ወያኔ ሱቆችን ማሸግ ጀመረ: ነጋዴው ህብረተሰብ እየታመሰ ነው!

EMF (Addis Ababa) በየፍጆታ ምርቶች ላይ ወያኔ ባወጣው ግብታዊ የዋጋ ተመን እና ቁጥጥር የነጋዴውን ህብረተሰብ እያመሰው ይገኛል:: የዋጋ ቁጥጥሩ የመጣው የዩሮ ውድነትን ለመቀነስ ነው የሚለው የአቶ መለስ መንግስት ከነጋዴው ህብረተሰብ ጋር የተያያዘው እልህ ችግሩን የበለጠ እያባባሰው እንደሆነ ይነገራል::

“ጣራ የነካው የሃገሪቱ የኑሮ ውድነት ችግር መንስኤ ወያኔ በአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶች ቀጥያ ትእዛዝ የሃገሪቱን የብር የመግዛት አቅም መግደሉ ነው:: የሃገሪቱ ብር የመግዛት አቅም በአንድ ጊዜ በብዙ እጥፍ ሲወድቅ: አከፋፋዮች: አምራቾችና አስመጪዎች በውጭ ምንዛሪ የሚያስገቡዋቸው ሸቀጦችም በብዙ እጥፍ ማደጋቸው የግድ ነው” የሚሉት ነጋዴዎች: አሁን እየተጫነባቸው ያለው የዋጋ ተመን ይህንን ግሽበት ግንዛቤ ውስጥ አለማስገባቱን ያማርራሉ::

ይባስ ብለው አቶ መለስ ዜናዊ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንን በማንአለብኝነት ያወጡትን መመሪያ ተግባራዊ የማያደርገውን ነጋዴ እጅ እንደሚቆርጡ አስጠንቅቀዋል::

የዋጋ ተመን እና ቁጥጥር መመርያው የወጣውና ተግባራዊ እንዲሆን የታቀደው ባለፈው ሳምንት ይሁን እንጂ በአዲስ አበባም ሆነ በክፍላተ-ሃገሩ ተቀባይነት አላገኘም:: በተለይ በችርቻሮ ላይ የተሰማራው ህብረተሰብ ሸቀጡን ከገዛበት ዋጋ ቀንሶ እንደማይሸጥ እየተናገረ ከመሆኑም በላይ ለገበያ መቅረብ ያለበትን ንብረት በኪሳራ ከመሸጥ ብሎ በየካዝናው ማስቀመጡን እንደተያያዘው ምንጮቻችን ገልጸዋል::

የአቶ መለስ መንግስት በነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል:: በዛሬው እለት በርካታ መጋዘኖችና ሱቆችን ማሸግ መጀመሩ ደግሞ ውጥረቱን የበለጠ አባብሶታል::

በገበያ ላይ የሸቀጦች መጥፋት በነጋዴውም ሆነ በሸማቹ ህዝብ ላይ ይህ ነው የማይባል ችግር በመፍጠር ላይ ይገኛል::

አዋጁ ከጅምሩ የገበያውን ሁኔታ ሊያረጋጋ እንደማይችል የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ተናግረዋል:: ከዚህ ቀደም መሰል አዋጆችን በተገበሩ ሀገሮች እንዲህ አይነቱ አዋጅ ተሞክሮ ውድቅ መሆኑም የሚታወስ ነው:: አሁን መተግበር ሲጀምር ደግሞ በነጋዴዎች ዘንድ ከፍተኛ የመንግስት ጥላቻን አስከትሏል። በአዋጁ ትግበራ የራሱ የወያኔ ደጋፊዎች ሳይቀር ቅሬታቸውን እያሰሙ መሆኑንም ለመወቅ ተችሏል::

የዋጋ ቁጥጥሩ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ሊቀርፈው አይችልም እንዲያውም ችግሩን አባብሶት ሃገሪቱን ወደከፋ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ያመራታል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም::

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 12, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.