እኛስ ለነጻነት ምን እንሰራለን? (ከዶ/ር አክሎግ ቢራራ)

በቁጥር ስድስት ለማስረዳት የሞከርኩት፤ የህወሓትን ተደጋጋሚ መራራ በደል በሚገባ ለማሳየት፤ ስርአቱ በቀጥታ፤ ጠባብ ዘረኝነትን፤ የገዥ ፓርቲን፤ መንግስትንና ጠቅላላ የመንግስት አስተዳደርን ከአንድ ላይ ቆላልፎ፤ (Total merger of ethnicity, political party, government and state) ወገናዊና አድሏዊ በሆነ መንገድ፤ የበላይነት ፍጹምነት መቀዳጀቱን ነው።በመሆኑም፤ ለይስሙላ ዳኛና ፍርድ ቤት፤ ህገ መንግስትና አስተዳደር አለ ቢባልም፤ ግለሰቦችና ተቋሞች የሚያስፈጽሙት የበላይ የፖለቲካ ውሳኔን ብቻ ነው። ለዚህ የቅርብ ማስረጃው፤ በአንዷለም አራጌና ሌሎች ሃያ ሁለት ሰላማዊ፤ አገር ወዳድ፤ ለነጻነትና፤ ለህዝብ እኩልነት፤ ታጋይ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን ላይ ሰኔ ሃያ ሁለት፤ ሁለት ሽህ አራት አመተምህረት፤ የተደረገው አሰቃቂ የእድሜ ልክ እስራት ብያኔ ነው። ታዛቢወች ገና ይህ ፍርድ ከመሰጠቱ አስቀድመው የፖለቲካ ውሳኔ እንዳይሆን አሳሰበው ነበር። ለማስመሰል ብቻ፤ ፍርድ ቤት ቀረቡ እንጂ፤ የተባለውና የተፈራው እንደተፈጸመ የጠቆመው፤ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ፤ የእነዚህን ግፋቸው፤ በደላቸው፤ ወንጀላቸው፤ ለስብአዊ መብትና የሰው ክብር፤ ለነጻነትና እኩልነት መቆም እንጂ፤ ሌላ ወንጀል እንዳልሰሩ፤ በማንም እንዳልተገዙ፤ አሽባሪ እንዳልነበሩ፤ እያወቁ ለተዘጋጀላቸው የማይቅር፤ የፖለቲካ ውሳኔ አጋልጠዋቸው ነበር። ከፍርዱ በኋላ፤ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የሰሰብአዊ መብቶች ድርጂትና ሌሎች ያስታወቁት ተቃውሞ ህወሓት ለእውነተኛ ፍርድ፤ ለህግ የበላይነት፤ ለግለሰብ መብትና ነጻነት እንዳልቆመ ነው። የጸረ ሽብርትኝነት ህግ ያወጣው ማንንም ተቃዋሚ ለማሰር፤ ለማሳደድ፤ ዘመድ አዝማዱን መድረሻ ለማሳጣት፤ ፍርሃት ፍጹም እንዲሆን ለማድረግ ነው፡፡ በተዳጋጋሚ የምናየውም ህወሓት የፖለቲካ ውሳኔ ካደረገ በኋላ፤ ህጋዊ ለማስመሰል ብቻ፤ ግለሰቦችን ለፍርድ ያቀርባል። ምስክሮችን ይጠቁማል፤ ያዘጋጃል፤ ውሸት ተናገሩ ይላል። ያዘዘው ከስራ ላይ ይውላል። እንደዚህ ባለ ቅድመ ሁኔታ፤ ያልተዛባ ፍርድ ሊኖር አይችልም።

ዳኛው፤ የስርአቱ አገልጋይ የሆኑት አቶ እንደሻው አዳነ የተሰጣቸውን የፖለቲካ ትዛዝ ከስራ ላይ ማዋል እንጂ የህግን የበላይነት ይዘው ለእውነተኛ፤ ለሚዛናዊ ፍርድ፤ ለፍትህ መቆም አልነበረም። ቢቆሙ ኖሮ ያስደንቅ ነበር። የተመለመሉበት፤ የተማሩበት፤ የሚኖሩበት፤የገቢያቸውና ድጎማው ይዘት፤ የወደፊት እድላቸው ሁኔታ በሙሉ የሚወሰነው ለህወሓት ባላቸው ታማኝነት እንጂ፤ በሕዝብ ያለ አድሎ አገልጋይነት፤ በህግ፡ የበላይነት፤ በህሊና ንጹህነት አይደለም። ስለሆነም፤ የተቋምና ግልሰቦች ነጻነት በሌለበት አገር ፍትሀ ይኖራል ብሎ ራስን መደለል ተጨማሪ ማስረጃ አይሻም። ደጋግመን አይተነዋል። ወደፊትም ይሆናል። የሚሻለውስ፤ ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ ዘላቂነት ባለው መልክ ለፍትህ፤ ለእኩልነት፤ ለህግ የበላይነት አብሮ መነሳት ብቻ ነው።

ፈራጁ ሳይሆን የተፈረደበት ታሪክ ሰራ፤

አብሮ ለመስራት፤ አቶ አንዷለም አራጌ ለታሪክ ያስመዘገበውን ማየቱና እኛስ ምን እንሰራለን ብሎ መጠየቁ ጠቃሚ ነው። ቢያንስ ህሊናን ይቀሰቅሳል፡፡ “እኔስ ማን ነኝ? ምን እሰራለሁ? ነግ በኔ አይደለም? እስከ መቸ ነው ለልዩነት፤ ለቡድን፤ ለግለሰብነት፤ ለጉራ፤ የምገዛው” ብለን በያለንበት ሁሉ ብንነሳ የፍርድ ጨለማ ለሆነችው አገራችን ተስፋ ልንሰጥ እንችላለን። በግፍ ለታሰሩ፤ ለተሰደዱ፤ ለሚሰደዱ፤ ለሚታገሉ፤ ወገኖቻችን አርአያ ልንሆን እንችላለን። የፍርድ መጓደልን በማየት፤ እኛ ይህን በደል ስንቀበል አንኖርም ለሚለው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር አገር ውስጥ በሆዱ ለሸፈተ ወገን ሁሉ፤ በተለይ ተቆርቋሪ ለሆነው ወጣት ትውልድ ያስቆጣል:: የተቃዋሚውን ቁጥር ያበዛል እንጂ አይቀንስም። ህወሓት ቢወድም ባይወድም ከአምሳ በመቶ በላይ የሆነው፤ ወጣቱ ትውልድ ለነጻነት፤ ለፍትህ፤ለእኩልነት፤ ለራስ መቻል፤ ለህግ የበላይነት፤ መታገሉ እያደገ፤ እየሰፋ ይሄዳል። አቶ አንዷለም የዚህ አዲስ ትውልድ አባልና ድምጽ ነው። በእስር ቤት ህይወቱን እንዲያሳልፍ መደረጉ፤ ያቀረበልንን ሃሳብ አይቀብረውም። እንዲያውም፤ ህያው ያደርገዋል። ህውሓት፤ ሰውን ማሰር፤ መግደል፤ ማሳደድ ይችላል። የሃሳቡን ስርጭት ግን ማንም ሃይል ሊያግደው አይችልም። አርቆ ላሰበው ከጠበንጃ ሃይል ይልቅ ለገንቢ ለውጥ፤ ለሃሳብ ጥራት፤ ለአስተዋይነት፤ የሚያበረታታ ድጋፍና አቅጣጫ ለመስጠት፤ ለመተባበር፤ ታግሎ ሌላውን ለማታገል መቆም አሸናፊ መሆኑ አይቅርም። የቱኒሲያ፤ የሊቢያ፤ የየመን፤ የግብጽና አሁን የሶሪያ ህዝቦች የሚያደርጉት ትግል ከዚህ መንፈስ የተነሳ ነው። ለመነሳት የቀሰቀሷቸው ነባር ሁኔታወች ከኢትዮጵያ ብዙም አይለዩም። በእነዚህ አገሮች፤ በተለያየ ወቅት ግለሰቦች የተናገሩትና የሚናገሩት፤ የታሰሩትና የተገደሉት ከኢትዮጵያ ታጋዮች አይለይም። ባናውቅበት ነው እንጂ፤ ለፍትህ-ርትእ፤ ለነጻነት፤ ለዲሞክራሳዊ ለውጥ በብዙ መቶ ሽህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን ሰጥተዋል፤ ታስረዋል፤ ተሰደዋል።

ኢትዮጵያዊ አመራር ከአስኳል ሲቀጭ፤

“እኔ ለራሴ፤ ለልጆቸና ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ ዲሞክራሲና ነጻነት እነደሚገባን በማወቅ አቅሜ በፈቀደው መጠን ታግያለሁ። ይህን በማድረጌ በማንም ላይ በክፋት አልተነሳሁም፤ ይህን በማድረጌ ህግ ጥሸ አላውቅም፤ ይህን በማድረጌ በድሃዋ አገሬ ጥቅም ላይ አልተነሳሁም፤ ይህን በማድረጌ ፈጣሪየን፤ የኢትዮጵያን ሕዝብም ሆነ፤ ህሊናየን፤ የሚያሳዝን አንዳች ነገር ፈጽሚያለሁ ብየ አላምንም። …እኔን፤ ከዚህ ያቆመኝ፤ የነጻነት ናፍቆት ነው” ብሎ አንዷለም ለአለም ህዝብ ያቀርበው፤ መላው የሃገራችን ህዝብ የሚጋራው፤ ተከታታይ ትውልድ ሲጠቅሰው የሚኖረው፤ የኔልሰን ማንዴላ፤ የማርቲን ሉዘር ኪንግ አባባል የሚሆነው። ፈራጆቹ የህወሓት ገዦች፤ እንደሱ አያስቡም። ለማሰብም ፈቃደኛ አይደሉም። ለእነርሱ፤ ለፍትህ፤ ለነጻነት፤ ለሃገር አንድነት፤ ለመላው ህዝብ የተሻሻለ ኑሮ የመኖር መብት የቆመ ሁሉ፤ “ጠላት” ነው። ክፋት፤ ምቀኝነት፤ ውሸት፤ ዘራፊነት፤ ደማቸው የሆነ፤ በድሃ አገር የራሳቸውን ጥቅም ከህዝብ ጥቅም በላይ አሳዳጆች ናቸው ለማለት የሚያቨቃ ብዙ ማስረጃ አለ።

ሌላው ቀርቶ፤ ቁመንለታል ለሚሉት ነጻነቱንና ክብሩን ላጣ የትግራይ ህብረተሰብ የማይረሳ በደል እንዲሸከም አድርገውታል። በስሙ ጥቂት ግለሰቦች፤ ቤተሰቦቻቸው፤ ምርጥና ታማኝ ወዳጆቻቸው ሃቭት እያካበቱ፤ አድሏዊ በሆነ መንገድ ከይሉንታ በላይ በብዙ ቢሊየን ብር የሚገመት መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ ለትግራይ ህዝብ አለንልህ እያሉ፤ ከሌላው ህብረተስብ ጋር በሰላም፤ በፍቅር፤ በመከባበር፤ በመተሳሰብ፤ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል እንዲጠላ እያደረጉት ነው። እኛ ለሃገርና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የቆምን ሁሉ፤ በትግራይ ህብረተሰብ የሚደረገውን ሽንገላ ለተንኮል እንጂ ለዘላቂ እድገት አለመሆኑን መገንዝብ አለብን። በአድሎ የተገነባ እድገት ይቆይ እንጂ፤ ማጠያየቁ እንደማይቅር ከሌሎች አገሮች ልምድ አይተናል፤ እያየን ነው። የትግራይ ተቃዋሚወችም፤ ይህን ህዝብ ከህዝብ የሚለያይ ዘዴ ያለመቆጠብ ማውገዝ፤ ከሌሎች ኢትይጵያዊያን እህቶችና ወንድምቻቸው ጋር እጅ ለእጂ ተያይዘው መቃወም ታሪካዊ ግዴታቸው ነው። የእኛ ብሄር፤ የኔ ብሄር፤ የኔ ሃይማኖት፤ የኔ ቡድን ወዘተ፤ እያልን ከቆየን የምንደግፈው የህወሓትን ስርአት መሆኑ አያጠራጥርም። መነሳት ያለብን፤ ኢትዮጵያና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ካለበት ጭቆና፤ ካለበት አደጋ፤ ካለበት ዝርፊያ ነጻ መውጣት የሁላችንም ሃላፊነት ብለን ነው። ይህ አዲስ፤ ልሁሉም የሚቨጅ፤ ብሩህ ምእራፍ ይከፍትልናል።

የህወሓት የበላይ አዛዦች የሚጠቀሙበት ዘዴ ከመለያየት የባሰ ነው። በተለይ አማራውን “ጨቋኝ፤ ነፍጠኛ፤ ብዝብዥ”እያሉ ማሳደድ፤ መግደል፤ ካለበት ማስወጣት፤ ሃብት/ጥሪት/ትምህርት/ጤና/ስራ እንዳይኖረው ማድረግ። ከዚያም፤ አፋሩን፤ ኦሮሞውን፤ ሶማሌውን፤ ጉራጌውን፤ አኟዋኩን፤ ወዘተ፤ በየተራ፤ ማሳደድ፤ ባልሰራው ወንጀል በሽብርተኝነት መክሰስ፤ መወንጀልና ማሰር ነው። የፖለቲካ ስልጣንን ትተን በኢኮኖሚው ያለውን ሁኔታ ስናይ፤ የዚህ አሰቃቂ አገዛዝ ተጠቃሚወች፤ ምርጥና ታማኝ የሆኑ ጥቂት ግለሰቦች፤ ቤተሰቦች፤ ለዚህ ሆነ ተብሎ የተቋቋሙ ድርጂቶች ናቸው። በኢኰኖሚው በኩል ታምራዊ እድገት አለ ተብሎ ህዝብ “ዳቦውስ የታል” በሚባልባት ኢትዮጵያ፤ የውሸት ምስክር ፈልጎ ዋሽተህ ተናገር ማለት ቀላል ነው። ከፍርሃቱ ሌላ፤ ድሃው ሰው በልቶ ማደር ስላለበት በትንሽ ገንዝብ ይገዛል። ውሸት፤ ሙስና፤ ስርቆት በጦፈበት፤ ህግ በሌለበት አገር የፍርድ ችሎት በአግባቡ ይካሄዳል ብሎ ለአለም ህዝብ መናገር ለህሊና ይቀፋል። በአጠቃላይ ሲታይ ግን ምንም ሊያስገርመን አይችልም። በፖለቲካ መነጽር አይቶ፤ የውሽት ምስክር ጠርቶ፤ የፖለቲካ ፍርድ መስጠት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ እሴት ነው። እድገት አለ እያሉ በተራ ህዝብ ላይ መቀለድ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስልት ነው። ስለዚህ ጎጅ ስርአት ከዚህ በፊት ብዙ ማስረጃወች አቅርቢያለሁ። ለማጠናከር አንድ ምሳሌ እሰጣለሁ።

የህወሓት የበላይ መሪወች ውሸትን፤ ትውልድ ጎጅ ተግባርን፤ ታሪክ መከለስን፤ ታላላቅ የኢትዮጵያ መሪወች ማዋረድን፤ ሙስናን፤ ስርቆትን፤ ግለስብና ብሄር ማዋረድን፤ እንደ እውቅት፤ እንደ ብልጠት፤ እንደ ዘመናዊ አመራር ስልት ያዩታል። የህሊና ገደብ የላቸውም። ከባህላችን የቀሰሙት፤ “ህሊናስ ለምን ይጠቅማል፤ ሰውስ ምን ይላል፤ ትዝብትስ፤ ታሪክስ፤ እውነትስ ምን ይመዘግባል” የሚሉ እሴቶች ለነሱ፤ ዋጋ የላቸውም፤ ባዶ ናቸው። በተደጋጋሚ፤ አስድናቂ የእርሻ ምርት አለ ብሎ ህወሓት አለምን ለማሳሳት የሚያደርገውን ውሸት፤ የአለም ባንክ ባለሙያወች “ታምራዊ የእርሻ እድገት የለም” ብለው ያስቀመጡትን፤ ጭብጥ ለማድረግ ከኢትዮጵያ የሚመጡ ግለሰቦችን ተራ በተራ አነጋገገርኩ። እነሱ፡ ከችግሩ ጋር አብረው ስለሚኖሩ የሚናገሩት እውነት ነው። በተጨማሪም፤ ማሰረጃወችን ሁሉ፤ እንደገና አየሁ። በአማራ ክልል፤ የህወሓት ካድሬወች የበላይ ትእዛዝ በማክበር አንድ ድሃና አፈ ጮሌ ወጣት ገበሬ ይመርጣሉ። አምስት መቶ ብር ጉርሻ ይሰጠዋል። ለጋዜጠኞች፤ ምንና አንዴት እንደሚናገር ያዘጋጁታል፡፡ መሬቱ የበሬ ግንባር የምታህል፤ ማደሪያ ቤቱ የጭቃ፤ ለስሙ መቶ ብር የሌለው፤ ጎተራ ቀርቶ ከእጅ ወደ አፍ የሚኖር ወጣት፤ አፈጮሌ ገበሬ፤ ወደ አዲስ አበባ ሄዶ “ ታታሪ፤ አዲስ ሃብታም ገበሬ፤ እህል አቅራቢ፤ ሚሊየነር” ተብሎ በጠቅላይ ሚንስትሩ ይሸለማል፡፡ ከተነገረው በላይ እንዴት ሃብታም እንደሆነ፤ መንግስት እንዴት እንደረዳው፤ የቤተሰቡ ህይወት እንዴት እንደተለወጠ፤ ለጋዜጠኞች ሁሉ ያስረዳል። ለማስተባበል የሚችል አማራጭ ስለሌለ የህወሓት ማስረጃ ሰጭ፤ እንደ ህያው ምስክር ቀረበ። ተመሳሳይ የሆኑ ምስክሮች ከልዩ፤ ልዩ ክልሎች ተመርጠው የዚህ አይነት “ተአምራዊ የእርሻ ውጤት” ዘገቫ አቅርበዋል።

የጎንደሩ ወጣት ገበሬ፤ እንደገና ትንሽ ድጎማ ተሰጥቶት፤ ወደ መጣበት ይመለሳል። ታዛቢወች፡ ለምን ዋሸህ፤ “የንብ ቀፎወች ከየት አምጥተህ አለኝ አልክ” እያሉ ጠየቁት። ሚሽቱና ልጆቹ፤ “ሚሊዮን ብር ደብቀህ ካስቀመጥክ አሁን ስጠን” ሲሉት “አይኑ ፍጥጥ አለ” ይባላል። ወጣቱን ገበሬ ያሳፈረው፤ በመጭው የእርሻ ወቅት (farming cycle) የሚዘራው አጥቶ ወደ አንድ ዘመዱ ሂዶ “እባክህ፤ የምዘራው ስጠኝ፤ ወይንም አበድረኝ” ማለቱ ነው። የገጠር ሚሊየኔሮች ታሪክ ይህን ይመስላል። አንድ የህወሓት ደጋፊ ስለዚህ እመርታዊ የገጠር እድገት ከእኔ ጋር በ ጀርመን ድምጽ ሲከራከሩ “የገጠሩ ህዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ እድገትና የኑሮ መሻሻል ተጎንጽፏል” ያሉት ትዝ ይለኛል። እንደዚህ ያለ እድገት ካለ “ኢትዮጵያ ለምን የምግብ ጥገኛ ሆነች፤ ህንዶችን፤ ቻይኒሶችን፤ ሳውዲወችን ጋብዞ ለም መሬትና ወንዝ መስጠት ለምን አስፈለገ? ቢል ጌትስ ‘የኢትዮጵያ ሕዝብ በተደጋጋሚ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው ተቀዳሚ አገር ነው’ ብለው ለምን ተናገሩ?” ብየ ስጠይቃቸው አጥጋቢ መልስ ለመስጠት አልቻሉም። የደመደሙት ግን “መሪወችን በመጥላት እድገቱን መካድ አይቻልም” ነው። ፖሊሲው ግድፈት ካለበት የማጋለጥ ሃላፊነት እንዳለብን ሊቀበሉ አልቻሉም። የህወሓት ባለስልጣኖች፤ ራሳቸው ዋሽተው ድሃውንም በመደጎም እንዲዋሽ ያስገድዱታል።ለህሊናው እንዳይገዛ፤ ይበክሉታል። ለሃፍረት ይዳርጉታል። ምንም ገንዘብ የሌለው ሰው ዋሽቶ ራሱንና ቤተሰቡን መመግብ የተለመደ የሆነው ለዚህ ነው። ሌላም ህይወት አዳሽ አማራጭ የለም።ፍርዱ፤ በድሃው ሳይሆን፤ አውቅልሃለሁ በሚለው የህወሓት አመራር፤ በተለይ፤ በከፍተኛ ባለስልጣኖች ላይ ነው። አመራሩ መዋሽት ባህሉ ከሆነ፤ መላው ህብረተሰብ ይበከላል፤ ወጣቱ ትውልድ አርአያ አይኖረውም።

ስለ አመራር ድክመት፤ ውርደት፤ የማላልፈው ሌላ ምሳሌ አለ። በአገራችን ሌብነትና ሙስና ጡፏል። ግድያ ጡፏል። መሰደድ ጡፋል። ወጣት ሴቶችን እንደ እቃ ወደ አረብ አገሮች፤ በተለይም፤ ወደ ሳውዲ አራቢያ መላክ ጡፏል። በቅርቡ ከአዲስ አበባ የመጡ አዛውንትና ባለቤታቸው ቦሌ ያዩትን ኢንዲህ ብለዋል። “የምንሰማው ብዙ ወጣት ሴቶች ወደ አረብ አገሮች እንደሚላኩ ነበር። ቁጭ ብለው አውሮፕላን ይጠብቁ የነበሩት ስላስገረመኝ፤ አንድ ወዻጀን የት ነው የሚሄዱ፤ ስንት ናቸው አልኩት። በቀን ቢያንስ ሶስት አውሮፕላን ጭኖ ይሄዳል። ቢያንስ ሰቫት መቶ፤ ብዙ ጊዜ አንድ ሽህ ብሎ ነገረኛ አሉ።” ከሰላሳ እስከ ሰላሳ ስድስት ሽህ የሚሆኑ ወጣት ሴቶች፤ ህወሓት ፈቃድ በሰጣቸው ድርጂቶች አማካይነት እንደ ሸቀጥ ይላካሉ ማለት ነው። ታምራዊ እድገት ካለ የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች፤ የትውልድ ተኪወች፤ የወደፊት እናቶች፤ አስተማሪወች፤ ሃኪሞች ወዘተ እንዴት እነደ ተራ ሸቀጥ ለውጭ ምንዛሬ ተብሎ ይላካሉ? እድገታዊው መንግስት ለምን በሃገራቸው ሌሎች አማራጮች አያቀርብም፤ አያመቻችም፤ሁኔታውን አይፈጥርም? ለመሆኑ፤ እየተመረጡ የሚላኩት ከየት ነው? ለዚህም፤ ከህወሓት እውነተኛ መልስ አናገኝም።

ዛሬ፤ መዋሽት ዕውነት ሁኗል። ስርቆትና ሙስና የኢኮኖሚ አስተዳደር ብልሽት መጸብራቅ ነው። የማንም አገር መሪ ለመናገር ቀርቶ የማያስበውን፤ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ደጋግመው ብለውታል። ስለስርቆት መስፋፋትና ስለ መንግስት ሃላፊነት ሲጠየቁ የመለሱት አንድ አስደናቅና አሳፋሪ፤ ማስረጃ ነው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ “መስረቅ ጀግንነት ነው፤ ክፉው መያዝ ነው” ብለው የተናገሩት የሃያ አንድ አመታት ገዥ ምን ማለታቸው ነው ብለን እንጠይቅ? መልሳቸው ከሚያስተዳድሩት ስርአት ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ነው። የምርጫ ዘጠና ሰባትን የህዝብ ድምጽ በአመጽ ሲሰርዙ ምርጫን “መስረቅ” ትክክል መሆኑን አስምረውበታል። “ጀግንነት” መሆኑ ነው። ህወሓት ባለፈው ምርጫ “መቶ በመቶ አሸነፍኩ” ሲል ጀግንነትን ማሳየቱ ነው። ብዙ ሽህ ቶን ቡና ተሰርቆ ሲጠፋ እያዩ አንዳላዩ ማለፍ የሰረቁት ደፋርና “ጀግኖች” መሆናቸውን፤ ከተጠቃሚወች መካከል የህወሓትና የመንግስት ተባባሪውች “ጀግኖች” እንዳሉበት አመልካች ነው። በአመት ቢያንስ ከሶስት ቢሊየን ዶላር በላይ ከሃገር የሚወጣውን ገንዘብ የሚያሸሹ፤ ደፋር፤ አይን አውጣ፤ “ጀግኖች” ናቸው ማለት ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ ስርቆትን እንደ ጀግንነት ካዩት ህወሓትና ደጋፊወቹ ሁሉ፤ ዘረፋን፤ ማሰርን፤ መግደልን፤ ማሳደድን፤ ፍርሃት መፍጠርን፤ እየመረጡ ዘር ማጥፋትን፤ እንደ ጀግንነት ያዩታል ማለት ነው። አንዱ ባህሪይ ከሌላው ሊለይ አይችልም። መዝረፍ ሆነ፤ ዘርፎ ለዘራፊ መዳረግ ጀግንነት ነው የሚል ከገዡ አለቆች ቁንጮ የመጣ ስርአት በይፋ ክሌሎች አገሮች የበለጠ፤ የሚሰራው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። በኢትዮጵያ ዛሬ መስረቅ፤ የውሸት ምስክር ጠርቶ በውሸት ክስ ማሰር፤ ሙስና፤ ገንዘብ ማሸሽ “ጀግንነት” ነው ማለት ነው። ስልጣኑ ከፍተኛ የሆነ ግለሰብ ወይንም ቤተሰብ ሌባ በምንም ሊያዝ አይችልም። ህጉ አይመለከተውም (Total immunity):: ቢያዝም ባይያዝም፤ ሰው ቢያየውም፤ ባያየው፤ ስርአቱን ተጠቅሞ የሰረቀ “ጀግና” ነው ማለት ነው። ስለሆነም፤ የስርአቱ አመራርና ጠቅላላው ስርአት፤ የሞራል ውድቅት (morally decadent) አለበት ማለት ነው። የሞራል ውድቅት በሚያሳይ ስርአት ፍርድ ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም፡፡ እድገት ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም። ማንም ስርአቱን የሚቃወም ግለሰብ በውሸት ተከሶ፤ በውሸት ምስክር፤ በውሸተኛ ዳኛ፤ የሚፈረድበት ለዚህ ነው።

አቶ አንዷለም እንዲህ ብሏል። “ከሳሾች እንድጠጣው የሚፈልጉትን የግፍ ጽዋ በጸጋ ከመጠጣት ውጭ ባልፈጸምኩት ወንጀል ማቅለያ የመጠየቅን አማራጭ ህሊናየ ስላልተወልኝ (ስላልፈቀደ) አዝናለሁ።”ይህ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ባልፈጸመው ወንጀል ተከሶ፤ የእስራት ዘመንህ እንዲቀነስ ከፈለግህ “ወንጀል ፈጽሚያለሁ፤ የመንግስትን ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብለህ ለምን፤ ተማጸን ብሎ ያስገደደው ስርአት ሁል ጊዜ የሚፈልገው እራስን ዝቅ አድርጎ/አዋርዶ፤ የመለስ ዜናዊይን ፍጹማዊነት፤ የበላይነት መቀበልን ነው። የሚለየው ይህ ነው። አንዷለም አራጌ እራሱን፤ ቤተሰቡን፤ አገሩን፤ ባህሉን አላዋረደም። ለጥቅም ሲል ህሊናውን፤ እምነቱን አልቸረቸረም።“አማራጩን” አልቀበልም ብሏል። ለሃገር፤ ለወገን፤ ለእውነት፤ ለታሪክ፤ ለፍትህ፤ ለነጻነት የቆመ ግለሰብና መሪ የሚያሳየው እሴት ይህን ይመስላል። ብንቀበልም፤ ባንቀበልም፤ ኢትዮጵያና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚያስፈልጉት፤ የሚፈልጉት ጠባብ ብሄርተኛ ድርጂትና አመራር ሳይሆን፤ ሆደ-ሰፊ፤ ሁለ-አቀፍ፤ እውነተኛ ዲሞክራሳዊ፤ ብቃት ያለው ኢትዮጵያዊ ድርጂትና ኢትዮጵያዊ አመራር ነው። መንግስቱ ሃይለማሪያምን ተክቶ፤ መለስ ዜናዊን፤ እሳቸውን ተክቶ ሌላ ትእቢተኛ፤ ወገኛ፤ አምባ ገነን አመራር ሊሆን አይችልም። አንዷለም አራጌ፤ እስክንድር ነጋና ሌሎች የሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወጣት፤ ብቃት፤ ተስፋ ሰጭ ፤ እምቅ መሪወች (a new generation of Ethiopian leaders with potential) የሚታሰሩት፤ የሚሳደዱት፤ በሌሎበትም ጭምር “በቃኝና የሞት ፍርድ” የሚፈረድባቸው አዲስ እሴት፤ አዲስ አስተሳሰብ፤ አዲስ የፖሊሲ አቅጣጫ (ጸረ ዘረኝነት፤ ጸረ አምባገነናዊነት) ይዘው ሰለተነሱ ነው።

የኢትዮጵያዊ ድርጂትና አመራር ቁልፍነት፤

የኔ ትውልድ የአገራዊ ድርጅትና ጥቨቫዊ አመራር (Responsive country wide political organization and wise and far-sighted leadership) አስፈላጊነትን ሁኔታወች ካለፉ በኋላ በከፊልም ቢሆን፤ እያወቀ የመጣ ይመስለኛል። ችግሩ ብዙ ቢሆንም፤ ያለ ኢትዮጵያዊ ድርጂት፤ ያለ አዋቂ፤ ጥበበኛና ሁሉን አገልጋይ አመራር ለውጥ ለማምጣት አይቻልም። ያልፈታነው፤ እኛ ሃሁ የቆጠርን ኢትዮጵያዊያን አመራርን ያየነው፤ የምናየው “እኔ፤ ለኔ፤ ለቡድኔ፤ ለፓርቲየ፤ ለብሄሬ፤ ለመንደሬ” ከሚል መነጸር ነበር፤ አሁንም የግለኝነት ተገዦች ነን ለማለት ይቻላል። ይህ ዘመን ያለፈበት የአመራር ዘይቤ፤ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን በምንም አይሰራም። በተልይ፡ ህወሓት ባመጣው “የከፋፍለህ ግዛው” ስርአት፤ ቡድናዊነት የትም አያደርሰንም። የህዝብ ጥያቄን ሊመልስ አይችልም። በብዛት እየጨመረ የሄደውን ወጣት ትውልድ ፍላጎት፤ ምኞት፤ ተስፋ አያሟላም። ከሰላ ሽህ በላይ በአመት አገራቸውን ለቀው በሳውዲ አረቢያ ክብራቸው ለሚገፈፈው ወጣት እህቶቻችን ሰቆቃ መልስ አይሰጥም። መልስ ሊሰጥ የሚችለው አንዷለም፤ እስክንድርና ሌሎች ወጣት የሃሳብ መሪወች የሚሉትና የቆሙበት፤ የታሰሩበት ነው። ማለትም፤ ከአገራዊ ድርጂትና ጥቨቫዊ አመራር የሚፈለገው፤ ለአንድ አገር፤ ለአንድ ህዝብ ሉአላዊነት፤ ለፍትህ፤ ለእኩልነት፤ ለነጻነት፤ ለመቻቻል፤ ለሰው ክብር፤ ለተጠያቂነትና ሃላፊነት፤ ለዘላቂና ፍትሃዊ እድገት ያለመሰልቸት ታግሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ አዛዥ እንዲሆን ተግቶ መስራትን ነው። ልንክደው የማንችለው ሃቅ አለ። አገር ክሌለ፤ ትግል ትርጉም የለውም። ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነትና እኩልነት ካልቆምን፤ ከህወሓት ልንለይ አንችልም።

ፍትህን-እርትን የተለየ የሚያደርገው እመርታዊ ለውጥ እናያለን። ይህም የወጣቱ ቁጥር እያደገ መሄድ ነው። የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፤ የወጣቱ ብዛት ያድጋል። ፍላጎቱ ይለወጣል። ለውጡን የማይረዳ ድርጂትና አመራር ይህን ሃይል ሊሰበስበው፤ ልቀሰቅሰው፤ ሊመራው አይችልም። ደጋግሜ የአስተሳሰብ ለውጥ (Dramatic change in the paradigm of thinking) ያስፈልጋል የምለው ለዚህ ነው።

ክፍል ስምንት ያለፈውን የፖሊቲካ አመራር ታሪካችን በአጭሩ እቅርቮ፤ የአገራዊ ድርጂትና ዘመናዊ አመራርን አስፈላጊነት፤ ጠቃሚነት፤ ወሳኝነት፤ ከወጣቱ ትውልድ ምኞትና ተስፋ ጋር አያይዞ ይዳሥሳል።

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on July 10, 2012. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.