ከአትላንታ የኢሳት ዝግጅት በኋላ፤ ታማኝ በየነ ወደ ድንገተኛ ሆስፒታል ተወሰደ!!

(ካለፈው የቀጠለ)

ኢ.ኤም.ኤፍ፡ አባ ገብረስላሴ በንግግራቸው መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ወገኖቻችን ያሉበትን አስከፊ የኑሮ ሁኔታ አስታውሰው፤ “ወገኖቼ እራስን በቁም በእሳት ከማቃጠል የበለጠ ስቃይና መከራ የለም።” በማለት በየኔሰው ገብሬ ላይ የደረሰውን እንደምሳሌ ጠቅሰዋል። በንግግራቸውም መጨረሻ በተለይ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን አስመልክተው፤ “በኔ እድሜ እስካሁን የተስማሙ ሰዎች አላየሁም። አገር ሲያድግ አላየንም። ስብሰባ ስብሰባ ስብሰባ… ግን ትንሽ ስራ። ይህ መሆን የለበትም። መስራት አለብን። ስትነጋገሩም በአመክዮ ላይ የተመሰረተ ውይይት አድርጉ። ሚዲያም ቢሆን ህዝቡን ለማስተማር መሆን አለበት እንጂ፤ ሌሎችን ለመወንጀል ሚዲያ አያስፈልግም።” በማለት አደራ የታከለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢሳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በአትላንታ።

በመቀጠልም ሃጂ ሳፊ በኢትዮጵያ ውስጥ የእስላም እና የክርስቲያኑን አንድነት ገልጸው፤ “እስላም እና ክርስቲያን በኢትዮጵያ ውስጥ በፍቅር እና በሰላም ኖረዋል። አሁን በቅርቡ ግን ሊለያዩን እና እርስ በርስ ሊያቀያይሙን ሞከሩ። በዚህ በኩል ቤተ ክርስቲያናትን በማቃጠል፤ ዞሮ ደግሞ መስጊድ በማቃጠል እኛን ለማለያየት ብዙ ሞከሩ። ህዝቡ ግን አልተለያየም። እስላምና ክርስቲያንን ማጣላት ሲያቅታቸው፤  አሁን ደግሞ እርስ በርስ ሊያጣሉን ብዙ እየጣሩ ነው። በእስልምና ውስጥ አህባሽ፣ ዋሃቢ እያሉ እየከፋፈሉን፣ እያጣሉን ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለእስር ተዳርገዋል። መጸለይ እና መታገል ብቻውን አይደለም። ወደ ኣላህ ጸልየህ ብቻ ዝም ማለት አያስፈልግም። ሰበብ ማድረግ አለብህ። ለዚህም ጸሎት ብቻ ሳይሆን በርትቶ ሰላም ለመፍጠር መታገል ያስፈልጋል።” ብለዋል ሃጂ ሳፊ።

በቀጣይ ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ፤ “ሁሉም ዜሮ ዜሮ” የሚለውን ዝውፍውን ተጫውቷል። ከዚያ በፊት ግን አንድ መል ዕክት አስተላልፎ ነበር። “ይህንን ዘፈን መጀመሪያ የተጫወትኩት እኔ ነበርኩ። አሁን ደግሞ እዚሁ አትላንታ ለሚገኘው በሬ ለሆነው ሰው እና እሱን ለመሰሉ ሰዎች እጫወተዋለሁ፤ በማለት… ፡ሁሉም ዜሮ ዜሮ፤ ዶላሩ በጓሮ።” እያለ ሲጫወት የተሰበሰበው ህዝብ በፈገግታና በጭብጨባ አጅበውት ነበር።

ቀጣዩ ተናጋሪ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ነበር። “በዘር ቢሆን ኖሮ ዛሬ የዚህ ህዝብ ተቃራኒ ሆነው የሚሰሩትን ስራ እኔ ነበርኩ መስራት የነበረብኝ” በማለት ነው ንግግሩን የጀመረው። ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረበት ወቅት ህዝቡ ለኢሳት ይሰጠው የነበረውን ግምት፤ ወደ ውጭ ከወጣም በኋላ በተለይ በዋሺንግተን ዲሲ ጋዜጠኞች ቀንና ለሊት ያለ እረፍት ለሚያደርጉት ጥረት አድናቆቱን ገልጿል።  “እስክንድር መስዋዕትነት የከፈለው ስሙ በጊነስ መጽሃፍ ላይ እንዲወጣለት ፈልጎ አይደለም። ነገር ግን  እውነትን ስለመሰከረ ነው ለ እስር የበቃው።” ካለ በኋላ እንዲህ ያሉ ጋዜጠኞችንና አማራጭ ሚዲያ የሆነውን ኢሳት ህዝቡ እንዲደግፈው ጥሪ አቅርቧል።

ምሽቱን ሲጠበቅ የነበረው ቀጣዩ ተናጋሪ አርቲስት ታማኝ በየነ ነበር። አርቲስት ታማኝ እንደከዚህ ቀደሙ ቀስቃሽ በሆኑ ንግግሮቹ ህዝቡን ከዳር እስከዳር አስደምሟል። ንግግሩንም በመረጃ እና በፊልም በማስደገፍ ነበር ያቀረበው። ዝግጅቱ ሲጠናቀቅ ግን በኢመርጀንሲ ወደ ዲካብ ሆስፒታል ነበር ያመራው።

አርቲስታ ታማኝ በእለቱ ባደረገው ንግግር የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ትግል ታሪክ ትላንት በነአቶ መለስ ዜናዊ ፈቃድ እና ቸርነት የተሰጠ ሳይሆን፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ በቆየ ታላቅ መስዋዕትነት የተገኘ መሆኑን ከገለጸ በኋላ፤ ደራሲና ጋዜጠኛ በአሉ ግርማ፣ መጽሃፈ ሲራክ እና ተፈራ አስማረን አስታውሷል። “ሌሎች የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞችም ሙያዊ ግዴታቸውን ሲወጡ ከቆዩ በኋላ በሚደርስባቸው ጫና ምክንያት የሚወዱትን አገራቸውን ለቀው ወጥተዋል።” ብሏል። ከዚያም ለእነዚህ ከመቶ በላይ የሚሆኑ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ክብር እና ምስጋና በመስጠት የሁሉንም ጋዜጠኞች ስም ዝርዝር አቅርቧል። አርቲስት ታማኝ በየነ በዚህ ዝግጅቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት፣ የአየር ኃይል እና የተሰደዱ ምሁራንን በክብር በማስታወስ ለውድ አገራቸው ላደረጉት የማይዘነጋ ውለታ ምስጋናውን ሲያቀርብ፤ ህዝቡም በጭብጨባ ድጋፉን ሲገልጽ ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን፤ በየንግግሩ ጣልቃ የጭንቀት አተነፋፈስ ያሰማ ነበር…. ታማኝ።

በዚህ አይነት በድምቀት የተከናወነው ዝግጅት፤ እስከ እኩለ ለሊት ነበር የዘለቀው። በመጨረሻም ህዝቡ በዚያኑ ቀን የገንዘብ መዋጮ አድርጎ፤ ከዚያም በተጨማሪ ቢያንስ በየወሩ አስር ዶላር ከባንክ አካውንቱ በቀጥታ ለመስጠት ቃል ገብቶ፤ ይህንንም ረስ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራው በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

ይህ ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ አርቲስት ታማኝ በአንድ ጎኑ በኩል የሚሰማው ህመም እያየለ መጣ።  ሰውነቱ በላብ መጠመቅ ጀመረ። በአንድ ጎኑ የሚሰማው ህመም ጨመረ። በስፍራው የነበረ ኢትዮጵያዊ ሃኪም (ዶ/ር ኤፍሬም) የአርቲስት ታማኝን በላብ የመጠመቅ ሁኔታ ተመልክቶ፤ ወደ አቅራቢያው የሚገኝ የዲካብ ድንገተኛ ሆስፒታል እንዲሄድ ምክር ሰጠው። የዲካብ ካውንቲ ሜዲካል ሆስፒታል የህክምና ውጤት እንደሚያሳየው ከሆነ፤ “የደም ውጤቱ ንጹህ ነው። በውሃ ሽንት ምርመራው ውስጥ ደም በመገኘቱ፤ በኩላሊቱ ላይ ወይም በተጓዳኝ የሰውነቱ አካል ላይ የድንጋይ ጠጠር ሊኖር እንደሚችል ሀኪሞች ገልጸዋል። ህክምናው ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው ከሆነ አትላንታ ቆይቶ አስቸኳይ የሆነ የህክምና ክትትል እንዲያደርግ አሳስበዋል። ሆኖም ህክምናውን በሚኖርበት ከተማ ማድረግ እንደሚፈልግ በመግለጹ ከለሊቱ 3፡30 A.M ላይ ከድንገተኛ ሆስፒታሉ ለቆ ወጥቷል።

እዚያው ሆስፒታል ውስጥ አርቲስት ታማኝ በየነን አግኝተን አናግረነው ነበር። “አሳሳቢ የሆነ ዜና ነው የሰማነው። የኩላሊት ጠጠር ከሆነ፤ ተጨማሪ ህክምና ማድረግህ ነው?” አልነው።

“አዎ።” የሚል አጭር መልስ ሰጠንና በዚያው አከታትሎ፤ “ህክምና የተደረገልኝ አሜሪካ ውስጥ መሆኑ በጀኝ። ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን፤ ማን ያውቃል ‘በኩላሊቱ ድንጋይ ይዞ በመዞር የአሸባሪነት ወንጀል ተከሷል’ የሚል ዜና ሳንሰማ እንቀር ነበር?” ሲለን እኛን ጋዜጠኞቹንና ሆስፒታል የነበሩትን አስቋቸዋል። መልሱ ፈጣን፤ መልዕክቱም ግልጽ ነበር። ቸር ያሰማን። ቸር እንሰንብት።

(ቀደም ሲል በዚህ ጉዳይ የተጻፈውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ) http://ethioforum.org/?p=9713

ይህ ዜና ከተጠናቀረ በኋላ፤ እንደተረዳነው ታማኝ ህክምናውን በሚኖርበት የቨርጂንያ ክፍለ ግዛት የቀጠለ መሆኑ ታውቋል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 6, 2012. Filed under ESAT. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.