የህወሃት ድርጅታዊ ጉባዔ እና ውዝግቡ (አብርሃ ደስታ – ከመቐለ)

በሦስት ቀናት እንዲጠናቀቅ ታስቦ የነበረው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ ወደ ስድስት ቀናት ፈጅቷል። ሌሎች ከዚህ በፊት ያልተያዙ ኣጀንዳዎችም ተጨምረዋል። በዚህ መሰረት ጉባኤው መጋቢት 8 ማታ ተጀምሮ በ 13 ይጠናቀቃል ተብሎ መርሃ ግብር ወጥቶለታል።

እነ ኣባይ ወልዱ በመተካካት ስም ‘የተማረው የህወሓት ኣባል’ ድጋፍ ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው። ኣብዛኛው ሙሁር ኣባል ይደግፋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ነገር ግን በቡድኑ መሪዎች ኣንድነት የለም። ለምሳሌ ኪሮስ ቢተው መጀመርያ ከነ ኣባይ ወልዱ ቡድን የነበረ ሲሆን የኣባላቱ ተቃውሞ ከተገነዘበ በኋላ የመሃል ሰፋሪነቱ ቦታ ተረክበዋል።

ኣዲስ ኣበባ የሚገኙ የህወሓት ኣባላትና የደህንነት ሰራተኞች ግን የነ ኣርከበ ዕቁባይ (ወይ ደብረፅዮን) ቡድን ደጋፊዎች ናቸው። ትግራይ ዉስጥ ያሉ ኣባላት ግን ፍርሓት ውስጥ ናቸው። ማንን መደገፍ እንዳለባቸው ግራ ተጋብተዋል።

ኣብዛኞቹ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላትና የድሮ ባለስልጣናት የነ ኣርከበ ቡድን ሲደግፉ ጠቅላይ ሚኒስተር ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ በረከት ስምዖን፣ ኣዲሱ ለገሰና ኩማ ደመቅሳ የነ ኣባይ ወልዱ ደጋፊዎች ሁነዋል።

የከረረ ጠብ ያለ በኣዜብ መስፍና ኣርከበ ዕቁባይ ሲሆን በኣባይ ወልዱና ደብረፂዮን ገብረሚካኤል መካካልም ከፍተኛ ኣለመግባባት ኣለ። ስብሓት ነጋና በረከት ስምዖንም ኣይዋደዱም።

በኣሁኑ ሰዓት የህወሓት መሪዎች (የሁለቱም ቡድኖች ተወካዮች) በመቀሌ ከተማ ተሰብስበው እየተነታረኩ (እየተጨቃጨቁ) ይገኛሉ። መግባባት ባለ መቻላቸው ከኣዲስ ኣበባ የመጡ እነ ኣርከበ ዕቁባይ የሚንቀሳቀሱበት መኪና ኣልተሰጣቸውም። በእግርና በቤተሰብ መኪና ይንቀሳቀሳሉ።

የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላትና ተሰሚነት ያላቸው የፓርቲው ሰዎች በከፍተኛ ንትርክ የታጀበ ስብሰባ አድርገዋል። የስብሰባው ኣጀንዳም ለሚቀጥለው የፓርቲው ድርጅታዊ ጉባኤ ስብሰባ ኣጀንዳ መያዝ (ና ማስያዝ) ሲሆን እንደዉጤትም ብዙ እንዳልተስማሙ ተገልፀዋል።

በስብሰባው መግባባት ካልቻሉበት ነጥብ ኣንዱ “የመተካካት መርህ” ነው። “መተካካት” መኖር እንዳለበትና በጉባኤው ከሚተገበሩ ኣንዱ እንደሆነ ብዙ ልዩነት የለም። በመተካካት ኣፈፃፀም ላይ ግን የከረረ ልዩነት (ጠብ ያስከተለ) ኣለ። እስካሁንም ኣልተግባቡም።

የልዩነቱ ነጥብ፣ “በህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ የመተካካት ኣፈፃፀም በምን መስፈርት ይተግበር? በትግል ቆይታ፣ (የህወሓት ነባር ታጋዮች ይወገዱ ወይስ ይቀጥሉ?) በዕድሜ፣ በብቃት ወይስ በስልጣን ረዥም ግዜ በመቆየት ?” የሚሉ ነጥቦች ሊያግባቧቸው ኣልቻሉም።

ኣብዛኞቹ የማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላት፣ ‘መተካካት በወጣትና ሽማግሌ (በዕድሜ) መሆን የለበትም’ ብለው ይከራከራሉ። በስልጣን የመቆየት ፍላጎት ኣላቸው። እያንዳንዱ የማ/ኮሚቴ ኣባል ከስልጣኑ (ከሓላፊነቱ) ሊወገድ እንደሚችል በመስጋት የየራሱ ተወካይ (ጥቅም ኣስከባሪ) ወደ ኮሚቴው ለማስመረጥ ተዘጋጅተዋል።

ለምሳሌ ቴድሮስ ሓጎስ (ከጀነራል ሰዓረ መኮነን ጋር በመመካከር)፣ ኣልጋ ወራሹ ዶክተር ክንደያ ገበረሂወት (የኣሁኑ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕረዚደንት) መሆኑ ኣሳውቀዋል። ተክለወይኒ ኣሰፋ (የማረት ዳይሬክተር) ታጋይ በላይ ገበረዮውሃንስ እንዲመረጥለት መልምለዋል። ጌታቸው ረዳ (በጠቅላይ ሚኒስተር ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሓላፊ) ከኣዲስ ኣበባ በመጡ ሰዎች ለማእከላዊ ኮሚቴ ኣባልነት ታጭተዋል። ባጭሩ የማእከላዊ ኮሚቴ ኣባላት (ከጉባኤው በፊት) እየተመረጡ ናቸው። እርስበርስ መግባባት የለም እንጂ።

እያንዳንዱ የማእከላዊ ኮሚቴ ኣባል የራሱ ደጋፊዎች ለማፍራትና ለመመረጥ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ዶር ቴድሮስ ኣድሓኖም (ከነ ኪሮስ ቢተው፣ ኣባይ ፀሃየና ሌሎች) የሽምጋይነት ሚና ይጫወታል።

ፀጋይ በርሀና ኣርከበ ዕቁባይ በተለያዩ ኣከባቢዎች (ካፌዎች፣ መጠጥ ቤቶች, Coffe House …) እየተዘዋወሩ የህዝቡ ስሜት (በህወሓት ያለው ግምት) እየፈተሹ ሲሆን በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪል የለበሱ የደህንነት ሰዎች፣ የፖሊስና መከላከያ ሰላዮች (እንዲሁም ፈጥኖ) የህዝቡንና የኣባላቱ መንፈስ እንዲያጠኑ ታዝዘዋል። ፀጋይ በርሀ ከትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዘኣማኑኤል ለገሰ (ወደ ሻምበል) ጋር በመሆን ስላልታወቀ ጉዳይ በተደጋጋሚ ለብቻቸው እንደሚነጋገሩ የዓይን እማኞች ጠቁመዋል።

የነ ኣባይ ወልዱ ቡድን ግን ያላቸው የክልል ስልጣን ተጠቅመው እስከ ቀበሌ ወርደው ድጋፍ ለማሰባሰብ ሞክረዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የህወሓት ኣባላት በመተካካቱ ኣፈፃፀም ተስፋ ቆርጠዋል።

በሙስና በበሰበሰ ስርዓት የመተካካት መርህ ዉጤት ኣያመጣም። ምክንያቱም መሪዎቹ በሙስና ከተዘፈቁ ብቁና ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ተተኪ ወጣት የመመረጥ ዕድሉ ኣነስተኛ ነው። ወጣት ተተኪዎቹ ማነው የሚመርጣቸው? ኣለቆቻቸው ናቸው (ገምግመው የሚያቀርብዋቸው)። ሲመለምሉ ታድያ ለነሱ ታማኝ ሁኖ ያገለገለ፣ ሙስና ሲበሉ የማያጋልጣቸው (ወይም የተባበራቸው ……. ኣብሮ ሙስና የበላ ቢሆን ይመረጣል ምክንያቱም በኋላ እንዳያሳስራቸው)፣ የነሱ ዘመድ የሆነ (እንደማይጥላቸው የሚተማመኑበት)፣ ባጭሩ የራሳቸው ኣምሳያ ተክተው ይሄዳሉ (ተተኪዎች የመመልመል ስልጣን ስለተሰጣቸው)።

ስለዚ መተካካት እንኳ ቢደረግ (ዘሮ ዘሮ ከእጃቸው ስለማይወጣ) ስርዓቱ የሚፈለገው የመልካም ኣስተዳደርና የኢኮኖሚ ልማት ማስመዝገብ ኣይቻለውም። ለውጥ ለማምጣት መጀመርያ ሙስና ማጥፋት ኣለባቸው፤ ሙስና ካጠፉ ደግሞ ገዢው ፓርቲ ጠፋ ማለት ነው። ምክንያቱም ፓርቲው የተገነባ በሙስና ነው። ግንቡ ከፈረሰ ፓርቲው ወደቀ።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on March 14, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.