ዛሬም ሁሉን-አቀፍ ትብብር አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው

ከዳኮታ የጥናት ማዕከል –

መግቢያ:

ዳኮታ የጥናት ማዕከል በኢትዮጵያችን ለ20 ዓመታት የዘለቀው የትግራይ “ምርጥ” ልጆች አገዛዝ መላውን የሀገሪቱን ሕዝቦች መብት አልባና የበዪ ተመልካች እያደረገ መምጣቱን በማገናዘብ በብሔረሰብ የተደራጁትን ጨምሮ ሁሉን ያካተተ የወያኔ ተቃዋሚዎች ትብብር መመስረት አስፈላጊነትንና መቻልን በራዕይ ደረጃ ከዚህ ቀደም በጻፍናቸው ጽሁፎች ላይ አስፍረናል። የዚህን ዓይነት ሁሉን-አቀፍ ማለትም በተግባር ፀረ-ወያኔ የሆኑትን በሀገርና በብሔረሰብ ደርጃ የተደራጁ ድርጅቶችን ትብብር መመስረት የወያኔን አምባገነን ሥርዓት ፍጻሜ ለማድረስ ከሚኖረው ጠቀሜታ በተጨማሪ የአገርን ህልውናና የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መንገድ ሰላማዊ ሽግግር ለማካሄድ ዓይነተኛ መፍትሄ ነው ብሎ በማመን የተቃዋሚ ድርጅቶች በዚህ ላይ እንዲሰሩ ሲያሳስብና ሲያበረታታ ቆይቷል።

ይህን ሀሳብ ድርጅቶቻችን በጊዜው ትኩረትን ሰጥተውት ስራ ጀምረውበት ቢሆን ኖሮ ዛሬ የተፈጠሩ አመቺ የአካባቢና አገራዊ ሁኔታዎችን ተጠቅመው በአገራችንም፤ በህዝባችንም ደህንነት ላይ በማን አህሎኝነት ጥፋት የሚፈጽመውን የወያኔ መንግሥትን ለማስወገድ የተሻለ እድል ይኖረን ነበር የሚል ግምት አለን። ዛሬም በአገራችን እስካሁን ካደረሰው በላይ ጥፋት ሊያደርስ ብቃት ያለው መንግሥት የስልጣን ባለቤት ነው። ይህንን የጥፋት ኃይል ተቃዋሚዎች ተባብረው ማስወገድ አለባቸው የሚለውን ሃሳብ የማይጋራ ዜጋም፤ ድርጅትም ያለ አይመስለንም። ደጋግመን በጻፍነው ርዕስ ላይ በዚህ ጽሁፋችን ተመልሰን እንድናተኩር ያደረገን ግን ባለፉት ጥቂት ወራቶች እኛ ሁሉን-አቀፍ ብለን በሰየምነው በሚመስል መልኩ በሀገርና በብሔረሰብ ደረጃ የተደራጁት ግንቦት 7፤ ኦነግና ኦብነግ ተባብሮ ለመታገል ያላቸውን ዝግጁነት ይፋ ካደረጉ በኋላ የተገነዝብነው ተቃዋሚዎች እንዴት ይተባበሩ የሚለው የሃሳብ ልዩነት ነው።

እኛ የምንለው አገራችን ባለፈው ሃያ ዓመታት በወያኔ ስር ከተለወጠችበት ሁኔታ አንጻር፤ በወያኔ የተጨቆኑና ፀረ-ወያኔ የሆኑ ብሔረሰባዊና ሀገራዊ ድርጅቶችን ያካተተ ትብብር በመመስረት የመለስ መንግስት የሚፈጽመውን ጥፋት መመለሻ የሌለው ደረጃ ከመድረሱ በፊት ማስቆም ይቻላል ነው። በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደሚባለውም ጥፋቱን በቶሎ ከማስቆምም በተጨማሪ የዚህ ዓይነት ትብብርና ትግል በትክክልኛ መንገድ ከተመራ በሸግግር ወቅት ሊኖሩ የሚችሉ ችግሮችን ማስቀረት ይችላል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀገራችን በአሁኑ ሰዓት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የተረጋጉ ሀገራት ረድፍ ውስጥ ለመግባት በታሪኳ ምክንያት ያለባትን የእኩልነት፤ የዲሞክራሲና የፍትህ ጉድለቶች ማስተካከል አለባት። ከዚህ ታሪካዊ ጉድለት በተጨማሪ መረን የለቀቀው የ1966 አብዮተኛ አስተሳሰብና ያለፈው 20 ዓመታት የወያኔ ከፋፍለህ ግዛ ሥርዓት ያባባስቧትን የአንድነትና የሰላም አደጋ ልጆቿ በጋራ ከሥሩ ለመፍታት ሁሉን-አቀፍ ትብብርና ትግል ዓይነተኛ እድል ይሰጣል ብለን እናምናለን።

በሌላው በኩል ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ትብብር ወያኔን ማስወገድ እንኳን ቢችል የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት አይችልም የሚሉ የወያኔ ተቃዋሚዎች እንዳሉ በደንብ እናውቃለን። እነዚህ ወንድሞቻችን እንዳውም ይህ ዓይነት ትብብር የአገርንና የህዝብን አንድነት አደጋ ላይ ይጥላል ይላሉ። እነዚህ ሰዎችም ባለፉት ጥቂት ወራቶች ይህን ተቃውሟቸውን ከነ ምክንያታቸው በአንዳንዶች አባባል ወያኔን መታገልና መቃወም የረሱ በሚመስል መልኩ ሙሉ ጊዜያቸውን የሁሉን-አቀፍ ትብብር አራማጆችን በየመድረኩ በመተቸት እያሳለፉ ነው።

እንደ ሁሉን-አቀፍ ትብብር ደጋፊነታችን ይህንን ጽሁፍ የተወሰኑ ዓላማዎችን ግብ አድርገን ጽፈንዋል። የመጀመርያው ግባችን ሁሉን-አቀፍ ትብብርን የሚቃወሙት ያስቀመጧቸውን ምክንያቶችን በበቂ ሁኔታ አሳማኝ እንዳልሆኑና ብዙዎቹም የዚህን ትብብር ጥቅምና ጉዳት ሲዘረዝሩ ከሀገራችን የወቅቱ ተጨባጭና የሁሉንም ሕዝባችንን እይታና ፍላጎት በማቻቻል ሳይሆን የአንድ አስተሳሰብን መፍትሄነት በመመልከት ብቻ የተዛነፉ ምክንያቶች መሆናቸውን እናሳያለን። ይህንን በማድረግም ሁሉን-አቀፍ ትብብርን የሚቃወሙ ድርጅቶችና ደጋፊዎቻቸው እንደ እኛ ያሉ የሃሳቡ አራማጆችና እዚህ ጉዳይ ላይ በተግባር የተሰማሩትን የግንቦት ሰባት አይነት ድርጅቶች ምክንያቶች ተረድተው ድርጅቶቹና ደጋፊዎቻቸው የትብብሩ ደጋፊ እንኳን ባይሆኑ የጀመሩትን “የተቃዋሚ-ተቃዋሚነት” ሚና እንዲተዉ ለማድረግ ነው። ሁለተኛውና እንዳውም ዋናው ግባችን ደግሞ በሀገሩ አንድነትና ደህንነት ላይ ቀኒአ የሆነው ሕዝባችን የትብብር ጥያቄችን በተመለከት ያሉትን አማራጭ አቋሞች በግራ በቀኝ መርምሮ ለአገር የሚበጀው የትኛው ነው ብሎ ፍርዱን እንዲሰጥ የበኩላችንን የሃሳብ አስተዋጾ ለማድረግ ነው።

በዚህ ጽሁፍ ሁሉን-አቀፍ ትብብር አይሰራም ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው ተብሎ የተሰጡትን ዋናዋና ምክንያቶች አንድ በአንድ አንስተን እንቃኛቸዋለን። ስህተት ናቸው የምንላቸውን ለምን ስህተት እንደሆኑ እናሳያለን። በአንድ አቅጣጫ ብቻ የታዩትን ደግሞ በሌላ አቅጣጫም እንዲታዩ ለማድረግ እንሞክራለን። የተለጠጠ ትርጉምና ስም እየሰጡ አግባብ ያልሆነ ትችት የሚደረግባቸውን የመከራከሪያ ሃሳቦች ደግሞ በሁሉን-አቀፍ ትብብር ደጋፊዎች እይታ እነዚህ መከራከሪያዎችን በተመለከተ ያለውን በሂደትና በጊዜ የተወሰነ አተረጓጎም በማሳየት ትችቱ ቀና እንዳልሆነ እናስረዳለን።

ይህ ጽሁፍ ግን ሁሉን አቀፍ ትብብር ያለውን መጠነ ሰፊ ጥቅም አይገልጽም። ትብብሩ እንዴት ተግባራዊ ይሁን የሚለውንም ጥያቄ አያነሳምም፤ አይመልስምም። ይህን ያደረግንበት ምክንያት ከዚህ በፊት በጻፍናቸው ጽሁፎች በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሰፊው ሄድንበታል ብለን ስላሰብን ነው። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ወደፊት ልንመልስባቸው እንችላለን።

በተረፈ ለእኛ ተቃራኒ ሃሳቦች መልስ ስንሰጥ ሳንፈልገው አልፎ አልፎ የግለሰቦችና የድርጅቶችን ሀሳብ አንስተን አጠንክረን እንተቻለን ። ከዛ በላይ ግን የግለሰብ ወይም የድርጅቶች አታካሮ ውስጥ የመግባት ፍላጎቱም ሆነ አንጀቱ የለንም። በእኛ እምነት የሁሉ-አቀፍ ትብብር የማይሳካው በሃሳብ ደረጃ በተነሳበት ተቃውሞ ሳይሆን የትብብሩ ተግባር ላይ አዋዮች አብሮ ለመምጣት የሚያስፈልገውን እርምጃ በሙሉ በመሄድና ባለመሄድ፤ ከዛም አልፎ አብሮ መጥቶ በሚሰሩት የስራ ጥራትና ጥንካሬ ይወሰናል ብለን እናምናለን።

መርህን መሰረት ያደረጉ የሁሉ-አቀፍ ትብብር መቃወሚያዎች

በዚህ ንዑስ ርዕስ ስር የሁሉ-አቀፍ (ለምሳሌ ግንቦት 7፤ ኦነግና ኦብነግ ለመመስረት የሚሞክሩት ዓይነት) ህብረትን የሚቃወሙ ወገኖች በመርህ ደረጃ የሚቃወሙባቸውን ሥስት ምክንያቶች እንመረምራለን። እነዚህ ሶስት ምክንያቶች ከቀድሞው “ማርኪስት-ሌኒናዊ” ተማሪው ንቅናቄ ጀምሮ እስከ አሁን ያልተላቀቀን የብሔረ-ሰቦች እስከ-መንገጠል የሚለው “መብት” ጽንሰ-ሀሳብ፤ የሕዝብ ይወስንን አባብል ትርጓሜና በሀገርና በብሔርሰብ አቀፍነት መርህ ላይ ተመስርተው የሚደራጁ ድርጅቶች የባህሪ ልዩነቶችን አስመልክቶ የሚነሱ ናቸው።

  1. 1. እስከ መገንጠል የሚለው ዓላማ

በአሁኑ ወቅት እስከ መገንጠል የሚለው የብሔረሰቦች መብት አስፈሪም ስህተትም የሆነ አላማ ነው። አይደለም የኢትዮጵያን አንድነት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለሚቀበለው ኃይል፤ ጊዜ እየረዘመ ሲመጣ በመገንጠል የእኩልነትን መፍትሔ እናገኛለን ብለው የሚያምኑ ኃይሎች እንኳን ሃሳቡ እንገነጥለዋለን የተባለውን ብሔረሰብ ታሪካዊ፤ ማህበራዊ፤ ጂኦግራፊያዊና ባህላዊ መሰረት ግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ እየተረዱት ነው።

የመገንጠል መብት እንደ እኩልነት መብት ተደርጎ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣው በሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛው ምክንያት በርግጥ ሀገራችን ውስጥ ብሔረሰቦችን አስመልክቶ ለረጂም ጊዜ የቆዬ የእኩልነት ችግር መኖርና አሁንም አለመጥፋቱ ነው። እንዳውም በአሁኑ ጊዜ ወያኔ ይህንን ችግር አባብሶት ይገኛል። ስለዚህ የእኩልነት እጦቱ ገፈት ቀማሽ የነበረውና አሁንም የሆነው የሕዝባችን ክፍል ተቆርቆሪዎች ሁኔታውን ለማሻሻል ሃሳቡን እንደመፍትሔ አንስተውታል። በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች የሚያረጋግጡት ግን እኩልነት ለማምጣት እስከመገንጠል የሚለውን አቋም መደገፊያ ሁነው የሚሰጡት ምክንያቶች ከመጠን በላይ መጋነናቸውንና ለፖለቲካል ፍጆታ መዋላቸውን ነው።

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እስከ መገንጠል የሚለው ሀሳብ የማርኪሲስት-ሌኒንስቱ አብዮታዊ የሀገራችን ትውልድ የትግል አርማ ተደርጎ ያለ ትክክለኛ የሃሳብ መመርመሪያ የረጂም ጊዜ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰውነት ውስጥ ስር እንዲሰድ መደረጉ ነው። ስለዚህ ነው የብሔረሰቦች እኩልነት ማጣት በዓለም ላይ በሰፊው በተለይም ዲሞክራሲ ባልተስፋፋባት በመላው አፍሪካችን እያለ፤ ከሀገራችን በስተቀር ለእኩልነት መገንጠል እንድመፍትሔ ሆኖ በሌሎች ቦታ በፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራም ደረጃ ያልቀረበው። በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ግልጽ የሆነ በዘር ላይ የተመሰረተ የርስ በርስ መተላለቅ እንኳን ደርሶ የእኩልነታችን መፍትሔ መገንጠል ነው ተብሎ አልቀረበም። መገንጠል የተፈጸመባችው ቦታዎችን ብንወስድ፤ ለምሳሌ ኤርትራና ደቡብ ሱዳን፤ መገንጠል በተግባር የተተረጎመው የፖለቲካ ጥያቄዎች ብልሃት ያለው አያያዝ በማጣት ወደ አጠቃላይ ጦርነት አምረተው የተገነጠሉት ሃይሎች በጦር አቸናፊ ወይም የማይቸነፉበት ደረጃ በመድረሳቸው ነው። በሀገራችን ውስጥ ግን የመገንጠል ጥያቄ ከላይ በጠቀስናቸው ጣምራ አነሳስ ምክንያት በየፖለቲካ ፕሮግራሞችና ካዛም አልፎ በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት ላይ ሰፍኖ ይገኛል። የወያኔ መንግሥትም ትነኩኝና ሀገር አይኖራችሁም እያለ እንደማስፈራሪያ ከመጠቀም አልፎ በብልሃት ካልተሰራ ይህንን መሳሪያ እንደ አንድ የፖለቲካ መሳሪያ ጠምዶ እንዳስቀመጠው ማወቅ ያስፈልጋል።

ስለዚህ እስከመገንጠል የሚለው አስተሳሰብ በአንድ በኩል በሀገራችን ውስጥ ከመንግሥት እስከ ፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ለረጂም ጊዜ ተንሰራፍቶ የቆዬ አስተሳሰብ መሆኑን ተረድቶ መራመድን ይጠይቃል። በሌላ በኩል ግን የዚህ የብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል የሚለው ኃይል ዋና አቀንቃኝ የሆነው የወያኔ አገዛዝ ባለፈው 20 አመታት በሀገሪቱ በዘረጋው ዓይን ያወጣ የአናሳ የትግሬ “ምርጥ” ልጆች አምባገነንና አድሏዊ አገዛዝ ምክንያት የሃሳቡ ባዶነት ብቻ ሳይሆን አደገኛነቱም ለሁሉም የሀገሪቱ ብሔረሰቦች ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ለምሳሌ በመድረክ ስር የተሰባሰቡ የብሔረሰብ ድርጅቶች አንዳንዶቹ ከወያኔ ጋር ያጸደቁትን አንቀጽ 39 በዶነት ተረድተው ከአሁኑ ሁሉ-አቀፍ ትብብራቸው ፕሮግራም አስወጥተውታል።

ግትር የፖለቲካ ክርክር ከሚፈልግ ሰው በስተቀር በውጭም ያሉት እንደ ኦነግ ዓይነት ድርጅቶች ቀድመው የአቢሲኒያ ቅኝ ግዛት፤ ነጻ ኦሮሚያ ወይም ሞት ከሚለው አቋማቸ ብዙ ርቀው የብሄረሰቦች ጥያቄ በዲሞክራሲ፤ በእኩልነትና በፍትህ ላይ በተመሰረት ሥርዓት ለመፍታት እንደሚቻል በየቦታው በቱባ ቱባ መሪዎቸቸው እየተናገሩ ነው። በተጨማሪም ኦነግም ሆነ ኦብነግ በወያኔ ተገፍተው እስከወጡ ድረስ በአገራችን ማዕከላዊ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለመሳተፍ መሞከራቸውን መካድ አይቻልም። ትብብር ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ሲመሰረትም ሆነ አሁንም እስከመገንጠል የሚለውን አቋም የመነጋገሪያም ሆነ የስምምነት ቅድመ ሁኔታ አድርገው ጠረጴዛ ላይ አላማጡም። ይህንን ስንል እነዚህ ድርጅቶች የመገንጠልን ጥያቄ ከነጭራሹ ትተውታል እያልን አይደለም። ነገር ግን የፖለቲካ አኪያሄድን ቅደም ተከተል አውቆና ከዛም በላይ ጊዜው የፈጠረውን የሰላምና የቀና መንገድ ለሚፈልግ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ አበረታች ምልክት አይተናል ነው የምንለው።

ለዚህም ነው በእኛ ዕይታ እስከ መገንጠል የሚለውን የብሔረሰቦች መብት የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈልጉ ኃይሎች በአንድ በኩል በምንም መልኩ እንደ እኩልነት መፍትሔ ሊያስቡት አይገባም ስንል በሌላ በኩል ግን አንድነት ፈላጊዎች አሁንም የመገንጠልን ሃሳብ በመፍትሄነት ከሚያዩት ጋር ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ ውይይትና ተቀራርቦ መስራት አለባችው የምንለው። ይህን ድምዳሜ ያደረግነው እስከ መገንጠል የሚለው አስተሳሰብ በሀገራችን እንዴት መጥቶ አሁን ያለበት ደረጃ እንደደረሰና በዚህ ወቅቱ ሀገራችን ያለችበትን አደገኛ ሁኔታ በማገናዘብ ነው።

ለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ተቃዋሚዎች አንድ አይነት ስምምነት ላይ ለመድረስና አብሮ የሚያሰራ ስምምነት ለማድረግ በርግጥ ዋና ችግር የሆነው መገንጠል የሚለው አላማ ነው ወይ ብለን ስንጠይቅ የእኛ መልስ አይመስለንም ነው። እስቲ ነው እንበልና እንየው ። ለአንድ ኢትጵያዊ ድርጅት የብሔረሰብ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር በሰላማዊ መንገድ መገንጠል የሚለውን ሀሳብ እንዲተዉ ወይም ሁላችንን አቸናፊ በሚያደርግ አማራጭ መፍትሔ እንዲተካ መሞከር ስህተት ነው ወይ? ይህ ሙከራስ ምን ያህል ጊዜ ደጋግሞ ቢጣርበት በዛ ይባላል ወይ? መቼስ ነው ተስፋ ተቆርጦ የሚተወው? በኛ እምነት መልሱ በውይይትና በመቀራረብ ሰላማዊ መፍትሄ መፈለጉ በአገራችን ሁኔታ በአርቆ አስተዋይነትና በኃላፊነትም የሚደረግ ሆኖ ይታየናል። ሁሌም ክፍት የሆነ በር የሚተውለት፤ ሁሌም በጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ የስራ አጀንዳ መሆን ያለበት ነው እንላለን።

  1. 2. ህዝብ ይወስን የሚለው አባባል

ህዝብ ይወስን የሚለውን ዲሞክራቲክ መርህ በተምታታ ሁኔታ ሲተረጎም ሰምተናል። ሕዝብ ይወስን ማለት የብሔረሰቦች የወደፊት በኢትዮጵያዊነት መቀጠልና አለመቀጠል ሕዝበ-ውሳኔ (ሪፈረንደም) ይሰጥበት ነው ተብሎ ይቀርባል። ይህን ትርጉም እየሰጡ የሚከራከሩት በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በ ግንቦት 7፤ በኦነግና በኦብነግ መካከል የሚደረገውን የመተባበር ሙከራ አጥብቀው የሚቃወሙት ናቸው። ከ ግንቦት 7 ፕሮግራምና የድርጅቱ መሪዎች የሁልጊዜ ገለጻ የምንስማው ደግሞ ሕዝብ ይወስን ማለት ከወያኔ በኋላ የሚቋቋም መንግሥት ከትንሿ የቀበሌ አስተዳደር እስከ ፌደራሊዊ መንግሥት ድረስ በምርጫ ይወሰን ነው። እስከ አሁን ድረስ በኦነግ በኩል የምንሰማቸው የህዝብ ይወስን ትርጉም ይህንን ከላይ የተጠቀስውን የግንቦት 7 ዓይነት ትርጉምና አልፍ አልፎ ደግሞ የራስን እድል በራስ መወሰንን ጽንሰ-ሃሳብ የሚያቀላቅል ይመስላል። በግልጽ ግን የሪፈራንደም ጉዳይ ሲነሳ አልሰማንም።

እንዳውም በቅርቡ በዋሺንግተን ዲሲ በተደረገ የግንቦት 7ና የኦነግ ሕዝባዊ ስብስባ ግለጽ የሆነልን በሁለቱም ድርጅቶች በኩል ህዝብ ይወስን ሲባል ነፃ በሆነ ምርጫ የህዝብ ፍላጎት የሚገለጽበትን ሁኔታ እናመቻች የሚል ሆኖ ነው ያገኘነው። ይህ ጥሩ አዝማሚያ ሆኖ አልፎ አልፎ የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚለው አባባል ግን የሚያሳየው በዚህ ጉዳይ ላይ ገና ንግግሩ ጥርት ያለ ስምምነት እንዳልተደረሰ ነው። ጥራት እስኪገኝ ድረስ ንግግሩና ውይይቱ መቀጠል የሚኖርበትም ለዚህ ነው።

በግድ የማያግባባን ምክንያት እናድርገው ካላልን በስተቀር ህዝብ ይወስን የሚለውን ድርጅቶቹ በዚህ ወቅት ካሉት ውጭ እየለጠጥን ሪፈረንደም ማለት ነው እያልን መከራከር ግን ቀና ሃሳብ አይመስለንም። በእኛ እምነት ወያኔን አስወግደው ሕዝቦቿን በእኩልነትና በሕግ የበላይነት የምታስናግድ ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን ፈላጊዎች በሁለት ምክንያቶች የሪፈረንደምን ስምምነት ውስጥ መግባት የለባቸውም እንላለን። በአንድ በኩል ግንቦት 7 ደጋግሞ እንደ ገለጸው ኢትዮጵያን በሪፈረንደም ለመቀየር መሞከር ወያኔን አስወግዶ የማያቋርጥን የርስበርስ ግጭት መጋበዝ ነው። ሁለተኛ የግንቦት 7 ሊቀ መንበር ዶ/ር ብርሃኑ በየ ሕዝባዊ ስብሰባው እንዳብራሩት ድርጅቶች የዚህ ዓይነት ሕዝባዊ ውሳኔ የመዋዋል ምንም መብት የላቸውም።

በአማራጩ ለዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ የሚታገሉ ድርጅቶች ስምምነት ማድረግ ያለባቸው ከ ፀረ-ወያኔ ትግሉ አካሄድ አንስቶ፤ የሽግግር ወቅቱን ይዘት ጨምሮ እስከ የዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ ቋሚ መንግሥት ምስረታ ድረስ ትብብሩን በጋራ ራዕይና ግብ ላይ በዝርዝር የሚያስማማ ሂደት (ሮድ-ማፕ) ላይ ነው። እዚህም ለመድረስ የተጀመረውን የሁሉ-አቀፍ የድርጅቶች ግንኙነትንና ውይይት ቀጥሉበት እንላለን።

  1. 3. የሀገራዊና ብሔረሰባዊ ድርጅቶች የባህሪ ልዩነቶችና ትብብር

ትብብርን ለመመስረት በሀገር አቀፍና በብሔረሰብ አደረጃጀት መካከል ያለው ልዩነት በየመወያያ ድረኮች ሲቀርቡ የግንቦት 7ንና የኦነግን የትብብር ጅማሮ የሚቃወሙ ኃይሎች አቋም ትንሽ ዝብርቅርቅ ያለ ነው። በአንድ በኩል የሀገራዊና የብሔረሰባዊ አደራጃጀት የባህሪ ልዮነት አብሮ ለመስራት ሊታለፍ እንደማይቻል ችግር ሆኖ ሲቀርብ ይሰማል። የተቃውሞውም ገደብ ለምን በብሔረሰብ ተወስነው ተደራጁ ከሚል መከራከርያ ጀምሮ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር ምንም አይነት ትብብር አያስፈለግም እስከሚል ምክንያት ድረስ ይሄዳል። በሌላ በኩል ደግሞ በብሔረሰብ ተወስነው የተደራጁትን የወያኔ ተቃዋሚ ድርጅቶች እስከመገንጠል የሚለውን ሀሳብ በፕሮግራም ደረጃ እስካልያዙ ድረስ በፀረ-ወያኔው የትግል ትብብር አስፈላጊ ናቸው የሚል አቋም ያላቸውም አሉ።

ለምሳሌ የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ኃይሎች ሕብረት በምህጻሩ ሕብረት ተብሎ የሚታወቀው የአመራር አባል የሆኑት አቶ አያልሰው ደሴ ያለፉ ትብብሮችን በሰፊው በገመገሙበት ጽሁፋቸው ለሕብረት ስኬታማ አለመሆን ዋና ምክንያት በብሔረሰብ ተወስነው የተደራጁት የህብረቱ አባል ድርጅቶች የባህሪ ችግር ነው ብለው ደጋግመው ይገልጻሉ።

እንደ አቶ አያልሰው ግምገማ ከሆነ የሕብረት ዋና ድክመት የዶ/ር በየነ ጴጥሮስና የዶ/ር መራራ ብሔረሰባዊ ድርጅቶች ባህሪ ነው ይሉናል። ምርጫ 97ን እንደተገነዘብነው ግን እነዚህ ግለሰቦች መጨረሻ ላይ እስከፈጸሙት ትልቅ ስህተት ድረስ የህብረቱ ስኬትማ የምርጫ ተሳትፎም ሆነ መስዋዕትነት ከፋዮች የነበሩት የዶክተሮቹ ድረጅቶች መሆናቸውን ለምናውቅ ሰዎች የግምገማውን ወረቀት አንብበን ግራ ገብቶናል።

በአጠቃላዩ ከሁሉም ዓይነት የብሔረስባዊ ድርጅቶች ጋር ወይም በተለይ እስከመገንጠል የሚለውን ዓላማ ከሚደግፉ ጋር ሀገራዊ ድርጅቶች መተባበር የለባቸውም የሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች የሚዘነጉት ነገር የፖለቲካ ትብብር በተወሰነ ጊዜና በተወሰነ ቦታ ተመርምሮ የሚደረስበት ውሳኔ መሆኑን ነው። በኢትዮጵያ በብሔረሰብ ተወስነው የተደራጁ ድርጅቶች አገር ቤት ያሉትንም ጨምረን ስንቆጥር ቁጥራቸው የትየለሌ ነው። ይህ አደራጃጀት ለአለፉት ሀያ አመታት በመንግሥት ፖሊሲ ጭምር በሰፊው ሲበረታታም የነበረ ከመሆኑም በላይ ህዝብ ውስጥም በሚሰማ ደረጃ ተጽኖ ያለው ጉዳይ ነው። የመብት ጉዳይም አለበት። ስለዚህ በሀገራችን ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ ሀገር-አቀፍ ድርጅቶች ሀገር-አቀፍ የሆነ ፀረ-ወያኔ ትግል ለማድረግ በብሔረሰብ ከተደራጁ ማንኛውም ዓይነት ድርጅቶች ጋር ትብብር ላለማድረግ ቢወስኑ የትግሉን ጠባይና ግዙፉን ወያኔን ለማውረድ በሚመጥን የሚደረገውን የትግል ወሰንና መጠን ያጠበዋልም፤ ያሳንሰዋልም የሚል ዕምነት አለን። ከዚህም በላይ ደጋግመን እንደገለጽነው እንደዚህ ዓይነት አኪያሄድ ከወያኔ በኋላ የሚፈጠረውን ሥርዓት መሰረተ ጠባብ አድርጎ ወደ እማያቋርጥ አለመረጋጋት ይመራናል።

ተግባራዊና ስትራተጃዊ የመቃወሚያ ምክንያቶች

ሁሉን-አቀፍ ትብብርን ለመመስረት ተግባራዊና እስትራተጂያዊ የመቃወሚያ ምክንያት ተደርገው የሚቀርቡትን ሌላ ሶስቱን ዋናዋና ምክንያቶች ደግሞ በሚቀጥለው የጽሁፋችን ንዑስ ክፍል እንመረምራለን። በመጀመሪያ ወያኔን ለማቸነፍ ከብሔረሰብ ድርጅቶች ጋር መተባበር አይስፈልገንም የሚለውን መቃወሚያ እናያለን። ቀጥለን ደግሞ እነዚህ ትብብሮች ኦነግን ለመሰሉ ድርጅቶች እውቅናን መስጠት ነው የሚባለውን ሀሳብ እንመለከታለን። በመጨረሻም የዚህ ዓይነት ትብብር ወቅት አሁን አይደለም የሚሉትን መቃዋሚያ በቂ አለመሆን እናስረዳለን።

  1. 1. ወያኔን ለማሸነፍ ከኦነግና ኦብነግ ጋር የግድ መተባበር የለብንም

ወያኔን ከማቸነፍ አኳያ ብቻ ሲታይ ይህ መቃወሚያ በመጠኑም ቢሆን እውነትነት ሊኖረው ይችላል። ፖለቲካዊ ችግሮቻችን ላይ መፍትሄ ለመስራትና ሽግግሩ ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ መሰራት ያለበትን ስራ ጨምረን ግንዛቤ ውስጥ ካስገባን ግን ስህተት መሆኑን በቀላሉ እንረዳለን። ወያኔን መታገልን እስከማቸነፍ ብቻ ሳይሆን እስከሚተካው የተረጋጋ ሀገራዊ ሥርዓት ድረስ ካያነው ግን በጠረጴዛ ዙሪያ አሁን ቁጭ ብሎ ከነዚህ ድርጅቶች ጋር መፍትሄ መስራት ከአስፈላጊም በላይ ይሆናል።

ከማሸነፍ አኳያም ብቻ እንኳ ስናየው የእስካሁኑ ትግላችን አሸናፊ አላደረገንም። አሸናፊ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን በቅርብም የሚፈለገውን ሀይል አግኝቶ የሚፈለገውን ውጤት ያመጣል ብሎ ለመናገር የሚያስተማምኑ ሁኔታዎች አይታዩም። በርግጥ እስካሁን ውጤታማ ያልተሆነው ከነዚህ ድርጅቶች ጋር ትብብር ስላልተመሰረተ ብቻ ነው ማለት አይደለም። ሌላ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ ግን ሙሉ ሀይላችንን አለማስተባበራችን ዋንኛው ምክንያት ነው። አሁንም እነዚህ ድርጅቶች ሊያበረክቱ የሚችሉትን መጠነ ሰፊ አስተዋጾ እያወቅን መግፋቱ ከማሸነፍ አኳያም ቢታይ ብልጠት ያለበት ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም።

  1. 2. በመተባበር እውቅናን መስጠትና ጉልበት እንዲያገኙ ማድረግ አንፈለግም

ይሄ መቸም የትብብር ፖለቲካ ሂደትን “ሀሁ” ካለማወቅ የሚነገር አባባል ነው የመሰለን። ሁልጊዜም ትብብር የሚደረገው የጋራ ጥንካሬን ለማምጣት ነው። እስከዛሬም በአየናቸው ትብብሮች በሙሉ ተባባሪ ክፍሎች በተናጠል ከትብብሩ ሂደት ካገኙት ጥንካሬ በተጨማሪ የትብብሮችን ጥንካሬ መጨመር ነበር። ሁሌም ግን ሌላው የተሻለ ተጠቀመበት ጉርምርምታ አለ። ትብብሮች ለመፍረስም ለመዳከምም ዋናው ምክንያት ይህ ነው። በትብብሩ ተጎዳን ብለው ጨዋታው ፈረስ ዳቦም ተቆረሰ ባሉ ጊዜ የነበራቸውን ጥንካሬ ይዘው እንኳ መቆየት ሳይችሉ እንደቀሩ ግን በተደጋጋሚ የታየ ነው።

እኛ እስከምንረዳው ድረስ ድርጅቶች ሲተባበሩ የትብብሩ አባላት ድርጅቶች በሙሉ ጉልበት ያገኛሉ። የበለጠ ደግሞ ትብብሩ ጉልበት ይኖረዋል። ትብብሩ የሚፈጥራቸውን ምቹ አጋጣሚዎች ተጠቅሞ ሁሉም የሚጠናከሩበትን ጉዳይ ላይ ጠንክሮ መስራት ለትብብሩ ጥንካሬ ሰጪ እንጂ ጎጂ አይደለም። የድርጅቶቹ ዓላማ ትብብር ውስጥ ገብቶ እጅን አጣጥፎ ለመቀመጥና በሌሎች ጥረትና መሰዋትነት ውጤትን ለመጠበቅ ከሆነ ሌሎች ጉልበት እንዲያገኙ እናደርጋለን የሚለው ምክንያት እውነትነት ይኖረዋል።

በአገራችን ሁኔታ ሀገር-አቀፍም ሆኑ ብሔረሰባዊ ድርጅቶች ህልውናቸውን አጥፍተው የሚተባበሩ አይመስለንም። ግንባር ወይ ቅንጅት ነው የሚፈጠረው። የዚህ አይነት ትብብር ደግሞ ጥንካሬው በየድርጅቶቹ ጉልበት ላይ ነው። ትብብሩ ሲደረግ አንዱ ክፍል አጋጣሚውን እሱን በሚጠቅም መንገድ ብቻ እንዳይጠቀምበት መካኒዝም ማስቀመጥ አንድ ነገር ነው። በደፈናው ላለመተባበር የዚህ አይነት ምክንያቶች ትልቅ ቦታ መስጠት ግን ስህተት ነው።

ይህ ጉዳይ ተጋኖ የሌሎችን ፕሮግራም አስፈጻሚ አንሆንም ድረስ ሄዷል። በሀገራችን ለትብብር የሚቀርቡ ድርጅቶች በሀይል ሚዛን ደረጃ ስንመለከታቸው ይህን ያህል የጎላ ልዩነት ኖሮ በተጽኖ አንዱ የአንዱን አላማ አስፈጻሚ ለመሆን የሚዳረግበት ጉዳይ አልታየንም። ድርጅትም ሆነ ግለሰብ የማያምንበትን የሌሎችን ፍላጎት አስፈጻሚ የሚሆነው ባለማወቅ በፍጹም ሊሆን አይችልም። ተስማማቶ ወይም ፍጹም የሆነ አስገዳጅ ሁኔታ ሲኖር ነው። ይህን የሚሉ ክፍሎች ለራሳቸው የሚሰጡትን ግምት አናውቅም እስከምናውቀው ድረስ ግን ይህን ያህል እጃቸውን ተጠምዝዘው በቀላሉ አንዱ ሌላውን የሚያገለግሉ ድርጅቶች አሉ ብለን አናምንም። ዋናው ቁምነገር ግን ስምምነት ላይ ተደርሶ ትብብር የሚመሰረት ከሆነ የጋራ የሆነ መድረሻው የሚታወቅ ፕሮግራምና አላማ የሚቀረጽ መስሎናል። ያለዚያማ ምን ላይ ነው ስምምነት የሚደረገው።

እውቅናን መስጠት የሚለው ደግሞ በሀገራችን ሁኔታ አንዱ ድርጅት ሌላውን በደጋፊዎቹ ዘንድ በጎ አስተያየት እንዲያገኝ ማድረጉ የሚያመጣው ጉዳት ጨርሶ አይታየንም። እንዳውም እንደ ኦነግ፤ ግንቦት 7 ና ሌሎችም ብሔረሰባዊና ሀገር አቀፍ ድርጅቶች በሰላሚ መንገድ ተባብሮ መስራት ለሀያ አመታት በሕዝብ መካከል ሆን ተብሎ የተዘራውን ጥርጣሬና ጥላቻ በማጥፋት በህዝብ ዘንድ መልሶ መተማመንን ይፈጥራል። በአንድነት ወያኔን ለመታገልም ፍቱን መድኃኒት ነው። በአጠቃላይ ተባብረን እውቅናን መስጠት ጉልበት እንዲያገኙ ማድረግ አንፈለግም የሚለው እንዴት ብሎ የሚጠይቅ የለም ተብሎ የሚደረደር የደከመ ምክንያት ሆኖ ነው ያገኘነው።

  1. 3. የመተባበሪያ ጊዜው አሁን አይደለም

ሌላው ለየት ያለ አቀራረብ ያለው ምክንያት ደግሞ አሁን ጊዜው አይደለም የሚለው ነው። በዚህ መንገድ በቀጥታ ምክንያት ሆኖ ሲቅርብ ባንሰማም ከኦብነግና ከኦነግ ጋር ከማበራችን በፊት እኛ መጠንከር አለብን፤ አሁን አግባብ ባለው መንገድ መፍትሄ ሊስራለት ስለማይችል እራሳችንን ካጠናከርን በኋላ እዚህ ችግር ላይ እንመለስበታለን የሚባሉ ምክንያቶችን አሉ።

ይህ ምክንያት በዚህም ሆነ በዛ መንገድ መፍትሄ ልንፈልግለት የሚገባ ችግር መኖሩን በማመን ነው የሚነሳው። መፍትሄው ላይ ለመነጋገርና ለመስራት ግን አሁን ጊዜው አይደለም ነው አንደምታው። ተጽኖ ማሳደር እንድንችል መጀመርያ እኛ መጠንከር አለብን ነው። ጥንካሬ ደግሞ እንደሚታወቀው አንጻራዊ ነው። ስለዚህ ይህ አስተሳሰብ የሀገር-አቀፍ ድርጅቶች በብሄረሰብ የተደራጁ ድርጅቶች ላይ የጥንካሬ የበላይነት እስክናገኝ እንጠብቅ ነው። ይህ አይነት አካሄድ የሚሰራበት ሁኔታ ይኖራል። አሁን የትግሬ ዘረኞች የሀገሪቱን የጦር፤ የጸጥታ፤ የፕሮፖጋንዳና የኢኮኖሚ አውታር በተቆጣጠሩብትና ሆን ብለው በሕዝቡ ውስጥ የከፈፍለህ ግዛ ፖሊሲ በሚያራምዱበት ሰዓት አንዱ ዓይነት ተቃዋሚ በሌላው ዓይነት ተቃዋሚ ላይ እዚህ ግባ የሚባል የጥንካሬ የበላይነት ሊኖረው አይችልም። የሚፈለገው ጥንካሬ የሚመጣው በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ በሀገር-አቀፍ ድርጅቶች ፕሮግራም ዙሪያ ያለው ድጋፍ ስፋት ነው። ይህ ደግም አሁንም ቢሆን ለ20 ዓመታት ወያኔን እንቅልፍ የነሳው ኃይል ነው።

ስለዚህ ከሁሉም በፊት ተቃዋሚዎች አብረው ለመስራት የሚያስፈልገው በመጀመርያ አሉ የምንላቸው ችግሮቻችን ላይ መፍትሄ ለመስራት ቀናነትና ማቻቻል እንጂ ይህን ያህል አንፃራዊ ጉልበት የሚፈልግ አይመስለንም። ያም ሆኖ ይህ አቀራረብ መፍትሄ ለመሻት ለሰላም የተዘረጋን እጅ ይጠመዝዛል። በአሁኑ ጊዜ የተገኙ ሁሉን-አቀፍ ትብብርን ለመመስረት አጋዥ የሆኑ ሁኔታዎች ሁሌም ይኖራሉ ማለት አይቻልም። ይህ አሁን ጊዜው አይደለም የሚለው አኪያሄድ በወቅቱ የተፈጠረን አጋጣሚ ሁሉ ለሚፈልጉት ውጤት መቶ በመቶ እርግጠኛ ካልሆኑ እርምጃ መውሰድ ያማይችሉ ሰዎች አኪያሄድ ነው። በዚህ ዓይነት አኪያሄድ ታግለው ያቸነፉ፤ ነግደው የከበሩ በጣት አይቆጠሩም።

በሌላ በኩል ድግሞ ነገ ማን አሸናፊ ወይ ጉልበተኛ ሆኖ ይወጣል የሚለው ላይ የተጠጋ ግምት ሊደረግበት ይቻላል። በርግጠኝነት ዛሬ ላይ ሆነን ልንናገርበት የምንችለው ግን አይደለም። በዘውግ የተደራጁት ወይ በህብረ ብሄር የተደራጁት አንዳቸው አሸንፈው ሊወጡ የመቻላቸው እድል አለ። በነዚህና በሌሎችም ብዙ ምክንያቶች ዛሬ መግባባት ላይ መድረስና አብሮ በመታገል አንድነትን ማጠንከር የተሻለ ይመስለናል።

ችግር እንዳለ እያወቁ ለዛውም አንድነታችን ላይ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ጊዜው አሁን አይደለም ማለት ምን የሚሉት ምክንያት እንደሆነ አይገባንም። ለዛውም ተነጋግሮ መፍትሄ ለመስራትና በአንድ ሆኖ ለመታገል በጎ ፍቃድ እያለ ነው። ለድርጅት ሰዎች ይህ ሊያሳምን ይችል ይሆናል፤ ለጠቅላላው ህዝብ ግን የሚዋጥ ምክንያት በፍጹም አይመስለንም።

መደምደሚያ።

በዚህ ጽሁፍ የግንቦት 7፤ ኦነግ፤ ኦብነግና ሌሎች ኃይሎች በሁሉን-አቀፍ ትብብር ሥር መጥተው ወያኔን ለማስወገድና በምትኩ በእኩልነት፤ በፍትህና በዲሞክራሲያዊ መርህ ላይ የተመሰረተ ለውጥ በኢትዮጵያ ለማምጣት የጀመሩትን መልካምና አስቸጋሪ የትብብር ውይይት ደግፈን – በአንፃሩ ደግሞ ይህን የሚቃወሙ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚሰጧቸውን የመርህ፤ የስትራተጂና የተግባር መቃወሚያ ሃሳቦች ላይ የተቻለንን ሂስ አቅርበንባቸዋል። ይህንን በማድረግ የሁሉን-አቀፍ ትብብር ተቃዋሚዎችን ሃሳብ ሙሉ በሙሉ እናስቀይራለን የሚል ግብዝ ዕምነት የለንም። ሆኖም ግን ባቀረብነው ማብራሪዎች ምክንያት ስለ ሁሉን-አቀፍ ትብብር የተለጠጠ ትርጉምና አቋም እየሰጡ “የተቃዋሚ ተቃዋሚ” በሚያሰኛቸው ዓይነት የትብብሩ ሙከራ ላይ ያነሱትን ዘመቻ ጋብ ያደርገው ይሆናል ብለን እንገምታለን። ከተፈለገና ከጠቀመ ደግሞ ሁሉን-አቀፍ ትብብርን በተመልከተ በሚነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ የሰከነ ውይይቱን መቀጠል ይቻላል። እንደ እኛ እምነት ይህን ዓይነት ውይይት ጠቃሚኑቱ የላቀ ነው ብለን አናምንም። ጉዳዩ የሚጠይቀው ከማያቋርጥ ውይይት ይልቅ የተግባር ፍተሻ ለማድረግ አቋም መያዝን ነው።

ይህን የሚያሰኘን የሀገራችን ፀረ-ወያኔ የትግል ሜዳ ከስፋቱ የተነሳ በትብብር ጉዳይ ላይ ሁለት አይደለም ሶስትና አራት የትግል ሙከራዎችን ያለምንም መጠላለፍ ማስተናገድ ይችላል። ለዚህም ጧት ማታ የሁሉን-አቀፍ ትብብር ብለው የሚታገሉትን መቃወም አቁሞ በአማራጩ “የአንድነት ኃይሎች” በሚል መጠሪያ የሚደረገውን የትብብር ሥራ ላይ የድጋፍ ሥራ መሥራት ይመረጣል። ይህንን የአንድነት ኃይሎችን የህብረት ሃሳብ ማብራራት የተሻለና የበለጠ ጠቃሚ ስሚሪት ይመስለናል። ለምሳሌ ለእኛ ይህ የአንድነት ኃይሎች ብላችሁ የሰየማችሁት ትብብር ከአሁን በፊት ተፈጥሮ እስከ አሁንም ካለው የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ኃይሎች ሕብረት እንዴት እንደሚለይ ግልጽ አይደለም። ልዩነት ከሌለ ደግሞ አዲሱ ትብብር ምን ምን ቢሰራ ነው ከቀድሞው ህብረት የተሻለ ውጤት የሚያመጣው? በተጨማሪም የዚህ የአንድነት ኃይሎች ትብብር ጥሪ አቅራቢዎችና ደጋፊዎቻቸው የትግል ጥሪያቸው ወያኔን ተሻግሮ በአዲስ የፊልሚያ ግንባር እስከመገንጠል የሚሉትን ኃይሎችንም እንደሚጨምር አልፎ አልፎ ይሰማል። ይህ በአሁኑ ሰዓት ትርጉም ያለው የፖለቲካ አኪያሄድ ነው ወይ? ምን አገባችሁ ባትሉን በሁሉን-አቀፍ ትብብር ላይ የማትስማሙ ክፍሎች ኃይላችሁን የሌላውን ፀረ-ወያኔ ሙከራ ለማስተጓጎል ከማጥፋት ይልቅ ለነዚህ ከላይ ለጠቀስናቸውና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች ተግባራዊ መፍትሄ መፈለጉ የተሻለ የትግል ሜዳ አይደለም ወይ? ይህን ብታደርጉና ሁሉም በየራሱ ሥራ ቢሰማራ ሁለቱም ዓይነት የትብብር ኃይሎች በየ አቅጣጫው ወያኔን ማጥቃት ይጀምራሉ። ከዚህ ተግባራዊ ሥራን ወደፊት ሕዝቡም እኛም አሁን እንድምናደርገው ከመላምት አልፈን በተግባር የተፈተኑ ወያኔን የማታጋያ መሳሪያዎች እናገኛለን።

ሃሳባችንን ለማጠቃለል የሁሉ-አቀፍ ትብብር ኢትዮጵያችን ውስጥ አሉ የሚባሉ ችግሮችን፤ እስከመገንጠል ብለው የሚጀምሩ የብሔረሰብ ድርጅቶች ጥያቄዎችንም ጨምሮ በጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሄ ለመፈለግ ማስተናገድ የሚያስችል ነው እንላለን። ለሚነሱ ብዙ የመብት ጥያቄዎች መልስ መስጠትና የሚመለሱበትን መንገድ ማመቻቸት እንዲሁ ያስችላል ባዮች ነን። ቀላልና በሁሉም ነገር ሁሉንም መቶ በመቶ የሚያስደስት መፍትሄ አለው ብለን ግን አንገምትም።

ስለዚህ ተባበሩ ሲባል የምንለው ተቀምጣችሁ ተነጋገሩ ነው። የጋራ ግብ አስቀምጡ። በሁሉም መስክ የአገራችንን የወደፊት እጣ ፋንታ ተልሙ ነው። ሁሉም ተፈጻሚ የሚሆነው ግን የመንግስት ስልጣንን መቀማትና መቆጣጠር ሲቻል ነው። ያም ሆኖ በአንድ ጀንበር ተፈጻሚ የሚሆን መፍትሄ የለም። ጊዜን ይፈልጋል። የሚፈልገው ላስቀመጣችሁት ግብና ትልም ቁርጠኛነትና ታማኝነት ነው። ግንቦቶችና ኦነጎች ሁሉን ያካተተ ትብብር ለመመስረትና የአገራችን የፖለቲካ ችግሮች ላይ ያገባኛል የሚል ሁሉ ያሳተፉ መፍትሄ ለመሻት የሚያደርጉትን ጥረት እናደንቃለን። እንደግፋለን መደገፍ ያለበት ጥረት ነው ብለን እናምናለን።

የተጀመረው የሁሉን-አቀፍ ትብብር ውይይት ጉዞ የት ስምምነት ላይ እንድሚደርስ ለጊዜና ለትብብሩ ቀጥተኛ ተሳታፊዎች እንተወዋለን። እንደ እኛ እምነት ግን ይውይዩ መዳራሸ የሚቀጥሉት ሁለት ሃሳቦች ቢሆኑ ሁላችንንም አቸናፊ ያደርገናል የሚል ጽኑ ዕምነት አለን። አንደኛው የትብብሩ መዳረሻ ዲሞክራሲያዊ ስርአት በአገራችን መመስረት መሆን አለበት። ይህም ማለት አንድ ሰው አንድ ድምጽ በሚለው በምርጫ ሂደት ለመዳኘት ሁሉም ፍቃደኛ መሆን አለበት። ሁለተኛው የትብብሩ መዳረሻ ደግሞ የኢትዮጵያ ሉዕላዊነት መሆን አለበት። ከዛ መለስ የሆኑ ጥያቄዎች በሙሉ ጠረጴዛ ላይ ቀርበው ልንነጋርበት እንችላለን። አሉ የሚባሉ ጥያቄዎችና ችግሮች በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ ናቸው። ኢትዮጵያን አንድ ሉአላዊ አገር መሆኗን ጥያቄ ውስጥ ሳናስገባ ምፍትሄ ልንሰራ በደንብ እንችላለን የሚለው ቅድመ ሁኔታ ሚዛናዊና ሊያቀራርብ የሚችል አቋም ሆኖ አግኝተንዋል። በርግጥ በመጀመርያ ይህ ሁለተኛ ሃሳብ በቅድመ ሁኔታ መቀመጡ ላያቀራርብ ይችላል ብለን አስፈርቶን ነበር።

ዳኮታ የጥናት ማዕከል ስለአገራችን መጠነ ሰፊ ችግር፤ ስለወያኔ አምባገነንና አውዳሚ ሥርዓትና ትግሉ ስላለበት ደረጃ ከዚህ በፊት ጽፈናል። በመፍትሄ ደረጃ ደግሞ ሰለ ትብብር አስፈላጊነትና ጠቃሚነት፤ ስለ ጠንካራ የመረጃ መረብ መዘርጋት፤ ትግሉን በሚያስፈለገው መጠን በገንዘብ ሰለመደገፍ፤ መሳርያ የያዘውን ፀረ-ወያኔ ኃይል እንዴት እንድረሰው በሚሉና በሌሎች ርእሶችም ላይ ሃሳባችንን ሰጥተናል። ሁሌም መፍትሄ ላይ ስንጽፍ መፍትሄ ብለን የምናስበው ነገር ሁሉ ስኬታማነቱ ከድርጅቶቻችን በአንድ መቆምና በጋራ መታገል ቅድመ ሁኔታ ጋር ይያያዝብናል። ሁሌም ተቃዋሚ ኃይሎች ልዩነታቸውን አቻችለው በአንድ ሊቆሙ ካልቻሉስ የሚለው ጥያቄ ሲያሳስበን ቆይቷል።

የቅርብ ጊዜው የሁሉን-አቀፍ ትብብር ድርጅቶች ውይይትና ሂደቶች መፍትሄ ሊሆን የሚችል ነገር አጭሮልናል። በዚህ ሁኔታ በአንድ በኩል ስንበረታታ በሌ በኩል ደግም ፀረ-ወያኔ ከሆነው ኃይል የተወሰነው ክፍል ትብብሩን አልቀበልም ያለ ይመስላል። ይህ ብቻውን ችግር አይደለም።የግድ ሁሉም ድርጅቶች በአንድ አቅጣጫ መሄድ አለባቸው አንልም። ዳሩ ግን የተቃዋሚ ተቃዋሚነት መቆም አለበት። እንዲሁም በሁሉን-አቀፍ ትብብር የተሰማሩት ድርጅቶችም ሆኑ በአንድነት ኃይሎች የተጀመሩ ትብብሮችን በቶሎ ሥራ ተተርጉመው ትግሉን እንዲያጧጡፉ እናሳስባለን።

Wednesday, July 27, 2011

dakotreserch2@yahoo.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 29, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.