ከአንድ ደራሲ ከዚህ በላይ ምን ይጠበቃል?

ጩኸት – ደራሲ ፈቃደ አዘዘ

(መስከረም 1985)

 [PDF]

አሮጌ መጽሐፍትን ከአሮጌ ተራ ገዝቶ ማንበብ የተለመደ ነው ። በታተሙበት ወቅት ለመግዛት አቅም በማጣት ወይም በወቅቱ በአካባቢው ባለመኖር ሳይነበቡ የታለፉ መጽሐፍት የሚገኙት አሮጌ መጽሐፍት ከሚሸጡባቸው ቦታዎች ነው ። ይህንን “ጩኸት” የሚል የግጥም መድበል ከአሮጌ መጽሐፍት ተራ ወንድም ታናሽን (ከሌላ ቋንቋ ያልተተረጎመ ወይም እንደ ዘንድሮዎቹ ብዙ መጽሐፍት የወሲብ ያልሆነውን) ገዝተህ ላክልኝ ባልኩት መሠረት “ጩኸት” የሚል በዶክተር ፈቃደ አዘዘ የተደረሰ አነስተኛ የግጥም መጽሐፍ ላከልኝ ። መጽሐፉ በመስከረም ወር 1985 ዓ.ም ይታተም እንጂ በውስጡ 1965 እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ የተገጠሙ ውብ የሆኑ ግጥሞችን አካትቷል።
የራስን ማንንነት ለራስ መንገር ከባድ ስለሆነ የዶክተር ፈቃደን ግጥሞቹን ያነበበ ሁሉ ራስን ወቃሽ ኅሊና ካለው እንቅልፍ የለሽ ሌሊቶችን ሊያሳልፍ ይችላል ። ራስን ወቃሽ ያልሆነ ኅሊና ያላቸው ደግሞ በተጻፈው አላግጠው እንቅልፋቸውን ቢለጥጡም አያስደንቅም ። ስንት አይተናልና ! ። በሃገራችን ውስጥ ወሳኝ የሆነ ታሪክ በሚሠራበት ወቅት ምን አደርግ ነበር ? በሕዝብ ላይ ግፍ ሲፈፀም በአድርባይነት ተመለከትኩ ? ለግል ጥቅሜ ሮጥኩ ? ወይስ ለውጥ ለማምጣት ታገልጉ ? ለሕዝብ ምን ጠቃሚ ተግባር አከናወንኩ ? ወይስ ሕዝብን ጎዳሁ ? የሚሉትን ጥያቄዎች ራስን ጠይቆ የራስንም ማንንነት ማወቅ ያልቻሉ ግለሰቦች ሌሎች ለሕብረተስብ ጥቅም ፣ ለሃገር እድገት ፣ብልጽግና የተቻላቸውን ያበረከቱትን ሲያጣጥሉ ማየት በአሁኑ ወቅት የተለመደ ነው ። እንዲያውም አልፎ ተርፎ ይህ አሳፋሪ ተግባር እንደ አዋቂነት ሲቆጠር ይታያል ። ታሪክ ግን ታሪክ ነው በሕዝብ አዕምሮ ውስጥ በማይጠፋ ቀለም ተፅፎ የሚቀመጥ ፣ ቢያጣጥሉት የማይጣጣል ፣ቢያንኳስሱት የማይኳስስ ነው።
ይህ የግጥም መጽሐፍ የተጻፈው በአብዛኛው የሚመለከተው በዘመኑ አባባል “ያን ትውልድ” ነው” ። “ያ ትውልድ” ከየትኛው ትውልድ ጀምሮ እስከ የትኛው ትውልድ ድረስ ያለው መሆኑን በውል አይታወቅም። በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች ስለ “ያ ትውልድ” ብለው ሲጽፉ ፣ ሲተቹ ፣ ሲራቀቁ ፣ ሲያመሰግኑ ፣ ሲያዋርዱ ይታያሉ ። ስለዚህ ትውልድ ብዙዎቹ የሚስማሙበት አንድ ነገር ቢኖር እንቢ ባይነቱን፣ ቆራጥነቱን ፣ አልገዛም ባይነቱን ብቻ ነው ። ጭቆናን በደልን መቃወም ዋና ባሕሪው የነበረው ትውልድ የሕዝብን ሰቆቃ ለማስወገድ ያደረገው ትግል ለሃገር አሳቢ ምሁራን ዓይን እንደ ታላቅ ተግባር ሲቆጠር ፣ለአድርባይ ፣ ልታይ ባይ ምሁራን ደግሞ እንደ ጥፋት የሚታይበት አጋጣሚ ትንሽ አይደለም ።
በተለይ ዘንድሮ የፖለቲካን ሀ ሁ ለመጀመር የተነሳ ሁሉ ያንን ትውልድ ካልሰደበ ፣ ካላዋረደ በግል ከሚያገኘው ክብር ይቀነስበት ይመስል ትውልዱን በመስደብ ፣ በማዋረድ ይጀምርና የራሱን “እኔ እኔ” የሚለውን “አዋቂነቱን” አክሎ ንግግሩን ያቆማል ። ለትንሽ ደቂቃ እንኳን በያዘው አቋም ላይ በጽናት መቆም የሚያቅተው መስዋዕትነት በከፈሉት ላይ ያሾፋል ። ለትዝብት ያህል እንደነዚህ ዓይነት ጥራዝ ነጠቅ ፖለቲከኞችን መስማት ገና ያልሰለቻችሁ ካላችሁ መታዘብ የሚኖርባችሁ በንግግራቸው ማህል በአብዛኛው የግልን ተክለ ሰውነታቸውን ለመትከል የሚያደረጉትን ጥረት ነው። በንግግራቸው ውስጥ ከሚበዘው “እኔ ፣እኔ፣ እኔ “መረዳት የሚቻለው ከራሳቸው በላይ ለሕዝብ መቆም እንደማይችሉ ነው ።
ብዙ ወጣቶች የዶክተር ፈቃደ አዘዘን የግጥም መጽሐፍ “ጩኸትን” ቢያነቡ ከእነርሱ በፊት የነበረው ትውልድ ከምን ተነስቶ ምን እንደደረሰ ፣ ለምንስ መስዋዕትነትን እንደከፈለ ለማወቅ ይረዳል። ወጣቱ ትውልድ እንደነዚህ ዓይነት ምሁሮች የፃፉትን እንጂ ከመንግሥት መንግሥት ሲቀያየር ከመጣው ጋር አብሮ ለመደነስ ፣ የሄደውን ለማውገዝ የሚጣደፉትን የፃፉትን በማንበብ የተሳሳተ አመለካከት ይዘው ሊጓዙ አይገባም ። ለመሆኑ ዶክተር ፍቃደ አዘዘ ማን ናቸው ?
ከድረ ገጽ ያገኘሁት መረጃ እንደሚያስረዳው ዶክተር ፈቃደ አዘዘ አዲስ አበባ ውስጥ የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው ያገኙት ። የማስተርስና የዶክተርነት ማዕረጋቸውን ያገኙት ከእንግሊዝ ሃገር ሲሆን የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ አስተማሪ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ ። ከሥራዎቻቸው መካከል አሻረ ፣ ሃበሾች ይኑሩ ፣አያ ጎሽሜ፣ ጩኸት የሚሉ ይገኙባቸዋል ።። የሕይወት ታሪካቸውን በተመለከተ በቅርብ የሚያውቋቸው

ወይም ራሳቸው የተጨመረና ገላጭ የሆነ ሐተታ ወደፊት እንዲጽፉ ምኞቴ ነው ።

http://sirius-c.ncat.edu/AAU-Network/news/fekade/index.html መጽሐፉን ደግሜ ደጋግሜ አንብብዬ ይህንን ታላቅ ሥራቸውን ቢያንስ በድረ ገጽ ለማስተዋወቅ ተነሳሁ ። በአሥር ብር የተገዛች ማለትም በሰሞኑ ዝርዝር አንድ ዶላር የማትሞላ መጽሐፍ ብዙ ታላላቅ ቁም ነገሮችን አካታለች ። ለአንባቢያን እንዴት አድርጌ ላስተዋውቃት ብዬ ሳስብ በመጽሐፉ መጀመሪያ ላይ ሌላው በኢትዮጵያውያን ሊረሱ የማይችሉትን ታላቁ ምሁር ዶክተር እሸቱ ጮሌ ስለመጽሐፉ የሰጡትን አስተያየት አነበብኩት ። ከዚህ በላይ እኔስ ምን እጽፋለሁ? በሚል ሙሉን የዶክተርን ቃል ላሠፍረው ወሰንኩ ። ዶክተር እሸቱ ጮሌስ ማን ናቸው ?
ከድረ ገጽ ያገኙት መረጃ ዶክተር እሸቱ ጮሌ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር 1945 ተወልደው 1998 ዓ.ም ከዚህ አለም ተለይተዋል ። እኝህ የታወቁ ኢኮኖሚስት የተወለዱት ነጌሌ ቦረና ውስጥ ሲሆን አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ነው የፈፀሙት ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጀኔራል ዊንጌት ውስጥ ያጠናቀቁ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማስተርና ዶክተርነታቸውን ከሰሜን አሜሪካ አግኝተዋል ። በአዲስ አባባ ዩንቨርስቲ ለብዙ ግዜ አስተማሪ የነበሩት እሸቱ ጮሌ በስነፅሁፍም ታዋቂነትም አትርፈዋል። ዶክተር እሸቱ ጮሌ ለሰዎች እኩልነት ፣ ለሰብአዊ መብት ታላቅ ትግል ያደረጉ ምሁር ነበሩ ። የሕይወት ታሪካቸውን በተመለከተ በቅርብ የሚያውቋቸው የተጨመረና ገላጭ የሆነ ሐተታ ወደፊት በሰፊው እንዲጽፉ ምኞቴ ነው።
http://www.blackpast.org/?q=gah/chole-eshetu-1945-1998 በዚሁ አጋጣሚ ደራሲውን ዶክተር ፍቃደ አዘዘንና ጥሩ የመጽሐፍ አስተያየት የሰጡትን ዶክተር እሸቱ ጮሌን ከልቤ እያመሰገንኩ ። ዶክተር እሽቱ ጮሌ ስለመጽሐፉ የሰጡትን አስተያየት እንዳለ እነሆ ።
ጩኸት “ጩኸት” በሚል አጠቃላይ ስያሜ በዚች መጽሐፍ ውስጥ የተሰባሰቡት ግጥሞች ከአንድ ግለሰብ ብዕር ይፍለቁ እንጂ የሚያስተጋቡት ግለሰቡን ብቻ ሳይሆን የአንድ ትውልድ ፣የአንድ የኅብረተሰብ ክፍል ፣ የአንድ ዘመን ፣ የአንድ ሕዝብ እሮሮ ነው ።
በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ትውልድ ነበረ ፣ውብ ሕልም ያለመ ። ታሪክ ሳይፈቅድ ቀረና ያ ሕልም ወደ አስከፊ ቅዠት ተቀየረ ። ያም ትውልድ በአማዛኙ የመሰዋዕትነት ፣ እንዲሁም የትራጀዲ ታሪክ ጽፎ ተነነ ። እርስ በእርሱ ተላለቀ ፣ ለአጥፊዎቹ ( እንዲሁም ለኢትዮጵያ አጥፊዎች ) እራሱን አመቻችቶ ሰጠ ። መስዋዕትነቱ ከፍሬ አልባነት አልፎ እጅግ መራራ ፍሬ አበቀለ ።
ይሁን እንጂ ያ ትውልድ በአመለካከቱም ሆነ በታሪካዊው ሚናው አንድ ወጥ አልነበረም ። የዓላማ ፅናት ያህል አድርባይነትን ፣ የቆራጥነትነትን ያህል ወላዋይነትንና ልፍስፍስነትን ፣ የሕዝብ ፍቅር ያህል ራስ ወዳድነትን አልታጣበትም ።በመሆኑም አብሮ ያለመ ሁሉ አብሮ አልዘለቀም ። ያለቀው አልቆ ፣ የተረፈው ገሚሱ በስደት ፣ገሚሱ በአገር ውስጥ በተለያየ መልክ ኑሮውን ቀጠለ። አንዳንዱ ስልጣን ውስጥ ሥር ተጠለለ ፣ሌላው ያንን ሕልም ከድቶ ” የልጅ ነገር ” እያለ ማውገዝን የዕለት እንጀራውን ማሳደጃ ዘይቤ አደረገ ፣ ሌላው ደግሞ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ ትቶ ከራሱ ጋር ተስማምቶ ተቀመጠ። እንዲሁም ሌላው ” አቅሙን አውቆ ” ውስጡን እየቆሰለ ማዝገሙን ቀጠለ።
የነዚህ ግጥሞች ደራሲ የዚህ ዝብርቅርቅ ሂደት ውጤት ሰለሆነ ግጥሞቹን ለመረዳት በስተጀርባቸው ያለውን ሁኔታ በውል ማጤን ያለብን ይመስለኛል ። ደራሲው በ1960 ዎቹ የመጀመሪያ አመት በዩኒቨርስቲ ተማሪነት ፣ከዚያም በኋላ በመምህርነት ከመሰማራቱ በላይ የዚህ ትውልድ አባልና ተካፋይም ነበር ። አልፎ ተርፎም ያን ሁሉ ዘመን አቋርጦ ( ግጥሞቹ 1965 አስከ 1984 የተፃፉ ናቸው ) እነዚህ ግጥሞቹን ለማሳተም በመብቃቱ ብዙ አይቷል ፣ብዙ ታዝቧል።
የታዘበው ሌሎቹን ብቻ ሳይሆን እራሱንም ጭምር ስለሆነ ግጥሞቹ ሐቀኛ የድርሰት ሥራ ናቸው ። “ጩኸት” ብሎ ሰይሟቸዋል ፣ በእርግጥ ብዙ ጮኸት አለባቸው ። ጩኸት በማን ላይ ? በተማረው ክፍል ፣በራሱ ትውልድ ላይ

እንዲሁም በራሱ ላይ ። ጩኸት ለማን ? ለኢትዮጵያ ሕዝብ ( ጮህንለት ስንል ጮኽንበት ይሆን? ) ግን ይበልጥ ጩኸት ለራሱ ሰላም ሲል ።
ጩኸቱ ከውስጥ ፈንቅሎ የወጣ መሆኑ አያጠራጥርም ፣ በመሆኑም ግጥሞቹ ይዘታቸው መራራ ቢሆንም ውበታቸው አይጠያይቅም ። ስሜትን በቃላት ሸፋፍኖ የማለፍ ሙከራ አይታይም ። ደራሲው በግጥሞቹ አማካይነት ስሜቱ ውስጥ እንድንገባ ይጋብዘናል ። ግን በገባንበት ሁኔታ እንድንወጣ አይፈቅድልንም .እራሳችንን እንድንጠይቅ ስለሚያስገድደን ።
ለመሆኑ ምን ነበር የወጣትነት ሕልሙ ፣ የኅሊናው ጥሪ?

ዓለም ቡትቶዋን ከላይዋ አውልቃ ፣
“ጃኖ ልልበስ!” ስትል አስባ አርቃ ፣
መዶሻ ይዛችሁ ማጭድ ጨብጣችሁ ተነሱ ባንድጋ
ትልበስ ቀይ ሰንደቅ ፣ ቀይ የዓለም ባንድራ ፣
የልጆቿ ትግል አርማቸው ነውና
ተነሱ ጭቁኞች ተነሱ ባንድጋ ።
( ጃኖ ለባሽ ፣ሰኔ 21፣1965)

ግን ዓለምን ጃኖ ለማልበስ መስዋዕትነት እንደሚያስፈልግ ያልተረዳ ትውልድ አልነበረም ።

ሁለት ሞት ከመሞት ፣ክብርንም ተገፎ ፣
ቢሞቱም ግድ የለም ፣ ከእምነት ጋር ተቃቅፎ ፣
ኅሊናን ገስጾ፣
አንጀትንም ገርፎ ።
ቢሞቱም ግድ የለም ።
( ከራስ ጋር ምልልስ ፣1967)

ሆኖም የመስዋዕትነት ጎዳና እንደታሰበው ለሁሉም ቀላል አልሆነም ።ደራሲው የወሎ ረሀብን አስመልክቶ ሲጽፍ የራሱንም የሌሎችንም ኅሊና ሰንጥቆ በሚገባ ሁኔታ እንዲህ ይላል ።
እሱ

ስድስት ፍሬ ባቄላ
በምጣዱ ሙሉ ሲቆላ
ክትፎ እንመርጥ ነበር እኛ
ቁርጥ እንቁረጥ
ወሬ እናውራ
እንመቻች እንጣለፍ ፣ በሥልጣን ለሥልጣን
እኛ !!
(እንባዬ ፣ 1976 )

ይህ ከራሱ ጋር የሚያካሂደው ሙግት ብቅ ይላል ። ለምሳሌ ፣

እስከመቼ ነው ዝምታ እስከመቼ ነው አርምሞ
የልብ ሐቅ አስታሞ ፣ የብእር አንደበት ለጉሞ
እስከመቼ ነው ዝሙ ? እስከመቼ ነው አርምሞ ?
(የእኔና ’ኔ ወግ 1970)
ጥያቄው ወቅታዊ ሳይሆን የታሪክ ወቀሳም የሚያስከትል ነው ።
ኋላ ታሪክ ይሉኝታ ገፍቶ ፣
ጊዜ ቆጥሮ ሲጠይቅ ፣ ባህላችንን ንቆ
የሕይወት ታሪካችንን መዝገብ ፣ አገላብጦ “ታዲያስ!”ሲለን
እስኪ በሉ ! ምን ልንል ያኔ ባፋችን ?
“አለና” ሊሆን መልሳችን ?
(ታሪክ “ጥያቄውና” ዘመነኛው ፣1970)

እርግጥ ይህ ጥያቄ ሁላችንንም ላያስጨንቀን ይችላል ።በ ” አይተነው ጊዜ ወደሚያደላው ” ፍልስፍና ተክኖ ፣አቋምን ከመቅጽበት ማስተካከልንና መስሎ ማደርን የጥበብ ሁሉ ቁንጮ የሚያደርግን ሰው የኅሊና ጥያቄ አያስጨንቀውም ። ለመጨነቅ ኅሊና ያስፈልጋልና ። ደራሲው እንዲህ ያለውን ባህርይ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል ።

” የመሬት ሥሪት ይፍረስ
ባርነት ይገርሰስ ” ስለው ያሰቃየኝ
በይሁዳ አንበሳ መፈክር እጅና አፌን ያሰረኝ
” አንተ የማኦ ቅጥረኛ የሌኒን ሰላይ ያለኝ
በ66 ቀደመኝ
መች በዚህ በቃ ይኸው ኮሞዩኒዝምን አስተማረው ፣ቡርዧ ምሁር ብሎ አወገዘው ። ይባስ ብሎ የደርግ ዘመን ሲያከተም አጅሬ ሌላ ካባ ደርቦ ብቅ አለ ።
እንዲህ እንዲህ እድሜ ተስፋዬን የነጠቀኝ
በአበሳዬ ተፍለቅልቆ ያንጓጠጠኝ
ጉልበት መንፈሴን መጥምጦ ኅሊናዬን ያሳደፈኝ
በግንቦት 20ም ቀደመኝ
የ17ቱን መከራ ሻይ ቡና ላይ እያጫወተኝ
የገዛ አበሳዬን ለኔው እየጠቀጠቀኝ
” አቤት ያሳለፍነው ፍዳ
ቀላል መሰለህ ?” እያለኝ
ኢሠፓን ባፉ ጨፍጭፎ ፣” አውሬ ነበር ደርግ “እያለኝ
በዴሞክራሲና ነፃነት ቱልቱላውን ሊያደነቁረኝ
( ኝ ኝ ኝ (“ለአብዮተኛ ” ” ምሁራን ” ፣ኅዳር 26፣1984)

ይህ ስር የሰደደ የአድርባይነት በሽታ ደራሲው ብዕሩን ጠንቁሎበታል ፣ እሰይ የሚያሰኝ ነው ። በተለይ ተማረ በሚባለው የኅብረተሰባችን ክፍል ውስጥ የታየ ዕውቀትንና ችሎታን ያለአስገዳጅ ምክንያት አንዴ ለአንዱ ፓለቲካ ፣ ሌላ ጊዜ ለተቃራኒው የመቸርቸር ሁኔታ ብዙዎቻችንን የሚያስጠይቅ ነው ።
ሌላው በሽታችን “ዝም አይነቅዝም ” በሚል ብልሃት አይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን የምንሆነው ነው ። ለዚህ ነው ደራሲው “እረ ማን አለ ፣ነፃ ’ሚወጣ ?” ብሎ የሰነዘረው ጥያቄ “እኔ ” ብሎ በድፍረት መመለስ የሚችል ብዙ ሰው የማይገኘው ፡ –

እረ ማን አለ ከቶ ?
ወይ ጩቤ ያላቀበለ = = =
አንድ እሳት ያልጫረ = = =
ወይ ውሃ ያላፈሰሰ = = =
ወይ ተሸፋፍኖ በመተኛቱ ፣
ድምጿን ያፈነ ጨክኖ ፣
መድረክ ነስቶ ለእውነቲቱ ።
እረ ማን አለ፣ ነፃ ’ሚወጣ?
(ኑዛዜ ፣ ከ1968-1970 )

እንግዲህ ግጥሞቹ ለራሳችንና ለኅብረተሰባችን ብዙ እንድንጠይቅ የሚያደርጉ ናቸው ። ለመዝናኛ ብለን የምናነባቸው አይመስሉኝም ። አልጋዬ ላይ ተጋድሜ አነባቸዋለሁ ብዬ ጀመርኳቸው ፣አነበብኳቸውም ። ግን እንቅልፍ አልጋበዙኝም ። እራሴንና ትውልዴን ግጥሞቹ ውስጥ ብዙ ጊዜ አገኛኋቸው ። ሐቀኛ ሥዕል ነው፣ ግን ( ወይስ ስለዚህ ? ) አያዝናናም ። እንድናስብ ግን ያስገድደናል ።
ከአንድ ደራሲ ከዚህ በላይ ምን ይጠበቃል?

እሸቱ ጮሌ ጥቅምት / 1985

ሰለ ትውልዱ የሚያስብ በሰላም ይክረም!
ሎንዶን – 2011

ከበልጅግ አሊ፣ Beljig.ali@gmail.com

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on January 27, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.