እህል ወደ አዲስ አበባ እንዳይጫን ነዋሪዎች እየከለከሉ ነው

በአሰግድ ተፈራ (Reporter) -በጎጃም የተለያዩ ወረዳዎች እህል እንዳይጫን ነዋሪዎች ተጽዕኖ እያደረጉ መሆኑ ተገለፀ፡፡ አንደኛ ደረጃ የሚባለውን የአድአ ጤፍ ደላሎች በሕገወጥ መንገድ እየሸጡ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት በዱከም ከተማ ተዘዋውረን እንደተመለከትነው እንደ ወትሮው ጤፍ ገበያ አልቀረበም፡፡ ስግብግብ ነጋዴዎችን የመቆጣጠር ሥራ እንደሚከናወን የሰሙ ነጋዴዎች በሞባይል ስልክ ገበሬዎች እህል ወደ ገበያ እንዳያወጡ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን እማኞች ገልፀውልናል፡፡

የአካባቢው ጤፍ በጥራቱ ስለሚወደድ በቅስቀሳ የተፈጠረውን እጥረት ተከትሎ ጤፍ በሕገወጥ መንገድ በደላሎች እየተሸጠ ነው፡፡ ስለ ግብይቱ የሚያውቁ እንደገለፁት ስራው የሚሰራው በአህያና በሞባይል ስልክ ነው፡፡

“በጤፍ አይነትና ጥራት ላይ ክርክር የለም፡፡ ኪሎውም አይጎድልም” ያሉን የዱከም ነዋሪ ጤፍ መግዛት የሚፈልጉ ቤታቸውን ወይም ጤፍ የሚራገፍበትን ቦታ ይናገራሉ፡፡ ጤፉ በተመረጠ ሰዓት ለሸማቹ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ ነዋሪው እንደገለፁት በዚሁ አሻጥር ኩንታሉን 1ሺህ ሃምሳ ብር የሚሸጡ አሉ፡፡

በሌላ በኩል በጎጃም ፍኖተሰላም፣ ሸንዲ፣ ጅጋ፣ ማንኩሳ፣ ቡሬ፣ መተከል ያሉ ነጋዴዎች የገዙትን እህል ወደ አዲስ አበባ መሸጥ አልቻሉም፡፡ ነጋዴዎቹ በስልክ ለሪፖርተር እንደገለፁት የየወረዳው ነዋሪዎች እህል እንዳይጫን የሚከለክሉት በአካባቢው የእህል ዋጋ ተወደደ በሚል ነው፡፡

በየዕለቱ እህል ገበያ ስለሚቀርብ እየገዙ መጋዘን እንደሚያስቀምጡና ወደ አዲስ አበባ ሲጭኑ ስለሚከለከሉ እህል በመጋዘናቸው ተጠራቅሟል፡፡ በዚህም ሳቢያ “እህል ከዘናችሁ (እህል አከማቻችሁ) እንዳንባል ሰግተናል” የሚሉት የማንኩሳ ነጋዴዎች ናቸው፡፡

የየወረዳው አስተዳደሮች፣ ንግድ ቢሮና የአገር ውስጥ ገቢ መስሪያ ቤቶች አቤቱታ ሲቀርብላቸው “እንደፈለጋችሁ ነግዱ” ከማለት የዘለለ ምላሽ እንደማይሰጡ ነጋዴዎቹ ተናግረዋል፡፡ የቀበሌ ነዋሪዎች እህል እንዳይጫን ሲከለክሉ የቀበሌ አመራሮችም ተባባሪዎች ናቸው፡፡

ነጋዴዎቹ እንደገለፁት በትላንትናው እለት ህዝቡን እንዴት እናረጋጋ በሚል ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ ለህትመት እስከገባንበት ድረስ የስብሰባውን ውጤት ማግኘት አልቻልንም፡፡

የፌደራል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስለ ሁኔታው ተጠይቆ “እህል ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ አልተከለከለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚፈጽሙ ህገወጦች ናቸው” የሚል መልስ በህዝብ ግንኙነት በኩል ተናግሯል፡፡

የእህል ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ነጋሽ ደበሌ እህል ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ አንዳንድ ቦታ ህዝብ እየከለከለ ነው የሚል ሪፖርት እንደቀረበላቸው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቦታው ድረስ በመሄድ ሳይመለከቱና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሳይወያዩ መልስ መስጠት እንደማይችሉ ገልፀዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት የመንግሥት መዋቅር የሆኑት የገበሬ ማኅበራት (ዩኒየን) በመጋዘናቸው እህል አከማችተዋል፡፡ እንደ መንግሥት መዋቅርነታቸው ገበያውን የማረጋጋት ሥራ እንዲሰሩና የያዙትን እህል የማይለቁበት ምክንያት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on May 26, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.