የመለስ የጋምቤላ ጉብኝት

(በኦቦኒ ኦኮቺ)

ሙሰኞች በዙ። ፍትህንም ሰቀሉዋት። አገሪቱን ህገወጥነትና ስርዓት አልበኛነት ወረራት። የሃብት፣ የንብረት፣ የገንዘብ፣ የዝርፊያ ኑሮ! መንግስት ለመንግስት ጉቦ መስጠት ጀመረ። መንግስት የሰጠውን በጀት ማስገበር ልማድ ሆነ። ሁሉም በየደረጃው በሙስና ተጨመላልቀው መንበራቸው ላይ የተቀመጡ ፍትህን ረገጡዋት። ሙስና በጋምቤላ ፍትህን ሲሰቅላት አየን። ይህንን ማስታወሻ የጻፍኩት እዛው ጋምቤላ ተቀምጬ ነው። ወደፊትም እጽፋለሁ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ረሃብ ገብቷል ተብሎ ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ለስራ ጉብኝት ወደዚያው አምርተው ነበር። የግብርና ሚኒስትራቸውን አስከትለው እስፍራው የደረሱት መንግሥቱ ዙሪያ ገባውን ሲመለከቱ አገሩ ለም ነው። አንድም የደረቀ ነገር አላዩም። እንዲህ ያለ ለም ቦታ ለበቆሎ፣ ለስንዴ፣ ለገብስ፣ ለማሽላ . . . አንዴት ለገመ? እያሉ የግብርና ሚኒስትሩን ማብራሪያ እየጠየቁ ማሳ ውስጥ ገቡ።

በቀረበላቸው ማብራሪያ ያልተደሰቱት ጓድ መንግሥቱ፣ ሲረግጡት ትሙክ፣ ትሙክ የሚለውን አፈር ቆንጠር አድርገው ቀመስ አደረጉና “ይሄ አፈር በቆሎ አያበቅልም?” ብለው ለግብርና ሚኒስትሩ አቀመሱዋቸው። የግብርና ሚኒስትሩም “አሳምሮ” በማለት አፈሩን እያጣጣሙ መለሱ። ታዲያ ይህ ቀልድ የተቀለደው “ለብሄር ብሄረሰቦች መብትና ልዕልና አጥንቴን እየከሰከስኩ ነው” እያለ ከበረሃ የሚያነባው ወያኔ በትረ መንግስቱን ሳይጨብጥ ነበር።

ደደቢት ተረግዞ፣ ትግራይን ነጻ ለማውጣት ትግል የጀመረው ወያኔ ባላሰበውና ባልጠበቀው መንገድ ህዝብ የከዳውን ደርግ ወደ መጣሉ ሲዳረስ መንገድ ላይ ያገኛቸውን ሁሉ እንደ ደራሽ ውሃ እየሰበሰበ የጭቃ ያህል ጠፍጥፎ እየሰራቸው “ኢህአዴግ” ሆነ። “የዘመናት ብሶት የወለደው” እያለ በብሄሮች ስም እየተገዘተ መንግስት ለመሆን በቃ። በጊዜያዊ፣ በሽግግር መንግስት፣ ብሎም በምርጫ እየተውገረገረ ዛሬ ላይ ደረሰ። ሃያ አንድ ዓመት። የጠፈጠፋቸውን አሻንጉሊቶች በየክልሉ ረጨና ኢትዮጵያን በጥፍሮቹ ነክሰው ያዙ።

ይህ የተባለ፣ የሚታወቅ፣ ማንም የሚረዳውን እውነት ያስቀደምኩት ሰሞኑን ከጋምቤላ አካባቢ የሚነፍሰውን ንፋስ በተመለከተ የማውቀውን ለማለት ነው። “ፓርቲያችን ከእንጥሉ በስብሷል፤ ገምተናል” በማለት የትግል አጋሮቻቸውን ያመነዠጉት አቶ መለስ ሰሞኑን ወደ ጋምቤላ ምን ታያቸው? ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት በጥይት የተቆሉት የአኙዋክ ንጹሃን ደም እንዴት ታወሳቸው? አስከሬናቸው በየጥሻው የወደቀውና የውሻ ሞት እንዲሞቱ የተፈረደባቸው አኙዋኮች ለምን አጀንዳ ሆኑ? ሁለት ሳምንት ፈጀ የተባለው ግምገማስ እንዴት የእስስት መልክ ያዘ? የሚሉትና ተመሳሳይ ጉዳዮችን ትኩረት የማደርግባቸው ይሆናሉ።

የሰሞኑ ግምገማ አጀማመሩ ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ትግበራና የትግበራው ጉድለት፣ የአካባቢው ሰላም ችግርና አኩርፈው ጫካ የገቡ የአኙዋክ ልጆችን አባብሎ ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነበር። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በስም ዘርዝሮ የግምገማውንና አስገምጋሚዎቹ የተወኑትን “የቀለጠው መንደር” ድራማ ዝርዝር አጠር አጠር እያደረኩ ላሳይ።

በጋምቤላ ፍትህ፣ ግምገማ፣ አስገምጋሚና የንጹሃን ደም ከሙስና በታች ናቸው

ጋምቤላ በሙስና ምጣድ ላይ የምትቆላ ጥሬን ትመስላለች። “ህንድ ጨብጦ ሲለቅህ ጣቶችህን ቁጠር” የሚለው ተረት በጋምቤላ በስፋት እየተተረተ ነው። ለምን ቢሉ ሙስናው ኪስ ገብቶ የመስረቅ ያህል ያፈጠጠ በመሆኑ ነው። ህንጻ ተገንብቶ ርክክቡ ሳያልቅ ይሰነጣጠቃል፤ ይዘማል። አዲስ ህንጻ ተሰርቶ ሲመረቅ ውለታው ስንጥቅ ያለበት እንዲሆን አስገዳጅ ህግ ያለ ይመስላል። ቀዳዳዎቹንና ስንጥቅጥቆቹን ህንጻዎች እያዩ “አይታይም” የሚሉት የክልላችን ልጆች፣ መሪዎችና፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪ ተብለው የተመደቡ የዋናው መንግስት መልዕክተኞች በተዋረድ በሚቀራመቱት የክልሉ አንጡራ ሃብት አይናቸው ስለተደፈነ ነው።

በርካታ የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች አሉ። በለብ ለብ ጭቃና ጠጠር እየፈሰሰ የሚሰራው መንገድ ጥራቱን ጠብቆ እንደተገነባ በማስመሰል ርክክብ ለሚፈጽሙት ብር፤ ለዋናው ንጉሳችን ደግሞ በጥሬው ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ የቱባዎቹን ሃብታሞች መኖሪያ እንዲቀላቀሉ ካንትሪ ክለብ እንደ አይናፋር ሴት የተሽኮረመመ ቪላ ተበጅቶላቸዋል። ሌላም አለ። በነገራችን ላይ መንገዶቹን ከዋልታ ተመድበው የመጡ ጋዜጠኞች “ሽሮ ፈሰስ” የሚል ስም አውጥተውላቸው ነበር። በሚስጢር!!

በጨረታና በግዢ ከሚዘረፈው ገንዘብ በላይ አሳሳቢው በምድራቸው ከተፈጥሮ ጋር እየታገሉ የሚኖሩትን ህዝቦች ክፉኛ የሚፈታተንና ጣጣው ህይወትና የእለት ከዕለት ኑሮ የሚፈታተነው የመሬት ንግድ  ነው። መሬት በጋምቤላ እንደ ቅርጫ እየተሸነሸነ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተፈጥሮ ሃብቷን እየበላ እየተቆመረበት ነው። አገር እንደሚያውቀው “ባለሃብት” ተብለው ሰባ ከመቶ በላይ መሬት የተቀራመቱት የአንድ ብሄር አባላት ናቸው። የዋናዎቹ ዘሮች!! ይህ የሚደረገው ደግሞ በግልጽ ባደባባይ በፖለቲካ መዋቅራዊ ትዕዛዝና አይን ባወጣው ሙስና ነው። እንዲህ ይዘፈንለታል “አይተሽኝ ነው ባይንሽ ወይስ በቴሌቪዥን ሙሰኛ ሙሰኛ ብለሽ የወቀስሽኝ” የዋልታ ጋዜጠኞች ዘፈን ነው።

ከዋልታ ጋዜጠኞች ጋር ጎን ለጎን የሚተላለፈው የፌደራሉ አማካሪ፣ ዛሬ ስራውን ትቶ እዛው መሬት ወስዶ ብር እንደ በቆሎ ገለባ የሚሸለቀቀው በዛው በፖለቲካው ደልዳላ ወንበር ላይ ተቀምጦ “ፈርም፣ እዘዝ፣ ወስን…” እያለ ትዕዛዝ በማሰጠት ከብሮ ከፖለቲካ ንግድ ወደ ኢንቨስተርነት ተሸጋግሯል። ስሙን እንዳልጠራው ስቅ ይለዋል ብዬ አልፈዋለሁ። ጋምቤላ ገብቶ አለሙን ያየው ኮንትራክተርም “የፕሬዚዳንቱ ኪስ” ተብሎ የተሰየመው ከዛው እንደተፈጠሩ ካሉትና አቶ መለስ ዘወትር ያለፉትን ስርዓቶች እየረገሙ ከሚምሉበት የተረሳ ህዝብ ላይ በመዝረፍ ነው።

ካማካሪውም፣ ከኮንትራክተሩም፣ ከግል ኮሌጁም ጠቃቀስኩ እንጂ በጋምቤላ ያለው ንቅዘት በቃላት የሚገለጽ አይደለም። በዚህ እሳቤና እውነት ነበር ግምገማው ሲጀመር ፕሬዚዳንቱና አብረዋቸው በብር የዋኙ፣ በወንጀል የተሻተቱ፣ ፍትህ በማጉደል የገለሙ፣ የተፈጠሩበትን ህዝብ እርቃኑን ጥለው በዝርፊያ የተጨመላለቁ የደነገጡት።

እንደ ሁሴን ቦልት ፍጥነት የፕሬዚዳንቱን ጎዶሎ አመራርና ከላይ የተዘረዘሩትን ሃጢአቶች በየተራ እንደ መብረቅ ማውረድ የጀመሩት የፓርቲው አባላት ስሜት ክፉኛ የተቆጣ ስለነበር ፕሬዚዳንቱ የስብሰባው አዳራሽ ቁና ሆነባቸው። ባላቸው የባለሃብቶችና የዋናዎቹ መሪዎቻችን ድጋፍ ጋዳፊን ሆነው የነበሩት አቶ ኦሞት ብርክ ያዛቸው። ስራ አስፈጻሚው ስላመረረ አስገምጋሚዎቹ ሊሸፍኑት የማይችሉት ሆነባቸውና በመጀመሪያ የአራት ቀናት ተከታታይ ግምገማዎች ፕሬዚዳንቱ ከነምክትላቸው ተሽቀንጥረው እንዲጣሉ ተወሰነ። ሌሎች ሶስት አመራሮችም ተመሳሳይ ብይን ተበየነባቸው።

ጋምቤላ ቸኮላታ

በግምገማው መጀመሪያ ቀን ቀልባቸው ጥሏቸው የኮበለለው ፕሬዚዳንቱ ውስጥ ውስጡን የማፈግፈግ ስልት በመጠቀም ስራቸውን ይሰሩ ጀመር። ነጋዴዎችም ፕሬዚዳንቱ ከተነኩ ንግዳቸው እንዳይኮላሽ ሰጉ። በየቢሮው በልማትና በኮንስትራክሽን ሰበብ የዘረጉት የብር ማፍሰሻ ቱቦ እንዳይነጥፍ ጨነቃቸው። ምናልባትም ቀጣዩ ሂደት “ውሾን ያየ . . .” እንዳይሆን ተርበተበቱ። ዋናዎቹ የሄክታር ተዋናዮችም አይናቸው ውስጥ አዋራ የገባ ያህል ጉዳዩ ለበለባቸው። እናም ተሰባሰቡ።

የፕሬዚዳንቱ የወቅቱ አማካሪ ቀን ቀን አስገምጋሚ፣ ማታ ማታ የመዋጮ አሰባሳቢ ሆኑ። በዚህ ግምገማን በሙስና “የመድፈቅ” ዘመቻ የተሰራው ስራ ግምገማው በተጀመረ በስድስተኛው ቀን ከላይ በዋናዎቹ ባለሃብቶች ተጽዕኖ፣ በቅርብ በሚሊዮኖች በቀረበ የአፍ ማዘጊያ መስዋዕት የግምገማው ሰብሳቢ አቋም ተቀየረ። ሃይለቃል መናገር ጀመሩ። አስተያየት የሚሰጡትን በዱላ መደብደብ ጀመሩ። ተለጉመው የነበሩት ፕሬዚዳንቱ አንደበታቸው ተላቀቀ። ከመሸማቀቅ ወደ ማሸማቀቅ ተዛወሩ። ሙስና መናገር ስትጀምር ግምገማ ጸጥ አለች። ፍትህ በነነች። ይህንን ጽሁፍ እስከጻፍኩበት እለት ድረስ የመፍራትና የመትባት ነገር ቢኖርም አዲስ ነገር ይኖራል የሚለው የኛም፣ የሁሉም ፍትህ ናፋቂዎች ጉጉት ነው።

ፍትህን ጉቦ አንጠልጥሏት ስታጣጥር፣ አሸናፊ የሆኑት አቶ ኦሞትና ድራቸው “ጋምቤላ ቸኮላታ” እያሉ እየዘፈኑ ነው። የጋምቤላ ህዝብ ግን ከቤቱና ከተወለደበት ቀዬው በገዛ ልጆቹ እየተሰደደ ነው። ሌሎች በረሃ የሆነውን አገራቸውን ሲያለሙ የጋምቤላን የተፈጥሮ ደን እየተጨፈጨፈ ነው። ውድ የአኙዋክ ልጆች ተጨፍጭፈው፣ የተረፉት ለልመና ተሰደው፣ የተቀሩት በዱር መሽገው እነ ባለስልጣኖች ደሙን ረግጠው “ቸኮላታ” ይላሉ። ውስኪ እየጨለጡ ያሽካካሉ። ወይ ነዶ!!

የአቶ መለስ ጉብኝት በጋምቤላ!

“በብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ አትምጡብኝ። የብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ የማንደራደርበት መሃላችን ነው። የታጋዮች ደም ይጮሃል። የታጋዮች አጽም ይወጋናል።. . .” እያሉ ሲምሉና ሲገዘቱ የኖሩት አቶ መለስ የጋምቤላ ጉብኝት ያካሄዱት በተላላኪዎቻቸው ነው። ተላላኪዎች ያዛሉ። ታዛዦቹ የራሳቸውን ህዝብ ደምና የተፈጥሮ ሃብት እያለቡ ለሌሎች ይግታሉ። ሰሞኑን የተካሄደው ግምገማ ‹‹የመለስ ጉብኝት›› የተባለው መለስ አጀንዳ በማስቀመጣቸው ነው። አጀንዳው ራስን ነጻ የማውጣትና ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚያወጣውን ሪፖርት ለመከላከል የመስዋዕትነት በግ ለማዘጋጀት ነው።

ለዚህም ምክንያቴ ከዘጠኝ ዓመት በፊት በአኙዋክ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በተመለከተ በግንባር ቀደምትነት እየተወነጀሉ ያሉት አቶ መለስ ሃጢአቱን በተባባሪዎችና በታዛዦች ላይ ለመለጠፍ መንፈሳቸውን ልከው ጉዳዩን በማንሳት ቅኝት ማካሄዳቸው ነው። የወንድሞቻችንን ደምና ደመኛ አጀንዳ ያደረጉትና በጨረፍታ እንዲሰማ ማድረግ በአካል ከመገኘት በላይ ነው።

በግብርማ አቶ መለስ ጋምቤላን የሚያውቋት በተላላኪዎቻቸውና አፈሯን ሊበሉ ባሰቡ ባለሃብት ተብዬዎች በሚቀርብላቸው ጨረታ ብቻ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነማ አቶ መለስ እንደ መሀላቸው አገልድመው ሃመርና ገለብ፣ማጠቃለያ ጋምቤላና ቦረና ገብተው “የሐመሯ ወጣት”እያሉ ባዜሙ ነበር።

ዱር የገቡት አኙዋኮች

የወገኖቻቸው ደም ጎፍንኗቸው የአኙዋክን ዱር የተቀላቀሉት ወጣቶች በግምገማው  ፕሬዚዳንቱን በመወንጀል  የጭፍጨፋው ተጠያቂ ለማድረግ የተሞከረው ሙከራ በድንገት አምልጦ የወጣ ሳይሆን “ማስወራት” ቀጥሎም “መተግበር” የሚለው የወያኔዎች ጨዋታ እንደሆነ የተነቃ ይመስለኛል። በግምገማው የጥፋተኛነት ተኩስ የተተኮሰባቸው አቶ ኦሞት ያዘዙዋቸውን፣ መሳሪያና ወታደር የላኩላቸውና ለታጠቡበት ወንጀል ደም የቀዱላቸውን አቶ መለስንም ተጠያቂ እንደሚሆኑ ሲናገሩ በኩራት ነበር። ሙስናው ታክሎበት ግምገማው የተገለበጠው ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። ጠርጥር ከገንፎም አለ ስንጥር። ለጉዳዩ ቅርብ እንደመሆኔ ይህ የተነካካው ጉዳይ በቅርቡ ይነጥራል። ዱር የገቡትም ቢሆኑ የተሸሸጉበት ጫካ እንደ ባሌጎባ ደን ቤንዚን ተርከፍክፎ ካልጋየ በስተቀር መውጫ ያላቸው አይመስልም።   

ማጠቃለያ  

ጓድ መንግሥቱ አፈር ቀምሰው አቀመሱ ተብሎ የተቀለደውን ቀልድ ያነሳሁት ወድጄ አይደለም። መንግሥቱ አፈሩን የቀመሱት ጨንቋቸው ነው። አረንጓዴ አገር እንዴት ረሃብ ገባው ብለው ነው። ይህንን ስል ላሞካሻቸው ፈልጌ ወይም በመሪነታቸው አድናቆት ልቸራቸው ፈልጌ ሳይሆን ዛሬ ያገራችንን መሬት በባንዳና በተላላኪ ለባዕዳን በመስጠት የሚካሄደውን ዝርፊያ ለማሳየት ነው።

የጋምቤላ ህዝብ እንዳይኖር ግራ እየተጋባና ደሙን እየተመጠጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሂውማን ራይትስ ዎች ይፋ ያደረገውን ሪፖርት ለመከላከል መለስ የጀመሩት መንፈራገጥ “እኛም አለን ሙዚቃ” እንድንል ረዳን። አቶ ኦሞት ከተተኮሰባቸው ጥይት ተረፉ። ሙስና ተናገረ። በጋምቤላ ፍትህ ተሰቀለ። መንግስቱ አፈር ቀምሰው አቀመሱ። የዛሬዎቹ ደግሞ የጋምቤላን ህዝብ ደምና አጥንት፣ መሬትና ደን ተምነሸነሹበት። ደግሜ እላለሁ “ሙስና በጋምቤላ አፍ አወጣ፣ ፍትህንም አኮላሸ”!!

በኦቦኒ ኦኮቺ E-mail: oobonni@yahoo.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 18, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.