የሒላሪን እውነቶች፤ለኛ ውሸታሞች

ሉሉ ከበደ |

ቀኑን በስራ የዛለ ሰውነቴን ላሳርፍ አልኩና፤ የሁለት ዓመት ህጻን ልጄ አልፋን ይዤ ወደ መኝታ ቤት ገባሁ። ደንገዝገዝ ያለ ውሀ ሰማያዊ ብርሀን የሚሰጠውን የመኝታ ሰዓት መብራት አበራሁና በጀርባዬ አልጋ ላይ ተንጋለልኩ። ልጄ አልፋን ከአዲሷ አሻንጉሊቷ ጋር ደረቴ ላይ አድርጌያት፤ እሷም ከደረቴ ወደ አልጋው፤ ካልጋው ወደ ደረቴ እየተመላለሰች ባሻንጉሊቷ ስትጫወት፤ ቀኝ እጄን ግንባሬ ላይ አሳረፍኩ። ትራሴን ከፍ አድርጌ፤ አራት ባራት በሆነችው መኝታ ቤት ውስጥ ከፊት ለፊቴ ግርግዳ ላይ የተሰቀሉ ስዕሎችን እመለከት ጀመር። ከሁሉ ጎልቶ የሚታየው በሀገሬ ባንዲራ ከፈፍ ዙሪያውን ተሰግጦ ያማረው ትልቁ የኢትዮጵያ ካርታ ነበር።

በመላእክቶች ስእል ተከቧል። በግራና በቀኝ ሚካኤልና ገብርዔል አሉ። ሚካኤል ጎራዴውን እንደሰበቀ፤ ላይና ታች ቅድስት ድንግል ማርያም። ዘወትር ወደመኝታ በሄደች ቁጥር፤ እኒያን መላእክት “ኢትዮጵያን ጠብቁ” እያለች፤ በጸሎቷ አደራ የምትላቸው ባለቤቴ ነች። ስዕሎቹንም ቢሆን በኢትዮጵያ ዙሪያ ሆን ብላ የሰበሰበቻቸውም አራሷ ነች። በዚያው የሀገር ትዝታ ተቀሰቀሰና ያን ሳወጣ ያን ሳወርድ፤ ልጄም ደረቴ ላይ ስትመላለስ፤ ስትጫወት፤ ሸለብለብ አደረገኝ። ለጊዜው ካለሁበት እየራቅሁ እየራቅሁ ሔድኩ …

ስልክ ይጮሀል። አነሳሁት። “ ሀለው ” አልኩ።

“ እባክዎ አቶ ዜጋን ማናገር እችላለሁ ? ’’ አለ ሰምቸው የማላውቅ እንግዳ ድምጽ።

“ ነኝ ማን ልበል ጌታዬ ? ”

“ አቶ እንቶኔ እባላለሁ። የምደውለው ከጠቅላይ ሚኒስሩ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ነው። ዛሬ ከሰዓት በሗላ የህዝብ ተወካዮችና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉበት አገራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ውይይት ስለሚደረግ ንግግር እንዲያደርጉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጋብዘዋል”

እነዚያን ሰዎች “እንዲህ ሁኑ” ብዬ በግንባር ለመንገር ካለኝ ጉጉት የተነሳ፤ ጊዜውንና ቦታውን ብቻ ነበር የጠየኩት። ወዲያውም ወደ ጠረጴዛ ሄድኩና ስለማደርገው ንግግር ማሰላሰል ጀመርኩ። የቱን ተናግሬ የቱን እንደምተው ግራ ገባኝ። ሌላ የተሻለ ሀሳብ መጣልኝ። ሂላሪ ክሊንተን በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ ለአፍሪካ ህብረት መሪዎች እጅግ ወቅታዊ መልእክት ያዘለ ንግግር አድርገው ነበር። ከንግግራቸው ውስጥ ለኛ ሰዎች የሚስማማውን ነቅሼ አውጥቼ፤ ልዋሳቸው ወሰንኩ። ያንን ጠራርቤ እሳቸው ላጠቃላዩ ያሉትን እኔ ደሞ ለኛዎቹ አዙሬ፤ ንግግር ላደርግ በጽሁፍ አዘጋጀሁ። እና በተባለው ቦታና ሰዓት አዲስ አበባ የተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ተገኘሁ። አዳራሹ ከዳር እዳር በህዝብ ተወካዮች ተሞልቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ዋና ዋና ባለስልጣናት አፈጉባዔውን ጨምሮ ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል። አፈጉባኤው ስብሰባ ይመራሉ። በንግግሩ መካከል ሀሳብ መስጠት ይፈቀዳል። የተያዘልኝ ሰዓት ሲደርስ ንግግሬን ጀመርኩ።

“ዛሬ በሶስት ጉዳዮች ላይ ባጭሩ ለመነጋገር እፈልጋለሁ። ለሕዝባችንም ሆነ ለናንተ አጽንኦት የሚሹ ጉዳዮች። በተወካዮች ምክርቤትም በኩል ረብ ያለው እርምጃ እንደምንራመድ ተስፋ አደርጋለሁ። ዲሞክራሲ፤ ኢኮኖሚ፤ ሰላምና ደህንነት። እርግጥ እነዚህ ጉዳዮች ላፍሪካ ህብረትም ዋና የትኩረት አኳያዎች ናቸው። ምክንያትም አለው። ለሚያድግ አሕጉርና ሐገር እነዚህ ሶስቱ ጉዳዮች በጣም መሰረታዊና አስፈላጊ ናቸው። እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች የእያንዳንዱ አገርና ነዋሪ ህዝብ በመተባበር ሊሰራላቸው የሚገባ ጉዳዮች ናቸው። ሶስቱም ደግሞ ትግልና ፈተናም አላቸው። መልካም አጋጣሚዎችንም ያመጣሉ። ሀላፊነትንም ያስከትላሉ።

ዲሞክራሲ፤ ይህ ወቅት ላፍሪካ ዲሞክራሲ መነሻ ወቅት ነው ብዬ እንድጀምር ይፈቀድልኝ። ከሰሀራ በታች ከግማሽ በላይ የአፍሪካ ሀገሮች ዲሞክራሲያዊ የሆነ ህገመንግስታዊ መድበለ ፓርቲ አስተዳደርን ይደግፋሉ። ይቀበላሉ። እንደቦትሰዋና፤ ጋና፤ ታንዛኒያ ጠንካራ ተቋማትንና ሰላማዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን ለመገንባት አስርታት ዓመታትን አሳልፈዋል። እነዚህ የጠቀስኳቸው ሀገሮች ናሙናዎች ናቸው። ለጎረቤቶቻቸው ብቻም አይደለም። በየትም ላሉ ሀገሮች ሁሉ’’

አንድ የምክር ቤት አባል እጃቸውን አወጡና እንድናገር ይፈቀድልኝ አሉ። እንዲቀጥሉ በጄ ምልክት ሰጠሗቸው። ወደ አፈጉባዔው ተመለከቱ። “ይቀጥሉ “ ተባሉ።

“እውነት ነው የምትለው ” አሉ ተወካዩ ወደኔ እየተመለከቱ፡ ቀጠሉና “ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ብርቱ ጥረትና በኛ በህዝብ ተወካዮች ፍጹም ትብብርና ድጋፍ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄር ብሄረሰቦች እንደፈለጋቸው ተናግረው መግባት እንዲችሉ፤ የራሳቸውን እድል በራሳቸው መወሰን እንዲችሉ ለማድረግ እኛም ይህን የመሰለ ዲሞክራሲ ለመገንባት ሁለት አስርታትን ተጉዘናል። ባሳየነው ውጤት ከሁሉ በፊት የዓለም ሞዴሎች ተብለናል። ከላይ የጠቀስካቸው ያፍሪካ ሀገሮች ሁሉ ከኛ ተምረው እነሱም ዛሬ እንደምሳሌ ለመጠቀስ በቁ። ከሁሉም ግን የመጀመሪያዎቹ እኛው ነን … አመሰግናለሁ “

አዳራሹ በጭብጨባ ተናጋ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናጋሪውን ፈገግ ብለው ተመለከቷቸው። ተናጋሪውም የምክር ቤት አባል “ተሳስቸ ይሆን ?’’ በሚል አይነት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመለከቱና የሰውየውን ፈገግ ያለ ፊት ሲያዩ ደስስስስ አላቸው።

ጭብጨባው ጋብ እንዳለ እኔም ንግግሬን ቀጠልኩ “እነዚህ ብቻም አይደሉ እናንተን በአርአያነት የተከተሉ፤ ሌሎች ያፍሪካ ሀገሮችም ጠቃሚ እርምጃ እያሳዩ ነው። የበለጠ ልትኮሩ ይገባል “አጨበጨቡልኝ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ። እኔም ደስ አለኝና ንግግሬን ቀጠልኩ።

“ናይጄሪያ ውስጥ ፕሬዚዳንት ዮናታን በናይጄሪያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ አግባብነት አለው በተባለለት ምርጫ አሸንፈው ስራ ጀምረዋል። ቤኒንና ማላዊ ውጤታማ ምርጫ አካሂደው ቀደም ሲል የነበራቸውን የመድበለ ፓርቲ ፉክክር ይበለጥ አዳብረዋል። የኬኒያ ዲሞክራሲ ባለፈው ዓመት ባዲሱ ህገመንግስት ላይ በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ፤ ወደ ላይ ከፍ የሚያደርገውን ካብ ገንብቷል። ሕዝበ ውሳኔው የተካሔደው ያለ ሑከትና ብጥበጥ ነበር። የመብት ረቂቅ ሕጎች፤ የስልጣን ገደብ፤ ያካተተው ሕገመንግስት በከፍተኛ ድምጽ ነው ያለፈው። ኒጀርና ጊኒ በቅርቡ የገጠማቸውን ወታደራዊ ግልበጣ አልፈው ባለፈው ዓመት የተሳካ ምርጫ አካሂደዋል። በኳትዲቮር ምርጫ 2010 ን ተከትሎ የተከሰተው ቀውስ በአፍሪካ ህብረት እርዳታ መፍትሄ አግኝቶ አሸናፊው ተመራጭ አሁን ፕሬዚዳንት ሆኖ በማገልገል ላይ ነው ’’

አሁንም በድንገት ንግግሬን ሳልጨርስ ከምክር ቤቱ ሌላ ጥግ አንድ ተወካይ እጅ ሲያወጡ ተመለከትኩ። አገጬን ከፍከፍ አድርጌ ምልክት አሳየሗቸው። ገባቸው። ይቀጥሉ ማለቴ ነበር። እኔው ተናጋሪ እኔው የስብሰባ መሪ ሆንኩና አረፍኩት።

“ ስለ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ አንድ ነገር መናገር ፈልጌ ነው ‘’ አሉና ተወካዩ መጀመሪያ ወደጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚያ ወደኔ ተመለከቱና፤ “ እችላለሁ ወይ” በሚል አይነት እንደገና ወደጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመለከቱ “ ይቀጥሉ ” አልኩ።

“እርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በዚህ ምክር ቤትም ሆነ በሬዲዮ በቴሌቪዢን ካሁን በፊት እንደሚታወቀው ከሁለት ጊዜ በላይ አልመረጥም። አልችልም። በቃኝ። ስልጣኑን ሌላ ሰው ይረከበኝ። እኔ ብቻ አይደለሁም በዚህች አገር ውስጥ ያለሁት። እያሉ ዘወትር እዚህ ምክር ቤትም ሆነ ህዝቡን ደጋግመው ቢለምኑም ሕዝቡ ደግሞ ከሳቸው የተሻለ ሰው ወይም የተስተካከለ እንኳ ፈልጎ በማጣቱ፤ መልሶ መልሶ እንዲመሩት እየመረጣቸው፤ እያስገደዳቸው ማለት ይቻላል ሀያ ዓመታት ተጉዘናል። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በቅን መንፈስ ሀገራቸውን ከማንም በላይ አገልግለዋል። ወደፊትም ኢትዮጵያ ውስጥ እሳቸውን የሚመጥን ስለማይኖር፤ ሕዝቡ ካውሮፓ ወይም ካሜሪካ መሪ በኮንትራት እስከሚቀጥር እሳቸውኑ መምረጡ ስለማይቀር፤ ለሚመሩን የወደፊት ጊዜም በቅድሚያ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።“

አዳራሹ ተናጋ። ረጅም ጭብጨባ። የምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ከመቀመጫቸው ተነስተው ጭብጨባ ቀጠሉ። ፉጨትም ተከተለ። ይባስ ብሎ ጭፈራ ተጀመረ። ባልታሰበ ፍጥነትና ቅልጥፍና የምክር ቤት ተወካዮች በሙሉ የየአካባቢያቸውን ባህል ጭፈራ ተያያዙት። ትግሬው ወደ ላይ እየዘለለ፤ ብብቱ ስር ያለውን ከበሮ እንደሚደቃ፤ በባዶው እየመታ፤ ኦሮሞው ገሚስ ያንበሳ ጎፈሩን እየነሰነሰ፤ ገሚስ ወተት እንደሚንጥ በባዶው እያስመሰለ ሲወዛወዝ፤ አማራው ወገቡን በሁለት እጆቹ ግጥም አድርጎ ይዞ ዋንጫ ልቅለቃ እስክስታውን አያስነካ፤ አፋሩ ባንድ አጁ ወገቡን ይዞ በሌላው ጩቤውን እየወዘወዘ ወደላይ ወደላይ እየዘለለ፤ ሌሎቹም … ሁሉም … ምክር ቤቱ ባንድ አፍታ ስልት በሌለው የጥምቀት ጭፈራ ትርምስምሱ ወጣ ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያንን ደስታ ይሁን እብደት ውሉ የማይታወቅ ነገር ከመድረክ ላይ ሆነው ቁልቁል ትንሽ ከተመለከቱ በሗላ ምን እንዳናደዳቸው፤ ምን ደማቸውን እንዳፈላው አይታወቅም ብቻ ከዚያ አጭር ሰውነታቸው ይወጣል በማይባል ነጎድጓዳማ ድምጽ፤

‘ በቃ!’. አቁም! ” ብለው ሲያዝገመግሙ ያ ሁሉ ናላውን ስቶ ይጨፍር የነበረ ጎበዝ፤ በመብረቅ የተመታ ያክል ወይም ደግሞ እንደሙጃ ከግሩ ስር የታጨደ ይመስል በቂጡ ቁጭ ዝም አለ። ባልታሰበ ቅጽበትና ሁኔታ እንደገና ምክር በቱ የመቃብር ያክል በሚከብድ ዝምታ ተዋጠ። የሚያስፈራ የዝምታ ድባብ አዳራሹን ወረረው።

እኔን ያስደነቀኝ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምትሀታዊ ሐይል ነው። ያን ሁሉ ጎበዝ በሪሞት ኮንትሮል እንደሚንቀሳቀስ አሻንጉሊት ባንዲት ቃል ቁጭ ብድግ የሚያደርጉት፤ የሚገሉት የሚያነሱት፤ ምንኛ መለኮታዊ ሀይል ቢታደሉ ነው አልኩ። እና በፍርሀት እየተቁለጨለጩ የጌታቸውን አይኖች ለምህረት የሚለምኑ የሚመስሉ አንድ ሺህ አይኖችን ተመለከትኩና ሰላም ላወርድ ብዬ መንፈሴን ያወከው ረጅም ጭብጨባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይበቃችሗል” ከቆመ በሗላ ንግግሬን ቀጠልኩ።

‘’እነዚህ ከቅርቡ የአፍሪካ ዲሞክራሲ ግኝቶች ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው። በበርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ያለውን መሻሻል ሙሉ ዝርዝር ለማቅረብ ዛሬ ያለንን ጊዜ ሁሉ ይፈጃል። የዲሞክራሲ ተቋማት እየተጠናከሩ ነው። ነጻ መገናኛ ብዙሀን አሉ። ፍትህን ያለ አድሎ እኩል የሚያዳርሱ አካላት አሉ። የሚታመኑ የህግ አውጭዎች አሉ። ለነዚህ በብርቱ ጥረት ለተገኙ ውጤቶች ተመስጋኞቹ ህዝቡና የነዚህ አገር መሪዎች ሊሆኑ ይገባል። ሕዝቡም ከልቡ በጽናት አንዳንዴም እራሱን ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ መሪዎች ሕግን እንዲያከብሩ፤ እንዲጠብቁ፤ የምርጫ ውጤትን እንዲያከብሩ መብትና ነጻነትን እንዲያነግሱ በመጠየቁ ነው“

“ይህን መልካም እርምጃ እያደነቅን ባለንበት ሁኔታ ብዙ ያፍሪካ ህዝቦች ደግሞ በግለሰቦች የረጅም አመታት አገዛዝ ስር መኖራቸውን እናውቃለን። ለስልጣን ዘመናቸው እድሜ መርዘም ብዙ የሚጨነቁ ግለሰቦች፤ ስለሀገራቸው የወደፊት እጣፈንታ፤ ስለሚገነባ ውርስና ቅርስ ኢምንት የማያስቡ። አንዳንዶች እንዲያውም በዲሞክራሲ እናምናለን ይላሉ። በነዚህ መሪዎች አተረጓጎም ዲሞክራሲ ማለት አንድ ምርጫ አንድ ጊዜ ማለት ነው ”

ድንገት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግ ብለው በቁጣ ተነሱና ንግግሬን አቋረጡት ። ንግግራቸው ንዴት የተቀላቀለበት ይመስላል።

“አማራጭ እስከሌለ ድረ“ አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ “አማራጭ እስከሌለ ድረስ አንድ ምርጫ አንድ ጊዜ የሚለው አካሄድ ትክክል ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር የሕዝቡን ልብ መማረክ ያልቻሉ ፋይዳቢስ ተቃዋሚዎች በሞሉበት፤ ህዝቡ ከፈቀደ አንድ ፓርቲ አምስትም ፤ አስርም ፤ አስራ አምስትም ጊዜ ሊመረጥ ይችላል። ከ 70 በላይ ፓርቲዎች ባሉበት ነው የኢትዮጵያ ህዝብ 99.6 % ኢህደግን መርጦ ያምስት ዓመት ኮንትራት የጨመረለት ’

የተለመደው ጭብጨባና ፉጨት የተወካዮቹን ምክር ቤት አዳራሽ አዝገመገመበት።

ጸጥታ እስኪሰፍን ጠበኩና ከዚያ እኔም ደፈር ብዬ ንግግሬን ቀጠልኩ።

“አሁን ይህ አይነቱ ያገዛዝ ዘዬ በአፍሪካ አህጉርም ሆነ ከዚያ ባሻገር እየተወገደ ነው። በቅርቡ ሰሜን አፍሪካንና መካከለኛው ምስራቅን እየጠረገ ያለውን ለውጥ ልብ በሉ። ከብዙ ዓመታት የአንባገነኖች አገዛዝ ቆይታ በሗላ፤ ለዘመናት ታፍነው የቆዩ ሕዝቦች፤ አዲስ አስተዳደር እየጠየቁ ነው። የመናገር መብታቸውን መጠቀም እየተለማመዱ ነው። ለብዙሀኑ ስራ በጠፋበትና ጥቂቱ ላእላይ መዋቅር ውስጥ የተሰባሰቡ እየበለጸጉ፤ ምልዓተ ህዝቡ ግን ለለት አዳሩ ጥሮ ግሮ እየኖረ ባለበት ሁኔታ፤ ሕዝቡ፤ በተለይም ወጣቶች ጭንቀትና ስቃያቸውን ወደ ማህበራዊ ፤ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ እየቀየሩት ነው“

“ጎበዝ ከዚህ አደጋ ይጠብቀን ማለት ነው” አሉ አንድ ተወካይ ድምጻቸውን ዝቅ አድርገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሙኝ አልሰሙኝ በሚል ስጋት እየተርበተበቱ። “ይጠብቀን፡ ይጠብቀን፤ይጠብቀን“ እያሉ ሌሎቹም ተወካዮዮች በሙሉ አልጎመጎሙ። የሁሉም አይኖች አለቃውን በፍርሀት ይመለከቱ ነበር።

ንግግሬን ቀጠልኩ።

“መልእክታቸው ለሁላችንም ግልጽ ነው ። አሁን ያለው ሁኔታ ውድቅ ነው። ያረጁ ያፈጁ ያገዛዝ ስልቶች ከንግዲህ ተቀባይነት የላቸውም። መሪዎች በተጠያቂነት የሚመሩበት ጊዜ ነው። ሕዝባቸውን በክብር ማስተናገድ፤ መብታቸውን ማክበር ፤ የኢኮኖሚ መልካም አጋጣሚዎችንም መስጠት፤ ይህን ካላደረጉ ከህዝቡ ፊት ዘወር የሚሉበት ጊዜም አሁን ነው“

“እያንዳንዱ ዓለም ከሰሜን አፍሪካው የዲሞክራሲ ንቅናቄ ለመማር ቆሟል። ላፍሪካ መሪዎችም ሆነ በየትም ለሚገኙ ማናቸውንም ዋጋ እየከፈሉ ስልጣን ላይ የሙጢኝ የሚሉ፤ ተቃውሞን የሚያፍኑ፤ በሕዝባቸው ኪሳራ እራሳቸውንና ደጋፊዎቻቸውን የሚያበለጽጉ ፤ ለነዚያ መሪዎች ያለን መልእክት ግልጽ መሆን አልበት። በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ተነሱ። የህዝባችሁን ምኞትና ፍላጎት የሚያከብር፡ እውነተኛ መንገድ የተከተለ አመራር አሳዩ። ወጣቱ ትውልዳችሁ የሚተማመንበት የሚያምንበትን የወደፊት ጊዜ ፍጠሩለት። የሚንከባከበውና ለስኬቱ ለግንባታው እገዛ የሚያደርግለት መጪ ተስፋ ያለው ጊዜ ቀይሱለት። ያን ካላደረጋችሁ፤ የምንናገረው ነጻነትና መልካም አጋጣሚ ለሁሉም ዓለም የምንለው የገዛ ሕዝባችሁ ወንዱም ሴቱም ሊካፈለው አይገባም ብላችሁ የምታምኑ ከሆነ፤ ወይም ደግሞ የገዛ ሕዝባችሁ እየሰራ በክብር እንዲኖር ልትረዱት ካልጓጓችሁ፤ በተሳሳተ የታሪክ ጎን ላይ መሆናችሁን እወቁ። ይህንንም ጊዜ ያረጋግጠዋል“

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደለመዱት አጃቸውን እያወናጨፉ ድንገት ጣልቃ ገቡ። ንግግሬን አቁሜ አደመጥኳቸው።

“እድልን በማሳመር ፤ ስራን በመፍጠር ረገድ፤ ዓለም ከኛ ሊማረው የሚገባ ተሞክሮ አለን። ወጣቱን እያደራጀን፡ በአነስተኛ ወለድ ብድር ገንዘብ እየሰጠን፡ ንግድ የሚፈልገው ንግድ፤ ማረስ የሚፈልገው እርሻ፤ እደ ጥበብ የፈለገው እያነጠረ እየፋቀ፤ ሁሉም እራሱን ችሎ በመኖር ላይ ይገኛል። አስተዳደራችንን በተመለከት ብሄር ብሄረሰቦች በራሳቸው ክልል በራሳቸው ቋንቋ እየተማሩ ፤ እየተናገሩና እየተዳኙ በሙሉ ነጻነት እራሳቸውን በማስተዳደር ላይ ናቸው። ፍርድ ቤቶች ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በነጻነት እየሰሩ ነው። የነፍጠኛው ስርዓት ከተደመሰሰ በሗላ ሌላ ቀርቶ አማርኛ የሚባለውን የመጨቆኛ መሳሪያ ቋንቋ ሳይቀር ሕዝቡ ወደ ቆሻሻ እንዲያወርደው የተቻለንን እያደረግን ነው። የኢትዮጵያ አርሶ አደር ዛሬ የሚበላው የነጭ ጤፍ እንጀራነው። የሚበላው ነጭ ማር ፤ የሚጠጣው ወተት ነው’’ ጭብጨባ…

ሲጨርሱ፤ ቀጥል በሚል አይነት በጃቸው ምልክት ሰጡኝ። ንግግሬን ቀጠልኩ፡

“እርግጥ ሕዝብና ማህበረሰብ በዲሞክራሲ እንዲበለጽግ የሚፈቅድ ሁኔታን መፍጠር ማለት ምርጫ ማካሄድ ብቻ ሊሆን አይችልም። ያ አስፈላጊነቱ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን በራሱ በቂ ሁኔታ አይደለም። መልካም አስተዳደር ነጻ ግልጽና ሚዛኑን የጠበቀ ምርጫ ያሻዋል። ነጻ የመገናኛ ብዙሀን፤ ገለልተኛ የዳኝነት አካል፤ የህዳጣን መብት ጥበቃ። ዲሞክራሲ ለህዝብ ውጤቱን ማሳየት ያለበት መልካም የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን በማምጣት፤ ስራ በመፍጠር፤ የኑሮ ደረጃን ከፍ በማድረግ ነው“

“አሁን አፍሪካ በስኬት ታሪክ እያንጸባረቀች ነው። ባለፉት አስርት ዓመታት አስሩ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከሚታይባቸው አገሮች ስድስቱ ከሰሀራ በታች ያሉት ያፍሪካ አገሮች ናቸው። ያም ፐርሰንት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የበለጠ እንደሚያድግ ይጠበቃል ። ከየአለሙ አዳዲስ መዋእለ ንዋይ አፍሳሽ ባለሀብቶች አዳዲስ ገበያ አሰሳ ላይ በተሰማሩበት ሁኔታ ፤ አፍሪካ ከየአለሙ ጥግ ብዙዎችን ማርካለች። ግን ለወደፊቱ ብልጽግና ዋስትና የለውም። ብዙዎች ጥሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይዘዋል የሚባሉ የአፍሪካ አገሮች በነጠላ ምርት በነጠላ ሸቀጥ ላይ ጥገኛ ናቸው ። አንድ ነገር ብቻ ነው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት ። የአዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን መፈጠርና ይዘው የሚመጡትን የስራ እድል አያበረታታም። የሀገርን ሀብት በተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች እጅ ብቻ እንዲከማች ያደርገዋል። በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገሮች የኢኮኖሚው እድገት በፍጥነት እየመጠቀ እያለ በሌላው ወገን ደግሞ እጅግ እያዘገመ በወረቀት ላይ የሚታየውን የኢኮኖሚ እድገት ስራ አድርጎ ለመተርጎም፤ አደገ የተባለው ኢኮኖሚ ስራ ሆኖ ለመታየት ረጅም ጊዜ ይወስዳል። ለአፍሪካ ወጣት አስቸኳዩ ነገር ደግሞ ይህን በተግባር ማየቱ ነው“

አንድ የምክር ቤት አባል ብድግ አሉ። “ይቅርታ አንዴ ላቋርጦት “ አሉኝ “ይቀጥሉ“ አልኩ

ጉሮሮአቸውን አጸዱና “የኢትዮጵያ ወጣት ማየት የሚፈልገው የተለየ ነገር የለውም። ከንግዲህ የሚያጓጓው ነገር የለም። ዛሬ እድሜ ለኢህአደግ ወጣቱ የሚፈልገውን ነገር አግኝቷል። የአርሶ አደሩ ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ዩኒቨርስቲ የገባበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ከሀምሳ በላይ ዩኒቨርስቲዎችን በየክልሉ አቋቁመንለታል። ወጣቱ ባምስቱ ዓመት ትራንስፎርሜሽን የልማት መርሀ ግብር ስራ ላይ እየተረባረበ ይገኛል። የኢትዮጵያ ወጣት የሚያሳስበው ችግር የለም። እየለማለት ነው። ኢኮኖሚያችን 11 % አድጓል። በሚቀጥለው ዙር 22 % ፡ ከዚያ 44 እያለ ይቀጥላል። ወጣቱ ይበላል። ይጠጣል። ይቅማል። ይተኛል። ከዚህ የተሻለ ህይወት ከየት ሊመጣ ነው ?’’ ጭብጨባ። ረጅም ጭብጨባ…

ከጸጥታ በሗላ ንግግሬን ቀጠልኩ።

“በቱኒዚያና በግብጽ የመጣውን መነሳሳት ያየን እንደሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጥ ጉዳይ ነው። እጅግ ብዙ ወጣቶች ደክመን፤ ለፍተን ተምረናል ይላሉ። እራሱን ያቃጠለው የቱኒዚያው ጭንቅ ውስጥ የወደቀ ወጣት፤ ምንኛ ብርቱ ጥረት ቢያደርግም በንቅዘት የበሸቀጠው ስርዓት የላቡን ጠብታ ወደ ንዋይ ለውጦ፤ የድካሙን ፍሬ ወደ ገንዘብ ለውጦ፤ ለራሱና ለቤተሰቡ እንዳይጠቅም አገዛዙ እድል ነፈገው”

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድንገት ተግ ብለው ንግግሬን አቋረጡ። “መንግስቱ የነጋዴውን ጣት ነበር መቁረጥ ያለበት“ አሉ። “ጥቂት ባለሀብቶች ንግዱን ተቆጣጥረው እራሳቸው ገበያውን እንደፈለጋቸው በመወሰን፤ እቃ በመደበቅ፤ የኑሮ ውድነት ፈጠሩ። ትንንሾቹን ነጋዴዎች አግባብ ባልሆነ ውድድር አጠፏቸው። የቱኒዚያው ወጣት የመንግስት ስራ እንዲሰጠው ከነቤተሰቡ በኔት ዎርክ መታቀፍ ነበረበት። የመንግስት ስራ እንኳ ባይኖረው እነዚያ ስራውን በሞኖፖል የያዙት ነጋዴዎች ቢጠፉ ኖሮ ልጁ ሙዝና ጎመን እየሸጠ ይበለጽግ ነበር። ስህተቱ የራሱ ነው። መንግስቱም የነጋዴውን ጣት መቁረጥ ነበረበት’’

ረጅም ጭብጨባ ተከተለ። በመከራ ጸጥታ ሰፈነ። ንግግሬን ቀጠልኩ።

“ከአፍሪካ ህዝብ ከ 40% በላይ ከ 15 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች ናቸው። ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው ከ 30 አመት እድሜ በታች ነው። እነዚህ ሁሉ ወጣቶች ባንድ ዘመን ውስጥ አብረው የሚያድጉ ናቸው። የሚያቆራኛቸው ነገር አለ። አንድ የሚያደርጋቸው፤ የሚያገናኛቸው ነገር አለ። ማህበራዊ መገናኛ ብዙሀን እስካሉ ድረስ ከንግዲህ ምንም ሚስጢር አይኖርም። ምክንያቱም የመኪና መንገድ የሌለበት እልም ያለ ገጠር ውስጥ ያለን ወጣት ማመን በሚያስቸግር መልኩ የዘመናዊ ቲክኖሎጂ ውጤት የሆነ መገናኛ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ምን እየተካሄደ እንዳለ ይነግረዋል … ሴልፎን”

ሌላው የምክር ቤት አባል ተነሱ።

“ለዚህም ነው“ አሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው “ለዚህም ነው በኛ የህዝብ ተወካዮች ጥረትና ትጋት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ትግልና ቸርነት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ባልነበረ መልኩ፤ የኢንተርኔት ግንኙነት፤ የሞባይል ቴክኖሎጂ፤ ፕሬስ፤ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሳይቀር እንዲስፋፋ ያደረግነው። የሚያስመሰግን ስራ ነው። ዛሬ ወደ ገጠር ወጣ ያለ ሰው ጉድ ያያል። ገበሬው ባለቴሌቪዢን ነው። ባለፍሪጅ ነው“

ረጅም ጭብጨባ ….ፋታ

ንግግሬን ቀጠልኩ።

“ለነዚህ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ብርቱ ጥረት የሚሻ ተግባር ነው። ወጣቱ ትውልድ እንዳቅሙና እንደ እውቀቱ ስራ ሰርቶ ሕይወቱን መምራት አለበት። ብሩህ አእምሮ፤ አፍላ ጉልበት፤ የመለወጥ የማደግ ጉጉትና ምኞት፤ ሀገሩን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ የሚያስችል ብርታት ያለው ሀይል ነው። የህይወትን እድል ከተነፈገና ጭለማ ተስፋ ከፊቱ ከተደቀነ ወይ በመሪዎቹ ላይ በቁጣ ይፈነዳል፤ ወይ ሀገሩን ጥሎ ይሄዳል። የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር የተከበራችሁ ተወካዮች ለምሆኑ ይህን እውነት መካድ ይቻላል?’’

አልኩና ወደ ምልዓተ ጉባዔው ተመለከትኩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብድግ አሉ “የኢትዮጵያ ወጣት ብንጎረጉረውም አይፈነዳም። ምክንያቱም ውስጡ የታመቀ ምንም በሽታ የለበትም። ልማታችን በጣም እየተፋጠነ ነው። የኢትዮጵያ ወጣት ሰርቶ እንኳ ደሞዝ ባይኖረው፤ ለምኖ የመብላት መብቱን እህአደግ ይጠብቅለታል። ይህ ሁሉ እድል እያለ የምን መፈንዳት ነው? ሕዝቡም ቢሆን ያው ነው። ከውስጥ የሚጎረብጠው ችግር ስለሌለ አይፈነዳም። ግብጾች ገንዘብ ተሰቷቸው ነው የተነሱት። እኛ ገንዘብ አንጡ ነው ያልናቸው። የሚነሳ የለም። ሁሉም ተኮላሽቷል። አገሩን ጥሎ ይጠፋል የተባለው፤ ክልሉን ጥሎ ይጠፋል በሚለው ይታረም’ ጭብጨባ ፉጨት ጭፈራ ቀጠለ …የተወካዮች ምክር ቤት።

ድንገት እንደ ቃሪያ የሚያቃጥል ነገር ጉንጬ ላይ ሲያርፍብኝና ከእንቅልፌ ስነቃ አንድ ሆነ። ተደነጋገርኩ። ዞረብኝ። የት ነው ያለሁት? ምክር ቤትም ያለሁ መሰለኝ ። እንደገና በጥፊ ተመታሁ። ያኔ በደንብ ነቃሁ። በረጅሙ ተነፈስኩ። ለካንስ ያሁሉ የማወራው ህልም ኖሯል። ከፊት ለፊቴ ግርግዳ ላይ የነበረው ትልቁ የኢትዮጵያ ካርታ በሀገሬ ባንዲራ ያጌጠው መልሶ አፈጠጠብኝ ። እዚያችው መኝታ ቤት ውስጥ….

ልጄም እዚያው ደረቴ ላይ እንዳለች እንቅልፍ ይዟት ሂዶ ኖር፤ ከንቅልፏ ብንን ብላ አይኑን እንዳልገለጠ የውሻ ቡችላ፤ በጭፍኗ እንዳለች፤ ባፏም በጇም የናቷን ጡት ከደረቴ ላይ ብትፈልገው የለም፤ ብትፈልገው የለም። አይኗን ገልጣ ብታይ እኔ ነኝ። ተናደደች። ደጋግማ በጥፊ አጋለችኝ። እሳትም ውሀም የሆነች ቡቃያ ነች። እሳት ሆነው ከመጡባት፤ ካናደዷት፤ ተንበልብላ ማንበልበል ነው። ውሀ ሆነው ከመጡም ሲጠጡት ቢውሉ የማትጠገብ የተራራ ምንጭ፤ ቀዝቃዛ ውሀ ነች… አልፋ… ከቅዠት ገላገለችኝ… ልጄ!

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 21, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.