ኢንቨስትመንት በደረቴ (AL AMOUDI’S STYLE INVESTEMENT)

alamudi.jpgለኢንቬስትመንት ልዩ ትኩረት መንግሥትም፣ ሕዝብም ባለሃብትም ሲሰጡ ይታያል፡፡ ልዩ ትኩረት የሚሰጥበት ልዩ ምክንያት የልማትና የእድገት ዋስትናና ከድኅነት ለመላቀቅ ብቸኛው መንገድ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ስለሆነ ነው፡፡ኢንቨስተሩ ማን ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳ እንደሆነ እንጂ፣ የኢንቨስትመንት አስፈላጊነት አያጠያይቅም፡፡ ኢንቨስትመንት  ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡ ስለዚህ ነው የኢንቨስትመንት ፖሊሲ የወጣውና በየጊዜው የሚሻሻለው ልዩ ትኩረት ስለሚያስፈልገው ነው፤ ራሱን የቻለ የኢንቨስትመንት ባለሥልጣን የተቋቋመው፡፡ ዲፕሎማሲያችንም በኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ ሆኖ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚጥር እንዲሆን አቅጣጫ የተሰጠው፡፡ 

ኢንቨስትመንቱ የውጭ ኢንቨስትመንት ሲሆን ደግሞ የበለጠ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ልዩ ጥንቃቄም ይደረግበታል፡፡ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች፣ በመሳብ፣ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና እንዲጠናከር የማድረግ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት እጅግ በጣም ብዙ ቢሆንም በአገራችን ያለው የውጭ እንቨስትመንት ጤነኛ ነው በሽተኛ? ሃቀኛ ነው ጉረኛ? ልባዊ ነው አፍአዊ? አትራፊ ነው አክሳሪ? ልማታዊ ኢንቨስትመንት ነው ወይስ “ኢንቨስትመንት በደረቁ”? የሚለውን ለመለየት ቢያንስ ቢያንስ የሚከተሉት አምስት መስፈርቶች እጅግ መሠረታዊና ቁልፍ ናቸው፡፡ 

እነሱም፡- አንደኛ – ሐብት ይፈጥራልን? አትራፊ ነውን? (ዌልዝ ክርኤሽን)ሁለተኛ – ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያሸጋግራልን? (ትራንስፈር Oፍ ቴክኖሎጂ)ሦስተኛ – የሰው ሃይል ይፈጥራል? ያዳብራል? (ሂዩማን ሪሶርስ ዲቨሎፕመንት)አራተኛ – ሕገ መንግሥት ሕግና ሥርዓት አክብሮ ይጓዛልን?አምስተኛ – ሕብረተሰብዓዊ ጠቀሜታና አስተዋፅO አለውን? የሚሉትናቸው፡፡ 

በዚህ አንፃር፣ ከኢሕአዴግ በፊት የነበረው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ሲታይ፣ በዋነኛነት በግል ኢንቨስትመንት የሚጠቀሰው በንጉሱ ጊዜ የነበረ ሆኖ አነሰም በዛም የተጠቀሱት ነገሮች አሟልቶ ይሄድ ነበር፡፡ ጣሊያኖች፣ ግሪኮች፣ አርመኖች፣ አረቦች፣ ህንዶችና ሌሎቹ እንግሊዞችና ፈረንሳዮች ዝቅተኛ ኢንቨስትመንት ቢሆንም የአገር ሕግና ሥርዓት አክብረው ይሰሩ ነበር፡፡ ከውጭ አገር በሚያመጡት ቴክኖሎጂና የማኔጅመንት ልምድም ኢትዮጵያዊ ይማርና ይሰለጥን

ነበር፡፡ በርካታ ሰዎች እነሱ ጋር እየሰለጠኑ የራሳቸውን እያቋቋሙ ባለሃብቶች ሆነው ነበር፡፡ ስራቸውም አትራፊ ነበር፡፡ ሃብት በመፍጠርም የራሳቸው ድርሻ ነበራቸው፡፡

 ስፖርት ዘመናዊ ባህልንና ሌላ ሌላ እንዲያድግ በማድረጋቸው፣ ትምህርት እንዲስፋፋ በመሞከራቸው ማህበራዊ ጠቀሜታቸው በአዎንታ የሚታይ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ የስልጣን ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ ለኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ወጣ፡፡ ባለሥልጣን ተቋቋመለት፡፡ ማበረታቻ ተደረገለት፡፡ በአጭሩ ጊዜም የግል ዘርፉ በኢንቨስትመንት እየተጠናከረ መጣ፡፡ ህልውናውን እያሳወቀ መስፋፋት ጀመረ፡፡ በውጭ ኢንቨስትመንት የሚጠቀሱም መምጣት ጀመሩ፡፡ ህንዶች መጡ፣ ቻይናዊያን መጡ፤ ሌሎችም መጡ፡፡ ከውጭ የመጣ ኢንቨስትመንት ተብሎ በዋነኛነት የሚጠቀሰው ግን የሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አላሙዲ ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ይህ ኢንቨስትመንት በእርሻ፣ በእንዱስትሪ፣ በማእድን፣ በትራንስፖርት፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በእምፖርትና ኤክስፖርት ወ.ዘ.ተ የገባና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ካሬ ሜትር ይዞ በቢሊዮን የሚቆጠር ኢንቨስትመንት አለኝ የሚል ነው፡፡ ጠቀሜታውስ? ሃብት እየፈጠረ ነውን? አትራፊ ነውን? ቴክኖሎጂ እያሸጋገረ ነውን? የብር ሃይል እየዳበረ ነውን? ማህበራዊ ጠቀሜታ እያስገኘ ነውን? የሚሉት መመዘኛዎች ሲመዘን ግን ውጤቱ የሚያሳዝን እየሆነ መጥቷል፡፡ ሃብት ይፈጥራል፣ አትራፊ ይሆናል፤ ተብሎ ሲጠበቅ እንኳን ሃብት ሊፈጥር ሃብት እየባከነ ይገኛል፡፡ ወይ በኢንቨስትመንቱ አልለማ፤ ወይ በሌሎች እንዲለማ አልተደረገ፤ መሬት ታጥሮ፣ ታጥሮ ቀርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተገነባና የለማ ከማየት ይልቅ የታጠረና ያላለቀ ጅምር ለማየት ብቻ የተፈረደበት መስሏል፡፡ አለቁ የተባሉት እነ ሸራተን እንኳ ገና አልተጠናቀቁም፡፡ ያልከፈሉት ገንዘብ ስላለ፣ ያላሟሉት ነገር ስላለ ስማቸው ራሱ ይነጠቃል፣ ይሰረዛል የሚባልባቸው ሆነዋል፡፡ ሃብት ይፈጥራል፤ ሲባል የነበረው ኮንስትራክሽን የመንገድ ኮንትራት መስራት አቅቶት ይቆማል፡፡ የሚያቀርበው አስፋልት ከደረጃ በታች ነው ተብሎ ይነጠቃል፡፡ የገዛ ራሱ ኮንስትራክሽን በሌላ ኮንትራክተር ሲያሰራ ይታያል፡፡ የራሱ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በእዳ ሲጠየቅና ሲከሰስ ይውላል፡፡  ሰራተኞች ደሞዝ የሚከፍላቸው ያጣሉ፡፡ ፕሮጀክቶች ይረሳሉ፡፡ ማሽነሪዎች ስራ ያቆማሉ፡፡ ሃብት ይፈጥራል፤ ተብሎ የተዘመረት ኢንቨስትመንት ሃብት አባካኝና ራሱን መሸከም አቅቶት ከውጭ ድጎማ ሲደረግለት ይስተዋላል፡፡ ትልቁ መመዘኛ ውድቅ ሆነ፡፡ የነበረው ተስፋ ባዶ.. ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያሸጋግራል፤ የተባለው ኢንቨስትመንት፣ በተወሰነ አካል ብቻ ካልሆነ በስተቀር ስለቴክኖሎጂ ደንታ የለውም፡፡ በውድ ዋጋ የገዛቸው የቴክኖሎጂ ውጤት ማሽነሪዎችም ሳር እንዲበቅልባቸው አድርጓል፡፡ ተጥለው ዝገዋል፡፡ ተራ የቤት እቃ ሆነው ያሉት ኮምፒውተሮች እንኳ በአግባቡ መጠቀም ያልቻለ ኢንቨስትመንት ሆኗል፡፡ ማኔጅመንት የሌላቸው እቃዎች ናቸውና፡፡ የነበረን ተስፋ ባዶ.. የሰው ሃይል እየሰለጠነ ያዳብራል፣ ያሳድጋል የተባለው ባዶ ሆኖ ቀረ፡፡ በድርጅቱም በገንዘቡ ተጠቃሚ ለመሆን ቢኤ ዲግሪ አለን፣ ኤም.ኤ አለኝ፤ ፒ ኤች አለኝ፤ ትርጉም የለውም፡፡ በአቅምና በእውቀት በልምድ በታታሪነት መወዳደር ትርጉም የለውም፡፡ ተጠቃሚዎች የሚወዳደሩት የኔ አፍንጫ ስልክክ ይላል፣ የእኔ ቁመት ዘለግ ይላል፣ የኔ ፈገግታና መውረግረግ ሞቅ ይላል፤ በሚለው ይመስላል፡፡ በወንዱ ዙሪያም እከሌ ሲያስቅ ተአምረኛ ነው፤ ሲመታ አይምሬ ነው፣ ሲለምን አሳማኝ ነው፤ የሚለው ነው፡፡ ይህን እውቀትና ልምድ ስላለኝ ኢንቨስትመንቱን አጠናክረዋለሁ የሚል እየጠፋ እሳቸው ቢቆርጡልኝ፣ ቢራሩልኝ፣ ቢያስቀምጡኝ የሚል ተስፈኛ በዝቶ የሰው ሀይል ማዳበር ቀርቶ የሰው ሃይል ማበላሻ ማእከል ሆነ፡፡ የተጠበቀው ተስፋ ባዶ!! ሕግና ሥርዓት አክብሮ የመሄድ ጉዳይም እንደዚሁ በመጥፎ አርአያነት የሚጠቀስ እየሆነ ነው፡፡ ከኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ከመሬት አስተዳደር ጋር የተደረጉ ውሎች አይከበሩም፡፡ የባንክ እዳዎች በወቅቱ አይከፈሉም፡፡ ሕግና ሥርዓት አክብሮ ከመጓዝ ይልቅ፣ እከሌ ባለሥልጣን በነፃ እንዲዋኝ ካደረግነው፣ እከሌ ሚኒስትር ልጁን ውጭ አገር ከላክልነት፣ እከሌ ሚኒስትርን ካሳከምነው፣ እከሌ ሁሌ እኛ ጋር እየመጣ ምሳ እንዲበላ ከፈቀድንለት፣ የእከሌ ባለሥልጣን ዘመዱን ከቀጠርን፣ እከሌን ግን ካስፈራራን አገር በቁጥጥራችን ስር ትሆናለች፡፡ “እትዮጵያ እጆቿን ወደኛ ትዘረጋለች” የሚል አቅጣጫ ተያዘ፡፡ ሕግና ሥርዓት ተናቀ፡፡ በዘመናዊ ማኔጅመንት ሕግና ሥርዓት አከባበርነት ከውጭ አገር ልምድ ይመጣልናል፤ ሁላችንም እንማርበታለን ያልነው ተስፋም ባዶ! ባህልና ወጋችንን በማክበርና በማሳደግ አንፃርና ሕብረተሰባዊ ጠቀሜታና እሴት በመፍጠር አንጻርም ተጻራሪው እየሆነ ነው፡፡ ውሸትና መለማመጥ፣ ጥገኝነትና ለማኝነት፣ ህሊናችንን መሸጥ፣ ቅናትና ምቀኝነት እየተስፋፋ ነው፡፡ ሙያየንና ልምዴም ይህ ነው፤ ብሎ መቀጠር ማደግ መቀጠል እየቀረ ነው፡፡ ከእናንተ ጋር ይሰራ ስለነበር ከዚያ ከወጣ በኋላ አለፈለት፤ የሚል ወሬ በዛ ሰፈር አይሰማም፡፡ ስለወጣ ከሰረ፣ ንብረትና መኪና ተቀማ፣ ተሰደደ፣ ታመመ፣ ደኸየ፣ ባለቤቱ ጥላው ሄደች፣ ወይም እሱ ከግቢው ተወረወረ፤ የሚለው ወሬ ነው የሚሰማው፡፡ ተመፅዋችነት ነገሰ፡፡፡ ሕብረተሰቡን የሚጠቅሙ የሚመስሉ የቴሌቶን ልገሳዎችም ወይ አይተገበሩም፤ ወይ ደግሞ ሰራተኛው የሚከፈለው ደሞዝ አጥቶ፣ ባንክ እዳ ይጣራልኝ እያለ እያለቀሰ፣ ለእነሱ ማሽነሪ ያከራዩ የሚከፍላቸው እጥተው እያለቀሱ፣ ህንፃ ተጀምሮ ተቋርጦ ተዘግቶ ወ.ዘ.ተ ባለበት ሁኔታ የሚደረግ ስለሆነ አንጀት ውስጥ አልገባ እያለ ነው፡፡ ተስፋው ባዶ!! መፍትሔውስ? ሶስት አቅጣጫ ያለው መፍትሔ ነው፡፡ አቅጣጫ አንድ – የባለሃብቱ መፍትሔ – ቀደም ብለን በፃፍነው ባለ ሰባት ነጥብ የመፍትሄ ሃሳብ መሰረት ባለሃብቱ ሊፈፅሙት የሚገባ ነው፡፡ እዚህ አንደግመውም፡፡  

አቅጣጫ ሁለት – የመንግሥት መፍትሔ – ቀዳሚ ዓላማው ለመርዳትና ለማስተካከል ሆኖ ካለማወላወል የአገራችን ሕግና ሥርዓት፣ የኢንቨስትመንት ሕግ በሚጠይቀው መሰረት ሆኖ፣ ባለሃብቱ የአገራችን ሥርዓትና ወግ አክብረው የገቡትና የቆረቆሩትን ተቀብለው እንዲፈጽሙ መቆጣጠርና መከታተል ነው፡፡ በተለይ በተለይ ከሕግ በላይ ሃይልና ማስፈራራት ወንጀል እንደሆነ ግልፅ ማድረግና መቆጣጠር ነው፡፡ ይህ የአቅጣጫ አንድ ገፅታ ነው፡፡  ሌላው የመንግሥታዊ መፍትሔ፣ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት በጥቅማ ጥቅም መሳሪያ እንዳይሆኑ፣ ከጥቅም ግጭት እንዲቆጠቡ ማድረግና መቆጣጠር ነው፡፡ አስፈላጊ ከሆነም የባለሥልጣን ደሞዝ ጨምሮ የሰው እጅ እንዳያዩ ማድረግና ሲታመሙም መንግሥት ራሱ ሊያሳክማቸው የሚችልበትን አሰራር መዘርጋት ነው፡፡ አቅጣጫ ሶስት – የሕዝብ መፍትሄ – ሕዝብም በትኩረት ሊያይና ሊከታተል ይገባል፡፡ በድህነቱ መጫዎቻ እንደማይሆን ግልፅ ማድረግ አለበት፡፡ በተለይ በተለይ ኢትዮጵያዊ ችግር ቢያጋጥመውም፣ አገራችን ሺ ጊዜ ብትቸገርም “ኢትዮጵያ እጆቿን የምትዘረጋው ወደ እግዚአብሄር ብቻ ነው” የሚል መልእክት በግልፅ ለሁሉም ሊያስተላልፍ ይገባል፡፡ ችግሩ የአገር ችግር ነው፡፡ በአስቸኳይ ሊፈታ ይገባል፡፡ ለሌላም መጥፎ አርአያ እንዳይሆን በአስቸኳይ ይታረም፡፡ኢንቨስትመንት ያልነው ሲመዘን “ሱቅ በደረቴ” ሆኗል፡፡  አጋነናችሁ ከተባልንም በይቅርታ እናስተካክለው፡፡ኢንቨስትመንት በደረቴ!!

Source: http://ethiosun.com/?p=1591

Share Button
Disclaimer: We are not responsible for any losses or damages that may have caused by using our services. EMF declines all responsibility for the contents of the materials stored by users. Each and every user is solely responsible for the posts.
Posted by on November 18, 2008. Filed under Uncategorized. You can follow any responses to this entry through the RSS 2.0. Both comments and pings are currently closed.