“ኡ…ኡ…ኡ…ኡ…ገደሉን….ጨፈጨፉን… የመን ያሉ ስደተኞች

በግሩም ተ ሀይማኖት

         የምሰራበት ሱቅ ያለው ሰነዓ ከተማ ውስጥ አሉ ከሚባሉት አራት ዋና ዋና የገበያ ቦታዎች በአንዱ ነው።  ቦታው ሻራ ሀየል/ሀየል መንገድ/ ይባላል። ዳይሪ የሚባለውን ጎዳና ይዘው ለስምንት ወር የተቀመጡት ተቃዋሚዎች እሁድ ዕለት በ17/09/2011 ከጠዋት ጀምሮ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው። እኔ ለምሰራበት ሱቅ ከ400 ሜትር ያነሰ ርቀት ላይ ነው እንቅስቃሴያቸው። ልክ ከቀኑ 10፡56 ላይ የመሳሪያው ድምጽ ከወትሮው የተለየ ሆነ። ደመቅ ከማለት አልፎ አህመድ አልራሚ የሚባል ልጅ/የመኒ/ ፊት ለፊቴ  ተመታ።

         ግርግሩ ነገሰ።

     የሱቁን በር ለመዝጋት ጊዜ አላገኘሁም። አብረውኝ ያሉት ጸሀይ በየነ..ሄለን ገ/እግዚዐብሄር..አስማ ገ/እግዚአብሄር..እና እቃ እየገዛች የነበረች አይሻ የምትባል ልጅ ከውስጥ ሆነን በሩን እየተጣደፍን ዘጋን። ዋና መንገድ ላይ ያለ በመሆኑ ሱቁ ፍርሀታችን ተባራሪ ጥይት በሩን በስቶ እንዳይደፋን ነው። የከባድ  መሳሪያው ድምጽ ከመቅረቡ የተነሳ እንደገደል ማሚቱ እያስተጋባ የነበረው ልቤ ላይ ነበር ማለት እችላለሁ። የሚያስተጋባው ጩኸት ግን ከእኔ አልፎ ለሌላ አይሰማም።የጭንቅ ሰዓት አረዛዘሙን ያወኩት ያኔ ነው። የማደርገው ጠፋኝ ለጓደኞቼ ደዋወልኩ። ሚሴጀ ማድረግ ለቻልኩት አደረኩ። <<ጢው…>>የምትለውን የክላሽ ድምጽ ብዙም አልፈራሁዋትም። ሰሞኑን አብራን ከመክረሟ ጋር ለምደናታል። ከባድ መሳሪያው ግን ቤቱን ብቻ ሳይሆን የእኛንም ልብ እያንቀጠቀጠው ነው። መሀል ላይ ቀዝቀዝ አለ ብለን ገና በሩን ስከፍተው ጥይቱ በሩ ጫፍ ላይ ነጠረ።

    አራቱ ሴቶች እና እኔ የሚነጠፍ ነገር የለን፣ የሚለበስ ነገረ የለን፣ ከሚሸጠው በርበሬ ላይ በውሀ በጥብጠን እንጀራ ስላለ በላን እና ወንበር ላይ ቁጢጥ..ቁጢጥ ብለን የተኩሱን ሁኔታ መብረዱን ስንጠባበቅ ከሌሊቱ 7 ሰዓት ሆነ፡፡ <<ስንት ኢትዮጵያዊ ላይ ጉዳት ደረሰ?..>>የሚለው እሳቤ ውስጤ ስንቅር ቢልም ምላሽ ለማግኘት ወጥቼ መረጃ ማሰባሰብ የምችልበት ደረጃ ላይ አይደለም  ያለሁት። ሻማም ሆነ ሌላ ብርሀን የሚሰጥ ነገር እንዳንጠቀም ብርሀን ሲያዩ ቢመቱንስ የሚል ፍርሃት ሰንቀን በጨለማ እንዳደፈጥን ነን። ትልቁን ሞት ተሸክመን እንቅልፍ ከየት ይምጣ?

      በዚሁ ሁኔታ ነጋ።

 ሰኞ ዕለት ጠዋት ተኩሱ ጋብ ሰላለ በሩን ከፍተን ወጣን። ከአካባቢው ለመሸሽ የሚኖረውን መንገድ ለመጠቀም ሞከርን። ዳይሪ በሚባለው በኩል ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። ለ8 ወር ተቃዋሚዎቹ የተቀመጡበት ቦታ ነው። ተቀማጮቹ አሁንም ዋና የእንቅስቃሴው ሞተሮች ናቸው። ቦታው በጥይት እየታረስ ነው። ወደ አሰር መንገድ የመንግሰት ወታደሮች ያሉበት እና አንደኛው የውጊያ ቀጠና ነው። በሻራ ሲታ አሽ/በ16መንገድ/ ተቃዋሚው የፕሬዘዳንቱ ወንድም ወታድሮች አሉ… ዙሪያውን ተከበናል። ዋናውን ገበያ ለሁለት አቋርጦ የሚያልፈው መንገድን ማቋረጥ ነው ትልቅ ፈተና የሆነው። ከፎቅ ላይ ሆነው መንገዱ ላይ ላዩት ሁሉ ስለሚተኩሱ በርካታዎች እዚህ ጋር ተመረዋል። አማራጭ በማጣቴ ከሱቁ ቀጥሎ ሁለተኛው ጊቢ ውሰጥ ወዳሉት ከእኔ ጋር ወዳደሩት ሁለት እህታማቾች ቤት ገባን። መውጫ መንገድ አጥቼ እዚህ መሞቴ መሆኑ ካልቀረ ብዬ ወደ ሱቅ ተመልሼ ጄኔሬተሬን አብርቼ ኢንተርኔት ከፈትኩ። ጋዜጠኛ ዘላለም ገብሬን መስመር ላይ ስላገኘሁት ሁኔታውን ነገርኩት። ዜናውን ለማስተላለፍ መጻፍ ጀመርኩ። ከ20 ደቂቃ በሁዋላ እንደገና ጦርነቱ አገረሸ። ዳግም ፍርሃት ስላደረብኝ አጠፈፋሁት። ሞባይል ስልኬ በየሰከንዱ ያንቃጭላል። እንደሌለ ቀኑ እንዲህ ሆነ ሊሉኝ ሳይሆን መከበባችንን ሰላወቁ  እንዴት ሆንክ ለማለት ነው:፡ ሲሳይ ሲደውልልኝ ለነብዩ ሲራክ ደውልለት አለኩኝ። ወዲያው ሉልሰገድ ደወለልኝ። ለአሉላ ከበደ እንዲደውል ነገርኩት። << ቤቶቸቻው የተመቱባቸው ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን አውቄያለሁ ጉዳት መድረሱን ግን ማጣራት አልቻልኩም።..>> ብዬ ነገርኩት።  ቢያንስ እኛ ብንጎዳ ለሌሎቹ ወገን መድረስ አለበት የሚል አምኛለሁ።

            ሰኞ እለት ከበባው እንደለ ቢሆንም ልጆች ቤት አደርኩ። ማክሰኞ ጠዋት ድረስ በርካታ የመናዊያን መመታታቸውን አይቻለሁ። ረፈዱ ላይ ግን በመስኮት እያሾለቅን ስናይ ያስጠጉኝ ልጆች ቤት ያለበት ፎቅ ላይ ያለች ልጅ ወጥታ ስትሄድ እና ጭንቅላቷ ላይ ስትመታ አየሁ። ሮጠን ሁላችንም ወጣን። የእኔን ተውት ብርክ ያዘኝ ሮጥኩ ከምል ተወናከርኩ ብል ይቀላል። በድንጋጤ ውሀ ሆንኩ። ሀኪም ቤት በመውሰድ ሰበብ ከዛ ጦር ቀጠና ውሰጥ ወጣን። በኦፕሬሽን ጥይቱ ወጣላት። ከተማዋ ሁለት ገጽታ እንዳላት ያየሁት በዚህ ጊዜ ነበር። እኛ በጦርነት ከታገትንበት ቦታ ትንሽ ስርቅ ሰዉ ጦርነት ያለም አልመሰለው። በደስታ የወትሮውን ኑሮውን ቀጥሏል። ድምጹንም ከምንም አይቆጥሩት የሚቃጠለውን ከርቀት እያዩ <<አዲ>>ይላሉ። ያለ ነው እንደማለት ነው። አመሻሽ ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደረገ ተበለ። ረቡዕ ዕለት ጠዋት /ትላንት/ ሰላም ከሆነ ስለሁኔታው ለማጣራት፣ ቤታቸው ስለተመታባቸው ልጆች እንዴት እንደሆኑ ለማየት፣ በዛው ሱቁንም ለመቃኘት በታክሲ ተሳፍሬ ሄደኩ።ሳንደርስ መንገዱ ተዘጋ።

        ወዲያው ተኩስ ተከፈተ።   

     ተመልሼ ወደሁዋላ መንገዴን ስጀምር ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ አካባቢውን አናወጠው። ሁሉም ባለበት መሬት ላይ ተኛ። እኔ ግን በድንጋጤ ሮጨ ግንብ ስር ተሸጎጥኩ። በቅርብ እርቀት የነበረ ታንክ ተመቶ ነው ያ-ድምጽ ከትንሽ ቆይታ በሁዋላ ወይኔ መሀመድ አልዬ ተመታ የሚል ድምጽ ሰማሁና ዞር ስል ለካ አጠገቤ አንድ ኢትዮጵያዊ ነበር። በድንጋጤ አይኔ የተጠናገረ ወይ የማያይ መሰለኝ። አልታይ ስላለኝ <<የታል?>> አልኩት። ሜዳ ላይ ተዘርሯል። ተኩሱ እስኪበርድ መጠበቅ ግድ ነበር። ሲበርድ ግን አምቡላንስ አነሳው። ቀኑን ሙሉ ሰውነቴ ሲርገደገድ ዋለ። እስከመቼ ይሆን እንዲህ በስደት የምናልቀው? ይህ ሳምንት ደግሞ የመን ላለን ስደተኞች አልሆነንም። ከዛ በፊት ባለው ሀሙስ………………………………

        ባለፈው ረቡዕ እለት ምሽት <<አሳባ>>  የሚባለው አካባቢ የተጀመረው ጦርነት እንዲሁ ሲያሳስበኝ አደረ። ምክንያቱም በተደጋጋሚ ተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ በጀመሩ ቁጥር UNHCR በር ላይ ያለነውን ስደተኞች በተደጋጋሚ መተውናል። እንደፈራሁትም ሀሙስ እለት ከሰዓት በሁዋላ ሞባይል ስልኬ ደግማ ደጋግማ አንቃጨለች። ለምን እንደሆነ ሳላውቅ ውስጤ ተረበሸ።

      <<ሀሎ!!..>> አልኩ መነጋገሪያውን ተጭኜ

      <<ኡ..ኡ..ኡ…ገደሉን ጨፈጨፉን…ኡኡኡኡ!!!!..ገደሉኝ….>> የሚል ድምጽ ከተናጋሪው ጀርባ ጎልቶ ተሰማ።

       <<ሀሎ!.. ካለድ ነኝ። UNHCR በር ላይ ዛሬም ጨፈጨፉን..>> አፌ ደረቀ።

      << የምሰራበትን ሱቅ ገና ከፍቼ መግባቴ ስለሆነ ሰው ፈልጌ ጠብቁልኝ ብዬ እመጣለሁ>> አልኩና ስልኬን ዘጋሁ። ሰው ፈለኩና አስጠበቄ ታክሲ ላይ ተሰቀልኩ። ምንም እንደማላደርግላቸው አውቃለሁ። ያለኝ አቅም መጻፍ ነውና አይቼ ለመጻፍ ተጓዝኩ። አካሌን እንደሸቀጥ ጫንኩት እንጂ መንፍሴ ቀድሞ ሽምጥ ጋልቧል። ከቦታው ደርሶ እንዳለፈው በአስለቃሽ ጭስ እና በዱላ፣ በጥይት..ሲደበድቧቸው ታየኝ። ሰቀጠጠኝ። አስለቃሽ ጭሱ እንዳለፈው ጊዜ ልቤን ችግር እንዳይፈጥርብኝ ሰጋሁ።

ደርሼ ሳይ አይኔን ማመን አቃተኝ። አራት የቀይ መስቀል አምቡላንስ እየተሯሯጡ ጉዳት የደረሰበትን ወደ ህክምና ይወስዳሉ። እንዴት ዛሬ ሰው መሆናችን ታወቃቸው? እንዴት ዛሬ ሊረዱን መጡ? እስከዛሬ ወደ 10 ጊዜ ስንደበደብ የት ነበሩ? አሁን ያላስታወሰኳቸው ጥያቄዎች ሁሉ ተግተለተሉ። አንድ በእድሜያቸው ሀምሳዎቹን ሊያሰናብቱ ጥቂት የቀራቸው ኤርትራዊት ስደተኛ ወታደሩ በሰደፍ ሲመታቸው በቁመታቸው ዝርግፍ ሲሉ አየሁ። ሮጨ ልሻገር ስል አስፈራራኝ። ፍርት፣ስቅቅ ብዬ ተመለስኩ። ለካ ይህን ያህል ፈሪ ነኝ እሰክል ወድቀው እያየሁ በመመለሴ ራሴን ታዘብኩት። ግን ምን ማድረግስ እችል ነበር? ያለኝ አቅም ማዘን ነው እና አዘንኩ። በእልህ ደሞ እንባዬን ፈነጠኩ።    

      ወደቅርብ ርቀት የሄደው አንድ አንቡላንስ ወዲያው መለስ አለና ተጠጋቸው። እኔም ተጠጋሁ። ሲያነሱዋቸው ደስ አለኝ። ሌሎቹን እያባረሩ ሌባና ፖሊስ የሚጫወቱ መስለዋል። ወዲያው ቀይ መስቀል ሰዎች ወጡና ለምን የመታሉ? የሚል ነገር አነሱና ነገሩ በረደ። የሚያሳዝነው ግን በዛን ቀንም ከልጆቹ የሰበሰበኩት መረጃ እና የቀይ መስቀል ሰራተኛዋ የነገረችኝ አንድ አይነት መረጃ ነበር። 33 ሰው ጉዳት ደርሶበታል። ከሌላው ጊዜ የሚለየው በጥይት ሳይሆን በሰደፉ እ በዱላ ነበር የተማቱት። 

       የሚገርመው ግን  UNHCR ቢሮ ሰራተኞች አሁንም የተለመደው ቅጥፈታቸውን አሰሙ። የአካባቢው ሰው ስላለፈለጋችሁ ሊያሰነሳቸሁ ወታደሮቹነ አመጣ አሉ። ይሁን ያምጣ ቀይ መስቀል ለምን የመታሉ ብሎ እንደጠየቀና እንዳይመቱ እንዳደረገው ለምን አልሞከሩም? የ UNHCR ቢሮ ሁሌ ለኢትዮጵያን ስደተኞች ያለው አመለካከት የተዛባ ነው ለምን? ለምን መፍትሄ ይሰጠን ባልን ዱላ ያሰጋብዘናል? የመን ያለን ኢትዮጵያዊያን መከራ አላልቀ ብሏል። በኤምባሲ በኩል ያለውስ ወገኖችን ማሰቃየት ችግር እንዴት ነው? እምለስበታልሁ።

                                              ቸር  እንሰንብት

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on September 22, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.