ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ የመከላከያ መኮንኖች እየታሰሩ ነው

ethiopian_armyReporter, 29 April 2009 – በአሰግድ ተፈራ — ህገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመገርሰስ ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ይፋ ከሆነ በኋላ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ማዕረግ ያሉዋቸው የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን የመከላከያ ምንጮች ገለፁ፡፡ የፌደራል ፖሊስ ምርመራው ተጠናክሮ እንደቀጠለና ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ህግ ፊት እንደሚቀርቡ ለሪፖርተር ጋዜጣ አስረድቷል፡፡ 

ያነጋገርናቸው የመከላከያ ምንጮቻችን እንደገለፁት በህቡዕ ተደራጅተው ሲንቀሳቀሱ ነበሩ በሚል ተጠርጥረው የፖሊስና የደህንነት ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉዋቸው በተጨማሪ እየተያዙ ያሉት የመከላከያ አባላት ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡

የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል ሚያዚያ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “. . . ጥቂት በስራ ላይ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና በብዛት ደግሞ ከመከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የዲሲፒሊን ጥፋት የተቀነሱ አባላትን ያቀፈ . . . ” በማለት በወንጀል በተጠረጠሩት ውስጥ የሚገኙትን የመከላከያ አባላት ይገልፃቸዋል፡፡

በወታደራዊ የንዑስ ቡድንና በሲቪል ንዑስ ቡድን እንደተደራጁና በሁለቱም ዘርፍ የተደራጁትን ቡድኖች የሚመሩት መሪዎችን ስም የጠቀሰው መግለጫው የቀሪዎቹን ወደፊት እንደሚገልፅ አስታውቋል፡፡

የወታደራዊ ንዑስ ቡድን መሪ ናቸው የተባሉት ብርጋዴር ጄኔራል ተረፈ ማሞ በኢህአዴግ የትጥቅ ትግል ዘመን ስመጥር የጦር መሪ እንደነበሩ ያነጋገርናቸው የመከላከያ ምንጮች ያስታውሳሉ፡፡

የህዳሴው ዋዜማ በሚለው ዶክመንተሪ ፊልም ከሌፍተናንት ጄኔራል አበባው ታደሰ ጋር በመሆን ስለ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የትግል ትውስታ በአስረጂነት የቀረቡት ብ/ጀኔራል ተረፈ በ1997 ዓ.ም. በመጨረሻ ከሽሬ ግንባር ምክትል አዛዥነታቸው ተዛውረው አዲስ አበባ ተመድበው እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡

ላሊበላ የተወለዱት ብርጋዴር ጀነራል ተረፈ በቅርቡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተከታታይ ሲተላለፍ በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ዘጋቢ ፊልም ስለ ኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ብቃት በፊልሙ መካከል መግለጫ ሲሰጡ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ የፀረ ሽብር ግብረ ኃይል በወታደራዊና በሲቪል ንዑስ ቡድን የተደራጁና ህገ መንግሥቱን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር እንዳዋሉዋቸው ገለፆ፣ በቁጥጥር ስር እስካዋላቸው ድረስ በአንድ መምሪያ ውስጥ በኃላፊነት ሲሰሩ እንደነበር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ቡድን መሪ ናቸው ተብለው ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውና የአንድነት ፓርቲ ተለዋጭ የአመራር አባል አቶ መላኩ ተፈራ የሚመሯቸው በመንግሥት መስሪያ ቤቶችና በግል ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ አባላትን እንደሆነ መግለጫው አስታውቋል፡፡ አቶ መላኩ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ታስረው የነበሩና መንግሥትን ይቅርታ ጠይቀው ከእስር የተፈቱ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

የግንቦት 7 ንቅናቄ መስራችና መሪ የሆኑትን ዶክተር ብርሃኑ ነጋ በመጥቀስ በህቡዕ ከተደራጀው ቡድን ጋር ያያዘው የብሔራዊ ደህንነት መግለጫ ቡድኑ ሊያደርስ ስላሰበው አደጋና እንቅስቃሴ በዝርዝር አላብራራም፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንዳሉት ከሆነ በወታደራዊና በሲቪል ተደራጅቶ በህቡዕ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቡድን ዋንኛ ዓላማ መፈንቅለ መንግሥት ማካሄድ ነበር፡፡

ህገ መንግሥታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሁሉ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ፖሊስ የምርመራ ስራውን አጠናክሮ እየሰራ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ደምሳሽ ኃይሉ ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለፁት ፖሊስ ምርመራውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ምርመራው ሊሰፋ እንደሚችል የጠቆሙት ኮማንደር ደምሳሽ “ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካሎች ከህግ ተጠያቂነት አያመልጡም፤ በቁጥጥር ስር ይውላሉ” ብለዋል፡፡

በድርጊቱ የውጭ ኃይሎች እንዳሉበት ለተጠየቁት “የውጭ ኃይል የለበትም ማለት አይቻልም፡፡ ምርመራው ሲጠናቀቅ ወደፊት ይፋ ይሆናል” በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

የግንቦት 7 ንቅናቄ መስራችና መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መጠቀሳቸውን ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚኖሩት አባታቸው አቶ ነጋ ቦንገር እንደታሰሩ ተደርጐ የሚወራው ፍፁም ሀሰት መሆኑን ኮማንደሩ ተናግረዋል፡፡ ሌላው የንቅናቄው መስራች የሆኑት የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አባት ታስረዋል ስለመባላቸው ተጠይቀው ኮማንደሩ መልስ አልሰጡም፡፡ በጥቅሉ ግን “ከወንጀል ተግባሩ ጋር ተሳታፊ መሆናቸው በመረጃና በማስረጃ የተረጋገጠባቸው ከሆነ ከህግ በላይ ሊሆኑ አይችሉም” ብለዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኤርሚያስ ለገሠ ስለሁኔታው ተጠይቀው የአቶ አዳርጋቸው ፅጌ አባት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የመረጃ ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብርተኛነት ግብረ ኃይል ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የግንቦት 7 ንቅናቄ መሪ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የእንግሊዝኛ ፕሮግራም እንደተናገሩት ንቅናቄው ማንኛውንም ርምጃ በመውሰድ መንግሥትን ከሥልጣን የማውረድ ግልፅ የሆነ አላማ እንዳላቸው አስቀምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሰሞኑን መንግሥት በቁጥጥር አዋልኩት ባለው እንቅስቃሴ እጃቸው እንደሌለበትና የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ እንቅስቃሴ ስለመደረጉ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የግንቦት 7 ንቅናቄ የተቋቋመው በአሜሪካን በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አማካይነት ሲሆን ስሙም የተሰየመው ከግንቦት 7 ምርጫ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ ንቅናቄው በማንኛውም መንገድ ኢህአዴግን ከስልጣን ማስወገድ ዋንኛ አጀንዳው እንደሆነ በወቅቱ ዶ/ር ብርሃኑ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ባለፈው እሁድ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ በመከላከያ የተለያየ የአመራር ቦታ ላይ ያሉ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡ የማስተካከያ ሥራ በመሰራቱ በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥም ሆነ በአመራር ውስጥ ምንም ችግር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on April 29, 2009. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.