እነ እስክንድር ነጋ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠየቀባቸው

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት ሰባትን፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባርን (ኦብነግ)፣ አልሸባብንና አልቃዒዳን በሽብርተኝነት ከሰየመ በኋላ፤ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ጋዜጠኞች፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራርና አባላት ለሁለተኛ ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸዋል፡፡ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም በቁጥጥር ሥር የዋሉት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ፍትሕ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የፓርቲው አባላት አቶ ናትናኤል መኮንን እና አቶ አሳምነው ብርሃኑ እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) ዋና ጸሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው የ28 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው ለጥቅምት 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 8 ሰዓት እንዲቀርቡ ታዝዞ ነበር፡፡
የእስረኞቹ ቤተሰቦች ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፣ የተጠርጣሪዎቹ ቤተሰቦች፣ የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል ፍላጐት ያላቸው ጋዜጠኞች እና ሌሎች አካላት ቀጠሮውን የጠበቁት ለቀትር በኋላው ችሎት የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ግን እስረኞቹን ይዞ የቀረበው ጠዋት 2፡30 ላይ ነበር፡፡

ወደ ችሎት ከገቡም በኋላ ጉዳያቸው የታየው በዝግ ችሎት ሲሆን ማንም ሰው ወደ ችሎቱ እንዳይገባ እና እንዳይጠጋ ፖሊሶች መከልከላቸውን ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል፡፡

የችሎቱ ሥነ ሥርዓት በ45 ደቂቃ ውስጥ ተጠናቆ እስረኞቹ በመጡበት አኳኋን እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከፍርድ ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የ28 ቀን የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶለት ለጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲቀርቡ ትእዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል እስረኞቹ በማዕከላዊ ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሳይገናኙ የቆዩ ሲሆን ከጥቅምት 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ቀናት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዱዓለም አራጌ እና አቶ አሳምነው ብርሃኑ ባለቤቶቻቸውን እንዲያገኙ መደረጉ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል በዚሁ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት አርቲስት ደበበ እሸቱ እና አቶ ስለሺ ሐጐስ መስከረም 26 ቀን 2004 ዓ.ም በተመሳሳይ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት ማስረጃ ተገኝቶባቸው እንደሆነ መንግሥት በይፋ ከተናገረ በኋላ ፖሊስ “ምርመራዬን አልጨረስኩም ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱ ተገቢ አይደለም” በሚል ጠበቆቹ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄውን ተቃውመው ተከራክረዋል፡፡ ፖሊስ በበኩሉ እስረኞቹ በዋስ ቢወጡ ምስክሮች እና ያልተያዙ ግብረ አበሮች ስላሏቸው የምርመራው ሂደት እንደሚደናቀፍ በመግለጽ፣ ሕጉ እስከ አራት ወር የምርመራ ጊዜ ስለሚፈቅድላቸው ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፤ ፍርድ ቤቱም የተጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዶ አርቲስት ደበበ እሸቱን ለጥቅምት 24 አቶ ስለሺ ሐጐስን ለጥቅምት 23 እንዲቀርቡ ቀጥሯል፡፡
ምንጭ፡ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on October 15, 2011. Filed under COMMENTARY. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.