ ወቅት በ እስር ላይ የሚገኘው የአንዷለም አራጌ ፎቶግራፍ ሆኗል። በፎቶግራፉም ጀርባ ላይ እንግዶቹ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ ተገልጿል። ከጨረታው በኋላ… የጥያቄ እና መልስ ዝግጅት ይደረጓል ተብሏል።

የአቶ አንዷለም አራጌ ፎቶግራፍ በአንድ ሺህ 300 ዶላር ተሽጧል።

ከዚህ በኋላ የጥያቄ እና የመልስ ዝግጅት ነው። ህዝቡ ያለውን ጥያቄ ለፖለቲካ ድርጅት መሪዎቹ ያቀርባል። እኛም በቀጥታ እየተከታተልን እናቀርብላችኋለን።

7፡10 PM -ስብሰባው እንደገና ተጀመረ።

ጥያቄ – ከሁለት አመት በፊት እዚህ ስትመጡ በኢትዮጵያ አንድነት በኩል ስንጠይቅ የሰታሁን ምላሽ አትጋቢ አልነበረም። አሁን ግን አንቀጽ 39ኝን በተመለከተ የመገንጠል ጥያቄ ግልጽ የሆነ አቋም በመያዛችሁ እናመሰግናለን። ወደ ጥያቄዬ ልሂድ። 1ኛ – የ እስልምና እምነት ተከታዮች ላይ እየደረሰ ያለውን ሁኔታ ትከታተላላችሁ ወይ? ምንስ አደረጋችሁ? 2ኛ – አቶ አንዷለም አራጌ እና ሌሎች የተቃዋሚ አባላት  በ እስር ላይ ይገኛሉ እነሱን ለማስፈታት ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ ገብሩ አስራትንቀደም ሲል እንደገለጽኩት ነጻ የሲቪክ ማህበራት የሉንም። እንደአንድ ተነስተው የህዝቡን ብሶት አንስተው የሚጠይቁበት ሁኔታ የለም። ሆኖም እራሱ ኢህ አዴግ ደግፎ ቢያቋቁማቸውም መልሰው ተቃውሞ እያነሱ ነው። የመምህራን ማህበር፣ የሰራተኛ ማህበር የሙስሊሙ ህብረተሰብ የመብት ጥያቄዎች እያነሱ ነው። እነዚህ ደግሞ የሲቪክ ማህበራት ጥያቄ በመሆኑ፤ በሲቪክ ማህበራት ጥያቄ መካከል ጣልቃ መግባት አልፈለግንም። ነገር ግን ጥያቄያቸውን ደግፈን መንግስት ምላሽ እንዲሰጥበት ጥያቄ አቅርበናል። የሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚያደርገውን ትግል በተመለከተ እኛም ብንሆን ትምህርት ልናገኝበት የሚገባ ነው። መናገር እንኳን ቢከለከሉ፤ አፋቸውን ሸፍነው ሃሳባቸውን እየገለጹ ይገኛል። በተለይ ዲሞክራሲያዊ ጥያቄዎቻቸውን ራሳቸው እየመሩ ያለው ጉዳይ ነው። በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ገብተን መግለጫ ባንሰጥም፤ እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ እና በደል የምንቃወመው ነው።

የነአንዷለምን ጉዳይ አስመልክቶ… ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ አንችልም። ቀደም ሲል ለኢህ አዴግ የምናደርገውን ጥያቄ አሁንም እያቀረብን ነው። የዲሞክራሲው ምህዳር በመጥበቡ ሰፋ ማለት አለበት። ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ህጋዊ ነው፤ ኢህ አዴግ ግን አይፈቅድም። መንግስት ራሱ የተቀመጠውን ህግ እየረገጠ በመሆኑ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጭምር ጥያቄዎቻችንን ማቅረብ እንቀጥላለን። ከምናካሂደው ሰላማዊ ትግል ውጪ በአመጽ ጫና ለመፍጠር አንችልም። ከዚህ በኋላ ያለው… መንግስት ምህዳሩን ሰፋ አድርጎ ከኛ ጋር መደራደር አለበት። ይህ ካልሆነ ግን እኛ ባናደርገውም  አገሪቱን ወደ ትርምስ እየወሰዱት ነው። ይህ ደግሞ አገሪቱን ወደ ባሰ ችግር ይወስዳታል። ስለዚህ እስካሁን ለታሰሩት ወገኖቻችን ሰላማዊ ሰልፍ አ

 

ጥያቄ – እናንተ የምትከተሉት ሰላማዊ ትግል ነው። ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ደግሞ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ የስራ ማቆም አድማ እና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ማድረግ አለባችሁ። ይህ ደግሞ ተከልክሏል። በርግጥ ይህ መንግስት ዘላለማዊ አይደለም። ስለዚህ ምን እየተደረገ ነው?

አቶ  ተመስገን ዘውዴ – በአንድ ወቅት ፓርላማ በነበርኩበት ወቅት፤ አንድ ካጠገቡ ያለ ሆቴል ነበር። በምሳ ሰአት 13 የምንሆን ሰዎች ሰብሰብ ብለን ምሳ እየበላን ለመነጋገር አሰብን። ስራ አስኪያጁ ወደኛ መጣና “መሰብሰብ አትችሉም” አለን። “ምሳ እየበላን መነጋገር አንችልም?” አልኩት። “አትችሉም።” አለን።

“እና ምን እንድናደርግ ነው የምትፈልገው?” ስንለው፤ “እንድትወጡልኝ ነው የምፈልገው” አለ። “እንደዚያማ ማድረግአይቻልም። ዜጎች ነን አንወጣም” ስንለው ስልኩን አንስቶ መደወል ጀመረ። የሚደውለው የነበረው ወደ ደህንነቶች ነበር። በአሁኑ ወቅት በዚህ አይነት፤ ደህንነቶች ለሆቴል ስራ አስኪያጆች ጭምር ስልካቸውን እየሰጡ ግንኙነት በማድረግ ዜጎችን እየበደሉ ይገኛሉ።

በሌላ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መስቀል አደባባይ እንዲፈቀድልን ጠየቅን። በኋላ ላይ አስተዳደሩ መልስ ሲሰጠን፤ “መስቀል አደባባይ ለአንድ አመት ተይዟል።” ብሎ ነገሩን ዘጋብን። ይህ በሆነበት ሁኔታ ታዲያ እንዴት ብለን ሰላማዊ ሰልፍ እናድርግ።

 

ጥያቄ – እኛ ህልም እና ራዕያችን የናንተ መጠናከር ነው። ሌሎችንስ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን አካታችሁ ለመቀጠል ምን እየተሰራ ነው?

አቶ ተመስገን ዘውዴ -እኛ ቀደም ሲል እንዳልኩት፤ተባብረን ለመስራት ምንግዜም ዝግጁ ነን ። እንሰራለን።

ጥያቄ – እንዲህ አይነት ጥያቄ ጠይቄ አላውቅም። ነገር ግን ወልቃይት ጠገዴ ጎንደር ምድር እንደሆነ ይታወቃል። ነገር ግን አሁን ወደ ትግራይ ተከልሏል።

አቶ ገብሩ አስራት – ወልቃይት እንዴት ወደ ትግራይ ተካለለ? ለሚለው መሰረቱን ቋንቋ ነው ያደረገው። ጠገዴም ከፊሉ ትግርኛ ተናጋሪበመሆኑ ወደ ትግራይ ነው የተካለለው። እኔም እዚያ በነበርኩበት ወቅት የተከተልነው የማካለል አካሄድ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው አከላለሉም ትክክል አይደለም የሚባል ከሆነ ወደፊት ማየት ይኖርብናል።

ወልቃይት ጠገዴም ቢሆን ወደ ሌላ አገር አልሄደም። ወደ ኤርትራ ወይም ወደ ሱዳን አልሄደም። እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ እስካለ ድረስ ወደፊት መስተካከል ካለበት የማይስተካከልበት ምክንያት የለም።

ጥያቄ – የኔ ጥያቄ በቀጥታ ለአቶ ገብሩ አስራት እና ለመድረክ ይሆናል። የዋልድባ ገዳም ነው። 1ሺ600 አመት ታሪክ ያለው፤ የዋልድባን ገዳም ያህል እድሜ ያለው ገዳም የለም። እዚያ ውስጥ ያሉ ቅርሶች እንዲጠፉ እየተደረገ ነው። በርግጥ በ ኤርትራ በትግራይ እና በሰሜን ተራሮች ተደርጎ ተካሏል። እስከምናውቀው ድረስ ያ መሬት የጎንደር መሬት ነው። መድረክ እስካሁን በዚህ ጉዳይ ለምን ዝምታን መረጠ?

አቶ ገብሩ አስራት – የዋልድባም ሆነ የአክሱም ጉዳይ የኔም ጉዳይ ነው። ይሄ የስኳር ፕሮጀክት የሚባለው ገዳሙን እስከማፍረስ ይደርሳል ወይ የሚለውን ማጥናት አለብን። ስለዚህ ችላ  አላልነውም። ዝርዝሩን አላጠናነውም። መንግስት የሚለው አለ። ሌላም መግለጫም አለ። ይህንን በግንባር ሄደን አላየነውም። በርግጥ ቅርስ ተነክቶ ከሆነ፤ ከስኳሩ ይልቅ ቅርሱን እንመርጣለን። ስኳር ፋብሪካው የትም ቦታ ላይ ሊገነባ ይችላል። ቅርስ ግን አንዴ ከጠፋ አናገኘውም። ስለዚህ ሁኔታውን በዝርዝር ካየን በኋላ መግለጫ የማናወጣበት ምክንያት የለም።

ጥያቄ – በሚቀጥለው ጥቂት ወራት የቀበሌ ምርጫ ይደረጋል። እናንተ የቀበሌ እና የወረዳ ምርጫ ላይ ስትሰሩ አይታይም።

አቶ ገብሩ አስራት በሚቀጥለው የቀበሌ እና የወረዳ ምርጫ መሳተፋችንን አልወሰንም። ባለፈው ምርጫ ከ80 በላይ መረጃዎችን ይዘን፤ ኢህ አዴግ የድምጽ ኮሮጆ የሰረቀበትን መረጃ ይዘን ፍርድ ቤት ቀርበን ውጤት አላገኘንም። ይህ በዚህ እንዳለ ዝም ብለን ወደ ምርጫው ብንገባ ምን ጥቅም እንደሚሰጥ እንነጋገርበታለን።

አቶ ተመስገን ዘውዴ – የወረዳ እና የቀበሌ ምርጫዎች ለኛ በጣም ጠቃሚዎች ናቸው። ሆኖም ነጻ የምርጫ ቦርድ እና ታዛቢዎች ካለ የማንሳተፍበት ምክንያት የለም። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ መሳተፋችን በጥያቄ ውስጥ የሚቆይ ነው።

 

ጥያቄ – የአቶ ኃይለማርያም አዲስ ሹመት እንዴት ታዩታላቹህ?

አቶ ገብሩ አስራት -ኢህአዴግ ተናግቷል። አቶ መለስ ዜናዊ የኢህአዴግ ጭንቅላት ሆኖ መከላከያውንም፣ ኢኮኖኖሚውንም፣ ፖለቲካውንም በሱ ጭንቅላት ብቻ ነበር የሚመራው። አሁን እሱ የለም። ከአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ያለመታዘዝ እና ያለመከባበርም ሊመጣ ይችላል። ሆኖም አንድ አምባገነን ሄዶ አንዱ ስለተተካ ለውጥ ይመጣል ብዬ አላምንም።

አቶ ኃይለማርያምን በተመለከተ ከፊትም ይደግፉኛል፤ ከኋላም ግፉኝ የሚለውን አቋም ይዘው ይቀጥሉ ይሆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ አቶ ኃይለማርያም ብቻቸውን የሚያደርጉት ነገር ያለ አይመስለኝም። ስለሆነም ደካማ አስተዳደር ተቃዋሚውንም አቅፎ ይሄዳል ወይስ የባሰ አፋኝ ይሆናል? ጊዜ ሰጥተን የምናየው ሆኗል። አሁንም የማየው መግለጫቸው የጭንቀት ነው። ይህ የደካማነታቸው ውጤት ነው።

አቶ ተመስገን ዘውዴ – ሰሞኑን ጄነራሎች ሲሾሙ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚንስትር አልነበሩም። መሾም የሚገባው ጠቅላይ ሚንስትር ነው።

ሰዎች ሲሾሙ ብዙ ንግግር ሰምቻለሁ። የሳቸው ንግግር መለስ ዜናዊን ከማሞገስ ውጪ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ እንደዚህ አደርጋለሁ አላሉም። በራሳቸው የሚሰሩት ነገር ካለ ወደፊት የምናየው ይሆናል፤ ከዚያ ውጪ የአቶ መለስን ሌጋሲ አስቀጥላለሁ የሚለው የትም አያስኬድም።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 23, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.