ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ የተፈራ ዋልዋ ባለቤት ታስረው ነበር

06 May 2009 — የአቅም ግንባታ ሚኒስትር አቶ ተፈራ ዋልዋ ባለቤትና የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እህት ወ/ሮ ዓይነ ጽጌ ሰሞኑን ፖሊስ አስሮ እንደለቀቃቸው ታወቀ፡፡

ወ/ሮ ዓይነ ጽጌን ፖሊስ ያሰራቸው፣ በተጠረጠሩበት ወንጀል ፖሊስ የፍርድ ቤት ማዘዣ አውጥቶ አባታቸውን አቶ ጽጌ ሀብተማርያም ለመያዝ መኖሪያ ቤታቸው በተገኘበት ወቅት በመቃወማቸው እንደሆነ የሪፖርተር ጋዜጣ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው የግንቦት 7 ንቅናቄ ድጋፍ እንደሚያደርግለት የተገለፀውና ቁልፍ ባለስልጣናትን ለመግደል ሲንቀሳቀስ ተደርሶበታል ከተባለው ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩት አቶ ጽጌን፣ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ለማዋል መኖሪያ ቤታቸው በገባበት ወቅት ወ/ሮ ዓይነ ጽጌም በአጋጣሚ በአባታቸው ቤት ውስጥ እንደነበሩ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

የአቶ ተፈራ ባለቤት የአባታቸውን መፈለግ በመቃወምና የፖሊስ አባላቱን ኃይለ ቃል በመናገራቸው የተነሳ፣ እሳቸውም በፖሊስ እንዲወሰዱ መደረጉን የገለጹት ምንጮች አቶ ተፈራ የባለቤታቸውን በፖሊስ መወሰድ እንደሰሙ፣ ስብሰባ አቋርጠው ወጥተዋል ብለዋል፡፡

ፖሊስ ወ/ሮ ዓይነ ጽጌ ከእሥር ፈትቶ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ሲያደርግ፣ አባታቸው አቶ ጽጌ ግን በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በእስር ላይ ናቸው፡፡

ከግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር በተያያዘ የወ/ሮ ዓይነ ጽጌ ወንድምና አባት በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ነው፡፡

የወ/ሮ ዓይነ ጽጌ ወንድም አቶ አንዳርጋቸው በአሁኑ ደግሞ የግንቦት 7 ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ ሆነው እየሰሩ ነው፡፡

ንቅናቄው ኢህአዴግን በኃይል ጭምር ማስወገድ ዋና ዓላማው አድርጐ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ መግለጹ አይዘነጋም፡፡

Source: Reporter

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 6, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.