ከሁለቱ ስዊድናዊያን ጋራ “በሽብርተኝነት” የተከሰሱት የ17 ዓመት ጽኑ እሥራት ተፈረደባቸው

(ኤፍሬም ካሳ)

ከሁለቱ ስዊድናዊያን ጋራ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በዋና ወንጀል አድራጊነት የተከሰሱት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) አባላት የኾኑት አብዲወሊ መሐመድ እስማኤል እና ከሊፍ ዐሊ ዳሂር የ17 ዓመት ጽኑ እሥራት ዛሬ ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 9፡30 ተፈረደባቸው፡፡

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ዳኛ ሸምሱ ሲርጋጋ ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት ላይ እንደተናገሩት ፍርድ ቤቱ ጠዋት በዋለው ችሎት ያደመጠውን የግራ ቀኙን (የዐቃቤ- ሕግ እና የተከላካይ ጠበቃ) የቅጣት አስተያየት አገናዝቦ ተገቢውን ውሳኔ ሰጥቷል፤ የፍርዱ ዓላማ ጥፋተኛውን ማስተማር፣ ኅብረተሰቡን እና አገርን ደግሞ ከጥቃት መከላከል በመኾኑ ወንጀሉን በመካከለኛ ደረጃ መድበነዋል ብለዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን በንባብ ሲያሰማ እንደገለጸው መነሻ ያደረጋቸው አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት የጸረ ሽብር ሕግ 652/2001 አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 2 በመተላለፍ ወንጀል መፈጸማቸው በዐቃቤ- ሕግ ማስረጃ መረጋገጡ፣ ሁለቱ ተከሳሾች ከ2000 ዓ.ም እና ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የኦብነግ አባል በመኾን የጦር መሣሪያ ሥልጠና በመውሰድ እና በመታጠቅ በውጊያ ላይ እስከተማረኩበት ጊዜ ድረስ በሶማልያ ክልል ልዩ ልዩ ዞኖች ኅብረተሰቡን በሽብር ተግባር ማወካቸው እና በዚሁ ተግባር ላይ መኾናቸው ተረጋግጧል፡፡

የአጥፊዎችን የግል ባሕርይ እና አደገኝነት መጠን በማገናዘብ እና የቅጣት አወሳሰን መርህን በማየት ምንም እንኳ የቀረበባቸው ክስ ከ15 ዓመት እስከ እድሜ ልክ ጽኑ እሥራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ ቢችልም ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ- ሕግን “ቅጣቱ በከፍተኛ ደረጃ ይያዝልኝ” እና የተከላካይ ጠበቃን ደግሞ “በዝቅተኛ ደረጃ ይያዝልኝ” ጥያቄ ባለመቀበል በመካከለኛ ደረጃ በመውሰድ እያንዳንዳቸው በ20 ዓመት መነሻ ጽኑ ቅጣት በይነን የተከላካይ ጠበቃ ባቀረቧቸው የቅጣት ማቅለያ ነጥቦች ሦስት ዓመት በመቀነስ የ17 ዓመት ጽኑ እስራት እና በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23 ሕዝባዊ መብቶቻቸው እንዲሻር ወስነናል፤ ተከሳሾች በውሳኔው ቅሬታ ካላቸው ይግባኝ የመጠየቅ መብታቸው የተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

ዛሬ ጠዋት በዋለው ችሎት ላይ ዐቃቤ- ሕግ እና የተከላካይ ጠበቃ የቅጣት ማክበጃ እና የቅጣት ማቅለያ ነጥቦቻቸውን ለፍርድ ቤቱ ያቀረቡ ሲኾን ተከሳሾችም የቤተሰባቸውን ኹኔታ በመግለጽ ፍርዱ እንዲቀልላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ወንድማገኝ ባቀረባቸው የፍርድ ማክበጃ ነጥቦች ላይ እንደጠቀሰው በአገሪቱ ሕግ አውጪ ተቋም (ፓርላማ) በሽብርተኝነት በተፈረጀው ኦብነግ ውስጥ በአባልነት በመሳተፍ የመሣርያ ሥልጠና በመውሰድ እና በመታጠቅ በሶማሌ ክልል ዞኖች በለሊት በመንቀሳቀስ ኅብረተሰቡን በማስገደድ በሽብር በማወክ፣ የአገሪቱን መሠረታዊ ተቋማት በማናጋት የክልሉን ሠላም በማደፍረስ ኅብረተሰቡን ሲዘርፉ ነበር፣ በወቅቱ በውጊያ ላይ ሲያዙም በሦስተኝነት እና በአራተኝነት የተከሰሱትን ሲዊዲናውያን ጋዜጠኞች በሕገ-ወጥ መንገድ አገር ውስጥ በመሣርያ አጅቦ በማስገባት ወንጀል የፈጸሙ በመኾናቸው ሌላውንም ለማስተማር በከባድ ደረጃ ወንጀል እንዲያዝልኝ እጠይቃለሁ ሲል ዐቃቤ- ሕግ ጠይቆ ነበር፡፡

የተከላካይ ጠበቃ አቶ ሳሙኤል አባተ በበኩላቸው ዐቃቤ- ሕግ ያቀረባቸው የቅጣት ማክበጃ ነጥቦች በሙሉ በክሱ ላይ የተካተቱ በመኾናቸው ፍርድ ቤቱ ውድቅ እንዲያደርጋቸው ጠይቆ፣ አንደኛ ተከሳሾቹ ግለሰቦች የሚኖሩበት ማኅበረሰብ ዘላን (አርብቶ አደር) ማኅበረሰብ በመኾኑ የአኗኗር ኹኔታቸው ተጽዕኖ ስላለው ከግንዛቤ እንዲገባ፣ ሁለተኛ ምንም ዐይነት መደበኛ እና ኢ-መደበኛ ትምህርት የሌላቸው በመኾኑ የርዕዮተ ዓለማዊ ኹኔታዎችን ለመረዳት ስለሚከብዳቸው በቀላሉ ለኦብነግ ዓላማ መልማዮች የሚጋለጡ መኾናቸው ታሳቢ እንዲኾን፣ ሦስተኛ ድርጊታቸውን ከመጀመሪያው ምርመራ ጀምሮ ያልካዱ መኾናቸው እና ከዚህ በፊት በምንም ዐይነት ወንጀል ተከሰው የሚያውቁ ሰዎች ባለመኾናቸው እና ዐቃቤ- ሕግም ይህን ባለማሳየቱ ከዚህ ቀደም ሕይወታቸው ሰላማዊ ሰዎች እንደነበሩ ስለሚያመላክት ፍርድ ቤቱ የቅጣቱን መነሻ እርከን 15 ዓመት በማድረግ የቅጣት ማቅለያውን ታሳቢ በማድረግ ከ7 እስከ 9 ዓመት ቢቀጣቸው ሊያስተምራቸው ይችላል፤ የቅጣት ዓላማውም ማስተማር ነውና ብሏል፡፡

የመጀመሪያ ተከሳሽ አብዲወሊ መሐመድ እስማኤል የማቅለያ ሐሳቡን ፍርድ ቤቱ በአስተርጓሚ በኩል ሲጠይቀው እኔ የ7 ልጆች አባት፤ የሁለት ሚስቶች አባወራ እና ቤተሰብ አስተዳዳሪ ነኝ ፣ አሁን በምን ኹኔታ ላይ እንዳሉም አላውቅም፣ ምንም ዐይነት ሀብት የላቸውም ብሏል፡፡ ሁለተኛው ተከሳሽ ከሊፍ ዐሊ ዳሂር በበኩሉ ቀለል ባለ መንፈስ በአጭር ቋንቋ ልጆች የሉኝም ሚስት እና ቤተሰብ ግን አለኝ ብሏል፡፡

የመሀል ዳኛ ሸምሱ ሲርጋጋ ዐቃቤ-ሕግ በአብዛኛው ያቀረባቸው ቅጣት ማክበጃዎች በክሱ ላይ እንደተካተተ ጠቅሰው፣ ተከሳሾቹ በሌሊት ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባለው ማንኛውም ወንጀለኛ ቀንም ኾነ በሌሊት ስለሚንቀሳቀስ ምንም የተለየ ነገር ስለሌለው ውድቅ መደረጉን፣ የአሸባሪ ቡድኑ ጋር ስምምነት አድርገዋል የሚለውም ለማክበጃ እንደሚያገለግል ኾኖ አላገኘነውም፡፡

በሌላ በኩል የተከሳሽ ጠበቃ ያቀረቡት የተከሳሾቹ የኑሮ ዘዬ፣ ኹኔታ፣ የቤተሰብ መሪ መኾናቸው፣ ትምህርት አለመማራቸው ታሳቢ ተደርጎ እና ከዚህ ቀደም ምንም ተከሰው የማያውቁ መኾናቸው አሊያም ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ባሕርይ ዐቃቤ- ሕግ በማስረጃ ባለማሳየቱ የቅጣት ማቅለያውን ተቀብለነዋል፡፡

ስለዚህ አንደኛ እና ሁለተኛ ተከሳሾች በመካከለኛ ደረጃ ወንጀል 20 ዓመት ጽኑ እሥራት የሚቀጡ ቢኾንም እስከ አሁን የታሰሩት ታሳቢ ተደርጎ 17 ዓመት ጽኑ እሥራት እንዲቀጡ ወስነናል፤ በውጊያ ላይ ሲያዙ ታጥቀውት የነበረው ሁለት ክለሽንኮቭ መሣርያ ለመንግሥት ውርስ እንዲኾን፣ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 23 በእሥር ላይ በሚቆዩበት ጊዜ የመምረጥ እና የመመረጥ ሕዝባዊ መብቶቻቸው እንዲሻር ወስነናል በማለት 10፡30 ሰዓት ላይ ችሎቱ ተበትኗል፡፡

Source: Addis Neger

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 4, 2011. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.