ኦ ጋዜጠኞች አሁንስ ለህሊናችሁ፡ ፖለቲከኞችም!! (ክፍል ሁለት – በዳንኤል ገዛኸኝ)

ክፍል ሁለት   (በዳንኤል ገዛኸኝ)

በክፍል አንድ ጽሁፌ ከበጎ አስተያየቶች ይልቅ ተለሳልሰሃል እንደዚሁም ወቀሳዎቹ አድልተዋል። በአንጻሩ የመለሳለሴን ሃሳብ የሰጡኝ ጎን ለጎን መልካም አስተያየታቸውን ቸረውኛል። የምጽፈው ያመንኩበትን ነው። በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ ወሰን ሰገድ ገብረ ኪዳን ሰሞኑን “የኔ ወጋጎዳ”ሲል ስለ ሳንሆዜ ካሊፎርኒያው አሰፋ ጫቦ በዘሃበሻ ድረ-ገጽ ላይ የጻፈውን ጽሑፍ አንብቤ እውነትም ያ ሃያሲ ያ ፖለቲከኛ…ያ ወግ አርቃቂ ደራሲ…ያ የሶስት መንግስታት ታሳሪ…ያ የወያኔ ዘመን በጎ አድራጊም በክፉም ተሳዳጅ የሰባዊ መብት ተከራካሪ እውነትም ወጋጎዳ አሰፋ ጫቦ የት ሄደ ? ብዬ እንደ ወሰን ሁሉ እንድጠይቅ ሆኛለሁ። በዚሁ ዛሬ አሉ የሚሉዋቸውን ፖለቲከኛዎች እየፈለጉ እያፈላለጉ የሚጠይቁ ጋዜጠኛዎች ተነግሮ የማያልቅ የተለያየ ታሪክ ባለቤት የሆነው አቶ አሰፋ ጫቦ ጠፍቶዋቸው ይሆን ? ወይንስ የ አሰፋ ጫቦ አቅጣጫ አይፈለግ ይሆን ? እርግጥ ነው አሰፋ ጫቦ በሶስት ስራት ውስጥ የራሱን አሻራዎች ማስቀመጥ ችሎዋል ግን ደግሞ ሶስቱም ስራቶች ለአሰፋ ጫቦ አመቺ አልነበሩም። አሰፋም ከዚም ከዚያም የመሆን ዝንባሌው በብዙዎች ዘንድ ባይወደድለትም መሆን የቻለውን ሁሉ ግን ሆኖዋል። የሆነው ሆኖ ወሰን በአሰፋ ያስታወሰው ወጋጎዳ/ በዘመነ ወያኔ ሌላም ትውስታ አለው እግረ መንገዴን ለማስታወስ እንጂ በዚህ ዙሪያ የምለው ጉዳይ የለኝም። (ሙሉውን ጽሁፍ በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)

ወጋጎዳ/ ወ.ጋ.ጎ.ዳ ወያኔ የደቡብን ህዝብ በአንድ ቁዋንቁዋ በአንድ የአገዛዝ አስተዳደር ስር ጨፍልቆ ለመግዛት የተለመው ሌላ የቁዋንቁዋም ስልት ነበረ አልተሳካም እንጂ። የወጋጎዳ ትንታኔም ወ.ወላይታ…ጋ.ጋሞ…ጎ.ጎፋ…ዳ.ዳውሮ የሚል ትንታኔ ያለው ሲሆን በብዙ ሚሊዮን በሚቆጠር የገንዘብ በጀት ያለ ደቡብ ህዝቦች የጉዳዩ ባለቤቶች ፍላጎት እና ሃሳብ የቋንቋውን መጽሃፍ አሳትመው እነ ታጋይ አባይ ጸሃዬ የሚመሩት ቡድን ስራውን ሰርቶ ሲያበቃ ህዝቡ ባለመቀበሉ በደቡብ ክልል በተለይ አዋሳ አካባቢ የተከሰተውን እልቂት የምናስታውሰው እናስታውሰዋለን። በተመሳሳይ ወጋጎዳ ታላቁ ጌታ የሚለው የነ አሰፋ ጫቦ ትርጉዋሜ እንዳለ ማለት ነው።

እንግዲ አንድ የመገናኛ ብዙሃን የራሱ የሆነ ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አለው። ሃ ብሎ ተቁዋሙ ሲመሰረት አላማ እና እቅድ የራሱ የሆነ ፕላን እንዳለው ሁሉ ያ የሚዲያ ተቁዋም ለጋዜጠኛው የሚሰጠው ነጻነት ደግሞ የቱ ድረስ እንደሆነ ጋዜጠኛው በዚያ ተቁዋም ሲሰራ የሚቀበለው ሃላፊነትን ጨምሮ የሚሰጠው ነጻነት ምን ያህል እና የት ድረስ እንደሆነ ያውቃል። ስለሆነም የመስራት ያለመስራት ሃላፊነት የባለሞያው ይሆናል ማለት ነው። ምክንያቱም ጋዜጠኛው የሚኖረው ሁለት አይነት ጉዳይ ነው። አንዱ የተቁዋሙ አላማ የራሱ እንደሆነ አድርጎ በመቀበል ከተቁዋሙ ፍላጎት ዝንፍ ሳይል አብሮ መጉዋዝ።

ምክንያቱም ተቁዋሙም እሱም አንድ ስለሆኑ ማለት ነው። ለምሳሌ በወያኔ ሚዲያ ውስጥ ያሉትን ካድሬ ጋዜጠኛዎች ልብ ይሉዋል። ሚዲያው የፓርቲው ስለሆነ ካድሬው ጋዜጠኛም የፓርቲው አባል ስለሆነ ፓርቲው የማይፈልገው ጉዳይ የፓርቲውን እና የሚዲያውን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሚጎዳው የጋዜጠኛውንም ስለሆነ ለተቁዋሙ ፍላጎት እና ሃሳብ ያድራል ማለት ነው። ሁለተኛውን ጉዳይ ስንመለከት ጋዜጠኛው ለሙያው ስነ-ምግባር ተገዢ ሆኖ የሚሰራበትን ፎርማት ተቁዋሙ አክብሮለት እየሰራ የሚጉዋዝበት ሂደት ነው የሚኖረው። ዛሬ በ እጅጉ እየተስተናገደ ያለው የመጀምሪያው ጉዳይ ነው። ጋዜጠኛዎች በዚህ ነጻነት በገፍ ባለበት ሃገር እንኩዋን ነጻነታቸውን አሳልፈው የሰጡበትን ሂደት ነው በግሌ እየታዘብኩ ያለሁት። እንደ እውነቱ ከሆነ ጋዜጠኛ ከ እውነት እና እውነት ነጻ ከምታወጣው ህዝብ ጎን መሰለፍ ግድ ይለዋል። በአሁኑ ወቅት እኮ ህዝብ እውነት አርነት እንድታወጣው ከፓርቲዎች እና ከግንባሮች በላይ ተጨንቆ ህዝባዊ የንቅናቄ ሃይል መስርቶ ጦር አደራጅቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። ስለዚህ ጋዜጠኛው ተአማኒነቱ ለፓርቲ ሳይሆን ለህዝብ መሆን ይገባዋል። ይልቅ ህዝባዊ ንቅናቄ ስል አንድ ጉዳይ ትውስ ብሎኛል። ባለፈው ጊዜ የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ንቅናቄ ሰራዊት መመስረቱን ኢሳት ከዘገበ በሁዋላ ንቅናቄው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከሚመሩት ፓርቲ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ሚዲያው ለማጣራት ያደረገው ሙከራ አለመሳካቱን የዜና አንባቢው ሲናገር ይሄ ብቸኛ የሚዲያ ተቁዋም እውነትም ገለልተኛ ነው ብዬ በንጹህነት እንዳስብ ሆኜ ነበር። ነገር ግን በተመሳሳይ በ ኤርትራ አንድ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መከሰቱን የተለያዩ ድረ ገጾች ብሎጎች እና የአሜሪካ ሬድዮን ጨምሮ በጉዳዩ ዙሪያ በርካታ ሚዲያዎች በ ኤርትራ ጉዳይ ላይ ጽሁፍ የሚጽፉ አንድ የውጪ ሃገር ጋዜጠኛን በመጥቀስ ትንታኔ ሲያቀርቡ የ ኢሳት ዜና ግን በ ኤርትራ የሚኖሩ አንድ ኢትዮጲያዊ የሚል ምንጭን ተጠቅሞ አቀረበ።

በ እውነት በ ኤርትራ ኢትዮጲያውያን የዚህን ያህል ለዜና ምንጭ ሆነው መረጃ በሚያቀብሉበት ሂደት ነው በዚያ ሃገር ያሉት ? እንኩዋን በአስመራ ያሉ ኢትዮጲያውያን ስደተኛ ህዝቦች ቀርቶ የ እልጀዚራ ዘጋቢዎች ፕረዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለማነጋገር ተፈቅዶላቸው ወደሃገሪቱ በገቡበት ወቅት የሞባይል ሲምካርድ ከመከልከል አንስቶ ከተማዋ ውስጥ መዘዋወር መከልከላቸውን እንዘነጋዋለን ?…። ቀደም ባሉት የ ኤርትራ የናጽነት ማግስት እና በዋዜማው ኢትዮጲያውያን ከአስመራ እና አክባቢዋ ከአሰብ የተባረሩበትን የታሪክ ሂደት በማንሻፈፍ በቴሌቪዥን ቀርበው ሃሰት የመሰከሩትን ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴን ስንተች አልነበረም ? ታዲያ ዛሬ ለምን እውነት ተንሻፎ እንዲቀርብ ተባባሪ እንሆናለን። ምንጊዜም እኮ እውነት በ እጃችን እስካለ ድረስ ለጊዜያዊ ትርፍ ብለን የምናደርገው ቁንጽል ውሸት ነገ ይሞግተናል። ስንቶቻችን እንሆን በኤርትራ ውስጥ የ እትዮጲያን አንድነት በተመለከተ ትግል የሚያደርጉ ታጋዮች አበሳ እንደሚቆጥሩ የምናውቅ ስንቶቻችን ነን ?…። ስለዚህ ጋዜጠኛ በዚህ ሃገራችን ኢትዮጲያ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ወቅት እና ሂደት ጋዜጠኛዎች ከ እውነት እና ከእውነት ጋር ቁሙ። በስሌት መንቀሳቀስ አያዋጣም። ማለት የምፈልገው ለህሊናችን እንደር ነው። ምናልባትም የመናገሪያውን አፍ እኛ ከፍ ብለን ስለጨበጥን ሌላው ከ እውነታው ላይ አይደርስም ማለት መሳሳት ነው። ኦ ጋዜጠኛዎች አሁንስ ለህሊናችሁ። ፖለቲከኛዎቹም አማራጫችን በሚል ብሂል…የጠላቴ ጠላት በሚል ስሌት ብቻ መራመድ የማያዋጣባቸው ብዙ መንገዶች መኖራቸውን ልብ በሉ። በዚህ ሃሳብ ወደፊት እመለስበታለሁ።

እርግጥ ነው ጋዜጠኛው በነጻነት ሃገር የሙያ ግዴታውን ስነ-ምግባሩን ጠብቆ እንዳይሰራ በሚያስገድደው ተቁዋም ውስጥ ላለመቆየት ውስኖ ቢሄድ የሚያጣው ነገር አለ። የሚያስበውን በሞያው እየሰራ የሚያገኘውን ገንዘብ ያጣል በትክክል። ነገር ግን ተቁዋሙ እንደሚፈልገው ከተጉዋዘ ያንን ገቢውን አያጣም። እኔን በቅርቡ ያጋጠመኝን እዚህ ጋር ልጥቀስ። በአንድ የሬድዮ ጣቢያ ውስጥ በምኖርበት በዚሁ በአትላንታ ከተማ በሳምንት የአንድ ሰአት ፕሮግራም አዘጋጅቼ ሳቀርብ ቆይቻለሁ ነገር ግን በጥቂት ተከታታይ ዜናዎች የተነሳ በሚዲያው ላይ ልትሰራ የገባሐውን ቃል አልተገበርክም የሚል ክስ ከፕሮዲውሰሩ ተሰነዘረብኝ። እናም ከሚከፈለኝ ነገር ይልቅ ነጻነቴ ይቀድማል አልኩ እና ትቼው ለሁለት ሳምንት በማኩረፍ ተቃውሞዬን ለመግለጽ ሞከርኩ። “እረኛ ቢያኮርፍ ምሳው እራቱ ይሆናል…” ይባል የለ ያንን ድምጼን የማሰማበትን የአንድ ሰአት ፕሮግራም ላለማጣት ሞያዬን ተግባራዊ ለማድረግ ድርድር ለማድረግ አሰቤያለሁ። ድርድሬ ግን ሞያዊውን ስነ ምግባር በሚጥስ መልኩ ግን አይደለም። ቢሆንም የመናገር ነጻነቴን በገደብ የሚተው ከሆነ ስራውን ከመተው ውጪ አማራጭ የለኝም።

ማናችንም በዚህ በስደት ሃገር ለመኖር የጥገኝነት መብት አግኝተን ስንመጣ በትክክል ሃገር ቤት እንተገብረው የነበረውን ሞያዊ ህይወት እዚህ ተመቻችቶ ይጠብቀናል የሚል እምነት አልነበረንም። ከኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች አንጻር ማለቴ ነው። ምናልባትም በሌላ መልኩ የተለየ ስራ ገቢ እንድናገኝበት ህይወታችንን እንድንኖርበት ተቀጥረን እየሰራን ሞያችንን በተመለከተ ግን በምንችለው አጋጣሚ ተግባራዊ እያደረግን ልንጉዋዝ እንችላለን። በተረፍ በስደት ሃገር በሚዲያ ተቁዋም ተቀጥሮ የመስራት እድል ጠባብ ከመሆኑ አንጻር ሌላ አይነቶቹን የስራ አለም ላለመሞከር ማነነትን አሳልፎ በመስጠት በዚህ የመጀመሪያው የመናገር ነጻነት ማሻሻያ በጸደቀበት ሃገር ሎሌ መሆን ምን ያህል ለህሊና እንደሚያስደስት እኔ አላውቅም። እርግጥ ነው “ያጣ ለማኝ…” የሚለውን ተረት ያስተርት ይሆናል። ምክንያቱም ነጻ የሆኑ ቀጥረው ማሰራት የሚችሉ የሚድያ ተቁዋማት ሲገኙ ብዙዎቻችን ለመስራት ስለምንጉዋጉዋ ግን ደግሞ “የተጠሩት ብዙ ናቸው የመጡት ግን ጥቂት ናቸው” እንዲሉ ብሂል ተመኝተነዋል እንጂ በ እድሉ መጠቀም የቻሉት ትንሽ ናቸው።

እንግዲ እንዴት ከተባለ መስፈርቱ ችሎታም…ሌላም ሌላም ጉዳዮች ይሆናሉ። ዞሮ ዞሮ ነጥቤ ይሄ አይደለም የኔ ነጥብ ጋዜጠኛዎች ነጻ ጋዜጠኛዎች ናቸው እየተባሉ ህዝብ እያመነባቸው ከበሮ እየተመታላቸው እንደገና ለተወሰነ ሃሳብ ባለቤቶች ብቻ አድረው የነሱ አራጋቢ ሲሆኑ ይህ በ እጅጉ ያሳዝናል። ምክንያቱም ከትላንቱ የዛሬውም “አልሸሹም ዞር አሉ” ይሆንብኛል። በአንጻሩ ስመለከተው ደግሞ ከሰሞኑ አንጀት የሚያርሱ የሰፊውን የ ኢትዮጲያን ህዝብ ተባብሮ የመታገል ጥም የሚቆርጥ ጅምር አስተውያለሁ የኢሃፓ አመራር የሆኑት እነ እያሱ ለማየሁ በኢሳት ቴሌቪዥን የትግል ትሪ ሲያቀርቡ ተደስቻለሁ። ከዚህ ቀደም አቶ እያሱ አለማየሁ በመሳይ አለማየሁ የ ኢሳት ሬድዮ ፕሮግራም መቅረባቸው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። ወጣም ወረደ ግን ሚዲያው ላይ ለ ኢትዮጲያ ትንሳኤ ሚና ይኖራቸዋል ተብለው የተገመቱ እና ታሪክ ያላቸው ሰዎች መቅረባቸው ብቻ በአንድ በኩል ፋይዳ የለውም። ለህዝቡ ሊጠቅሙ የሚችሉ ጉዳዮችን እንዲያብራሩ ጥያቄዎችን ማፍለቅ ሃሳቦችን መሰንዘር ከጋዜጠኛው ያስፈልጋል። ለአብነት ብዙ ስንጠብቅ አይነተኛ የትግል ታሪክ ብቻም አይደለም ህዝቡ በምን መልኩ አብሮ መታገል እንደሚገባው አቅጣጫ የሚያስይዝ ጥያቄ ሳይቀርብላቸው ቃለ-ምልልሳቸው የተጠናቀቀውን የፕ/ር ማሞ ሙጬን ቆይታ ማስታወስ ያስፈልጋል።

ወያኔ የነጻውን ፕሬስ ጋዜጠኛዎች እኩል ያስረን በነበረበት ወቅት የመግለጫ አወጣጥ እንኩዋን ብዙ ልዩነት እና ታሪክነበረው። ይህ ይታሪክ ሽሙት የመጣውም የተወሰኑ ጋዜጣዎች ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ቅርበት ያላቸው ናቸው ሌሎቹ ደግሞ በራሳቸው መንገድ የሚጉዋዙ ናቸው በሚሉ ከፕሬሱ ባሻገር ያሉ ቡድኖች በሰየሙዋቸው ጽንፎች ነው። እነዚህም ስንፎች ነጻ ፕሬስ እና ነጻው ፕሬስ የሚሉ ነበሩ። በሌላ በኩል ወያኔ ያኔ ከ 97 ቀደም ሲል መሆኑ ነው ሁሉንም የነጻው ፕሬስ ዝግጅት ክፍል ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በውጪ ካሉ ሃይሎች በፋይናንስ በተለያዩ ሁኔታዎች የሚደጎም እያለ ሲከስ ኖሮዋል ዛሬስ ታዲያ በፋይናንስ መደገፉ ቢቀር በተቃዋሚዎች ሃሳብ የተቃኘ ጋዜጠኛ ይሄንን ሃሳብ ብቻ ስሙ እያለ እየሞገተን ነው ለምን ? ሃቀኝነት…ሚዛናዊነት…ገለልተኝነት የጋዜጠኝነት የሙያ ስነ ምግባሮች የት ገቡ ? ሙያዊ የሞራል ግዴታስ ? አንዳንድ ጊዜ ከፊትለፊታችን ብዙ ጊዜ የማናያቸውን አማራጫቸውን እና የትግል ስልታቸውን የምንገነዘብላቸውን ብቻም ሳይሆን ከነሱም የሚበልጥ አቅጣጫ አላቸው ብለን የምናስባቸውን ማስታወስ ተገቢ ነው። ብዙ ጊዜ አንጋፋ በሚለው ደረጃ ያሉቱ የተቃውሞ መሪዎች አንድ ጊዜም ሳት ብሎዋቸው እነሱ ባቀጣጠሉት የፖለቲካ ቋያ ሰደድ ምክንያት ሃገር ለቀው የተሰደዱ ወገኖችን በተመለከ አንድ ቃል ሲተነፍሱ ሰምቼ አላውቅም። ጉዳዩን በተመለከተ ጋዜጠኛዎም አይጠይቅም። ይልቅም ከዚህ በባሰ አኳዃን ለማሳወቅ መረጃ ለማቀበል የተመሰረቱ ብሎጎች እያዘጋጁ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ አፍሪካ…ከአፍሪካ እስከ ሩቅ ምስራቅ ሃገራት እንደጨው የተበተኑ ኢትዮጵያውያንን በማስታወስ ወገናዊ ሚና እየተወጡ ያሉትን እነ ጌታቸው ረዳን/ኢትዮ ሰማይ/…የሲያትልዋን ወ/ሮ ሙሉ እመቤት ደበበን…ግርማ ካሳ…ስንቶቹን ጠርቼ ስንቶቹን ልተው እነዚህ እና መሰል ኢትዮጵያውያን የአትላንታው አቶ ቸሩ…በተለይም በኢሳት ዝግጅቶች በሚችለው ሁሉ የሚታገለውን እየፈለፈልን እንፈልግ እንጂ ለምን እንቦዝናለን ? እርግጥ ነው በስራችሁ ምስጋና ያሻችሗል። አደራ ለህሊናችሁ ምስጋናው ግን እንዳያዘናጋችሁ ባይ ነኝ።

ዛሬ እኛ የገዢውን ሆድ እቃ መቀመጫ ታዛቸው አድርገው ሙያቸውን የሚሸቅጡ ግለሰቦችን ማሳፈር ይኖርብናል። ይህንን ስንል ታዲያ የምንሻልበትን ሚዛናዊነት እና ገለልተንነታችንን በማሳየት ነው። በበኩሌ ለኔ የሽግግር ምክር ቤቱ ፕረዚዳንት እና መስራች ዶ/ር ፍሰሃ እሸቱ እና የግንቦት ሰባቱ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እኩል ናቸው። በኔ አስተሳሰብ አመለካከት እና እይታ የሁለቱም ግለሰቦች አላማ እና አቁዋም ኢትዮጲያን ከዚህ ዘረኛ እና ጎጠኛ ቀማኛ አገዛዝ ነጻ ማውጣት ነው ታዲያ እንዴት ሁለቱን ለያይቼ ማየት ይቻለኛል ? በፍጹም። ነገር ግን ሁለቱን የማበላልጥበት አጋጣሚ ግን አይኖርም ማለት ግን አልችልም። ለምሳሌ ከሁለቱ አንዳቸው ፓርቲያቸውን ወይንም ምክር ቤታቸውን እነሱ በግል ወይንም ከጉዋዶቻቸው ጋር በመሆን ስላቁዋቁዋሙ የዘላለም ሊቀመንበር የዘላለም ፕረዚዳንት ከሆኑ በዚህ ማበላለጤ በዚህ ስልጣን ላይ ሙጭጭ ያለውን መተቸት መንቀፌን አልተውም። ለዚህ ነው ጋዜጠኛ የፓርቲ አባል ከሆነ ነገር የሚበላሸው ለመተቸት ሙሉ ነጻነት ስለማይኖረው ነው ማለት ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ የምናጣው ነገር እንደሚኖር ማመን አለብን። ነገር ግን በፍጹም ምንም ነገር ማጣት የለብንም ካልን እዚያ ላይ ተሳስተናል።

እኔ እና መሰሎች ወያኔን ለመጣል በሚደረጉ የትግል እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተሳታፊ የመሆን ግዴታ አለብን። ይህንን ስል ግን በጎ ነው ብለን ያሰብነውን ነገር ግን የ እንቅስቃሴው ፊት አውራሪ የሆኑ ወገኖች ሲሳሳቱ እና አቅጣጫ ሲስቱ በዝምታ ማለፍ ትግሉን ከማደናቀፍ ተለይቶ አይታይም ስለዚህ መናገር እና ማለት የሚገባንን ልንል ስለሚገባን ነው ይህንን ጽሁፍ የምጽፈው እንጂ በማንም ቂም…በማንም ጥላቻ ስለሚኖረኝ እንዳልሆነ ልብ ሊባልልኝ ይገባል። የህነው ሆኖ ግን በአብዛኛው እንደሚታየው የገዢው ሃይል ለነጻ መገናኛ ብዙሃን መረጃ ሲጠየቅ ስለማይሰጥ ጋዜጠኛዎች ዘገባቸውን ሚዛናዊ ለማድረግ ስለሚቸገሩ ያለ ውድ ግዴታቸው የተቃዋሚውን ወይንም የአንድ ወገን መረጃ ብቻ ለማቅረብ የሚገደዱበት ቀዳዳ ሰፊ ነው። ስለዚህ በሌላ ወገን ያሉት እና ለነጻው ሚዲያ መልካም አመለካከት የሌላቸው የመንግስት ደጋፊዎችም ሆኑ ራሱ መራሹ ሃይል ነጻውን ሚዲያ ለማጣጣል አመቺ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል። ይህንን ሂደት ማስታረቅ የሚቻለው ታዲያ ያለ ስጋት እና ፍርሃት አንዳንዴም መተቸት የሚገባውን የመንግስትን ተቀናቃኝ ሃይል መተቸት እና ማየስ በሚቻልበት አጋጣሚ ያለወገንተንነት መናገር ማቅረብ ሲቻል ነው። ይህንን ግን በድፍረት ስናደርግ አንታይም። ለአብነት ያህል የአቶ ስዬ አብርሃን የተለያዩ ጊዜያቶች ንግግሮች ማንሳት ይቻላል። ለጊዜው የመነሻዬ ፈትለ ነገር ወይም ጭብጥ ይህ ባይሆንም አብነቱን ለመጠቆም ያህል ነው።

እንደምሳሌ አቶ ስዬ ከውጪው አለም በተለይ የሰሜን አሜሪካ ሃገሮች ውይይቶች ላይ አቶ ስዬ የመከላከያ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት በሃረርጌ በወያኔ በራሳቸው በአቶ ስዬ የስልጣን ዘመን የተቀናበረውን የጅምላ አሰቃቂ ግድያ ጉዳይ ሲጠየቁ ሰውየው ወደፊት በግህ የሚታይ ነው ይበሉ እንጂ ነጻ የሚዲያ ሰዎች ይህንን ጉዳይ በስፋት ያልሄድንበት ሂደት ይጠቀሳል። ይህ ለምን ሆነ ? አቶ ስዬ የተቃውሞውን ጎራ ስለተቀላቀሉ ይሆን ?…። ሌላም አለ አቶ ስዬ በወያኔ አገዛዝ ዙሪያ ዲስኩር  ሲያሰሙ ግልጽ በግልጽ…አግር በ እግር ስለወቅታዊ የሰባዊ መብት አያያዝ እና ዝርዝር ጉዳዮች አስተያየት እምብዛም አልሰጡም። የሲያትሉን የቪድዮ መልዕክት ማስታወስ በቂ ነው። ይህንንስ ታዲያ ልምን ይሆን ? ዘጋቢዎች ያልተጉዋዙበት። አቶ ስዬ ተቃዋሚ ነኝ ስላሉ ይሆን ?…። ይሄ መቅረት እና መወገዝ የሚገባው ጉዳይ ነው። አቶ ገብሩ አስራት እንደዛሬው ከህውሃት ሳይባረሩ የትግራይ ክልል አስተዳደር በነበሩበት ወቅት ወደክልሉ ነጻ ጋዜጣ እንዳይገባ አግደው የነበሩ ባለስልጣን ነበሩ ነገር ግን ይህም ጉዳይ አንድም ቀን ተነስቶባቸው አይውቅም ለምን ? የተቃውሞውን ጎራ ተቀላቅያለሁ ስላሉ ?…። ዛሬ ላይ ሆነን ትላንት ከትላንት በስቲያ ይፈራ በነበረው ስራት ውስጥ ያለፉ አንጋፋ ባለስልጣናትን በትያቄ ስናርበደብድ ነገር ግን ወደተቃውሞ ጎራ የመጡትን መፍራት እና ችላ ማለት በፍጹም አይገባንም።

ጋዜጠኛዎች ሌላው ትልቁ ጉዳይ ነገራችንን እና ጉዞዋችንን ሁሉ በአንድ አቅጣጫ ካላደረግን የያዝነውን ሁሉ እናጣለን በሚል ስሌት ውስጥ አናውል። እርግጠኛ ነኝ በርካታዎቹ በነጻ ሚዲያ ውስጥ ያለፋችሁ ጋዜጠኛዎች የማይገፋ ግንብ የገፋችሁ የመጨረሻውን የምስዋ ዕትነት ጽዋ የተጎነጫችሁ ናችሁ ስልዚህ ከፊሉ የወደደውን መውደድ ከፊሉ የጠላውን

እንደንፋስ አብሮ እየነፈሱ መጥላት ተገቢ አይመስለኝም። እርግጥ ነው የዘር ፖለቲካ የቱን ያህል እንዳናከሰን እንውቃለን። በዘር ምክንያት ብዙዎች ተጠርጣሪ እየሆኑ ለገዢው ቡድን የፕሮፓጋንዳ ማሙዋያ እየሆንን እንደሆነ እንገነዘባለን። አንዳንዴ አስተማሪዎች መሆን የሚገባን ተመልሰን ስንወርድ እየታዘብኩ ነው። አበበ ቶላ ከሰሞኑ በብሎጉ ላይ ያሰፈረውን ስመለከት በእውነት አዝኛለሁ። ያዘንኩት አበበ ቶላ ስለ ዳዊት በመጻፉ ሳይሆን የወያኔ ደጋፊ ከሆነው ፓልቶክ ሩም አዘጋጅ ከአባ መላ ጋር ቆይታ በማድረጉ መሆኑን አበበ መናገሩ ቅር አስኝቶኛል። እርግጥ ነው የዳዊት ወደዚያ መሄድ በመከፋቱ መሆኑን አበበ “ልውጋሽ ብሎ ይማርሽ” አይነት ሽንቆጣውን ሲሸነቁጥ እመለከታለሁ። የዳዊትን መከፋት አበበ ከልቡ ተመልክቶት ቢሆን ይህንን ባላለ። ነገሩ “እማን ላይ ተቀምጠሽ…” ይሆንብኛል። ማንም ይህንን ያስበው የማላምንበት እምነቴ እምነትህ ነው እየተባልኩ መገለል እየደረሰብኝ ነው የሚለው ዳዊት ከበደ አባ መላ አይደለም አባ ገዳ ጋር ቢሄድ ሊያስገርም አይገባም። እዛም ሄደ እዚያ ዋናው አቁዋሙን ዝንፍ አለማድረጉ ነው። እንደማሰበው የያዘው አቁዋም እየተፈረጅኩ ነው

ያለበት ነጥብ አግባብነት እይኖረው ይሆናል። ነገር ግን ዳዊት የደረሰበትን…የዳዊትን መከፋት በዳዊት መነጽር መመልከት ያስፈልጋል። ነገሮችንም ማጤን የግድ ይላል። እንጂማ በትግራይ ተወላጅነቱ የተወሰኑ ክፍሎች ዳዊትን ቢወቅጡት ሌሎችም ተደርበን “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ…”ልናደርገው አይገባንም።

ይሄ ብቻም አይደለም። አበበ ቶላ ከኬንያ ወደ እንግሊዝ መጥቶ በአጭር ቆይታ ተደላድሎ ኢሳትን ሲቀላቀል የአውራምባው ዳዊት ከበደ አሜሪካን ምድር ላይ ተቸግሮ አበሳውን መቁጠሩን መዘንጋት የልብንም። ዳዊት ለወራቶች ስራ አልነበረውም። ምንም ገቢም አልነበረውም። ነገር ግን ዳዊት ለምን ወደ ኢሳት ሚዲያ የምንወድለትን የጋዜጠኝነት ሞያውን ቱርፋት እንዲያቁዋድሰን አልተደረገም ? ወይንስ የግድ በቦታው ይፈለግ የነበረው ሳታየሪስት ነበረ ?…። እርግጥ ነው በሚዲያው ሙያዊ ግልጋሎት ተርታ እንድምንታዘበው የድል አጥቢያ አርበኛ ጋዜጠኛዎች እየበረከቱ ነው እሰየው ዋናው አገልግሎታቸው ታማኝነታቸው ግልጽነታቸው እና ገለልተኝነታቸው ነው።

ወደ አበበ እና ዳዊት ጉዳይ ስመለስ ታዲያ ዳዊትን ፖለቲከኛዎቹም ሆኑ ጋዜጠኛዎቹ የምታውቁት ከ አበበ ቶላ ቀደም ብሎ ነው እኔም አበበን የማውቀው ዳንኤል ወርቁ ቼበለው ፊልም ላይ ዲቪ የድረሰውን ሸዋፈራሁ ደሳለኝን ሲያበሽቀው ድራፍት ቀጂ ገጸ ባህሪይ ወክሎ ሲተውን ነው። ጎበዝ ነው ቀስ ብሎ በሳታየራዊ ጽሁፎቹ ሃበሻን ማስደመም ጀመረ። ለመታሰሩ ለመጋዙ እና ለምንገላታቱ ግን አበበ ከዳዊት አይቀድምም። እንዳውም ዳዊት ከበደ ተሸላሚ ጋዜጠኛ ሆኖ ወደ አሜሪካን ሃገር ሲመጣ ለጭብጨባ እና ለሙገሳ የተሰነዘሩ እጆች ከምኔው ታጥፈው ወደ ዳዊት መጠቁዋቆም እንደጀመሩ ስታዘብ ሃዘኔ የበረታ ሆኖዋል። እናስ ያኔ ዛሬ አይበለው እና ዳዊት አባ መላ ጋር ሲሄድ ዳዊትን በጥርጣሬ አይን የተመለከቱ ዜጎች ዳዊትን መጠራጠር ሳይጀምሩ በችግሩ ጊዜ የት ነበሩ ? አይደለም ሰባት ስምንት ወራት አንድ ቀን በሰው ሃገር ስንት መክራ እና ስቃይ አለው ? ሁላችንም እናውቃለን። ፖለቲከኛውም ጋዜጠኛውም አብሮ ማደሙ ያሳዝናል። ምናልባትም ይሄ ወደምፈልገው ያልዘመመን ከማሳደዴ በፊት እንዲሳደድ ማድረግ …ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው “ውጻዕ አይትበሎ ከምዝወጻዕ ግበሮ” እንደሚሉት የወያኔዎች አስተሳሰብ ወደመሆን የሚያደላ አኩሁዋን ካልሆነ በቀር ዳዊትን የመሰለ መስዋእትትነቱን ያሳየ ጋዜጠኛ መስመሩን ቢስት እንኩዋን በዚህ መልኩ አልንበረም አካሄዱ።

አበበም ነገሩ “ጌታዋን የተማመነች…” ያስመስልብሃል እንጂ አንተ መድረክ ኖሮህ ልጠይቅህ ያላልከው ጋዜጠኛ የራሱን በራሱ ሃሳቡን ከሚገልጽበት ባሻገር መድረክ ያልተሰጠው ጋዜጠኛ የትስ ሄዶ ሃሳቡን ቢያጋራ ምን ቁብ ይሰጣል ? በበኩሌ ላለው ነጻ ሚዲያ አክብሮትም ድጋፍም አለኝ። የመተቸት የመውቀስ ነጻነቴ ደግሞ የተጠበቀ ነው። ይህ እምነቴን መጻፌ ሌላ ስም ያሰጠኛል በሚል ስሌት ወደሁዋላ ግን አልልም። እኔ ብቻ አይደለሁም በስም መጥቀስ አይስፈልግም የባለቤቶቹን ፈቃድ እስካላገኘሁ ድረስ። ስለዚህ በርካታዎቹ ነጻ ጋዜጠኛዎች ስንወያይ ስነነጋገር የነበረነውን በአግልግሎታቸው የምንወዳቸውን ፈጽሞ እድሜያቸውን የብረት ምሶሶ እንዲሆንልን የምንፈልጋቸው ሚዲያዎች እንዲጠናከሩ አስተያየታችሁን ስጡ። ህዝቡ ከ እናንተ ብዙ ይጠብቃል። በስተመጨረሻም …የሆነው ሆኖ መረጃውን በይፋ ባላገኘውም ዳዊትም በበኩሉ “ብዙዎቹ በውጪ የሚገኙ ጋዜጠኛዎች የተቃዋሚዎች ደጋፊዎች ናቸው” በማለት የጋለ ወቀሳ ሰንዝሮዋል የሚል ነገር ወደ እኔ ቢመጣም የነገሩን እውነትነት ስላላረጋጋጥኩ ዳዊትን በዚህ በኩል መተቸት አልቻልኩም። ነገር ግን ዳዊት ይህንን ብሎ ከሆነ ከላይ በሱ ላይ ያልኩት ሁሉ እንዳለ ሆነ ግን ተናገረ በተባለው ነገር ከማዘን ውጪ የምለው ባይኖርም ግን ብዙዎቻችን ሳንሆን ጥቂቶች ሊሆኑ ይችላሉ በሚለው እኔም እስማማለሁ። ምክንያቱም በደምሳሳው ሁሉንም መፈረጅ ተገቢ ባለመሆኑ። አበቃሁ ሰላም።__

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on February 10, 2013. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.

One Response to ኦ ጋዜጠኞች አሁንስ ለህሊናችሁ፡ ፖለቲከኞችም!! (ክፍል ሁለት – በዳንኤል ገዛኸኝ)

  1. ትዝበት

    February 16, 2013 at 10:55 AM

    ጋዜጠኛ ዳኒኤል ገዛኸኝ፦ ሰላምታዬን ላስቀድምና፣ “ሲዋን” ከአነበብኳት አንዱ ነኝ፣ በሲዋን መጽሃፍ የአንባቢን ልብ አንጠልጥለህ፣ የኢትዮጵያን ልጆች መከራና ስቃይ እንዲሁም አንተም የደረሰብህን እንግልት እያዋዛህ በሚጣፍጥ የድራማ ስነ ጽሁፍ በሚመስል የሰውን ልጅ ስቃይ፣እልቂት፣ መከራ፣ሞት፣….እየጓጓንና በእንባ እየተራጨን አስነብበህን ስታበቃ፣ “ፍየል ከመድረሷ….”እንዲሉ ለዚህ ተሰፋው ለጨለመበት ህዝብ ብልጭ ድርግም እያለች ትንሽ የብርሃን ጭላንጭል የምታሳየውና ስሜቱን እንዲተነፍስ የሚያደርገው “ኢሳት” መሆኑ እየታወቀ ከመድረስህ ትችት ማብዛቱ ዓለማህ ለምን ይሆን? እነዛ እየተሰቃዩ ብለህ በመጽሃፍህ የተረክላቸው የዓረብ ሃገር ስቃያቸቸውን ማን ነው የሚጋራና ከእለት እለት ብሲታቸውን የሚያሰማላቸው? አንተና የኢትዮጵያ መንግስት ናችሁን? ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እንደሚታሰር ተነግሮት “በቦሌ” ያለምንም ችግርና ስቃይ አሜሪካ ተንደላቆ የገባ ሰው እኮ ነው! እንዳንተ እና እንደሌሎች ጓደኞችህ የደህንነት ችግር ነህ ተብሎ የሚበላው፣የሚለብሰው፣ የሚጠጣው፣….አጥቶ በበርሃ መንገድ ተሰቃይቶ አይደለም አሜሪካ የደረሰው!! ደግሞስ አሜሪካ በከፈተው ብሎግ ይጽፈውና ቃለ-መጠይቆችን በቪዲዮ ተከታትለሃል? ጥያቄዎቹ የማያረኩ!ወላዋይ!…..የነበሩና የሚያናድዱ ነበሩ!! አቋሙማ ሊለይ ይገባዋል!! ፍጹም ጽናት የሌለው መሆኑን ባደረገው የፓል-ቶክ ንግግሩ አዳምጠነዋል!! እንኳንም ብዙ ሰው ሳያሳስት አቋሙ ታወቀ!! በጊዜያዊ ኩርፊያ ምክንያት እንደገና እታሰር ይሆናል ብሎ በፍርሃት ሃገር ጥሉ የሸሸ ሁሉ ፖለቲከኛ ነው ማለት አይደለም። ሲመቸውና ሞቅ ያለ ጥቅም ሲያገኝ መገልበጡ የተለመደ ነው። ስለዚህ “ኢሳትን” ገና ከውጥኑ የምትተቹ ሁሉ ለወያኔ አጋዦች፣ ለህዝብ ጸር መሆናችሁን ተረድታችሁ ወደ ህሊናችሁ ተመለሱ!! ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር!!