ከታሰሩት የዞን ዘጠኝ ጦማርያን መካከል ስለተስፋለም ይህን ልበል (ኤልያስ ገብሩ)

ተስፋለም ሆይ! ስላንተ ምን ልናገር? ስለልጅነትህ?!
ሚያዚያ 18 ቀን 2006 ዓ.ም ንጋት ላይ ትንሿ ስልኬ አንጫረረጭ፡፡ ከእንቅልፌ ብንን ብዬ ስልኬን ተመለከትኩት፡፡ የደወለው ወዳጄከዚህ ቀደም በዚህ ሰዓት ደውሎልኝ አያውቅም ነበር፡፡ ስልኩን ሳላነሳው ‹‹ምን አንዳች ነገር ተፈጥሮ ይሆን?›› ብዬ ማሰላለሌን ተያያዝኩት፡፡ ከ20 ደቂቃ በኋላ ስልኩ በድጋሚ ተደወለ፣ አነሳሁት፡፡ ከደዋዩ ወዳጄጋርም ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ‹‹ጓደኞችህ ታሰሩ አይደል?›› አለኝ፡፡ ‹‹እነማን?›› በማለት በችኮላ መለስኩለት፡፡ ‹‹ተስፋለም፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ዞን ዘጠኞች…›› ደንግጬ መረጃው እንደለሌለኝ ነገርኩት፡፡ …ተስፋለም ከመታሰሩ ሁለት ቀናት በፊት ደውሎ ከሥራ ጋር የተገናኘ መረጃ ጠይቆኝ ነበር፡፡

አሁን በ እስር ላይ ከሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን አንዱ - ጋዜጠኛ ተስፋለም።

አሁን በ እስር ላይ ከሚገኙት የዞን 9 ጦማርያን አንዱ – ጋዜጠኛ ተስፋለም።


ያለ ወትሮ ስልክ ሲደወል በተቻለ አቅም እረጋ ብሎ ማሰላለሰልን ከተሞክሮ ተምሬያለሁ፡፡ የቀድሞ የአውራምባ ታይምስ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደን ከኢትዮጵያ መሰደድ ንጋትላይ ‹‹አለቃችሁ ተሰደደ አይደል?›› ብሎ የነገረኝ፣ እስከአሁን ድረስ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ መታሰሩ በጣም የገረመኝ፣ የማከብረው እና የምወደው የልጅነት ጓደኛዬ እና ወንድሜ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ ነበር፡፡ እንደአንድ ነጻ እና ጎበዝ ጋዜጠኛ ለመረጃ ያለውን ቅርበት ተመልከቱ!

የሌሎቹም የጋዜጠኛ አስማማው ኃይለጊዮርጊስ፣ የጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ (በፍቄ)፣ የጦማሪያኑ የማህሌት ፋንታሁን፣ የአጥናፍ ብርሃኔ፣ የዘላለም ክብረት፣ የናትናኤል ፈለቀ፣ የአቤል ዋበላና የኤዶም ካሳዬ መሰል እስርም እጅግ አሳዝኖኛል፡፡ ዋይ! ሀገሬ!
ከተስፋለም ወልደየስ ጋር ትውውቃችን ከለጋ አፍላ ዕድሜያችን ይጀምራል፡፡ ወላጆቹ ጦላይ ወታደራዊ ካምፕን ለቅቀው አዲስ አበባ መኖር ከጀመሩ በኋላ ማለት ነው፡፡ ዛሬ በሕይወት የሌሉት የተስፍሽ ወላጅ እናት ወ/ሮ አበበች አክስት ከወላጅ አባቴ ጋር በጣም የቅርብቤተሰባዊ ትስስር አላቸው፡፡ ወ/ሮ አበበች እና አክስታቸው ለረዥም ዓመታት ልደታ መኮንኖች ክበብ አቅራቢያ አንድ ግቢ ውስጥ ኖረዋል፡፡

ዛሬ በሕይወት የሌሉት ወላጅ አባቱ እና እናቱ እንዲሁም አሁን ላይ በቅርቡ ያለችው እህቱ ራሄል ተስፋለምን ‹‹አቡሽ/አቡሼ›› በማለት ነበር ፍቅራቸውን በመግለጽ የሚጠሩት፡፡ እኔም እስከቅርብ ዓመታት ድረስ ‹‹አቡሽ›› ነበር የምለው፡፡
ከተስፋለም ጋር አብሮ በመሆን በነበሩን አጋጣሚዎች ሁሉ በጣም ደስ የሚል ጨዋታ፣ እያወጉ ረዥም ወክ የማድረግ ተደጋጋሚ ልምድናእውቀት የመካፈልየቁም ነገር ጊዜያቶችን በልጅነታችን በደንብ አጣጥመን አሳልፈናል፡፡ …እነዚህ መቼም አይደገሙ! ትዝታ ሆነው አልፈዋል፡፡ ተስፋለም አዲስ ነገር ለማወቅ እና አዲስ ነገርን ለመንካት ያለውን ጉጉት እና ትጋት ወደር የለውም፡፡ አከባቢያዊ፣ ሀገራዊ እና ዓለማቀፋዊ መረጃዎችን ከአቅሙ በላይ ለማወቅ ይታትር ነበር፡፡ ለዕውቀት እና ለመረጃ የነበረውም የተንቀለቀ ስሜት እና ጥማትየላቀ ነው፡፡ ለዚህ ይሆን፣በብዙዎች ዘንድ በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ትልቅ ተምሳሌት ከነበረችው የ‹‹አዲስ ነገር›› ጋዜጣ መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው?

ተስፋለምን ልጅነት ካወኩት ጊዜ አንስቶ የንባብ ቀበኛ ነው፡፡ ገበያ ላይ ያሉ መጽሐፍትን፣ ጋዜጦችንና መጽሄቶችን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከሰዎች ይዋሳል፣ ያነብባል፣ ይገዛል፣ አደራጅቶ በጥንቃቄ ያስቀምጣል፡፡ ለምሳሌ፣ ሆሊውድ ጋዜጣ እና ኢንፎቴይንመንት መጽሄትለአንባቢያን ቀርበው ህትመታቸው እስከተቋረጠባቸውጊዜያት ድረስ ያሉትን ቅጾች በተስፋለም ቤት አሁንም ድረስ በክብር ተቀምጠው ያገኟቸዋል፡፡ የሬዲዮ እና የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችንበሚያስገርምመልኩ በአንክሮ ይከታተላል፡፡ ፊልሞችንም እንደዚሁ፡፡ የተመለከታቸውን ፊልሞች መቼ እንደተመለከታቸውጠቅሶ ከነዕርሶቻቸው ማስቀመጥም ልምዱ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ምን እንዳደረጋቸው ባላውቅም በርካታ ግጥሞችንም ይጽፍ ነበር፡፡ ግለ-ሀሳቡንም ይጽፋል፡፡

ተስፋለም፣ የጋዜጠኝነት ሙያን መማር ጥልቅ ፍላጎቱ መሆኑንለወላጆቹ ተናግሮ ካሳመነ በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ጋር በሚገኘው በቀድሞ የማስሚዲያ ማሰልጠኛ ኤጀንሲ የጋዜጠኝነትትምህርትን ለመመዝገብ የሄደው ከእኔ ጋር ነበር፡፡ …ከዚህ መደበኛ ትምህርት ባሻገር በሂደት ሙያውን በራሱ ጥረት ለማሻሻል ጥረቱ ትልቅ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት የፍሪላንስ ሥራን በጎን በመጀመሩ ምክንያት እና በትምህርት ጥናት የተነሳ አምሽቶ ከእኩለ ሌሊት በኋላወደቤት መግባትን ልምድ አድርጎም ነበር፡፡በዚህ ወቅት በመኖሪያ ቤቶቹ ግቢ ውስጥ በጣም አምሽቶ የሚገባው ተስፋለም ነው፡፡ ተስፋለም ‹‹ለእውነተኛ ጋዜጠኝነት የተፈጠረ›› ብል አፌን ሞልቼ ነው፡፡ ሙሉ ሕይወቱን ለጋዜጠኝት ሙያ ስለመስጠቱም ሆነ ስለጥንቃቄውእመሰክራለሁ፡፡

አሁን ላይ ቀን እና ዓመተምህረቱን ዘንግቼዋለሁ፡፡ ወላጅ አባቱ ለረዥም ወራት እያመማቸው እና እየተሸላቸው ከቆዩበኋላአመሻሽ ላይ ሕይወታቸው አለፈ፡፡ በቦታውም ነበርኩ፡፡ ተስፋለም ግን ከነፍሱ ለሚወደው ሙያ ሌሊቱን ሙሉ ሲሰራ አድሮ ንጋት ላይ ወደቤቱ ሊገባ የአጥሩንበር ሲከፍት መኖሪያ ቤታቸው በሰዎች ተከብቧል፡፡ ድንጋጤው ፊቱ ላይ በግልጽ ያስታውቅበት ነበር፡፡ ማንምም ሳያናግር ወደቤቱ ዘለቀ፡፡ በጥልቅ የሚወዳቸው እና የሚሳሱለትየወላጅ አባቱ ሞት እውነት መሆኑን ተረዳ፡፡ ፊቱ ተቀያየረ፣ ግራ ተጋባ፣ አይኖቹ በዕንባ ተሞሉ፣ የአባቱን መሪር ሀዘን …

ከደቡብ ዩኒቨርሲቲ በደን ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ከተመረኩኝ በኋላ አንድ ቀን አመሻሽ ላይ ከተስፋለም ጋር ከልደታ ተነስተን ወደቦሌ መስመር ወክ በማድረግ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይበተመስጦ እያወጋን ነበር፡፡ አስታውሳለሁ፣ ወሎ ሰፈር ጋር አንድ ጥያቄ ጠየኩት፡፡ ‹‹በተማርኩት ትምህርት ደስተኛ ብሆንም ነፍሴ ግን አልረካችም›› አልኩት፡፡ ‹‹ኤልያስ ውስጥህን በእርጋታ አዳምጠው›› በማለት ተስፋለም መለሰልኝ፡፡ እውነቱን ለመናገር ውስጥን ማዳመጥ ምን ማለት እንደሆነ እስከዚያች ቅጽበት ድረስ አላውቅም ነበር፡፡ ዛሬ ከነፍሴ በምወደው የጋዜጠኝነት ሙያ ላይ እንድገኝ ‹‹…ውስጥህን አዳምጠው›› የሚለው የተስፋለም ወንድማዊ ምክር እጅጉን እንደጠቀመኝ ዛሬ ላይ ተነፈስኩት፡፡ ተስፍሽ አስተዋይ የሆነ የትንሽ ትልቅ ነበር፡፡

ተስፍሽ፣ ድንገተኛ እስርህ አመመኝ፣ ቁጭት ፈጠረብኝ፡፡ ዛሬም ድረስ ውስጤን እያንገበገበው ይገኛል፡፡ ሆኖም እሰሩ የዜጎችን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ ሕገ-መንግስታዊም ሆነ ዓለማቀፋዊ መብት እንዲከበር ለምወደው ሙያ ይበልጥ በጽኑ እንድቆም ጤናማ እልህ አቀጣጥሎብኛል፡፡ የእናንተ እስርም በነጻው ፕሬስ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ጋዜጠኞችን ልብ በሃዘን ነክቷል፣ ንዴታዊ ስሜት ውስጥም ከትቷል፡፡ በጋዜጠኝነት ለመስራት ‹‹ሙያው አስጠላን›› ያሉኝም አሉ – መፍትሄ ባይሆንም፡፡

በአዲስ አበባ አራዳ ፍርድ ቤት የጓደኞችህን እና የአንተን ሁለት እጅችህ በብረት ካቴና ተጠፍንገው ስመለከት ደግሞ በመንግሥታችን እጅጉን አዘንኩ፡፡ ጠረጼዛ ላይ ያሉ ጋዜጦችን፣ መጽሄቶችንና መጽሐፍቶችን እንኳን ከልጅነትህ ጀምሮ ማዝረክረክ የማትወደው ልጅ ከነፍስህ የምትወዳትን እምዬ ኢትዮጵያን ከሙያ አጋሮችህ ጋርበሽብር እና በአመጽ ለማተራምስ ተንቀሳቅሰሃል ብዬ ለሰከንድ እኩሌታ እንኳን በጭራሽ አላስብም፡፡ለምትወደው ሙያህ ዘወትር ሚዛናዊ ዘገባን ለማቅረብ መታተርህ መንግሥት ላይ ስጋት ፈጥሮ ይሆን እንዴ? …በእናንተ ላይ የሚቀርበውን ክስ ለማወቅ በጣም የጓጓሁትምለዚሁ ነው፡፡
አይደለም ከልጅነቴ ጀምሮ በደንብ የማውቀውን ተስፋለምን ቀርቶ ሌሎች የታሰሩት የሙያ አጋሮቻችንእንኳን በሚወዷት ሀገር ላይ ሽብር እና አመጽ ለማካሄድ የማሴርዓላማ እና ዕቅድ አላቸው ብዬ ለማሰብ ፍጹም እቸገራለሁ፣ይህ የግሌ እምነት ነው፡፡
…ተስፋለምን ለረዥም ዓመታት ከማውቀው አኳያ ብዙ ማለት ብችልምለዛሬ የልጅነት ሕይወቱን ብቻ ጠቅሼ ለማለፍ ወደድኩ፡፡ተስፍሽ፣ ንጽሕናህ እና ሙያዊ ጥንቃቄህ ነጻ ያወጣሃል!!! ነገር ግን፣ በጊዜው የኢሕአዴግ መንግሥት የፍትሕ ሥርዓት ላይ እምነት ካጣሁ ቆየሁ፡፡

እንደመውጫ
ስለተስፋለም በሥራው ላይ ስለላው ባህሪ እና ትጋት በቅርበት የሚያውቁት ጓደኞቹ፣ ባልደረቦቹና ወዳጆቹ በማኅበራዊ ድረ-ገጽ እና በሕትመት ሚዲያዎች ላይ ሃሳባቸውን መግለጻቸው ይታወቃል፣ አሁንም እየገለጹ ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል ሁለትጓደኞቹለእሱ ከጻፉለት ጽሑፎች ውስጥመርጬ በድጋሚ በዚህ ጽሑፌላይ ባሰፍርለት ልቤ ወደደ፡፡ የቀድሞ አዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባው ጋዜጠኛ ማስረሻ ማሞ በፌስ ቡክ ገጹ እንዲህ ብሎ ነበር፡-
‹‹ …ተስፋለም የግል ፖለቲካ አመለካከቱ ከጋዜጠኝነቱ ጋር እንዳይጋጭበት የሚጠነቀቅ ወጣት ነው፡፡ ከጋዜጠኝነት ከፍ ያለ ክብር እና ዋጋ ይሰጣል፡፡ አንዳንዴ እቀናበታለሁ፡፡ ስለሚዛናዊነቱ እቀናበታለሁ፡፡ ስለሚዛናዊነቱ፣ ስለተገቢነትና ስለእውነተኛ ዘገባ አብዝቶ ይጨነቃል፡፡ ማንኛውም ዓይነት ዘገባ ከትክክለኛው ወንዝ ተቀድቶ እንዲፈስ ይመኛል፣ ያደርጋል፣ ይጓዛል፡፡ መጀመሪያ ለሙያው ታማኝ መሆንን ያስቀድማል፡፡ ከተስፋለም ጋር ሳወራ ከታናሽ ወንድሜ ጋር የማወራ ነው የሚመስለኝ፡፡ ኢሕአዴግ እንደተስፋለም መሥመራቸውን ጠብቀው ለሚሰሩ ሰዎች የማይመለስ ይሆናል ብዬአስቤ አላውቅም፡፡ አሁንም መታሰሩን ማመን እውነት እውነት አልመስልህ ብሎኛል! የሚሰማኝ እልህ፣ ቁጭት፣ ተስፋቢስነትና ቁጣ ነው፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ተስፋለም የማንም ወገን አይደለም፡፡ ብቻውን በራሱ የቆመ ጋዜጠኛ ነው፡፡››
ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ደግሞ ባለፈው ሳምንት ለንባብ በበቃው ‹‹ፋክት› መጽሔት ላይ ‹‹ትንሹ ተስፋለም›› በሚል ርዕስ ከጻፈችው የቀነጨብኩትን ደግሞ እንዲህ አስቀመጥኩት፡-
‹‹በአነጋገሩ ቀጥተኛና በጠባዩ ገራገር ነው፡፡ ‹ጥርስ ያሳብራል› በሚባሉ ስብሰባዎች፣ በኃይለ ቃል በተሞሉ የኢዲቶሪያል ውይይቶችና ግምገማዎች ሳይቀር ስሜቱን ውጦ በተረጋጋ መንፈስና በለዘብታ ቃል መመላለስ ጸጋው ነው፡፡ በኤዲቶሪያል ጠረጼዛዎች እና ዴስኮች ዙሪያ በሐሳብ ለመግባባት ከሚደረጉ ግብግቦች ውጭና ባሻገር ቂም እና በቃል አያውቅም፡፡ በደሙ ውስጥ ከሚዘዋወረውና ራሱን ከሰጠለት የጋዜጠኝነት ሙያውና የጋዜጠኝነት መርህ የተነሳ ሌላ ዓለም፣ ሌላ ኑሮ ያለም አይመስለው፡፡ ለእርሱ ኑሮው፣ ለእርሱ ዓለሙ፣ ተጨባጭ መረጃን ከወገናዊነት በጻዳ መልኩ ለሕዝብ ማድረስ ነው፡፡…››

…ከቀናቶች በኋላም ለተወሰኑ ወራት በዕንቁ መጽሄት ላይ አብረን በመሰራት ስለማውቀው ጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ (በፍቄ) ብዕሬን አንስቼ እጽፋለሁ፡፡
በእስር ላይ የሚገኙትን፣ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በፖሊስ እንደተፈጸመባቸው በፍርድ /ቤት የተናሩትን ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያን እግዚአብሄር ጽናት፣ ብርታትና ጥንካሬ ይስጣቸው፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 13, 2014. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.