ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አፈር ስሆን፤ ፌስ ቡክዎ ላይ ‘አድ’ ያድርጉኝ!

[አቤ ቶኪቻው]

ውድ ጠቅላይ ሚኒስትር… ብዬ ልጀምር ነበር “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት!” ሲሉኝ ታየኝና ተውኩት።

ቆይ እስቲ ወዳጄ መጀመሪያ ከእርስዎ ጋር ሰላምታ እንለዋወጥ። እርስዎ ኖት ቀሪ ሃብቴ…! እንዴት አሉልኝ…? ጤናዎ አማን ነው? ግራ ቀኙ ሁሉ ሰላም ውሎ አድሯል? ጎሽ እንዲህ ነው እንጂ የጨዋ መልስ! እርሱ ጠባቂው ለወደፊቱም እቅፍ ድግፍ አድርጎ ይጠብቅልኝ።

የዛሬው ጨዋታዬ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሬ ጋር ነው… ሰሞኑን ከአኪልዳማ ቀጥሎ ቴሌቪዥናችን አስቸኳይ ያደረሰው አንድ ፊልም ደግሞ ተሰርቷል። እርሱን ካየሁ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አግኝቶ የማውራት ጉጉት አደረብኝ። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሬን በፌስ ቡክ ባገኛቸው ብዬ ተመኘሁ… ይሄኔ አንዳንድ ከእኛ በላይ ለርሳቸው ተቆርቆሪ የሆናችሁ ወዳጆቻችን “አለቀረብህም… በየትኛው ግዜያቸው ነው አንተን ፌስ ቡክ ላይ አድ የሚያደርጉት?” ብለው ሊጠይቁኝ እንደሚችሉ እጠረጥራለሁ። ጠርጥሬም እመልሳለሁ… “አድ ቢያደርጉኝ ለራሳቸው ነው… ህዝባቸው ምን እንደሚል ለማየት ከፈለጉ ይምጡ ቻትም ያድርጉኝ…!” እላለሁ። ደሞም እጨምራለሁ “እንኳን ለቻት ለጫት የሚሆን ግዜስ ይገኝ የለም እንዴ!?”

ለማንኛውም ቆይ… አሁን የማነጋግራቸው ጉዳይ አለኝ። ፌስ ቡክ ላይ አድ ካደረጉኝ፤ ባይሆን እጨምርላቸዋለሁ። ለዛሬው ግን እንደሚከተለው እጀምራለሁ።

እኔ የምልዎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት ይዞታል? ባለቤትዎስ እንዴት ናቸው…? ልጆችዎስ…? በነገራችን ላይ እንግሊዝ አገር የምትማረው ልጅዎ… ስምሃል መለስ ከእርስዎ እኩል ታዋቂ ሆናልዎታለች…! የምሬን ነው የምልዎ… ከፈለጉ ጎግል ላይ ካሰኝዎት ፌስ ቡክ ላይ “ስምሃል መለስ” ብለው ፈለግ ፈለግ ቢያደርጓት ከሰው መሃል ፈልፍሎ ያመጣልዎታል። ያኔ በዘጠና ሰባቱ ምርጫ ግዜ ህፃን ካዋቂ ሳይይለዩ ያስለቀሙበት አንድ አለሞ መተኮሻ መሳሪያ የለም? እሱን ይዛ የተነሳችውን ፎቶግራፏን ቢያዩማ ቁርጥ እርስዎን!!!

እኔማ እርሱን ያየሁ ግዜ፤ “አቤት… ጀግና የጀግና ልጅ…!” ብዬ አደነቅሁለዎት። ታድያ አድናቆቴን የሰማ አንድ ወዳጄ ከት ብሎ ሳቀብኝ… ምነው? ብዬ ማብራሪያ ብጠይቅልዎ… “እርሰቸውን ጀግና ስትል ራሳቸውም ቢሰሙህ ይቀየሙሃል?” አለኝ። ነገሩን ሲያጫውተኝ ተገርሜ ተገርሜ ላበቃልዎ ነው? ለካስ ርስዎ ማስተኮስ እንጂ መተኮሱ ላይ እጅግም ነዎትና። እኔ ይሄንን መቼ አወቅሁ…!? ይሄው ወዳጄ አይደል እንዴ፤ ባለፈው ግዜ ኢሳት ቴሌቪዥን ኢንተርቪው ያደረጋቸውን አንድ የጥንት የትግል አጋርዎን ቃለ ምልልስ ያሳየኝ!?

አቶ ገብረመድን ይባላሉ… ረስተዋቸው ብቻ እንዳይሆን… ምነው እንኳ ያኔ “አሸባሪ” እያላችሁ… ባንክ ቤት በምትዘርፉበት ዘመን አክሱም ባንክን ለመዝረፍ አብረዎት የተመደቡ ታጋይ…! (ይቆዩኝማ አንዴ ቅንፌ ውስጥ ላስገባዎ… (አይዞት ቅንፍ ነው ያልኩዎ… እኛ እርስዎ ስንት መከራ እና ችግር ውስጥ ሲያስገቡን ዝም አይደል ያልንዎት…? ስለዚህ እሺ ይበሉኝና አንዴ በቅንፍ ላውራዎ….(ያኔ ጫካ እያላችሁ ከአምባ ገነኑ ደርግ ጋር ስትታገሉ… ያኔ የይስሙላ ምርጫ ከሚያደርገው ደርግ ጋር ስትፋለሙ… ያኔ የተቃወሙትን ሁሉ ከሚያስረው እና ከሚያሳድደው ደርግ ጋር ስትፋለሙ… ይገርምዎታል ያንን የመሰለ ትግል አንዳንድ ሃይሎች “ሽብርተኝነት” ነበር… ብለው፤ በአሸባሪነት መዝዝገብ ላይ ፅፈዋችሁ አይቻለሁ። እኔ እና ወዳጆቼ ግን… ምንም እንኳ በባንክ ዘረፋ ሳይቀር ተሰማርታችሁ እንደነበር ከራሳችሁ አንደበት ሁላ ብንሰማም፤ ያንን ግዜ ከነበረባችሁ ችግር አንፃር አሸባሪ ሳትሆኑ የነፃነት ታጋዮች እንደነበራችሁ እናምናለን (በሌላ ቅንፍ ነግ በኔ ነው ብለን እንጨምራለን ምን ነግ ዛሬ እንጂ…!)))) ቅንፍ ውስጥ አቆየሆት። ይቅርታ ያድርጉልኝ… አዩት አይደል እርስዎ ሃያ አመት በችግር ቀንፈውን ምን ያህል እንደተጎዳን ተመለከቱልኝ…? እንኳን የችግር የፅሁፍ ቅንፍ ራሱ እንዴት እንደሚያደክም… እዩልኝ እንጂ… (አይዞት ለጨዋታ ነው)

የሆነ ሆኖ  ብዬ እቀጥላለሁ… የሆነ ሆኖ እርስዎን ጀግና ስል የሰማኝ ወዳጄ በኢሳት ቴሌቪዥን የተላለፈ አንድ ቪዲዮ አቋደሰኝ። ሰውየው በእርሰዎ መሪነት ለባንክ ዘረፋ ስለተሰማራው ቡድን እየተረኩ ነበር። ታድያ ድንገት ተኩስ ተከፍቶ ኖሮ ጋንታዎን አንደ አድባር ቆሎ በትነው እንዴት ከአካባቢው እንደተሰወሩ ሲያወሩ ሰውየው አሁን ራሱ እየተደነቁ ነበር…! ለነገሩ የጥይት ጩህትም ሆነ ተኩስ እኔም አልወድም… በዚሁ ልክ ሌሎች ላይም ይህ እንዲመጣ አልመኝም…

እኔ የምልዎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር… እርስዎ ግን እንደዛ የሚፈሩትን ጥይት ስለምን በሌሎች ላይ ደጋግሞ እንዲተኮስ ያዛሉ…? ብዬ ልጠይቅዎ ነበር ለካስ መንግስት ነዎት… “መንግስት አይከሰሰ ሰማይ አይታረስ…” በምንለው በኛ መሃል የነገሱ ማንም የማይከስዎ ማንም የማይወቅስዎ ንጉስ ነዎትና…!

ከዛሬ አስር አመት በበፊት፤ በኤርትራ ተወረርን ብለው… “ኡኡ!” ቢሉ ግዜ ብዙዎች እምነት ጥለውብዎ … “አዎ ተወረን እንጂ ባንወረረ እንዲህ አይጮሁም ነበር…” በማለት ሻብያን ልክ እናስገባዋለን ብለው ፋኖን እየዘፈኑ ዘመቱ… በዛ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች እንደሞቱ ሰምተን አምርረን አለቀስን… ያ ሁሉ ሞቶብን ያገኘነው ድል ግን በዜሮ ተባዛና የተዋደቅንላት ባድመ ለኤርትራ ተፈረደች… ለማይረባ ጦርነት ያ ሁሉ አምራች ወጣት አለቀ። ከዛን ግዜው ድራማ ምንም የማይረሳኝ… “ባድመ ለኛ ተፈረደልን” ብለው እርስዎ ይሁን ሌላ ባለስልጣን ብቻ ባጠቃላይ መንግስትዎ ያስወጣንን የደስታ ሰልፍ ነው። የተጭበረበረ ደስታ! ታድያ አሁንም የጭዳ ሰዓት ደረሰብዎ መሰል ሌላ ጦርነት እያሰቡ እንደሆነ ተሰማ…!

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አፈር ስሆን ፌስ ቡክዎ ላይ አድ ያድርጉኝ…! አሁን እያወጁ ስላሉት ጦርነት ጥቅምና ጉዳቱን… ትንትን ብትንትን አድርገው የሚያሳዩዎት በርካታ የፌስ ቡክ ወዳጆች አሉኝ… የምሬን ነው የምልዎ  በፍሪጁ ፓርላማዎ ውስጥ ሃሳብዎን እያቀረቡ ቃላትዎችዎ በረዶ ከሚሰሩብዎ፤  ከእኛ ጋር ፌስ ቡክ ላይ ቢወያዩበት ይመኑኝ አጥጋቢ የሆነ ግብረ መልስ ያገኛሉ። (ግብረ መልስ ማለት “ፊድ ባክ” ማለት ነው።)

በነገራችን ላይ “ግብረ መልስ” የምትለውን ቃል ያገኘነው ከ ተወዳጁ ኢቲቪዎ ነው… ባለፈው ግዜ “አኪልዳማ” የተባለ አንድ ድራማ ሲያሳዩን አልነበር…!? እኔ የምልዎ አረ ሳልጠይቅዎ… አንድ ቀን በፓርላማዎ “የታሰሩትን ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች አሸባሪ ስለመሆናቸው ከበቂ በላይ ማስረጃ አለ ሁለት ሳምንት ታገሱ…” ሲሉን የነበረው… ይሄንኑ አኪልዳማዎን ነበር እንዴ…? እውነቴን ነው የምልዎ ፌስ ቡክ ላይ አድ አድርገውኝ ቢሆን ኖሮ… ወዳጆቼ በዚህ ድራማዎ ላይ እንዴት እንዴት እንደተሳለቁበት ያዩ ነበር። ደግሞም ዝምብሎ መሳለቅ ብቻ እንዳይመስልዎ… ከነ ማስረጃቸው የተሰጠውን አስተያየት ተመልክተው ቢሆን፤ በዛ ድራማ ላይ የተሳተፈ አንድም ሰው ሳይቀርዎ ከኢቲቪ ሙልጭ አድርገው ያባርሩ ነበር። አውነቱን ለመናገር ፊልሙ ላይ በብቃት የተወነው ታዋቂው አርቲስት ደበበ እሸቱ ብቻ ነበር።

አሁን በቅርቡ ደግሞ አዲስ ፊልም አስመርቀውናል። በዚህ አጋጣሚ ፊልም በማምረት  ሆሊውድንም ቦሊውድንም እየበለጡ እንደሆነ ላረጋግጥልዎ እወዳለሁ። የምሬን ነው የምልዎ…! እኔ እንደ አንዳንድ አሽሟጣጮች ፊልሞቹ፤ “የኦስካር ሽልማት ባያገኙ፤ የስካር ሽልማት አያጡም…” ብዬ አላሽሟጥጥብዎም። ይልቅስ ከሌሎቹ ፕሮግራሞች በተሻለ ጉጉት እንደማያቸው እነግርዎታለሁ። ታድያ በዛው ልክ አስተያየቱ እና ትችቱንም እከታተላለሁ። ይሄ በቴሌቪዥን እየቀረቡ “በጣም አስተማሪ ነው… ድጋሚ ቢታይ ላላዩት የህብረተሰብ ክፍሎች ይጠቅማል… በእውነቱ መንግስት ይሄንን ፊልም ባያሳየን ኖሮ አልቆልን ነበር… ወዘተ ወዘተርፈ…” የሚሉትን አይደለም። አስተያየት የምልዎት፤ እነርሱ ራሳቸው በፌስ ቡካቸው ለይ የሚለጥፉትን አስተያየት ማለቴ ነው። እባክዎን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፌስ ቡክ ላይ አድ ያድርጉኝና ብዙ የማሳይዎት ነገር አለኝ።

እኔ የምልዎ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄ አዲሱን ፊልም ደግሞ ስመለከት የክበበው ገዳ ቀልድ ትዝ አለኝ። ሚስቱ አርግዛበት “ሰላማዊ ሰልፍ አማረኝ!” ያለችው፤ ሸምሱን አስታወሱኝ። እርሱ ያኔ ሚስቱ ነብሰ ጡር የነበረች ግዜ… “መቶ ብር አማረኝ” ስትለው እያለቃቀሰ ሲሰጣት፤ አማረኝ ያለችውን ሁሉ ሲያሟላላት… “ሰላማዊ ሰልፍ አማረኝ!” ያለችው ግዜ የተጨነቀው ጭንቀት ትዝ አለኝ። ምን ያድርግ ብለው ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ከየት ይመጣል? ባለፈው ግዜ ታዛዥዎ ጓድ በረከት ስሞን በፃፉት መፅሐፍ ላይ “ብዙዎች ባለፈው በ97 የተከለከለው ሰላማዊ ሰልፍ አሁንም ጭምር የተከለከለ ይመስላቸዋል።” ብለው ነግረውን ነበር። አዎና እውነታቸውን እኮ ነው እንኳን ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ቀርቶ ሰላማዊ ሰለፍ የሚፈቅደው አካል ራሱ ያኔ የከለከሉት ሰልፍ አሁንም እንደተከለከለ ያለ ነው የሚመስለው እኮ!… በዚህ አጋጣሚ እባክዎን አንድ አፍታ ወጣ ብለው “ከዛሬ ጀምሮ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፣ ከቤት ውጭ መሰብሰብ… ተከልክሏል!” ባሉበት አንደበትዎ “ያኔ የከለከልኩት ተፈቅዷልኮ!” ብለው ይንገሩንማ!

እናልዎ የሰሞኑን ፊልም በቲቪ ሳየው የክበበው ገዳ “ሰላማዊ ሰልፍ አማረኝ…” ትዝ አለኝ አላልኮትም…!? ለምን መሰልዎ እኒህ ሰውዬ “ጦርነት አማረኝ!” ያለቻቸው ነብሰ ጡር አለች እንዴ? ብዬ አስቤ እኮ ነው። መግቢያዬ ላይ ባለቤትዎስ ደህና ናቸው..? አባባሌን እና ለጥቄም ልጆችዎስ?  ብዬ የጠየኮትን ልብ ቢሉትኮ ውስጡ ጥርጣሬ ብጤ አለው…!  ምን ላድርግ ብለው ነው ጭንቅ ቢለኝ ነዋ። “ጦርነት አማረኝ!” ያልዎት አለ እንዴ?

ፉከራዎ… እንደ ተኳሽ ነው። “በማያዳግም ሁኔታ መቀጣት አለበት!” ሲሉ ራስዎ ሄደው ኢሳያስን በጥፊ በርግጫ ሊሏቸው የፈለጉ ይመስላሉ። ግን በማያዳግምም ሆነ በሚያዳክምም መልኩ ቢሆን ለሚወሰደው እርምጃ መስዋት የሚሆነው ምስኪኑ የአገሬ ወጣት ነው። ታድያ ይህ ምስኪን ወጣት እንደያኔው ሆ…! ብሎ ሊዘምት ዝግጁ ይመስልዎታል…? እንጃልዎ!

ቆይ አንድ ጨዋታ ላጫውትዎ…

አሁን ባለሁበት የስደት አገር በርካታ ኤርትራዊ ወዳጆች አሉኝ። ሴቶቹ ቡና ወንዶቹ ቢራ የሚጠጡት ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ጋር ነው። በኤርትራውያኑ ቤት ጎራ ሲሉ የቴዲ አፍሮ እና ሌሎች የኢትዮጵያ አማርኛ እና ትግርኛ ሙዚቃ መስማት እንግዳ አይደለም። ይሄንን ልብ ያልኩ ግዜ መሃመድ ሰልማን “በኤርትራ ሙዚቃ የምትደንስ ከተማ” በሚል ርዕስ ስለ መቀሌ የፃፈው ጣፋጭ ወግ ትዝ ይለኛል። ልብ አድርጉልኝ መሃመድ ሰልማን እንደነገረን ከሆነ…(ደግሞ አምነዋለሁ መሆኑ አይቀርም) አደይ መቀሌ በኤርትራውያን ሙዚቃ እየጨፈረች ነው። እኔ እንዳለኝ መረጃ ደግሞ ኤርትራውያንም አስመራ ከተማን በኢትዮጵጵያውያኑ ሙዚቃ አድምቀዋታል።

ከዚህ ምን ይረዳሉ? እኔ የምረዳውን ልንገርዎ… ህዝቦቹ ተነፋፍቀዋል። እኒያ አንድ የነበሩ ህዝቦች ዛሬም “ከምድላዬ… አነ ከምድላዬ…” እያሉ እየተዛፈኑ ጥሩ ግዜ እንዲመጣ ይመኛሉ። ታድያ ርስዎ ዛሬ ከመሬት ተነስተው ሊያታኩሱን የሚሹት ለምንድነው?

እባክዎ ጠቅላይ ሚኒስትር ፌስ ቡክ አድ ያድርሁኝ እና ሰው ምን እንደሚልዎ “ሼር” ላድርግልዎ… “ከፈለጋችሁ እናንተ ገለልተኛ ሜዳ ተቀጣጠሩ እና ተደባደቡ፤ እንጂ እኛን አታስጨርሱን!” እያለ ፖስት ያደረገ ብዙ ሰው አለልዎ!

በአፋር ክልል ሲጎበኙ የነበሩ ቱሪስቶች ተገደሉ። ያሳዝናል። ይህንን ማን ፈፀመው? እርስዎ እንዳሉት ከሆነ ሻቢያ ያሰታጠቃቸው የመንግስት ተቃዋሚዎች ናቸው! እናም ይህንን ደም መመለስ አለብን ብለው ወደ ኤርትራ ሊዘምቱ እየተንደረደሩ ይመስላሉ። እኔ የምለው ግን እነዚህ ተቃዋሚዎች ቱሪስቶች ያሉበት ደረስ መጥተው ገድለው፣ አግተው ሲሄዱ የእኛ ጠባቂዎች ምን እየሰሩ ነበር? ብዬ ፈታኝ ጥያቄ ብጠይቅዎ ይመልሱልኛል? የሆነ ሆኖ በኤርትራ ውስጥ በርካታ ተቃዋሚዎች እንዳሉ እራሳቸው ተቃዋሚዎቹም ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እርስዎ ደግሞ ይሄ ነገር እንቅልፍ ነስትዎታል። (እኔ እንቅልፍ ልጣልዎ…)

ግን እኮ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር… (በነገራችን ላይ “ክቡር” ስልዎ በርካታ ወዳጆቼ ቅር እያላቸው ነው… “ምክንያቱም እየሰሩ ካለው ስራ አንፃር እርሳቸው የተከበሩ ሳይሆኑ የተቀበሩ ናቸው” የሚሉኝ ብዙ ናቸው። ነገር ግን ለተቀመጡበት የምኒሊክ ወንበር እና ለወዳጅነታችን ስል ክቡር ብዬ እቀጥላለሁ…) ስቀጥልም፤ ግን እኮ እርስዎም የኤርትራን ተቃዋሚዎች እየረዱ ነው። በቴሌቪዥን የአየር ሰዓት ሰጥተው፣ እኛ የተከለከልነውን ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ ፈቅደው፣ በርካታ የድጋፍ ስራ ለኤርትራ ተቃዋሚዎች እያደረጉ ነው። ታድያ ኤርትራስ የእርስዎን ተቃዋሚዎች ብትረዳ ለምን ይደነቃሉ…?

ትዝ ይልዎት እንደሆነ እርስዎ ታጋይ በነበሩበት በዛ ዘመን በወቅቱ የነበረው መንግስት “የእናት ጡት ነካሽ… አባት አስለቃሽ… ወንበዴ!!!” ይላችሁ ነበር። (አረ ዛሬም መንጌ ዚምባቡዌ ሆነው ባደረሱን መፅሐፍ እንደዛው እያሏችሁ ነው!) ኢንተርናሽናል ድርጅቶችም በሽብርተኝነት ፈርጀዋችሁ ነበር። ደግሞም ስታደርጉ የነበረው ሁሉ የአሁኖቹ ተቃዋሚዎች ከሚያደርጉት ይብስ እንደሆን እንጂ አይተናነስም። ታድያ በወቅቱ እኔን ጨምሮ እናንተን ታጋይ ሲላችሁ የነበረው ህዝብ ዛሬ በረሃ ያሉ ፋኖዎችን እናንተ አሸባሪ ስትሏቸው እንዴት ሳቃችን እንደሚመጣ በተመለከቱን!

ታጋይ አንዴ ብረት አይያዝ እንጂ ቆርጦ ጫካ ከገባ እና ዱር ቤቴ ካለ የፈለገ ግዜው ይርዘም እንጂ ያለ ድል እንደማይመለስ ከእርስዎ በላይ የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም። እናም አንድ ምክር ልምከርዎ በኦጋዴን፣ በቦረና፣ በአፋር፣ በአርማጭሆ የተለያዩ ታጋዮች ጫካ ገብተው እየታገሉ እንደሆነ የእነርሱን ፕሮፖጋንዳ መስማት ሳያስፈልግ ራስዎ በቴሌቪዥንዎ በሚያቀርቡልን ዶክመንተሪዎች ተረድተናል። እነዚህን ታጋዮች አሸባሪዎች ቢሏቸውም ህዝቡ “አሸባሪ ማለት የነፃነት ታጋይ ማለት ነው!!!” ካለ ሰንብቷል።

ስለዚህ ምክሬ ምን መሰልዎ እነዚህ “ዱር ቤቴ” ያሉ ታጋዮች ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለሱ ወይ ይፀልዩ ወይ ደግሞ አንድ ግዜ እንደምንም አይንዎን በጨው አጥበው “ለበደልኳችሁ በደል ይቅር በሉኝ!” ብለው እርቅ ያውርዱ! ከዛም፤ ሁሉንም ያሳተፈ አዲስ ምርጫ ያከናውኑ። እውነቴን ነው የምልዎ… ያኔ ርስዎም ሊመረጡ ይችላሉ።

ለማንኛውም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እባክዎን እሺ ይበሉኝና ፌስ ቡክዎ ላይ አድ ያድርጉኝ ብዙ የማወጋዎ አለኝ።

በመጨረሻም

አንድ ጨዋታ

ይሄውልዎ ሰሞኑን የፌስ ቡክ ወዳጆቼ ከአዲሳባ የሚከተለውን ጨዋታ አድርሰውኝ ነበር…

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሆዬ ዋና ዋና የተባሉ አትሌቶችን ከተለያየ የአለም አቀፍ ውድርዶች አግድዎሎታል። ታድያልዎ ከተሜው ምን እያለ ያወጋል መሰልዎ… አንዱ ጠየቂ “እኔ የምለህ አትሌቶቹ ምን አድርገው ነው የታገዱት?” ብሎ ይጠይቃል አሉ። መላሹ ታድያ ቀልጠፍ ብሎ፤ ግን ደግሞ ድምፁን ዝግ አድርጎ… “ከሻቢያ ጋር በህቡዕ ሲሰሩ ተደርሶባቸው ነው አሉ…” ብሎት እርፍ…! መላሹን ትንሽ የአየር ሰዓት ብንሰጠውማ… “አብዛኛዎቹ አትሌቶች አስመራ ሄደው ስልጠና መውሰዳቸው ተደርሶበታል!” ይለን ነበር።

ለዛሬ በዚህ ይብቃኝ… ከጦርነት ይሰውረን!

አማን ያሰንብተን!

abeto2007@yahoo.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 25, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.