ዓባይ ደረቀ አሉ!

አሥራደው (ከፈረንሳይ)

ዓባይ ደረቀ አሉ የወንዞች አባት፤
እጅግ ቢበዛበት የዜጎች ጩኸት፤
ዓባይ ደረቀ አሉ ድንጋዩ ፈጠጠ፤
ከሱ ጅረት ይልቅ የ’ንባ ጎርፍ በለጠ፤
ዳግም ላይታለብ ላይሰጥ ወተቱን፤
ጣናን አመከነ አሟጠጠ ምንጩን፤
እኔ ድርቅ ልበል እኔ ልሙትልሽ፤
ብሎ ዓባይ ደረቀ ጦቢያ ለልጆችሽ ::
ዓባይ ደረቀ አሉ ጣናን አሟጠጠ፤
ጦርነት ያማረው ቀረ እንደቋመጠ ::
በጭራሽ ! እንዲያውም ! እንዲፈስ አልሻም !

ንጹሕ የድሃ ደም፤
በኔ ተመካኝቶ፤
መከበር መኮፈስ አይገኝም ከቶ፤
ብሎ ዓባይ ደረቀ፤
ጦር ለናፈቃቸው ቁርጡን አሳወቀ ::
ዓባይ እንደ እንቶኔ ጨካኝ ዜጋ አይደለም፤
በሱ ጅረት ፋንታ ንጹሕ ደም አይፈስም ::

« ዓባይ ሞላልሽ ! ሞላልሽ ! አዘቅት ሆነልሽ ! » ብሎ ያዜመለት፤
ሽማግሌው ወጣት፤
ኮረዳዋ አሮጊት፤
ሳይቀሩ ሕፃናት፤
እንዴት?! ለምን?! ይሙት፤
እንቶኔ ሊሞካሽ ሊዘባነንበት ::

አገር አመሳቅሎ አገር ወዳድ መሳይ፤
ያፍ ዝልዝል ለማቅረብ ዛሬ መማል ባባይ፤
ያውቀዋል ልባችን ይቅር መዘላበድ፤
አይገኝምና ካባይ ወዲያ ዘመድ ::

የማይሞት ወንዝ ሞተ ዓባይ ደረቀ አሉ፤
በፈለቀበት ምድር በዝቶበት በደሉ፤
ዳግም ላይታለብ ላይሰጥ ወተቱን፤
ጣናን አመከነ አሟጠጠ ምንጩን፤
እኔ ድርቅ ልበል እኔ ልሙትልሽ፤
ብሎ ዓባይ ደረቀ ጦቢያ ለልጆችሽ ::

አንተስ ?! እኔስ ?! አንቺስ ?! እኛስ ?!
አንድ ቀን : ለዓባይ ወንዝ መታሰቢያ ትሁንልኝ ::


ግብጥ
ዳውላ በአህያ- አህያ ዳውላ
ቀልቀሎ አቁማዳ- ሆነና ቱልቱላ
ግብጥ ድርቡሽ ቢባል- ደደቢት አስመራ
እስኪ ስለአባይ ስል- ማንን ልውደድ ልጥላ?
ላኪና ተላኪ- ሆናቹህ ሳላቹህ
ማንን ልውደድና- ጠላሁ ልበላቹህ?
አእምሮ የማይፈትን-ፍንትው ላለ እውነት
እንካስላንትያ- ባንባባልበት!

ዳግማዊ ዳዊት
ታህሳስ 2003 ዓ.ም.
Ethio_dagmawi@yahoo.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on December 10, 2010. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.